መጠነኛ ቅኝት ስለ ኹለፋኡ ራሽዲን ዘመን (ክፍል 6)

0
2637

በባለፈው መጣጥፋችን በተለይ አስተዳደርና ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና  በኢስላማዊው መንግስት ውስጥ ያስገቡትን አዳዲስ የአሠራር ለውጦች፣ በዜጎች መካከል ፍትህና እኩልነት ይሰፍን ዘንድ የሰሩትን ሥራና በነቢያት ዘንድ ካልሆነ በስተቀር በታሪክ አምሣያ ያልተገኘለትን ለሰው ልጆች ሁሉ የነበራቸው እዝነትና ርህራሄ እንዴት እንደነበር ለማየት ሞክረን ነበር፡፡

ዛሬ ደግሞ አላህ ካለ በፖለቲካዊና አስተዳራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ታሪካቸውን በመጠኑ እንዳስሣለን፡፡

ባለፈውም እንዳየነው ዑመር ሀላፊዎችን በመምረጡ ረገድ ከስሜታዊነትና ከደመነፈስ ፈፅሞ የራቁ ሰው ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ከመስለሙ በፊት የማማ በተባለ ቦታ ላይ ወንድማቸውን ዘይድ ኢብኑ አልኸጧብን ገድሎ የነበረውን አባ መርየም አልሀነፊን የበስራ ቃዲ/ዳኛ/ አድርገው ሹመዋል፡፡ ዑመር በወንድማቸው ሞት እጅግ የተሰማቸውና ያዘኑ ከመሆናቸው ጋር ቂሙን ረስተው የወንድማቸውን ገዳይ ለዚህ ታላቅ ቦታ ማጨታቸው በርግጥም ታላቅነታቸውን ያመላከተ ነበር፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ዳኞችን ሲሾሙ የሰዎችን እያንዳንዷን ትናንሽ ስህተትና ድልጠት እንዳይከታተሉ ያሳስቡአቸውም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ሸርሃቢል ኢብኑ አስ ሰመጥ አልክንዲ በአልመዳኢን ላይ በተሾመበት ወቅት እንዲህ በማለት ተጣራ ‹ሰዎች ሆይ! እናንተ ያላችሁት መጠጥ እጅግ በተስፋፋበት ሀገር ውስጥ ነው፡፡ ሴቶችም በዝተው ነው ያሉት፡፡ የአላህን ወሰን የተላለፈ ሰው ወደኛ ይምጣ፡፡ እኛም የአላህን ህግ እናስፈፅምበታለን፡፡ ይህም ለሱ ንፅህናው ይሆንለታል፡› ይህ ጉዳይ ወደ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በደረሠ ጊዜ እንዲህ በማለት ፃፉለት ‹ ሰዎች አላህ ገመናቸውን እስከሸፈነ ድረስ ገመናቸውን እንደትገልጥ አልፈቅድልህም፡፡› (1)

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና የሰው ልጅ ነፍስ በባህሪዋ በየትኛውም ጊዜ ለስህተትና ለወንጀል የተጋለጠች መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓይነቱ ጊዜ አላህ እስካላጋለጠ ድረስ እራስ ለአደባባይ አለማብቃት /መሰተር/ ይመረጣል፡፡ ነገሩ ወደማህበረሰቡ ተዛምቶ ጉዳት እስካላደረሠ ድረስም የሰዎችንም ጉዳይ ለአላህ መተው ይበጃል፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በህግ ፊት ለመቆምም እራሣቸውን የመጀመሪያው ምሣሌ ያደረጉ ሰው ናቸው። ይህም ድርጊታቸው አንድ ሰው ምንም እንኳን ከፍ ያለ ሥልጣን ቢኖረውም እንዳይኩራራ ትምህርት ይሆነዋል፡፡ በአንድ ወቅት ከታላቁ ሰሃባ ኡበይ ኢብኑ ከዕብ ጋር በአንዲት የእርሻ ማሣ ይገባኛል ላይ ተካሰሱ፡፡ ዘይድ ኢብኑ ሣቢት በመካከላቸው እንዲፈርድም ፈቀዱ፡፡ ወደቤቱ ሄደውም ሲገቡ ዑመር ለዘይድ እንዲህ አሉት፡፡ ‹ወዳንተ የመጣነው በመካከላችን እንድትፈርድ ነው፡፡ ዳኛ ደግሞ በቤቱ እያለ ነው የሚመጣበት፡፡› (2)

