ለዓለማት እዝነት የተላኩት ነብያችን (ክፍል 2)

0
2014

የጨለማው ዘመን

የተውሂድ እምነት የተናጋባቸው ዘመናት ሁሉ “የጨለማ ዘመናት” በመባል ይታወቃሉ። ምክንያቱም የሰማያትና የምድር ብርሃን በአላህ ማመን ነውና። እምነት ልቦናዎችን ሁሉ ካልተቆጣጠረ መንፈሶችን ጨለማ ይወርሳቸዋል። ቀልቦች ይጠቁራሉ። የክስተቶችን ትክክለኛ ሂደት የመረዳት አቅማቸው ይደክማል። እይታቸው የደፈረሰ እና የተጭበረበረ ይሆናል።

የሐይማኖት መሠረቶች ሁሉ ከስር በተናጉበት፣ ሰማያዊ ሐይማኖቶች በተበከሉበት በዚያ ዘመን አላህን በብቸኝነት የሚያመልኩ ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ እነርሱም ቢሆኑ የአላህን ትክክለኛ ማንነት፣ ባህሪዎቹንና ስሞቹን በወጉ ያልተረዱ በመሆናቸው እርሱን በትክክል የማምለክ ሐላፊነታቸውን እንዴት መወጣት እንዳለባቸው አያውቁም ነበር።

1. የታወሩ ዓይኖች

ጣኦታዊያን ካእባን የሞሉትን ጣኦታትና ታቦታት ያመልኩ ነበር። በዚህ የአምልኮ ስርዓታቸውም ይፎካከሩ ነበር። ደስታም ያገኙ ነበር። ጥቂት የእውቀት ፍንጣቂ የደረሳቸው ወገኖችም፡- “እነዚህን ጣኦታት ወደ አምላክ እንዲያቃርቡን እንጅ አናመልካቸውም” የሚል ምክንያት ይሰጣሉ። ቁርአን ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-

وَالَّذِينَ اتَّخَذُوا مِن دُونِهِ أَوْلِيَاءَ مَا نَعْبُدُهُمْ إِلَّا لِيُقَرِّبُونَا إِلَى اللَّهِ زُلْفَىٰ

“እነዚያም ከእርሱ ሌላ (ጣዖታትን) ረዳቶች የያዙት ‘ወደ አላህ ማቃረብን እንዲያቀርቡን እንጅ ለሌላ አንገዛቸውም’ (ይላሉ)።” (አል-ዙመር 39፤ 3)

አላህ በሰው ልጆች ልቦና ውስጥ ያስቀመጠው እርሱን የማምለክ አደራ በዚህ መልኩ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ውሎ ተበደለ። ሁኔታው በእርግጥም ይገርማል። ዛፍና ድንጋይ፣ ጨረቃና ጸሐይ እንዴት ሊመለኩ ይችላሉ? ከዚህም አልፎ በእጆቻቸው ይሰሯቸው የነበሩ ምግቦችን እንኳ ያመልኩ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያመልኳቸውና ሲርባቸው ይመገቧቸዋል። ቁርአን ይህን ዓይነቱን የተበላሸ አመለካከት አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡-

وَيَعْبُدُونَ مِن دُونِ اللَّهِ مَا لَا يَضُرُّهُمْ وَلَا يَنفَعُهُمْ وَيَقُولُونَ هَٰؤُلَاءِ شُفَعَاؤُنَا عِندَ اللَّهِ قُلْ أَتُنَبِّئُونَ اللَّهَ بِمَا لَا يَعْلَمُ فِي السَّمَاوَاتِ وَلَا فِي الْأَرْضِ سُبْحَانَهُ وَتَعَالَىٰ عَمَّا يُشْرِكُونَ

“ከአላህም ሌላ የማይጎዳቸውን የማይጠቅማቸውንም ይግገዛሉ። ‘እነዚህም አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው’ ይላሉ። ‘አላህን በሰማያትና በምድር ውስጥ የማያውቀው ነገር ኖሮ ትነግሩታላችሁን?’ በላቸው። ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ፤ ላቀም።” (ዩኑስ 10፤ 18)

