ዲን ነሲሃ (ምክክር) ነው (ሰባተኛ ሀዲስ: ከአርበዒን አን-ነወዊያ)

0
6629

عَنْ أَبِي رُقَيَّةَ تَمِيمِ بْنِ أَوْسٍ الدَّارِيِّ رَضِيَ اللَّهُ أَنَّ النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم قَالَ: “الدِّينُ النَّصِيحَةُ قُلْنَا: لِمَنْ؟ قَالَ لِلَّهِ، وَلِكِتَابِهِ، وَلِرَسُولِهِ، وَلِأَئِمَّةِ الْمُسْلِمِينَ وَعَامَّتِهِمْ”  رَوَاهُ مُسْلِمٌ

ከአቢ ሩቅያ ተማም ቢን አውስ አድዳሪይ – እንደተዘገበው የአሏህ ነብይ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ

“ዲን (ሓይማኖት) ነሲሃ (ምክክር) ነው፡፡ ‹‹(ነሲሓው) ለማን ነው?›› አልናቸው፡፡ ነብዩም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ለአሏህ፣ ለመልዕክተኛው፣ ለሙስሊሞች መሪዎች እና ለተርታዎቻቸው፡፡  በማለት መለሱ፡፡ ሙስሊም ዘግበውታል፡፡


የሀዲሱ አሳሳቢነት

ይህ ሀዲስ የመጨረሻው መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከሌሎች ነቢያቶች ከተለዩባቸው ክብሮች መካከል አንዱ የሆነውን ድንቅ የንግግር ችሎታ (ጀዋሚዑል ከሊም) የሚያንፀባርቅ ሐዲስ ነው፡፡ ጀዋሚዑል-ከሊም ማለት ብዙ ታላላቅ ትምህርቶችንና የላቀ ፋይዳን ያዘሉ በርካታ ጉዳዮችን በአንድ አጭርና ጠቅላይ ገለፃ ማስቀመጥ ማለት ነው፡፡ ገለፃው በግልፅ ከሚያሳየው ነጥብ በተጨማሪ በውስጡ ሌሎች ብዙ ህግጋትንና ሱናዎችን በመሰረታዊነት አልያም በቅርንጫፋዊ ትንተና ያዘለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህኛው ሀዲስ የኢስላም ምሁራን ሲናገሩ ‹‹ይህ ሀዲስ የእስልምና መዘውር የተመሰረተበት ሀዲስ ነው፡፡››

የቃላትና ሀረጎች ትረጓሜዎች

“ዲን”፡- (ኃይማኖት) ሲባል እስልምናን ኢማንን እና አህሳንን (ማሳመርን) ለማመልከት ነው፡፡

“ነሲሃ”፡- ይህችን ንግግር ነሲሃ ለምታረገው አካል መልካም መፈለግህን ለመግለፅ የሚጠቅም ንግግር ነው፡፡ ወይም ሌሎች እንደሚተረጉሙት ነሲሃ ልብስ መስፋትን ከሚጠቁም ቃል የተፈለቀቀ ቃል ነው፡፡ ነሲሃ የሚያደርገው ሰው ነሲሃ የሚያደርግለትን አካል ቀዳዳ ለመሸፈን የሚያከናውነው ተግባር ስለሆነ ቃሉም ይህን ለማመሣሠል ጥቅም ላይ ውሏል ማለት እንችላለን፡፡ በሌላ አተረጓጎም ነሲሃ የሚለው ቃል ማርን ከሰሙና ከእንጀራው መለየትን የሚያስጠቅም ንግግር ነው፡፡ ህዝብን ከክህደት ማጥራትን ማርን ከማይጠቅመው ቆሻሻ ከማጥራት ጋር አመሳሰሉት፡፡

