ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የተከተልነው ብርሃን

0
3088

ምን አይነት አስተማሪ? ምን አይነት ሰው?…!

አዋጅ! እነዝያ ታላቅነቱ ያስገረማቸው ቢገረሙም ምክንያት አላቸው!

እነዚያ በነፍሳቸው የተሰዉለት.. እነርሱ አትራፊዎች ናቸው!

ምን አይነት ምስጢር ቢኖረው ነው ከሰዎች የበላይ የሆኑ ሰዎችን ያመረተው?! ምን በተከበረ እጅ ወደ ሰማይ በዘረጋት ከዚያም በእያንዳንዱ የእዝነት፤ የፀጋና፤ የመመራት በሮቿ በሰፊው የተከፈተችው?! ምን አይነት እምነት? ምን አይነትስ ቁርጠኝነት? ምን አይነት ልፋት? ምን አይነት እውነት? ምን አይነት ወኔ? ምን አይነት ፍቅር? ምን ቁምነገረኝነት!? ምን ለእውነት መታመን? ምን ፍጥረትን ማክበር?!

የእርሱን ባንዲራ እስኪሸከምና በስሙ እስኪናገር ድረስ አሏህ ከፀጋዎቹ ችሮታል። እንደውም የመጨረሻ መልእክተኛነትን ክብር እስካጠለቀ ድረስ ፀጋዎቹን በርሱ ላይ አስፍኗል። በዚህም በሙሀመድ  (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የአላህ ችሮታ ታላቅ ነበር።

ያ ረሱለላህ! ምላስ፣ ሃሳብ፣ ቀለም ስለርሶ ቢናገሩ፤ ዝማሬዎችም በአንድነት የእርሶን እልቅና ቢያዜሙ ከዚያም ሁሏም ቦታዋን እንዳላገኘች ትሆናለች። ምላሷንም እርሶን ለማወደስ ለንግግር እንዳላንቀሳቀሰች…

ይህች ጽሁፍም ምንም ቃላቶቿ ቢዋቡ ንግግሯም ቢኳል ምንም ያህል ነቢን (ሰ.ዐ.ወ) ብታሞካሽ የርዕሷን ግማሽ ክብር እንኳን አትወጣም፤ እንዳውም ታላቁን ነብይ ለንባብ አቅርቢያለሁ አትልም። ይች ምናልባትም ታላቅነታቸውንና ከፍ ያለው ደረጃቸውን ጠቋሚ ጣት እንጂ ሌላ አይደለችም።

አዎን! ይች ፅሁፍ የሰዎችን ልብ ወደርሳቸው የገፋችና በዘመንና በትውልድ የማይገደብ አቻ የሌለው ፍቅርን ወደርሳቸው የሳበች ልቅናና ግሩም ስብዕናን የምናመለክትባት ጠቋሚ ብቻ ናት። ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስለጦርነትና ሁከት ሰብኳል የሚሉ ሁሉ ይምጡ። ዛሬ እኛ ተከታዮቻቸው ስለፍቅር፣ ስለእዝነትና ስለሰላም እንጂ ሌላ ወሬ የለንም። ታላቁ ነብይ ያስተማሩንን ንፁህ ፍቅር ዛሬ እንዘክራለን።

የጎሳ አለቆችን ወደሚሰብኩት እምነት እንዲቸኩሉ ያደረጋቸው ምንድን ነው?! ለምንድን ነው አቡበከር፣ ጦልሃ፣ ዙበይር፣ ኡስማን፣ አበዱረህማን ቢን ዐውፍ፣ ሰዕድ ቢን አቢወቃስ እና ሌሎችም በታላቅ የኢማን ፍጥነት ህዝቦቻቸው የቸሯቸውን ክብርና ድሎት ትተው በከባድ ችግርና በፍፁም ጭንቀት ወደተወጠረው አፍላው ኢስላማዊ ህይወት የዞሩት?!

ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በገንዘብና በአቅም ደካማ ሆነው ችግር፣ መከራና አስፈሪ አደጋዎች እየወረዱባቸው እራሳቸውንም ከአደጋ መጠበቅ ሳይችሉ… ደካሞች ግን ወደ እርሳቸው ጥበቃ እንዲጠጉና ወዳነገቡት ባንዲራም እንዲሰበሰቡ ያደረጋቸው ምን ይሆን?!

