ሲራ ክፍል 6 – ሚስጥራዊው የዳእዋ ሂደት

0
4822

ነብያችን (ሠ.ዐ.ወ) ለአላህ ትእዛዝ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል፤ አላህን አንድ ብቻ አድርጎ ማምለክና ጣኦታትን ወደ መተው መጣራትን ተያያዙት። ነገር ግን ቁረይሾች ለጣኦቶቻቸው እና ለሽርክ አምልኮቶቻቸው ካላቸው ጭፍን ታማኝነትና ወገንተኝነት አንጻር ጥሪው ድንገተኛ እናዳይሆንባቸው በመስጋት ዳዕዋውን በሚስጥር ያካሂዱ ነበር። በቁረይሾች መቀማመጫ አደባባዮች በግልፅ ዳዕዋ አያደርጉምም ነበር። በጣም የሚቀርባቸው ዘመድ ወይም ከዚህ በፊት ለሚያውቁት ሰው ካልሆነ በስተቀር ጥሪያቸውን አያደርጉለትም ነበር።

የመጀመሪያዎቹ መጀመሪያዎች

መጀመሪያ ወደ ኢስላም ከገቡት ውስጥ፤ ኸዲጃ (ረ.ዓ)፣ ዐሊይ ኢብኑ አቡጧሊብ የነብያችን (ሠ.ዐ.ወ) ያሳደጉትና ኻዲማቸው (አገልጋይ) የነበረው ዘይድ ኢበኑ ሐሪሳ፣ አቡበክር ኢብኑ አቢቁሀፋ፣ እና አቡበክር ሲዲቅ ወደ ኢስላም የጠሯቸው ዑስማን ኢብኑ ዐፋን፣ ዙበይር ኢብኑል ዐዋም፣ ዐብድረህማን ኢብኑ ዐውፍ፣ ሰእድ ኢብኑ አቢወቃስ … እንዲሁም ሌሎችም ይጠቀሱ ነበር።

የተርቢያ ስብስብ በአርቀም ቤት

እነዚህ ሰሀቦች ከነብያችን ጋ በሚስጢር ይገናኙ ነበር። አንድኛቸው መስገድ አልያም ኢባዳ ማድረግ ሲፈልግ ከቁረይሾች እይታ ለመደበቅ መካ ውስጥ ከሚገኙ ገደላ ገደሎች ወደ አንዱ ይሄዱ ነበር። ወደ ኢስላም የሚገቡት ወንድና ሴቶች ቁጥር ከሰላሳ መብለጡን የተመለከቱት ነቢይ ከእነርሱ መካከል የአርቀም ኢብኑ አቢ አርቀምን ቤት በመምረጥ እዚያ እየተገናኙ የዳእዋውን ጉዳይ ያስተምሯቸውና ተርቢያን ይሰጧቸው ገቡ። በዚህን ወቅት ዳዕዋው ደርሷቸው ወደ ኢስላም የገቡ ሰዎች ቁጥር አርባ አካባቢ ይደርስ ነበር። ታዲያ አብዛኞቹ ድሆችና ባሪያዎች በቁረይሽም ዘንድ ቦታ የማይሰጣቸው ግልሰቦች ነበሩ።

የዳእዋው ድብቅነት ለዳዕዋው ችግርን ከመስጋት እንጂ ለነፍስ ከመፍራት የመነጨ አልነበረም። ነብያችን (ሠ.ዐ.ወ) በመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት የድብቅ ዳዕዋን የመረጡበት ምክንያት ለነፍስ ጉዳትን ከመስጋት የመነጨ አልነበረም። ዳእዋውን ከጅምሩ ለሁሉም አይነት ሰዎች ግልጽ እንዲያደርጉት ከጌታቸው ትእዛዝ ቢመጣ ኖሮ ከፊታቸው ሞት ቢጠብቃቸው እንኳን ለመፈጸም ምንም ሰዓት አያባክኑም ነበር።

ነገር ግን የመጀመሪዎቹን የዳዕዋ ግዜያት ዳዕዋውን በድብቅና በሚስጥር ያምኑልኛል እንዲሁም ዳዕዋውን ይቀበሉኛል ብለው ለጠረጠሯቸው ሰዎች ብቻ እንዲያደርጉ አላህ አሳወቃቸው። ይህም የሆነው በአላህ ላይ የሚኖረን መሰረታዊ ኢማን እንዳይበረዝና ቀጥሎ የሚመጡ ዳዒዎች በአላህ ላይ ብቻ መተማመን እና መታገዝ ላይ እንዲያተኩሩ ትምህርት እዲሆን ነው።

ከዚህ በመነሳት በየትኛውም ዘመን የሚኖሩ የኢስላማዊ ዳዕዋ ባለቤቶች ዳእዋቸውን የሚያደርጉበትን ስልት (በሚስጢር ወይስ በግልፅ የሚለውን) ካሉበት ዘመን ሁኔታና ተጨባጭ አንፃር መወሰን ይችላሉ ማለት ነው። ይህ የኢስላም ሸሪዐ ገር ከመሆኑ አንፃር የተቀመጠ ሲሆን ስልቱ የነብያችን (ሠ.ዐ.ወ) ሲራ ላይ የተመረኮዘ እንዲሁም ከላይ የተጠቀሱትን አራት ሂደቶችን መሰረት ያደረገ በዋነኝነት የሙስሊሞችና የዳእዋውን መስላሀ (ጥቅም) ከግምት ያስገባ መሆኑ ነው።