ዘይድ ከፍራሹ ግርጌ እንዲቀመጡ በማሰብ ቦታውን አሠፋላቸው፡፡ የምእመናን መሪ ሆይ! ና እዚህ ጋ አላቸው፡፡ ዑመርም ‹ዘይድ ሆይ! ዳኝነትን ፈልጌ  ወዳንተ የመጣሁት እኔ ነኝ፡፡ በመሆኑም ከተሟጋቼ ጋር አስቀምጠኝ፡፡› አሉት፡፡ ሁለቱም ፊት ለፊቱ ተቀመጡ፡፡ ኡበይ ክሱን አሠማ፡፡ ዑመር ደግሞ ክሱን አስተባበሉ፡፡ ዘይድ ለኡበይ ‹የምእመናን መሪ በዚህ ጉዳይ ላይ ከማለ ይቅር በለው፡፡ ከሱ ውጭ ይህንን ነገር ለማንም አልጠይቅም፡፡› አሉት፡፡ ዑመር ማሉ፡፡ ደግመውም ማሉ፡፡ በዚህ መልኩ እርሣቸውና አንድ ተራ ሙስሊም በህግ ፊት ኩል መሆናቸውን ለዘይድ አስገነዘቡ፡፡

በዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ዘመን ምንም እንኳን ኢስላማዊው መንግስት በእድሜ ገና ልጅ መሆኑ ቢታወቅም በሁሉም ነገሮች ዙሪያ ብልሃትና ብልጠትን የተላበሠ ነበር፡፡ መንግስቱ ሌላው ቀርቶ አምባሣደሮችን በመምረጥ ጭምር ጥንቃቄ የሚያደርግ የነበረ ሲሆን የቀለም ትምህርት ባይኖረውም እንኳ ለዚህ ተልእኮ ንግግሩ፣ ቁመናው እና ሞገሱ እንዲሁም የማሳመን ብቃቱ  አስደማሚ የሆነ ሰው ነበር የሚታጨው፡፡

በአንድ ወቅት ዙሕረህ ኢብኑ ዐብዱሏህ ኢብኑ ቀታዳህ በአምባሣደርነት ተሹሞ የፋርሦች መሪ ወደሆነው ሩስቱም ዘንድ ተላከ፡፡ ሩስቱምም ባየው ጊዜ እንዲህ አለው ‹እናንተ ጎረቤቶቻችን ናችሁ፡፡ ከናንተ የተወሰኑት ክፍሎች ደግሞ በኛ አገዛዝ ሥር ነበሩ፡፡ እኛ ደግሞ ለነርሱ ያሣየነው ጉርብትና እጅግ መልካም ነበር፡፡ አናስቸግራቸውም፡፡ ብዙ ነገሮችንም አብረን እንሠራ ነበር፡፡ በገጠር ያሉ ሰዎቻቸውን እንንከባከብላቸው ነበር፡፡ የግጦሽ ማሣዎችቻንን ይጠቀሙ፤ በሀገራችንም ተደላድለው በየትኛውም ክልል እንዲነግዱ የማንከለክላቸው የነበረ ሲሆን ይህም ጥሩ የመተዳደሪያ ገቢ ሆኖላቸው ነበር፡፡›