أَلَا لِلَّهِ الدِّينُ الْخَالِصُ وَالَّذِينَ اتَّخَذُوا مِن دُونِهِ أَوْلِيَاءَ مَا نَعْبُدُهُمْ إِلَّا لِيُقَرِّبُونَا إِلَى اللَّهِ زُلْفَىٰ إِنَّ اللَّهَ يَحْكُمُ بَيْنَهُمْ فِي مَا هُمْ فِيهِ يَخْتَلِفُونَ إِنَّ اللَّهَ لَا يَهْدِي مَنْ هُوَ كَاذِبٌ كَفَّارٌ

“ንቁ! ፍጹም ጥሩ የኾነው ሃይማኖት የአላህ ብቻ ነው። እነዚያም ከእርሱ ሌላ (ጣዖታትን) ረዳቶች የያዙት ‘ወደ አላህ ማቃረብን እንዲያቀርቡን እንጅ ለሌላ አንገዛቸውም’ (ይላሉ)። አላህ በዚያ እነርሱ በእርሱ በሚለያዩበት ነገር በመካከላቸው ይፈርዳል። አላህ እርሱ ውሸታም ከሓዲ የኾነን ሰው አያቀናም።” (አል-ዙመር 39፤ 3)

ለአስተሳሰባቸው መበከል የተለያዩ ሰበቦችንም ይደረድሩ ነበር። አንዱ ሰበባቸው አባቶቻችን ትተውልን ያለፉት እምነትና ባህል ነው የሚል ሲሆን ቁርአን እንዲህ ገልጾታል፡-

وَإِذَا قِيلَ لَهُمُ اتَّبِعُوا مَا أَنزَلَ اللَّهُ قَالُوا بَلْ نَتَّبِعُ مَا أَلْفَيْنَا عَلَيْهِ آبَاءَنَا أَوَلَوْ كَانَ آبَاؤُهُمْ لَا يَعْقِلُونَ شَيْئًا وَلَا يَهْتَدُونَ

“ለእነርሱም ‘አላህ ያወረደውን ተከተሉ’ በተባሉ ጊዜ ‘አይደለም አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር እንከተላለን’ ይላሉ። አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና (ወደ እውነት) የማይመሩም ቢኾኑ (ይከተሉዋቸዋልን?)።” (አል-በቀራህ 2፤ 170)

2. ከነ ነፍሳቸው የሚቀበሩ ሕጻናት

ቁርአን የመሐይምነት ዘመን ሌላ አስከፊ ልማድ እንዲህ ሲል ይጠቁመናል፡-

وَإِذَا بُشِّرَ أَحَدُهُم بِالْأُنثَىٰ ظَلَّ وَجْهُهُ مُسْوَدًّا وَهُوَ كَظِيمٌ ﴿٥٨﴾ يَتَوَارَىٰ مِنَ الْقَوْمِ مِن سُوءِ مَا بُشِّرَ بِهِ أَيُمْسِكُهُ عَلَىٰ هُونٍ أَمْ يَدُسُّهُ فِي التُّرَابِ أَلَا سَاءَ مَا يَحْكُمُونَ

“አንዳቸውም በሴት ልጅ በተበሰረ ጊዜ እርሱ የተቆጨ ኾኖ ፊቱ ጠቁሮ ይውላል። በእርሱ ከተበሰረበት ነገር መጥፎነት በውርደት ላይ ኾኖ ይያዘውን?ወይስ በዐፈር ውስጥ ይደብቀውን? (በማለት እያምታታ) ከሰዎች ይደበቃል። ንቁ! የሚፈርዱት (ፍርድ) ምንኛ ከፋ!” (አል-ነህል 16፤ 58-59)

አዎ፣ አባት እንስት እንደተወለደለት ሲነገረው ፊቱ በሐዘንና በቁጣ ይጠቁራል። በሐፍረት ይከስላል። ስሜቱን ለመደበቅ እንኳ አይሞክርም። ወይም አይቻለውም። ክስተቱ ከአጥንቱ ድረስ ዘልቆ ከመግባቱ የተነሳ ከሰው ለመደበቅ ይጥራል። ከሁለት ነገሮች መካከልም አንዱን የመምረጥ ግዴታ አለበት። አንድም ነውሩን እንደተሸከመ መኖር፣ ካልሆነም ሴት ልጁን ከነ ሕይወቷ በመቅበር ሐፍረቱን ማስወገድ። አንድን መወሰን አቅቶት ይዋልላል።

