ልዩ ስብእና ልዩ ተምሳሌት (ክፍል 1)

0
6711

አላህ ነቢዩ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ለሰው ልጆች በታላቅ ስጦታነት አበረከተ። ይህም የሆነው ከአላህ ዘንድ እጅግ የላቀ ክብር ስላላቸው ነው። ወዳጁን ነቢዩን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መታዘዝን እርሱን የመታዘዝ አካል፣ ከርሳቸው ጋር ቃል መጋባትን ከርሱ ጋር ቃል መጋባት እንደሆነ ገለጸ። የርሱን ውዴታ ለማግኘትም ዋነኛው መስፈርት ነቢዩን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መከተል መሆኑንም አሳወቀ።

ተከታዮች የቁርአን አናቅጽ ይህን መልእክት ያዘሉ ናቸው፦

وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا رَحْمَةً لِّلْعَالَمِينَ

“(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም።” (አል አንቢያእ፤ 107)

ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይሉ ነበር፦

“እናንተ ሰዎች ሆይ፣ እኔ እዝነትና ቅን መመሪያ ነኝ።” (ዳሪሚ)

مَّن يُطِعِ الرَّسُولَ فَقَدْ أَطَاعَ اللَّهَ ۖ وَمَن تَوَلَّىٰ فَمَا أَرْسَلْنَاكَ عَلَيْهِمْ حَفِيظًا

“መልክተኛውን የሚታዘዝ ሰው በእርግጥ አላህን ታዘዘ። ከትእዛዝም የሸሸ ሰው (አያሳስብህ)። በእነሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አልላክንህምና።” (አል ኒሣእ፤ 80)

إِنَّ الَّذِينَ يُبَايِعُونَكَ إِنَّمَا يُبَايِعُونَ اللَّهَ يَدُ اللَّهِ فَوْقَ أَيْدِيهِمْ ۚ فَمَن نَّكَثَ فَإِنَّمَا يَنكُثُ عَلَىٰ نَفْسِهِ ۖ وَمَنْ أَوْفَىٰ بِمَا عَاهَدَ عَلَيْهُ اللَّهَ فَسَيُؤْتِيهِ أَجْرًا عَظِيمًا

“እነዚያ ቃል ኪዳን የሚጋቡህ ቃል ኪዳን የሚጋቡት አላህን ብቻ ነው። የአላህ እጅ (ኀይሉ) ከእጆቻቸው በላይ ነው። ያፈረሰም ሰው የሚያፈርሰው በነፍሱ ላይ ብቻ ነው። በእርሱ ላይ አላህን ቃል ኪዳን የተጋባበትን የሞላም ሰው ታላቅ ምንዳን በእርግጥ ይሰጠዋል።” (አል ፈትህ፤ 10)

قُلْ إِن كُنتُمْ تُحِبُّونَ اللَّهَ فَاتَّبِعُونِي يُحْبِبْكُمُ اللَّهُ وَيَغْفِرْ لَكُمْ ذُنُوبَكُمْ ۗ وَاللَّهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ

“በላቸው፡- «አላህን የምትወዱ እንደኾናችሁ ተከተሉኝ፤ አላህ ይወዳችኋልና። ኀጢኣቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና። አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።»” (አሊ ዒምራን፤ 31)

አንድም ሰው እርሳቸውን መቅደም እንደሌለበት አላህ በግልጽ አዟል፦

۞ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تُقَدِّمُوا بَيْنَ يَدَيِ اللَّهِ وَرَسُولِهِ ۖ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۚ إِنَّ اللَّهَ سَمِيعٌ عَلِيمٌ

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው ፊት (ነፍሶቻችሁን) አታስቀድሙ። አላህንም ፍሩ። አላህ ሰሚ ዐዋቂ ነውና።” (አል ሁጁራት፤ 1)

ይህ አንቀጽ በቁርአንና በሐዲስ ማእቀፍ ውስጥ መሆንን ያዛል። ስለሆነም ከአላህና ከመልእክተኛው ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም  ትእዛዛት፣ ከቁርአንና ከሐዲስ መመሪያዎች መውጣት ፈጽሞ የሚፈቀድ አይደለም።