ዙህረህም በበኩሉ እንዲህ አለው ‹ያነሣሀው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ እኛና ያልካቸው ሰዎች እንለያያለን፡፡ እኛ የምንፈልገው አንተ ያልካቸው ሰዎች የሚፈልጉትን አይደለም፡፡ እኛ ገንዘብ ፈልገን አይደለም ወደናንተ የመጣነው፡፡ የምንፈልገውና የሚያሣስበን ነገር የመጨረሻው ዓለም ጉዳይ ነው፡፡ አንተም እንዳልከው ከኛ መካከል የተወሰኑ ወገኖች ለናንተ ተገዥዎች ነበሩ፡፡ ከናንተ ዘንድ ያለውንም በመከጀል ይተናነሱላችሁ ነበር፡፡ ኋላ ግን አላህ ተባረከ ወተዓላ ወደኛ መልእክተኛን ላከ፡፡ ወደጌታውም ጠራንና ጥሪውን ተቀበልን፡፡ አላህም ለነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ አሉ ‹እኔ በሃይማኖቴ የማይመራውን ወገን ይህችን አንጃ ልኬበታለሁ፡፡ እኔም በነሱ አማካይነት እበቀለዋለሁ፡፡ በሱ እስከረጉ ድረስ ሁልጊዜም የበላይነትንና አሸናፊነትን ለነሱ አደርጋለሁ። እሱ እውነተኛ ሃይማኖት ነው፡፡ እሱን አጥብቆ የያዘ መክበሩ አይቀርም፡፡› ሩስቱምም እንዲህ አለው ‹ምንድነው እሱ?›  ‹እሱማ በሱ አንድም ነገር የማይስተካከል የሆነ ምሰሶ ሲሆን እሱም ‹ላ ኢላሀ ኢለላህ ሙሀመድ ረሱሉላህ/ ከላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም ሙሀመድ የአላህ መልእክተና ናቸው፡፡› ብሎ መመስከር ነው፡፡ እሱ ከተላቀው አላህ ዘንድ ይዞ የመጣውንም ነገር እውነትነት ማረጋገጥ ነው፡፡› አለው፡፡ ሩስቱምም ‹ይህ ምንኛ መልካም ነው! ምንድነው እሱ ደግሞ?› አለ፡፡ ዙህረህም ‹እሱም ባሮችን ከባሮች አምልኮ ወደ ተላቀውና ተከበረው አምልኮ ነፃ ማውጣት ነው፡፡› ሩስቱምም ‹እሺ መልካም፡፡ አሁንም ምንድነው እሱ?› አለው፡፡ ዙህረህም ‹የሰው ልጆች ሁሉ የአደም እና የሀዋ ሲሆኑ በእናትም በአባትም ወንድማማቾች ናቸው፡፡› ሩስቱምም ‹ይህ ምንኛ ያማረ ነው!› አለ፡፡

የዛሬዎቹን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ብንመለከት ትምህርታቸው ከዚህ የሚስተካከል አይደለም፡፡ ገለፃቸውም ከኢስላማዊዉ ገለፃ ጋር ፈፅሞ አይስተካከልም፡፡

ሩስቱምም ለዙህረህ እንዲህ አለው፡፡ ‹እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ብስማማና ከህዝቦቼም ጋር ሆኜ ለመቀበል እሺ ብል ምን ትላላችሁ? ወደመጣችሁበት ትመለሣላችሁን?›፡፡ ዙህራም ‹አዎን፡፡ ወላሂ ለንግድ እና ለጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ወደ ሀገራችሁ አንቀርብም፡፡› አለው፡፡ ሩስቱምም ‹እውነት ብለሃል፡፡› አለው፡፡ ወላሂ የፋርስ ሰዎች አርደሺር ስልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ አንድንም ሰው ከታችኛው የማህበረሰብ ክፍል በኩል ወደላይ እንዲወጣ አይፈቅዱም፡፡› እንዲህም ይሉ ነበር ‹ከሥራቸው የወጡ እንደሆነ ድንበራቸውን ያልፋሉ፡፡ አለቆቻቻቸውንም ይዳፈራሉ፡፡›

