መጠነኛ ቅኝት ስለ ኹለፋኡ ራሽዲን ዘመን (ክፍል 7)

0
2919

ባለፉት ቀደምት ተከታታይ ክፍሎች የሁለቱን ኸሊፋዎች ማለትም የአቡበክርን እና የዑመርን ታሪክ ለማየት ሞክረናል፡፡ ዛሬ ደግሞ በአላህ ፈቃድ የሶስተኛውን ኸሊፋ የዑስማንን ታሪክ በመጠኑ እንዳስሣለን፡፡

የአላህ መልእክተኛን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሁለት ልጆች በማግባታቸው ዙኑረይን (የሁለት ብርሃን ባለቤት) በመባል የሚታወቁት ታላቁ ሰሃባ

ዑስማን ኢብኑ ዓፋን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ህልፈት በኋላ በኸሊፋነት የተመረጡት እጅግ በሣል እና ዘመናዊ በሆነ አካሄድ ነበር፡፡ በርግጥም በዚያን ዘመን የዚህ ዓይነቱን ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ የማይታሰብ ነበር፡፡

አንዳንድ ሰሃቦች ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከመሞታቸው በፊት እነሱ የሚስማሙበትን ሰው በኸሊፋነት ይተኩለቸው ዘንድ ሀሣብ አቅርበው ነበር፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ግን እንዲህ በማለት መለሱላቸው ‹በህይወት እያለሁም ሆነ ሞቼ ይህን ነገር መሸከም አልፈልግም፡፡ አደራችሁን እነዚያን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ‹የጀነት ሰዎች ናቸው› ብለው በመሰከሩላቸው ሰዎች አደራችሁን፡፡ ሰዒድ ኢብኑ ዘይድ ከነሱ መካከል ቢሆንም እሱን ግን አላስገባም (የቅርብ ዘመዳቸው ስለሆነ ነው)፡፡ ነገርግን ስድስቶቹ ማለትም የዐብዱመናፍ ልጆች የሆኑት ዐሊ እና ዑስማን፣ የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አጎቶች የሆኑት ዐብዱረህማን እና ሰዕድ፣ የአላህ መልእክተኛ ሀዋሪያና የአክስታቸው ልጅ የሆነው ዙበይር ኢብኑ አል ዐዋም እና ኸይረኛው ጦልሃ /ጦልሃቱ አልኸይር/ ኢብኑ ዑበይዱሏህ ከመካከላቸው አንድ ሰው ይምረጡ፡፡ እነሱም የመረጡትንም ሰው በመልካም ነገር ሁሉ አግዙት፤ እርዱት፡፡ ከናንተ መካከል አንዳችሁን አምኖ አደራ የሠጣችሁ እንደሆነ ያ የታመነ ሰው የታመነበትን ነገር በአግባቡ ይመልስ፡፡› (1)

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ጧት ላይ ዐሊን፣ ዑስማንን፣ ሰዕድን፣ ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍን እና ዙበይር ኢብኑ አልዐዋምን ወደራሣቸው በመጥራት ‹እኔ ብዙ ካሠላሰልኩ በኋላ የህዝቡ አለቆች እና መሪ መሆን የምትችሉት እናንተ እንደሆናችሁ ተሠማኝ፡፡ ይህ ጉዳይ በርግጥም ከናንተ ውስጥ እንጂ መሆን የለበትም፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከናንተ ወደው ነበር የሞቱት፡፡ እኔ ሰዎች አይከተሏችሁም ብዬ አልሠጋም፡፡ ነገርግን በመካከላችሁ ልዩነት ተፈጥሮ ሰዎች በናንተ ምክኒያት እንዳይለያዩ እፈራለሁ፡፡ በሉ ተነሱ! ዓኢሻን አስፈቅዳችሁ ወደ ክፍሏ ግቡና ተመካክራችሁ ከመካከላችሁ አንድ ሰው ምረጡ፡፡› አሏቸው፡፡

አክለውም ‹የሞትኩ እንደሆነ ለሦስት ቀን ተመካከሩ፡፡ ሱሀይብ በሰላት ሰዎችን ያሰግድ፡፡ አሚር ሳይኖራችሁም አራተኛ ቀን አይምጣባችሁ፡፡› አሏቸው፡፡

ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር ምንም እንኳ ለአሚርነት የመመረጡ ጉዳይ እሱን የማይመለከተው ቢሆንም አማካሪና ሀሣብ ሰጭ ሆኖ እነሱ ዘንድ ይገባ ነበር፡፡ ዐብደላህ ከታላላቅ ሰሃቦች መካከል ስለመሆኑ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጭምር መስክረውለታል፡፡ በወቅቱ ጦልሃ በአካባቢው ስላልነበር ‹ጦልሃም በዚህ ጉዳይ ላይ ከናንተ ጋር ይስራ፡፡ በጉዳያችሁ ላይ እንዲገኝም አድርጉ፡፡ እሱ ሣይመጣ ሦስት ቀን ያለፈ እንደሆነ ግን በጉዳያችሁን ቀጥሉ፡፡› በማለት ካሳሰቧቸው በኋላ ‹እስከዚያው ግን ጦልሃን ማን ይተካልኛል?› በማለት ጠየቁ፡፡ ሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስም ‹እኔ ለዚህ አለሁ፡፡ ኢንሻአላህ ይስማማል ብዬ አስባለሁ፡፡› አለ፡፡ ዑመርም ‹ በሀሣቡ ከናንተ አይለያይም ብዬ እገምታለሁ ኢንሻአላህ፡፡› አሉ፡፡ (2)

ከመዲና ሰዎች አንዱ ለሆነው ለአቢ ጦልሃ አል አንሷሪም  ‹ የጦልሃ አባት ሆይ! የተከበረውና የተላቀው አላህ በናንተ አማካይነት ዲኑን አጠንክሯል፡፡ ከአንሷር የሆኑ ሃምሣ ሰዎችን ምረጥና እነኚህ ሰዎች ከመካከላቸው አንድ ሰው እስኪመርጡ ድረስ ተከታተል፡፡› አሉት፡፡

ለአል ሚቅዳድ ኢብኑ አል አስወድም ‹በመቃብሬ ውስጥ እንዳኖራችሁኝ እነዚያ ሰዎች በሆነ ቤት ተሰብስበው ከመካከላቸው አንድ ሰው እንዲመርጡ ሰብስባቸው፡፡ ለሱሀይብ ደግሞ ለሦስት ቀን ሰዎችን ሰላትን ያሰግድ፡፡› አሉት፡፡

ለኸሊፋነት የታጩት ስድስቱ ሰሃቦች ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እስኪሞቱና እስኪቀበሩ ድረስ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር አልተሰበሰቡም ነበር፡፡  ሞተው ከተቀበሩ በኋላ ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ ተነሣና ‹በላጫችሁ ይህንን ቦታ ይረከብ ዘንድ ማናችሁ ናችሁ እራሣችሁን ከዚህ ጉዳይ ነፃ የምታደርጉት?› አላቸው፡፡ አንድም የመለሠለት ሰው አልነበረም፡፡

ዐብዱረህማን በበኩሉ ‹እኔ ከእጩነት እራሴን አግልያለሁ፡፡› አለ፡፡

ዑስማን ደግሞ ‹ለመቀበል ዝግጁ ከሆኑት የመጀመሪያው እኔ ነኝ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ‹በምድር ላይ ታማኝ ሰው በሰማይም ታማኝ ነው፡፡› ሲሉ ሠምቻቸዋለሁ፡፡› አለ፡፡ ሌሎች በቦታው የነበሩትም ‹ወደናል› አሉ፡፡ ዐሊ ግን ዝም አለ፡፡ ዐብዱረህማን ‹የሀሠን አባት ሆይ! ምን ትላለህ?› አለው፡፡ እሱም ‹እውነትን ልታስበልጥና ልትመርጥ፣ የስሜትህን ላትከተል፣ ለዘመዶችህ ላታደላ፣ ከህዝብ ለታስበልጥ ቃልህን ስጠኝ፡፡› አለው፡፡

ዐብዱረህማንም ‹ነገሮችን ከመለወጥ አንፃር አብራችሁኝ ልትሆኑ፣ በአላህ ኪዳንም እኔ የመረጥኩላችሁን ልትወዱና ልትቀበሉ ቃላችሁን ስጡኝ፡፡ እኔም ለዝምድናው ብዬ ወደ ዘመዴ ላላደላ፣ የሙስሊሞችን ጥቅም ላላስበልጥ ቃሌን እሠጣለሁ፡፡› በማለት ቃልኪዳን ተቀበላቸውና ተመሣሣዩን ሠጣቸው ፡፡፡

ከዚያም ዐብዱረህማን ለዐሊ ‹ለአላህ መልእክተኛ የተሻለ የዝምድና ቅርበት ስላለህ፣ ወደ እምነትም ለመግባት ቀዳሚ በመሆንህ፣ ለዲኑም ካበረከትከው አስተዋፅኦ አንፃር እዚህ ከተገኘው ሰው በበለጠ ጉዳዩ (ኸሊፋነቱ) የሚገባው ለኔ ነው እያልክ ነው፡፡ በርግጥ ብዙም አልተሣሣትክም፡፡ ነገርግን አንተ ባትኖርና ይህ ጉዳይ ለሌላ ሰው ይሠጥ ቢባል ከነኚህ ሰዎች መካከል የሚገባው ለማነው ትላለህ?› አለው፡፡ እሱም ‹ለዑስማን ነው› አለ፡፡

