የብስራቱ ዜና፦ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም

0
5831

ነብዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ለሰው ልጅ ምርጥ አርአያ ተደርገው የተላኩ ነብይ ናቸው። ለሳቸውም ብዙ መገለጫዎችና መጠሪያዎች ያሏቸው ሲሆን ከነዚህ መካከል የእዝነቱ ነቢይ (ረህማ) የቅኑን መንገድ መሪ ነቢይ (ሂዳያ)፣ አስጠንቃቂው መልዕክተኛ (ኢንዛር) ወዘተ ይጠቀሳሉ። በዚህች ጽሁፍ ከነቢዩ መጠሪያዎች መካከል ውስጥ አብሳሪው (በሺር) የሚለውን ስማቸውን እንመልከት።

በአጠቃላይ በቁርዓን የተጠቀሱት ነቢያት አብሳሪና አስጠንቃቂ (ሙበሺሪን ወሙንዚሪን) በመባል ተወስተዋል።

ነቢዩ ሙሀመድም የዚህ መጠሪያ ባለቤት ሲሆኑ ቁርአንም በተደጋጋሚ የዘህን የነቢዩን ሚና በተደጋጋሚ ገልጾታል።

ኢንዛር ” የሚለው የአረብኛ ቃል ማስጠንቀቂያ የሚል ብቻ ትርጉም አያመላክትም። “ኢንዛር” ማለት ቅድመ-ጥንቃቄን፣ ቅድመ-ዝግጅት ወደፊት ለሚገጥሙ ችግሮች ቀድሞ መታጠቅን፣ ራስን ከሚከሰቱ መከራዎች ማራቅንና መከላከልን በሙሉ ያካትታል። በመሆኑም “ኢንዛር” ከማሸበር ወይም ከማስፈራራት (ተህዲድ) የሚመነጭ ሳይሆን ከርህራሄና ከእዝነት የሚፈልቅ የፍቅር ማመላከቻ መሆኑን ያሳያል። ለዚሁም ነው ነቢዩሙሀዲድ ከሚለው ይልቅ ሙንዚር ብሎ የሰየማቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ነብዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “በሺር” (አበሳሪና መልካም-ዘካሪ) በመባል ተጠርተዋል። ማብሰር፣ ሲያበረታታ፣ በጥሩ ስራ ላይም ጥንካሬን ይጨምራል።

ማስጠንቀቅና ማብሰር ለአካላዊና ለመንፈሳዊ እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ስለሆነም ጥሩ መምህር፣ ጥሩ አለቃ፣ ጥሩ መሪ ወዘተ ሁለቱን ባህሪያት በሚዛናዊነት ያስተምራል። ማስጠንቀቅን ማዘውተር ሰዎችን ያስፈራራል፤ ያስደነግጣል፤ ሀይልን ያከስማል፤ መሸሽንም ይወልዳል። እንደዚሁም ብስራትን አለቅጥ ማብዛትም ያሰንፋል፤ ታካችም ያደርጋል። ኢስላም ሁለቱንም በተሟላና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ማስኬድን ይመክራል። አላህ እነደዚሁም ነቢዩ የነዚህ ባህሪያት ባለቤት አንደሆኑ ቁርኣን በግልጽ ያስተምራል። አላህ ኃያል፤ አሸናፊ፣ ፍትሀዊና ቅጣተ ብርቱ ከመሆኑ ጋር አፍቃሪ፣ ርህሩህ፣ ደግና የታላቅ እዝነት ባለቤትም ነው፤ሀጢያትን ይምራል፤ መልካምን ስራ ይቀበላል። ቁርአን በእንደዚህ አይነት ሁለቲዮሽ ገለፃ የተሞላ ነው። ጀነትና በጀሃነምን አንድ ላይ ያነሳቸዋል፣ በአምላከዊ ፍትህና በመለኮታዊ ፍቅርና ምህረት መካከል ሚዛናዊ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ የሚያመለክተው፣ ማብሰርና ማስፈራራት ሁለት ተቃራኒ ባህሪያት ሳይሆኑ አብረው የሚጓዙ ተደጋጋፊ ጉዳዮች መሆናቸውን ነው።