ዙህረህም እንዲህ አለው ‹እኛ ለሰዎች እጅግ መልካም የሆንን ሰዎች ነን፡፡ እናንተ እንደምትሉት አይደለንም፡፡ በአላህ ጉዳይ ከበታቻችን ያሉትንም ቢሆን እንታዘዛለን፡፡ በኛ ጉዳይ አላህን ያልታዘዘ እኛን አይጎዳንም፡፡› (4)

የያኔዎቹ ሙስሊሞች ካላቸው አስፈሪ ሞገስ እንዳይወርዱ በጣም ይጠነቀቁ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ሩብዒይ ኢብኑ ዓሚር ከነመሣሪያው የፋርሦች መሪ ከሆነው ሩስቱም ዘንድ ሊገባ ሲል መሳሪያውን እንዲያስቀምጥ አዙት፡፡ እሱም ቆፍጠን በማለት ‹እኔ አይደለሁም ወደናንተ የመጣሁት፡፡ የጠራችሁኝ እናንተ ናችሁና መሣሪያዬን አላስቀምጥም፡፡ እንዲህ እንደመጣሁ እንዳልገባ የማትፈቅዱልኝ ከሆነ እመለሣለሁ፡፡› አላቸው፡፡

 እንዲሁም ንግግራቸውም ምጥንና የተስተካከለ ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ፋርስ ንጉሦች የሚልኳቸው ደብዳቤዎች ቃላቶቻቸውና መልእክቶቻቸው አንድ ወይም ብዙም ያልራቁ ነበሩ፡፡

ፋርሦች እና ሩሞች በዘመኑ ሰዎች የልቅና ምልክት ብለው የሚያስቧቸውን የውሸት የሆኑ ማስመሰያዎችን ያከብሩ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በዚህ አስተሣሰባቸው ኪሣራን እንጂ ሌላ ነገር አላተረፉም፡፡ ወደ ሩስቱም እንመለስ፡፡ ከዙህረህ ከተለያየ በኋላ ሩስቱም የፋርስ ትላልቅ ሰዎችን በመሰብሰብ ‹ምን ይመስላችኋል? ከዚህ ሰውዬ የበለጠ ግልፅ እና ክቡር የሆነ ንግግር አይታችኋልን?› አላቸው፡፡ እነሱም ‹ወደዚህ ነገር እንዳታዘነብልና ለዚህ ውሻ ብለህ ሃይማኖትህን እንዳትተው በፈጣሪ እንጠበቃለን፡፡ ልብሱን አትመለከትም እንዴ!› አሉት፡፡ እሱም ‹ወየውላችሁ ወደ ልብስ አትመልከቱ፡፡ ነገርግን ወደ ሀሣብ፣ ወደ ንግግርና ታሪክ ተመልከቱ፡፡ ዐረቦች ስለ ልብስና ምግብ ግድ የላቸውም፡፡ ክብራቸውን ይጠብቃሉ፡፡ በልብስ ጉዳይ እንደናንተ አይደሉም፡፡ በሱ ጉዳይ ለናንተ የሚታያችሁ አይታያቸውም፡፡› አላቸው፡፡ (5)

