ሲራ ክፍል 7 – ይፋዊ ጥሪ

0
3660

ኢብኑ ሀሺም “ሰዎች በብዛት ከሴትም ከወንድም ወሬው በመካ ውስጥ እስኪሰራጭ ድረስ ወደ ኢስላም ገቡ። ይህ ወቅት ረሱል ዳእዋውን በድብቅ ማድረግ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በአላህ ትዕዛዝ ግልጽ እስከወጣበት ጊዜ የነበሩት ሶስት አመታት ናቸው።”

ይህኔ ረሡል (ሠ.ዐ.ወ) “የታዘዝክበትን ነገር በይፋ ግለፅ። አጋሪዎችንም ተዋቸው።” ለሚለው የአላህ ትዕዛዝ ምላሽ መስጠት እና መተግበር ጀመሩ። ሶፋ ተራራም ላይ ወጡና “የፈህር ጎሳዎች፤ የኡደይ ጎሳ ልጆች ….” እያሉ መጣራትቱን ተያያዙት። በዙሪያቸው ሰዎች ይሰባሰቡ ጀመር፤ ራሳቸው መምጣት ያልቻሉትም ምን እንደሆነ ለማወቅ መልክተኛ ላኩ።

ነብዩም (ሠ.ዐ.ወ) “በሸለቆው አቅጣጫ ወራሪ ሊወጋችሁ እየመጣ ነው ብላችሁ ታምኑኛላችሁን?” ብለው ጠየቁ “ውሸት ከአንተ አይተን አናውቅም” ብለው መለሱላቸው ነቢዩም “እንግዲያውስ ብርቱ ቅጣት እንዳያገኛችሁ አስጥንቃቂያችሁ ነኝ” በማለት ሲናገሩ አቡ ለሃብ በቁጣ ቀኑን ሙሉ የከሰርክ ሆነህ ዋል! የሰበሰብከን ለዚሁ ነውን? አላህም “የአቡ ለሃብ እጆች ከሰሩ (ጠፉ)፤ እርሱም ከሰረ።” የሚለው የቁርአን አንቀፅ አወረደ። ከዚያም ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ወረዱ። “ቅርብ ዘመዶችህን አስጠንቅቅ” ለሚለው የአላህ ቃልም እንዲሁ ምላሽ ሰጡ። በዙሪያቸው ያሉትን ዘመዶችና የቅርብ ቤተሰቦች ሰበሰቡና “እናንተ የካዕብ ኢብኑ ሉአይ ልጆች ሆይ እራሳችሁን ከእሳት አድኑ። የሙረት ኢብኑ ካእብ ልጆች ሆይ እራሳችሁን ከእሳት አድኑ፤ የዐብድ ሸምስ ልጆች ሆይ እራሳችሁን ከእሳት አድኑ፤ የአብድ መናፍ ልጆች ሆይ እራሳችሁን ከእሳት አድኑ፤ የአብዱል ሙጦሊብ ልጆች ሆይ እራሳችሁን ከእሳት አድኑ አንቺ ፋጢማ ሆይ እራስሽን ከእሳት አድኚ፤ እኔ ከአላህ ዘንድ ምንም አልጠቅምሽም። ግና ዘመዶቼ ናችሁና ዝምድናችንን እንከባከባታለሁ።”

ደዕዋው በግልፅ መደረግ ሲጀምር የቁረይሽ ምላሽ ጀርባ መስጠትና ማውገዝ ሲሆን ለዚህም ከአባቶቻቸው የወረሱትን እምነት ፈጽሞ መተው እንደማይችሉ ምክንያት በማቅረብ ነበር። አላህ ይህን እውነታ ሲናገር ለእነርሱም

وَإِذَا قِيلَ لَهُمُ اتَّبِعُوا مَا أَنزَلَ اللَّهُ قَالُوا بَلْ نَتَّبِعُ مَا أَلْفَيْنَا عَلَيْهِ آبَاءَنَا أَوَلَوْ كَانَ آبَاؤُهُمْ لَا يَعْقِلُونَ شَيْئًا وَلَا يَهْتَدُونَ ﴿١٧٠﴾ وَمَثَلُ الَّذِينَ كَفَرُوا كَمَثَلِ الَّذِي يَنْعِقُ بِمَا لَا يَسْمَعُ إِلَّا دُعَاءً وَنِدَاءً صُمٌّ بُكْمٌ عُمْيٌ فَهُمْ لَا يَعْقِلُونَ

