ለዓለማት እዝነት የተላኩት ነብያችን (ክፍል 6)

0
3106

ለምን አላመኑም?

አይሁዶችና ክርስትያኖች ነቢዩ ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን ቢያውቁም ጥላቻና ምቀኝነት በርሳቸው ከማመን አቀቧቸው። ነቢዩን የማወቃቸው መጠን እጅግ ሲበዛ ጉልህና ምንም ዓይነት መድበስበስ የሌለበት ከመሆኑ የተነሳ እርሳቸው የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን ለማወቅ የአንድ ጊዜ እይታ ብቻ በቂያቸው ነበር። ምክንያቱም አካላዊ ገጽታቸውንም ሆነ ባህሪያቸውን በሚገባ ያውቁ ነበርና። አላህ ይህን እውነታ እንዲህ ሲል አረጋግጧል፡-

الَّذِينَ آتَيْنَاهُمُ الْكِتَابَ يَعْرِفُونَهُ كَمَا يَعْرِفُونَ أَبْنَاءَهُمْ وَإِنَّ فَرِيقًا مِّنْهُمْ لَيَكْتُمُونَ الْحَقَّ وَهُمْ يَعْلَمُونَ

“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል። ከነሱም የተለዩ ክፍሎች እነርሱ የሚያወቁ ሲኾኑ እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ።” (አል-በቀራህ 2፤ 146)

አላህ በዚህ አንቀጽ ውስጥ የነቢዩ ሙሐመድን ስም አላወሳም። ተውላጠ ስም በመጠቀም ብቻ ተወስኗል። ምክንያቱም አይሁዶችም ክርስትያኖች ነቢዩን እጅግ ከማወቃቸው የተነሳ ስማቸውን መጥቀስ አላስፈለገም። “እርሱ” መባላቸው ብቻ በቂ ነው። ተውላጠ ስማቸው መዘከሩ በተውራት እና በኢንጅል የተበሰሩት ነብይ መሆናቸውን በጉልህ ያሳያል። ይህም ነብይ አህመድ ወይም ሙሐመድ መሆናቸው ከመጽሐፉ ሰዎች ዘንድ ይታወቃል። ስለዚህም ልጆቻቸውን የሚያውቋቸውን ያህል ነቢዩንም ያውቋቸዋል።

ዑመር ቢን አልኸጧብ ለአብደላህ ቢን ሰላም፡- “ሙሐመድን የልጅህን ያህል ታውቃቸዋለህን?” ሲሉ ጠየቁት። “ከልጄም በላይ አውቃቸዋለሁ።” የሰማዩ ታማኝ ለምድሩ ታማኝ ባወረደው የርሳቸውን ባህሪ የሚዘረዝር መልእክት አማካይነት አወቅኳቸው። ልጄን በተመለከተ ግን እናቱ ከማን እንደጸነሰችው በእርግጠኝነት አላውቅም።” ሲል መለሰ። (ሙኽተሰር ተፍሲር ቢን ከሲር-ሷቡኒ 1/140፣ ዱረል መንሱር ሱዩጢ 1/357)

1. ቅናትና ምቀኝነት

አዎ፣ ነቢዩን በትክክል ያውቋቸዋል። ግና ማወቅ አንድ ነገር ነው። በርሳቸው ማመን ደግሞ ሌላ ነገር። ያውቋቸው ነበር። ግና በርሳቸው የማመን ጉዳይ በእነርሱ እጅ አልነበረም። ቅናታቸውና ምቀኝነታቸው በርሳቸው እንዳያምኑ እንቅፋት ሆነባቸው፡-

وَلَمَّا جَاءَهُمْ كِتَابٌ مِّنْ عِندِ اللَّهِ مُصَدِّقٌ لِّمَا مَعَهُمْ وَكَانُوا مِن قَبْلُ يَسْتَفْتِحُونَ عَلَى الَّذِينَ كَفَرُوا فَلَمَّا جَاءَهُم مَّا عَرَفُوا كَفَرُوا بِهِ فَلَعْنَةُ اللَّهِ عَلَى الْكَافِرِينَ

“ከነሱም ጋር ያለውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የኾነ መጽሐፍ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ (ከመምጣቱ) በፊት በነዚያ በካዱት ላይ ይረዱበት የነበሩ ሲኾኑ ያወቁት ነገር በመጣላቸው ጊዜ በርሱ ካዱ። የአላህም ርግማን በከሓዲዎች ላይ ይኹን።” (አል-በቀራህ 2፤ 89)

አላህ በዚህ አንቀጽ ያለማመናቸውን እውነተኛ ምክንያት ያብራራል። ክህደታቸው ዋነኛ ሰበብ ነቢዩ አይሁድ አለመሆናቸው ብቻ ነው። ከአይሁድ የተገኙ ቢሆኑ ኖሮ ምላሻቸው ያለ ጥርጥር የተለየ በሆነ ነበር። የዚህ አባባል ማስረጃው አብደላህ ቢን ሰላም ከሰለመ በኋላ ለመልእክተኛው፡-

