መላኢኮች /መላእክት/ (ክፍል 1)

0
5191

አላህ እንዲህ ብሏል፡-

آمَنَ الرَّسُولُ بِمَا أُنزِلَ إِلَيْهِ مِن رَّبِّهِ وَالْمُؤْمِنُونَ كُلٌّ آمَنَ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِّن رُّسُلِهِ وَقَالُوا سَمِعْنَا وَأَطَعْنَا غُفْرَانَكَ رَبَّنَا وَإِلَيْكَ الْمَصِيرُ
 

“መልክተኛው ከጌታው ወደ ርሱ በተወረደው አመነ። ምእምኖቹም (እንደዚሁ)። ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ ‘በአንድም መካከል አንለይም’ (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ። ‘ሰማን፤ ታዘዝንም። ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)። መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው’ አሉም።” (አል-በቀራህ 2፤ 285)

እውቅ በሆነው የጅብሪል (ዐ.ሰ) ሐዲስ ውስጥ ጅብሪል በደዊን ተመስሎ ወደነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በመምጣት ስለ ኢስላም፣ ኢማንና ኢሕሳን በጠየቃቸው ጊዜ ኢማንን እንዲህ አብራርተውለታል፡-

أن تؤمن بالله وملائكته وكتبه ورسله واليوم الآخر وتؤمن بالقدر خيره وشره- رواه مسلم

“በአላህ፣ በመላኢኮች፣ በመጽሐፎች፣ በመልእክተኞች፣ በመጨረሻው ቀንና በቀዷ ቀደር- በጎም ሆነ ክፉ- ማመንህ ነው።” (ሙስሊም)

ከላይ ከተወሱትና ከሌሎች በርካታ የቁርአን አናቅጽና የሐዲስ ዘገባ እንደምንረዳው ኢማን ስድስት ጽንሰ ሐሳቦችን አካትቷል። ከነዚህ ስድስት የእምነት ምሶሶዎችን (አርካን አል-ኢማን) በሁለተኛነት የተወሳው በመላኢኮች ማመን ነው። በዚህ ጽሁፍ ይህንን አበይት የእምነት ክፍል በዝርዝል እንመለከታለን።

1.መላእክት ምንድናቸው?

አልመለኡ አዕላ (የላይኛው ዓለም ነዋሪዎች) አሊያም የመላእክት ዓለም የሚባለው ከሰው ዓይን የራቀ ረቂቅና በስሜት ህዋሣት የማይደረስበት ዓለም ነው። መላእክት የሚደረስበት የሆነ የሚዳሰስና በቅርፅ የተወሠነ አካል የላቸውም። በተለምዶ ከምናውቀው ዓለም ለየት ያሉ በዐይን የማይታዩ ፍጡራን ሲሆኑ ትክክለኛ ምንነታቸውንም አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ብቻ ነው የሚያውቀው።

መላኢኮች ከእንሠሳዊ ስሜት የፀዱ ናቸው። ነፍስ ከምታዘነብልባቸው ነገሮችም የጠሩ ናቸው። ከወንጀልና ከሀጢኣትም የተጠበቁ ናቸው።

መላእክት እንደ ሰው ልጅ የሚበሉ፣ የሚጠጡ፣ የሚያንቀላፉ፣ በወንድም ሆነ በሴት ባህሪ የሚገለፁ አይደሉም። የመላኢካ ዓለም እራሱን የቻለና ከሌሎችም ዓለም ነፃ የሆነ ዓለም ነው። የሰው ልጅ በሚገለፅባቸው ቁሣዊ ባህሪዎች አይገለፁም።

መላኢኮች በሰው ልጅና በሌላ በሚዳሠስ ነገር ተመስለው የመታየት ችሎታ አላቸው። ጅብሪል ዐለይህ ሠላም ወደ ነቢዩ ዒሣ ዐለይህ ሠላም እናት መርየም የመጣው በሰው ቅርፅ ተመስሎ ነበር። በቁርኣን ላይ እንዲህ ተገልጧል።

وَاذْكُرْ فِي الْكِتَابِ مَرْيَمَ إِذِ انتَبَذَتْ مِنْ أَهْلِهَا مَكَانًا شَرْقِيًّا فَاتَّخَذَتْ مِن دُونِهِمْ حِجَابًا فَأَرْسَلْنَا إِلَيْهَا رُوحَنَا فَتَمَثَّلَ لَهَا بَشَرًا سَوِيًّا
 