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ባልደረቦቻቸውን ከቁርአን መመሪያ አኳያ ቀርጸዋቸዋል። ይህም በመሆኑ ሶሐቦች አንዳች ነገር በተጠየቁ ጊዜ፦“አላህና መልእክተኛው ያውቃሉ።” የማለት ልምድ ነበራቸው። አጀንዳውን የሚያውቁት ቢሆን እንኳ ምላሻቸው ይህ ነበር። ከዚህ የተነሳ ስብእናቸው መጠቀ፤ የመልካም ስርዓት ባለቤት ሆኑ፤ የቀልብን መርጠብ አገኙ፤ የአደብን ጣሪያ ደረሱ።

አላህ ሙእሚኖችን ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ዘንድ እጅግ ስርዓታማና አንደበታቸው የታረመ እንዲሆን፣ ድምጻቸውን ከርሳቸው ፊት ከፍ አድርገው እንዳይናገሩ አዟል። ከዚህ ስርዓት ከወጡ ስራቸው እንደሚበላሽ አስጠንቅቋል። ይህን የሚመለከቱ የቁርአን አናቅጽ በርካታ ናቸው።

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَرْفَعُوا أَصْوَاتَكُمْ فَوْقَ صَوْتِ النَّبِيِّ وَلَا تَجْهَرُوا لَهُ بِالْقَوْلِ كَجَهْرِ بَعْضِكُمْ لِبَعْضٍ أَن تَحْبَطَ أَعْمَالُكُمْ وَأَنتُمْ لَا تَشْعُرُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ድምጾቻችሁን ከነቢዩ ድምጽ በላይ ከፍ አታድርጉ። ከፊላችሁም ለከፊሉ እንደሚጮህ በንግግር ለርሱ አትጩሁ። እናንተ የማታውቁ ስትኾኑ ሥራዎቻችሁ እንዳይበላሹ (ተከልከሉ)።” (አል ሁጁራት፤ 2)

አላህ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ማላቅን የቀልብ ተቅዋ መመዘኛ አደረገው። የሰው ልጅ የአላህ ተገዥነትን (ዑቡድያን) ክብር ለማግኘት ነቢዩን ማላቅ አብይ መስፈርት መሆኑን ገለጸ። ከነቢዩ ጋር ባለ ግንኙነት አደብ አለመያዝ የመሐይምነት ትልቅ ምልክት መሆኑን አብራራ።

إِنَّ الَّذِينَ يَغُضُّونَ أَصْوَاتَهُمْ عِندَ رَسُولِ اللَّهِ أُولَٰئِكَ الَّذِينَ امْتَحَنَ اللَّهُ قُلُوبَهُمْ لِلتَّقْوَىٰ ۚ لَهُم مَّغْفِرَةٌ وَأَجْرٌ عَظِيمٌ-إِنَّ الَّذِينَ يُنَادُونَكَ مِن وَرَاءِ الْحُجُرَاتِ أَكْثَرُهُمْ لَا يَعْقِلُونَ

እነዚያ በአላህ መልክተኛ ዘንድ ድምጾቻቸውን ዝቅ የሚያደርጉ እነዚህ እነዚያ አላህ ልቦቻቸውን ለፍርሃት የፈተናቸው ናቸው። ለእነርሱም ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አላቸው። እነዚያ ከክፍሎቹ ውጭ ኾነው የሚጠሩህ አብዛኞቻቸው አያውቁም።” (አል ሁጁራት፤ 3-4)

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተከታዩን የቁርአን አንቀጽ መረጃ አድርገን ማምጣትም ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም፦

لَّا تَجْعَلُوا دُعَاءَ الرَّسُولِ بَيْنَكُمْ كَدُعَاءِ بَعْضِكُم بَعْضًا ۚ قَدْ يَعْلَمُ اللَّهُ الَّذِينَ يَتَسَلَّلُونَ مِنكُمْ لِوَاذًا ۚ فَلْيَحْذَرِ الَّذِينَ يُخَالِفُونَ عَنْ أَمْرِهِ أَن تُصِيبَهُمْ فِتْنَةٌ أَوْ يُصِيبَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ

“በመካከላችሁ የመልክተኛውን ጥሪ ከፊላችሁ ከፊሉን እንደ መጥራት አታድርጉት። ከእናንተ ውስጥ እነዚያን እየተከለሉ በመስለክለክ የሚወጡትን አላህ በእርግጥ ያውቃቸዋል። እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ።” (አል ኑር፤ 63)

ኢብን አባስ ይህን አንቀጽ እንዲህ በማለት ተርጉመውታል፦

ሙሐመድ ወይም አቡል ቃሲም በማለት ብቻ ነቢዩን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አንጠልጥሎ መጥራትን በዚህ አንቀጽ አላህ ከልክሏል። ይህን ያደረገው ነቢዩን ለማላቅ ነው።“የአላህ ነብይ ሆይ፣ የአላህ መልእክተኛ ሆይ” በማለት እንድንጠራቸውም አዟል።[1]

አላህ ነቢዩ ሙሐመድን  ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም  እንደሌሎች ነብያት በስማቸው ከአንድም ቦታ ላይ ጠርቶ አላናገራቸውም። “የአላህ ነብይ ሆይ፣ የአላህ መልእክተኛ ሆይ፡” የሚለውን የክብር ስም ምንጊዜም በመጠቀም ለርሳቸው ያለውን ክብር ገልጿል። ለኛ ለባሮቹም ወዳጃችንን ሙሐመድን በተመለከተ ልንከተለው የሚገባንን ስርዓት አስተምሮናል።

የነቢዩን ሰለላሁዓ ለይሂ ወሰለም የላቀ ደረጃ እና ክብር የሚዘነጉ ሰዎችንም የቁርአን ሕያው ማብራሪያ በሆነ ሕይወታቸው በመማል አስጠንቅቋል።

لَعَمْرُكَ إِنَّهُمْ لَفِي سَكْرَتِهِمْ يَعْمَهُونَ

“በዕድሜህ እንምላለን እነሱ በእርግጥ በስከራቸው ውስጥ ይዋልላሉ።” (አል ሂጅር፤ 72)

ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ውጭ በሌላ ሰው ሕይወት አላህ የማለበትን ሁኔታ በቁርአን ውስጥ ፈጽሞ አናገኝም። ይህ በእርግጥ ልቅናቸውን ያሳያል። ከአላህ ዘንድ የተቸረ የተለየ ደረጃ እንዳላቸው ያመለክታል። አላህ ራሱና መላኢኮች በርሳቸው ላይ ሰለዋት ማውረዳቸው፣ አማኞችም ሶለዋት እንዲያደርጉ መታዘዛቸው ለልእልናቸው ሌላ ምስክር ነው።

إِنَّ اللَّهَ وَمَلَائِكَتَهُ يُصَلُّونَ عَلَى النَّبِيِّ ۚ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا صَلُّوا عَلَيْهِ وَسَلِّمُوا تَسْلِيمًا

አላህና መላእክቱ በነቢዩ ላይ የአክብሮት እዝነትን ያወርዳሉ። እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በእርሱ ላይ የአክብሮት እዝነትን አውርዱ። የማክበርንም ሰላምታ ሰላም በሉ። (አል አህዛብ፤ 56)

አላህ ለነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የዋለው በጎ ውለታና የቸረው ልቅና መቼም ቢሆን የሚቋረጥ አይደለም። እስከ እለተ ቂያማ ድረስ ይቀጥላል።

وَلَسَوْفَ يُعْطِيكَ رَبُّكَ فَتَرْضَىٰ

“ጌታህም ወደ ፊት (ብዙን ስጦታ) በእርግጥ ይሰጥሃል። ትደሰታለህም።” (አል ዱሐ፤ 5)