“የአላህ መልእክተኛ ሆይ፣ አይሁዶች ቃል አባይ ሕዝቦች ናቸው። ስለኔ ሳይጠይቋቸው በፊት መስለሜን ካወቁ ከርስዎ ፊት ስሜን በሐሰት ያጠለሹታል።” አላቸው። አይሁዶች መጡ። አብደላህም ወደ ውስጥ ገባ። የአላህ መልእክተኛም “አብደላህ ቢን ሰላም ከናንተ ዘንድ እንዴት ያለ ሰው ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው። “ከማንኛችንም በላይ አዋቂና የአዋቂያችን ልጅ ነው። ከማንኛችንም በላይ ምርጥና የምርጣችን ልጅ ነው።” አሉ። የአላህ መልእክተኛም “አብደላህ ቢሰልም ምን ይሰማችኋል?” ሲሉ ጠየቋቸው። “አላህ ከዚህ ጥፋት ይጠብቀው” አሉ። አብደላህ ወደነርሱ መጣና፡- “ከአላህ ሌላ አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ” አለ። እነርሱም፡- “ከማንኛችንም በላይ ክፉና የክፏችን ልጅ ነው።” አሉ። (ቡኻሪና አህመድ)

ይህ ክስተት አይሁዶች የአላህን መልእክተኛ በሚገባ ያውቋቸው እንደነበር ያመለክታል። ሆኖም ግን ትእቢታቸው እምነትን ከለከላቸው።

በዚህ ረገድ ሰልማኑል ፋሪስ ብቻውን ቋሚ ምስክር ሊሆን ይበቃል። በመጀመሪያ መጁሳዊ ነበር። ግና እውነተኛውን ሐይማኖት ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉትና ፍላጎት ነበረው። ወደ ክርስትና ሐይማኖት ገባ። በቤተ ክርስትያንም ውስጥ ተቀመጠ። በቤተ ክርስትያን ውስጥ የሚገኝ ዋነኛው መነኩሴ ሊሞት ሲል ሌላ መነኩሴ ይጠቁመው ዘንድ ጠየቀው። እርሱም አመለከተው። በዚህ መልኩ ከአንድ መነኩሴ ወደሌላው እየተዘዋወረ ቆየ። ከብዙዎቹ ጋር ተጎዳኘ። በመጨረሻም ከሕይወቱ የመጨረሻዎች ደቂቃዎች ላይ የሚገኝን መነኩሴ ተመሳሳይ ጥያቄ ጠየቀው። መነኩሴውም እንዲህ አለው፡-

“የኛን ሐይማኖት የሚከተል ሌላ ሰው አላውቅም። ግና የአንድ ነብይ መገለጫ ዘመን ደርሷል። የኢብራሂምን ሐይማኖት ይዞ ይመጣል። በአረብ ምድርም ይነሳል። የሚሰደደው በሁለት ጥቋቁር ድንጋዮች መሐል ወዳለች ከተማ ነው። በነዚህ ድንጋዮች መሐል ዘንባባዎች አሏት። ይህ ነብይ ግልጽ ምልክቶች አሉት። ስጦታን ይመገባል። ምጽዋትን ግን አይመገብም። በትከሻዎቹ መሐል የነብይነት ማህተም ይገኛል። ወደዚያች ሐገር መሄድ ከቻልክ ሂድ።” ሰልማን ከዚህ በኋላ የሆነውን እንዲህ ሲል ይተርካል፡-

ሰውየው ሞተ። ለተወሰነ ጊዜ እዚያው ቆየሁ። ከኪላብ ጎሳ የሆኑ ነጋዴዎች እኔ ባለሁበት ቀዬ አለፉ።(ኪላብ የዓረብ ጎሳ ነው- ተርጓሚው)። “ወደ አረብ ምድር ውሰዱኝ። ከብቶቼንና ፍየሎቼን እሰጣችኋለሁ።” አልኳቸው። “እሽ” አሉኝ። ሰጠኋቸው። ከነርሱ ጋር ይዘውኝ ተጓዙ። ዋደል ቁራ ከተባለ ቦታ ስንደርስ በደል ፈጸሙብኝ። ለአንድ የአይሁድ ሰው በባርነት ሸጡኝ። ከርሱ ዘንድም ተቀመጥኩ። የዘንባባውን ዛፍ ተመለከትኩ። ያ መነኩሴ የነገረኝ አገር ይህ እንደሆነ ተስፋ አደረግኩ። ግና እርግጠኛ አልነበርኩም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ የበኒ ቁረይዟ ጎሳ የሆነ የአሳዳሪዬ የአጎት ልጅ ከመዲና መጣና ከአሳዳሪዬ ገዝቶ ወሰደኝ። ወደ መዲና ተጓዝን። ወዲያውኑ ሳያት ያ መነኩሴ የነገረኝ ቀዬ እንደሆነች አወቅኩ። ከርሷ ውስጥም እኖር ጀመር። የአላህ መልእክተኛ በመካ ተነሱ። ለተወሰኑ ዓመታትም እዚያው ቆዩ። የባርነት ስራ ስለሚበዛብኝ በነዚህ አመታት ውስጥ ስለርሳቸው አልሰማሁም። ወደ መዲናም ተሰደዱ። አንድ ቀን እኔ ከአሳዳሪዬ ዘምባባ ዛፍ ላይ አሳዳሪዬ ደግሞ ከስር ተቀምጦ እያለን የአጎቱ ልጅ መጣና እንዲህ አለ፡- “እገሌ ሆይ፣ በኒ ቀይላዎችን አላህ ይጋደላቸው። ከመካ ከመጣው ሰው ዘንድ ተሰብስበዋል። ነብይ ነኝ ይላል።” አለ።