የጃሂሊያ ጉልበተኛው ዑመር ኢብኑልኸጣብ አንገታቸውን በሰይፍ ሊቆርጥ ሄዶ ነበር። ነገር ግን በያዛት ሰይፍ ኢማን ክህደትን የጨመረበትን የጠላታቸውን አንገት ወደ መቀንጠስ ያስዞረው ምን ይሆን?!…

“ለነፍሴ ጥቅምንም ጉዳትንም አልችልም፤ በእኔም ሆነ በናንተ ላይ የሚሰራውንም አላውቅም!” እያሏቸው በርሳቸው የሚያምኑ ሰዎች ግን እንዲጨምሩ እንጂ እንዲቀንሱ ያልሆኑት ለምንድን ነው?!…

ምድር ከየአቅጣጫዎቿ እንደምትከፈትላቸውና እግሮቻቸው የአለምን የሀብትና የዘውድ ማማ እንደምትረግጥ… እልቅናንና ክብረትንም እንደምትሸለም… ተደብቀው የሚያነቡት ቁርኣንን በአለም… (በህዝቦቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን… በደሴታቸውም ብቻ ሳይሆን…) መልዕክቱ ለሚመለከተው የሰው ዘር ሁሉ እንደሚያነቡትና እንደሚያስተምሩት፤ በየዘመኑና በየቦታው ሰዎች ከፍ ባለ ድምጽ እንደሚያነቡት ሲነገሯቸው እንዴት አመኑ!?… የሚደንቀው! ወደፊትና ወደኋላቸው፣ ወደ ቀኝና ወደ ግራቸው ሲዞሩ ህይወታቸው ችግር፣ ጥበት፣ ጭንቀት፣ ረሀብ፣ ስቃይና ሰቆቃ ሆኖ ይህን መልእከተኛቸው የሚነግሯቸውን ትንቢት እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምን ይሆን?!… ምንድን ነው ልባቸውን የቂንና ቁርጠኝነት የሞላው?!… እርሳቸው የዐብደላህ ልጅ “ሙሐመድ” ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ናቸው!

ከእርሳቸው ውጪ እንደዚህ ያለ ማን አለ?!…

ህዝቦቻቸው ታላቁን ስብእናቸውንና ታላቅነታቸውን በዐይናቸው ተመልክተዋል። ንጽህናቸውን፣ ጥብቅነታቸውን፣ አደራ ጠባቂነታቸውን፣ ጽናታቸውንና ጀግንነታቸውን በዓይናቸው አይተዋል። እዝነታቸውንና ፍቅራቸውን አስተውለዋል፤ አስተዋይነታቸውንና ግልጽነታቸውን ተመልክተዋል። ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የቀን ራዕያቸውንና የማታ ፍካሬያቸውን በሚያፈሱባት ጊዜ የህይወትን ስፋት ህይወት በደረሰበት ሁሉ ሲጓዝ አዳመጡ! ይህን ሁሉ ተመለከቱ፤ ከዚህም ሌላ የማይቆጠር ብዙ የሚደንቅን ነገር..!

የዚያን ዘመን ዐረቦች አንድን ነገር ያዩና ያጠኑት ጊዜ ያኔ እንደ አዋቂስ ማንም አይነግርህም! እነርሱ ፈታኝና ተጠራጣሪዎች ናቸው። መሬት ላይ የእግር ኮቴን በመመልከት ይች የእገሌ ተረከዝ ነች የሚሉ… የሚያወራቸውን ሰው ትንፋሽ በማሽተት ልቡ ውስጥ እውነት ወይስ ቅጥፈት እንዳፈነ የሚደርሱበት ሰዎች ነበሩ። ታዲያ እነዚህ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ተመልክተዋል፤ ተወልደውም ወደ ምድር ከመጡ ጀምሮ አብረዋቸው ኖረዋል። ህይወታቸውም ከነርሱ የሚደበቅ ምንም ሚስጥር የለውም፤ የልጅነት ጊዜያቸውም ቢሆን!…

ልጅነታቸው አንደሌሎች ልጆች አልነበረም። ከህፃናት የዛዛታ ቦታ ወደ ጎልማሶች ቁምነገረኝነት በማዘንበሏ የሰዎችን ልብ የሳበች ህፃንነት። ወደ ጨዋታ የተጠሩ ጊዜ “እኔ ለዚህ አልተፈጠርኩም!” ይሉ እንደነበር ተዘግቧል።…

ወጣትነታቸውማ ምን ያማረ ወጣትነት?!…

የህዝቦቻቸው መነጋገሪያ ነበሩ። በጣም የሚደንቁ፣ የተከበሩና የተወደዱ።…

በጉልምስናዎማ የሁሉንም አይን ጆሮና ልብ የሞሉ ፍፁም ፅድቅ ነበሩ። ህይወታቸው በሙሉ የህዝቦቻቸው መንገድ ነበር። እንደምሳሌ እውነት ግብረገብነትና ቁንጅና የሚገለጽበት ህይወት።…

ይህቺ እንግዲህ ከአንቀልባ እስከህልፈት የተነበበች ግልፅ ህይወት ነች።

ያ ረሱለላህ! አስተሳሰቦ፣ እርምጃዎ፣ ንግግርዎና አንቅስቃሴዎ በሙሉ እውነት ነበር። እንደውም ህልሞችዎ፣ ምኞትዎና ፍላጐትዎ ወደዚህች ህይወት ከመጡበት ቀን ጀምሮ እውነትና ፍቅር ብቻ ነበር!…