ዛሬ ላይ ሆነን ስናይ ግን የዐረቦች ሁኔታ ተለውጧል፡፡ ስለ ውጫዊ እይታቸው መጨነቅ መጠበባቸው ከቀደምት ፋርሦች ጋር አመሣስሎአቸዋል፡፡ አብዛኞቹ የዐረቡና የሙስሊሙ ዓለም አምባሣደሮችም የዛሬው ሙስሊም ማህበረሰብ ሁኔታ ብዙም የሚያሣስባቸው አይመስሉም፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በተፈቀዱ ነገሮች ውስጥ እንኳ አንድም ሰው ብክነት ውስጥ እንዲገባ አይፈቅዱም ነበር፡፡ በተለይ ያ ነገር በብዙሃኑ ማህበረሰቡ ጥቅም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሣድር ከሆነ፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና አንድ ህዝብ ያመፀ እንደሆን ምክኒያቱን ሣያውቁ በጅምላ አይቀጡም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በአንዳንድ የፋርስ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች አመፁ፡፡ በዚህን ጊዜ ዑመር መጀመሪያ ያደረጉት ነገር የአመፁ ምክኒያት ምን እንደሆነ ማጣራት ነበር፡፡ ለአስተዳዳሪዎቻቸም ‹ወየውላችሁ እናንተ ጨቁናችኋቸው እንዳይሆን!› አሏቸው፡፡ እነሱም ‹ወላሂ አይደለም፡፡ የአመፃቸውም ምክኒያት ሀገሪቱን የተነጠቀው የዝድጅርድ ከኋላቸው ሆኖ  ግዛቱን ለማስመለስ እያነሣሣቸው ስለሆነ ነው፡፡› አሏቸው፡፡

በአንድ ወቅት በሙስሊሞች እና በሩሞች መካከል ጦርነት ተቀስቅሦ እያለ የሀገሬው ህዝብ በሰላም ይገበያይና ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ በሁለቱ ሀገራት የነበሩ ኤምባሲዎችም እንደነበሩ ቀጥለዋል፡፡ በወቅቱ ኡሙ ኩልሱም ቢንት ዐሊ ቢን አቢ ጧሊብ ለሩሟ ንግስት (የሂረቅል ሚስት) ሽቶ፣ ለምግብና መጠጥ የሚሆኑ ነገሮችን እና ሌሎች የሴቶች የመዋቢያ ቁሣቁሶችን በፖስታ አድርጋ ላከችላት፡፡ የሂረቅልም ሚስትም ሴቶችን በመሰብሰብ ‹ይህ የዐረብ ንጉስ እና የነቢያቸው ሚስት የሆነችው ሴት ስጦታ ነው፡፡› አለቻቸው፡፡ ለመልሱም ደብዳቤ ፃፈችላት፣ ውለታዋን መለሠችላት፣ ስጦታም ላከችላት፡፡› (6)

በረማዳ አመት በመዲና እና ዙሪያው ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ ነበር፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በሰዎች ጉዳይ በጣም ተጨናንቀው ስለነበር የኢስቲስቃእ ሰላትን (በዝናብ መጥፋት ጊዜ የሚሰገድ) እስከመርሣት ደረሱ፡፡ አንድ ቀን ግን አንድ ሰው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መልእክተኛ የሆነ ሰው በህልሙ እንዳየና ‹ለዑመር እንዲህ በል› የሚል መልእክት እንደነገረው ለመንገር ወደ ዑመር ሄደ ‹የኔ ቃልኪዳን ባንተ ላይ አለ፡፡ አንተ ደግሞ ቃልኪዳንን ከሚሞሉት ነህ፡፡ ቃልህንም አጥብቀህ ትይዛለህ፡፡ ዑመር ሆይ! ብልህ ሁን ብልህ ሁን፡፡› ሰውዬውም መጣና ዑመር በር ላይ ደረሠ፡፡ ለአገልጋዩም ‹የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የሆነ መልእክተኛ ይገባ ዘንድ ፍቀድለት፡፡›  አለው፡፡ አገልጋዩም ወደ ዑመር መጣና የሆነው ነገረው፡፡ ዑመርም ደነገጠ፡፡ ለአገልጋዩም ‹መጥፎ ነገር አይተህበታልን?› አለው፡፡ አገልጋዩም ‹የለም› አለው፡፡ ዑመርም ‹እንግዲያውስ አስገባው፡፡› አለው፡፡ ሰውዬው ገባና ወሬውን ሁሉ ነገረው፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ወጡና ሰዎችን ተጣሩ፡፡ ሚንበሩ ላይም ወጡ፡፡ ‹ወደ እስልምና በመራችሁ አላህ ይዤያችኋለሁ በኔ ላይ የምትጠሉትን ነገር አይታችኋልን?› አሏቸው፡፡ ‹በአላህ እንምላለን ምንም፡፡› አሉት፡፡ ‹ታዲያ ያ ለምን ሆነ?› አላቸው፡፡ ታሪኩን ነገራቸው፡፡ እነሱም መልእክቱ ገባቸው፡፡ ዑመር ግን አልገባቸውም ነበር፡፡ ‹ይህማ ለኢስቲስቃእ ሰላት መዘግየትህ ነው፡፡ በል እንስገድ፡፡› አሏቸው፡፡ ሰዎችን ተጣሩ፡፡ ቆመውም ንግግር አደረጉ፡፡ ንግግራቸው አጠር ያለ ነበር፡፡ ሁለት አጠር ያሉ ረከዓዎች አሰገዱ፡፡ ‹አላህ ሆይ! ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ መላም ሆነ ብልሀትም የለንም፡፡ ውስጣችንም ሀይል የለንም፡፡ መላም ሆነ ጥንካሬ ባንተ እንጂ የለም፡፡ አላህ ሆይ አዝንብልን፡፡ ባሮችህንም ሀገሪቱንም ነፍስ ዝራባቸው፡፡› አሉ፡፡ (7)

