ሲራ ክፍል 5 – የነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) በሂራዕ ዋሻ መገለል /ኸልዋ/

0
5074

የነብያችን (ሠ.ዐ.ወ) እድሜያቸው ወደ 40 እየተቃረበ ሲመጣ፤ ከወትሮው በተለየ ከሠው መነጠልን በተለያዩ ጊዜያት እየወደዱት መጥተዋል። አላህም ለመገለያው ቦታ የሂራዕ ዋሻን እንዲወዱት አድርጓቸዋል። ሂራዕ ማለት ከመካ በሰሜን ምዕራብ የሚገኝ ተራራ ሲሆን ነቢያችንም ዋሻው ውስጥ ለብዙ ሌሊቶች አንዳንዴም አስር ሌላ ጊዜም ከዘያ ለሚዘልቁ ቀናት አላህን በመገዛት ያሳልፉ ነበር።

ወደ ቤታቸው ሲመለሱም ብዙም ሳይቆዩ ለሚቀጥለው ኸልዋ በአዲስ ስንቅ ይቋጥሩ ነበር። በእነዚህ ኸልዋዎች (ብቸኝነት) በአንደኛው ላይ ወህይ እስከመጣላቸው ድረስ በዚህ ሁኔታ አሳልፈዋል።

ኸልዋ /አላህን ለመገዛት ብቸኝነትን በመምረጥ መገልል/

ያኔ የነብያችን ቀልብ እንዲህ በፍቅር የገዛው ኸልዋ፤ ለአጠቃላይ ሙስሊሞች በተለይ ደግሞ ወደ ኢስላም ለሚጣሩ ዳዒዎች እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ያለበት ነው። ከዚህም ውስጥ፡-

1. በቀልብ ውስጥ የአላህን ሙሀባ /ውዴታ/ ማሳደግ

አእምሮን ብቻ በእውቀት ማጥገብ በቂ አይደለም። ይህማ ቢሆን ኖሮ ኦረይንታሊስቶች /ሙስሊም ያልሆኑ ኢሰላምንና ሌሎች የምስራቅ ሀይማኖትን የሚያጠኑ/ ከሙስሊሞች የበለጠ አሏህና የነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ወዳጅ ይሆኑ ነበር። ለመሆኑ ከምሁሮች አንድም እራሱን አሳልፎ ለአንድ ሂሳባዊ የስሌት ህግ አለያም አልጀብራ ጥያቄ መስዋእትነት የሠጠ ሰምተሀልን?… ይልቁንም በአላህ ከማመን በኋላ ወደ እሱ ውዴታ መዳረሻ መንገዶች በዋነኝነት፡-

  1. የታላቅነቱ ማረጋገጫ የሆኑ ምልክቶችን፤ ውለታውና ፀጋዎቹን በሠፊው ማስተንተን
  2. በምላስና በቀልብ በብዛት እሱን ማውሳት
  3. ፈርድ የሆኑ ነገሮች በጥንቃቄ ተጠባብቆ መስራት ሡና /ነዋፊል/ የሆኑትንም ማባዛት

ይህ ሁሉ ሊገራ የሚችለው በተደጋጋሚ ከአላህ ጋር ብቸኝነትን /ኸልዋ/ በማዘውተር ነው።

2. ነፍስን መተሣሠብና በሽታዎቿን ማከም

የሰው ልጅ ነፍስ የብዙ በሽታዎች መናኸሪያ ናት። ታዲያ ከነዚህ በሽታዎች መካከል ከሰዎች ተነጥሎ ነፍስን በመተሳሰብና ያለፈቻቸውን ድንበሮች እያሰታወሱ ጉድለቶቹዋን በማሰተዋል እንጂ የማይታከሙ አሉ። ብቻውን ሆኖ ሲያስተነትን ግን የሰው ልጅ የነፍስያ እውነታ ይገለጽለታል። ምን ያህል ነፍስ አላህን ፈላጊና ደሀ እንደሆነችና በእያንዳንዷ ቅጽበት የእሱን (አላህ) እርዳታ ፈላጊ መሆኗ፤ ሠዎች እሱን ለመጥቀምም ሆነ ለመጉዳት የማይችሉ ደካሞች መሆናቸውን ይደርስበታል። ስለሆነም ሙገሳቸውም ሆነ ወቀሳቸው ውጤት አልባ እንደሆነ ይገለጥለታል፤ ይህና ሌሎችም መሠል እውነታዎች ፍንትው ብለው ሲታዩት ስራውን ለአላህ ብቻ አጥርቶ ይሰራል፤ ይተናነሳል… በተደጋጋሚ መገልልን /ኸልዋን/ በማብዛቱ የተነሳ ባገኘው ብርሃን የነፍስን እውነታ ሲረዳ አብሮ የነፍስ ጣጣ /መዘዞች/ አብረው ይገረሰሳሉ /ይወገዳሉ/።