አሏህም ለሰዎች “ይህ ወደናንተ የምልከው መልእክተኛዬ ነው!… እስትንታኔ እና እውቀት ነው መንገዱ፤ ይህ ጽንስ ከነበረ ጀምሮ የኖረው ህይወቱ ነው፤ ተመልከቱት!… ይህ ሰው ወደ እናንተ መልእክተኛዬ ነው፤ ተከተሉት!…” ሊላቸው ፈልጎ ይመስላል።

ባላችሁ እውቀት እና ጥበብ ህይወቱን መርምሩት፤ ፈትሹት!… ስህተትን ተመለከታችሁን!? ጥመትን አያችሁን!? አንዴም ቢሆን ዋሽቷልን!? አንዴም ቢሆን ከድቷል!? አንዴም ቢሆን ሰውን አዋርዷል!? ሰውን በድሏል!? ቃልን አፍርሷል!? ዝምድናን ቆርጧል!? የሰውን ገንዘብ በልቷል!? ከመልካም ባህሪያት ተራቁቷል!? አንድን ሰው ሰድቧል!? ጣኦት አምልኳል!?… ይህ ሁሉ ይህ ንፁህ ስብእና ውስጥ የለም። ህይወቱን በደንብ ፈትሹ! ተመራመሩት! አንዲት ግርዶሽም ሽፋንም የለውም። ህይወቱ ግልጽ ነው ምስጢርም የለውም።…

እንግዲህ ህይወቱን እንደምታዩት ንፁህ እውነትና ልቅና ከሆነ ከአርባ አመት የህይወት ቆይታው በኋላ ዋሸ ማለት አእምሮ ይዋጥለታል?!…

ደግሞስ በማን ላይ ነው የሚዋሸው?! በአሏህ ላይ?! የአሏህ መልእክተኛ ነኝ ሊል?! አሏህ መርጦኛል፤ ራዕይንም ሰጥቶኛል ሊል?! በፍጹም አይሆንም!? ማስረጃም እውቀትም፣ አእምሮም እውነትም በፍፁም አይሆንም ይላሉ!…

በምን ዘዴ ነው የምታስተነተኑት?! በምን ሚዛንስ ነው የምትመዝኑት?! በምን እውነታስ ነው የምታስተባብሉት?!

እንደምናስበው… የመጀመሪያዎቹ የሙእሚን ሙሃጂሮችና የአንሷሮች ስሜት ይህ ነበር። በአርግጥም መሸማቀቅ የሌለበት ስር ነቀልና ፈጣን ስሜት ነበር። ወዲያው ነበር እንዲህ አንፀባራቂና ንፁህ ህይወት ያለው ሰው በአሏህ ላይ በፈፁም አይዋሽም ያሉት።

በዚህ ሚዛናዊ ልቦና እነዚያ ሙእሚኖች የአላህን ብርሃን በአይናቸው አይተው ተከተሉት። በእርግጥም ሚዛናዊ እንዲሆኑ የረዳቸውን ንፁህ ልባቸውን አላህ መልእክተኛውን ባለድል በሚያደርግ ጊዜ ያመሰግኑታል። ደሴቱ ሁሉ ለእርሱ ሆኖ ሳለ የዱንያ ጥላቻና የአላህ ፈራቻ እንጂ ሌላን ሳይጨምር፤ ሰንበሌጥ ላይ ተኝቶ የሰንበሌጡ ምስል ሰውነቱ ላይ ሲሳል፤ ከዚህ ሁኔታውም ሳይቀየር ጌታውን የተገናኘ ጊዜ ሲገናኝ… ያኔ ልባቸውን ያፈቅሩታል። ሚዛናዊ እይታውንም ያወድሱለታል።

ባንዲራው አለምን የሞላ መሪና የተከበረ የአሏህ መልእክተኛ ሆነው ሳለ ሚንበር ላይ ሲወጡ እያለቀሱና “ያለአግባብ ጀርባውን የገረፍኩት ሰው ካለ ይኸው ጀርባዬን ይበቀለኝ! ገንዘቡን ያላግባብ የወሰድኩበት ካለ ይኸው ገንዘቤን ይቀበለኝ!” እያሉ ሲጣሩ ባዩዋቸው ጊዜ…

አጐታቸው ዐባስ ሹመት እንዲሰጡት በጠየቃቸው ጊዜ “ወሏሂ አጐቴ! ስልጣንን ለሚፈልጓት ወይም ለሚጓጉላት አንሰጥም!” ብለው ሲመልሱ በተመለከቱ ጊዜ…

የሰዎችን ችግርና ረሃብ መቋደስ ብቻ ሳይሆን እራሳቸውና ቤተሰባቸው የችግሮች ዋና ገፈት ቀማሽ ሆነው ሰዎች ሲራቡ የመጀመሪያዎቹ ራብተኞች፤ ሰዎች ሲጠግቡም የመጨረሻዎቹ ጠጋቢዎች ሆነው ባዩዋቸው ጊዜ… በእርግጥም ወደ ኢስላም ጐዳና ለመራቸው ጌታ ምስጋናን ከመጨመር በኋላ ነገርን በንጽህናና በሚዛናዊነት አንዲያስተውሉ ላደረጋቸው አስተዋይ ልቦናቸው ያላቸው ክብር ይጨምራል።

