ከመሀይምነት ወደ ፋና ወጊነት፡- የነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ታላቅ ስኬት

1
5572

لَقَدْ مَنَّ اللَّهُ عَلَى الْمُؤْمِنِينَ إِذْ بَعَثَ فِيهِمْ رَسُولًا مِّنْ أَنفُسِهِمْ يَتْلُو عَلَيْهِمْ آيَاتِهِ وَيُزَكِّيهِمْ وَيُعَلِّمُهُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَإِن كَانُوا مِن قَبْلُ لَفِي ضَلَالٍ مُّبِينٍ

“አላህ በምእምናን ላይ ከጎሳቸው የኾነን፤ በእነርሱ ላይ አንቀጾቹን የሚያነብ፣ የሚጠራቸውም፣ መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የኾነን መልእክተኛ በውስጣቸው በላከ ጊዜ፤ በእርግጥ ለገሰላቸው። እነርሱም ከዚያ በፊት በግልጽ ስህተት ውስጥ ነበሩ።” (ኣሊ-ኢምራን 3፤164)

ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተላኩት የሰው ልጅን ለመምራት ነው። የተልዕኮ ዋነኛ ዓላማ ሰዎችን ቅኑን መንገድ ማመላከት፣ ከሽርክ (ከአላህ ውጭ ሌላን አካል ማምለክ) ጨለማ ወደ ተውሂድ (አላህ ብቻ መገዛት) ብርሀን፣ ከበደልና ሀጢያት ጥፋት ወደ ሰላምና በጎ መንገድ፣ ከጠባብ ቁሳዊነት ወደ ዘላለማዊ ፀጋና ስኬት ማሸጋገር ነበር።

በመጀመሪያው የሀበሻ ስደት፤ ታላቁ ሰሀባ ጃዕፈር ኢብኑ አቡጣሊብ (ረ.ዐ) ከሀበሻው ንጉስ ነጃሺ ፊት ያደረገው ንግግር አረቦቹ የነበሩበትን ድንቁርና ግልጭልጥ አድርጎ ያሳየ ነበር።

“ንጉስ ሆይ! እኛ የድንቁርና (ጃሂሊያ) ጨለማ ያካበበን ህዝቦች ነበርን፤ ብዙ ጣኦታትን እምንገዛ፣ የሞተንም እንስሳ ስጋ የምንመገብ፣ አስነዋሪ ተግባራትን የምንፈፀም፣ አደራን የማንጠብቅ፣ ጎረቤቶቸችን የምናስከፋ፣ ዝምድንና የምንቆርጥና ጠንከራው ደካማውን የሚጮቅንበት ህዝብ ነበርን። አላህ ከመካከላችን ከራሳችን ህዝብ መልዕክተኛ እስከላከልን ድረስ…” (ቡኻሪ 1649)

ከታሪክ አስተምሮት አንፃር ዋና ዋና የጃሂሊያ ችግርችን በአስር ከፍለን ማየት እንችላለን:-

  1. ሺርክ (አጋሪነት) ወይም ኢአማኒነት፡- ብዙ አማልክትን ያመልካሉ ወይም ለአምልኮ ወይም ለፈጣሪ ደንታ የላቸውም፤

2. ጎሰኝነትና ዘረኝነት፡- ሁሉም ማህበረሰብ በጎሳና በዘር የተከፋፈለ ብሎም የህይወቱ ዋነኛ ዓላማ ጎሳውን ዘሩን የበላይ ማድረግ ነበር። የዘረኝነት፤ የጎሰኝነት፤ የቀለም ጥላቻ ስሜት ተፀናውቶታል፡

3. ደካሞችና ድሆችን መበዝበዝ፡- ባርነት የሸቀጥ ያህል የበረከተበት፤ ሀብታሙ ደሀውና ችግረኛውን የሚበዘብዝበት ዘመን ነበር።

4. ኢ-ፍትሀዊነትና ሁለቲዮሽ መመዘኛ፡- የፍትህ ፍሬዎች የከሰሙበት፤ የእኩልነት ፍና የጠፋበት ዘመን ነበር። ጥሩ ነገር ብሎ ማለት ለራስና ለጎሳ ጥሩ ገፅታን የሚፈጥር መጥፎም ብሎ ማለት ለስራና ለጎስ ህይወት እክል የሆነ ማለት ነበር። ወጥ የሆነ ፍትሀዊ ሚዛን አልነበረም።

5. ህጻናትን መግደል፡- በተለይም ሴት ህፃናት ክብርና ልቅና በሚል አጉል ባህል ብሎም ድህነትን በመፍራት በጨልቅላታቸው ይቀጯው ነበር።

6. እፍረተ ቢስነት፡- እፍረት (ሀያእ) የሚባል ነገር የተነፈጉ ህዝቦች ነበሩ። አንዳንዴ በካዕባ ዙሪያ እርቃናቸውን ጠዋፍ (በካዕባ ዙሪያ የሚደረግ ፀሎት) ያደርጉ ነበር።

7. የመጠጥ ፍቅር፡- አስካሪ መጠጥና እፆች ከህይወታችው የዕለት ተዕለት ተግባራት ውስጥ ታላቅ ሰፍር ነበራቸው፤ በጣም ያፈቅሩትም ነበር።