“በመጽሐፉ ውስጥ መርየምንም ከቤተሰቧ ወደ ምሥራቃዊ ስፍራ በተለይች ጊዜ (የሆነውን ታሪኳን) አውሳ። ከእነሱም መጋረጃን አደረገች። መንፈሳችንምም (ጂብሪልን) ወደርሷ ላክን። ለእርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት።” (መርየም 19: 16-17)

ነቢዩ ኢብራሂም በልጅ ለማብሠር ብለው ከመላኢኮች የተወሠኑት ወደርሣቸው ሲመጡ በሰው ልጅ ተመስለው ነበር የመጡት። ነቢዩ ኢብራሂምም እንግዶች መስለዋቸው ምግብ አቀረቡላቸው። የሚከተለው የቁርኣን አንቀፅ ይህንን ይገልፅልናል።

وَلَقَدْ جَاءَتْ رُسُلُنَا إِبْرَاهِيمَ بِالْبُشْرَىٰ قَالُوا سَلَامًا قَالَ سَلَامٌ فَمَا لَبِثَ أَن جَاءَ بِعِجْلٍ حَنِيذٍ ﴿٦٩﴾ فَلَمَّا رَأَىٰ أَيْدِيَهُمْ لَا تَصِلُ إِلَيْهِ نَكِرَهُمْ وَأَوْجَسَ مِنْهُمْ خِيفَةً قَالُوا لَا تَخَفْ إِنَّا أُرْسِلْنَا إِلَىٰ قَوْمِ لُوطٍ ﴿٧٠﴾ وَامْرَأَتُهُ قَائِمَةٌ فَضَحِكَتْ فَبَشَّرْنَاهَا بِإِسْحَاقَ وَمِن وَرَاءِ إِسْحَاقَ يَعْقُوبَ ﴿٧١﴾ قَالَتْ يَا وَيْلَتَىٰ أَأَلِدُ وَأَنَا عَجُوزٌ وَهَـٰذَا بَعْلِي شَيْخًا إِنَّ هَـٰذَا لَشَيْءٌ عَجِيبٌ ﴿٧٢﴾ قَالُوا أَتَعْجَبِينَ مِنْ أَمْرِ اللَّهِ رَحْمَتُ اللَّهِ وَبَرَكَاتُهُ عَلَيْكُمْ أَهْلَ الْبَيْتِ إِنَّهُ حَمِيدٌ مَّجِيدٌ
 

“መልክተኞቻችንም ኢብራሂምን በ(ልጅ) ብስራት በእርግጥ መጡት። ሰላም አሉት። ሰላም አላቸው። ጥቂትም ሳይቆይ ወዲያውኑ የተጠበሰን የወይፈን ስጋ አመጣ። እጆቻቸውም ወደ እርሱ የማይደርሱ መኾነቸውን ባየ ጊዜ ሸሻቸው። ከነሱም ፍርሃት ተሰማው። ‘አትፍራ እኛ ወደ ሉጥ ሕዝቦች ተልከናልና’ አሉት። ሚስቱም የቆመች ስትኾን (አትፍራ አሉት) ሳቀችም። በኢስሐቅም አበሰርናት። ከኢስሐቅም በኋላ (በልጁ) በያዕቁብ (አበሰርናት)። (እርሷም) ዋልኝ! እኔ አሮጊት ይህም ባሌ ሽማግሌ ሆኖ ሳለ እወልዳለሁን? ይህ በእርግጥ አስደናቂ ነገር ነው አለች። ‘ከአላህ ትዕዛዝ ትደነቂያለሽን? የአላህ ችሮታና በረከቶቹ በእናንተ በኢብራሂም ቤተሰቦች ላይ ይሁን እርሱ ምስጉን ለጋስ ነውና’ አሉ።” (ሁድ ፡69-73)

2.ከምን ተፈጠሩ?

አላህ (ሱ.ወ) መላእክትን የፈጠረው ከብርሃን ነው። አደም (ዐ.ሰ) የተፈጠሩት ከጭቃ ሲሆን ጅኖች /አጋንንት/ ደግሞ የተፈጠሩት ከእሣት ነው። ኢማሙ ሙስሊም ከእናታችን ዓኢሻ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም

خُلِقت الملائكة من نور, وخُلق الجانّ من مارج من نار, وخُلق آدم مما وصف لكم- مسلم

“መላእክት የተፈጠሩት ከብርሃን ነው። ጅኖች ደግሞ ከእሣት ከሆነ ነበልባል የተፈጠሩ ሲሆን አደም ደግሞ ከዚህ በፊት ከተገለፀላችሁ ነገር ነው የተፈጠሩት።” ብለዋል (ሙስሊም)።