“ሰዎች ሆይ እኔ ወደናንተ የተላኩ የአሏህ መልክተኛ ነኝ!” ባሉ ጊዜ ለእውነተኝነታቸው ምርጥ ምስክር የሚሆነውን ታላቅ ህይወት ይመለከቱታል!? ይች ህይወት በፅድቅነቷና በታላቅነቷ የምርጡን አስተማሪና የቸሩን መልዕክተኛ እውነተኛነት ትመሰክራለች። እኔ የአሏህ መልዕክተኛ ነኝ ሊሉም ይገባቸዋል!…

ያ ረሱለላህ! የህይወቶ የልቅናና የጽድቅ ደረጃ ለሰከንድም ዝቅ አላለም። አንደውም አንደነበረው ሳይቀየር ከእቅፍ እስከ ህልፈት ዘልቋል። በዚህ የህይወት ቆይታ በተለይም የህይወቶን ታላቁን ግብ ካሳኩ በኋላ ለገንዘብና ለስልጣን የሚተጉ እንዳልነበሩ እነደፀሀይ ብርሃን ግልጽ ሆነ። እነዚህ ሁሉ በታላቅ እድል ታጭቀው ሲመጡ እርስዎ ግን አልተቀበሏቸውም። ለነርሱም አልተሸነፉም። ህይወትዎ ከታላቅ ዓላማው የፀጉር ብጣሽ ታክል እንኳን ፈቀቅ አላለችም። በአምልኮ የኖሩትን ህይወት አልገደፉም።

የመጨረሻው የለሊቱ ክፍል በሚገባ ጊዜ ከእንቅልፍ ቀጥ ብለው ይቆማሉ። ውዱእም አድርገው ወዳስለመዱት ጌታዎን ወደማናገርና ወደማልቀስ ይዞራሉ። ይሰግዳሉ፤ ያለቅሳሉ። ገንዘብ እንደተራራ ከፊትዎ ቢከመርም አልተቀየሩም። ሃብትንም ከሙስሊሞች የመጨረሻዎቹ ድሆች እንደያዙት እንጂ አልያዙም። በመጨረሻም የጦር ቀሚሶት በእዳ ተይዞ አለፉ።…

አገሩ ሁሉ ለጥሪያቸው በተገዛ ጊዜ… የምድር ነገስታትም ወደርሳቸው መልእክት ጌታቸውን የፈሩና ለግርማቸው የተናነሱ ሲሆኑ በዞሩ ጊዜ… ቅንጣት ኩራትና እራስ ወዳድነት አላለፈችባቸውም፤ በኪሎሜትሮችም ቢሆን።…

አዲስ ገቢዎች በፈሯቸውና ለግርማቸው በደነገጡ ጊዜ… “አይዟችሁ እናቴ መካ ላይ የደረቀ ስጋ የምትበላ ሴት ነበረች!” ብለው ሲያባሽሯቸው ስንመለከት…

የኃይማኖታቸው ጠላቶች ትጥቃቸውን ፈትተው በድል መካን የከፈቱ ጊዜ… አእላፍ የሙሰሊም ሰይፎች በደስታ ሲፋጩ ጠላቶችም የፈለጉትን እንዲፈርዱ አንገታቸውን በሰጧቸው ጊዜ “ሂዱ ነፃ ናችሁ!” ከማለት ውጭ አንዲትም ቃል አልጨመሩም።…

ሕይወታቸውን በሰዉለት በድላቸው ቀን ሳይቀር መተናነስን እና ይቅርታን አስተምረውናል። ነፍሳቸውን ደሰታና እረፍት ከልክለው- መካን በከፈቱበት እግራቸው- ሰዎች ፊታቸውን ለማየት እስከሚቸገሩ አናታቸውን ዝቅ አድርገው… በልብና በነፍሳቸው መካከል የምስጋናን ጩኸት እያደመጡ ጉንጫቸውን በእንባ እያረጠቡ ፊታቸውን በሀፍረት ወደ ታላቁ ጌታቸው ከፍ አድርገው ካዕባ ውስጥ ገቡ። “እውነት መጣ ውሸትም ጠፋ ውሸት ጠፊ ነውና!” እያሉ በያዙት ዘንግ ጣዖታትን በናዱ ጊዜ… ያኔስ በሙሃመድ ( ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መልእክተኝነት ጥርጣሬ ይኖራልን?!…