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አበሳሪ ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ከአላህ ብስራቶች ውስጥ አንዱ መሆናቸውን ልናውቅ ይገባናል። ከነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በፊት የነበሩ ሁሉም ነቢያት ስለ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ያበስሩ እንደነበር ቁርኣን ይናገራል

الَّذِينَ يَتَّبِعُونَ الرَّسُولَ النَّبِيَّ الأمِّيَّ الَّذِي يَجِدُونَهُ مَكْتُوبًا عِنْدَهُمْ فِي التَّوْرَاةِ وَالإنْجِيلِ يَأْمُرُهُمْ بِالْمَعْرُوفِ وَيَنْهَاهُمْ عَنِ الْمُنْكَرِ وَيُحِلُّ لَهُمُ الطَّيِّبَاتِ وَيُحَرِّمُ عَلَيْهِمُ الْخَبَائِثَ وَيَضَعُ عَنْهُمْ إِصْرَهُمْ وَالأغْلالَ الَّتِي كَانَتْ عَلَيْهِمْ فَالَّذِينَ آمَنُوا بِهِ وَعَزَّرُوهُ وَنَصَرُوهُ وَاتَّبَعُوا النُّورَ الَّذِي أُنْزِلَ مَعَهُ أُولَئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

“ለእነዚያ ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ የኾነውን መልክተኛ የሚከተሉ ለኾኑት (በእርግጥ እጽፍለታለሁ)። በበጎ ሥራ ያዛቸዋል። ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል። መልካም ነገሮችንም ለነርሱ ይፈቅድላቸዋል። መጥፎ ነገሮችንም በእነርሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል። ከእነሱም ላይ ሸክማቸውንና እነዚያንም በእነርሱ ላይ የነበሩትን እንዛዝላዎች (ከባድ ሕግጋቶች) ያነሳላቸዋል። እነዚያም በእርሱ ያመኑ ያከበሩትም የረዱትም ያንንም ከእርሱ ጋር የተወረደውን ብርሃን የተከተሉ እነዚያ እነሱ የሚያድኑ ናቸው።” (አል-አዕራፍ 7፣ 157) ።

ከዚህ በተጨማሪ ነቢዩ ዒሳ ስለ ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም መምጣት ብስራት መናገራቸውን አላህ በቁርኣኑ ሲያትት እንዲህ ይላል፡-

وَإِذْ قَالَ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ يَا بَنِي إِسْرَائِيلَ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ مُصَدِّقًا لِمَا بَيْنَ يَدَيَّ مِنَ التَّوْرَاةِ وَمُبَشِّرًا بِرَسُولٍ يَأْتِي مِنْ بَعْدِي اسْمُهُ أَحْمَدُ فَلَمَّا جَاءَهُمْ بِالْبَيِّنَاتِ قَالُوا هَذَا سِحْرٌ مُبِينٌ

“የመርየም ልጅ ዒሳም፡- ‘የእስራኤል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደእናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ’ ባለ ጊዜ (አስታውስ)። በግልጽ ተዓምራቶች በመጣቸውም ጊዜ ‘ይህ ግልጽ ድግምት ነው’ አሉ።” (አስ-ሷፍ 61፣ 6)።

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ብስራት ሆነው ወደዚች ምድር ከመጡ በኋላ ለኛ ሌሎች ብስራቶችን አመጡ።

የመጀመሪያው ብስራትም ቁርኣን ነው። የቁርኣን ሌላ ስሙም (ቡሽራ) የሚለው እንደሆነ አላህ በአል-ነሕል (16፤89) እና በአል-ነምል (27፤2) ምዕራፎች ይናገራል፡-

وَنَزَّلْنَا عَلَيْكَ الْكِتَابَ تِبْيَانًا لِكُلِّ شَيْءٍ وَهُدًى وَرَحْمَةً وَبُشْرَى لِلْمُسْلِمِينَ

“መጽሐፉንም ለሁሉ ነገር አብራሪ፣ መሪም፣ እዝነትም፣ ለሙስሊሞችም አብሳሪ ኾኖ ባንተ ላይ አወረድነው።” (አል-ነሕል 16፤ 89)

