ሲራ ክፍል 8 – ጥሪውን ለማኮላሸት ጥቅም ላይ የዋሉ ልዩ ልዩ ስልቶች

0
4615

ቁረይሾች ሙሀመድን (ሠ.ዐ.ወ) ማስዋሸታቸው እና ችላ ማለታቸው ከዳዕዋው እንደማይነቀንቀው ሲያዩ በድጋሚ ቆም ብለው ማሰብ ጀምሩ፤ ይህንን ደዕዋ ለማቆምና ለማኮላሸት የሚረዱ ዘዴዎችንም መረጡ። ይህም እንደሚከተለው ይቀርባል።

1. ማፌዝ፣ ማናናቅ፣ ማላገጥና ማስተባበል

የዚህ ስልት ጠቀሜታ ሙስሊሞችን ማዋረድና ውስጣዊ ጥንካሬያቸውን ማዳከም ነበር። ነብያችንንም (ሠ.ዐ.ወ) የዘቀጡ ቅጥፈቶችን እና የቂል ስድቦችን ሰደቧቸው። እብድ ብለውም ይጠሯቸው ነበር።

وَقَالُوا يَا أَيُّهَا الَّذِي نُزِّلَ عَلَيْهِ الذِّكْرُ إِنَّكَ لَمَجْنُونٌ

“‘አንተ ያ በእርሱ ላይ ቁርኣን የተወረደለት ሆይ! አንተ በእርግጥ ዕብድ ነህ’ አሉም።” (አል-ሂጅር 15፤ 6)

ደጋሚና ቀጣፊ ይሏቸው ጀመር፡-

وَعَجِبُوا أَن جَاءَهُم مُّنذِرٌ مِّنْهُمْ وَقَالَ الْكَافِرُونَ هَٰذَا سَاحِرٌ كَذَّابٌ

“ከእነርሱ የሆነ አስፈራሪም ስለ መጣላቸው ተደነቁ። ከሓዲዎቹም ‘ይህ ድግምተኛ (ጠንቋይ) ውሸታም ነው’ አሉ።” (አሷድ 38፤ 4)

በጥላቻ እይታና ስሜት ይሸኟቸዋል፤ ይቀበሏቸዋል።

وَإِن يَكَادُ الَّذِينَ كَفَرُوا لَيُزْلِقُونَكَ بِأَبْصَارِهِمْ لَمَّا سَمِعُوا الذِّكْرَ وَيَقُولُونَ إِنَّهُ لَمَجْنُونٌ

“እነሆ እነዚያም የካዱት ሰዎች ቁርኣኑን በሰሙ ጊዜ በዓይኖቻቸው ሊጥሉህ (ሊያጠፉህ) ይቀርባሉ። ‘እርሱም በእርግጥ ዕብድ ነው’ ይላሉ።” (አል-ቀለም 68፤ 51)

ነቢዩ በደካማ ባልንጀሮቻቸው ተከበው በሚቀመጡ ጊዜ አቀማማጮቹ እነዚህ ናቸው እያሉ ያፌዙባቸው እንደነበር ቁርአን ሲገልፅ

وَكَذَٰلِكَ فَتَنَّا بَعْضَهُم بِبَعْضٍ لِّيَقُولُوا أَهَٰؤُلَاءِ مَنَّ اللَّهُ عَلَيْهِم مِّن بَيْنِنَا
 

“እንደዚሁም ‘ከመካከላችን አላህ የለገሰላቸው እነዚህ ናቸውን?’ ይሉ ዘንድ ከፊላቸውን በከፊሉ ሞከርን።” (አል-አንዐም 6፤ 53)

አላህ እንዲህ በማለት ይመልሳል

أَلَيْسَ اللَّهُ بِأَعْلَمَ بِالشَّاكِرِينَ

“አላህ አመስጋኞቹን ዐዋቂ አይደለምን?” (አል-አንዐም 6፤ 53)

ሁኔታቸውን አላህ እንዲህ ሲል ተርኮልናል

إِنَّ الَّذِينَ أَجْرَمُوا كَانُوا مِنَ الَّذِينَ آمَنُوا يَضْحَكُونَ ﴿٢٩﴾ وَإِذَا مَرُّوا بِهِمْ يَتَغَامَزُونَ ﴿٣٠﴾ وَإِذَا انقَلَبُوا إِلَىٰ أَهْلِهِمُ انقَلَبُوا فَكِهِينَ ﴿٣١﴾ وَإِذَا رَأَوْهُمْ قَالُوا إِنَّ هَٰؤُلَاءِ لَضَالُّونَ ﴿٣٢﴾ وَمَا أُرْسِلُوا عَلَيْهِمْ حَافِظِينَ

