ለዓለማት እዝነት የተላኩት ነብያችን (ክፍል 5)

0
2559

ለረዥም ጊዜ የተጠበቀ እንግዳ

የነቢዩ ሙሐመድን መምጣት ይጠባበቁ የነበሩ ሰዎች አንድ ወይም ሁለት ብቻ አልነበሩም። በቁጥር እጅግ በርካታ ናቸው። ዘይድ ቢን ዓምር ቢን ኑፈይል ከነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ዘይድ ከአስሩ በጀነት የተበሰሩ ሶሐቦች መካከል አንዱ የሆነው የሰኢድ ቢን ዘይድ አባትና የዑመር ቢን አልኸጧብ የአጎት ልጅ ነው። ጣኦት አምልኮን ከራቁና በአንድ አምላክ ሕልውና ከሚያምኑ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ነቢዩ ሙሐመድ ከመነሳታቸው ጥቂት ጊዜያት ቀደም ብሎ ነው የሞተው። ግና የአዲሱን ነብይ መነሳት ይጠባበቅ እንደነበር የሚያመለክቱ በርካታ ብስራቶች ተናግሯል።

ለአብነት ያህል፡-

“የአዲሱ ሐይማኖት መምጫ ዘመን ደርሷል። እኔ ያኔ በሕይወት ልኑር አልኑር የማውቀው ነገር የለም።”

ይህ የዘይድን ልቦና የዳበሰ ስሜት መለኮታዊ እስትንፋስ ሆኖ ልቦናውን ሐቅን ለመቀበል ሙሉ በሙሉ እንዲከፈት አደረገው። በአንዱ አላህ ያምን ነበር። ሁለመናውን ለርሱ ሊሰጥ ተዘጋጅቷል። ግና ይህ ያመነበት አምላክ ባህሪው እንዴት እንደሆነ፣ እንዴትስ ማምለክ እንዳለበት ግልጽ አልሆነለትም።

ከነቢዩ ባልደረቦች መካከል አንዱ የሆነው ዓሚር ቢን ረቢዓህ እንዲህ ሲል አውግቷል፡-

“ዘይድ ቢን ዓምር ቢን ኑፈይል የሚከተለውን ነገረኝ። በአብዱል ሙጦሊብ በኩል ከእስማኤል ዝርያ የሆነን ነብይ በመጠባበቅ ላይ ነኝ። አገኘዋለሁ ብዬ አላስብም። በርሱ አምናለሁ። እውነት እለዋለሁ። ነቢይ መሆኑንም እመሰክራለሁ። እድሜህ ረዝሞ ካገኘህው ሰላምታ አቅርብልኝ። ላንተ ማንነት እንዳይሰወርብህ ባህሪውን እገልጽልሐለሁ።

‘እሺ ባህሪውን ግለጽልኝ’ አልኩት። ‘አጭርም ረዥምም ያልሆነ ጸጉሩ ያልረዘመም ያላነሰም ነው በዓይኖቹ ቅላት አይለያቸውም። የነብይነት ማህተም ከትከሻዎቹ መካከል አርፏል። ስሙ አህመድ ይባላል። የሚወለደውም ነብይ ሆኖ የሚነሳውም እዚሁ አገር ውስጥ ነው። ከዚያም ወገኖቹ ያስወጡታል። ያመጣውን መልእክትም ይጠሉበታል። ወደ የስሪብም ይሰደዳል። እውቅናም ያገኛል። አደራህን ከርሱ እንዳትርቅ። እኔ የኢብራሃምን ሐይማኖት ፍለጋ አገሩን ሁሉ አስሻለሁ። አይሁዶችም ክርስትያኖችም መጁሶችም፡- ይህ ሐይማኖት ከእንግዲህ የሚመጣ ነው፤ ይሉኛል። መምህሩ የሆነውን ነብይም ባህሪ ልክ አሁን እንደገለጽኩልህ አድርገው ገልጸውልኛል። ከዚህ ሰው ውጭ ሌላ ነብይ ከእንግዲህ እንደማይኖርም አውግተውኛል።’ አለ።

ዓሚር እንዲህ ሲል አውግቷል፡-

በሰለምኩ ጊዜ ለአላህ መልእክተኛ የዘይድን መልእክት ነገርኳቸው። ሰላምታውንም አደረስኩላቸው። ለሰላምታው ምላሽ ሰጡ። አላህ ያዝንለት ዘንድም ተማጸኑ። ‘ጀነት ውስጥ ሲራመድ አየሁት’ አሉም።” (አልብዳየቱ ወኒሐያ ኢብን ከሲር 2/296-299)

