እዝነትና ፍትህ በረሱል (ሰዐወ) ሲጣመሩ

1
5254

የዚህን ታላቅ ነብይ ሁለንተናዊ ስኬት ለመረዳት ብሎም ለሰብዓዊና ቁሳዊው ስልጣኔ መነሻ የሚሆን ትውልድን በመፍጠር ሂደት ውስጥ የተከፈለውን መስዋትነት ክብደት ለመረዳት ይረዳ ዘንድ ከውልደታቸው በፊት የነበረውን ጨለማ አለም በተለይም የአረቡ ምድር ሰጥሞበት የነበረውን ባስ ያለ ጨለማ ወደ ኋላ መመልከት በራሱ በቂ ማስረጃ ሊሆን ይችላል። አለም ጥቂቶች በርካታ ሀብትን ሰብስበው ብዙዎች ግን በረሀብ አለንጋ የሚረግፉበት፣ ጥቂቶች በአምባገነንነት ስልጣንን ተቆናጥጠው ብዙዎች በባርነት ቀንበር ውስጥ ከመኖር በታች የሆኑባት አስፈሪና መራራ ቦታ ሆና ነበር።

ይሄኔ ነበር የነብዩ ውልደት ህይወት ላላቸውም ህይወት ለሌላቸውም ፍጡራን የተለየ ትርጓሜ የቸረው። ከውልደታቸው ጀምሮ እስከመላካቸው ያለው ክቡሩ ህይወታቸው በራሱ አንድ ግለሰብ በመለኮታዊ ራዕይ ሳይታገዝ ንፁህ ተፈጥሯዊ ማንነቱን ጠብቆ እንደሰው ልጅ ለትክክለኛ መርህ መገዛት መሻትን የምንመለከትበት ብርቅዬ ተምሳሌት ነው።በመሆኑም በመወለዳቸው አለም ይሄን ታላቅ ብርሀን ተለገሰው ልንል ያስችለናል። ተልዕኳቸው በራሱ ከሰው ልጅ ሁሉ አልፎ ፍጡራንን በጠቅላላ ያካተተ፤ በዕዝነት መሰረት ላይ የቆመ፤ ሆድ ለባሳቸውና ለተቸገሩ፣  በሀዘንና ትካዜ ለተከበቡ፣ መሄጃ ጠፍቷቸው ለተወዛገቡ፣ ህይወት በአንዱ መራራ ኩርባዋ ላይ ለጣለቻቸውና የእርዳታ እጆችን ለተነፈጉ፣ የውስጣቸውን ምሬት አዳማጭ ጆሮዎችን ለተከለከሉ፣ በጉንጮቻቸው ላይ የሚፈሱ ዕንባዎችን አባሽ መዳፎችን ላጡ ታላቅ ብስራት ሆነ።

በዛ በርካታ ቀናትንና ሌሊቶችን ያዘወትሩበት ከነበረበት የሂራ ዋሻ ውስጥ “አንብብ!” የሚለው የመለኮታዊ ጥሪ ጅማሮ ድምፅ ከገቡበት ጥልቅ ሀሳብና የማሰላሰል አለም አባነናቸው።ፈጣሪያችንና ተንከባካቢያችን ጠባቂያችንና ጌታችን የሆነው አላህ(ሱ.ወ) በርግጥም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በፊደላት ስብስብ የተሰሩ ፅሁፎችን ማንበብ እንደማይችሉ ያውቃል ለዚህም ነው የተሰማው “የአንብብ” ጥሪ ሁለንተናዊ ንባብን የሚመለከት መሆኑን የምንረዳው። ለዚህም ነው ጥሪው የነበረውን የግለሰባዊ ፤ የማህበራዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ህይወትን የማስተንተን ሁለንተናዊ የንባብ ጥሪ መሆኑን የምንገነዘበው።