“እነዚያ ያምመጹት በእነዚያ ባመኑት በእርግጥ ይስቁ ነበሩ። በእነርሱም ላይ ባለፉ ጊዜ ይጠቃቀሱ ነበር። ወደ ቤተሰቦቻቸውም በተመለሱ ጊዜ (በመሳለቃቸው) ተደሳቾች ኾነው ይመለሱ ነበር። ባዩዋቸውም ጊዜ ‘እነዚህ በእርግጥ ተሳሳቾች ናቸው’ ይሉ ነበር። በነርሱ ላይ ተጠባባቂዎች ተደርገው ያልተላኩ ሲኾኑ።” (አል-ሙጠፊፊን 83፤ 29-33)

2. አስተምህሯቸውን ጥላሸት መቀባት፣ ብዥታዎችን መፍጠር

በመልእክተኛውና በስብእናቸው ዙሪያ የሀሰት ወሬዎችን መንዛት፣ ጥርጣሬን ማንገስ ተራው ሰው ቆም ብሎ ለማሰብና ለማስተንተን ፋታ በማያገኝበት አኳኋን የሀሰት ዘመቻውን በስፋትና በብዛት ማሰራጨት። ቁርአንን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡-

وَقَالُوا أَسَاطِيرُ الْأَوَّلِينَ اكْتَتَبَهَا فَهِيَ تُمْلَىٰ عَلَيْهِ بُكْرَةً وَأَصِيلًا

“አሉም ‘የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናት። አስጻፋት። እርሷም በእርሱ ላይ ጧትና ማታ ትነበብለታለች።’” (አል-ፉርቃን 25፤ 5)

وَقَالَ الَّذِينَ كَفَرُوا إِنْ هَٰذَا إِلَّا إِفْكٌ افْتَرَاهُ وَأَعَانَهُ عَلَيْهِ قَوْمٌ آخَرُونَ فَقَدْ جَاءُوا ظُلْمًا وَزُورًا

“እነዚያም የካዱት ይህ (ቁርኣን ሙሐመድ) የቀጠፈው በእርሱም ላይ ሌሎች ሕዝቦች ያገዙት የኾነ ውሸት እንጂ ሌላ አይደለም አሉ። በእርግጥም በደልንና እብለትን ሠሩ።” (አል- ፉርቃን 25፤ 4)

وَلَقَدْ نَعْلَمُ أَنَّهُمْ يَقُولُونَ إِنَّمَا يُعَلِّمُهُ بَشَرٌ

“እነርሱም ‘እርሱን (ቁርኣንን) የሚያስተምረው ሰው ብቻ ነው’ ማለታቸውን በእርግጥ እናውቃለን።” (ነህል 16፤ 103) ይሉ ነበር።

መልእክተኛውን (ሠ.ዐ.ወ) አስመልክቶ

وَقَالُوا مَالِ هَٰذَا الرَّسُولِ يَأْكُلُ الطَّعَامَ وَيَمْشِي فِي الْأَسْوَاقِ لَوْلَا أُنزِلَ إِلَيْهِ مَلَكٌ فَيَكُونَ مَعَهُ نَذِيرًا

“ለዚህም መልክተኛ ምግብን የሚበላ፣ በገበያዎችም የሚኼድ ሲኾን ምን (መልክተኛነት) አለው? ከርሱ ጋር አስፈራሪ ይኾን ዘንድ ወደርሱ መልአክ (ገሃድ) አይወረድም ኖሯልን? አሉ።” (ፉርቃን 25፤ 7) ይሉ ነበር።

ለነዚህና መሰል እብለቶቻቸው የተሰጡ ምላሾችን ቁርአን ውስጥ በብዛት እናገኛለን።

3. ቁርአንን የጥንት አፈታሪክ ነው በማለት ማጣጣል

ይህን ስልት ሰዎች ቁርአንን እንዳይሰሙና ትኩረታቸው ወደ እሱ እንዳያደርጉ የሰዎን ህሊና ለመጥመድ የተጠቀሙበት መንገድ ነበር። ነድር ቢን አል-ሐሪስ በአንድ ወቅት ለቁረይሾች እንዲህ አላቸው፡-