ሀብትን፣ ስልጣንን፣ ክብርንና ተሰሚነትን ታሳቢ ሳያደርግ፤ ጌታው ጋር በመዘውተር እንጂ በሌላ የማያምን ሲሆን፤ ለታሪካዊ ማንነቱም ዘውታሪነት እንኳን ሳይጨነቅ ላነገበው ጥሪ ህይወቱን የሰዋ… ከልጅነት እሰከ አርባ አመት አድሜው ድረስ በንጽህናና በአስተዋይነት የኖረ… ከዚያም ከአርባ አመት ጀምሮ እስከ እድሜው ጣሪያ በአምልኮና በትግል ያከተመ ሰው… ዱንያ በሙሉ ተከፍታለት ሳለ ከነብላሽ ክበሮቿ ትቷት ወደ አምልኮና ወደ የሰውን ልጅ የማቅናት ትግል የሸሸ ሰው አንዴት ውሸታም ይባላል?!… እምን ላይ ነው እሺ ቅጥፈቱ?! አዋጅ! የአሏህ መልዕክተኛ ከዚህ ጠሩ!…

እንደኛ እምነት አእምሮና እውቀት፣ ማስተንተንና ጥበብ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የአሏህ መልእክተኛ ነኝ ባሉ ጊዜ እውነተኛ አንደነበሩ መስካሪዎች ናቸው። ሚዛናዊ አዕምሮ የዚህች ብሩክ ህይወት ባለቤት ጌታው ላይ ዋሸ ማለት አይዋጥለትም።

ይኸው ይህ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከመልእክታቸው በፊት እኚህ ናቸው። ከመልእክታቸው በኋላም… ይኸው እርሳቸው ያው ናቸው። በህይወት ዘመን እርዝመትና በአጋጣሚዎች ተቀይረዋልን? በፍፁም!…

አሁን የመጀመሪያው የመልእክት ዘመናቸው ጋር እንቁም። እነዚህ አመታት በሰው ልጅ ታሪክ ውሰጥ አቻ የማናገኝላቸው የእውነት፣ የታላቅነትና የጽናት አመታት ናቸው። እነዚህ አመታት የህያው ማንነታቸው መጽሀፍ መግቢያ ናቸው፤ የህይወትና የልፋት መጽሐፋቸው… እንደውም ከመቼም በፊት የተአምራቱ መክፈቻ አመታት ናቸው።

እነዚህ አመታት የአሏህ መልእክተኛ ብቸኛና ባይተዋር ሆነው አለፉ።… የኖሩበትን እረፍት፣ ሰላምና መደላደል ትተው ሰዎችን -ወዳልገባቸው… ወደማያውቁት… አንደውም ወደማይወዱት… ወደሚጠሉት… ነገር- ሊጣሩ ተላኩ። ከጥቂቶች ይልቅ ወደ ብዙሃኑ የአለም ህዝብ መልእክቱን የማድረሰ ኃላፊነት የተሰጠው ሰው ምን አይነት ከባድ ሸክም አለበት!? የአላህ መልእክተኛ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ግን ይህንን ብቻ አይደለም የሰሩት…

በእርግጥም አኮ… ሰዎችን በፍካሬያቸው ዙሪያ፣ በእውቀታቸው ልክ እና የጋራ በሆነ ሀሳብ ላይ ማናገር ቀላል ሊሆን ይችላል። ከርቀት ሆነህ ስትጠራቸውማ!… እነርሱም የማያዩት ላንተ ይታይሀል። አንተ የምትኖርበትን እነርሱ አያውቁት፤ አይገባቸው!…

ከዚህ ሲከፋ ደግሞ የህይወታቸውን መሰረት ልታናጋ ምሶሶውን ልትነቀንቅ ስትጠራቸው… ከቆሻሻ የጠራህና የታመንክ ልትሆን… ክብርና ሰሜትህን አሽቀንጥረህ ጥለህ በእስትንፋስህ ተረማምደህ… ህይወትህን አንጥፈህ… ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ ሳትል… የማይሰሙህን ልታሰማ… የማይገባቸውን ልታስረዳ… የማይወዱትን ልትግት… ልትቆርጥ ይገባሃል። በዚህ ጊዜ እነዚያ የትእግስት ባለቤት የሆኑት መልእክተኞችና ደጋጐች እንጂ ሌሎች የማይችሉት ፈተና ውስጥ ትወድቃለህ። የአሏህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የዚህ መንገድ ተዋናይና ታላቅ አስተማሪ ናቸው።

በእርግጥም የጣኦት ግዞት አምልኳቸው ነበር፤ የቁረይሾች መገለጫና ሀይማኖትም።…

የአሏህ መልእክተኛ ይህንን ትግል ከዚህ በፊት አልሰለጠኑትም። በተማሪ-ቤትም አልተማሩትም። ቀልድም ተውኔትም አይደለም። የምር ልፋት ቁርጥ ትግል እንጂ።… የመንገዱ ጥንካሬና የትግሉ ክብደት ከሰዎች በራቀው በተውሂድ ንግግር “በላኢላሀኢለሏህ” ሰዎችን ከመፋጠጥ ይልቅ ተራ ጥበባቸውንና የማይጠገበው ውድ ስብዕናቸውን የሰዎችን ልብ ለማለሳለሰ እንዲጠቀሙበተ ጊዜ በሰጣቸው ነበር። ሰዎችን ከምእተ አመታት በፊት ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው የጣኦት አምልኮ ለማላቀቅ በተቻላቸው መጠን ከአስደንጋጩና አስፈሪው ከተቃዋሚዎች ጥላቻና ወቀሳ… እንደውም በቅፅበት ያላቸውን ጦር ሁሉ ሊያዘምቱባቸው የሚችሉ መሆኑን ከሚያውቁት ጦርነት በመሰናዶና በዝግጅት ቀዝቃዛውንና የዳርዳርታውን መንገድ በመረጡ ነበር። ነገር ግን እንዲህ አላደረጉም። ይህም መልእክተኛ ለመሆናቸው ትልቅ ምልክት ነው።