ወረቃህ ቢን ኑፈይል የክርስትና እምነት አዋቂ ነበር። የእናታችን ኸዲጃ የአጎት ልጅም ነበር። መጽሐፍት በይብራይስጥኛ ይጽፍ ነበር። ወንጌልን ከይብራይስጥ ቋንቋ ጽፏል። አይነ ስውር አዛውንት ነበር። በነቢዩ ላይ የመጀመሪያው ራእይ በተገለጸላቸው (ወህይ በወረደላቸው ጊዜ) ኸዲጃ ወደ ወረቃ ይዛቸው ሄደች። “የአጎቴ ልጅ ሆይ፣ የወንድምህ ልጅ ያጋጠመውን ነገር ስማ።” ስትልም ለወረቃ ነገረችው። ወረቃም፡- “የወንድሜ ልጅ ሆይ፣ ምን አጋጠመህ?” ሲል ነቢዩን ጠየቃቸው። ነቢዩም ያዩትን ነገር ነገሩት። ወረቃህም፡- “ይህ አላህ በሙሳ ላይ ያወረደው መልእክት ነው። ወይኔ፣ ወገኖችህ ከሐገር ሲያባርሩህ በሕይወት ብኖር መልካም ነበር።” አለ። የአላህ መልእክተኛም፡- “ከሐገር ያስወጡኛልን?” ሲሉ በመገረም ጠየቁት። “አዎ፣ አንተ ያመጣህውን ዓይነት መልእክት ያመጣ ሁሉ ጠላቶች ይሰየሙበታል። ያኔ በሕይወት ካለሁ አንተን መርዳት እጸናለሁ።” አለ። (ቡኻሪና ሙስሊም)

አብደላህ ቢን ሰላም አይሁዳዊ የሐይማኖት አዋቂ ነበር። የሰለመበትን አኳኋን እንዲህ ተርኳል፡-

“ነቢዩ ወደ መዲና ሲገቡ ሰዎች ወደርሳቸው ተመሙ። እኔም አብሬያቸው ሄድኩ። ገና ሳያቸው ፊታቸው የውሸታም ፊት እንዳልሆነ አወቅኩ። መጀመሪያ ሲናገሩ የሰማሁት ቃል፡- ‘ሰላምታን አብዙ። ምግብን መግቡ፣ ዝምድናን ቀጥሉ፣ ሰዎች በተኙበት እናንተ ስገዱ። ጀነት በሰላም ትገቡ ዘንድ ይህን አድርጉ’ የሚለውን ንግግራቸውን ነበር።” (አህመድ፣ ቲርሚዚና ቢን ማጃህ)

አብደላህ ቢን ሰላም ክብደት የሚሰጠው ስብእና ነው። ቢን ሐጀር “አልኢሷባህ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል፡-

“እውቅ ሰው ነበር። የነቢ ዩሱፍ ዝርያም ነበር። ቁርአን የርሱን ምስክርነት አወድሷል። በካህድያን ላይም መረጃ አድርጎ አቅርቦታል፡-

قُلْ أَرَأَيْتُمْ إِن كَانَ مِنْ عِندِ اللَّهِ وَكَفَرْتُم بِهِ وَشَهِدَ شَاهِدٌ مِّن بَنِي إِسْرَائِيلَ عَلَىٰ مِثْلِهِ فَآمَنَ وَاسْتَكْبَرْتُمْ إِنَّ اللَّهَ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الظَّالِمِينَ

“(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው ‘እስቲ ንገሩኝ፤ (ቁርኣኑ) ከአላህ ዘንድ ቢኾን። በእርሱም ብትክዱ፣ ከእስራኤል ልጆችም መስካሪ በብጤው (በእርሱ) ላይ ቢመሰክር፣ ቢያምንም፣ (ከእምነት) ብትኮሩም፣ (በዳይ አትኾኑምን?)’ አላህ በእርግጥ በደለኞችን ሕዝቦች አያቀናም።” (አል-አህቃፍ 46፤ 10)

በዚህ አንቀጽ የተጠቀሰው ከበኒ እስራኤል የሆነ መስካሪ አብደላህ ቢን ሰላም ነው። አንዳንድ የተፍሲር ምሁራን ይህችን አንቀጽ መካዊ እንደሆነች በማሰብ የተጠቀሰው መስካሪ ሙሳ ናቸው ቢሉም ይበልጥ ክብደት የሚሰጠው አስተያየት አንቀጿ መዲናዊ መሆኗ ነው። አል-አህቃፍ መካዊ ምእራፍ ብትሆንም ይህች አንቀጽ ግን መዲናዊ ናት። የምታመላክተውም አብደላህ ቢን ሰላምን ነው።”

________________

ምንጭ፡- ፈትሁላህ ጉለን- “ኑሩል ኻሊድ” /ዘልዓለማዊው ብርሃን/፤ ትርጉም በሐሰን ታጁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here