ይህን ስሰማ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ። ከአሳዳሪዬ ላይ እንዳልወድቅ እስክፈራ ድረስ። ከዛፏ ወረኁደኩና የአሳዳሪዬን የአጎት ልጅ “ምን አልክ?” አልኩት። አሳዳሪዬ ተቆጣ። በጥፊም አጮለኝ። “ምን ጥልቅ አደረገህ? ስራህን ስራ” አለኝ። “እውነትህን ነው። አያገባኝም። የተናገረውን ለማረጋገጥ ብቻ ነው” አልኩት።

ጥቂት ተምሮች ሰብስቤ ነበር። ምሽት ላይ እርሱን ይዥ ወደ አላህ መልእክተኛ ሄድኩ። ቁባእ ውስጥ ነበሩ። ወደርሳቸው ገባሁ። “አንተ ደግ ሰው እንደሆንክ ሰምቻለሁ። ባይተዋር እና እገዛ የሚያስፈልጋቸው ባልንጀሮች አሉህ። ይህ ለምጽዋት ያዘጋጀሁት ተምር ነው። ለእናንተ ይበልጥ ተገቢ ሆኖ ስላገኘሁት አምጥቸዋለሁ” አልኳቸውና አቀረብኩላቸው። የአላህ መልእክተኛም ለባልደረቦቻቸው “ብሉ” አሉ። እርሳቸው ግን እጃቸውን ሰበሰቡ። አልተመገቡም። በውስጤም “አንዷ ምልክት ተረጋገጠች” አልኩ። ከዚያም ወጥቼ ሄድኩ። ተምሮችንም ሰበሰብኩ። ነቢዩ ወደ መዲና ተዛውረው ነበር። ከርሳቸው ዘንድ ሄድኩና “ምጽዋት እንደማትመገብ አይቻለሁ። ይህ ላንተ ስጦታ ያዘጋጀሁት ነው” አልኳቸው። ከርሱ ተመገቡለት። ባልደረቦቻቸውም አብረዋቸው ተመገቡ። በውስጤም፡- “ሁለተኛው ምልክት ተረጋገጠ” አልኩ። ከዚያም የአላህ መልእክተኛ የአንድ ባልንጀራቸውን በድን ለመሸኘት በቂእ አልገርቀድ በተባለው የመቃብር ስፍራ ላይ እያሉ ወደርሳቸው ዘንድ መጣሁ። ሁለት ኩታዎችን ለብሻለሁ። ሰላምታ አቀረብኩላቸው። ከጀርባቸው ላይ ያ መነኩሴ የነገረኝ የነብይነት ማህተም ይኖር እንደሁ ለማረጋገጥ ወደ ጀርባቸው በኩል ዞርኩ። የአላህ መልእክተኛ ሲያዩኝ ማረጋገጥ የፈለግኩት አንዳች ነገር መኖሩን ተገነዘቡ። ኩታቸውንም ከጀርባቸው አነሱ። ምልክቱን አየሁት። አወቅኩትም። ከርሱ ላይ ተደፋሁና እያለቀስኩ ሳምኩት። የአላህ መልእክተኛም “ወደ ፊት ለፊቴ ና” አሉኝ። ከፊት ለፊታቸው ተቀመጥኩ። ታሪኬንም ነገርኳቸው። ባልደረቦቻቸው ይህን ታሪክ መስማታቸው የአላህን መልእክተኛ አስደሰተ። (ሲረቱ ቢን ሐሺም 1/228-234)