የሰማዩ ድምፅ ቁም ሲላቸው ከልባቸው አደመጡና በፍጥነት ቆሙ። መልዕክትህን አድርስ ሲላቸውም አደረሱ። ያለ ስጋት… ያለ ፍራቻና ያለ ዝግጅት። ሰዎችን ከጅምሩ በአንኳር መልዕክታቸው ተጋፈጡ። “ሰዎች ሆይ ልታመልኩትና በእርሱ ላይ ምንንም ላታጋሩ እኔ ወደናንተ የአሏህ መልእክተኛ ነኝ! እነዚህ ጣኦታት ብላሽ ውሸቶች ናቸው! ለናንተ ጥቅምንም ሆነ ጉዳትን አይችሉም!” ከጅምሩ በነዚህ ግልጽና ቁልጭ ባሉት ንግግሮች ህዝቦቻቸውን ተፋጠጡ። ገና ከጅምሩ ህይወታቸውን እሰኪያጡ ድረስ ሊፋጠጡ ግድ ወደሚላቸው ከባድ ጦርነት ገቡ።

ታድያ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ምዕመናን ከዚህ ነብይ ጋር በቃል ኪዳን ሊያስተሳስር የሚችል ጥቅም ይኖራቸዋልን?! ይህ ልዩ… ባይተዋርና ብቸኛ ሰው ልፋት የማያንቀሳቅሰው ልብ ምን አይነቱ ልብ ነው?!…

ቀኑን በጥሪ ካሳለፉ በኋላ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ እራስዎ ይመለሳሉ። የህዝቦቻቸውን ጣኦታት እንደነገራቸው ትተው ጌታቸውን እንደሚሻው ይገዙታል። የህዝቦቻቸውን ኃይማኖት ወደርሳቸው ለመጣው እውነት ሰውተው መልእክተኝነታቸውንና መልእክትን ማድረስ ግድ እንደሆነባቸውም ለሰዎች አብራሩ። ዝም ማለትም ይሁን ነፍሳቸውን ከተመራችበት እውነትና ብርሀን ሊከለክሏት እንደማይችሉ ገለፁ። እንደውም የተፈጥሮም የአለምም ህግ በፍፁም ዝም ሊያሰኛቸው አይችልም! ምክንያቱም አሏህ ነው የሚያናግራቸው፣ የሚያንቀሳቅሳቸው እና መንገዳቸውን የሚመራቸው።

የቁረይሾች መልስ በፍጥነት መጣ። ልክ አውሎ ንፋስ እንደሚያቀጣጥለው ተንቀልቃይ እሳት ይመስላል። በሕይወት ዘመኗ ከበላይዋ ሌላ ክብር የሌለ በነበረ እልቅና ውስጥ በኖረች ነፍስ ላይ በደልና በቀል መዝመት ጀመሩ። የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አስገራሚና ወጣ ባለው አስተማሪነታቸው ልዩ ትምህርት ለሰዎች ማስተማር ጀመሩ። ዘመን፣ ቦታና ታሪክ የትግሉን ሂደት እይገድበውም።

… ሕያው ልብ ያላቸው ጥቂት መካውያን መዝለል መፍጠን መቅረብ ጀመሩ። ከፍ ያለ ታላቅ ሰውንም ተመለከቱ። አይተውት ከሚያውቁት ሁሉ ይበልጥ የሚያበራ ሰውን ተመለከቱ። እስከዛሬ ካዩት ሁሉ የሚያስፈራ ልዩ ሰው።…

ያኔ የቁይረሽ መሪዎች “አቡጧሊብ ሆይ ከኛ ውስጥ በእድሜም በክርብም በደረጃም የተከበርክ ነህ። ነገር ግን የወንድምህን ልጅ ከልክልልን ብለንህ አልከለክለውም አልክ። በአሏህ እንምላለን አባቶቻችንን እየሰደበ፣ በቂልነት እየፈረጀን፣ አማልክቶቻችንን እያነወረ ነው። እስካልከለከልከው ወይም እርሱንም አንተንም አንዳችን እስክንጠፋ እስካልተፋለምናችሁ ድረስ ትዕግስት አናደርግም።” ባሉ ቀን አቡጧሊብም የወንድማቸውን ልጅ “የወንድሜ ልጅ ሆይ ህዝቦቼ ወደ እኔ መጥተው ባንተ ጉዳይ ላይ አናግረውኛል። እባክህን ለእኔም ሆነ ለነፍስህ እዘን። ወደማልችለው ነገርም አትገፋፋኝ!” ብለው በላኩባቸው በዚህ ችግር ባፈጠጠበት የቀን ክፉ የመልእክተኛው አቋም ምን ይሆን?…

