የነቢዩ ሙሐመድ /ሰ.ዐ.ወ/ የታሪክ ምንጮች

0
6331

ለረሡል /ሰ.ዐ.ወ/ ታሪክ በዋናነት በምንጭነት የሚያለግሉት በአራት ይመደባሉ፡-

  1. አል-ቁርአን አል-ከሪም

ቁርአን የረሡልን ታሪክ ለመተረክ ዋነኛ ምንጭ ነው። ለምሳሌ ቁርአን ስለረሡል አስተዳደግ እንዲህ ይናገራል፡-

أَلَمْ يَجِدْكَ يَتِيمًا فَآوَىٰ وَوَجَدَكَ ضَالًّا فَهَدَىٰ

“የቲም ኾነህ አላገኘህምና አላስጠጋህምን? (አስጠግቶሃል)። የሳትክም ኾነህ አገኘህ መራህም።” (አድ-ዱሃ 93፣ 6-7)።

የረሡልን ድንቅ ስነ-ምግባርም ቁርአን እንዲህ ገልጾታል፡-

وَإِنَّكَ لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ

“አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።” (አል-ቀለም 68፣ 4)

ቁርአን ረሡል በዳዕዋ ሜዳ ላይ የገጠማቸውን ስቃይና መከራ ከመግለፁም በተጨማሪ ሙሽሪኮች ዳዕዋቸውን መሀን ለማድረግ ጠንቋይ፣ እብድ በሚሉ ቆሻሻ ስያሜዎች ሞራላቸውን ይነኩት እንደነበረም ይገልፃል። እንዲሁም ረሡልን ስደት ከማውሳቱ በተጨማሪ ከሂጅራ በኋላ ያከናወኗቸውን አበይተ ፍልሚያዎች ያትታል። ለምሳሌ ስለ ታላቁ በድር፣ ኡሁድ፣ አል-አህዛብ፣ ሱሉሑል ሑደይቢያ፣ ፈትሑ መካ፣ የሁነይን ዘመቻ። ቁርአንም ስለ ረሡል የተወሱትን ታዕምራት ለምሳሌ ስለ ኢስራእና ሚዕራጅ (ኢስራእ ወደ ቁድስ ከተማ ያደረጉትን ጉዞ የሚመለከት ሲሆን፣ ሚዕራጅ ደግሞ ወደ ሰማይ ማረግን ይመለከታል) አትቷል።

በአጠቃላይ ቁርአን ረሡልን የሚመለከቱ ታሪካዊ ክስተቶችን አትቷል። ቁርአን ምድር ላይ ካሉ መፃህፍት እጅግ በጣም ታማኙ ነው። ምክንያቱም ታማኝነቱ ታማኝ በሆነ የአዘጋጋብ መንገድ የተዘገበ በመሆኑና ማንኛውም ሠው የቁርአንን ትረካ በማይጠራጠርበት መንገድ የተተረከም በመሆኑ ነው። ስለሆነም ቁርአን ስለ ረሡል ታሪክ ከተረከ ይህ ታሪክ ከማንኛውም ታሪክ የበለጠ ትክክለኛ ምንጭ መሆኑ የተረጋገጠ ነው።

ነገር ግን የቁርአን የአተራረክ ዘዴ ሁሉንም ታሪካዊ ክስተቶች መዘርዘር ሳይሆን፣ ጥቅል ነገሮችን ብቻ ማስቀመጥ ነው። ለምሳሌ፡- ስለ አንድ ጦርነት ሲያትት፣ ጦርነቱን ብቻ በጥቅሉ ያስቀምጣል እንጅ ምክንያቱን የሙስሊሞችንና የሙሽሪኮችን /ጣኦት አምላኪ/ ቁጥር የሙሽሪኮችን ሙትና ቁስለኛ አያትትም። ይልቅ ሙዕሚኖች ከጦርነቱ የሚማሩትን ትምህርት በመግለፅ ያተኩራል። ይህ የቁርአን የአተራረክ ዘዴ ሲሆን ለረሡል ታሪክ ብቻ ሳይሆን ስለ ቀደምት ነቢያት ታሪክም ሲተርክ ይህንኑ የአተራረክ ዘዴን ነው የሚከተለው። ስለሆነም ስለ ረሡል የህይወት ታሪክ ቁርአን ሙሉውን የታሪክ ገፅታ አይነግረንም።