2. የውድድር መንፈስ

ሙጊረት ቢን ሸእባህ እንዲህ ሲል አውግቷል፡-

የአላህን መልእክተኛ ባወቅኩበት የመጀመሪያ ቀን እኔ እና አቡ ጀህል በአንድ የመካ ጎዳና ላይ በመጓዝ ላይ እያለን የአላህን መልእክተኛ አገኘናቸው። እርሳቸውም ለአቡ ጀህል፡- “አቡል ሐከም ሆይ፣ ወደ አላህና ወደ መልእክተኛው ላመላክትህን? ወደ አላህ እጠራሃለሁ” አሉት። አቡ ጀህልም፡- “ሙሐመድ ሆይ፣ አማልክቶቻችንን ከመሳደብ አትታቀብምን? መልእክትህን ማድረስህን ብቻ እንድንመሰክር አይደል የምትፈልገው? ማድረስህን እንመሰክራለን። በአላህ እምላለሁ፣ የምትለው ነገር እውነት መሆኑን ባውቅ ኖሮ እከተልህ ነበር” አለ። የአላህ መልእክተኛ ከአጠገባችን ሄዱ። አቡ ጀህል ወደኔ ዞረና፡- “በአላህ እምላለሁ፣ የሚናገረው እውነት መሆኑን አውቃለሁ። እንዳልቀበለውና እንዳልከተለው ያቀበኝ አንድ ነገር ብቻ ነው። በኒ ቁሱዮች፡- ከኛ ወገን የካእባ ጠባቂ አለ ሲሉ እኛም አለን አልናቸው። ሐጃጆችን የሚያጠጣ አለን ሲሉ፣ እኛም አለን አልናቸው። የምክር ቤት አባል አለን ሲሉ እኛም አለን አልናቸው። አርማ ያዥ አለን ሲሉ እኛም አለን አልናቸው። እነርሱ ሲያበሉ አበላን። ፈረሶቻችን እንኳ ሳይቀዳደሙ ነው የሚጓዙት። ከኛ ወገን የሆነ ነብይ አለን ሲሉ እኛ ምን ልንል ነው? በአላህ እምላለሁ በዚህ ሰው አላምንም” አለ። (አል ቢዳየቱ ወኒሐያ በኢብን ከሲር 3/83፣ ከንዘል ዑማል 14/39-40)

በሌላ ዘገባ ደግሞ አቡ ጀህል እንዲህ ብሏል፡-

“እኛ እና በኒ አብዱ መናፎች በክብር ተፎካከርን። እነርሱ ሲመግቡ እኛም መገብን። ሲሰጡ ሰጠን። ሲረዱ ረዳን። በግልቢያ ላይ ስንገናኝ እንኳ አንቀዳደምም። ፈረሶቻችን በአንድ ላይ ተቆራኝተው የታሰሩ ነው የሚመስለው። ከሰማይ ራእይ የሚገለጽለት ነብይ አለን ሲሉ እኛ ይህን ከየት ልናመጣ ነው? በአላህ እምላለሁ፣ በዚህ ሰው መቼም ቢሆን አናምንም። አንቀበለውም።” (አል ቢዳየቱ ወኒሐያ- ኢብን ከሲር 3/83)

የቁረይሽ ባላባቶች ስብሰባ ተቀመጡ። ዑትበት ቢን ረቢዓህ የአላህን መልእክተኛ ከጥሪያቸው ይታቀቡ ዘንድ እንዲያናግራቸው ወሰኑ። ዑትባህ ከቁረይሽ አዋቂዎች መካከል አንዱ ነበር። ከአዛውንቶቻቸው መካከልም ነው። የቋንቋ ክሕሎቱ የመጠቀ ነው። ባለሐብትም ነበር። ወደ አላህ መልእክተኛ ዘንድ በመሄድ በአመክንዮ ስልት ሊያሳምናቸው ሞከረ። “ሙሐመድ ሆይ፣ ካንተ እና ከአብደላህ ማን ይበልጣል?” አላቸው። መልእክተኛው መልስ አልሰጡትም። “ካንተና ከአብዱል ሙጦሊብ ማን ይበልጣል?” አላቸው። አሁንም ዝም አሉ። በእርግጥም ዝምታ ከቃል የተሻለ ምላሽ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። “እነዚህ የጠቀስኳቸው ሰዎች ካንተ እንደሚበልጡ ካወቅክ ሁሉም ጣኦታትን አምልክዋል። እኔ እበልጣለሁ የምትል ከሆነ ደግሞ ተናገር እንስማህ” አለ። መልእክተኛውም፡- “አባ ወሊድ ሆይ፣ ሐሳብህን ጨረስክን?” አሉት። “አዎ” አላቸው። ከፉሲለት ምእራፍ ውስጥ የሚከተሉትን አናቅጽ አነበቡለት፡-