የመላኢኮች መኖሪያ ሰማይ ውስጥ ነው። ከዚያ የሚወርዱትም በአላህ (ሱ.ወ.) ትእዛዝ ነው። ኢማሙ አህመድ እና ቡኻሪይ ኢብኑ ዐባስን ጠቅሰው ከአላህ መልእክተኛ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ለወህይ መልእክተኛው ለጅብሪል (ዐ.ሰ.):-

“ከምትጎበኘን በበለጠ መልኩ ለምን አብዝተህ አትጎበኘንም? በማለት ጠየቁት። ጅብሪል (ዐ.ሠ.) የሚንቀሣቀሰው በአላህ ትእዛዝ ብቻ እንደሆነ ለማሣወቅ ይህች የቁርኣን አንቀፅ ወረደች

وَمَا نَتَنَزَّلُ إِلاَّ بِأَمْرِ رَبِّكَ لَهُ مَا بَيْنَ أَيْدِينَا وَمَا خَلْفَنَا وَمَا بَيْنَ ذَلِكَ وَمَا كَانَ رَبُّكَ نَسِيّاً
 

“(ጂብሪል አለ) ‘በጌታህም ትእዛዝ እንጅ አንወርድም። በፊታችን ያለው፣ በኋላችንም ያለው በዚህም መካከል ያለው ሁሉ የርሱ ነው። ጌታህም ረሺ አይደለም።’ (መርየም 19፡64)”

መላኢኮች የተፈጠሩት ከሰው ልጅ መፈጠር ቀደም ብሎ ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሰው ልጆችን እንደሚፈጥርና በምድር ላይም ኸሊፋ /ምትክ/ ወኪል/ ተጠሪ እንደሚያደርጋቸው ለመላኢኮች ነግሯቸው ነበር። ይህም በቁርኣን ተገልጧል

وَإِذْ قَالَ رَبُّكَ لِلْمَلَائِكَةِ إِنِّي جَاعِلٌ فِي الْأَرْضِ خَلِيفَةً قَالُوا أَتَجْعَلُ فِيهَا مَن يُفْسِدُ فِيهَا وَيَسْفِكُ الدِّمَاءَ وَنَحْنُ نُسَبِّحُ بِحَمْدِكَ وَنُقَدِّسُ لَكَ قَالَ إِنِّي أَعْلَمُ مَا لَا تَعْلَمُونَ 

“(ሙሐመድ ሆይ) ጌታህ ለመላእክት፡- ‘እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤’ ባለ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ፤ እነርሱም) ‘እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን?’ አሉ። (አላህ) ‘እኔ የማታውቁትን ነገር አውቃለሁ’ አላቸው።” (አልበቀራህ 2፡30)

3. የሰው ልጅ በደረጃ ከነሱ የሚበልጥ ስለመሆኑ

ግርድፍ መረጃዎች የሚያመለክቱት የሰው ልጅ ከመላእክት በደረጃ የሚበልጥ መሆኑን ነው። ድክመታቸውን በግልፅ ከሚያሣዩ ነገሮች መካከል አላህ (ሱ.ወ.) ዝርዝሩን እንዲነግሩት የጠየቃቸውን ሥሞች መመለስ አለመቻላቸው አንዱ ነው። በአንፃሩ ግን ይህንኑ ጥያቄ አላህ ለአባታችን አደም (ዐ.ሠ.) አቅርቦ እርሣቸውም በትክክል የመለሡ መሆኑ ይታወቃል። ይህም አላህ (ሱ.ወ.) ለአደም (ዐ.ሠ.) የሠጠው ልዩ የሆነ የእውቀት ክብር ነው። ከዚህም ክስተት በመነሣት የሰው ልጆች አባትና መነሻ የሆነው አደም (ዐ.ሰ.) ነገሮችን በማወቅና በመገንዘብ ደረጃ ከነሱ የተሻለ መሆኑን እንገነዘባለን።

ሌላው ደግሞ የሰው ልጆች ከመላኢኮች የሚበልጡ ስለመሆኑ ከሚያመለክቱ ነገሮች መካከል አላህ (ሱ.ወ.) መላኢኮችን ለአደም (ዐ.ሰ.) ሱጁድ እንዲያደርጉ ማዘዙ ነው። አላህ ሱ.ወ. እንዲህ አለ