2. ትክክለኛ የነቢያዊ ሐዲሶች

በሙስሊሙ ዓለም ነቢያዊ ሐዲሶችን በታማኝነትና በእርግጠኝነት በመዝገብ የታወቁትና እውቅና የተሰጣቸው የሚከተሉት ናቸው። ስድስቱ የሐዲስ መፃህፍት፡- አል-ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ አቡዳውድ፣ አል-ነሳኢ፣ አል-ቲርሚዚ፣ ኢብኑ ማጃህ ሲሆኑ ከነሡም በተጨማሪ የኢማሙ ማሊክ “መወጦእ” የኢማሙ አህመድ “ሙሰነድ” ተጠቃሽ ናቸው። ከነዚህ መፃህፍት ከመረጃው ትክክለኛነት፣ እውነተኛነትና እርግጠኝነት አንፃር ቡኻሪና ሙስሊም ቀዳሚዎች ናቸው። ቀሪዎቹ የሐዲስ መፃህፍት ግን በውስጣቸው ትክክለኛ (ሶሒህ) ደህናና (ሐሰን) ደካማ (ዶኢፍ) ሐዲሶችን ዘግበውዋል። በነዚህ የሐዲስ መፃህፍት አብዛኛው ትኩረታቸው ስለ ረሡል የህይወት ገጠመኛቸው፣ ስላደረጉት ጦርነት፣ ስለ ስራዎቻቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ ሙሉ የሆነ ታሪክ ባያቀርቡት በአጠቃላይ ግን ሙሉ ሊባል የሚችል ጥቅል ትረካ ተርከዋል። እነዚህ ሐዲሳዊ ታሪኮች ትክክለኛ ታሪክ መሆናቸው፣ ሠንሠለቱን በትክክል በጠበቀ የአተራረክ መንገድ ከሰሃቦች መተረካቸው ነው። እነዚህ ሶሃቦች ደግሞ ረሡል ጋር የሚኖሩ፣ የተጎኙ፣ ለኢስላም ግንባር የቆሙ፣ ረሡልም ተንከባክበው ያሳደጉዋቸው /ያሰለጠኑአቸው/ ናቸው። በተጨማሪም ሰሃቦች የሰው ልጅ በታሪኩ ከሚያውቃቸው ትውልድ ውስጥ ከስነ-ምግባር አኳያ እጅግ በጣም የበለጡና ኢማናቸው ደግሞ እጅግ በጣም ጠንካራ ናቸው።እውነት ተናጋሪ፣ መንፈሰ-ታላቅ፣ ባለ ሙሉ አዕምሮ ናቸው። ስለሆነም እነሡ ስለ ረሡል በትክክለኛ የዘገባ ሰንሰለት የዘገቡት፣ እውነተኛ የታሪክ አካል ሆኖ ይመዘገባል። በመሆኑም ስለ ትክክለኛነቱ ጥርጣሬ አይገባንም።

3. የዘመነ-ነቢዩ ግጥሞች

ሙሽሪኮች በግጥሞቻቸው የረሡልን የዳዕዋ ስራ ለማደናቀፍ መሞከራቸው ግልፅ ነው። ስለሆነ ሙስሊሞች በግጥሞቹ የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመመለስም በገጣሚዎቻቸው አማካኝነት ምላሽ ጽፈዋል። ከገጣሚዎቹ መካከል ሐሳን ኢብኑ ሳቢት፣ ዓብደሏህ ኢብኑ ረዋሓና ሌሎቹም ይገኛሉ። የስነ-ጽሁፍና የታሪክ መፃህፍት የእነዚህን ገጣሚ ስራዎች ይዘው ይገኛሉ። በዚህም ረሡል የኖሩበትን ሁኔታና የዳዕዋውን ዕድገት ከግጥሞቹ መረዳትና መገንዘብ ይቻላል።

