ካዕባ በአላህ ስም፣ አላህን በብቸኝነት ለማምለክ የተገነባ የመጀመሪያው ቤት ነው። አባታችን ነብዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ከጣኦት አምልኮ ጋር ከፍተኛ ፍልሚያ ካደረጉ በኋላ ከአላህ በሆነ ትእዛዝ ካዕባን አነጹ።
“ኢብራሂምና ኢስማኢልም ‘ጌታችን ሆይ! ከእኛ ተቀበል። አንተ ሰሚውና ዐዋቂው አንተ ነህና’ የሚሉ ሲኾኑ ከቤቱ መሠረቶቹን ከፍ ባደረጉ ጊዜ (አስታውስ)።” (አል-በቀራህ 2፤ 127)
ካዕባ ከዚህ በኋላ ለብዙ አደጋዎች ተጋልጧል። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በነብይነት ከመላካቸው ከጥቂት አመታት በፊት መካን ያጥለቀለቀው ሐይለኛ ጎርፍ ይጠቀሳል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በነብይነት ከመላካቸው በፊት ካዕባን ለማደስ በተደረገው ጥረት ላይ በንቃት ተሳትፈዋል፤ በትከሻቸው ድንጋይ እየተሸከሙ ያቀብሉ እንደነበር ተዘግቧል። ያኔ እድሜያቸው 35 ዓመት እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ። ቡኻሪ እንደዘገቡት ጃቢር ኢቢን ዐብደላህ (ረ.ዐ) የሚከተለውን ሐዲስ አስተላልፈዋል፡-
لما بنيت الكعبة، ذهب النبي صلى الله عليه وسلم والعباس ينقلان الحجارة ، فقال العباس للنبي صلى الله عليه وسلم : اجعل إزارك على رقبتك ، فخرّ إلى الأرض وطمحت عيناه إلى السماء فقال : أرني إزاري فشده عليه
“ካዕባ በሚገነባ ጊዜ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እና አጎታቸው ዐብባስ (ረ.ዐ) ድንጋይ ያቀብሉ ነበር። ዐብባስም ለነቢዩ ‹‹ሽርጥህን ከአንገትህ ላይ ደልድለህ ተሸከም›› አሏቸው። ነቢዩም እንደተባሉት ሲያደርጉ ራሳቸውን ስተው ወደቁ። ዓይናቸው ወደ ላይ ተንጋጠጠ። ‘ሽርጡን አቀብሉኝ’ አሉና ከወገባቸው ላይ ታጠቁት።”
አላህ ይህን ያደረገው ሐፍረተ ገላቸውን ሌላ ሰው እንዳያየው ለመከላከል ነው። ይህ ክስተት እኒህ ሰው ለታላቅ ጉዳይ የታጩ መሆናቸውን አመላካች ነበር።
ጥቁሩን ድንጋይ ወደ ቦታው የመመለስን ክብር ለማግኘት በጎሳዎች መካከል የተነሳውን ውዝግብ በማፍታቱ ሂደትም ነቢዩ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ውዝግቡ ወደ ጦርነት ሊያመራ ተቃርቦ ነበር። የበኒ ዐብዱዳርና የበኒ ዓድይ ጎሣዎች በደም የተሞላ ገበታ አቅርበው ለክብራቸው በጋራ ለመፋለም እጃቸውን ከገበታው ውስጥ በማስገባት ቃል ተገባቡ። ቁረይሾች ውዝግቡን ለመፍታት ለአራት ወይም ለአምስት ቀናት ቢቀመጡም አልተሳካላቸውም። በመጨረሻም አቡ ኡመየህ አል- መኽዙሚ የተባለ ሰው፡- “ወገኖቼ ሆይ! አትወዛገቡ። ሁላችሁም የምትስማሙበትን ሰው ዳኛ አድርጉ” ሲል ሐሳብ አቀረበ። “በተቀደሰው ካእባ በር መጀመሪያ ለሚገባው ሰው ዳኝነት እናድራለን” ሲሉም ተስማሙ። ያ ሰው ታማኙ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሆኑ። “ይህ ታማኝ የሚሰጠንን ብይንስ በደሰታ እንቀበላለን” አሉ። ጉዳዩን አጫወቷቸው። እርሳቸውም ኩታቸውን ዘረጉ። ሁሉም ጎሳዎች የኩታውን ጫፍ እንዲይዙ አዘዙ። ድንጋዩን አነሱና ከኩታቸው ላይ አስቀመጡት። እንዲያነሱትም አዘዟቸው። ከሚቀመጥበት ቦታ ላይ ሲደርስ እርሳቸው ድንጋዩን ያዙና አስቀመጡት። ይህ ክስተት የነቢዩን አዎንታዊ ስብእና፣ ጥበባቸውንና የላቀ ደረጃቸውን ያሳያል። ታዲያ ወገኖቻቸው መልእከታቸውን ላለመቀበል ለምን ያን ያህል አንገራገሩ?
የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ተቀጣጥሎ የነበረውን የጦርነት እሳት ማጥፋታቸው አራት እውነታዎችን ይከስትልናል፡-
አንደኛ፡- አዎንታዊነት የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስብእና መሠረታዊ አካል ነው። በካዕባ ግንባታም ሆነ በሌሎች የማሕበረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ያሳዩት የነበረው የላቀ ተሳትፎ ከዚህ ባህሪያቸው የመነጨ ነው።
ሁለተኛ፡- ጉዳዮችን የሚያስኬዱበትን፣ ችግሮችን የሚፈቱበትን እጅግ አስደናቂ ጥበብ ያሳያል። በተለይም ይህን በጥበብ የከበረ የሽምግልና ሂደት ያከናወኑት በመካከላቸው ውዝግብ በተነሱባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ብዙ ደም ከመፍሰሱ በፊት እርቅ በማያወርዱ ጎሳዎች መሐል መሆኑ ደግሞ ለድርጊታቸው የበለጠ ድምቀት ይሰጠዋል።
ሦስተኛ፡- ከቁረይሾች ዘንድ የነበራቸውን የላቀ የክብር ደረጃ ያመለክታል። “ታማኙ” (አል-አሚን) በሚል ማእረግ ይጠሯቸው ነበር። በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ነበሩ።
አራተኛ፡- ከአላህ ዘንድ መልእከት ወርዶላቸው እርሱን ማድረስ በጀመሩ ጊዜ የነዚህ ወገኖቻቸው ልቦች በክህደት መሞላታቸው፣ በማስተባበልና በማወክ ጥሪያቸውን ማስተናገዳቸው በጣም ያስገርማል። በየትኛውም ቦታና ዘመን የሚገኙ የእውነት ተጣሪዎችን የሚቀናቀኑ ወንጀለኞችን እኩይ ባህሪም በጉልህ ያሳያል።