ለዓለማት እዝነት የተላኩት ነብያችን (ክፍል 3)

0
2180

የነብይነት ምልክቶች

1. ወደ ሻም ያደረጉት ጉዞና መነኩሴው ቡሐይራ

የታሪክ መጽሐፍት እንደሚስማሙት ነቢዩ ሙሐመድ ከመካ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጓዙት ወደ ሻም ከአጎታቸው ከአቡ ጧሊብ ጋር ነበር። እድሚያቸውም ያኔ 12 ዓመት ነበር። ቅፍለቱ በመንገድ ላይ ለእረፍት በቆመ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ ቅፍለቱን ለመጠበቅ ወደ ኋላ ቀሩ። በዚህ ጊዜ ቡሐይራ የተባለ መነኩሴ በዚህ ቅፍለት ውስጥ እንግዳ ነገር ተመለከተ። ይህውም ዳመና ቅፍለቱን እየተከተለ ሲያጠልለው አየ። ቅፍለቱ ሲሄድ ይሄዳል። ሲቆም ዳመናውም ይቆማል። በዚህ ጊዜ የቅፍለቱን አባላት ምግብ ለመጋበዝ ሰው ላከባቸው። የቅፍለቱ አባላት ጥሪው ሲደርሳቸው ተገረሙ። ምክንያቱም ይህ መነኩሴ ከዚህ ቀደም ለቅፍለቶች ትኩረት ሲሰጥ ታይቶ አይታወቅም። እናም ሁሉም ግብዣውን ተቀብለው ሄዱ። የዓለማት ፈርጥ ብቻ ተነጥለው ወደ ኋላ ቀሩ። መነኩሴው ከመሐከላቸው የሚፈልገውን ሰው አላገኘም። ምን አልባትም ወደ ማእዱ ሳይመጣ ወደ ኋላ ተነጥሎ የቀረ ሰው ይኖር እንደሁ ጠየቃቸው። አንድ ልጅ ብቻ እንጅ የቀረ ሰው እንደሌለ ነገሩት። ልጁን አስጠርቶ አስመጣው። ገና ሲያየው ልእልናውን ተገነዘበ። ለአቡ ጧሊብም ስለ ማንነቱ ጠየቃቸው። “ልጄ ነው” አሉት። መነኩሴው ግን አላመናቸውም። ምክንያቱም ይህ ልጅ በእርሱ ግምት የነብያት መቋጫ ይሆናል። ስለዚህ አባቱ ከመወለዱ በፊት ነው መሞት ያለበት። ወደ አቡጧሊብ ጆሮ ጠጋ አለና ይህን ጉዟቸውን እንዲሰርዙ መከራቸው። “አይሁዶች ምቀኝነት ያየለባቸው ሕዝቦች ናቸው። ይህን ልጅ በምልክቱ የነብያት መቋጫ መሆኑን ካወቁ የነርሱ ወገን ባለመሆኑ ሊጎዱት ይችላሉ።” አላቸው። አቡ ጧሊብ የመነኩሴውን ምክር ተቀበሉና ጉዟቸውን ሰርዘው ወደ መካ ተመለሱ። (ሲረት ቢን ሂሻም 1/191-195)

ቡሐይራ እውነት ብሏል። አንድ ነገር ግን ዘንግቷል። ይህ መልእክተኛ በዓለማት ጌታ እንክብካቤና ጥበቃ ስር መሆኑን አላወቀም። አላህ እንዲህ ሲል እንደገለጸው፡-

وَاللَّهُ يَعْصِمُكَ مِنَ النَّاسِ

“አላህም ከሰዎች ይጠብቅሃል።” (አል-ማኢዳህ 5፤ 67)

አዎ፣ አላህ ከጥቃት እንደሚጠብቀው ቃል ገባ። ቃሉንም ፈጸመ።

2. ወደ ሻም ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉት ጉዞ

ነቢዩ ውደ ሻም ለሁለተኛ ጊዜ የተጓዙት እድሚያቸው ሃያ አምስት ዓመት እያለ ነው። ኸዲጃ ያሰማራችው ቅፍለት አለቃ ነበሩ። ከእርሷ ጋር ንግደ በሽርክና ይሰሩ ነበር። በዚህ ጉዟቸውም “ነስጡራ” የተባለ መነኩሴ አግኝተዋል። ይህኛውም መነኩሴ ከርሳቸው ላይ የነብይነት ምልክት እንዳዬ አውግቷል። (ሲረት ቢን ሂሻም 1/199)

________________

ምንጭ፡- ፈትሁላህ ጉለን- “ኑሩል ኻሊድ” /ዘልዓለማዊው ብርሃን/፤ ትርጉም በሐሰን ታጁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here