ተግባራዊ ልምምድ፡-

ይህ ሁሉ የሚሆነው ከዱንያ ጭንቅንቅ፣ ከጩኅቷ፣ ከከንቱ ብለጭልጯ በቀን፣ በለሊት፤ በወራትና፤ በዓመታት ለተወሰኑ ግን ተደጋጋሚ ለሆኑ ወቅቶች ገለል ብሎ ራስን መመልከት ሲቻል ነው። ለዚሁም ለምሳሌ

  1. እዕቲካፍ በረመዷን የመጨረሻው አስር ቀናት ወይም አንዲት ምሽት ከሁሉም ወራት በመስጂድ ውስጥ ማሳለፍ
  2. በሁሉም ሌሊቱ የመጨረሻው 1/3ኛ ክፍል ላይ የማገባደጃ ጥቂት የኢስቲግፋር ወቅት
  3. በጠዋት እና በማታ ውዳሴ /አዝካር/ ወቅት
  4. ከመኝታ በፊት ነፍስን በመተሳሰቢያና የመኝታ ዚክር በሚደረግበት ወቅት
  5. መስጂድ ቀደም ብሎ ለሰላት መግባትና ሰላትን ቁጭ ብለው እየተጠባበቁ
  6. ከሰላት በኋላ ቁጭ ብሎ ዱዓ በማድረግ ወቅት ላይ
  7. ሌላው ቢቀር አዛን እየሰማ ከሙአዚኑ ተከትሎ ካለ በኋላም ሊሆን ይችላል

ከላይ የተጠቀሱት ጊዜያት ሁሉም ቀልብ ከዱንያ ጋ ያለውን መገናኛ በመቁረጥ ትኩረቱን ትልቅና አሸናፊ ወደ ሆነው አላህ በአዲስ መልክ የሚያቆራኝበት ነው።

የወህይ መጀመር

ኢማሙል ቡኻሪ እንደዘገቡት እናታችን ዐዒሻ /ረ.ዐ./ የወህይ አጀማመር እንዴት እንደነበር ስትገልፅ እንዲህ ትላለች።

أول ما بدء به رسول الله  الرؤيا الصالحة في النوم، فكان لا يرى رؤيا إلا جاءت مثل فلق الصبح، ثم حبب إليه الخلاء وكان يخلو بغار حراء فيتحنث فيه الليالي ذوات العدد قبل أن ينزع إلى أهله ويتزود لذلك ثم يرجع إلى خديجة فيتزود لمثلها، حتى جاءه الحق وهو في غار حراء . فجاءه الملك فقال له اقرأ : فقال ما أنا بقارئ قال فأخذني فغطني حتى بلغ منى الجهد ثم أرسلني فقال: اقرأ : فقلت ما أنا بقارئ، فأخذني وغطني حتى بلغ منى الجهد فقال اقرأ: فقلت : ما أنا بقارئ فأخذني وغطني الثالثة ثم أرسلني فقال : اقْرأْ بِاسْمِ رَبِّكَ الَّذِي خَلَقَ . خَلَقَ الإنسَانَ مِنْ عَلَقٍ . اقْرَأْ ورَبُّكَ الأَكْرَمُ . الَّذِي عَلَّمَ بِالْقَلَمِ . عَلَّمَ الإنسَانَ مَا لَمْ يَعْلَمْ.

“መጀመሪያ ጥሩ ጥሩ ህልሞች በእንቅልፋቸው ያዩ ነበር ታዲያ ያዩዋቸው ህልሞች ልክ እንደ ንጋት ጎህ በእውን ይከሰቱ ነበር። ከዚያ በኋላ በሂራ ዋሻ ዉስጥ መገለልን ወደዱ በዚህም ዋሻ ዉስጥ ብቻቸውን ለዚህ የሚሆን ስንቅን ለመሰነቅ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሳይመለሱ ብዙ ሌሊቶችን ያሳልፉ ጀመር። ከዚያም ወደ ኸዲጃ (ረ.ዐ) ይመለሱና ስንቅ ይሰንቃሉ በእንዲህ አይነት ሁኔታ በሂራ ዋሻ ዉስጥ ከጌታቸው የሆነው ሃቅ እስከመጣላቸው ድረስ ቀጠለው ነበር።

መላኢካው መጥቶ ‘አንብብ’ አላቸው ‘እኔ አንባቢ አይደለሁም’ በማለት መለሱ፤ ይዞኝ ነፍሴ እስክትወጣ ድረስ ጭምቅ አደረገኝና ለቀቀኝ። እንደገና ‘አንብብ’ አለኝ ‘እኔ አንባቢ አይደለሁም’ ስል መለሰስኩኝ። ይዞኝ በድጋሚ ነፍሴ እስክትወጣ ድረስ ጭምቅ አድርጎኝ ለቀቀኝና ‘አንብብ’ አለኝ እኔም ‘አንባቢ አይደለሁም’ አልኩት። ለሶስተኛ ጊዜ ነፍሴ ልትወጣ እስክትደርስ ጨምቆ ለቀቀኝና እንዲህ በማለት ተናገረኝ ‘አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም። ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)። አንብብ ጌታህ በጣም ቸር ሲኾን፤ ያ በብዕር ያስተማረ፤ ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲኾን።’”