“አኢመቲል ሙስሊሚን”፡- አስተዳዳሪዎቻቸው፤ መሪዎቻቸው

“ዓመቲሂም”፡- ተርታው የማህበረሰብ ክፍል

አጠቃላይ ትርጓሜ

ለአሏህ ነሲሃ ማድረግ፡- ይህ የሚሆነው በአሏህ በማመንና ከእርሱ ጋር የሚያጋሩትን ሁሉ በመካድ ነው፡፡ ለአላህ ነሲሓ ማድረግ በባህሪያቱ ላይ ክህደት ከመፈፀም መጠንቀቅን ያካትታል፡፡ እርሱን በተሟሉ በሆኑት ባህሪያት መግለፅን ይይዛል፡፡ ከጉድለት በሙሉ እርሱን በማጥራት፣ አምልኮንም ለእርሱ በማድረግ፣ ለርሱ ብሎ በመውደድ ለርሱ ብሎ በመጥላትም ይገለጣል፡፡ እርሱን የታዘዙትን ወዳጅ በማድረግና እርሱን የነቀፈን በመጥላት ይታወቃል፡፡ ሙስሊም ይህን ሁሉ በንግግርና በተግባሩ መፈፀሙ በዱኒያና በአኼራ ውስጥ ጥቅሙ ወደርሱ ይመለሳል፡፡ ምክንያቱም አሏህ ነሲሃ ከሚያደርጉ ሠዎች ነሲሃ የተብቃቃና ንፁህ አምላክ ነውና፡፡

ለአሏህ መፅሐፍት ነሲሃ ማድረግ፡- ይህ ከሠማይ በወረዱ መፅሐፍት በሙሉ በማመን፣ ሁሉም ከአሏህ ዘንድ መሆናቸውን በመቀበል እና ይህ ቁርአንም የሁሉም መደምደሚያ እና መስካሪ እንደሆነ በማመን የሚተገበር ሥራ ነው፡፡ ለጌታው መፅሐፍ የሚያደርግ የሙስሊም ነሲሃ እንደሚከተለው ይገለፃል፡-

  • ማንበብና መሸምደድ፡- ምክንያቱም እርሱን ማንበብ ነፍስን ያጠራል፤ ተቅዋንም ይጨምራል፡፡ ሙስሊም ከአሏህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንደዘገቡት “ቁርአንን አንብቡ፡፡ እርሱ የቂያማ ቀን ለጓደኞቹ አማላጅ ሆኖ ይመጣል፡፡” ብለዋል፡፡ በልብ ውስጥ የአላህን መፅሐፍ መሸምደድ ልብን ልዩ በሆነ የአሏህ ብርሃን ያሸበርቃል፡፡ አቡዳውድና ቲርሚዚ ከአሏህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንደዘገቡት ‹‹ለቁርአንንን ለሚያነብ ሰው የቂያማ ቀን እንዲህ ይባላል፡- “አንብበና ደረጃህን ውጣ፤ በዱኒያ ውስጥ ታነብ እንደነበረውም አሳምረህ አንብብ፡፡ የአንተ ደረጃ መጨረሻ ከምታነበው አንቀፅ ዘንድ ነው፡፡”
  • ረጋ ብሎ ማንበብ፤ ሲነበብ ድምፅን ማሳመር፡፡
  • ትርጉሙን ማስተንተን እና አንቀፆቹን ለመረዳት ጥረት ማድረግ፡፡
  • ለማህበረሰቡ እና ለትውልድ ማስተማር፡፡ ቡኻሪ ከአሏህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንደዘገቡት “ከመሃላችሁ ምርጥ ሰው ቁርአንን ተምሮ ያስተማረ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
  • ትክክለኛን ግንዛቤ በመጨበጥና በዚያም ለመስራት መጣር፡፡ ማንበብ ያለግንዛቤ ጥቅሙ እምብዛም ሲሆን ግንዛቤ ያለ ተግባር ደግሞ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡

ለአሏህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ነሲሃ ማድረግ፡- ይህ የነብዩን መልእክት በማመን ይዘው የመጡትን ቁርአንና አስተምሮ ሁሉ እውነት ብሎ በመቀበል ይገልፃል፡፡ እርሳቸውን በመውደድና በመታዘዝም ይንፀባረቃል፡፡