በዘመነ መሐይምነት ሴት ልጅ የነበራት ቦታ ይህ ነበር። ሴትን እንዲህ ማዋረድ እና መናቅ በዓረብ መሐይማን ብቻ የተወሰነ አይደለም። በሮማና በፐርሺያ ኢምፓየር የነበረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም በመሐይማን ዓረቦች ውስጥ ሴትን አስመልክቶ በቁርአን የተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ በዓለም ላይ በዚህ ረገድ ወደር አይገኝለትም። ይህን አውሪያዊ ድርጊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃወመውና ሴትን ልጅ በምንም ምክንያት መግደልን ያወገዘው ቁርአን ነበር፡-

وَلَا تَقْتُلُوا أَوْلَادَكُم مِّنْ إِمْلَاقٍ نَّحْنُ نَرْزُقُكُمْ وَإِيَّاهُمْ

“ልጆቻችሁንም ከድህንት (ፍራቻ) አትግደሉ። እኛ እናንተንም እነርሱንም እንመግባችኋለንና።” (አል-አንዓም 6፤ 151)

“ልጃችሁን ለምን ትገድላላችሁ?” ይላቸዋል። “እናንተንም ሆነ እነርሱን የምመግባችሁ እኔ አይደለሁምን? ምድር በመቶዎች የሚቆጠሩ የምግብ አይነቶች የተሞላች አይደለችምን? አላህ እናንተን ለመርዳት እንደሚተጋ አታስተውሉምን? ዝናብ ሊያወርድላችሁ ደመናን ይነዳል። እነዚህን በሚሊዮን የሚቆጠሩ እጽዋት ከኔ ውጭ ማን ነው ያበቀላቸው? ይህን ሁሉ እያያችሁ ልጆቻችሁን ሲሳይ ፍለጋ እንድትገድሉ የሚገፋፋችሁ ምን ዓይነት ሕሊና ነው? ይህን ዓይነቱን ወንጀል የሚፈጽም አላህ ሊያናግረው ተገቢው ሰው እንዳልሆነ ተገንዘቡ። ይልቁንም እነዚያን ንጹሐንን ነው አላህ የሚያናግረው። ለምን ለዚህ አሰቃቂ ወንጀልና በደል እንደተዳረጉም ይጠይቃቸዋል። በዳዮችም ይህን ግፍ በመፈጸማቸው ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَإِذَا الْمَوْءُودَةُ سُئِلَتْ ﴿٨﴾ بِأَيِّ ذَنبٍ قُتِلَتْ

“በሕይወቷ የተቀበረችውም ሴት ልጅ በተጠየቀች ጊዜ፤ በምን ወንጀል እንደ ተገደለች፤” (አል-ተክዊር 81፤ 8-9)

የዚያ ዘመን ሁኔታ ይዘገንናል። አንድ ጊዜ ከሶሐቦች መካከል አንዱ ከአላህ መልእክተኛ ዘንድ መጣና የዚያን አሰቃቂ ዘመን ሁኔታ እንዲህ ሲል ተረከላቸው፡-

“የአላህ መልእክተኛ ሆይ፣ የመሐይምነት ዘመን ሰዎች ነበርን። ጣኦታትን እናመልካለን። ልጆቻችንን እንገድላለን። ሴት ልጅ ነበረችኝ። ስጠራት በደስታ ትመጣለች። አንድ ቀን ጠራኋት። መጣች። ወጣሁ። ተከተለችኝ። ጥቂት እንደተጓዝን ከአንድ የቤተሰቦቼ ጉድጓድ ውሃ አጠገብ ደረስን። እጇን ያዝኩና ወደ ውስጥ ወረወርኳት። በመጨረሻ ከአንደበቷ የሰማሁት ቃል ‘አባዬ፣ አባዬ’ የሚል ነበር።”

ነቢዩ ይህን ታሪክ ሲሰሙ እንባቸው እስኪፈስ ድረስ ተንሰቅስቀው አለቀሱ። ከታዳሚዎች መካከል አንዱ፡- “የአላህን መልእክተኛ አሳዘንካቸው” በማለት ሰውየውን ወቀሰው። ነቢዩም፡- “አትውቀሰው። ውስጡን የሚያውከውን ሐሳብ እየጠየቀ ነው” አሉና “ታሪኩን ድገምልኝ” አሉት። አሁንም ተንሰቅስቀው አለቀሱና እንዲህ አሉ፡-

