ሲራ ክፍል 3 – እመት ኸዲጃን ማግባታቸው

0
3509

ኢብን ሂሻም እንደዘገቡት ኸዲጃ (ረ.ዐ) ማሕበራዊ ክብር እና ሃብት የነበራት ነጋዴ እንስት ናት። ወንዶችን በሽርክና ታስነግዳለች። የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሐቀኝነትና ታማኝነት እንዲሁም መልካም ስብእና ስትሰማ ወደርሳቸው መልእክት በመላክ ገንዘቧን ይዘው ለንግደ ወደ ሻም እንዲሄዱ ጠየቀቻቸው። ለሌሎች ከምትሰጠው በላይ ገንዘብም ልትሰጣቸውና መይሰራህ የተባለ አገልጋይዋን ከርሳቸው ጋር ልትልክ ቃል ገባች።

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጥያቄዋን ተቀበሉ። ገንዘቧንም ይዘው ከአገልጋይዋ ከመይሰራህ ጋር ወደ ሻም ተጓዙ። ጉዟቸው የተሳካ ነበር። እጥፍ ድርብ ትርፍ ይዘው ወደ ኸዲጃ ተመለሱ። ገንዘቡንም በታማኝነት አስረከቡ። መይሰራህ የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ስብእናና ውብ ባህሪ ሲያይ ልቦናው በአድናቆትና በክብር ተሞላ። ያየውንም ለኸዲጃ አወጋት። እርሷም በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ታማኝነት ተደነቀኝ። በርሳቸው ሰበብ ያገኘችው በረከትም ሳያስገርማት አልቀረም፡፡ ይህ ሁኔታ ለጋብቻ እንድትጠይቃቸው አነሳሳት። ሐሳቧን አቀረበችላቸው። እርሳቸውም ተቀበሏት። አጎቷን ዐምር ኢቢን አሰድን በአጎታቸው በአቡ ጧሊብ በኩል አስጠየቁ። አቡ ጧሊብ የጋብቻ ጥያቄውን ያቀረቡት በሚከተለው ንግግር ነበር፡-

الحمد لله الذي جعلنا من ذرية إبراهيم، وجعلنا حضنة بيته، وجعلنا خدام الناس ثم إن ابن أخي هذا محمد بن عبد الله لا يوزن به رجل (إلا رجح به) شرفًا ونبلاً وفضلاً (وعقلاً) وإن كان في المال قلاًّ (أي فقيرًا) فإن المال ظل زائل وأمر حائل وعارية مسترجعة، وهو والله بعد هذا له نبأ عظيم وخطر جليل وقد خطب إليكم رغبة في كريمتكم خديجة وقد بذل لها من الصداق (كذا)….،

“የኢብራሂም ዝርያ፣ የቤቱ ጠባቂ፣ የሐጃጆች አገልጋይ ላደረገን አምላክ ምስጋና ይድረሰው። ይህ የወንድሜ ልጅ ሙሐመድ በገንዘብ በኩል ድሃ ቢሆንም በመልካም ስብእናና በአስተዋይነት ከየትኛውም ወንድ ሚዛን ይደፋል። ገንዘብ ደግሞ አላፊና ጠፊ ነገር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሙሐመድ ታላቅ እድል ያለው ሰው ነው። ልቅናችሁን በመሻትም ኸዲጃን ለጋብቻ ጠይቋታል። ይህን ያህል ጥሎሽም ይጥላል።”

የኸዲጃ ቤተሰቦች ተስማሙ። ጋበቻውም ተፈጸመ። ያኔ የርሳቸው እድሜ 25 ዓመት ሲሆን፣ የርሷ ደግሞ 40 ዓመት ነበር። ኸዲጃ እርሳቸውን ከማግባቷ በፊት ሁለት ባሎችን አግብታ ፈትታለች።

መሠረት-አልባ ሂስ

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከኸዲጃ (ረ.ዐ) ጋር ያደረጉት ጋብቻ ለስጋዊ ሐሴት ብዙም ትኩረት የማይሰጡ እንደነበሩ ያመለክታል። እንደሌሎች የእድሜ እኩዮቻቸው ወጣቶች ስጋዊ ደስታን የሚሹ ቢሆን ኖሮ በእድሜ ከርሳቸው የምታንስ፣ ቢያንስ ቢያንስ የእድሜ እኩያቻውን ያገቡ ነበር። እርሷን ለማግባት የወሰኑት ክብሯንና መልካም ስብእናዋን ተመልክተው ነበር። በዘመነ መሐይምነት ንጹህና ከአጓጉል ድርጊት የተጠበቀች እንደነበረች ተመስክሮላታል። (የአንተም የትዳር ጓደኛ ምርጫ የነብይህን አርአያነት የተከተለ ይሁን።)