هُدًى وَبُشْرَى لِلْمُؤْمِنِينَ

“ለምእምናን መሪና ብስራት ናት።” (አል-ነምል 27፤ 2)

ሁለተኛው ደግሞ በጥፋቶቻችንና በወንጀሎቻችን ምንም ያህል ቢከፉ ተስፋ እንዳንቆርጥ የነገሩን ይጠቀሳል። አላህ ሁሌም የተውበት በር እስከ ህይወት የመጨረሻ ደቂቃ ድረስ ክፍት እንዳደረጋትና የኛን መመለስና መፀፀት ለመቀበል ፈጣን መሆኑንም አስተማሩ። ለፍቅሩና ምህረቱ ወሰን የላቸውም፤ ሊቀጣ ግድ አይለውም፤ ሊያልፍ፣ ለሸፍንና ይቅር ሊል ይችላል። ይህን በተመለከተ ዝነኛው የቁርዐን አያ አላህ እንዲህ ይላል፡-

قُلْ يَا عِبَادِيَ الَّذِينَ أَسْرَفُوا عَلَىٰ أَنفُسِهِمْ لَا تَقْنَطُوا مِن رَّحْمَةِ اللَّهِ إِنَّ اللَّهَ يَغْفِرُ الذُّنُوبَ جَمِيعًا إِنَّهُ هُوَ الْغَفُورُ الرَّحِيمُ

“በላቸው እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ። አላህ ኃጢኣቶችን በመላ ይምራልና። እነሆ እርሱ መሓሪው አዛኙ ነውና።” (አል-ዙመር 39፤ 53) ።

ሦስተኛው ድንቅ ብስራት ደግሞ በመጪው አለም “ሻፊ ” (አማላጅ) መሆናቸውን የገለፁት ነው። በቋንቋ ደረጃ “ማማለድ” ማለት አንድን አካል ሌላውን አካል ይማፀንለት ዘንድ “መሸምገል” ማለት ሲሆን በኢስላም “ሸፋዓ” የሚባለው ጉዳይ በፍርዱ ቀን ለነቢዩ ከተሰጡ ድንቅ ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው። ሸፋአ በቁርዐንና በሀዲስ የተረጋገጠ ሲሆን ልክ እንደ ዱአ ነው፤ ግለሰቡ ለራሱ ወይም ለሌላው ሰው ዱአ እንደሚያደርገው ነው። ነቢዩ ሙሀመድም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከየትኛውም ጊዜ በላይ አማላጅ በሚያስፈልግበት የጭንቁ እለት (የፍርድ ቀን) ፀሐይ ሰዎችን የአንድ ስንዝር ያህል ርቀት በቀረበችበት ወቅትና ሰዎች አንገታቸው ድረስ በላብ በተጠመቁበት ጊዜ፣ ረሱል በአማላጅነት “አላህ ህዝቦቼን ማርልኝ” በማለት ይማጸናሉ። ስለዚህም “ሸፋዓ” መጥፎ ተግባርን በምድር ላይ ለሰሩ ሰዎች ተስፋን ይሰጣል። ሁሌም ከአላህ ተስፋን እንዳይቆርጡ ያደርጋል። ልክ አንድ ሰው ከጥፋት በኋላ በተውበት ወደ አላህ ሲመለስ በአላህ ምህረት ላይ ተስፋ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ በፍርድ ቀን ለሱ ከጥፋቱ አላህ ይምረው ዘንድ የሚያማልደውና የጀነትን ምርጥ ስፍራዎች የሚለግሰው አካል መኖሩን ሲያውቅ ልቡ በተስፋ ይሞላል።

ቁርዐን “ሸፋዓ” (ምልጃ)ን እንዴት እንደተመለከተው በአግባቡ መረዳት ያሻል። ቁርዐን የተወሰኑ የምልጃ አይነቶችን ሲያወግዝ የተወሰኑትን ተቀብሎታል። በዚህ ጉዳይ ቁርአንን በአንክሮ ስንመለከት አምስት አይነት ሸፋአን የሚዳስሱ የቁርዐን አንቀጾችን እናገኛለን፡-