قلْ إنْ كُنتم تُحِبُّونَ الله فاتَّبعُوني يُحببْكُم اللهُ

“በላቸው፡- «አላህን የምትወዱ እንደኾናችሁ ተከተሉኝ፤ አላህ ይወዳችኋልና፡፡ ኀጢኣቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።” (አሊ ኢምራን፤ 31)

مَّن يُطِعِ الرَّسُولَ فَقَدْ أَطَاعَ اللَّهَ وَمَن تَوَلَّىٰ فَمَا أَرْسَلْنَاكَ عَلَيْهِمْ حَفِيظًا

“መልክተኛውን የሚታዘዝ ሰው በእርግጥ አላህን ታዘዘ። ከትእዛዝም የሸሸ ሰው (አያሳስብህ)። በእነሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አልላክንህምና።”  (ኒሳእ: 80)

እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ለአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ነሲሃ ማድረግ ሙስሊሞች በየቤታቸው የእርሳቸውን ታሪክ እንዲያነቡ፣ መልካም ስብእናቸውን እንዲላበሱ፣ ስርአታቸውንም እንዲከተሉና ፈለጋቸውን አጥብቀው እንዲከተሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ለጠላቶችና በርሳቸው ላይ ድንበር ለሚያልፉ ተናጋሪዎችም መልስ እንዲሰጡ ይገፋቸዋል፡፡

ለሙስሊሞች መሪዎች ነሲሃ ማድረግ፡- የሙስሊሞች መሪዎች ሲባል አስተዳዳሪዎች አልያም የእነርሱ ምትኮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወይንም ዑለማዎችና ሷሊሆች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የሙስሊሞች መሪ ከሙስሊሞች ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆኑ ብቻ እነርሱን መታዘዝ ግዴታ ይሆናል፡፡ አላህም እንዲህ አለ፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا أَطِيعُوا اللَّهَ وَأَطِيعُوا الرَّسُولَ وَأُولِي الْأَمْرِ مِنكُمْ فَإِن تَنَازَعْتُمْ فِي شَيْءٍ فَرُدُّوهُ إِلَى اللَّهِ وَالرَّسُولِ إِن كُنتُمْ تُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ ذَٰلِكَ خَيْرٌ وَأَحْسَنُ تَأْوِيلًا

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፡፡ መልክተኛውንና ከእናንተም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፡፡ በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፡፡ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው፡፡” (ኒሳእ: 59)

ለእርሱ ነሲሃ ማድረግ ማለት የነርሱን መስተካከል፣ መመራትና ፍትህን መውደድ ማለት ነው፡፡ የነርሱን  ግል መውደድ ማለት አይደለም፡፡ ለነርሱ ነሲሃ በማድረግ በእውነት ላይ እንረዳቸዋለን፤ እንታዘዛቸዋለን፤ ሲረሱ እናስታውሳቸዋለን፡፡ በጥበብ፣ በርጋታና በእዝነት እናነቃቸዋለን፡፡ መሪዎቹን የማይመክር ህብረተሰብ ከመልካም የራቀ ነው፡፡ በደለኛን ‹አንተ በዳይ!› ብሎ በስሙ የማይጠራ ህዝብም መንገድ የሳተ ነው፡፡ ህዝቡን የሚያዋርድ፣ የመካሪዎችን ልሳን የሚዘጋ እና እውነትን ከመስማት ጆሮውን የሚያደነቁር መሪም መልካምን የተነፈገና ከበጎ የራቀ ነው፡፡

ዑለሞችና ለውጥ ፈጣሪዎች ለአሏህ መፅሐፍ እና ለመልእክተኛው አስተምሮ ነሲሃ በማድረግ በኩል ያለባቸው ኃላፊነት ከባድ ነው፡፡ መንገድ የሳተ ዝንባሌን ወደ ቅናት መመለስ የዚህ ኃላፊነት አካል ነው፡፡ መሪዎችን በአሏህ መፅሐፍና በመልዕክተኛው አስተምሮ እንዲያስተዳድሩ መምከርም ታላቁ ኃላፊነታቸው ነው። መሪን በውሸት ሙገሳ በበደሉ ላይ እንዲዘወትር፣ አባገነንነቱም ላይ እንዲፀና ካደረጉም አሏህ በከባድ ሁኔታ ይተሳሰባቸዋል፡፡ ጀርባቸውን ለመሪዎች የተመቸ መቀመጫና መጋለቢያ ካደረጉም ይጠየቁበታል፡፡ እናም እነርሱን ነሲሃ ማድረግ አለብን ስንል ጫንቃቸው ላይ ያለውን ይህን ኃላፊነታቸውን እንዲያስታውሱ ማድረግ እንዳለብን ለመግለፅ ነው፡፡