وَعَلَّمَ آدَمَ الْأَسْمَاءَ كُلَّهَا ثُمَّ عَرَضَهُمْ عَلَى الْمَلَائِكَةِ فَقَالَ أَنبِئُونِي بِأَسْمَاءِ هَٰؤُلَاءِ إِن كُنتُمْ صَادِقِينَ ﴿٣١﴾ قَالُوا سُبْحَانَكَ لَا عِلْمَ لَنَا إِلَّا مَا عَلَّمْتَنَا إِنَّكَ أَنتَ الْعَلِيمُ الْحَكِيمُ ﴿٣٢﴾ قَالَ يَا آدَمُ أَنبِئْهُم بِأَسْمَائِهِمْ فَلَمَّا أَنبَأَهُم بِأَسْمَائِهِمْ قَالَ أَلَمْ أَقُل لَّكُمْ إِنِّي أَعْلَمُ غَيْبَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَأَعْلَمُ مَا تُبْدُونَ وَمَا كُنتُمْ تَكْتُمُونَ ﴿٣٣﴾ وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ أَبَىٰ وَاسْتَكْبَرَ وَكَانَ مِنَ الْكَافِرِينَ ﴿٣٤﴾

“አደምንም ስሞችን ሁሏንም አስተማረው። ከዚያም በመላእክት ላይ (ተጠሪዎቹን) አቀረባቸው። ‘እውነተኞችም እንደኾናችሁ የነዚህን (ተጠሪዎች) ስሞች ንገሩኝ’ አላቸው። ‘ጥራት ይገባህ፤ ከአስተማርከን ነገር በስተቀር ለኛ ዕውቀት የለንም። አንተ ዐዋቂው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና’ (አሉ)። ‘አደም ሆይ ስሞቻቸውን ንገራቸው’ አለው። ስሞቻቸውን በነገራቸውም ጊዜ ‘እኔ የሰማያትንና የምድርን ሩቅ ምስጢር ዐውቃለሁ፤ የምትገልጹትንና ያንንም ትደብቁት የነበራችሁትን ዐውቃለሁ አላልኳችሁምን?’ አላቸው። ለመላእክትም ‘ለአደም ስገዱ’ ባልን ጊዜ (አስታውስ)። ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ።”(አልበቀራህ 2፡31-34)

መላኢኮች ከሰው ልጆች ተሽለው የሚታዩበትን ጎን ያየን እንደሆነ አላህን ፍፁም በሆነ መልኩ መታዘዛቸው ነው። ነገር ግን ይህ ባህሪ ቀድሞውኑ የተፈጠሩበት እንጂ እራሣቸው በትግልና በጥረት ያመጡት አይደለም። ሀጢኣትን መተው መቻላቸው ጥቂት ትግል እንኳ አይጠይቃቸውም። ለምን ቢባል በሰው ልጅ ላይ ያለው የስሜት ፈተና የለባቸውምና።

ልብ እንደሚመታው፣ ደምም በሰውነት ውስጥ እንደሚዘዋወረውና ሁለቱ ሣንባዎችም በደመነፍስ እንደሚተነፍሱ ሁሉ መላኢኮችም አላህን መታዘዝና ሀጢኣትን መራቃቸው እነሱ የተፈጠሩለት ዓላማ ነውና ከሰው ልጅ የተሻሉ ናቸው አያስብልም። በአንፃሩ የሰው ልጅ ግን ነፍሱን ይታገላል፤ ከስሜቱ ጋር ግብግብ ይገጥማል፤ ሸይጧንን ይፋለማል፤ በአላህ ትእዛዝ ለመገኘት ይጥራል፤ ነፍሱን ምሉእ ለማድረግም የዘወትር ትግል ይጠበቅበታል፤ መንፈሱንም ለማምጠቅ በፍራቻና በክጀላ መካከል ይኖራል።

4.ባህሪያቸው

የመላእክት ባህሪ ሙሉ በሙሉ ለአላህ መታዘዝ፣ ለሀያልነቱ ማጎብደድና ትእዛዛቱን መፈፀም ነው። በአላህ ፈቃድና መሻትም በዓለም ጉዳዮች ወዲህ ወደያ ይንቀሣቀሣሉ። በነሱ አማካይነት አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሥልጣኑን ያሰፈፅማል። መላእክት በራሣቸው ፈቃድ አንድም ነገር ለማድረግ አቅም የላቸውም።

የሚከተሉት የቁርኣን አንቀፆችም ይህንኑ ያመለክታሉ

يَخَافُونَ رَبَّهُم مِّن فَوْقِهِمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ 