حم ﴿١﴾ تَنزِيلٌ مِّنَ الرَّحْمَٰنِ الرَّحِيمِ ﴿٢﴾ كِتَابٌ فُصِّلَتْ آيَاتُهُ قُرْآنًا عَرَبِيًّا لِّقَوْمٍ يَعْلَمُونَ ﴿٣﴾ بَشِيرًا وَنَذِيرًا فَأَعْرَضَ أَكْثَرُهُمْ فَهُمْ لَا يَسْمَعُونَ ﴿٤﴾ وَقَالُوا قُلُوبُنَا فِي أَكِنَّةٍ مِّمَّا تَدْعُونَا إِلَيْهِ وَفِي آذَانِنَا وَقْرٌ وَمِن بَيْنِنَا وَبَيْنِكَ حِجَابٌ فَاعْمَلْ إِنَّنَا عَامِلُونَ ﴿٥﴾ قُلْ إِنَّمَا أَنَا بَشَرٌ مِّثْلُكُمْ يُوحَىٰ إِلَيَّ أَنَّمَا إِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌ وَاحِدٌ فَاسْتَقِيمُوا إِلَيْهِ وَاسْتَغْفِرُوهُ وَوَيْلٌ لِّلْمُشْرِكِينَ﴿٦﴾ الَّذِينَ لَا يُؤْتُونَ الزَّكَاةَ وَهُم بِالْآخِرَةِ هُمْ كَافِرُونَ ﴿٧﴾ إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ لَهُمْ أَجْرٌ غَيْرُ مَمْنُونٍ﴿٨﴾ قُلْ أَئِنَّكُمْ لَتَكْفُرُونَ بِالَّذِي خَلَقَ الْأَرْضَ فِي يَوْمَيْنِ وَتَجْعَلُونَ لَهُ أَندَادًا ذَٰلِكَ رَبُّ الْعَالَمِينَ ﴿٩﴾ وَجَعَلَ فِيهَا رَوَاسِيَ مِن فَوْقِهَا وَبَارَكَ فِيهَا وَقَدَّرَ فِيهَا أَقْوَاتَهَا فِي أَرْبَعَةِ أَيَّامٍ سَوَاءً لِّلسَّائِلِينَ ﴿١٠﴾ ثُمَّ اسْتَوَىٰ إِلَى السَّمَاءِ وَهِيَ دُخَانٌ فَقَالَ لَهَا وَلِلْأَرْضِ ائْتِيَا طَوْعًا أَوْ كَرْهًا قَالَتَا أَتَيْنَا طَائِعِينَ ﴿١١﴾ فَقَضَاهُنَّ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ فِي يَوْمَيْنِ وَأَوْحَىٰ فِي كُلِّ سَمَاءٍ أَمْرَهَا وَزَيَّنَّا السَّمَاءَ الدُّنْيَا بِمَصَابِيحَ وَحِفْظًا ذَٰلِكَ تَقْدِيرُ الْعَزِيزِ الْعَلِيمِ ﴿١٢﴾ فَإِنْ أَعْرَضُوا فَقُلْ أَنذَرْتُكُمْ صَاعِقَةً مِّثْلَ صَاعِقَةِ عَادٍ وَثَمُودَ

“ሐ.መ.(ሓ ሚም)። (ይህ ቁርኣን) እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ ከሆነው (አላህ) የተወረደ ነው። አንቀጾቹ የተብራሩ የኾነ መጽሐፍ ነው። ዐረብኛ ቁርኣን ሲኾን ለሚያውቁ ሕዝቦች (የተብራራ) ነው። አብሳሪና አስፈራሪ ሲኾን (ተወረደ)። አብዛኛዎቻቸውም ተዉት። እነርሱም አይሰሙም። አሉም ‘ልቦቻችን ከእዚያ ወደእርሱ ከምትጠራን እምነት በመሸፈኛዎች ውስጥ ናቸው። በጆሮዎቻችንም ላይ ድንቁርና አልለ፤ በእኛና ባንተም መካከል ግርዶሽ አልለ። (በሃይማኖትህ) ሥስራም፤ እኛ ሠሪዎች ነንና።’ (እንዲህ) በላቸው ‘እኔ መሰላችሁ ሰው ብቻ ነኝ። አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ወደእርሱም ቀጥ በሉ ምሕረትንም ለምኑት ማለት ወደእኔ ይወረድልኛል። ለአጋሪዎቹም ወዮላቸው። ለእነዚያ ዘካን ለማይሰጡት እነርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም እነርሱ ከሓዲዎች ለኾኑት (ወዮላቸው)። እነዚያ ያመኑትና በጎ ሥራዎችን የሠሩት ለእነርሱ የማይቆረጥ ምንዳ አልላቸው። በላቸው ‘እናንተ በዚያ ምድርን በሁለት ቀኖች ውስጥ በፈጠረው አምላክ በእርግጥ ትክዳላችሁን? ለእርሱም ባለንጣዎችን ታደርጋላችሁን? ያ (ይህንን የሠራው) የዓለማት ጌታ ነው። በእርሷም ከበላይዋ የረጉ ጋራዎችን አደረገ። በእርሷም በረከትን አደረገ። በውስጧም ምግቦችዋን (ካለፉት ሁለት ቀኖች ጋር) በአራት ቀናት ውሰጥ ለጠያቂዎች ትክክል ሲኾኑ ወሰነ። ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ኾና ሳለች አሰበ። ለእርሷም ለምድርም ‘ወዳችሁም ኾነ ወይም ጠልታችሁ ኑ’ አላቸው። ‘ታዛዦች ኾነን መጣን’ አሉ። በሁለት ቀኖችም ውስጥ ሰባት ሰማያት አደረጋቸው። በሰማይቱም ሁሉ ነገሯን አዘጋጀ። ቅርቢቱንም ሰማይ በመብራቶች አጌጥን። (ከሰይጣናት) መጠበቅንም ጠበቅናት። ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው (ጌታ) ውሳኔ ነው። (ከእምነት) እንቢ ቢሉም እንደ ዓድና ሰሙድ መቅሰፍት ብጤ የኾነን መቅሰፍት አስጠነቅቃችኋለሁ’ በላቸው።” (ፉሲለት 41፤ 1-13)