ለተራው ለሙስሊም ነሲሃ ማድረግ፡- ይህ ተርታውን የሙስሊም ማህበረሰብ በዱኒያና ለአኼራ ጉዳዮቹ ላይ መንገድን በማመላከት ይተገበራል፡፡ ነገር ግን በጣም በሚያሳስብ ሁኔታ ሙስሊሞች ይህን ሓላፊነታቸውን ችላ ብለውታል፡፡ በተለይም ለአኼራቸው የሚጠቅማቸውን ነገር ከመመካከር ርቀዋል፡፡ ጭንቀታቸውን በሙሉም በዱኒያ ጥቅሞቻቸው ላይ ብቻ አትኩረዋል፡፡ በተጨማሪም ልንረዳው የሚገባው ነጥብ ነሲሃ በንግግር ብቻ የሚገደብ ሳይሆን ወደ ተግባር መዝለቅም ይገበዋል፡፡

ታላቅ የነሲሃ አይነት፡- በሙስሊሞች መሃል ከሚደረጉ ታላላቅ ነሲሃዎች መሃል በግል ጉዳዩ ላይ ያማከረውን ሰው ነሲሃ ማድረግ ነው፡፡ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ ‹‹አንድ ወንድሙ ነሲሃን በጠየቀው ጊዜ ነሲሃውን ሊለግሰው ይገባል››

ከዚህ እጅግ የላቀው ደግሞ ወንድሙን በሌለበት ነሲሃ ማድረጉ ነውና እርዳታውንም መለገሱ ነው፡፡ ይህ ያለውን እውነተኝነትና ታማኝነት ያረጋግጣል፡፡ ይህን አስመልክተው ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ፡- “በሙስሊም ላይ ከሚኖሩት መብቶች ውስጥ በሌለበት ለርሱ ነሲሃ ማድረጉ አንዱ ነው፡፡”

የነሲሃ አደብ፡- እንደ ኢስላም እምነት አንድ ሙስሊም ወንድሙን ነሲሃ ሲያደርግ በሚስጢር ማድረጉ የነሲሃ አደብ ነው፡፡ ፉደይል ኢብኑ ዒያድ እንዲህ አሉ፡- ‹ሙእሚን ነውርን ይሸፍናል፤ ይመክራል፡፡ ጠማማ (ሙናፊቅ) ነውርን ይገልፃል፤ ያሰራጫል፡፡›

ከሃዲሱ የምንቀስመው ትምህርት

ነሲሃ ዲን (ሐይማኖት) ነው፡፡ ዲን ንግግር ላይ እንደሚገኝ ሁሉ ተግባር ላይም ይኖራል፡፡

ነሲሃ ከማህበረሰብ ውስት በቂ ቁጥርና ብቃት ያላቸው ሰዎች ሊሰሩት የሚገባ የወል ግዴታ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሚገባ ከፈፀሙት አጅር ያገኛሉ፤ ሌላው የማህበረሰቡም ክፍል በዚህ ሐላፊነት ከመጠየቅ ይድናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ይህን ኃላፊነት ባለመወጣቱ ይከሰሳል፡፡

ማንኛውም ሰው ነሲሃውን ለሚቀበሉና ትእዛዙን ለሚፈጽሙ ብሎም ለደህንነቱ የማይሰጋ ከሆነ የችሎታውን ያህል ነሲሃ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ነፍሱን ጥፋት ላይ እንዲጥል እንደማይገደድ የሀዲሱ ጭብጥ ያስረዳል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here