በ
ethiomuslims.net የሚወጡ መጣጥፎችና የመልቲ-ሚዲያ ውጤቶች የጸሐፊዎችን ግላዊ አመለካከት ቢያንጸባርቁም ባጠቃላይ የድህረ-ገጹ ህልምና መርሆዎች የሚከተለውን ይመስላሉ፡-
1. አሷላ (ምልሰታ)፡- ወደ መሰረታዊ የኢስላም ምንጮች ቁርአን እና ሀዲስ በመመለስና የቀደምት ሙስሊም ምሁራን (ሰለፉ- ሷሊህ) ጥልቅ የእውቀት ውጤቶችን በመጠቀም ኢስላምን መረዳት።
“አላህና መልክተኛውም ነገርን በፈረዱ ጊዜ ለምእምናንና ለምእምናት ከነገራቸው ለእነርሱ ምርጫ ሊኖራቸው አይገባም! የአላህንና የመልክተኛውንም ትእዛዝ የጣሰ ሰው ግልጽ የሆነን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።” (አል-አህዛብ 33፤36)
2. ረባኒያ (መለኮታዊነት)- የኢስላም አንኳር መልእክት የሆነው አላህን ጥርት አድርጎ በብቸኛነት ማምለክን (ተውሂድ)፣ ልብንና ነፍስን በዒባዳ ማጽዳትንና የማጥራት (ተዝኪያ/ተሰዉፍ) እና በሁሉም የህይወት ዘርፍ በጥሩ ስነ-ምግባር (አኽላቅ) መታነጽን የሙስሊሙ ህብረተስብ የህይወት ምህዋር እንዲሆን ማድረግ።
“ግን መጽሐፍን የምታስተምሩ በነበራችሁትና የምታጠኑም በነበራችሁት በዕውቀታችሁ ሠሪዎች (ረባኒይ) ኹኑ” (ኣሊ ኢምራን 3፤79)
“በነፍስም ባስተካከላትም፤ አመጽዋንና ፍርሃትዋንም ባሳወቃት (አምላክ እምላለሁ)። (ከኀጢኣት) ያጠራት ሰው ፍላጎቱን በእርግጥ አገኘ። (በኀጢኣት) የሸፈናትም ሰው በእውነት አፈረ።” (አሽ-ሸምስ 91፤7-10 )
ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እንዳሉት፡-
إنما بعثت لأتمم مكارم الأخلاق
“እኔ የተላኩት መልካም ስነ-ምግባርን ላሟላ ነው” (በይሃቂይ የዘገቡት)::
3. ሹሙል (ሁለንተናዊነት፤ ምሉእነት)፡- የሰውን ልጅ ሙሉ ማንነት፣ አእምሮውን፣ ህሊናውን፣ ልቦናውን፣ መንፈሱን እና አካሉን ያማከለ፤ ሁሉንም የእድሜ ክልል እና ጾታ ግምት ውስጥ ያስገባ፤ የግለሰብ የቤተሰብ የማህበረሰብ እንዲሁም ሁሉንም የህይወት ዘርፍ የዳሰሰ የኢስላምን ሁለንተናዊነትና ምሉእ አስተምህሮት ማንጸባረቅ።
“መጽሐፉንም ለሁሉ ነገር አብራሪ፣ መሪም፣ እዝነትም፣ ለሙስሊሞችም አብሳሪ ኾኖ ባንተ ላይ አወረድነው።” (አን-ነህል 16፤89)
4. ወሰጥ (ሚዛናዊ፤ ማዕከላዊ፤ ፍትሃዊ):- የኢስላም መለያ የሆነውን ሚዛናዊነት፤ ማዕከላዊነት እና ፍትሃዊነት በተጨባጭ የሙስሊሙ ማህበረሰብ መገለጫ እንዲሆንና በአንጻሩም ከጠርዘኝነትንና ከቸልተኝነት (ጉሉው ወተቅሲር/ extremism and laxity) እንዲርቅ ማገዝ።
“እንደዚሁም (እንደመራናችሁ) በሰዎች ላይ መስካሪዎች ልትሆኑና መልክተኛውም በናንተ ላይ መስካሪ ይሆን ዘንድ ምርጥ ሕዝቦች (ወሰጥ) አደረግናችሁ።” (አል-በቀራ 2፤143)