“እናንት የቁረይሽ ህዝቦች ሆይ፤ ወላሂ ዘዴው ያልተሰጣችሁ የሆነ ነገር ነው እናንተ ላይ የወረደው። ሙሀመድ እኮ እናንተ ውስጥ የነበረ ያደገ የምትወዱት የነበረ ወጣት ነበር። ከሁላችሁም በላይ በንግግሩ እውነተኛና በአደራ ታማኝ ነበር። ባመጣላችሁን ነገር ሲመጣላችሁ ግን ድግምተኛ አላችሁት በእርግጥ የድግምተኞችን ንፍስታ እና ትብታብ አይተናል፤ ወላሂ! በፍጹም ድግምተኛ አይደለም። ጠንቋይ አላችሁት በእርግጥ የጠንቋዮችን ማስፈራሪያ አይተናል ማጓራታቸውንም ሰምተናል፤ ወላሂ! በፍጹም ጠንቋይ አይደለም። ገጣሚ አላችሁት በአላህ ይሁንብኝ ገጣሚም አይደለም፤ እብድ አላችሁት በእርግጥ እብዶችን አይተናል ከመተናነቁም ሆነ ንግግሩም ከማምታታትና ነገር ከማደበላለቅ የጸዳ ነው እናንተ ቁረይሽ ጎሳዎች ሆይ በሚገባ ወደራሳችሁ ተመልከቱ በእውነቱ ትልቅ ዱብዳ ነው የወረደባችሁ።”

ቀጥሎም ነድር ጉዞውን ወደ ሒይራህ (ኢራቅ) በማድረግ የፋርስን የጥንት ንጉሳን ወሬዎች፣ የሩስቱምንና የአስፈንድሪያን ታሪክ ተምሯል። እናም ረሱል (ሠ.ዐ.ወ) ስለ አላህ ሊያስታውሱና ቅጣቱን ሊያስጠነቅቁ ከሰዎች ጋር ቆይታ አድርገው ሲያጠናቅቁ ነድር ቢን አል ሀሪስ እርሳቸውን በመተካት እንዲህ ይላል፡- “በአላህ እምላለሁ ሙሀመድ ከኔ ይበልጥ ያማረ ወግ የለውም።” ከዚያም ስለ ፋርስ ንጉሳን፣ ስለ ሩስቱምና አስፈንደሪያስ ያወጋቸዋል። እንዲህም ሲል ይጠይቃቸዋል “ታዲያ ሙሀመድ በወግ ከኔ የሚበልጠው እንዴት ሆን ነው?”

የኢብኑ አባስ ዘገባ እንደሚያመላክተው ነድር ዘማሪ እንስት ገዝቶ ነበር። አንድ ሰው ለመስለም እንደሚፈልግ በሰማ ጊዜ ወደዚህች ዘፋኝ ይሄድና “አብይው፣ አጠጪው፣ ዝፈኝለት። ሙሀመድ ከሚጋብዝህ ነገር የተሻለ ነውም በይው።” ይላታል። እርሱን በማስመልከት የቁርአን መልእክት ተላልፏል፡-

وَمِنَ النَّاسِ مَن يَشْتَرِي لَهْوَ الْحَدِيثِ لِيُضِلَّ عَن سَبِيلِ اللَّهِ بِغَيْرِ عِلْمٍ وَيَتَّخِذَهَا هُزُوًا أُولَٰئِكَ لَهُمْ عَذَابٌ مُّهِينٌ

“ከሰዎችም ያለ ዕውቀት ሆኖ ከአላህ መንገድ ሊያሳስትና ማላገጫ አድርጎ ሊይዛት አታላይ ወሬን የሚገዛ አልለ። እነዚያ ለእነርሱ አዋራጅ ቅጣት አላቸው።” (ሉቅማን 31፤ 6)

4. የድርድር ፖለቲካ

በሲራ ዑለማኦች ዘንድ እንደተዘገበው ዑትባ ኢብኑ ረቢዕ በህዝቦቹ ዘንድ የተከበረ ጥበብና ብልሀት ያለው ሰው ነበር። በቁረይሾች ስብሰባ ላይ “እናንተ ቁረይሽች ሆይ፣ ሙሃመድ ጋር ሄጄ ባናግረውስ? አንዳንድ ነገሮችንም በድርድር አቅርቤለት ከፊሉን ቢቀበለኝና ብቻ የፈለገውን ሰጥተነው ቢተወን?” አላቸው። እነሱም እንዴታ አንተ የወሊድ አባት ሆይ ተነስ ሂድና አናግረው አሉት። ዑትባም ወደ ረሱል (ሠ.ዐ.ወ) ጋር መጥቶ ቁጭ አለና፡-

“የወንድሜ ልጅ ሆይ እስከማውቀው ድረስ አንተ እኛ ውስጥ በዝምድናም ሆነ በጎሳ ትልቅ ቦታና ክብር ያለህ ሰው ነህ በእርግጥ ወደ ህዝቦችህ ከባድ የሆነን ነገር ይዘህ መጥተሀል በእርሱም ሀብታቸውን በትነሀል፣ አስተሳሰባቸውን ቂላቂል አድርገሀል… አስኪ አንዳንድ ነገሮችን በድርድር አቀርብልሀለሁ ስማኝና አስበህበት ምናልባት ከፊሉን ትቀበለኝ ይሆናል” አላቸው።

