ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንደ ታላቅ የበጎ አድራጊ መሪ

0
2545

“በጎ አድራጊ/ ሰብኣዊ”’ በእንግሊዝኛ Humanitarian የሚለው ቃል በዌብስተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ገለፃ መሠረት “በተለይም ህመምና ሰቆቃውን በማስወገዱ ረገድ የሰውን ልጅ ደህንነት ለማረጋገጥ ሲል እራሱን አሣልፎ የሠጠ /የቆረጠ/ ሰው ማለት ነው።” ታላቁ መሪ ነቢያችን ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሰውን ልጆች አጠቃላይ ደህንነት ለማረጋገጥና ህይወታቸውን ለማሻሻል ሲሉ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ መሪ ከመሆናቸው ጋር ለዚህ ትልቁ ምሣሌ ናቸው።

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላም ለአለማት ሁሉ እዝነት ነው የላካቸው።

وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا رَحْمَةً لِّلْعَالَمِينَ

“ለዓለማት እዝነት እንጂ አልላክንህም።” (አል አንቢያእ 21፣ 107)

እንደ ነቢይና የአላህ መልእክተኛ የተሠጣቸው ዋና ተልእኮ ህዝቦችን ወደ እውነኛውና አስተማማኝ ደህንነትን ወደሚያስገኘው የስኬት ጎዳና መምራት የነበረ ቢሆንም እርሣቸው ግን ሥራቸውን እምነትን በመስበክና ፀሎትን በማስተማር ላይ ብቻ አልወሠኑም። በዘር፣ በቆዳ ቀለምና በሃይማኖት ከመለያየታቸው ጋር የሰው ልጆችን ሁሉ በመርዳቱ ረገድ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሰርተዋል። ለሰው ዘር በሙሉ መልካምና ደግ አሣቢ ነበሩ።

በዚህ አጭር ፅሁፍ በጎ አድራጊነትንና ሰብኣዊነትን በጥቂቱም ቢሆን ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሲራ /ታሪክ/ ለመማር እንሞክራለን።

በበጎ አድራጊነት ዙሪያ ነቢያዊ አስተምህሮ

ከተላኩበት ጊዜ ጀምሮ ይህችን ዓለም እስከተሰናበቱበት ጊዜ ድረስ ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሰው ልጆች በሙሉ ከአንድ እናትና አባት (አደምና ሀዋ) በተዋረድ የመጡ የአንድ ቤተሰብ አባላት ስለመሆናቸው ላይ አፅንኦት ሰጥተው አስተምረዋል። ከመነሻቸው ጀምሮ የዘረኝነትንና የቆዳ ቀለም መድልዎን በማውገዝ ሰብከዋል። ብሄርተኝነትን፣ ጎሠኝነትንና አግባብ ያልሆኑ ጥላቻዎችን በመፃረርም ትምህርት ሰጥተዋል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ አንድን ሰው የሚነካ አሊያም የሚያገል የዘረኝነት ቃል ከአፋቸው ፈፅሞ ወጥቶ አያውቅም። በተወለዱበትና ባደጉበት ማህበረሰብ ውስጥ የዘር መድልዎ እጅግ የተለመደና የተስፋፋ ቢሆንም እርሣቸው ግን ይህንን መጥፎ ልማድ በመቃወም ይናገሩ ተከታዮቻቸውንም ሰዎችን በአክብሮት እንዲይዙ ያስተምሩ ነበር።

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለሁሉም ህዝቦች ፍትህ ይደረግ ዘንድ ታግለዋል። የቆሙትና የተቆረቆሩትም ለሙስሊሞች ብቻ አልነበረም። ሙስሊም ለሆኑትም ሆነ ላልሆኑት፤ ለወዳጆቻቸውም ይሁን ለጠላቶቻቸው ጭምር ተከራክረዋል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ዓለማቀፋዊ የሆነ ፍትሃነትን አስይዞ ነውና የላካቸው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ አማኞችን እንዲህ በማለት ያዛል

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُونُوا قَوَّامِينَ لِلَّهِ شُهَدَاءَ بِالْقِسْطِ وَلَا يَجْرِمَنَّكُمْ شَنَآنُ قَوْمٍ عَلَىٰ أَلَّا تَعْدِلُوا اعْدِلُوا هُوَ أَقْرَبُ لِلتَّقْوَىٰ وَاتَّقُوا اللَّهَ إِنَّ اللَّهَ خَبِيرٌ بِمَا تَعْمَلُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለአላህ ቀጥተኞችና በትክክል መስካሪዎች ሁኑ። ህዝቦችን መጥላት ባለማስተካከል (ፍትህ ባለማድረግ) ላይ አያነሣሣችሁ። አስተካክሉ (ፍትህ አድርጉ) እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው። አላህንም ፍሩ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ አዋቂ ነውና።” ( አልማኢዳህ 5፣8 )