“ጌታቸውን ከበላያቸው ሲኾን ይፈሩታል። የታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ።” (አን-ነህል 16፤50)

بَلْ عِبَادٌ مُّكْرَمُونَ لَا يَسْبِقُونَهُ بِالْقَوْلِ وَهُم بِأَمْرِهِ يَعْمَلُونَ يَعْلَمُ مَا بَيْنَ أَيْدِيهِمْ وَمَا خَلْفَهُمْ وَلَا يَشْفَعُونَ إِلَّا لِمَنِ ارْتَضَىٰ وَهُم مِّنْ خَشْيَتِهِ مُشْفِقُونَ
 

“አይደለም (መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናቸው። በንግግር አይቀድሙትም፤ (ያላለውን አይሉም)። እነርሱም በትእዛዙ ይሠራሉ። በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል። ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም። እነርሱም እርሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተጨናቂዎች ናቸው።” (አል አንቢያእ 21፤26-28)

لَّا يَعْصُونَ اللَّهَ مَا أَمَرَهُمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ 

“አላህን ያዘዛቸውን ነገር (በመጣስ) አያምጹም። የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ።” (አት-ተህሪም 66፤6)

ኢማም ቡኻሪይ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ አሉ

إذا قضى الله الأمر فى السماء ضربت الملائكة بأجنحتها خضعانًا لقوله, كـأنه صلصلة على صفوان, فإذا فُزِّع عن قلوبهم قالوا: ماذا قال ربكم ؟ قال الحق, وهو العلى الكبير

“አላህ በሰማይ ውስጥ የአንድ ነገር ውሣኔ ያስተላለፈ እንደሆነ ለንግግሩ በመተናነስ መላኢኮች በክንፎቻቸው ይመታሉ፤ የምቱም ድምፁም ተከታታይ የሆነ የድንጋይ ደወል ይመስላል። ከልቦቻቸውም ከድንጋጤ በተገፈፈላቸው ጊዜ ‘ጌታችሁ ምን አለ’ በማለት ይጠይቃሉ። ‘እውነት ተናገረ፤ እሱ ከፍ ያለና ታላቅ ነው’ ይላሉ።” (ቡኻሪይ)

5.መበላለጣቸው

መላእክት በጥንካሬና በችሎታቸው እንደሚበላለጡ ሁሉ በአፈጣጠርም ይበላለጣሉ። ይህንንም የሚያውቅ አላህ ሱብሃሁ ወተኣላ ብቻ ነው። አላህ እንዲህ አለ

الْحَمْدُ لِلَّهِ فَاطِرِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ جَاعِلِ الْمَلَائِكَةِ رُسُلًا أُولِي أَجْنِحَةٍ مَّثْنَىٰ وَثُلَاثَ وَرُبَاعَ يَزِيدُ فِي الْخَلْقِ مَا يَشَاءُ إِنَّ اللَّهَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ 

“ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ፣ መላእክትን ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሶስት ሶስትም፣ ባለ አራት አራትም ክንፎች የኾኑ መልክተኞች አድራጊ ለኾነው አላህ ይገባው። በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል። አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና።” (ፋጢር 35፤1)

ከዚህ የቁርኣን አንቀፅ የምንረዳው አላህ መላኢኮችን የክንፍ ባለቤቶች ያደረጋቸው መሆኑን ነው። ከነሱ ውስጥ ሁለት ክንፍ ያለው አለ። ሦስት ክንፍ ያለውም አለ። አራት ክንፍ ያለውም እንዲሁ። ከዚህም በላይ ያለውም አለ። ይህም ከአላህ (ሱ.ወ.) ዘንድ የተሠጣቸው ችሎታም ሆነ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሣቀስ ብቃታቸው የሚበላላጥ ስለመሆኑ አመላካች ነው።

ኢማም ሙስሊም ከዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ (ረ.ዐ.) እንደዘገቡትም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ጅብሪልን ስድስት መቶ ክንፍ ያለው ሆኖ አይተውታል። የክንፎች መብዛት ጥንካሬንና ጉልበትን አመላካች ነው። የተሠጣቸውን ችሎታ በመጠቀምም የአላህን ትእዛዝ በብቃት ይፈፅማሉ፤ መልእክቱንም በአፋጣኝ ያደርሣሉ። አላህ እንዲህ አለ