የኚህን ታላቅ መልዕክተኛ ጥልቅ የሆነ የነፃነትና የፍትህ እንዲሁም የነፃነትና ፍትህ ውጤት የሆነውን ደስታና ሰላም የማስፈን ጉዞ የሚያረጋግጡ በውስጣቸው የርሳቸውን ድንቅ የሆነ መንፈሳዊ ልቅናና አእምሯዊ ብስለት የሚናገሩ ክስተቶችን ለአብነት ያህል እናንሳ። የባሪያ ንግድ በአረቢያ ባህረ ሰላጤ የዕለተዕለት ህይወት አንዱ አካል ከሆነ ሰነባብቷል።  ሰዎች ሰዎችን እንደዕቃ  ይገዛሉ ይሸጣሉ። ነቢዩ በመጀመሪያዎቹ የጥሪ ሂደቶች ሁኔታው ምንም እንኳን የአንበሳ ልብ ቢጠይቅም እርሳቸውን ከመቀበል አልፈው ጥሪው ከስጋቸውና ደማቸው ጋር የተዋሀደን ግለሰቦች ማግኘት ችለዋል። ለዚህ ታላቅ አላማ መሰዋትን እጅግ የሚመኙ አማኞችን ከግራና ቀኝ ይዘዋል። ይህም ሆኖ ግን በሳሉ መልዕክተኛ ለነዚሁ አማኞች የባሪያ ንግድ ውስጥ መሳተፍን በመከልከል አልጀመሩም። የባርነትን ስነልቦናዊ እውነታ መረመሩ ውስጣዊ መሰረቱን ከውጫዊ መገለጫው ለዩ። በዚህም መሰረት የሰው ልጅ የተፈጥሮአዊ መነሻ አንድ መሆኑን ፤ ማጠናቀቂያውና የምድራዊ ህይወቱ መዝጊያም አፈር መሆኑን፤ አንዱ ከሌላ እንደማይበልጥና የሰው ለጆች በሙሉ እኩል መሆናቸውን አስተማሩ፤ ነፃነት ከውስጥ ፈንቅሎ የሚወጣ፤ የሰው ልጅ ሲነቃ በራሱ ጊዜ የሚወስደው እንጂ በሌሎች የሚሰጠው አለመሆኑን አበሰሩ አስተማሩ። በዚህም የሁለተኛውን ዙር የባሪያ ንግድን የመደምሰስ እውነታ አስገኙ። በውጪ ገፅታው ከመሸጥና መገዛት ሂደት ባይወጡም እኩልነት የሚሰማቸው፤ ነፃነት ካለችበት ማንሳት እንደሚችሉ የሚያምኑ ግለሰቦች ግን ተፈጠሩ። በዚሁ ዙር ከተፈጠረው የነፃት ስሜት ጎን ለጎን ባሪያን ነፃ የማውጣት ደረጃና ምንዳ፣ በዚህና በመጪ አለም የሚኖረውን ጥቅም በማሳወቅ የተፈጠረውን የነፃነት ስሜት የሚያስተናግድ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ውጪያዊ ስርዓት አንዲኖር አደረጉ። የሚገርመው ሂደቱ ወደሌላ የሶስተኛ ዙር እራሱን ማሻገሩ ነው። እያየለ የመጣውን የነፃነት ውስጣዊ ፍላጎት ሊመዝን የሚችልና እራሱ በስም ብቻ ባሪያ ተብሎ የሚጠራው አካል አስፈላጊውን ክፍያ ፈፅሞ ምሉዕ ነፃነቱን የሚጎናፀፍበትን ስርዐት እንዲወለደ አደረጉ። በመሆኑም ግለሰቡ በትርፍ ጊዜው ሰርቶ በሚያካብተው ገንዘብ የራሱን እድል መወሰን እንዲችል ሆነ።