“አላህ በዘመነ መሐይምነት የፈጸማችሁትን ሐጢአት ሁሉ ውድቅ አድርጎላችኋል። እናም መልካም ስራ እንደ አዲስ ጀምር።” መልእክተኛው ታሪኩ እንዲደገምላቸው የጠየቁት በመሐይምነት ዘመን የነበሩበትን አስከፊ ሁኔታ ሊያስታውሷቸው ፈልገው ይሆናል። “እንዲህ ዓይነት አውሬዎች ነበራችሁ። ኢስላም የለገሳችሁን እጅግ አንጸባራቂ ሰብአዊ እሴት አስተውሉ” ሊሏቸው ሽተው ይሆናል።

ይህ እጅግ አሳዛኝ ናሙና የሰው ልጅ በዚያ ዘመን የነበረበትን ቀውስ አመላካች ነው። በሺዎች ከሚቆጠሩ ዘግናኝ ወንጀሎች መካከል ይህ አንዱ ብቻ ነው። ያን ጊዜ ዘወትር ሌሊት በዚያ በረሃ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥልቅ ጉድጓዶች ይቆፈራሉ። ንጹሐን ሕጻናትም ወደዚያ ይወረወራሉ። አዎ፣ የሰው ልጅ በጭካኔ አውሬዎችን በብዙ ርቀት ቀድሟል። ጉልበት የሌለው በጉልበታማው መጨፍለቅ፣ ስቃይና መከራን ማስተናገድ እጣ ፈንታው ነበር። መላ ማሕበረሰቡ ስቃይና ቀውስ ውስጥ ተዘፍቋል። ይህን ቀውስ ሊያስቀር ወይም ሊፈታ የሚችል አንድም ሰው የለም።

በዚህ ወቅት ነቢያችን በሐጢአት ዋሻ ውስጥ ነበሩ። ይህ ዋሻ በኋላ ላይ “ጀበሉኑር” (የብርሃን ተራራ) ተብሎ ተሰይሟል። ነቢዩ በዚህ ዋሻ ውስጥ ከሰዎች ተነጥለው ስለሰው ልጅ እጣ ፈንታ ያስተነትናሉ። ዓይናቸውን ከአድማሱ ላይ ተክለው የሰውን ልጅ መዳን ይጠባበቃሉ። ግንባራቸውን ከመሬት ላይ አሳርፈው ለሰአታት አምላካቸውን ይማጸናሉ። የሰው ልጅን ከተዘፈቀበት መከራ መንጥቆ የሚያወጣ አዳኝ ይልክ ዘንድ ይለምኑታል።

ነቢዩ በዋሻው ውስጥ በዚህ ሁኔታ ይቆያሉ። ወደ መካ የሚመለሱት የቋጠሩት ስንቅ ሲያልቅ ብቻ ነው። ከዚያም የሚበቃቸውን ያህል እህል ቋጥረው ወደዋሻው ይመለሳሉ። (ቡኻሪና ሙስሊም)

በዋሻው ውስጥ ስለዚህ ዩኒቨርስና ከዩኒቨርሱ ጀርባ ስላለው ሐይል፣ ስለ ፍጡራንና ኹነቶች፣ ስለ ፍጥረታት ዓላማና መዳረሻ፣ የሰው ልጅ ስለሚገኝበት እጅግ የሚዘገንን እና አሳዛኝ ውድቀት በጥልቀት ያስተነትኑ እንደነበር ጥርጥር የለውም።

3. የተለወጡ እሴቶች

ማሕበረሰቡ ከመጨረሻው የዝቅጠት ወለል ላይ ደርሷል። ሰብአዊ እሴቶች ሁሉ ተለዋውጠዋል። ከላይ ወደታች ተገልብጠዋል። መልካም ስነ ምግባሮች ከነውር ተቆጥረዋል። ነውሮች ሁሉ ደግሞ የኩራት ምንጭ ሆነዋል። አውሬነት ይወደሳል። እዝነት ይንኳሰሳል። ተኩላዎች ፍየሎችን እንዲጠብቁ ተሹመዋል። ፍየሎችም ሐይልና ብልሐት አጥተው በነዚያ ተኩላዎች ጭካኔ ይንገላታሉ። ዋይታቸው ሰሚ አላገኘም። ብልግናና ዝሙት ተስፋፍቷል። ስነ ምግባር ተበክሏል። አስካሪ መጠጥና ቁማር፣ መሠረታዊ ሸቀጦችን አከማችቶ ሸማቹን ማንገላታትና መዝረፍ ነውር አልነበሩም። ስርቆት፣ ቅሚያና ዝርፊያ ክብርና ሞገስ ያስቸራል። የሕዝብን ደም መምጠጥ ከብስለት ይቆጠራል።