ከሰላት በኋላም ለመዲናና በዙሪያዋ ላሉ ሰዎች በእርዳታ ይደርሱላቸው ዘንድ ወደ ሌሎች ከተሞች ወዳሉ አስተዳዳሪዎች ፃፉ፡፡ ቶሎ የደረሰው አቡ ዑበይዳ ነበር፡፡ አራት ሺህ ግመል የምግብ ጭነት ይዞ ደረሠ፡፡ በመዲና ዙሪያ ለሚገኙት ሁሉ እንዲያከፋፍልም ሀላፊነት ሰጡት፡፡ አከፋፍሎ ጨርሦ ሊመለስ ሲል አራት ሺህ ድርሃም እንዲሠጠው አዘዙ፡፡ እሱም ‹የምእመናን መሪ ሆይ! አያስፈልገኝም፡፡ እኔ የምፈልገው አላህን እና እሱ ዘንድ ያለውን ምንዳ ነው፡፡ ዱኒያን አታስገባብኝ፡፡› ብሎ ወደ ሥራው ተመለሠ፡፡ አቡ ዑበይዳን ተከትሎ የሂጃዝ ሰዎች እስኪብቃቁ ድረስ ሌሎችም እርዳታዎች ጎረፉ፡፡

አንድ ቀን ዐምር ኢብኑ አልዓስ እንዲህ አላቸው ‹የሻም ባህር የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በተላኩ ጊዜ የተቆፈረና ወደ ዐረብ ባህር እንዲፈስ የተደረገ ነው፡፡ ነገርግን ሩሞች እና ቂብጦች (የግብፅ ክርስቲያኖች) አገዱት፡፡ በመዲና ያለው የምግብ ዋጋ ግብፅ ካለው ጋር ተመሣሳይ እንዲሆን ከፈለግክ ወንዝ ልቆፍርለትና መፍሠሻ ልገንባለት› አለው፡፡ ዑመርም ‹ጥሩ አድርግ እንዲያውም ቶሎ ብለህ ፈፅም፡፡› በማለት ፃፉለት፡፡ ዐምርም በቀልዙም ከተማ እያሉ ይህን ሥራ ሰራ፡፡ የመዲና የምግብ ዋጋም ከግብፅ ጋር ተመሣሣይ ሆነ፡፡ ይህም ለግብፅ ብልፅግናን እና መረጋጋትን ጨመረላት፡፡ (8) ምክኒቱም እሱ በቀደደው ወንዝ ዙሪያ የእርሻ ሥራ በሰፊው በመስፋፋቱ ነው፡፡ ይህ ዐምር የቀደደው ወንዝ የናይል እና የስዊዝ ቦይን የሚያገናኝ ነበር፡፡

በዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና የኸሊፋነት ዘመን ኢስላማዊው መንግስት በምስራቁም ሆነ በምዕራቡም በኩል እየሠፋ መጣ፡፡ ሰላም ፍትህና ብልፅግናም ሀገራትን አዳረሠ፡፡ ይህ መሆኑ ለተንኮለኞችና ለኢስላም ጠላቶች የሚዋጥላቸው አልሆነም፡፡ ከውጭ በኩል አንድም አካል የናይልን ወንዝ የሚዳፈር ልነበረም፡፡ ነገርግን ኢስላማዊውን መንግስት በውስጥ በኩል ለመቦርቦርና ለማዳከም ሴራዎች ተጀመሩ፡፡ ዑመርንም ለመግደል አሴሩ፡፡ በዙሪያቸው ምንም ጠባቂ አለመኖሩ ደግሞ የልብ ልብ ሰጣቸው፡፡ እርሣቸውም ቢሆኑ በመዲና ውስጥ አንድም ጠላት እንደሌላቸው እርግጠኛ ነበሩ፡፡ እነዚህ አካላት ለመዲና ሰዎች ባሮች የነበሩት በመሰባሰብ ሌሎቹ ደግሞ ላያቸውን የሠለሙ በመምሰል በመዲና ውስጥ ለመኖር እንዲፈቀድላቸው ጠየቁ፡፡

የአል ሙጊራህ ኢብኑ ሹዕባ አገልጋይ የሆነው አቡ ሉእሉዓ የሚባል ሰው ከባልደረቦቹ ጋር ስለ ግድያው ካጠናና ከተመካከረ በኋላ አንድ ቀን ዑመር የፈጅርን ሰላት በማሰገድ ላይ ሣሉ  በድብቅ በመግባት በተመረዘና ሁለት ጫፍ ባለው ቢላዋ ስድሰት ጊዜ ሆዳቸውን ወጋቸው፡፡ አንዱ ከእንብርታቸው በታች ነበር፡፡ ተወግተው በወደቁ ጊዜም ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ‹ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ ይኖራልን?› በማለት ጠየቁ፡፡ ‹አዎን አለ አንቱ የምእመናን መሪ ሆይ!› አሏቸው፡፡ ‹ቅደምና አሰግድ፡፡› አሉት፡፡ ተሸክመውም ከቤታቸው አስገቧቸው፡፡ እዚያ እያሉም ሰዎች ገብተው ጎበኟቸው፡፡ ጎብኚዎቹ ሙሃጅሮች እና አንሷሮች ነበሩ፡፡ ‹ይህ ሰው የናንተ ሰው ነውን?› አሏቸው፡፡ እነሱም ‹በአላህ እንጠበቃለን፡፡› አሉ፡፡

ማን እንደወጋቸው ሰዎችን ጠየቁ፡፡ የአል ሙጊራ አገልጋይ እንደሆነ ተነገራቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ‹ሞቴን አንዲት ሱጅድ እንኳን ለአላህ ባላደረገ ሰው እጅ ላደረገው አላህ ምስጋና ይገባው፡፡› አሉ፡፡ አስከትለውም ‹ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር ሆይ! ዓኢሻ ዘንድ ሂድና ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ጎን እቀበር ዘንድ አስፈቅድልኝ፡፡› አሉ፡፡

ከዚያም ማክሰኞ ምሽት ለእሮብ አጥቢያ ህይወታቸው አለፈች፡፡ ጊዜውም 23 አመተ ሂጅራ ለዚልሂጃ ወር ሦስት ቀን ሲቀረው ነበር። ሮብ ጧትም አስከሬናቸውን ይዘው ወጡና ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እና አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ጎን በዓኢሻ ቤት ውስጥ ተቀበሩ፡፡ የአስተዳደር ዘመናቸውም አሥር አመት ከአምስት ወር ከሀያ አንድ ቀን ነበር።