  • ከሃዲያን የ “ሸፋዓ” (ምልጃ) ተጠቃሚ እንደማይሆኑ ቁርዐን ተናግሯል።

وَكُنَّا نُكَذِّبُ بِيَوْمِ الدِّينِ حَتَّىٰ أَتَانَا الْيَقِينُ فَمَا تَنفَعُهُمْ شَفَاعَةُ الشَّافِعِينَ

“በፍርዱ ቀንም እናስተባብል ነበርን። እርግጠኛው (ሞት) እስከ መጣን ድረስ። የአማላጆችም ምልጃ አትጠቅማቸውም።” (አል-ሙደሲር 74፣46-48)።

  • ጣኦታትና ከአላህ ውጪ ሀይል እንዳላቸው ሲቆጠሩና ሲመለኩ የነበሩ ሁሉ የማማለድም ሆነ የመጠየቅ ስልጣን የላቸውም። ቁርኣን ይህን ሲገልፅ፡-

وَلَقَدْ جِئْتُمُونَا فُرَادَىٰ كَمَا خَلَقْنَاكُمْ أَوَّلَ مَرَّةٍ وَتَرَكْتُم مَّا خَوَّلْنَاكُمْ وَرَاءَ ظُهُورِكُمْ وَمَا نَرَىٰ مَعَكُمْ شُفَعَاءَكُمُ الَّذِينَ زَعَمْتُمْ أَنَّهُمْ فِيكُمْ شُرَكَاءُ لَقَد تَّقَطَّعَ بَيْنَكُمْ وَضَلَّ عَنكُم مَّا كُنتُمْ تَزْعُمُونَ

“መጀመሪያም ጊዜ እንደ ፈጠርናችሁ ኾናችሁ የሰጠናችሁን ሁሉ በጀርባዎቻችሁ ኋላ የተዋችሁ ስትኾኑ የሰጠናችሁን ሁሉ በጀርባዎቻችሁ ኋላ የተዋችሁ ስትኾኑ ለየብቻችሁ ኾናችሁ በእርግጥ መጣችሁን? እነዚያንም እነሱ በእናንተ ውስጥ (ለአላህ) ተጋሪዎች ናቸው የምትሉዋቸውን አማላጆቻችሁን ከእናንተ ጋር አናይም። ግንኙነታችሁ በእርግጥ ተቋረጠ። ከእናንተም ያ (ያማልደናል) የምትሉት ጠፋ (ይባላሉ)።” (አል-አንዓም 6፣94)

  • ከአላህ ውጪ የሚረዳ አካል የለም። ቁርኣን፡-

وَأَنذِرْ بِهِ الَّذِينَ يَخَافُونَ أَن يُحْشَرُوا إِلَىٰ رَبِّهِمْ لَيْسَ لَهُم مِّن دُونِهِ وَلِيٌّ وَلَا شَفِيعٌ لَّعَلَّهُمْ يَتَّقُونَ

“እነዚያንም ከእርሱ ሌላ ረዳትና አማላጅ የሌላቸው ሲኾኑ ወደ ጌታቸው መስሰብሰብን የሚፈሩትን ይጠነቀቁ ዘንድ በርሱ (በቁርኣን) አስፈራራ።” (አል-አንዓም ÷51 ) ይላል።

  • በፍርድ ቀን አላህ ለአንዳንድ ሰዎች ለሌሎች እንዲያማልዱ ፍቃድ ይሰጣል። ቁርኣን፡-

يَوْمَئِذٍ لَّا تَنفَعُ الشَّفَاعَةُ إِلَّا مَنْ أَذِنَ لَهُ الرَّحْمَٰنُ وَرَضِيَ لَهُ قَوْلًا

“በዚያ ቀን ለእርሱ አልረሕማን የፈቀደለትንና ለእርሱም ቃልን የወደደለትን ሰው ቢኾን እንጅ ምልጃ (አንድንም) አትጠቅምም።” (ጧሃ 20፣ 109)

  • አላህ የወደደላቸው ሰዎች በእለቱ የምልጃ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ቁርኣን፡-