በመሆኑም ማራኪ እና ርቱእ አንደበት ያለው አንድ ቅን ሰው ተነስቶ ይህን ብክለት “በቃህ” ሊለው የግድ ነበር። የብክለቱ መጠን መለኮታዊውን እዝነት ቀሰቀሰ። አምላክም ለሰው ልጅ ዋይታ ምላሽ በመስጠት የሰው ልጆች ኩራት፣ የመልእክተኞች ዓይነታ የሆኑትን ነብይ አስነሳ። በርሳቸው መምጣት ሁሉም ነገር ተቀየረ። ግዙፍ አብዮትና ለውጥ ተከናወነ። የባለ ቅኔዎች ንጉስ አህመድ ሸውቂ እንዲህ ሲል እውነትን ተናግሯል፡-

ቅኑ (ነብይ) ሲወለድ ለፍጡራን ብርሃን ፈነጠቀ

ዘመን በሐሴት ተዋጠ። በደስታ በሳቅ ደመቀ።

በጽልመት የተዋጠችው ዓለም ነቢዩ ሙሐመድ ባመጡት ብርሃን አሸበረቀች። ከዓመታት በኋላ የመዲና ሰዎች ነቢዩን በሚከተለው ስንኝ ተቀብለዋቸዋል፡-

እልል እሰየው ጨረቃ መጣልን

ከ ‘ሰንየተል ወዳእ’ አበራ ደመቀልን።

ምስጋና ይግባው ለርሱ የበዛ በያይነቱ

ቅን ጎዳና ሊመራን ከሩቅ ቀዬ በመምጣቱ።

(አል ቢዳየቱ ወኒሐያ- በኢብን ከሲር 3/241፣ ደላኢሉ ኑቡዋህ- በይሐቂ 2/507)

4. መለኮታዊ መሰናዶ

የነቢዩ ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) እያንዳንዱ የልጅነት፣ የወጣትነትና የጉልምስና እርከን ለነብይነት ሐላፊነታቸው እንደ ቅድመ ዝግጅት ነበር። በመሆኑም ነብይነታቸውን ባወጁ ጊዜ በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች ወዲያውኑ ነበር የተቀበሏቸው።

እውነተኛ ነበሩ። አንድም ጊዜ ዋሽተው አያውቁም። እነሆ አሁን አላህን ወክለው እየተናገሩ ነው። እርሱ እንደላካቸው አውጀዋል። በጥቃቅን ጉዳዮች እንኳ ለመዋሸት ያልፈቀዱት ነብይ በዚህ ከባድና አደገኛ ጉዳይ ሊዋሹ አይችሉም። (ቡኻሪና ሙስሊም ይመልከቱ)

በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ያስቡ የነበሩት እንደዚህ ነው። ሁሉም በርሳቸው ቢያምኑም ምቀኝነትንና ትእቢትን አሽቀንጥረው የጣሉ ወገኖች ፈጥነው ነብይነታቸውን ተቀብለዋልሰ።

በእርግጥ እርሳቸው የኖሩበት ዘመን የጃሂልያ ዘመን ነው። ግና የዚያ ዘመን እኩይ ባህሪያት ከርሳቸው የራቁ ነበሩ። ነብዩ የጃሂልያን ሕይወት ለቅጽበት እንኳ አልኖሩም። ታማኝ ስብእና ነበሩ። ሁሉም ሰው በዚህ ባህሪያቸው ያውቃቸዋል። እንበልና ጉዞ ለመውጣት አሰብክ። ባለቤትህንም ከአንድ ስፍራ አደራ ልታኖራት አሰብክ። ያለ ጥርጥር ከታማኙ ሙሐመድ ዘንድ ልብህን ሞልተህ አደራ ልታኖራት ትችላለህ። እርግጠኛ ሁን በዓይኑ እንኳ አያያትም። ገንዘብህን ከአንድ ሰው ዘንድ አደራ ማስቀመጥ ብትሻም ለታማኙ ሙሐመድ ለመስጠት ለቅጽበት እንኳ አታመነታም። ከንብረትህ ቅንጣት ታክል እንኳ አደጋ እንደማያገኛት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ነብዩ ለታማኝነታቸው ወሰን፣ ለአደራ ጠባቂነታቸው አቻ የላቸውም። በአንዳች ጉዳይ ትክክለኛ ምክርና መረጃ ከከጀልክም ታማኙንና እውነተኛውን ሙሐመድን አወያይ። ጆሮ ሰጥተህ ስማቸው። በምክራቸውም በሙሉ ልብ ስራበት። ምክንያቱም ሕይወታቸው ሙሉ አንዲት እንኳ ውሸት ተናግረው አያውቁምና።