8. አራጣና ወለድ፡- አጠቃላይ የህብረተሰቡ ኢኮኖሚ መሰረት ያደረገው አራጣን ሲሆን የተለያዩ የወለድ ሰርዐቶች ተንሰራፍተው ነበር።

9.ዝሙትና ሴተኛ አዳሪነት፡- በወንዱም ሆነ በሴቶቹ ልቅ የግብረ-ስጋ ግንኙነት የተለመደ ነበር፤ የተለያዩ የወሲብ መፈፀሚያ ስርዐቶችም ተዘርግተው ነበር።

10. በትንሳኤ ቀን ወይም በመጨው አለም ሰለሚኖር ተጠያቂነት አለማመን፡- ከሞት በኋላ ተነስተው በሰሩት ተግበራት እንደሚጠየቁ አያምኑም ነበር።

ከዚህ ኢ-ፍትሀዊነትና ስርዓት አልበኝነት በተጨማሪ የተደራጀ የሀይማኖት ስርዐት፤ መለኮታዊ መጸሀፍት፤ ሀይማኖታዊ ህጎችና እሴቶች፤ የተማከለ መንግስታዊ ስርዐት አልነበራቸውም።

ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) እነዚህን ነገሮች በሙሉ በአጭር ጊዜ ቀያየሩት። የነበሩበትን የእምነት ስርዐት፣ ህግ፣ ስነምግባር፣ የማህበረሰባዊ ፤ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካው ሁኔታዎች ቀየሩት። ከሰማያዊ መፅሀፍ፤ ከአላህ ዘንድ ከተላከ ህግና ስርዓትም ጋር አስተዋውቋቸው፤ የኢባዳ ስርዐት ዘረጉላቸው፤ የትምህርትና የመማሪያ ተቋማትም አቋቋሙላቸው፤ በእምነት ወንድማማችነትና እህትማማችነትመ አንድ አደረጓቸው፤ ታማኝና ስልጡን ህዝቦች አደረጓቸው፤ በተጨማሪም የሰው ልጆችን ወደ ቅን መንገድ እንዲመሩ ታላቅ ተልኮንም አሸከሟቸው። ታላቁ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን ሁሉ ያከናወኑት በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር።

ከዚህ አንጻር አሜሪካዊው ምሁር ማይክል ሀረት በሰው ልጅ ታሪክ ስኬታማና ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ የአለማችን ምርጥ መቶ ሰዎችን በዳሰሰበት መፅሀፍ ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ቁጥር አንድ ማድረጉ የሚገርም ጉዳይ አይሆንም። ፈረንሳዊው የታሪክ ምሁር እንዲሁ ሲናገሩ “የምጡቀነት (geninous) ሶስት መለኪያዎች የአላማ ታላቅነት፤ የመንገድህ (ስልት) አጭርነትና የውጤትህ ፍቱንነት ከሆነ ከነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሊወዳደር የሚደፍር ማነው?” ሌሎች ይህና ይህን የመሳሰሉ ምስክሮች ሀቀኛ ከሆኑ የታሪክ ምሁራን ተሰጥተዋል።

ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የስኬት ሚስጥሮች ምን ነበሩ? የመጀመሪያው የአላህ (ሱ.ው) የማያቋርጥ እርዳታና ድንቅ መመሪያዎችን ያዘለው የቁርአን መልዕክት ሲሆን ይህንን መልዕክት ለመሸከም የነበራቸው ድንቅ ስብዕና፤ እዝነትና ርህራሄን የተላበሰው ባህሪያቸው የነበራቸው ቁርጥኝነትና የከፈሉት መስዋትነት ታላቅ አስተዋፅኦ ነበረው።

ሙስሊሙ ኡማም ነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) በጣሉት የስኬት መሰረት ላይ ግንባታውን በመቀጠል ለአለም ስልጣኔና የባህል እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። የሳቸውን አሰተምሮትና ምሳሌ እሰከተከተሉበት ጊዜ ድረስም ስኬታማ ነበሩ።

አሁን ግን የሰው ልጅች በዋነኝነት ሙስሊሞች ጉዞውን ወደ ቀድሞው የማሀይምነትና ጃሂሊያ እየመለሰ ይገኛል። አስሮቹ የቀደምት ጃሂሊያ መገለጫዎች ባሉበት ሁኔታ ወይም በከፋ መልኩ ብቅ ብለዋል። የዘመናችን ትልቁ ፈተናም የሰው ልጅን ከዚህ ጨለማ ማነው የሚታደገው የሚለው ነው። ሁላችንም የነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የታሪክ ማህደር እንቃኝ ዘንድ ግድ ይላል።ይህንንም መሰረት በማድረግ ራሳችንን ቤተሰባችንና ማህበረሰባችን ማዳን ይጠበቅብናል። ለሲራቸው (ህይወት ታሪካቸው)ና ሱናቸው (ምሳሌያቸው) ትኩረት በመስጠት ህይወታችንን ልንመራ ይገባል።

لَّقَدْ كَانَ لَكُمْ فِي رَسُولِ اللَّهِ أُسْوَةٌ حَسَنَةٌ لِّمَن كَانَ يَرْجُو اللَّهَ وَالْيَوْمَ الْآخِرَ وَذَكَرَ اللَّهَ كَثِيرًا

“ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አልላችሁ።”(አል-አህዛብ 33፤21)

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here