አላህ በፍፁም የማያዋርዳቸው ሰዎች ባህሪ

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ልባቸው በጣም እየመታና እየተርገፈገፉ ተመልሰው ወደ ባለቤታቸው ኸዲጃ ቢንቲ ኹወይሊድ (ረ.ዐ) ዘንድ “አከናንቡኝ፤ አከናንቡኝ” /ዘሚሉኒ ዘሚሉኒ/ እያሉ ገቡ። የያዛቸው ፍርሀት እስኪለቃቸው ድረስ አከናነቧቸውና ለኸዲጃ ክስተቱን ሁሉ ነገሯት። እኔ ለነፍሴ ፈራሁ! አሉ። ኸድጃም (ረ.ዐ)፡-

كلا والله لا يخزيك الله أبداً، إنك لتصل الرحم وتحمل الكل وتُكسب المعدوم وتقرى الضيف وتعين على نوائب الحق

“በፍፁም! ወላሂ አላህ በጭራሽ አያዋርድህም አንተኮ ዝምድናን የምትቀጥል፤ የተቸገረን የምትረዳ፤ እንግዳን የምታከብር፤ ለሌላቸው ሰጪና ሀቅ ላይ የምትተባበር ነህ።”

የአዋቂ ምስክርነትና የተዋረድ ፈለግ

እናታችን ኸዲጃ (ረ.ዐ) ነቢያችንን ወደ ወረቀት-ኢብኑ ነውፈል ዘንድ ወሰደቻቸው። ወረቀት ኢብኑ ነውፈል የአጎቷ ልጅ ሲሆን በጃሂሊያው ዘመን ክርስትናን ከተቀበሉት መሃል ነበር። ከወንጌልም አላህ የፈለገለትን በኢብራይስጥ ቋንቋ ይፅፍ ነበር። ከእርጅናም ብዛት ዓይኑ ታውሮ ነበር። ኸዲጃም የአጎቴ ልጅ ሆይ የወንድምህ ልጅ የሚልህን እስቲ ስማ ስትለው ወረቀትም ለነቢያችን የወንድሜ ልጅ ሆይ ምንድነው የሚታይህ በማለት ጠየቃቸው።

ነብያችንም (ሰ.ዐ.ወ) የታያቸውን ነገር ነገሩት ወረቀትም “ይህማ በሙሳ (ዐ.ሰ) ላይ የወረደው ናሙስ ነው (ጂብሪል/ወህይ) ዋ! ጠንካራ ወጣት ሆኜ በነበር! ዋ! ያኔ ወገኖችህ ከሀገርህ ሲያስወጡህ በህይወት ሆኘ በነበር!” አለ ነብያችንም “እውን ያስወጡኛልን” አዎ አንድም ሰው አንተ በመጣህበት ተመሳሳይ የመጣ በጭራሽ የለም ጠላት የሚያፈራ ቢሆን እንጂ ቀኑን ካደረሰኝ ሁነኛ እገዛን ባገዝኩህ ነበር።” ወረቀት ግን ብዙም ሣይቆይ ሞተ፣ ወህይም ለተወሰኑ ጊዜያት ተቋረጠ።

ቡኻሪ ከጃቢር ኢብኑ አብደላህ (ረ.ዐ) እንደዘገበው ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ስለወህይ መቋረጥ ሲናገሩ

بينما أنا أمشى إذ سمعت صوتاً من السماء فرفعت بصري، فإذا الملك الذي جاءني بحراء جالس على كرسي بين السماء والأرض فرعبت منه، فرجعت فقلت : زملوني زملوني فأنزل الله : يا أيها المدثر قم فأنذر – إلى قوله : والرجز فاهجر، فحمى الوحي وتتابع

“በመራመድ ላይ ሳለሁ ከሠማይ ድምጽ ሠማሁና አይኔን ቀና ሳደርግ ያ ሂራ ዋሻ ውስጥ የመጣብኝ መላኢካ በምድርና ሰማይ መካከል በሆነ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። በጣም ደነገጥኩኝ፤ በፍጥነትም ተመልሼ ‘አከናንቡኝ! አከናንቡኝ!’ አልኩ። አላህም ‘አንተ (ልብስህን) ደራቢው ሆይ። ተነስ አስጠንቅቅም። ጌታህንም አክብር። ልብስህም አጥራ። ጣኦትንም ራቅ። ማብዛትንም የምትፈልግ ኾነህ (በረከትን) አትለግስ። ለጌታህም ታገስ።’ የሚለውን አንቀድ አወረደ።”

ቀጥሎም ወሕይ ተቋረጠ፤ ወህይ የተቋረጠበትን የግዜ ቆይታ በተመለከተ የተለያዩ ንግግሮች የተሠነዘሩ ሲሆን ትክክለኛው ለተወሰኑ ቀናት ነበር የሚለው ነው። ኢብኑ ሠዕድ ከኢብኑ ዐባስ ያወሩት ይህን የሚደግፍ ነው (ረሂቀል መኽቱም፣ ሠፊዩ ረህማን ሙባረክ ፋሪ)።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here