በነፃነትና ፍትህ የታጀበው ጉዞዐቸው ከ13 ዓመት የመካ ቆይታ ቦሀላ ወደ መዲና መሰደድ ግድ አለው። በዚሁ የሂጅራ ሂደት ውስጥ ታላቅ ምሳሌንም ጥሎ አለፈ። ነብዩና ባልደረቦቻቸው አለም አቀፋዊ (የኒቨርሳል) የሆነውን የኢስላም መርሆ ከነበሩበት የመካ ባህል፤ ወግና ልምድ ነጥለው የሚመለከቱበት እድል በዚሁ ወደ መዲና በተደረገው ስደት ተፈጠረ። የመዲናው የህይወት ስርዓት ያካተተው የጎሳዎች የዕርስበርስ ግንኙነት፣ የሴቶች ማህበራዊ ሚና፣ የአይሁዶችና ክርስቲያኖች ተፅዕኖ እና በአጠቃላይ መሰረታዊ ከባህልና ኑሮ ጋር የተገናኙ ሂደቶች ከመካው የተለዩ በመሆናቸው ለሙስሊሞች ለፈጣሪና መርህ በተለየ ባህልና የህይወት ስርዐት ውስጥም ሆኖ ታማኝ የመሆንን ተሞክሮ ለግሷቸዋል። ይህም ሙስሊሞች በተመሳሳይ ርዕዮትና መርህ ለተለያዩ ባህሎችና ወጎች ክፍት በመሆን በአለም አቀፋዊ ወንድማማችነት መተሳሰር የሚቻልበትን ድንቅ ምሳሌ እንዲያስቀምጡ አስችሏቸዋል።

የነብዩን ፍትህን ሰፍኖ የመመልከት ጉጉት የሚያስረዳውና በርግጥም ተልዕኳቸው ሁሉንም ያካተተ መሆኑንና ፍትህን ለማስፈን እስከሆነ ድረስ ከማንም ጋር ለመቆም ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳየው ከመላካቸው በፊት በዐብደላ ኢብን ጁድዐን ጓሮ የተደረገች ስብሰባ ናት አላማውም ማንም ይሁን ማን ከየትም ይምጣ ከየት ከተበዳይ ጎን ለመቆም የሚያስችልን ዕቅድ ለማውጣት የተደረገች ነበረች። እርሳቸውም የዚህ ስብሰባ ተካፋይ ነበሩ።ከመላካቸው በኃላ ሲናገሩ “ያቺ ስብሰባ ዛሬ ብትኖርና ጥሪ ቢደረግልኝ በደስታ እገኝ ነበር” ሲሉ ተሰምተዋል። ተሰብሳቢዎቹ አጋሪዎች መሆናቸው የስብሰባው ቦታም የሙስሊም ግለሰብ አለመሆኑ ለፍትህ ከሚደረግ ጥረት ጎን እንዳይቆሙ አላደረጋቸውም። ሙሀመድ የአብደላህ ልጅ የጌታችን ሠላትና ሠላም በርሳቸው ላይ ይሁን በሚዕራጅ (ወደ ሰማይ አለም)ጉዞዓቸው ሲድረተል ሙንተሀን ተሻግረዋል። የሰው ልጅ ሎጂክ፤ ምክንያታዊነትን ሀሳብ ሊደርስ የማይችልበትን ድንበር አልፈዋል። ታዲያ ለዚህ ነብይ ፍቅርን ለመግለፅ ምን አይነት ምክንያታዊነትና ሎጂክ ሊሰራ ይችላል። ምን አይነት ደንብና ቅርፅ ይፈልጋል። የውዴታችን አላማ ግን አይዘነጋም። የመውደዳችን ጥበብ ግን ከፍቅሩ ጋር አብሮን ይጓዛል። እርሱም ከታላቁ ጌታችን አላህ ጋር አስተዋውቀውናል። ይህም የመውደዳችን ጥበብ ይሆናል።

ሰለዋቱ ረቢ ወሰላሙሁ አለይሂ

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here