يَعْلَمُ مَا بَيْنَ أَيْدِيهِمْ وَمَا خَلْفَهُمْ وَلَا يَشْفَعُونَ إِلَّا لِمَنِ ارْتَضَىٰ وَهُم مِّنْ خَشْيَتِهِ مُشْفِقُونَ

“በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል። ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም። እነርሱም እርሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተጨናቂዎች ናቸው።” (አል-አንቢያእ፤ 28 )

በሌላ የቁርኣን አንቀጽ ደግሞ

وَكَم مِّن مَّلَكٍ فِي السَّمَاوَاتِ لَا تُغْنِي شَفَاعَتُهُمْ شَيْئًا إِلَّا مِن بَعْدِ أَن يَأْذَنَ اللَّهُ لِمَن يَشَاءُ وَيَرْضَىٰ

“በሰማያት ውስጥ ካለ መልአክም ብዙዎች (ሊማለዱለት) ለሚሻውና ለሚወደው ሰው ከፈቀደ በኋላ ቢኾን እንጅ ምልጃቸው ምንም አትጠቅምም።” (አል-ነጅም 53፣26)።

ረሱል /ሶ.ዐ.ወ/ ይህን አስመልክተው እንዲህ ይላሉ፡-

لكل نبي دعوة مستجابة, فتعجل كل نبي دعوته, واني اختبأت دعوتي شفاعة لأمتي, وهي نائلة من مات منهم لا يشرك بالله شيئا (البخاري ومسلم(

“ለእያንዳንዱ ነቢይ ከአላህ ዘንድ ተቀባይነት የምታገኝ አንድ ልዩ ዱዓ ተሰጥታለች። እኔ ስቀር ሁሉም ነቢይ የተሰጠውን እድል (እዚሁ) ተጠቅሟል።እኔ ግን ለህዝቤ ለማማለድ ያስችለኝ ዘንድ ለፍርዱ ቀን አቆይቻታለሁ። በአላህ ባዕድ አምልኮ ሳይፈጽም የሞተ ሰው ሁሉ የምልጃዬ ተጠቃሚ ይሆናል።” (ቡኻሪ እና ሙስሊም)።

በሌላ የሙስነዱ የአህመድ ዘገባ ደግሞ፣ ረሱል /ሶ.ዐ.ወ/

أعطيت خمسا وأعطيت الشفاعة, فادخرتها لأمتي, فهي لمن لا يشرك بالله (صحيح البخاري ومسند أحمد(

“አምስት ልዩ ስጦታዎችንና ማማለድን ተሰጥቻለሁ። ምልጃዬንም ለፍርዱ ቀን ከህዝቤ በአላህ ባዕድ አምልኮ ሳይፈጽሙ ለሞቱ አቆይቻታለሁ።” ብለዋል።

ታላቁ የአለም ብስራት ሙሀመድ /ሰ.ዐ.ወ/ የዚያ ታላቅ ሸፋዓ (ሸፋዑል ዑዝማ ወይም መቃመል መሕሙድ) ባለቤት ናቸው። ጥፋት ሰርተው (ከባዕድ አምልኮ ውጪ) መፀፀትና መመለስ (ተውበት ማድረግ) ላልቻሉና ለጥቂቶች ያለ ሂሳብ ጀነት ይገቡ ዘንድ አላህን ይለምናሉ፤ ይማልዳሉ። እዚህ ጋር ግን ልንገነዘበው የሚገባው ቁምነገር “ተውባህ” እና “ሸፋዓ” ሀጢያትን አሳንሰን እንድንመለከት ሊያደርጉን አይገባም። ቀድሞውንም ሀጢያትን የሚንቅ ሰው ለተውበት እጁን አይሰጥም። ነገር ግን ተውበት በአላህ ላይ ያለንን ተስፋ እንድናዳብር፣ በምህረቱና በእዝነቱ እንድናምንና እንዲሁም በዒባዳ ላይ ፈፅሞ ታካች እንዳንሆን ድንቅ ትምህርት ይሰጣል። አላህ የእዝነትና የርህራሄ አምላክ ነውና በእርሱ እስካመንና የመልዕክተኛውን መንገድ እስከተከተልን ድረስ ምህረቱ እጅግ በጣም ሰፊ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here