ረሡልም (ሠ.ዐ.ወ) ተናገር የወሊድ አባት ሆይ ተናገር እሰማሀለሁ አሉት። “የወንድሜ ልጅ ሆይ በዚህ ይዘኸው በመጣኸው ጉዳይ ገንዘብ ከሆነ የፈለግከው ከኛ የበለጠ ሀብታም እስክትሆን ገንዘብ እንሰበስብልሀለን፣ ክብር ከሆነ የምትፈልገው በማንኛውም ጉዳይ ከአንተ ላንወጣ ከኛ በላይ እንሾምሀለን፣ ንግስናም ከሆነ የምትፈልገው ከላያችን እናነግስሀለን፣ ይህ የሚመጣብህን ራዕይ ስትመለከተው መከላከል የማትችለው ከሆነ ገንዘባችንን አውጥተን ሀኪም እንፈልግልህና ከእርሱ ነጻ እስክትሆን ድረስ ሁሉን እናድርግልሀለን።” ረሡልም (ሠ.ዐ.ወ) “የወሊድ አባት ሆይ ጨረስክ” አሉት “አዎ” አላቸው እንግዲያውስ ስማኝ አሉትና የሚከተሉትን የቁርአን አንቀጾች አነበቡለት፡-

حم ﴿١﴾ تَنزِيلٌ مِّنَ الرَّحْمَٰنِ الرَّحِيمِ ﴿٢﴾ كِتَابٌ فُصِّلَتْ آيَاتُهُ قُرْآنًا عَرَبِيًّا لِّقَوْمٍ يَعْلَمُونَ ﴿٣﴾ بَشِيرًا وَنَذِيرًا فَأَعْرَضَ أَكْثَرُهُمْ فَهُمْ لَا يَسْمَعُونَ ﴿٤﴾ وَقَالُوا قُلُوبُنَا فِي أَكِنَّةٍ مِّمَّا تَدْعُونَا إِلَيْهِ وَفِي آذَانِنَا وَقْرٌ وَمِن بَيْنِنَا وَبَيْنِكَ حِجَابٌ فَاعْمَلْ إِنَّنَا عَامِلُونَ ﴿٥﴾ قُلْ إِنَّمَا أَنَا بَشَرٌ مِّثْلُكُمْ يُوحَىٰ إِلَيَّ أَنَّمَا إِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌ وَاحِدٌ فَاسْتَقِيمُوا إِلَيْهِ وَاسْتَغْفِرُوهُ وَوَيْلٌ لِّلْمُشْرِكِينَ

“ሐ.መ.(ሓ ሚም)። (ይህ ቁርኣን) እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ ከሆነው (አላህ) የተወረደ ነው። አንቀጾቹ የተብራሩ የኾነ መጽሐፍ ነው። ዐረብኛ ቁርኣን ሲኾን ለሚያውቁ ሕዝቦች (የተብራራ) ነው። አብሳሪና አስፈራሪ ሲኾን (ተወረደ)። አብዛኛዎቻቸውም ተዉት። እነርሱም አይሰሙም። አሉም ‘ልቦቻችን ከእዚያ ወደእርሱ ከምትጠራን እምነት በመሸፈኛዎች ውስጥ ናቸው። በጆሮዎቻችንም ላይ ድንቁርና አልለ፤ በእኛና ባንተም መካከል ግርዶሽ አልለ። (በሃይማኖትህ) ሥስራም፤ እኛ ሠሪዎች ነንና።’ (እንዲህ) በላቸው ‘እኔ መሰላችሁ ሰው ብቻ ነኝ። አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ወደእርሱም ቀጥ በሉ ምሕረትንም ለምኑት ማለት ወደእኔ ይወረድልኛል። ለአጋሪዎቹም ወዮላቸው።” (ፉሲለት 41፤ 1-6)

ከዚያም ረሱል (ሠ.ዐ.ወ) ሲያነቡ ዑትባም እያዳመጠ

فَإِنْ أَعْرَضُوا فَقُلْ أَنذَرْتُكُمْ صَاعِقَةً مِّثْلَ صَاعِقَةِ عَادٍ وَثَمُودَ