4. ታሪካዊ መፃህፍት

የረሡልን /ሰ.ዐ.ወ/ ታሪካዊ ክስተቶች ባልደረቦቻቸው /ስራቸውን አላህ ይውደድላቸውና/ ለቀጣዩ ትውልድ ዘግበዋል። ስለሆነም ከቀዳሚው ትውልድ ይህን ታሪካዊ መረጃ በጥልቀትና በዝርዝር በመከታተል ትኩረት የሰጡ ኡለሞች ነበሩ። ከዚያም ከተከታዩ ትውልድ ከቀዳሚዎቹ ያገኘውን መረጃ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ማስተላለፍና መሰነድ ስራ አድርገው የያዙትም ይገኛሉ። ከነዚህም ታዋቂ የታሪክ ምሁራን መካከል አባን ኢብኑ ዑስማን ኢብኑ ዓፋን (32-105 ሂ)፣ ዑርወቱ ኢብኑ ዙበይር ኢብኑል ዐዋም /23-93 ሂ/ ይገኙበታል። ከዕድሜ አንፃርም አነስተኛ ዕድሜ የነበራቸው ታቢዒይን /ሁለተኛው ትውልድ/ መካከል ደግሞ ዐብደሏህ ኢብን አቢ በክር አል-አንሷሪይ /የሞተው 135 ሂ/፣ ሙሐመድ ኢብኑ ሙስሊም ኢብኑ ሸሃብ አል-ዙህሪይ (50-124 ሂ) ሲሆኑ፣ ሙሐመድ ኢብኑ ሙስሊም በኸሊፋው ዑመር ኢብኑ ዐብደል ዐዚዝ ትዕዛዝ መሰረት ይህን ተግባር ሰርቷል። ዓሲም ኢብኑ ዑመር ኢብኑ ቀታዳ አል-አንሷሪይም /የሞተው 129 ሂ/ ሌላው ተጠቃሽ ነው።

እነዚህ ቀዳሚ ትውልዶች ለታሪክ ያደረጉት ትኩረት ቀጣዩም ትውልድ በስራው ቀጥሎበታል። ሌላው ቀርቶ በምዕራፍ በምዕራፍ በመለያየት ለማስቀመጥ ችለዋል። ከነዚህም ድርሳናት ካዘጋጁት መካከል ግንባር ቀደሞቹ፣ ሙሐመድ ኢብኑ ኢስሃቅ ኢብኑ የሳር /የሞተው 152 ሂ/ አንዱ ሲሆን፣ ብዙኃኑ (ጁምሁር) ሙስሊም ሁለገብ ሊቃውንትና የሐዲስ ዑለሞች የተጣራ መረጃ የሰነደ ለመሆኑ ተስማምተውበታል። ምናልባት ማሊክና ሂሻም ኢብኑ ዙበይር ስራውን ለመተቸት ሞክረዋል። ነገር ግን ብዙ ምሁራን ሁለቱ ለኢብኑ ኢስሃቅ ባላንጣ የሆኑት ከግላዊ ጥላቻ እንጂ ከዘገባቸው ዘገባዎች አንፃር አይደለም ይላሉ።