ለዚህ አባባል መረጃ ትሻለህን? እነሆ ከሶፋ ጋራ ላይ በመውጣት በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎችን፡- “ፈረሶች ከዚህ ጋራ ስር ሊያጠቋቸው እየወጡ እየወጡ ነው ብላችሁ አታምኑኝምን?” ሲሉ ጠየቁ። የሰዎች ምላሽ፡- “ባንተ ላይ ውሸት አግኝተን አናውቅም” የሚል ነበር።

ዑትበት ቢን ረቢዓህ፣ ወሊድ ቢን ሙጊራህ፣ አቡ ጀህልና መሰል ቀንደኛ ጠላቶቻቸውም ይህን ምላሽ ከሰጡና የነቢዩን እውነተኛነት ካጸኑ ሰዎች መካከል ነበሩ። ሁሉም የርሳቸውን እውነተኛነት ያውቃሉ። የጥሩ ስብእና ባለቤት መሆናቸውን ያጸድቃሉ። ታማኝነታቸውን ያረጋግጣሉ።

ነቢዩ ከእናታቸው ሆድ እያሉ አባታቸውን አጡ። በስድስት ዓመት እድሚያቸው ደግሞ እናታቸውን አጡ። አያታቸው አብዱል ሙጦሊብም አሳደጓቸው። ስምንት ዓመት ሲሞላቸው አያታቸው ሞቱ። አላህ ከፍጡራን ድጋፍ ሁሉ አጽድቶ ሁለ ነገራቸውን ለርሱ ብቻ ይሰጡ ዘንድ ሊያደርጋቸው የወሰነ ይመስላል። እርሳቸውን ለመርዳት እጁን የዘረጋ ሁሉ፣ ያቀፈና የደገፋቸው ሁሉ ፈጥኖ ይሄዳል። አላህ የአንድን አምላክ ድጋፍ እና መከታነት ከወዲሁ ሊያሳውቃቸው፣ በዚሁ አግባብ ሊያንጻቸው፣ “ሐስቢየሏሁ ወኒእመል ወኪል” (አላህ ብቻ ይበቃኛል። መመኪያነቱ ምን አማረ) የሚለውን ጥልቅ የተውሂድ መልእክት ከልቦናቸው ውስጥ ሊያሰርጽ የወሰነ ይመስላል። ይህ ይሆን ዘንድ በዓይን የሚታይ የድጋፍና የመመኪያ ምድራዊ ምንጮች ሁሉ ከአጠገባቸው ገሸሽ እንዲሉ ያስፈልግ ነበር። በተጨባጭ የሆነውም ይህው ነው።

አባታቸው አብደላህ፣ እናታቸው ደግሞ አሚናህ ይባላሉ። በእርግጥ ይህ የወላጆቻቸው ስያሜ የአጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን በአላህ እቅድ የተፈጸመ ነው። አሚና የሚለው ስም ታማኝነትን ያመለክታል። አብደላህ ደግሞ የአላህ ባሪያ መሆንን። ይህ ለነቢዩ መለኮታዊ መሰናዶ ነው። አላህን በማምለክ አድማስ ውስጥ እጅግ እውነተኛ እና ታማኝ የሆነውን ስብእና ለመኮትኮት የተደረገ ነው።

የቲም ሆነው አደጉ። ከፊት ለፊታቸው ከባድ ሸክም፣ ትልቅ ሐላፊነትና ተግባር ስለሚጠብቃቸው ለዚያ ተግባር ራሳቸውን ማዘጋጀት ነበረባቸው። በአላህ ላይ ያላቸው መመካት የመጨረሻውን ደረጃ መድረስ ነበረበት። ሁሉንም ዓይነት መከራዎች ለመሸከም ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ነበረባቸው። ወደ ኩራትና ትእቢት ከሚመራ የተዝረከረከ ሐብት፣ እንዲሁም አቅም አልባና ወራዳ ከሚያደርግ ድህነት አላህ ጠበቃቸው። ሕይወታቸውን ሙሉ በሁሉም የሕይወታቸው ጉዳዮች ሚዛናዊና ልከኛ ስብእናን ይዘው ኖሩ።