“(ከእምነት) እንቢ ‘ቢሉም እንደ ዓድና ሰሙድ መቅሰፍት ብጤ የኾነን መቅሰፍት አስጠነቅቃችኋለሁ’ በላቸው።” (ፉሲለት 41፤ 13) ሲደርሱ አፋቸውን ያዛቸውና ማንበብ እንዲያቆሙ ተማጸናቸው። ይህም የሆነው ከአንቀጹ አስፈራሪነት የተነሳ ነው።

ከዛም ዑትባ ወደ ጓደኞቹ ተመልሶ በተቀመጠ ጊዜ “የወሊድ አባት ሆይ ከምን ደረስክ፣ ምን ነካህ” አሉት። ዑትባም “የነካኝማ.. ሰምቼ የማላውቀውን ንግግር መስማቴ ነው፤ ወላሂ ግጥም አይደለም፤ ድግምትም ጥንቆላም አይደለም፤ ወላሂ ጥፍጥና አለው ሰርጾም ይገባል፤ የሰው ልጅ ንግግርም አይደለም። የበላይ ይሆናል እንጂ የበላይ አይኮንበትም። እናንት ቁረይሾች ሆይ እሽ በሉኝና ይህን ሰዉ ከነ ጉዳዩ ተውት፤ ልቀቁት። ወላሂ የሰማሁት ነገር ትልቅ ይሆናል አረቦች ጉዳት ካደረሱበት (ከገደሉት) ተገላገላችሁት። ከአረቦች የበላይ ከሆነ ንግስናው ንግስናችሁ ነው ክብሩም ክብራችሁ ነው” አላቸው። “ወላሂ የወሊድ አባት ሆይ በምላሱ ደግሞብሀል” አሉት ዑትባም “ይህ የኔ ሀሳብ ነው የፈለጋችሁትን አድርጉ” አላቸው።

ጦበርይ፣ ኢብኑ ከሲር እና ሌሎችም እንደዘገቡት ወሊድ ኢብኑል ሙጊራ፣ አስ ኢብኑ ዋኢል እና ጥቂት ሙሽሪኮች ለረሱል የሚከተለውን የድርድር ሀሳብ አቀረቡ። ከነርሱ በላይ ሀብታም እስኪሆኑ ድረስ ብር ሊሰጧቸው እና ቆንጆ ድንግል ሴት ሊያጋቧቸው በምላሹ አማልክቶቻቸውን መስደብና ባህሎቻቸውን ማቄል እንዲተው ጠየቁ። ረሡል (ሠ.ዐ.ወ) የተላኩበትን ወደ ሀቅ ደዕዋ ማድረግ እንጂ አሻፈረኝ አሉ በዚህን ጊዜ “እኛ አምላክህን አንድ ቀን እንገዛውና ሌላ ቀን የኛን አማልክት ተገዛ አሏቸው” ይህንንም አሻፈረኝ አሉ። አላህም የሚከተለውን ቃል አወረደ፡-

قُلْ يَا أَيُّهَا الْكَافِرُونَ ﴿١﴾ لَا أَعْبُدُ مَا تَعْبُدُونَ ﴿٢﴾ وَلَا أَنتُمْ عَابِدُونَ مَا أَعْبُدُ ﴿٣﴾ وَلَا أَنَا عَابِدٌ مَّا عَبَدتُّمْ ﴿٤﴾ وَلَا أَنتُمْ عَابِدُونَ مَا أَعْبُدُ ﴿٥﴾ لَكُمْ دِينُكُمْ وَلِيَ دِينِ

“በላቸው ‘እናንተ ከሓዲዎች ሆይ! ‘ያንን የምትግገዙትን (ጣዖት አሁን) አልግገዛም። እናንተም እኔ የምግገዛውን (አምላክም አሁን) ተገዢዎች አይደላችሁም። እኔም ያንን የተገዛችሁትን (ወደፊት) ተገዢ አይደለሁም። እናንተም እኔ የምግገዛውን (ወደፊት) ተገዢዎች አይደላችሁም። ለእናንተ ሃይማኖታችሁ አልላችሁ። ለእኔም ሃይማኖቴ አለኝ።’ (አል-ካፊሩን)