የአላህ መልእክተኛ እዚህ አንቀጽ ላይ ሲደርሱ ዑትበት ወባ እንደያዘው ሰው ተንቀጠቀጠ። እጁንም ወደ አላህ መልእክተኛ አፍ በመላክ “ሙሐመድ ሆይ፣ በምታምንበት አምላክህ እለምንሐለሁ አቁም” ሲል ለመናቸው። ከዚያም ወደ ባልንጀሮቹ ተመለሰ። ከፊላቸውም ለከፊሎ፡- “በአላህ እንምላለን። አቡል ወሊድ በሄደበት ሁኔታ አይደለም የተመለሰው” አሉ። በተቀመጠ ጊዜም፡- “አቡል ወሊድ ሆይ፣ ምን ይዘህ መጣህ?” ሲሉ ጠየቁት። “አምሳያ የሌለው ንግግር ሰማሁ። ቅኔም ጥንቆላም አይደለም። ቁረይሾች ሆይ፣ ይህን ሰው ታዘዙት። ሐላፊነቱን እኔ እሸከማለሁ። ያሻውን ያድርግ ተውት። እንቅፋትም አትሁኑት። በአላህ እምላለሁ የሰማሁት ንግግር ወደፊት ትልቅ ዝና ይኖረዋል። አረቦች ካሸነፉት ያለ እናንተ ጣልቃ ገብነት የምትፈልጉት ነገር ተሳካ። እርሱ ካሸነፋቸውም ንግስናዉ ንግስናችሁ፣ ክብሩ ክብራችሁ በመሆኑ ከማንም በላይ በርሱ ስኬት እናንተ ደስተኞች ትሆናላችሁ።” አለ። “በአላህ እንምላለን፣ አቡል ወሊድ ሆይ፣ በአንደበቱ ድግምት አድርጎብሐል።” አሉት። “የኔ አስተያየት ይህ ነው። የመሰላችሁን አድርጉ” አላቸው።

3. ሌሎች ምክንያቶች

እነዚህ የአንድ ወይም የሁለት ግለሰቦች ምስክርነት ሳይሆኑ የብዙሐኑ እምነት ነበር። ግና የተለያዩ ምክንያቶች በርሱ እንዳያምኑ ያቅባቸው ነበር። ፍርሃት፣ ትእቢትና ምድራዊ ጸጋንና ክብርን መከጀል ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው። እውነተኛ ነብይ መሆናቸውን እያወቁ እነዚህ ሰበቦች በክህደት እንዲፀኑ አደረጋቸው። አላህ ለመልእክተኛው እንዲህ ብሏቸዋል፡-

قَدْ نَعْلَمُ إِنَّهُ لَيَحْزُنُكَ الَّذِي يَقُولُونَ فَإِنَّهُمْ لَا يُكَذِّبُونَكَ وَلَٰكِنَّ الظَّالِمِينَ بِآيَاتِ اللَّهِ يَجْحَدُونَ

“እነሆ ያ የሚሉህ ነገር እንደሚያሳዝንህ በእርግጥ እናውቃለን። እነርሱም (በልቦቻቸው) አያስተባብሉህም። ግን በዳዮቹ በአላህ አንቀጾች ይክዳሉ።” (አል-አንዓም ፤ 33)

ባንተ ላይ ብዙ የሐሰት ክሶችን ይደርታሉ። እነዚህ ክሶች አንተን ያሳዝናሉ። የአካላቸው ሸክም ክብደት ያሸነፋቸው፣ የስጋዊ ፍላጎት እስረኞች፣ የልምድና የባህል ምርኮኞች በሚነዙት ሐሰት አትዘን። እውነታውን ያውቁታል። ነብይ መሆንህን በእርግጠኝነት ተገንዝበዋል። አያስተባብሉህም። ምክንያቱም ባንተ ላይ አንድን ውሸት ማግኘት አይችሉምና። አንተ ከሐሰት የጸዳህ ነህ። ከአሁን ቀደም “አል-አሚን” (ታማኙ) በሚል ስም ጠርተውሃል። ቂልነታቸውን ተመልከት። ታማኝ ያሉትን ሰው አላመኑም። ይህም ሆኖ ስምህን ለማጥፋት ይደፍራሉ። ስለዚህ አትዘን።

አዎ፣ ማዘን ካለባቸው የዚህችንም ሆነ የመጭውን ዓለም በጎ ሕይወት በእጁ የዘረጋን ሰው በጠላትነት የፈረጁት እነርሱ ነው ማዘን የሚገባቸው። ካጠገባቸው ላለው ብርሃን ልቦናዎቻቸውን መክፈት የተሳናቸው ወገኖች ነው ሊያዝኑ የሚገባቸው።

ሌላ አድማስ

በርካታ እሴቶችን ያጣው የዘመኑ ሚስኪን ሰው ለነቢዩ ሙሐመድ ያለው እይታ ሊሆን ከሚገባው ፍጹም የተቃረነ ሆኗል። ነቢዩን በሰው ሚዛን መመዘን በእርግጥ ትልቅ ስህተት ነው። የማይቻልም ነው። ምክንያቱም አምሳያ የሌላቸው ስብእና ናቸውና። ፍጹም የተለየ በሆነ መንፈሳዊነት የከበሩ። ይህችን ዓለም እንደገና እንዲያደራጁ፣ ለሰው ልጅ አዲስ እና አንጸባራቂ አድማስ እንዲከፍቱ ተልከዋል። እናም እርሳቸውን መመዘን ከኛ አቅምና ችሎታ ውጭ ነው። በመሆኑም ሰዎች የቱንም ያህል እርሳቸውን ለመግለጽ ቢሞክሩም በተሟላ መልኩ አይገልጿቸውም። ከየትኛውም ሰው በላይ በቅርበት የሚያውቃቸው ሐሳን ቢን ሳቢት የሚከተለውን ስንኝ የቋጠረው ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት ነው፡-