ለዚህም ነው አብዛኛዎቹ የፊቅህ ምሁራን፤ ሙስሊሞች በቁጥር ሲያንሱ ወይም በዝግጅት ደካማ ሲሆኑ፣ ጠላቶቻቸው ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ መፍጠር ሳይችሉ እንሸነፋለን ወይም ጠላቶቻችን ይጎዱናል ብለው ከጠረጠሩ ነፍስን የመጠበቅ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የተስማሙት። ምክንያቱም ዲንን ጠብቆ ለማቆየት በየትኛውም መልኩ ህይወትን ጠብቆ ማቆየት የግድ ይለናልና።

እውነታው ላይ ላዩን ስንመለከተው ለነፍስ ቅድሚያ መስጠት ይመስላል። ነገር ግን ጉዳዩን በጥልቀት ከተመለከትነው በተጨባጭ ዲንን ጠብቆ ማቆየት ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህ እይነት የሙስሊሞችን ነፍስ በሰላም ጠብቆ ማቆየት፤ ወደፊት እንዲጓዙና ሌሎች ክፍት የሆኑ ሜዳዎች (የዳእዋ ዘርፍና ስልቶች) በተገኙ ጊዜ ትግል እንዲያደርጉ እድል ስለሚሰጣቸው ለዲኑ ቅድሚያ ተሰጥቷል እንላለን። ይህ ሳይሆን ቢቀርና ሙስሊሞች ቢጠፉ በዲኑ ላይ የመጣ ጉዳት ተደርጎ ይወሰዳል።

ደካሞችና ድሃዎች ቀድመው ለምን ተቀበሉ?

የሲራ ድርሳናት እንደሚገልፁልን በመጀመሪያዎቹ የዳእዋ ወቅቶች ወደ ኢስላም የገቡት ሰዎች በአብዛኛው ድሆች ደካሞችና ባሪያዎች የተቀላቀሉበት ነበር። ታዲያ ከዚህ ጀርባ ያለው ጥበብ ምንድን ነው? ኢስላማዊ መንግስቱስ ሲመሰረት በነዚህ ሰዎች መሰረት ላይ የመገንባቱ ሚስጥርስ ምንድንነው?

መልሱ፡- ይህ የነቢያት ዳዕዋ የመጀመሪያው ሂደት የሚያሰተናግደው ተፈጥሮኣዊ ክስተት ነው። ሚስጥሩም፤ አላህ ሁሉንም መልእክተኞች ሲልካቸው ከሰው ልጅ አገዛዝና የስልጣን ተፅእኖ ወደ አላህ ብቸኛ አስተዳደርና ስልጣን ነፃ ያወጡ ዘንድ ነው። ራሳቸውን አማልክትና ፈላጭ ቆራጭ አድርገው የበላይ ነን የሚሉትን አምባገነኖች ምንነት የሚያዋርድና የሚያንኮታኩት ጥሪ ነው።

ይህም ከደካሞች፣ ከተዋረዱ እና ከባሪያዎች ሁኔታ ጋር ስለሚገጣጠም ለጥሪው አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ በአፀፋው እነዚያ አምለክ ነን አስተዳዳሪ ነን ባዮች ከመኩራራትና ከጥላቻ በዘለለ ለኢስላማዊው ጥሪ መሰናክል ሆነው ይቆማሉ።

ይህ እውነታ የበለጠ ግልፅ እንዲሆንልህ በፋርሱ ጦር መሪ ሩስቱም እና በሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ ጦር ተራ ወታደር ረቢዕ ኢብን ዓምር መካከል በቃዲሲያ ጦርነት ወቅት የተካሄደውን ንግግር ተመልከት። ሩስቱም እንዲህ አለው “ምንድን ነው እኛን እንድትዋጉን እና ሀገራችንን ዘልቃችሁ እንደትመጡ ያደረጋችሁ?” ረቢዕ ኢብኑ አሚርም “እኛ የመጣነው በፍላጎት ሰዎችን ከሰዎች ባርነት ወደ አላህን ብቻ ወደ ማምለክ ነፃነት ለማምጣት ነው” አለው፤ ከዚያም ከቀኝ እና ከግራ ለሩስቱም ሩኩዕ ያደረጉ ሰዎችን ሰልፋ ተመለከተና በመገረም “በእርግጥ ከዚህ በፊት ስለናንተ ህልሞች ይደርሱን ነበር፤ አሁን በተጨባጭ ሳያችሁ ግን ከናንተ በታች ቂል የሆነን ህዝብ አልተመለከትኩም። እኛ ሙስሊሞች እኮ ከፊላችን ከፊሉን ባሪያ አደርጎ እኮ አይገዛውም! እናንተም እንደኛ በመካከላችሁ በመልካም እንደምትውሉ ነበር የማስበው ምናልባትም በጣም ጥሩ ከሰራችሁት ነገር አንዳችሁ የአንዳችሁ ጌታ (አምላክ) እንደሆናችሁ እየነገራችሁኝ መሆኑ ሊሆን ይችላል ……”

ይህኔ ደካሞቹ እርስበርሳቸው መጠቃቀስና ማጉረምረም ጀመሩ “ወላሂ ይህ አረብ እውነት ተናገረ” ነገር ግን መሪዎቹ እና አስተዳዳሪዎቹ የረቢዕን ንግግር ውስጣዊ ማንነታቸውን ያፈራረሰ መብረቅ ሆነባቸው። እርስበርስም “በእርግጥ ረቢዕ የወረወረው ንግግር ባሮቻችንን ወደ እርሱ ሳይጎትታቸው (ሳያዘናብላቸው) የሚቀር አይደለም” አሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here