ከቁረይሾች ውስጥ የተከበሩት ሹማምንቶች ካወጡና ካወረዱ በኃላ ኡትባ ኢብኑን ወሊድ ያደረገውን ሙከራ ደግመው ለመሞከር ተስማምተው ረሡል (ሠ.ዐ.ወ) ጋር ተሰባስበው በመሄድ ሹመት እና ገንዘብን በድርድር አቀረቡላቸው እንዲሁም የሚመጣባቸው ነገር የጅን ራዕይ ከሆነ ሀኪም ሊያመጡ ቃል ገቡላቸው። ረሡልም (ሠ.ዐ.ወ)፡- “እምትሉት ሁሉ እኔ ጋር የለም ወደናንተ የመጣሁበት ነገር ይዠ ስመጣ ገንዘብ፣ ክብርና ንግስና ፈልጌ አይደለም። ግና አላህ ወደናንተ መልክተኛ አድርጎ ላከኝ። መጽሀፉንም በኔ ላይ አወረደ። አብሳሪና አስጠንቃቂ እንድሆን ስላዘዘኝ የጌታየን መልክት አደረስኩላችሁ መከርኳችሁም። ያመጣሁትን ከተቀበላችሁኝ በዚህም በመጪው አለምም ድርሻችሁ ነው። እምቢ ካላችሁም አላህ በመካከላችን እስኪፈርድ በእርሱ ትዕዛዝ ስር እታገሳለሁ።”

እነሱም “ካቀረብንልህ ነገሮች ምንም የማትቀበለን ከሆነ ይሀን ብቻ አድርግልን ከህዝቦች ሁሉ ከኛ በላይ ጠባብ በሆነ ሀገር፣ ባነሰ ግብዓት እና በተጣበበ ኑሮ የሚኖር ማንም እንደሌለ ታውቃለህ፤ በላከህ (መልእክት) የላከህን ጌታ ጠይቅልን፤ ይሄን ያጣበበንን ተራራ ያንቀሳቅስልን ልክ እንደ ሻም እና ኢራቅ ወንዞች ወንዝ ያፍልቅልን ወይም ደግሞ ያለፉት አባቶቻችንን ከሞት ይቀስቅስልን። ታዲያ ከሚቀሰቀሱት ውስጥ አንዱ ቁሰይ ኢብኑ ኪላብ ይሁን እና እውነተኛ ሽማግሌ ስለነበር የምትለው ነገር እውነት ይሁን ውሸት እንጠይቀዋለን። ለአንተም የአትክልት ስፍራ፤ ያሸበረቀና ያማረ ቤት፣ ከምናይህ ሁኔታህ የሚያብቃቃህ በወርቅና በብር የተሞላ ካዝና ይስጥህና ሀብታም ያድርግህ። የጠየቅንህን ካስደረግክ እናምንልሀለን አላህ ዘንድም ያለህን ቦታ እንረዳለን እንደምትለውም መልክተኛ አድርጎ ልኮሀልም ማለት ነው።” አሉ።

ረሡልም (ሠ.ዐ.ወ) “ይህን አላደርገውም ጌታውንም በንዲህ አይነት ጥያቄ የሚጠይቅ ሰውም አይደለሁም አሏቸው።” ከብዙ ንግግር እና ክርክር በኃላ ቁረይሾችም “ይህን የሚያስተምርህ የማማ አካባቢ የሚገኝ ረህማን የሚባል ሰው እንደሆነ ደርሰንበታል። ወላሂ በረህማን በፍጹም አናምንም። ሙሀመድ (ሆይ) አማራጮችን ሁሉ ሰጥተንሀል ወላሂ ሳናጠፋህ ወይም ሳታጠፋን አንላቀቅም” ብለው ተነስተው ሄዱ።

5. ማሰቃየት

ቁረይረሾች ከዚህ በፊት የኢስላምን ደዕዋ ለማቆም የተጠቀሟቸው ስልቶች ምንም ጥቅም እንዳላስገኙላቸው በመረዳት ነብያችንን (ሠ.ዐ.ወ) እና ሰሀቦችን ማሰቃየትና መቅጣት ጀመሩ። ቡኻሪ ከአብደላህ ኢብኑ መስዑድ እንደዘገቡት ነብያችን (ሠ.ዐ.ወ) ካዕባ ጋር እየሰገዱ ሳለ አቡ ጃህልና ጓደኞቹ ተቀምጠው ባሉበት “ሙሀመድ ሱጁድ ሲወርደ የእርድ ሆድ እቃ (አንጀት) አምጥቶ ጀርባው ላይ የሚጥል ማን ነው” ብለው ተጠያየቁ። ከውስጣቸው እጅጉን የጠመመው ሰው (ኡቅባ ኢብኑ ሙዒጥ ይባላል) አምጥቶ ነብያችን (ሠ.ዐ.ወ) ሱጁድ እስከሚያደርጉ ጠብቆ በትከሻቸው መሀል ከጀርባቸው ላይ አስቀመጠው። ይህ ሁሉ ሲሆን ከመመልከት ውጭ ምንም ማድረግ አልችልም ነበር። ምን አለ አቅም ቢኖረኝ!! በኩራት በመምቦጣረር አንዳቸው አንዱ ላይ እየተዘናበለ ሲሳሳቁ ፋጢማ (ረ.ዐ) መጥታ ከጀርባቸው ላይ እስክታነሳላቸው ድረስ በሱጁድ ላይ ቆይተው ነበር። ከዛም እራሳቸውን ቀና አደረጉና ሶስት ግዜ ‘ያ አላህ ቁረይሾችን አንድ በላቸው’ ብለው ዱዕ ሲያደርጉ በዚያ ሀገር የተደረገ ዱዕ ተቀባይነት እንደሚኖረው ስለሚያውቁ በጣም ደነገጡ።