وَمَا مِنَّا إِلَّا لَهُ مَقَامٌ مَّعْلُومٌ وَإِنَّا لَنَحْنُ الصَّافُّونَ وَإِنَّا لَنَحْنُ الْمُسَبِّحُونَ 

“(ጂብሪል አለ) ከእኛም አንድም የለም፤ ለእርሱ የታወቀ ደረጃ ያለው ቢሆን እንጅ። እኛም (ጌታን ለመግገዛት) ተሰላፊዎቹ እኛ ነን። እኛም (አላህን) አጥሪዎቹ እኛ ነን።” (አስ ሷፋት ፤164-166)

ታዋቂው የቁርኣን ተንታኝ ኢማም ኢብኑ ከሲር ረሂመሁሏህ “ለያንዳንዱ መላኢካ በሰማያት ውስጥ ለሱ የተወሠነ ቦታ አለው፤ የአምልኮ ተግባራት የሚፈፅምባቸው ቦታዎችም አሉት፤ ከዚያ ከተወሠነለት ቦታ ርቆ አይሄድም ከድንበሩም አያልፍም።” ብለዋል።

ኢብኑ ዐሣኪር ደግሞ በትርጉማቸው ከዐብዱረህማን ኢብኑል ዐላእና ከአባቱ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) አንድ ቀን አብረዋቸው ይቀመጡ ለነበሩ ሰዎች:-

أطّت السماء وحُقّ لها أن تئط, ليس فيها موضع قدم إلا عليه ملك راكع أو ساجد.. ثم قرأ: وَمَا مِنَّا إِلاَّ لَهُ مَقَامٌ مَعْلُومٌ وَإِنَّا لَنَحْنُ الصَّافُّونَ وَإِنَّا لَنَحْنُ الْمُسَبِّحُونَ

“ ‘ሰማይ ጢጥ ስጢት አለች። ጢጥ ስጢጥ ማለቷም ተገቢ ነው። ምክኒያቱም በሷ ውስጥ ለአንድ እግር ማሣረፊያ እንኳን የሚሆን ቦታ የለም መልአክ በሩኩዕ አሊያም በሱጁድ ላይ የተገኘ ቢሆን እንጂ።’ አስከትለውም ከላይ የተጠቀሰውን የቁርአን አንቀፅ አነበቡ።”

6.መንፈሣዊ ተግባራቸው

በመንፈሣዊው ዓለምም ሆነ በምናውቀውና በተለመደው በኛ ዓለም መላኢኮች የተሠማሩበት ተግባራት አሉ። ከሰው ልጆች ጋርም ልዩ የሆነ ግንኙነት አላቸው።

ከመንፈሣዊው ዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት በአጭሩ ሲዳሠስ ይህን ይመስላል:-

1.አላህን መቀደስ እና ፍፁም በሆነ መልኩ ለሱ መተናነስ

አላህ (ሱ.ወ.) እንደህ አለ:-

إِنَّ الَّذِينَ عِندَ رَبِّكَ لَا يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِهِ وَيُسَبِّحُونَهُ وَلَهُ يَسْجُدُونَ 

“እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት (መላእክት) እርሱን ከመገዛት አይኮሩም። ያወድሱታልም። ለእርሱም ብቻ ይሰግዳሉ።” (አል-አዕራፍ 7፤206)

وَتَرَى الْمَلَائِكَةَ حَافِّينَ مِنْ حَوْلِ الْعَرْشِ يُسَبِّحُونَ بِحَمْدِ رَبِّهِمْ

“መላእክትንም በጌታቸው ምስጋና ቀላቅለው የሚያጠሩ ሲኾኑ በዐርሹ ዙሪያ ከባቢዎች ኾነው ታያለህ።” (ዙመር 39፤75)

2.ዐርሽን መሸከም

አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ አለ:-

الَّذِينَ يَحْمِلُونَ الْعَرْشَ وَمَنْ حَوْلَهُ يُسَبِّحُونَ بِحَمْدِ رَبِّهِمْ وَيُؤْمِنُونَ بِهِ وَيَسْتَغْفِرُونَ لِلَّذِينَ آمَنُوا رَبَّنَا وَسِعْتَ كُلَّ شَيْءٍ رَّحْمَةً وَعِلْمًا فَاغْفِرْ لِلَّذِينَ تَابُوا وَاتَّبَعُوا سَبِيلَكَ وَقِهِمْ عَذَابَ الْجَحِيمِ 