ይህ ጋብቻ እመት ኸዲጃ (ረ.ዐ) በ56 ዓመት እድሜያቸው እስከሞቱበት እለት ድረስ ቀጥሏል። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ሌላ ሴት የማግባት ሐሳብ ሳይኖራቸው እድሚያቸው 50ዎቹን ተሻገረ። ወንድ ልጅ ብርቱ የወሲብ ፍላጎቱን ለማርካት ሲል ብዙ ሚስቶችን ለማግባት የሚከጅለው ከ25-50 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ መሆኑ ይታወቃል።

ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በኸዲጃ (ረ.ዐ) ላይ ሌላ ሴት የመደረብ ሐሳብ ሳያድርባቸው ይህን የእድሜ ክልል አለፉ። ቢፈልጉ ኖሮ በርካታ እንስቶችን ያገኙ ነበር። የሕብረተሰቡ ባህልም ይደግፋቸውዋል። ኸዲጃ (ረ.ዐ) አግብታ የፈታች እና በእድሜም የርሳቸው እጥፍ ልትባል የምትችል ሆና እያለ ቢያገቧትም ከርሷ ጋር ሌላ እንስት ሳያገቡ አብረዋት ኖረዋል። ይህ እውነታ ለእስልምና የበረታ ጥላቻ ያላቸው ሚሽነሪዎችና ኦሪየነታሊስቶች፣ እንዲሁም የነርሱ አገልጋይ፣ የአስተሳሰባቸው አቀንቃኝ የሆኑ አምላክ የለሾችና ዓለማዊያን የሚሰነዝሩትን ክስ ባዶ የሚያስቀር ነው። እነዚህ ወገኖች የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጾታዊ ስሜት ያጠቃቸው አድርገው ለመሳል ጥረዋል። ዓላማቸው እውነትን መፈለግ ሳይሆን እምነትን ማናጋት፣ የርሳቸውን አርአያነት ጥላሸት መቀባትና የወሲብ ስሜትን እሳት ማቀጣጠል በመሆኑ ሂሳቸው አያስገርምም።

ለስጋዊ ስሜቱ ተገዥ የሆነ ሰው እንደ ዐረቢያ ባለ በብክለት የተከበበ ክልል ውስጥ እየኖረ፣ በዙሪያው በሚተራመሰው የብክለት ማእበል ሳይሳብ እስከ 25 ዓመት እድሜው ንጹህና ጥብቅ ሆኖ ሊኖር አይችልም። ከዚያ በኋላም በእጥፍ እድሜ የምትበልጠውን ፈት ሴት ለማግባት፣ ብሎም በዙሪያው ወዳሉ በርካታ እንስቶች አይኑን ሳይጥል፣ የፈለጋትን ሴት ለማግኘት ያለውን ሰፊ እድል ሳይጠቀም እድሜውን ሙሉ ከአዛውንት ሚስቱ ጋር ለመኖር አይፈቅድም።

ከኸዲጃ (ረ.ዐ) ሕልፈት በኋላ ዓኢሻን (ረ.ዐ) እና ሌሎች እንስቶችን ማግባታቸው በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልቅናና በምሉእ ባህሪያቸው ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩ ሰበቦችንና ጥበቦችን ያዘሉ ናቸው። የጋብቻዎች ምክንያቶች ምንም ይሁኑ ምን የእስልምና ጠላቶች እንደሚያናፍሱት ስጋዊ ስሜቱን ለማስተናገድ ሊሆን ፈጽሞ አይችሉም። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህ ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ ሊያስተናግዱበት በሚችሉበት ተፈጥሯዊ ጊዜ ባስተናገዱት ነበር። በዚያ ላይ ያኔ ከየትኛውም ሐሳብና ሐላፊነት ነጻ ስለነበሩ ይህን ጥሪ ለማስተናገድ እንቅፋት የሚሆናቸው ነገር አልነበረም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here