ከዚህም አልፈው ረሡል (ሠ.ዐ.ወ) በመካከላቸው፣ ባጠገባቸው አልያም በመንገድ ሲያልፉ እንዲሁም በስብሰባዎቻቸው ላይ ያፌዙ ይቀልዱ እና ያላግጡባቸው ነበር።

ጦበሪ እና ኢብኑ ኢስሀቅ እንደዘገቡት ከቁረይሾች አንዱ ረሡል (ሠ.ዐ.ወ) ከመካ መንገዶች በአንዱ ላይ ሲያልፉ አፈር ዘግኖ ጭንቅላታቸው ላይ በተነባቸው። በዚሁ ሁኔታ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ከልጆቻቸው አንዷ እያለቀሰች አፈሩን ስታጥብላቸው “ልጄ አታሰልቅሽ አላህ አባትሽን ይከላከልለታል” ይሏት ነበር። በአብዛሀኛው ህዝብም ሆነ በግለሰቦች ዘንድ ካላቸው ትልቅ ተምሳሌትነት እና ክብር እንዲሁም በአቡ ጧሊብ ከሚደረግላቸው ከለላ አልፎ ወራዳ የሆኑ በደሎች ይደርሱባቸው ነበር።

ሰሀቦቻቸውማ (ረ.ዐ) ታጋሽ እንኳን ሊያወሳው የሚዘገንን የሆኑ የስቃይ አይነቶች ተፈራርቀውባቸዋል። ከቅጣቱ ብዛት የሞተው ሞቶ የታወረው ታውሯል… ይህ ሁሉ ግን ከአላህ ዲን (ኢስላም) ቅንጣትን ታክል ንቅንቅ አላደረጋቸውም። በያንዳንዳቸው ዙሪያ የተዘገበውን ብናነሳ ስለሚረዝም ከገጠማቸው ቅጣቶች የተወሰኑ ምሳሌዎችን እንጥቅስ።