“እነዚያ ዐርሹን የሚሸከሙት እነዚያም በዙሪያው ያሉት በጌታቸው ምስጋና ያወድሳሉ። በእርሱም ያምናሉ። ‘ጌታችን ሆይ! ነገሩን ሁሉ በእዝነትና በዕውቀት ከበሃል። ስለዚህ ለእነዚያ ለተጸጸቱት መንገድህንም ለተከተሉት ምሕረት አድርግላቸው። የእሳትንም ቅጣት ጠብቃቸው።’ እያሉ ለእነዚያ ላመኑት ምሕረትን ይለምናሉ።” (ጋፍር 40፤7)

وَيَحْمِلُ عَرْشَ رَبِّكَ فَوْقَهُمْ يَوْمَئِذٍ ثَمَانِيَةٌ
 

“የጌታህንም ዐርሽ በዚያ ቀን ስምንት መላእክት ከበላያቸው ይሸከማሉ።” (አልሃቀህ 69፤17)

3.ለጀነት ሰዎች ሠላምታ ማቅረብ

جَنَّاتُ عَدْنٍ يَدْخُلُونَهَا وَمَن صَلَحَ مِنْ آبَائِهِمْ وَأَزْوَاجِهِمْ وَذُرِّيَّاتِهِمْ وَالْمَلَائِكَةُ يَدْخُلُونَ عَلَيْهِم مِّن كُلِّ بَابٍ سَلَامٌ عَلَيْكُم بِمَا صَبَرْتُمْ فَنِعْمَ عُقْبَى الدَّارِ 

“(እርሷም) የመኖሪያ ገነቶች ናት። ይገቡባታል። ከአባቶቻቸውም፣ ከሚስቶቻቸውም፣ ከዝርያቸውም መልካም የሠራ ሰው (ይገባታል)። መላእክትም በእነርሱ ላይ ከየደጃፉ ሁሉ ይገባሉ። ‘ሰላም ለእናንተ ይኹን። (ይህ ምንዳ) በመታገሳችሁ ነው። የመጨረሻይቱም አገር ምን ታምር!’ (ይሏቸዋል)።” (አር ረዕድ 13፤23-24)

4.እሳት/ጀሀነም/ እንዲገቡ የተደረጉ ሰዎችን መቅጣት

አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ አለ:-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا قُوا أَنفُسَكُمْ وَأَهْلِيكُمْ نَارًا وَقُودُهَا النَّاسُ وَالْحِجَارَةُ عَلَيْهَا مَلَائِكَةٌ غِلَاظٌ شِدَادٌ لَّا يَعْصُونَ اللَّهَ مَا أَمَرَهُمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ
 

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነፍሶቻችሁንና ቤተሰቦቻችሁን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጋዮች ከኾነች እሳት ጠብቁ። በእርሷ ላይ ጨካኞች፣ ኀይለኞች የኾኑ መላእክት አልሉ። አላህን ያዘዛቸውን ነገር (በመጣስ) አያምጹም። የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ።”(አት-ተህሪም 66፤6)

وَمَا أَدْرَاكَ مَا سَقَرُ ﴿٢٧﴾ لَا تُبْقِي وَلَا تَذَرُ ﴿٢٨﴾ لَوَّاحَةٌ لِّلْبَشَرِ ﴿٢٩﴾ عَلَيْهَا تِسْعَةَ عَشَرَ ﴿٣٠﴾ وَمَا جَعَلْنَا أَصْحَابَ النَّارِ إِلَّا مَلَائِكَةً 

“ሰቀር ምን እንደኾነች ምን አሳወቀህ? (ያገኘችውን ሁሉ) አታስቀርም አትተውምም። ቆዳን በጣም አክሳይ ናት። በእርሷም ላይ አሥራ ዘጠኝ (ዘበኞች) አሉባት። የእሳትንም ዘበኞች መላእክት እንጅ ሌላ አላደረግንም።” (አል ሙደሲር 74፤27-31)

5.የወህይ መልእክት /መለኮታዊ ራእይ/ ይዞ መውረድ

የወህይ መልአክ መልአኩ ጅብሪል ነው። አላህ እንዲህ አለ:-

قُلْ مَن كَانَ عَدُوًّا لِّجِبْرِيلَ فَإِنَّهُ نَزَّلَهُ عَلَىٰ قَلْبِكَ بِإِذْنِ اللَّهِ مُصَدِّقًا لِّمَا بَيْنَ يَدَيْهِ وَهُدًى وَبُشْرَىٰ لِلْمُؤْمِنِينَ

