እኩይ ነገሮችንና አዳዲስ ፈጠራዎችን ማውገዝ (አምስተኛ ሐዲስ: ከአርበዒን አን-ነወዊያ)

0
2980

 عن أُمِّ المُؤمِنينَ أُمِّ عَبْدِ الله عائِشَةَ رَضي اللهُ عنها قالَتْ: قالَ رسُولُ الله صلى الله عليه وسلم: ” مَنْ أَحْدَثَ في أَمْرِنا هذا ما لَيْسَ منهُ فَهُوَ رَدٌّ ” رَواهُ البُخارِيُّ ومُسْلمٌ. وفي رِوايَةٍ لمُسْلمٍ  : مَنْ عَمِلَ عَمَلاً لَيْسَ عليه أَمْرُنا فَهُوَ رَدٌّ 

የአማኞች እናት አኢሻ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡- “በዚህ በጉዳያችን ውስጥ የርሱ አካል ያልሆነን አዲስ ነገር የጨመረ ጭማሬው ውድቅ ነው፡፡” በሙስሊም ዘገባ መሠረትም፡- “የኛ ፈቃድ የሌለበትን አዲስ ስራ የሰራ ተግባሩ ውድቅ ነው፡፡” ተብሎ ተዘግቧል፡፡


አጠቃላይ መልእክት

ኢስላም ኢቲባእእንጅ ኢብቲዳእ አይደለም፡- የአላህ መልእክተኛ በዚህ ሐዲሳቸው እስልምናን ከጽንፈኞች አጥባቂነት እና ከበካዮች ግድፈት ጠብቀውታል፡፡ ሐዲሱ በጥቂት ቃላት እጅግ ጥልቅና ሰፊ መልእክት የማስተላለፍ ክህሎታቸውን ያስመሰከሩበት ነው፡፡ ነጃህና ፈላህ የሚገኘው ከአላህ መልእክተኛ መመሪያ ላይ ምንም ነገር ሳይጨምሩና ሳያጠባብቁ በመከተል መሆኑን የሚደነግጉ በበርካታ የቁርአን አናቅጽ ለዚህ ሐዲስ መነሻዎች ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል አላህ እንዲህ ብሏል፡-

قُلْ إِن كُنتُمْ تُحِبُّونَ اللَّهَ فَاتَّبِعُونِي يُحْبِبْكُمُ اللَّهُ وَيَغْفِرْ لَكُمْ ذُنُوبَكُمْ ۗ وَاللَّهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ

“በላቸው፡- «አላህን የምትወዱ እንደኾናችሁ ተከተሉኝ፤ አላህ ይወዳችኋልና፡፡ ኀጢኣቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” (አሊ-ዒምራን: 31)

ሙስሊም ባሰፈሩት ዘገባ እንደተወሳው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም     ዘወትር በንግግራቸው መሐል እንዲህ ይሉ ነበር፡-

“ከንግግሮች ሁሉ በላጩ የአላህ ኪታብ ሲሆን፣ ከመመሪያዎች ሁሉ በላጩ የነቢዩ ሙሐመድ መመሪያ ነው፡፡ ከነገሮች ሁሉ መጥፎ አዲስ ፈጠራዎች ናቸው፡፡ ፈጠራዎች ሁሉ ቢድዓ ሲሆኑ፣ ቢድዓ ሁሉ ደግሞ ጥመት ነው፡፡”

ውድቅ ተግባራት፡- የሸሪዓው ባለቤት ፈቃድ የሌለባቸውን ተግባራት ሁሉ ይህ ሐዲስ በግልጽ ውድቅ አድርጓል፡፡ ጥሬ መልእክቱ ስራን ሁሉ ከሸሪዓው አህካም አኳያ ብቻ መመዘን፣ በቁርአንና እና በሱንና ትእዛዛትና እቀባዎች ብቻ መወሰን የግድ እንደሆነ ያመለከታል፡፡ ስራዎች ከሸሪዓው ወሰን መውጣታቸውና በርሱ አለመገዛታቸው ፍጹም ጥመት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

ተቀባይነት ያላቸው ተግባራት፡– ከሸሪዓው መንፈስ የማይወጡ፣ ከድንጋጌዎቹ ወይም ከመሠረታዊ መርሆዎቹ ዋቢ ሊመዘዝላቸው የሚችሉ ተግባራት ውድቅ አይደሉም፡፡ ተቀባይነት አላቸው፡፡ የሚያስመሰግኑም ናቸው፡፡ ሶሐቦች እንዲህ ዓይነት በርካታ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ ፈቅደዋቸዋል፡፡ ተቀባይነታቸውንም በጋራ ውይይት (ኢጅማእ) አጽድቀዋል፡፡ የዚህ ጉልህ ምሳሌ በአቡበክር ዘመን ቁርአን በአንድ መጽሐፍ መሰብሰቡና በዑስማን ዘመን ይህ ቁርአን ተባዝቶ፣ ከሊቃውንት ጋር በሁሉም የእስልምና ግዛቶች እንዲሰራጭ መደረጉ ነው፡፡የአላህን ሸሪዓ የሚቃረኑ አዳዲስ ተግባራት መጥፎ ቢድዓዎችና ጥመቶች ሲሆኑ፣ ሸሪዓውን የማይቃረኑት፣ ከርሱ ጋር የሚጣጣሙት፣ በርሱ ሚዛን ተቀባይነት ያላቸው አዳዲስ ክንውኖች ግን ምስጋናና ጽድቅ የሚቸራቸው ናቸው፡፡ ከመካከላቸው የሚወደዱ ተግባራት አሉ፡፡ የወል ግዴታ (ፈርዱል ዓይን) የሚሆኑም አሉ፡፡ ለዚህ ነው ኢማም ሻፊዒ እንዲህ ሲሉ የተናገሩት፡-

“ቁርአንን፣ ሱንናን፣ ኢጅማእን ወይም አሰርን የሚቃረን አዲስ ፈጠራ ሁሉ ጥመት የሆነ ቢድዓ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ አንዳቸውንም ያልተቃረነ አዲስ በጎ ተግባር ሁሉ ግን የሚመሰገን ቢድዓ ነው፡፡”

የሐዲሱ ጠቀሜታ፡- ከሸሪዓው ጋር የማይጣጣም አዲስ ፈጠራ (ቢድዓ) የፈጠረ ወንጀሉን እርሱ ይሸከማል፡፡ ስራውም ተቀባይነት የለውም፡፡ ቅጣትም ይገባዋል፡፡

ክልክል ነገሮች ሁሉ መጥፎ መሆናቸውን፤ ኢስላማዊው ሸሪዓም ጉድለት የሌለበት ሙሉ መሆኑን ሐዲሱ ያመለክታል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here