ጎናቸውን ሲደግፈው የነበረ ሰው እርዳታውን ሊያቆም ይመስላል። ወይም ክራንቻቸውን አስለው ከመጡት የቁረይሽ መሪዎች ጋር ለመጋፈጥ አቅምም ፈቃደኝነትም የሌለው ይመስላል። የአሏህ መልዕክተኛ   ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ለመልስ አልዋለሉም። ቁርጠኝነታቸውም አልቀነሰም። ውስጣቸውን የሚገልፁበት ቋንቋ እንኳን አልቸገራቸውም። እዚህ ጋር ከአስተማሪነትም በላይ የሆነ ታላቅ ትምህርትን ለሰዎች በሙሉ ሰጥተዋል። “አጎቴ ሆይ! ይህን ነገር እንድተወው ፀሀይን በቀኜ ጨረቃንም በግራዬ ቢሰጡኝ በአሏህ እምላለሁ አልተወውም!” አሉ። የአሏህ ነብይ ሆይ ሰላም ባንቱ ላይ ይሁን አንቱ የጀግኖች አለቃ! ንግግሮት ውስጣችንን በቁርጠኝነት እና በጀግንነት ይሞላሉ!

ወዲያውም አቡጧሊብ የራሳቸውንም ሆነ የአባቶቻቸውን ጥሪት ጥለው በወኔ በመሞላት የወንድማቸውን ልጅ እጅ በመያዝ “የፈለግኸውን ብትል አሳልፌ አልሰጥህም!” አለ።

ንቁ!… ሙሐመድ (  ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከአጎታቸው እርዳታን፣ ሰላምንና ጥበቃን የሚለምኑ ሳይሆን ዙሪያቸው ላሉት ሁሉ ፅናትን፣ ጥበቃንና ሰላምን የሚሰጡ ሰው ነበሩ ማለት ነው።

ማን ነው እንግዲህ ያለ ገድልን ተመልክቶ የዚህን መልዕክተኛ እውነተኝነት የማያምን?!… ፍቅር፣ እክብሮትና ናፍቆትን የማይጨምር?! ይህ ሁሉ ንፁህ አእምሮን ማስገረሙ የግድ ነው። ሕያው የሆኑ ልቦናዎችንም መቀስቀሱ።… የሚጠራቸውን ብርሃን እንዲከተሉ ማድረጉ… ሊመራቸውና ከቆሻሻ ሊያነፃቸው ወደ መጣው ወደ ንፁሁና ታማኙ ብርሃን ፊታቸውን እንዲያዞሩ ማንቀሳቀሱ አይቀርም።…

በእርግጥ ችግርና መከራ ከየአቅጣጫው ሲያቆስሏቸው ሰዎች ሁሉ አይተዋል። በአጎታቸው አቡጧሊብ እና በባለቤታቸው ኸዲጃህ ያገኙት የነበረው መጽናናት አሁን ቆመ። ሁለቱም በተቀራራቢ ጊዜ ሞቱ።

ቁረይሾች በርሳቸው ላይ የከፈቱትን ሰፊ ጦርነት አስከፊነት መሳል የፈለገ ሰው የዋነኛውን ወቃሻቸውንና ጠላታቸውን የአቡ ለሀብን ማንነት ማወቅ ይበቃዋል። አንድ ቀን እርሱ እንኳን መልእክተኛው ላይ የሚሰራውን ግፍ አስተዋለና ልቡ ተነካ። ከጠላቶቻቸው እንደሚጠብቃቸውም አወጀ። ነገር ግን መልዕክተኛው   ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጥበቃውን መለሱበት። በብቸኝነት፣ በኢማን እና በቁርጠኝነት ያለማንም ጥበቃም ቆዩ።…

የጧኢፍ ጊዜ መልእክተኛውን ያየ እውነተኝነታቸውን፣ እልቅናቸውን፣ ቁርጠኝነታቸውንና ለተሰጣቸው ኃላፊነት ብቁ መሆናቸውን ይረዳል። ሰቂፍ ወደምትባል አገር ሰዎችን ወደ አሏህ ሊጣሩ ተጉዘው ነበር። ዐጂብ!… ከቤተሰቦቻቸውና ከመካ ሰዎች የሚያገኛቸውን መከራ አይበቃቸውምን?!… ቅርበት ወይም ዝምድና ወደሌላቸው ሰዎች ሲመጡ መከራቸው ሊገዝፍ እንደሚችል አይፈሩምን?!… የለም! ስጋት ልባቸው ውስጥ አይገባም። ለፍርሃት ቦታ የላቸውም። በዳእዋቸው ምክንያት የሚያገኛቸውን ችግር ከሂሳብ አይቆጥሩትም። ታላቁ ጌታቸው “ማድረስ ግዴታህ ነው” ብሏቸዋል፤ ስለዚህ ምንም ይከሰት ማድረስ ነው።…