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ አላህ የመልእክተኞች ፈርጥ አድርጓቸዋል። ከሁሉም ነብያት እና መልእክተኞች በከፍተኛ ሁኔታ አልቋቸዋል። ከነርሱ መሐል የተለየ ክብርና ደረጃ እንዲኖራቸው ወዷል። እንዲህ ብሏል፦

۞ تِلْكَ الرُّسُلُ فَضَّلْنَا بَعْضَهُمْ عَلَىٰ بَعْضٍ ۘ مِّنْهُم مَّن كَلَّمَ اللَّهُ ۖ وَرَفَعَ بَعْضَهُمْ دَرَجَاتٍ

“እነዚህን መልክተኞች ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ አበለጥን። ከእነርሱ ውስጥ አላህ ያነጋገረው አልለ። ከፊሎቻቸውንም በደረጃዎች ከፍ አደረገ።” (አል በቀራህ፤ 253)

“በእድ” (ከፊል) የሚለው ቃል አንዳቸውን ተብሎ ተተርጉሟል። የቃሉ የዓረብኛ ይዘት ይህን መልእክት በውስጡ ሊያካትት ይችላል። ይህም ማለት ከነብያት መሐከል ለአንዱ ከሌሎች የተለየና የላቀ ደረጃ አላህ ሰጥቶታል ማለት ነው። የዚህ እድል ባለቤት ደግሞ ያለ ጥርጥር ወዳጃችንና ነብያችን ሙሐመድ ናቸው።

ኢብን አባስ እንዳስተላለፉት አንድ ቀን ሰሐቦች ነቢዩ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ተቀምጠው ይጠባበቋቸው ጀመር። ጥቂት ቆይተውም ነቢዩ መጡ። ወደ ሰዎቹም ቀረቡ። ሲነጋገሩም ሰሟቸው። አንደኛው፦“አላህ ከፍጡራን በኩል ፍጹም ወዳጅ (ኸሊል) ማበጀቱ የሚገርም ነው። ኢብራሂምን ኸሊል አድርጓቸዋል።” አለ። ሌላኛው ደግሞ “ከዚህ ይበልጥ የሚያስገርመውስ አላህ ሙሳን ማነጋገሩ ነው።” አለ። ሌላኛውም፦“ኢሳ የአላህ መንፈስ እና ቃሉ ነው።” አለ። አራተኛው ሰው፦“አላህ አደምን መርጧቸዋል።” ሲል ተናገረ። ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰላምታ አቀረቡላቸውና እንዲህ አሉ፦

“ወጋችሁን ሰማሁ። ኢብራሂም የአላህ ኸሊል በመሆኑ መገረማችሁን አደመጥኩ። በእርግጥ ኢብራሂም እንዳላችሁት ነው። ሙሳንም ማናገሩ፣ ኢሳም የርሱ መንፈስና ቃሉ መሆኑ እርግጥ ነው። አደምንም መርጧቸዋል። አዋጅ፣ እኔ ደግሞ የአላህ ፍጹም ወዳጅ (ሐቢብ) ነኝ። ለጉራ አይደለም። በእለተ ቂያማ አደምንና ሌሎችንም ነብያት በስሩ የሚያሰልፈውን የምስጋና አርማ የምሸከመው እኔ ነኝ። ለጉራ አይደለም። በእለተ ቂያማ የመጀመሪያው አማላጅና ምልጃውም ቀድሞ ተቀባይነት የሚያገኝለት የመጀመሪያው ሰው እኔ ነኝ። ይህም ጉራ አይደለም። የጀነትን በር ዘለበት መጀመሪያ የማንቀሳቅሰው እኔ ነኝ። ለጉራ አይደለም። አላህም ይከፍትና እኔንና ከአማኞች መሐል ድሆችን ቀድሞ ያስገባል። ጉራ አይደለም። እኔ ከአላህ ዘንድ ከጥንቶቹም ከአሁኖቹም ሁሉ የተላቅኩ ነኝ። ጉራ አይደለም።” (ቲርሚዚ እና ዳሪሚ)

 


[1] ኢብን ከሲር ለአንቀጹ ከሰጡት ማብራሪያ የተወሰደ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here