ሙሐመድን በአንደበቴ አላወደስኩም።

አንደበቴን በርሱ አወደስኩ እንጅ።

(አልመሰሉ ሳኢር ኢብን አሲር 2/357፣ ሱብሁል አእላ ቀሽቀንዲ 2/231)

የርሳቸውን ስም ማንሳት የቋንቋን ውበት፣ የአንደበትን ርትዓት ይጨምራል። እርሳቸው ግን በኛ ገለጻ የሚያክሉት ውበት የለም። ፈረዝደቅ የተባለው ባለ ቅኔም ይህንኑ የሐሳን ሐሳብ ጥቂት የቃላት ለውጥ ብቻ በመጨመር ተቀኝቶታል። ታላቁ የዘመናችን ዓሊምና ሐሳብ አፍላቂ በዲኡ ዘማን ሰዒደ ነሩሲ ስለ ቁርአን ሲናገሩ ተመሳሳይ ገለጻ ተጠቅመዋል፡-

ቁርአንን በአንደበቴ አላወደስኩም

አንደበቴን በቁርአን አወደስኩ እንጅ።

(አል መክቱባት በዲዑ ዘማን ሰኢድ ነሩሲ ገጽ 477)

ይህ የቃላት መገጣጠም የመነጨው ከሐሳብና ከስሜት መገጣጠም ነው። ሁለቱም ከተመሳሳይ ምንጭ የተጎነጩ ስብእናዎች ናቸው። አንድን ነገር በተመሳሳይ ቋንቋ ገለጹት። አንዱ በጥቅሉ ያስቀመጠውን ሌላኛው አብራራው። አንዱ በስድ ንባብ የተነተነውን ሌላኛው በግጥም አሰፈረው። ሁሉም ግን የሚሽከረከሩት በተመሳሳይ መልእክት ዙሪያ ነው።

እኛም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞናል። የነቢዩ ሙሐመድ ተከታይ በመሆን ያገኘነውን ትልቅ ጸጋ መግለጽ እንሻለን። ይህን ትልቅ ጸጋ በመስጠት ወደር የሌለው ውለታ የዋለልንን አላህን ከልባችን ማመስገን እንፈልጋለን። አዎ፣ ይህ ትልቅ መለኮታዊ ጸጋ ነው። አላህ ጸጋውን ከሚሻው ሰው ላይ ያኖራል። ይህን ጸጋ መመዘን የሚችል ምድራዊ ሚዛን የለም። ዳርቻው የማይታወቅ ሰፊ ውቅያኖስ ነው። ግና ልናመልጠው የማንችለው ጥያቄ የግድ ይነሳብናል። ቀልባችን ይህን ታላቅ ስብእና ለማስተናገድ ዘወትር ክፍት ነውን? ስንቆም ስንቀመጥም፣ ስንበላም ስንጠጣም እርሳቸውን እናስታውሳለን? በየትኛውም እንቅስቃሴያችን ውስጥ የርሳቸው ትውስታ አብሮን አለን? በየትኛውም የሕይወት ጉዳያችን እርሳቸው ባሰመሩት መስመር እንጓዛለን? ለነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው ምላሽ አወንታዊ ከሆነ ምን ያህል የታደልን ነን! ይህ ማለት ምናባችን በርሳቸው ውብ ምስል ተሞልቷል ማለት ነው። ይህ ሲሆን የሙሐመዳዊው ሕብረት አካል እንሆናለን። የርሳቸውን አደብ እንማራለን። ስነ ምግባራቸውን እንወርሳለን። በርሳቸው ስነ ምግባር የታነፀ ስብስብ የዚህችን ዓለም ሚዛን የሚጠብቅ ሐይል ይሆናል። ወደዚህ ሚዛናዊነት እንድንደርስ የከለከለን አንድ ነገር ብቻ እንደሆነ አስባለሁ። እርሱም እኛ ገና ወደ ሙሐመዳዊው መንፈስ ደረጃ አለመዝለቃችን ነው።

ሙሐመድ በአላህ እይታ ስር የታነጸ ስብእና ናቸው። ሰው ሆነው መፈጠራቸውና ወደኛ መምጣታቸው ብቻ በራሱ ለኛ ትልቅ ደስታ ነው። ምክንያቱም ጀነት ራሷ፣ ፊርደውስ ራሷ በርሳቸው መምጣት ክብርን ይጨምራሉ። የኛ ትልቁ ስራ እርሳቸውን ማስተዋወቅ፣ ባህሪያቸውን መግለጽና ማብራራት ነው። የሰው ልጅ የሙእሚንነት ደረጃ ሊጎናጸፍ የሚችለው እርሳቸውን ሲያውቅና ፈለጋቸውን ሲከተል ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ ወስኛለሁ። ግና ከአሁን ቀደም እንደገለጽኩት ለዚህ ሐላፊነት ብቁ አይደለሁም። ቢሆንም የአቅሜን ያህል ማንነታቸውን ለመግለጽ እሞክራለሁ። በዚህ ረገድ የታጠቅኩት መሣሪያ ንጹህ ንያዬን ብቻ ነው።