ኢብኑ ኢስሃቅ “አል-መጋዚ” የሚል ራሳቸው መዲናና ግብፅ ሆነው ያዳመጧቸውን የሀዲሶችና የተለያዩ ትረካዎችን ያሰባሰቡበት መፅሀፍ አዘጋጅተዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ይህ ድንቅ ታሪካዊ መፅሀፍ ከአሁኑ ትውልድ እጅ ሊገባ አልቻለም። ሌሎቹ ድንቅ ዕውቀታዊ ቅርሶቻችን እንደጠፉት ሁሉ ይህም ታሪካዊ ስራ የመጥፋት ዕድል ገጥሞታል ማለት ነው። ቢሆንም ግን ኢብኑ ኢስሃቅ ያዘጋቸው ጥቅል ሃሳብ በኢብኑ ሂሻም ድርሳን ውስጥ ተጠቃሎ ይገኛል። ኢብኑ ሂሻም ይህን መረጃ ያገኘው የኢብኑ ኢስሃቅ ገናና ተማሪና የኢብኑ ሂሻም አስተማሪ ከነበረው ከአል-በጣኢይ ነው።

i. ሲረቱ ኢብኑ ሂሻም

ኢብኑ ሂሻም ስማቸው አቡ ሙሐመድ ዐብደ አል-መሊክ ኢብኑ አዩብ አል-ሂወይሪ ሲሆን የተወለዱት በ 213 ወይም በ 218 /እ.ሂ.አ/ ነው። ኢብኑ ሂሻም “አል-ሲረቱ አል-ነበዊያ” (የነቢዩ ታሪክ) የሚል መፅሀፍ አዘጋጅተዋል። ይህን መፅሀፍ ሲያዘጋጁ ከአስተማሪያቸው አል-በካኢና በካኢ ደግሞ ከኢብኑ ኢስሐቅ በወሰዱት መረጃ ነው። እንዲሁም ኢብኑ ሂሻም ከሌሎች አስተማሪዎቹ መረጃ ደርሶታል። ይህ ዘገባ ኢብኑ ኢስሀቅ ያልዘከረው ታሪካዊ ዘገባ ነው። ነገር ግን ኢብኑ ሂሻም ኢብኑ ኢስሐቅ ከዘገቧቸው ዘገባዎች መካከል ከሚያውቀው ጋር ያልተስማማውንና ከትችት ችሎታው አንፃር አብሮ መሄድ ያልቻለውን ችላ ብሎታል። ከተሟላ የመረጃ ምንጭ የተዘጋጀውንና እጅግ በጣም ትክክል፣ የተጣራ የሆነ የነቢዩን ታሪክ የሚተርክ መፅሀፍ ተዘጋጀ። እሰዎች ዘንድም ተቀባይነት አግኝቷል። ይህን መፅሀፍ /ታሪካዊ ድርሳን/ ሠዎች በስሙ በመጥራት “ሲረቱ ኢብኑ ሂሻም” ብለው ጠርተውታል። ስራውንም ሁለቱ የታወቁት የአንደሉስ /የቀድሞዎቹ ስፔንና ፖርቱጋል/ ዑለሞች አል-ሱህሊይ (508-581 ሂ) እና አል-ኸሸኒይ /535 – 604ሂ/ ማብራሪያ (ሸርህ) አብጅተውለታል።

ii. ጠበቃቱ ኢብኑ ሰዕድ

ኢብኑ ሰዕድ ሙሉ ስማቸው ሙሐመድ ኢብኑ ሰዕድ ኢብኑ መኒይዕ አል-ዙህርይ ሲሆን፣ በ 168 ሂ በበስራ ከተማ ተወልደው፣ በ 230 ሂ ባግዳድ ከተማ ሞተዋል። ኢብኑ ሰዕድ ለተዋቂው ሙሐመድ ኢብኑ ዑመር አል-ዋቂዲይ /የ “መጋዚ” የታሪክ መፅሀፍ አዘጋጅ እና ከ 130-208 ሂ ለቆየው/ ፀሀፊ ሆነው አገልግለዋል። ኢብኑ ሰዕድ በመፅሀፉ “አል-ጦበቃት” የረሡልን ታሪክ ከዘገቡ በኋላ የሶሃባንና የታቢዒይን ስሞች፣ ዘራቸውንና ቦታዎቻቸውን ዘርዝሯል። ይህ መፅሀፍ ለረሡል ታሪክ ዋነኛ ምንጭ እና የሰሃባንና የታቢዒይን ስሞች በትክክል መዝግቦ የያዘ ነው።