5. ዋህዳ (አንድነት)፡- ሁሉም ሙስሊም የሚስማማባቸውን መሰረታዊ የዲኑ ክፍሎች (ዑሱል) ላይ አንድ ሆኖ ልዩነት ባለባቸው ቅርንጫፍ ጉዳዮች (ፉሩዕ) ላይ በመከባበር በአላህ ገመድ በአንድነት ተሳስሮ ወንድማማችነቱን እውን ለማድረግ የሚያስችለውን አመለካከት እና አስተምህሮ ማስረጽ።
“የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ። አትለያዩም። ጠበኞችም በነበራችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (የዋለውን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ። በልቦቻችሁም መካከል አስማማ። በጸጋውም ወንድማማቾች ኾናችሁ። በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ። ከእርስዋም አዳናችሁ። እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀጾቹን ያብራራል።” (ኣሊ ኢምራን 3፤103)
6. ተሳሙህ (መቻቻል፤ መከባበርና መልካም መዋል)፡- ከመቻቻልና ከመከባበር በላይ የሆነውን ለሌላ እምነት ተከታዮች እንድናደርግ የታዘዝነውን መልካም የመዋል ግዴታ (አል-ቢር ወል-ቂስጥ) በተጨባጭ መወጣት የሚያስችለንን የአስተሳሰብ መሰረት መጣል፤ ሌሎች ወገኖች ይህንን አስተሳሰብ አስመልክቶ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ማረም።
“ከእነዚያ በሃይማኖት ካልተጋደሏችሁ ከአገሮቻችሁም ካላወጡዋችሁ (ከሓዲዎች) መልካም ብትውሉላቸውና ወደእነርሱ ብታስተካክሉ አላህ አይከለክላችሁም። አላህ ትክክለኞችን ይወዳልና።” (አል-ሙምታሀና 60፤8)
7. ሰላም፡- ኢስላም ለሰላም ያለውን ቦታ እና በምድር ላይ ሰላምን የማስፈን ተልዕኮውን እና ብቃቱን በማሳየት በሌሎች የሚፈጠሩ ብዥታዎችን መግፈፍ፤ በቀን ተቀን የሙስሊሙ ህይወት ሰላማዊነቱ ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ፤ የኢስላም ዓላማ የሆነውን ውስጣዊ እና ውጫዊ ሰላም ሙስሊሙ እንዲጎናጸፍ ማገዝ።
“ወደ ሰላም ቢያዘነብሉ ወደ እርሷ አዘንብል። በአላህም ላይ ተጠጋ። እነሆ እርሱ ሰሚ ዐዋቂ ነውና።” (አንፋል 8፤61)
የሙስሊሞች የዘወትር ከሰላት በኋላ ውዳሴ፡-
اللهم انت السلام ومنك السلام تباركت ياذا الجلال والاكرام
“አላህ ሆይ! አንተ ሰላም ነህ፤ ሰላምም ካንተ ነው፤ የታላቅነትና የልግስና ባለቤት የሆንከው ጌታ ሆይ! ረድዔተ-ብዙ ነህ፡፡”(ሙሰሊም የዘገቡት)
8. ኢዕማር (እድገት፤ ልማት፤ ምርታማነት፤ ብልጽግና)፡- አላህ (ሱ.ወ) የሰውን ልጅ የፈጠረበት አንዱ አላማ የሆነው መሬትን የማልማትና የማበልጸግ (ዒማረተል-አርድ) ጽንሰ ሀሳብ ማስረጽ።
“እርሱ ከምድር ፈጠራችሁ። በውስጧ እንድታለሟትም አደረጋችሁ።” (ሁድ 11፤61)
*****