“ለጂብሪል (ለገብርኤል) ጠላት የኾነ ሰው (በቁጭት ይሙት) በላቸው። እርሱ (ቁርኣኑን) ከበፊቱ ለነበሩት (መጻሕፍት) አረጋጋጭ ለምእመናን መሪና ብስራት ሲኾን በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና።” (አል በቀራህ 2፤97)

ጅብሪል ሩህ አል-አሚን /ታማኙ መንፈስ/ ይባላል። አላህ እንዲህ አለ:-

وَإِنَّهُ لَتَنزِيلُ رَبِّ الْعَالَمِينَ نَزَلَ بِهِ الرُّوحُ الْأَمِينُ عَلَىٰ قَلْبِكَ لِتَكُونَ مِنَ الْمُنذِرِينَ

“ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)።” (አሽ ሹዓራእ 26፤192-194)

ሩሁል ቁዱስ /ቅዱስ መንፈስ/ ም ይባላል። አላህ እንዳለው:-

قُلْ نَزَّلَهُ رُوحُ الْقُدُسِ مِن رَّبِّكَ بِالْحَقِّ لِيُثَبِّتَ الَّذِينَ آمَنُوا وَهُدًى وَبُشْرَىٰ لِلْمُسْلِمِينَ 

“እነዚያን ያመኑትን ለማረጋጋት ሙስሊሞቹንም ለመምራትና ለማብሰር (ቁርኣንን) ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲኾን ከጌታህ አወረደው በላቸው።” (አን ነህል 16፤102)

እንዲሁም ደግሞ “ናሙስ” ይባላል። በነቢዩ ሰ.ዐ.ወ. ታሪክ እንደምናውቀው ወረቀህ ኢብኑ ነውፈል ለአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በርግጥም አላህ በሙሣ ላይ ያወረደው ናሙስ ወዳንተ መጥቷል እንዳላቸው ይታወሣል።

ጅብሪል (ዐ.ሠ.) መለኮታዊዉን ራዕይ ወደ አላህ መልእክተኛ ይዞ ሲመጣ አንዳንዴ በሰው አምሣያ፤ አንዳንዴ ደግሞ የደወል በሚመስል ድምፅ መልክ ይመጣ ነበር። ቡኻሪይ ከእናታችን ዓኢሻ (ረ.ዐ.) እንደዘገቡት ሃሪስ ኢብኑ ሂሻም የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.)

أن الحارث بن هشام رضى الله عنه سأل الرسول صلى الله علية وسلم فقال: يا رسول الله, كيف يأتيك الوحى ؟ فقـال: «أحيانًا يـأتينى مثل صلصلة الجرس, وهو أشده علىّ, فيفصم عنى وقد وعيت عنه ما قال.. وأحيانًا يتمثل فى الملك رجلاً فيكلمنى فأعى ما يقول » ؛ قالت عائشة: ولقد رأيته ينزل عليه الوحى فى اليوم الشديد البرد فيفصم عنه, وإن جبينه ليتفصد عرقًا.

“ወህይ በምን መልኩ ነው ወዳንተ የሚመጣው? በማለት ጠየቃቸው። እርሣቸውም አንዳንዴ በደወል ድምፅ መልክ ወደኔ ይመጣል። ይህም በኔ ላይ ከባዱ ነው። ከዚያም ከኔ ይነቀላል፤ እኔ ያወቅኩ /የገባኝ/ ስሆን። አንዳንዴ ደግሞ መልአኩ በሰው ተመስሎ ይመጣና ያናግረኛል። እኔም የሚለውን እረዳለሁ።” ዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ ‘እጅግ ብርዳማ በሆነው ቀን ወህይ በሣቸው ላይ ሲወርድና ከሣቸው ላይ ሲነሳ አይቻለሁ፤ ከክስተቱ በኋላ ግንባራቸው በላብ ተጠምቆ ይታይ ነበር።’ ብላለች።” (ቡኻሪይ)

አቢ ዱንያ እና አል ሃኪም ከኢብኑ መስዑድ በዘገቡት ሀዲስ ደግሞ

إن روح القدس نفث فى روعى أن نفسًا لن تموت حتى تستكمل رزقها, فاتقوا الله وأجملوا فى الطلب

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሩሁል ቁዱስ (ቅዱስ መንፈስ /ጅብሪል) አንዲት ነፍስ ሲሳዩዋን ሣትጨርስ አትሞትምና አላህን ፍሩ፤ ሲሳይ አፈላለጋችሁም አሣምሩ በማለት በውስጤ አሣውቆኛል።” ብለዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here