iii. የጦበሪ ታሪክ

ጦበሪ ስማቸው ሙሐመድ ኢብኑ ጀሪር አል-ጦበሪይ /224-310 ሂ/ ሲሆን የፊቅህ፣ የሐዲስ ሊቅ ነበሩ። መዝሀባቸው ብዙም ባይስፋፋም የራሳቸው መዝሀብ ነበራቸው። የቅድመ ረሡል ህዝቦችንና የረሡልን ታሪክ ጽፈዋል። በመፅሀፉ ለረሡል ልዩ የሆነ ክፍል /ቦታ/ በመስጠት የፃፉ ሲሆን፣ ከዚያም እስከ ህይወታቸው መጨረሻ አካባቢ የነበረውን የኢስላማዊ ሀገሮችን ታሪክም ከትበዋል።

ኢማሙ ጦበሪይ ዘገባዎቻቸው ታማኝ ቢሆኑም፣ ብዙ ዘገባዎቻቸው ግን ደካማ መረጃን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ጦበሪይ ዘገባዎቻቸውን የሚወስዱት በዘመናቸው ከነበሩ ሠዎች ብቻ ነበር። በተለይ ጎጠኛ ሺዓ እንደነበረ ከሚነገርለት ከአቢ መኽነፍ ብዙ ዘገባዎችን ወስደዋል። እሳቸውም ይህንኑ /መረጃ መውሰዳቸውን/ በስራቸው አውስተዋል። ምናልባት ይህን ያደረጉበት ምክንያት ዘገባዎቹ ስህተት ሆነው ቢገኙ ሀላፊነትን ላለመሸከም ብለው ነው።

iv. የነቢዩ ታሪክ አመዘጋገብ መሻሻሎች

ስለ ረሡል /ሰ.ዐ.ወ/ የሚያትቱ ድርሳናት ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻሉ የአዘገጃጀት መልካቸውንም እያሻሻሉ መጥተዋል። ስለሆነም አንዳንድ ደራሲዎች በረሡል ውሱን የታሪክ ገፅታ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ድርሳናት አዘጋጅተዋል። ከነዚህም መካከል የአል-አሰበሃኒ “ደላኢል አል-ኑቡዋ” ፣ የቲርሚዚ “ሽማኢሉ አል-ነቡዋ” ፣ የኢብኑ አል-ቀይም “ዛድ አል-ሚዓድ” ፣ የቃዲ ዒያድ “ሺፋእ” ፣ በስምንት ጥራዝ ማብራሪያ የተበጀለት “አል-መዋሂሉል ለዱንያ” የቀስጦላኒ /1122 ሂ/ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ከላይ የተዘረዘረው እንዳለ ሆኖ ብዙ ምሁራን የዘመናቸው አንባቢ በሚጥመው ዘዴ የተለያዩ ነቢያዊ ታሪክን ከመፃፍ አልቦዘኑም። ከነዚህም መካከል በዘመናችን ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችሉና በብዙ ኢስላማዊ የትምህርት ተቋማትና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙት የሸይኽ ሙሐመድ አል-ኹደሪይ “ኑሩ አል-የቂን ፊሲረቲ ሰይድ አል-ሙርሰሊን” ፣ የዶ/ር ሙሰታፋ ሲባዒ “ሲራቱ ኑቡዋ ዱሩሱን ወዒበር” ፣ የሸይኽ ሙባራክፉሪ “ረሒቅ አል-መክቱም” እና “ረውዳቱል አንዋር” ፣ የዶ/ር ሙኒር አል-ጘድባን “ሚንሃጅ አል-ሃረኪ ሊሲራቲል ኑቡዋ” እና የዶ/ር ዓሊ ሙሐማድ አል-ሶላቢ “አል-ሲራቱ አል-ኑቡዋ” ተጠቃሽ ናቸው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here