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ይህንኑ መለኮታዊ መልእክት ለህዝቦች አድርሰዋል፤ ከማንም በተሻለ መልኩም ተግብረዋል። በሰላሙም ሆነ በጦርነት ጊዜ ከጠላቶቻቸው አንፃር ኢፍትሃዊ ሲሆኑ አልታየም። እንዲያውም በተቃራኒው የነበሩ ሲሆን ድል ባገኙባቸው በተለያዩ ጦርነቶች ወቅት ጠላቶቻቸውን ይቅር በማለት በነፃ አሠናብተዋቸዋል። ከዚህም ባለፈ ነቢዩ የሁሉም ህዝቦች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ አፅንኦት ሰጥተዋል። ከነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በፊት የሰብአዊ መብት ፅንሠ ሀሣብ አይታወቅም ነበር። ሁሉም የሰው ልጆች አምላካቸውና ፈጣሪያቸው አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሠጣቸው የማይሸራረፍ መብት እንዳላቸው ለዓለም ያስተማሩትም እርሣቸው ነበሩ። ስለ መኖር መብት፣ ለህይወት አስፈላጊ ስለሆኑ መሠረታዊ ነገሮች መብት፣ ስለ ንብረት ባለቤትነት መብት፣ ስለ ሥም መከበር መብት፣ ስለ ግለሰብ መብት፣ ሀሣብን በነፃነት ስለ መግለፅ መብት፣ የማሰብና አቋም የመያዝ መብት፣ በህግ ፊት እኩል የመሆን መብት እና ስለ መሣሠሉት መብቶች ሁሉ ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች ጋር በመከባበር ላይ በተመሠረተ አኳሃን መኗኗር እንዳለብን ምክር ሰጥተውናል። ሠራተኞችን ማክበር እንደሚገባና በተገቢው መልኩና ላባቸውም ሣይደርቅ የሥራቸው ዋጋ እንዲከፈላቸው አስተምረዋል።

መሪዎች በህዝባቸው ፊት ተጠያቂነት እንዳለባቸውና አስፈላጊ በሆነ ጊዜም ማህበረሰቡ እነሱን የማስወገድ መብት ያለው መሆኑንም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተማሩት ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ናቸው።

ነቢዩ ሙሀመድ ሰላለሁ ዐለይህ ወሠለም ለቤተሰብ በጎ መዋልን፣ ህፃናትን መውደድን፣ ወላጆችንና ታላላቆችን ማክበርን እንዲሁም ለጎረቤት ጥሩ መሆንን አስተምረዋል። ወላጆቻችንና ዘመዶቻችን የአላህን መልእክት መንገድ ለመቀበል ፈቃደኛ ሣይሆኑ ቀርተው በቀድሞ ክህደታቸውና ጣኦት አምላኪነታቸው ቢቀጥሉ እንኳ በመልካም ሁኔታ እንድንኗኗራቸው ያዘዙን ሲሆን መንገዳቸውን ሣንከተል በአለማዊ ጉዳዮች ላይ ግን ለነሱ መልካም መሆን እንደሚገባን ነግረውናል። ጎረቤቶችን በመልካም እንክብካቤና በጎነትን በተላበሠ መልኩ አብረናቸው እንድንኖር መልእክት አስተላልፈዋል። “ጎረቤቱ ተርቦ እያለ ጠግቦ ወደ መኝታ የሚሄድ እሱ አማኝ አይደለም” በማለት ለጎረቤት ሀቅ ትልቅ አፅንኦት ሰጥተዋል።

أَرَأَيْتَ الَّذِي يُكَذِّبُ بِالدِّينِ ﴿١﴾ فَذَٰلِكَ الَّذِي يَدُعُّ الْيَتِيمَ ﴿٢﴾ وَلَا يَحُضُّ عَلَىٰ طَعَامِ الْمِسْكِينِ ﴿٣﴾ فَوَيْلٌ لِّلْمُصَلِّينَ﴿٤﴾ الَّذِينَ هُمْ عَن صَلَاتِهِمْ سَاهُونَ ﴿٥﴾ الَّذِينَ هُمْ يُرَاءُونَ ﴿٦﴾ وَيَمْنَعُونَ الْمَاعُونَ

“ያን በሃይማኖት የሚያስተባብለውን አየህን? ያም የቲምን (ወላጅ አልባን) በሀይል የሚገፈትረውን። ድሃን በማብላት ላይ አያግባባም። ለነዚያ ለሰጋጆች ወዮላቸው! ለነዚያ ከስግደታቸው ዘንጊ ለሆኑት። ለነዚያ ይዩልኝ ባዮች ለሆኑት። የትውስትንም እቃ ለሚከለክሉት።” ( አል ማዑን 107፣1-7)

ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ በጎ እንድናደርግ ሲያዙ አጠቃላይ በሆነ መልኩ እንጂ በሙስሊምና ሙስሊም ባልሆኑት በዘመድና በጎረቤት መካከል ልዩነትን አላስቀመጡም።

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መልካምነታቸው ለሙስሊሞች ብቻ ሣይሆን ሙስሊሞች ላልሆኑትም ጭምር ነበር። ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን ሀሣብ በማድመጥ እጅግ ጥሩ በሆነ ሁኔታ መልስ ይሠጧቸው ነበር። የተሣሣተ ግንዛቤያቸውንም በማረም ኢስላማዊ መልእክት ያስተላልፉላቸው የነበረ ሲሆን አቅሙ ቢኖራቸውም እንኳ በነሱ ላይ ሀይልን በመጠቀም እስልምናን እንዲቀበሉ አላስገደዷቸውም። የተወሰኑ ዘመዶቻቸው እስልምናን ያልተቀበሉበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን በሀይል ሚዛን በነሱ ላይ የበላይነትን ባገኙ ጊዜም አግባብ ባልሆነ መልኩ አላስተናገዷቸውም። በአንፃሩ ግን እጅ ሲያጥራቸው አግዘዋቸዋል። ሙስሊምም ሆኑ አልሆኑ በጎነትን ለጎረቤትና ለአጠቃላይ ዘመዶቻችን እንድናዳርስ አስተምረዋል። ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም አንድ ሰው ወይንም ቡድን ቀድሞ ካልተተናኮለን በስተቀር ቀድመን እንድናጠቃው አልፈቀዱልንም። ሰላማዊ ግንኙነትን፣ መልካም ስምምነቶችንና ቃል ኪዳኖችን ያበረታቱ የነበረ ሲሆን ጠላት ቃልኪዳኑን እስካከበረ ድረስ ቃላችንን ማፍረስ እንደሌለብንም ነግረውናል።

የነቢዩ ሙሀመድ የበጎ አድራጊነት ተምሣሌት

ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በጎ አድራጎትን ላነገበ መሪ ሁሉ ምርጥ ምሣሌ ናቸው። አላህ በነቢይነት ሣይልካቸው በፊት ጭምር ታማኝና እውነተኛ ሰው ነበሩ። በመካ ሰዎች ዘንድ “ስዲቅ አልአሚን” (እጅግ እውነተኛውና ታማኙ) በመባል ይታወቁ ነበር። ተወዳጅና ሰላማዊ ከሆነው ባህሪያቸውም የተነሣ የመካ ቁረይሾች በአንድ ወቅት ከዕባን በሚያድሱበት ጊዜ ሀጀረልአስወድን በቦታው ላይ ማን ያስቀምጥ የሚለው ውዝግብ በመካከላቸው አስታራቂያቸው አድርገዋቸዋል። ለበጎ አድራጎት ባላቸው መንፈስ የተነሣ ነበር በአንድ ወቅት በመካ ውስጥ ካሉ ትላልቅ ሰዎች ጋር ባል የሞተባቸው ሴቶችን፣ ወላጅ አልባ ህፃናትንና በከተማው ውስጥ መጠጊያ የሌላቸውን የሚረዳ የትላልቅ ሰዎችን ቡድን ተመርጠው ሊቀላቀሉ የቻሉት። የተለያዩ የመካ የጎሣ መሪዎች ቤታቸውን በመክበብና ሊገድሏቸውም በማሰብ ህይወትን ባከበዱባቸው ጊዜ ነቢዩ የተበደሩትንና በአደራ የተቀበሉትን ንብረት ሁሉ ለየባለቤቱ መመለሱን ሣያረጋግጡ የመካ ቤታቸውን አልለቀቁም ነበር። ምንም እንኳ ከአደራ ባለቤቶቹ መካከል የተወሰኑት ነቢዩ ባመጡት የእስልምና መልእክት የተነሣ ጠላቶቻቸው የነበሩ ቢሆኑም እርሣቸው ግን ንብረታቸውን ከመመለስ ወደኋላ አላሉም ነበር። ይህም ቅንነትን፣ ታማኝነትንና የሰብኣዊነት መንፈስን የተላበሠ ትልቅና ልዩ የሆነ ምሣሌ ነው።

ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ወደ መዲና ከተሰደዱ በኋላ ጥቂት ቆይቶ ከሀገር ያስወጧቸው ጠላቶቻቸው የሆኑት የመካ ሰዎች የምግብ እጥረት እንደገጠማቸውና ረሃብ ላይ መውደቃቸውን በሰሙ ጊዜ ከመዲና የምግብ እርዳታ እንደላኩላቸውም ተዘግቧል። ይህም ሌላኛው ልዩ የሆነ የበጎ አድራጊነት መንፈሣቸውን ጥንካሬ የሚያመለክተን ነው። ከጠላቶቻቸው ጋር በጦርነት ላይ እያሉ እንኳ አንድም ሰው ይሁን እንሠሣ በርሃብ እንዲሞት አልፈቀዱም ነበር። ድመት አስራ አስቀምጣ ምግብ ሣትሠጣት አሊያም ሄዳ ሲሣይዋን እንድትፈልግ ባለማድረጓ ምክኒያት አንዲት ሴት ለአላህ የጀሀነም ቅጣት መዳረጓን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ ለተጠማ ውሻ ውሃ ያጠጣ አንድ ሰው በድርጊቱ የአላህን እዝነት ማግኘቱንም አስታውሰውናል። ነቢዩ ለሰው ልጅም ሆነ ለእንሠሣት ያሣዩትን ጥልቅ የሆነ እዝነትና ደግነታቸውን የሚያሣዩ ምሣሌዎች እጅግ በርካታ ናቸው።

በመዲና የማህበረሰቡ መሪ በነበሩበት ወቅት ነቢዩ ዘካና ምፅዋትን ከህዝቡ ይሰበስቡ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ምፅዋት ለራሣቸውም ሆነ ለሚያስተዳድሩት ቤተሰብ ተጠቅመው አያውቁም። ድሆችንና ችግረኞችን በመርዳቱ ረገድ በጣም ለጋስ ነበሩ። እንዲዚያ ሲለግሱ ያዩዋቸው ሰዎችም “ድህነትን የማይፈራ ሰው አሰጣጥ ይሠጡ ነበር” ይሏቸው እንደነበር ተወስቷል። ከማስተማሩና ወደ አላህ መንገድ ከመጥራቱ ጎን ለጎን የሰዎችን ሁሉ ስቃይ ማስተንፈስ ሌላው ታላቅ ተልእኮአቸው ነበር።

ሙስሊሞች ሁሉ ይህን የነቢያችንን የበጎ አድራጊነት መንፈስ ልናውቅና አጥብቀን ልንከተለውም ይገባል። ለሁሉም ህዝቦች ጥሩና መልካም ልንሆን ያስፈልጋል። አንዳንዶች ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የተላኩበትን የበጎ አድራጊነት ኢስላማዊ አስተምህሮ ባለማወቅ አሊያም በተሣሣተ ግንዛቤ ማህበራዊ ግልጋሎታችን፣ እገዛችንና የበጎ አድራጎት ጥረታችን ሙስሊሙ ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለበት ይመስላቸዋል። ይህም “እርጥብ ጉበት (ህይወት ላለው) ሁሉ መልካም መዋል ምንዳ አለው” የሚለውን ነቢያዊ አስተምህሮ የሚቃረን ነው ፡፡

እኛ ሙስሊሞች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚደረጉ የበጎ አድራጎት አገልግሎቶች አንፃር እጅጉን ወደኋላ ቀርተናል። ይህም የእስልምናን መንፈስና ግልፅ አስተምህሮውን የሚፃረር ድርጊት ነው። በመሆኑም በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል። ሰዎች በሃይማኖት የመለያየታቸው ነገር እንዳለ ሆኖ ቀውስ በገጠማቸው ጊዜ ልንረዳቸው የምንችልባቸውን መንገዶች ልንፈጥር ይገባል። የተራቡትን ማብላት፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦትን በማዳረስ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትንም ማልበስ ይኖርብናል። ለበሽተኞች እና እገዛችንን ለሚፈልጉ ሰዎች የሚያገለግሉ በነፃ ግልጋሎት የሚሰጡ የህክምና ክሊኒኮችም የሚገነቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርብናል። የእድሜ ባለፀጎችን፣ ወላጅ አልባ የሆኑትን ህፃናት፣ ጋለሞታ ሴቶችን በተቻለን ሁሉ መንከባከብና አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል። አስታዋፅኦአችንን ሣናናንቅ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ተጠቂዎች እርዳታ የምናደርስበትን ሥርኣት መዘርጋት ይኖርብናል። ደዕዋ /ወደ አላህ መንገድ መጥራት/ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ የበጎ አድራጎት ሥራዎችም እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ያለ ቅን ሰብኣዊ አገልግሎት ውጤታማ የሆነ የደዕዋ ሥራ ማካሄድ ይከብዳል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here