ያኔ… ያገሩ አለቆች ከበቧቸው ከመካዊያን ይበልጥ መጥፎ ሰዎችም ነበሩ። የዓረባውያንን እንግዳ የማክበርና ስደተኛን የመንከባከብ ባህል ጥሰው መልእክተኛውን በቂሎችና በህፃናት አስወገሯቸው። ቁረይሾች ከሰዎች በላይ የሚያደርጋቸውን ገንዘብ ያቀረቡላቸው ከክብርም ንግስናና የባለይነትን የሚቸራቸውን ክብር ሊሰጧቸው ቃል የገቡላቸውና “እኔ የአሏህ ባሪያና መልእክተኛው ነኝ!” ብለው የመለሱት ቁርጠኛው ሰው ይኸው እዚህ ጧኢፍ ውስጥ ወደ አንድ የአትክልት ስፍራ ተጠግተው ከቂሎች ድብደባና ወገራ ለመሸሽ ይሞክራሉ። ቀኛቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው ዱዓ እያደረጉ በግራቸው ደግሞ የሚወረወሩትን ድንጋዮች እየተከላከሉ ጌታቸውን እንዲህ ሲሉ ያናግሩ ነበር። “አምላኬ ሆይ! እስካልተቆጣህብኝ ድረስ አልከፋም።… ነገር ግን ደህንነትህና ሰላምህ ለኔ ሰፊ ናቸው…” አዎን!… ጌታቸውን በምን አይነት ስርአት ማናገር እንዳለባቸው የሚያውቁ መልዕክተኛ ናቸው። በአሏህ መንገድ ላይ ለሚያገኛቸው መከራ እንደማይገረሙ እያወጁ ነው። “እስካልተቆጣህብኝ ድረስ አልከፋም።…” በተጨማሪም ከጌታቸው የሆነን ደህንነትንም አጥብቀው እንደሚፈልጉ እያሳወቁ ነው።

በእርግጥም የአላህ መልእክተኛ ወደዚህ ምድር የመጡት ሰዎችን በአጠቃላይ ለማስተማርና ለመቀየር እንደሆነ ያውቃሉ።ለቁረይሾች ወይም ለአረቦች ብቻ የተላኩ መልእክተኛ እንዳልሆኑም ጠንቅቀው ይረዳሉ። ባንዲራቸው የሚውለበለብበትን የአለም ታላቁን የክብር ሰገነት ተመልክተዋል። የሚስብኩትንም ሃይማኖት መፃዒ ተስፋ በእርግጠኝነት አይተዋል። ምድርንና በውስጧ ያሉትን አሏህ እስከሚወርስ ድረስ የኃይማኖታቸውን መጨረሻ ያውቁታል። ይሁን እንጂ ሰማይና ምድር የመሰከረለት ማንነታቸውን ኃይማኖታቸውንም ሆነ ገድላቸውን አንድ ግንብ ላይ እንዳለ አንድ ጡብ እንጂ እንደሌላ አይቆጥሩትም ነበር። ታላቁ መልእክተኛ ግልጽ በሆነ ንግግር ይህን ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፡- “የኔና ከኔ በፊት የተላኩት ነብያት ምሳሌ ልክ ቤትን አሳምሮና አስውቦ እንደሰራ ሰው ነው። ሰዎችም በቤቱ ማማር ከመገረም ባሻገር ይህች ጡብ ለምን አልተደፈነችም ይላሉ። ይህች ጡብ እኔ ነኝ። እኔ የመጨረሻ ነብይ ነኝ!”

ይህ ሙሉ የኖሩት ህይወታቸው ነው። ይህ ሙሉ ትግላቸው ነው። ይህ ሙሉ እልቅናቸውና ንጽህናቸው ነው። ይህ ኃይማኖታቸውና በህይወታቸው ሳሉ ያረጋገጡት ድላቸውም ነው። ከርሳቸው ሞት በኋላም የአላማቸው መሳካትና የጥሪያቸው ግብ ነው። ይህ ሁሉ ትግልና ልፋት ጡብ እንጂ ሌላ አይደለም።

አንዲት ጡብ ባማረ ግዙፍ ግንብ ላይ።… ሰዎች ቤቱን ሲጎበኙ በውቡ ቤት ላይ ያለው የአንዲት ጡብ ክፍተት። እርሱ ሲሞላ ምድርም ሞላች።…

ይኸው እኚህ ናቸው የሰው ልጆች መምህር የነብያት መደምደሚያ።… ይኸው እኚህ ናቸው ሰው መስለው ሲኖሩ ሰዎች የተመለከቱት ብርሃን!… እኚህ ናቸው የልባችን መድሃኒት፣ የመንገዳችን ብርሃን። በመመሪያቸው እንኖራለን!… በፍቅራቸው ልባችንን እናበራለን!… ፈለጋቸውን እንከተላለን!… የርሳቸውን ልፋት ለፍተን እረፍታቸውን እናርፋለን!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here