“አንተ አስፈራሪ ብቻ ነህ። ለሕዝብም ሁሉ መሪ አላቸው።” (አል-ረዕድ 13፤7)
ይህ የነቢዩ ህይውት ድንቅ ክፍል ነው፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) ለሰው ልጅ ሁሉ ምርጥ አርአያ ናቸው። መመሪያና መንገድም ጭምር። ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በፊት የተላኩ ሌሎች ነቢያት ለህዝቦቻቸው ብቻ የተላኩና መልእክታቸውም በጊዜ የተገደበ ነበር። የነቢያቶች መደምደሚያና የመጨረሻው ነብይ የሆኑት ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ግን ለሁሉም ህዝቦችና ለሁሉም ጊዜ (እስከ አለም ፍጻሜ) በሚሆን መልዕክት ነበር የተላኩት።
በአስር የተለያዩ የቁርዐን አንቀጾች ለነቢዩ የመጣላቸው መልእክት “መመሪያና እዝነት” (ሁዳ ወራህማ) በሚል ሁለት ምርጥ ቃላት ጥምረት ተጠቅሷል። አል-አንዓም 6፡157፤ አል-አዕራፍ 7:52፣203፤ ዩኑስ 10፤57፤ ዩሱፍ 12፡111፤ አል-ነህል 16፡64፣89፤ አልነሞል 27፡77፤ ሉቅማን 31፡3፤ አል-ጃሲያህ 45፡20 መመልከት ይቻላል። እዚህ ጋ እነዚህ ሁለት ባህሪያት (መመሪያና እዝነት) (ሁዳ ወ-ራህማ) ለምን በጥምረትና በተደጋጋሚ ለነቢዩና በሳቸው በኩል ለተላከው መልእክት መገለጫ እንደሆኑ ማስተንተን ጠቃሚ ነው።
“ሁዳ” የሚለው ቃል በግርድፍ “መመሪያ” ማለት ሲሆን “ሂዳያ” ከሚለው ቃል የመጣ ሆኖ እናገኘዋለን። “ሂዳያ” መምራት እና ማሳየት የሚሉ ትርጉሞችን ይይዛል። ከዚህ በተጨማሪም “ሀዲያ” የሚለው ቃልም የዚሁ ግንድ ቅርንጫፍ ሲሆን ትርጉሙ “ስጦታ” ማለት ነው። በዚህ መሰረት “ሂዳያህ” ማለት ከአላህ ለፍጥረታቱ የተሰጠ ስጦታ ነው ማለት እንችላለን። እንደ ታዋቂው የቁርአን ተንታኝ ኢማም ራጊብ አል-ኢስፈሀኒ ገለፃ ሂዳያህ “ባማረና በመልካም ሁኔታ መንገድን ማመላከት ወይም ወደ ሚፈለገው መምራት” ማለት ነው። ይህ ማለት ማብራራትና ማመላከት (አል-ኢርሻድ ወል ደላላህ) ወይንም ወደሚፈለገው ዓላማ ይደርስ ዘንድ መርዳትና መደገፍ ብሎም ማስቻል(አተውፊቅ ወል ኢልሀም) ማለት ነው። የመጀመርያው የነቢያትና የደጋጋ የአላህ ባርያዎች ስራ ሲሆን ሁለተኛውን የአላህ ብቻ የተተወ ነው። በሌላ በኩል “ራህማ” የሚለው ቃል “እዝነት፣ ፍቅርና ርህራሄ” ማለት ሲሆን በቁርዐን ውስጥ “አል-ራህማን እና አል-ረሂም” (ሩህሩህና በጣም አዛኝ) የሚሉት ስሞች በተደጋጋሚ ተጠቅሰዋል፤ ነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ደግሞ “ራህመትን ሊል አለሚን” (የአለማት እዝነት) ተብለዋል።
የነዚህ ቃላት (መመሪያና እዝነት) ጥምረት የሚፈጠረው ትምህርት በሁለት መልኩ ይታየል። የመጀመሪያው የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት እውነት፤ ትክክለኛና ፍትሀዊ መሆኑንና መልዕክቱ ዋነኛ የእዝነትና የርህራሄ መልዕክት መሆኑን ያስረዳል። መልዕክቱ ከቸጋራነትና ሻካራነት በራቀ መልኩ ገርና በምህረቱ የተከሸነ ነው።በሁለተኛ ደረጃ ይህ በነቢዩ በኩል የመጣው መልእክት በዚች አለም ለቀን ተቀን ህይወታችን መመሪያ እንዲሆንና የአላህ ምህረት እንድናገኝ እንዲሁም በመጪው አለም ስኬትና መድህን እንድናገኝ የሚያደርግን ሁነኛ መሳረያ ነው።
የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ምራቻ (guidance) ሶስት ባህሪዎችን በትኩረት እንቃኝ፡-
- ሁሉንአቀፍ
2. እዝነት የተሞላበት
3. አለም አቀፋዊ
- ሁሉንአቀፍ
የነቢዩ መንገድ ሁሉን አቀፍ ነው ስንል ሁሉንም የህይወት መስኮችን ያካተተና ሁሉንም የተስተካከለና ያማረ ያደርጋል ማለት ነው። መመሪያው ትክክለኛ እምነትን፤ የተስተካከለ የአምልኮ መንገድን፤ ምርጥ ስነ-ምግባርን፤ የተቃና የግብይት ስርዓትን፤ ከቤተሰብ ጋር ያለ ግንኙነት፤ከወዳጅና ጠላት ጋር የሚኖርን ግንኙነት ሁሉ ይዳስሳል። ባጠቃላይ እንደ ግለሰብና እንደ ማህበረሰብ ሊኖረን የሚገባውን ሚና አጠቃሎ የያዘ ሲሆን ሁሉም ነገር ሚዛናዊና ገር በሆነ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት እናገኛለን። በዚህ መስክ የነቢዩን አጠቃላይ የህይወት መመሪያ ሰብስቦ የዘገበውን የታላቁን የኢስለም ሊቅ የኢብነል ቀይም ስራ የሆነውንና በስድስት ጥራዝ የተዘጋጀውን “ዛዱል ሚዓድ ፈሀድይ ኸይረል ኢባድ” ማየት ያሻል። ፀሀፊው ከግል እስከ ህብረተሰብ ባሉ ዝርዝር የህይወት መስኮች ከነቢዩ ሙሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) ህይወት ምሳሌ በማጣቀስ ያቀርባሉ።
2. እዝነት የተሞላበት
ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) መልካምና ገር መምህር ነበሩ፤ አስቸጋሪና ግትር አልነበሩም። ሁልጊዜም ለባልደረባዎቻቸው በንፁህና ገር (ሀነፊየቱ-ሰምሀእ) በሆነ ቅን መልዕክት የተላኩ እንዳሆኑ ያስተምሩ ነበር (ሙስነድ አህመድ 21916)። ሰዒድ ኢብኑ ቡርዳህንና ሙዓዝ ኢብኑ ጀበልን ወደ የመን በላኩ ወቅት ያሉትን እንዲሁ እናስታውስ፡-
يسرا ولا تعسرا وبشرا ولا تنفرا وتطاوعا (البخارى(
“አግራሩ አታካብዱ አበስሩ አታስደንብሩ በጋራም ስሩ።” (አል-ቡኻሪ)
ከነብዩ መልካም የማስተማሪያ ስልቶች አንዱ ባልደረቦቻቸውን በሁሉም ጊዜ የሚገስፁና የሚያስተምሩ አልነበሩም፤ ይልቁንስ ቦታና ጊዜ እንዲሁም አጋጣሚዎችን በመምረጥና በመጠቀም ያስተምሩ ነበር።
ኢብኑ መስዑድ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ:-
كان النبي- صلى الله عليه وسلم- يتخولنا بالموعظة في الأيام؛ كراه السآمة علينا. (البخارى(
“ነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) እኛን በማስተማሩ ሂደት እንዳንሰላች አመች ጊዜ ፈልገው ይጠቀሙ ነበር” (አል-ቡኻሪ)
3. አለም አቀፋዊ
የነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት አለም አቀፋዊ ነው። በአንድም መልዕክታቸው ላይ ለአረቦች ወይንም በጊዜው ለነበሩት ሰዎች ተብሎ የተተው ነገር የለም። ቁርአን የፈቀደው ነገር በማንኛውም ጊዜ ለሁሉም ሰው ጠቃሚና መልካም ሲሆን የከለከላቸው ነገሮችም እንዲሁ በማንኛውም ጊዜና ለሁሉም ሰው ጎጂና መጥፎ ናቸው። በየትኛውም ዘመን ያሉ ሰዎች የነብዩን መልዕክት ቢጠቀሙበት ውጤታማ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። ከዚህም ሁሉ ጋር ግን ነቢዩ በፍፁም እምነቱን በሌሎች ላይ በግድ አልጫኑም ነበር። ቁርዐን በሀይማኖት ማስገደድን በጥብቅ ከልክሎታል። (አል-በቀራህ 2፤256)
ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የሰው ልጅን መንገድ በማሳየት በኩል የተሳካላቸው ነበሩ። ነቢዩን አላህ መርጦ መልዕክቱን ሲሰጣቸው በጊዜው የነበሩት ብቸኛ ሙስሊም እርሳቸው ብቻ ነበሩ። ከብዙ ድካም፤ ልፋትና፤ ህመም በኋላ በአላህ ፍቃድ ትውልድን አቀኑ፤ ብሎም ሌሎችን ሊመሩና ምሳሌ ሲሆኑ የሚችሉ ሰዎችን አፈሩ፤ ተከታዮቻቸውን አንዲትን የእርሳቸውን መልዕክት በአግባቡ የተረዳ ሰው ያስተምር ዘንድ ሰበኩ፤ በሀያ ሶስት ዓመት ውስጥ መልዕክቱ መላውን አረቢያ አዳረሶ ወደ ውጪ ወጣ። ሰዎች በገፍ ወደ እምነቱ ይጎርፉ ጀመር። በስልሳ ሶስት ዓመታቸው ከዚህች ዓለም ሲለዩ የአረቢያን ሙሉ በሙሉ ቀያይረዋት ነበር። የተሟላ እምነት፤ የተጠናከረ መንግስት፤ የተቀናበረ የትምህርትና የእውቀት ስርዓት፤ የተቃና ስነ-ምግባርንና ምርጥ ስብዕናን አሰፈኑ ብሎም ላማረ ስልጣኔ መሰረት ጣሉ። የአላማ ሰዎችንና ለሰው ልጅ ቅኑን መንገድ የሚያመላክቱ ህዝቦችን አበጁ። ከኢስላም በፊት ወና የነበረው ታሪካቸውን በብርሀናማ ገድሎች አሳመሩት፤ በተዋቡ የስልጣኔ እርከኖች አሸበሩቁት።
እጅግ ብዙ ተንታኞች፤ የታሪክ ተመራማሪዎችና ፊላስፎች ይህንን አለምአቀፍ፣ ሁለንተናዊና ስኬታማ የሆነውን የነቢዩን ተልዕኮ እውነታ አፅድቀዋል። ድንቅ ኢንጊሊዛዊ ፀሀፊ ጆርጅ በርናንድ ሾው እንዲህ ይላሉ:- “ሁሌም የሙሀመድን እምነት የምሰጠው ቦታ እጅግ የላቀ ነው፤ ይኸውም ከምርጥ መገለጫዎቹ የመነጨ ነው። ይህ እምነት ከየትኛውም የአለም ተለዋዋጭ መልክ ጋር በየትኛው ቦታና ጊዜ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ብቸኛው እምነት ነው። ስለዚህ ድንቅ ሰው (ሙሀመድ) በጥልቀት አጥንቻለሁ በኔ አመለካከት ‘የክርስቶስ ጠላት’ ከመባል እጅግ የራቀና ይልቁንም ‘የሰው ልጅ አዳኝ’ ሊባል ይገባዋል።” (ዘ ጄኒዩን ኢስላም ጥራዝ 1፣ ቁ.8፤ 1936)
አሜረከዊው የታሪክ ሰው ማይክል ሀርት በታሪክ የታዩና ተፅዕኖ ያሳደሩ የአለምን ምርጥ ሰዎች ከደረጃ ባስቀመጡበት “ዘ 100፡ ኤ ራንኪንግ ኦፍ ዘ ሞስት ኢንፉሌንሺያል ፐርሰን” በተሰኘው መፅሀፍ ለምን ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመጀመሪያው ደረጃ እንደሰጣቸው ሲናገር እንዲህ ይላል:-
“በእርግጥ በታሪክ የአለማችን ምርጥና ታላቅ ተፅዕኖ ያሳደሩ ሰዎች ተርታ ለሙሀመድ አንደኛ ደረጃ መስጠቴ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊያስገርምና ሌሎችን ሊያጠያይቅ ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን በአለማዊው ሆነ በሀይማኖታዊው ዘርፍ ሙሉ በሙሉ የተሳካላት ብቸኛ ሰው ሙሀመድ ነው።” (ዘ 100፡ ኤ ራንኪንግ ኦፍ ዘ ሞስት ኢንፉሌንሺያል ፐርሰን፤ ኒዮርክ፤1978፣ ገፅ 33)
ይህን መመሪያ በአግባቡ ተከትለን መተግበሩ የወቀቱ ጥያቄና የእኛ ስራ ነው። እነዚያ ቀደምት አባቶቻችን የነበሩበትን የብርሀን ዘመን ላይ ለመድረስ ካለንበት የችግርንና የሰቆቃ አረንቋ ለመውጣት የዚህን ዓብይ ምሳሌ መስመር በመስመር ልንከተል ግድ ይላል።
ሁላችንንም አላህ ይርዳን አሜን!!