የዚህ ሰው የአካል ክፍል ብሆን እያልኩ ለረዥም ጊዜያት ተመኝቻለሁ። ግና እያደር ይህ ምኞቴ ትልቅ እንደሆነ ተሰማኝ። ከአካሉ ጸጉሮች አንዷ ሆኜ በተፈጠርኩ ስልም ተመኘሁ። ይህን የተመኘሁት የአምላክ እዝነት መገለጫ ከሆነው ከዚህ ሰው ለመቅረብ በማሰብ ነው። እያደር ግን ይህ ምኞቴ እንደሚበዛብኝ አወቅኩ። እናም ምኞቴና ጉጉቴ ሁሉ በአንድ ነገር ላይ ብቻ አተኮረ። እርሱም ከተከታዮቻቸው መካከል አንዱ የመሆንን ጸጋ ማግኘት ነው። ምክንያቱም አላህ የርሳቸው ኡመት አባል የሆነን ሰው ከርሳቸው አማላጅነት አይነፍገውም። እንዲህ በማለት ከነርሱው ውሰጥ እንደሚያስገባኝ እመኛለሁ። “እነርሱ አብሯቸው የተቀመጠ እድለ ቢስ የማይይሆንባቸው ሰዎች ናቸው።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ይህን ታላቅና የመጠቀ ስብእና ይበልጥ ለማወቅ ወሰንኩ። በዚህ ትውልድ ልቦና ውስጥ ቅንጣት ታክል የነቢዩን ፍቅር ማስረጽ ከቻልኩ እድለኛ ነኝ። ግና አቅመ ደካማ ነኝና ምን አደርጋለሁ። ሐጅ ለማድረግ እንደነያች (እንደወሰነች) ጉንዳን ማለት ነኝ። ያን ረዥም መንገድ ችላ እንደማትጨርሰው ታውቃለች። ግና በሐጅ ጉዞ ላይ እያለች የምትሞት መሆኗ ያስደስታታል። የኔም ተስፋ በዚህ ጎዳና ውስጥ እያለሁ መሞት ነው።

የነብዩ ስብዕና ሌላ ዓለም፣ ሌላ ዳይሜንሽን ነው። የኛ ሐላፊነት ራሳችን ከዚያ ዓለም ሞገድ ጋር ማጣጣም ነው። ይህ ሲከናወን መግባባት፣ መነጋገር፣ መስማማት ይቻላል። በሞገድ መደማመጥ እንችላለን። ትእዛዝ ከርሳቸው ልቦና ይመነጫል። አመራሩን እርሳቸው ራሳቸው ይወስዱታል። እርሳቸው የሚመሩት ስብሰባና ማሕበረሰብ ብርቅ ማሕበረሰብ ነው። መላኢኮች በርሱ ይቀናሉ። ምንነቱን ለመግለጽ ቃላት አቅም ያንሳቸዋል።

ለአንዳንዶቹ ይህ ኑዛዜያችን ከተጨባጩ የራቀ ሊመስላቸው ይችላል። ለዚህም በጣም እናዝናለን። ነቢዩ በአካል እንጅ በመንፈስ አልሞቱም። ትምህርታቸው ከመሐከላችን በተሟላ መልኩ ይገኛል። ለአንዳንዶቻችን በሕልም ዓለም ይገለጣሉ። ኢማሙ ሱዩጢ በርካታ ጊዜ በሕልም አይተዋቸዋል። አውግተዋቸዋልም። ነቢዩ እንደሌሎች ተራ ሰዎች ሞቱ አይባሉም፤ እርሳቸውን ይቅርና ሸሂዶችን እንኳ ሞቱ እንዳንል ቁርአን ከልክሎናል። ሸሂዶች በደረጃ በጣም ያነሱ መሆናቸው ይታወቃል። ከአካል እስር ተላቅቀው ወደ መንፈሳዊው ዓለም መምጠቅ የቻሉ፣ የቀልብን ሕይወት የተጎናጸፉ ሰዎች ትላንትንም ዛሬንም ነገንም በአንድ ላይ መኖር ይችላሉ። ነቢዩም እንደዚሁ ናቸው። ትላንትን ኖረዋል። ዛሬም በትምህርታቸው ከኛ ጋር ናቸው። ወደፊትም ይኖራሉ። ስለዚህ ስብእናቸውን ለመረዳት መንፈሳችን፣ አእምሯችንና ልቦናችን መዘጋጀት አለበት። ይህም ሆኖ በተሟላ መልኩ ላንረዳቸው እንችላለን።

*****

________________

ምንጭ፡- ፈትሁላህ ጉለን- “ኑሩል ኻሊድ” /ዘልዓለማዊው ብርሃን/፤ ትርጉም በሐሰን ታጁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here