ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እድሜያቸው 14 ሲሞላ “ሐርበል ፉጅጃር” በተባለው ጦርነት ላይ ተሳተፉ፡፡ የኪናናህና የቁረይሽ ጎሳ በአንድ ወገን፣ የቀይስ ጎሳ በሌላ ወገን ተሰልፈው ያደረጉት ጦርነት ነው። ለዐረቦች እጅግ አስፈሪ ጦርነት ነበር። የተቀደሰችውን የመካን ከተማ ክብር የገረሰሰ ስለነበር እለቱ “የውመል ፉጅጃር” (የአመጽ ቀን) ተባለ። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፡- “በዚያ ጦርነት ላይ ለአጎቶቼ ቀስት እየሰበሰብኩ አቀብል ነበር።”
ያኔ የአስራ አራት ወይም የአስራ አምስት አመት ልጅ እንደነበሩ ከፊል ዘገባዎች ያመለክታሉ። ሌሎቹ ደግሞ የ20 አመት ልጅ መሆናቸውን ዘግበዋል። የመጀመሪያው ሐሳብ ሚዛን ይደፋል። ምክንያቱም በጦርነቱ ወቅት የነበራቸው ሚና ቀስት እየሰበሰቡ ማቀበል መሆኑ ልጅ እግር እንደነበሩ ያመለክታል። ይህ ተሳትፎ ከልጅነታቸው ጀግንነትን እንዲማሩና የውጊያ ልምድ እንዲቀስሙ አደረጋቸው። ይህ ጦርነት እንደሌሎች የዐረብ ጦርነቶች ሁሉ በኢምንት ምክንያት የተነሳ ነው። ከዚያም የዘረኝነት እሳት አቀጣጠለው። የኢስላም ብርሃን ልቦናዎቻቸውን አስማምቶ ይህን ጥመት እስኪያስወግድላቸው ድረስ እንደዚሁ ነበሩ።
ቁረይሾች ከፉጅጃር ጦርነት እንደተመለሱ “ፈዱል” ለተባለው ስምምነት ለማድረግ ተጠራሩ። ስምምነቱ ከቁረይሽ ባላባቶች መካከል አንዱ በነበረው በጀድዓን ቢን ተይሚ ቤት ውስጥ ተፈጸመ። የስምምነቱ ይዘት መካ ውስጥ ተበድሎ ያገኙትን ማንኛውም ሰው -የከተማዋ ነዋሪ ይሁንም አይሁን- ከጎኑ ቆመው በደሉን ለማካካስ የተስማሙበት ነበር። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከአጎቶቻቸው ጋር በመሆን በስምምነቱ ላይ ተሳትፈዋል። አላህ በመልእክተኝነት ከላካቸው በኋላ እንዲህ ሲሉ ተደምጠዋል፡-
لقد شهدت مع عمومتي حلفًا في دار عبد الله بن جدعان ما أحب أن لي به حُمْر النَّعم، ولو دعيت به في الإسلام لأجبت
“በዐብደላህ ኢቢን ጀድዓን ቤት ውስጥ በተደረገው ስምምነት ላይ ተገኝቻለሁ። ከዚያ ሳልገኝ ቀርቼ በልዋጩ ቀይ ግመል ቢሰጠኝ የምመርጥ አይደለሁ። በእስልምና ውስጥ ሆኜም ወደዚያ ስምምነት ብጋበዝ ግብዣውን እቀበላለሁ።”
ምክንያቱም እርሳቸው የተላኩት መልካም ስነ ምግባራትን ለማሟላት ነው። የስምምነቱ ይዘትም የመልካም ስነ ምግባር አካል ነው። ኢስላም የስምምነቱን አብይ ይዘት ያጸድቃል። ይህ ስምምነት በርካታ ሰዎችን ከበደል ታድጓል።
ከ “ሒልፈል ፉዱል” ስምምነት ከምናገኛቸው ትምህርቶች መካከል ዋነኛው፡- “ከተበዳይ ጎን መቆምና በደሉን ማካካስ” ነው። ውድ አንባቢያችን! በዚህ ረገድ የሚወሳ የግል ተሞክሮ አለህን?