ምንም እንኳ ሴራው ግዙፍ እና ወንጀሉም ከባድ ቢሆንም በግዲያው ካበሩት ሰዎች መካከል የተገደሉት ሁለት ወይንም ሦስት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ በጥርጣሬ የታያዘ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ተተኪ ኸሊፋውም ቢሆኑ በጭፍን በሚያስተዳድሯቸው ሰዎች ላይ ሰይፋቸውን አልመዘዙም፡፡ በወቅቱም ለበርካታ በቀል፣ ደም መፋሰስ ሰብዓዊ ጥሰቶች ሊያደርሱ የሚችሉ ባህላዊ  አሰራሮችም አልተተገበሩም፡፡

በመጨረሻ ሞት አፋፍ ላይ ከተናገሯቸው ንግግሮች መካከል ‹ከኔ በኋላ የሚተካውን ኸሊፋ እምነትንና ሀገርን ባፀኑት አንሷሮች (የመዲና ሰዎች) አደራ እለዋለሁ፡፡ ለነሱ መልካም ነገር ይዋል አጥፊያቸውን ይለፍ፡፡ ከኔ በኋላ የሚተካውን ኸሊፋ በዐረቦች ጉዳይም አደራ ለዋለሁ እነርሱ የኢስላም መሠረት ናቸውና፡፡ ዘካንም ከሚለግሱት ሀብታቸው ወስዶ ለድሆቻቸው ይሥጥ፡፡ ከኔ በኋላ የሚተካውን ኸሊፋ አላህ መልእክተኛ ለሌሎች ሙስሊም ላለሆኑ ሰዎች የገቡትን ቃልኪዳን እንዲያፀና አደራ እላለለሁ፡፡›

ከመወጋታቸው በፊት የህዝቦቻቸውን ሁኔታ ለማየት ወደ ተለያዩ ሙስሊም ሀገሮች ለመሄድም ሀሣብ ነበራቸው፡፡ ‹አላህ ካቆየኝ ህዝቦቼን እጎበኛለሁ፡፡ እነሱ እኔን በቅርበት አግኝተው ያልነገሩኝ አስተዳዳሪዎቻቸውም ያልነገሩኝ እኔ እንጂ የማልፈፅምላቸው የሆኑ ጉዳዮች አሏቸው፡፡ ወደ ሻም/ሦሪያ እና አካባቢው/ ሀገር እሄድና ለሁለት ወር እዚያ እቆያለሁ፤ ወደ አልጀዚራ/መካከለኛው ዐረብ ምድር/ በመሄድም ሁለት ወር፤ ወደ ግብፅ በመሄድም እንዲሁ ሁለት ወር፤ ወደ ባህሬን አካባቢ በመሄድ ሁለት ወር፤ ወደ ኩፋ በመሄድም ሁለት ወር፤ ከዚም ወደ በስራ በመሄድም ሁለት ወር እቆያለሁ፡፡ በዚህ ላይ ሁሉ አላህ ትልቁ ጥንካሬዬ ነው፡፡› (10) ብለው ነበር፡፡

ህይወታቸው ረዝሞ ቢሆን ኖሮ ከዑመር ታሪክ ብዙ እንማር ብዙም እንደነቅ ነበር፡፡ ነገርግን ለሁሉም እድሜ ገደብ አለው፤ ይህ ቀድሞውኑ ተፅፏል፡፡

የፅሁፉ ምንጮች

[1].   ከንዝ አልዑማል ቅ.5 ገፅ 809

[2].  ዐስር አልኹለፋኡ ራሺዲን ሊዶ/ር አክረም ዲያእ አልዑመሪ ቅ. 1 ገፅ 162

[3].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2

[4].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 267

[5].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 601

[6]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 43

[7].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 192

[8].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 512

[9]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 560

[10].አል ከማል ፊ ታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 471

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here