መሪ በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ቀናት ውስጥ ማለፉ ለመሪነት ተግባሩ እጅግ ያስፈልገዋል። የየቲምነትን ሕመም የቀመሰ፣ ጥልቅ መልእክቱን የተረዳ ለተከታዮቹ አዛኝ አባት የመሆን ነገር ይቀልለታል። የድህነትን ሕመም መቅመሱም የሚመራው ሕዝብ ችግር እንዲሰማው ያደርገዋል። አዎ፣ የቲሞችን መርዳት፣ ድሆችን መንከባከብ፣ እንባቸውን ማበስ፣ ሕመማቸውን ማስታገስ ከአላህ መልእክተኛ ውብ ባህሪያት መካከል ነበር። እርሳቸውም በየቲምነት ስቃይ፣ በድህነት ሕመም አልፈዋልና። በመከራ ውስጥ ኖረዋል። በችግር ውስጥ አድገዋል። አየሩን ተንፍሰዋል። ውሃውን ጠጥተዋል። በኋላ ላይ ወደ ላይ ሲወጡ፣ የሐገር መሪ ሲሆኑ ከዚህ ባህሪ ፈቀቅ አላሉም። አልተቀየሩም። ቀላልና ገራገር ሕይወታቸውን አልለወጡም። ሕይወታቸውን ሙሉ የቲምን አንገላትተው ለማኝን መልሰውና ገላምጠው አያውቁም። ምክንያቱም ይህን ውብ ባህሪ አላህ አስተምሯቸው ነበርና። እንዲህ በማለት በመለኮታዊ መንክር ቀርጿቸዋልና፡-

أَلَمْ يَجِدْكَ يَتِيمًا فَآوَىٰ ﴿٦﴾ وَوَجَدَكَ ضَالًّا فَهَدَىٰ ﴿٧﴾ وَوَجَدَكَ عَائِلًا فَأَغْنَىٰ ﴿٨﴾ فَأَمَّا الْيَتِيمَ فَلَا تَقْهَرْ ﴿٩﴾ وَأَمَّا السَّائِلَ فَلَا تَنْهَرْ ﴿١٠﴾ وَأَمَّا بِنِعْمَةِ رَبِّكَ فَحَدِّثْ

“የቲም ኾነህ አላገኘህምና አላስጠጋህምን? (አስጠግቶሃል)። የሳትክም ኾነህ አገኘህ መራህም። ድኻም ኾነህ አገኘህ፤ አከበረህም። የቲምንማ አትጨቁን። ለማኝንም አትገላምጥ። በጌታህም ጸጋ አውራ፤ (ግለጻት)።” (አል-ዱሐ 93፤ 6-11)

ይህን የቁርአን አንቀጽ ባነበብኩ ቁጥር እርሳቸው አማላጃችን እንደመሆናቸው የቲምነቴን ልናዘዝላቸው እሻለሁ። አባቴን ያጣሁት ከብዙ ዓመታት በፊት ነው። “አላህ ሆይ፣ እነሆ እኔ የቲም ነኝ። ከበርህም ላይ ቆሜያለሁ። ስለዚህም አታባርረኝ። የነብይህን አማላጅነትም አትንፈገኝ።”