“ለእነርሱም ‘አላህ ያወረደውን ተከተሉ’ በተባሉ ጊዜ ‘አይደለም አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር እንከተላለን’ ይላሉ። አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና (ወደ እውነት) የማይመሩም ቢኾኑ (ይከተሉዋቸዋልን?) የነዚያም የካዱት (እና ወደ ቅን መንገድ የሚጠራቸው ሰው) ምሳሌ እንደዚያ ድምጽንና ጥሪን በስተቀር ሌላን በማይሰማ (እንስሳ) ላይ እንደሚጮህ ብጤ ነው። (እነርሱ) ደንቆሮዎች፣ ዲዳዎች፣ ዕውሮች ናቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አያውቁም።” (አል-በቀራ 2፤ 170-171)

የአማልክቶቻቸውን ዋጋ ቢስነት ሲያሳውቋቸው፤ ህልሞቻቸውን ውድቅ ሲያደርጉባቸውና ጣኦት አምልኮት ሙጥኝ ለማለታቸው ያቀረቡትን ምክንያት ውድቅ በማድረግ የአያቶቻቸውና አባቶቻቸው ፈለግ ስለሆነ ብቻ መሆኑን ሲያጋልጧቸው፤ አባቶቻቸውን አቅል ሁሉ እንደሌላቸው ሲናገሩ፤ ከእነርሱ ውስጥ አላህ በኢስለም ካዳናቸው እንዲሁም ከጎናቸው ቆመው ሲከላከሉላቸው ከነበሩት ከአጎታቸው አቡ ጧሊብ ውጭ ሁሉም ነገሩን ትልቅ ቦታ ሰጥተውት አወገዙትም፤ ፍፁም በጠላትነት ፈርጀው ለመቃወም አደሙ።

ቅድሚያ ለዘመድና ቤተሰብ

ጥያቄ፡- አላህ ለነቢዩ ለምን ዳዕዋውን ለቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው እንዲያደርሱ ነጥሎ አዘዛቸው?

መልስ፡- እዚህ ውስጥ ባጠቃላይ በሁሉም ሙስሊም በተለይ ደግሞ እንደ ደዕዋ ሰው የተለያዩ የተጠያቂነት ደረጃዎች እንዳሉ እንመለከታለን።

ትንሹ የተጠያቂነት ደረጃ፡- ይህ አንድ ሰው ስለ ራሱ ተጠያቂ የሚሆንበት ደረጃ ነው። ወህይ ሲጀምር እንደተመለከትነው ያን ያህል ረዘም ያለ ጊዜ የቆየው፤ ለዚህ እርከን ተገቢውን ጊዜ ከመስጠት አንፃር ነበር። ይህም ሙሐመድ (ሠ.ዐ.ወ) ተረጋግተው ከአላህ ዘንድ የተላኩ ነብይና የሚወርድላቸውም ወህይ ከአላህ (ሱ.ወ) መሆኑን ለራሳቸው አምነው ልባቸው እንዲረጋጋና ከዚያ በኋላ ለሚመጣላቸው ትእዛዝ መርህና ድንጋጌዎች እንዲዘገጁ ነበር።

ለጥቆ የሚመጣው የተጠያቂነት ደረጃ፡- አንድ ሙስሊም ስለቤተሰቦቹ እና ስለዘመዶቹ የሚኖረው ተጠያቂነት ነው። ይህን ሓላፊነት በአግባቡ መወጣትን ስንቃኝ አላህ ቤተሰብንና ዘመዶችን ማስጠንቀቅና ዳእዋን ለእነርሱ የማድረስ ግዴታን በይፋ ለሁሉም የማድረስ ሃላፊነትን ካዘዘ በኋላ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ይህም የተሰጠውን ስፍራ በሚገባ ያመላክታል። ይህን የሀላፊነት ደረጃ የመሸከሙ ሂደት ማንኛውም ቤተሰብና ቅርብ ዘመዶች ያሉትን በሙሉ የሚያካትት ሲሆን የጥሪውም ይዘት ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ለህዝቦቻቸው የሚያደርጉት ጥሪ ለቤተሰብና ለዘመዶች ከሚደረግ ጥሪ እምብዛም የተለየ ሆኖ አናገኘውም። ምናልባት የመጀመሪያው በአላህ ወህይ እየተመራ ወደ አዲስ እምነትና የህይወት ጎዳና ሲጣራ ሌላኛው ይህንን ጥሪ አድራሽና የሱ ቃል አቀባይ ከመሆኑ በስተቀር።

ሶስተኛው ደረጃ፡- አንድ አሊም ወይም ዳኢ ስለ መንደሩ ወይም ስለሀገሩ እንዲሁም አንድ አስተዳደሪ ስለሀገሩና ህዝቦቹ የሚኖርበት ኃላፊነት ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here