  1. ኡሰማን ኢብኑ አፋንን (ረ.ዐ) አጎታቸው ከዘምባባ ቅጠል በተሰራ ሰሌን ያፍኑትና ከስር ጭስ በማጨስ ይቀጡት ነበር።
  2. ሙስዐብ ኢብኑ ኡመይር (ረ.ዐ) እናቱ መስለሙን ባወቀች ግዜ ከሰዎች ሁሉ የተሻለ ፀጋ የሞላበት ኑሮ ከሚኖርበት ቤቱ አስወጥታው ቆዳው ልክ እንደ እባብ ቆዳ እየተቀረፈፈ እስኪላላጥ ድረስ ለረሀብ ዳረገችው።
  3. ቢላል (ረ.ዐ) የኡመያ ኢብኑ ኸለፍ አልጁመህይ ባሪያ ነበር። ኡመያ የፀሀይቷ ንዳድ ከፍ ሲል በጋለው የመካ አሸዋ ላይ ቢላልን አስተኝቶ ትልቅ ቋጥኝ ደረቱ ላይ በማስቀመጥ “ወላሂ በሙሃመድ ክደህ ኢዛና ላትን እስካላመለክ ድረስ ትሞታለህ እንጂ አለቅህም” ይለው ነበር። ከዚህ ሁሉ ስቃይ ጋር የቢላል መልስ ግን “አሃዱን አሃድ” ነበር።
  4. አማር ኢብኑ ያሲር (ረ.ዐ) የበኒ መህዙም አገልጋይ (ባሪያ) ነበር። ከነወላጆቹ ሰለመ። ጣኦታዊያን -በዋናኝነት አቡጃህል ፀሀይ ስትበረታ ወደ ሜዳ ያወጧቸውና በግለቱ ይቀጣቸው ነበር። በመቀጣት ላይ ሳሉ ነብያችን (ሠ.ዐ.ወ) ባጠገባቸው አለፉ። “የያሲር ቤተሰብ ሆይ ታገሱ። ጀነት ቃል ተገብቶላችኋል” አሏቸው። ያሲር ከቅጣቱ ብዛት ሲሞት ሱመያን (የአማርን እናት) አቡ ጃህል ብልቷ ላይ በስለት ወግቶ ገደላት። በዚህም በኢስላም ታሪክ የመጀመሪያዋ እንስት ሸሂድ (መስዋእት) ለመሆን ታደለች። አማር ላይ ስቃዩን አበረቱበት። አንድ ግዜ በጸሐይ ግለት፣ ሌላ ግዜ ደረቱ ላይ ቋጥኝ በማስቀመጥ፣ ቀጥሎም ውሃ ውስጥ በመድፈቅ ቅጣቶችን እያፈራረቁ አሰቃዩት። “ሙሀመድን ሳትሰድብ ወይም ስለ ላትና ኡዛ በጎ ነገር ካልተናገርክ አንተውህም” አሉት። ያሉትንም ለመፈፀም ተስማማ። ተገዶም ፍቃዳቸውን ፈፀመ። ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድም እያለቀሰ በመምጣት ይቅርታ ጠየቃቸው። አላህም ተከታዩን ቁርአናዊ መልእክት አስተላለፈ “ከእምነቱ በኋላ በአላህ የካደ ሰው (ብርቱ ቅጣት አልለው)። ልቡ በእምነት የረጋ ኾኖ (በክህደት ቃል በመናገር) የተገደደ ሰው ብቻ ሲቀር። ግን ልባቸውን በክሕደት የከፈቱ ሰዎች በነሱ ላይ ከአላህ ቁጣ አለባቸው። ለእነሱም ታላቅ ቅጣት አልላቸው።” (ነህል 16፤ 106) ።
  5. ስሙ አፍለህ (ረ.ዐ) የሚባል የበኒ ዐብደዳር ባሪያን፤ እግሩን በገመድ አጥብቀው አስረው መሬት ለመሬት ይጎትቱት ነበር።
  6. ኸባብ ኢብኑል ዐረት (ረ.ዐ) ጣኦታዊያን የበረታ ስቃይ ያደርሱበት ነበር። ብዙ ጊዜ በጠራራይቷ ነዲድ ጸሃይ በጋለ አለት ራቁቱን አስተኙት። መንቀሳቀስ እንዳይችልመ ትልቅ አለትን ደረቱ ላይ አስቀመጡበት። አለቱ ጀርባውን ሰርስሮ በመግባቱ ቀዝቅዞ ከላዩ ላይ ሲወድቅለት ሰውነቱ ላይ ትልቅ ሽንቁርን ትቶ ነበር።

ለአላህ ሲሉ መከራን የተሸከሙ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች (ሰሀቦች) ስም ዝርዝር ብዙ ነው። ጣኦታዊያን አንድ ሰው መስለሙን በሰሙ ቁጥር እጅግ የሚያሳቅቅ ቅጣት ይቀጡት ነበር። እዚህ ጋር ኢማሙ አል-ቡኻሪ የዘገቡትን አንድ ታሪክን እናውሳ። ኸባብ ኢብኑል ዐረት ሲናገር “አንድ ቀን ነብዩ (ሠ.ዐ.ወ) በካዕባ ጥላ ስር ፎጣቸውን ተንተርሰው ሳሉ ወደርሳቸው መጣሁ። በወቅቱ ከጣኦታዊያን ይደርስብን የነበረው መከራ ከባድ ስለነበር ነቢዩንም ‘አንቱ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አላህን አይለምኑልንምን?’ ስላቸው ፊታቸው በንዴት ቀላ። ከተጋደሙበት ቀና ብለው ተቀምጠው:-

لقد كان من قبلكم ليمشط بمشاط الحديد ما دون عظامه من لحم أو عصب ما يصرفه ذلك عن دينه، وليتمنّ الله هذا الأمر حتى يسير الراكب من صنعاء إلى حضرموت لا يخاف إلا الله والذئب على غنمه ولكنكم تستعجلون

‘ከናንተ በፊት የነበሩ ህዝቦች በብረት ሙሽጥ (መላጊያ) አጥንታቸው እስኪቀር ስጋቸው ሲቧጠጥ ከዲናቸው ንቅንቅ አይሉም ነበር። አላህም ይህንን ጉዳይ (ኢስላምን) ሙሉዕ ያደርገዋል (እተፈለገበት ያደርሰዋል)። አንድ ተጓዥ ከሰንዕ ተነስቶ ሀድረሞት እስኪደርስ አላህን ከዚያም ፍየሎቹን ተኩላ እንዳይበላበት እንጂ ማንንም ሳይፈራ ይጓዛል። እናንተ ግን ትቸኩላላችሁ’ አሉኝ” ብሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here