5. የሚጠበቀው ብርሃን

አያታቸው አብዱል ሙጦሊብ ገና ከመነሻው ጀምሮ የነብይነትን ብርሃንና ምልክት ከእርሳቸው ላይ አይተዋል። ከልጅ ልጃቸው ከሙሐመድ ጋር ያሳለፏቸው ጊዜያት የበረከትና የጸጋ ጊዜያት ነበሩ። ከታላላቅ ሰዎች ጉባኤ ይወስዷቸዋል። ያልቋቸዋል። ምን አልባትም የሰው ልጆችን የማዳን ምልክት አይተውባቸው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በሙሐመድ ዓይን ውስጥ በሌሎች ዓይኖች ያላዩትን ጥልቀት ያስተውሉ ነበር። እንዲሁም “ሉዓይ” ከተባለው አያታቸውም ከልጅ ልጁ ነብይ እንደሚወለድ ንግርት ሰምተዋል። ምን አልባትም ከዚህ ንግርት አኳያ ከሙሐመድ ላይ የነብይነት ምልክት አይተው ወይም ገምተው ሊሆን ይችላል። ምን አልባትም ለሙሐመድ የነበራቸው የበረታ ፍቅርና ስስት ከዚህ የመነጨ ሊሆን ይችላል። አብዱል ሙጦሊብ ሊሞቱ ሲሉ አምርረው አለቀሱ። ምክንያቱም ከእንግዲህ ሙሐመድን ወደ ደረታቸው አስጠግተው ማቀፍ አይችሉም። (ሲረቱ ነበዊያህ- ኢብን ሂሻም 1/178፣ ጦበቀቱል ኩብራ- ቢን ሰእድ 1/118)

በአብራሃት ሰራዊት ፊት ዓይናቸውን ያልሰበሩት፣ ከበርካታ ጠላት ጎሳዎች ጋር ለዓመታት በተደረገው የፋጁር ጦርነት ያላለቀሱት እኒህ ታላቅ ሰው ከሙሐመድ መለየታቸው ሲታወቃቸው እንደ ሕጻን ልጅ ተንሰቅስቀው አለቀሱ። አብዱል ሙጦሊብ ለነቢዩ ሙሐመድ የሚያደርጉት እንክብካቤና ድጋፍ በዚሁ ተጠናቀቀ። ሕይወትን ከመሰናበታቸው ጋር አብሮ አከተመ። የሰው ልጆች እንቁ ወደ አጎታቸው ወደ አባ ጧሊብ አሳዳጊነት ተሸጋገሩ።

6. ትልቅ ሽልማት

አቡ ጧሊብ ሐላፊነታቸውን ተወጡ። ለአርባ ዓመታት ያህል የአላህን መልእክተኛ ተንከባከቡ። አቀፉ፣ ደገፉ። ይህ ውለታቸው ያለ ምላሽ እንዲሁ አልቀረም። አላህ እንደ አልይ ዓይነት ልጅ ሰጣቸው። የሁሉም ነብያት የዘር ግንደ ቀጣይነት የሚያገኘው በራሳቸው በኩል ቢሆንም የነቢዩ ዘር ግን የቀጠለው በዓሊይ በኩል ሆነ። ይህን የሚያመለክት ሐዲስ ከነቢዩ ተላልፏል። (መጅሙእ ዘዋኢድ ሐይሰሚ 9/172፣ ፈይዱል ቀዲር- መናዊ 2/223፣ ታሪክ በግዳዲ 1/317)

ዓሊ እጅግ ሲበዛ ጀግና፣ የእስልምናም ባለውለታ ሲሆኑ፣ የነቢዩ አማች የመሆን እድልም አግኝተዋል። እኒህ ሰው ለአቡ ጧሊብ ከአላህ የተሰጡ ችሮታ ናቸው። አቡ ጧሊብ ነቢዩን ስለተንከባከቡ። አቡ ጧሊብና አባታቸው አብዱል ሙጦሊብ ነቢዩን በመንከባከብና በመደገፍ ቢታወቅም እውነተኛው ተንከባካቢና ደጋፊ ግን አላህ ነው።

አላህ ይህን ታላቅ ስብእና ከማምጠቁና ወደ ነብይነት ደረጃ ከማዝለቁ በተጓዳኝ ማሕበረሰቡንም ይቀበላቸው ዘንድ በማዘጋጀት ላይ ነበር። ምክንያቱም የነብይነታቸው ምልክት ከቀን ቀን ይበልጥ ግልጽ እየሆነ በመሄድ ላይ ነበር። በመሆኑም ሁሉም ስለርሳቸው የሚያወጋላቸው፣ ሁሉም የሚያውቃቸው፣ ክብደትና ግምት የሚሰጣቸው፣ እንደ ማንኛውም ዘመናት ከዋክብት ጎልተው እና ደምቀው የሚታዩ የዘመኑ ኮከብ ለመሆን በቅተው ነበር።

________________

ምንጭ፡- ፈትሁላህ ጉለን- “ኑሩል ኻሊድ” /ዘልዓለማዊው ብርሃን/፤ ትርጉም በሐሰን ታጁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here