ዑስማንንም በመነጠል ‹የበኒ ዐብዱመናፍ ትልቅ ሽማግሌ ከመሆኔ ባሻገር የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አማች እና የአጎቱ ልጅ ነኝ፤ ወደ እስልምናም ለመግባት ከቀደሙ ሰዎች መካከል ነኝና ይህ ነገር ለኔ ይገባኛል ትላለህ፡፡ በርግጥ አንተም አልተሣሣትክም፡፡ ነገርግን አንተ በዚህ ቦታ ላይ ባትገኝ ከነኚህ ሰዎች መካከል ለዚህ ቦታ ተገቢው ሰው ማነው ትላለህ?› በማለት ጠየቀው፡፡ ዑስማንም ‹ዐሊ ነው› በማለት መለሠለት፡፡ ዙበይርንም ለብቻው እንዲሁ ጠየቀው፡፡ እሱም ‹ዑስማን› ብሎ መለሠለት፡፡ ሰዕድንም በተመሣሣይ መልኩ ጠየቀው እሱም ‹ዑስማን› አለ፡፡(3)

ዐብዱረህማን ለሊቱን በሙሉ በአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰሃቦች፣ በመዲና በሚገኙ የሰራዊቱ መሪዎችና ትላልቅ ሰዎች ላይ ላይ በመዞር ሲያገኛቸው አደረ፡፡ ሁሉም ለማለት በሚያስችል መልኩ የጠቆሙት ዑስማንን ነበር፡፡ እንደ ነገ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ምሽት ላይ ዐብዱረህማን ወደ አልሚስወር ኢብኑ መክረማህ ቤት በለሊት መጣና ከእንቅልፍ ቀሠቀሰው፡፡ እንዲህም አለው ‹እኔ በዚህች ለሊት ዐይኔን ትንሽ እንኳ አልጨፈንኩም፡፡ አንተ ግን ትተኛለህ፡፡ በል ሂድና ዙበይርን እና ሰዕድን ጥራልኝ አለው፡፡› (4)

ዐሊንም ጠርቶ ‹ወላሂ የአላህን ኪታብ፣ የመልእክተኛው ፈለግና አስተምሮ እንዲሁም ከርሣቸው በኋላ የተተኩትን ኸሊፋዎች ታሪክ ልታስተምር የአላህ አደራና ቃልኪዳን አለብህ፡፡› አለው፡፡ ዐሊም ‹እውቀቴና ችሎታዬ በሚፈቅደው ያህል እሰራለሁ እተገብራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡› አለው፡፡ ዑስማንንም ጠራና ተመሣሣዩን አለው፡፡ ዑስማንም ‹እሺ› አለ፡፡ ዐብዱረህማንም የኸሊፋነት ቃልኪዳኑን ሰጠው፡፡

በዚያው ለዑስማን የኺለፋነት ቃልኪዳን በተፈፀመበት እለት ጦልሃ ደረሠ፡፡ ‹ዑስማን ቃልኪዳን ተገባለት፡፡› ተብሎም ተነገረው። እሱም ‹ሁሉም ቁረይሾች ወደውታልን?› በማለት ጠየቀ፡፡ ‹አዎን› በማለት መለሱለት፡፡ ጦልሃም ቃልኪዳን ሊገባለት ዑስማን ዘንድ መጣ፡፡ ዑስማንም ‹አንተ እራስህን የቻልክ ነህና አልስማማም ካልክ አለመቀበል ትችላለህ፡፡ (ለኺለፋነት እጩ ነበርክ ማለታቸው ነው፡፡) አለው፡፡› ጦልሃም ‹ትመልሣለህን?› አለው፡፡ ‹አዎን› አለው ዑስማን፡፡ ጦልሃ ‹ሁሉም ሰው ቃልኪዳን ገብቶልሃልን?› በማለት ጠየቀው፡፡ እሱም ‹አዎን› አለው፡፡ ጦልሃም ‹እንግዲያውስ ሰዎች የወደዱትን ነገር ወድጄያለሁ ብቻዬን አልሆንም፡፡› በማለት ቃልኪዳኑን ሰጠው፡፡(5)

ከቃልኪዳን ፍፃሜው በኋላ ዑስማን ከሁሉም ሰው በላይ እጅግ የተጨነቁ ሆነው ወጡ፡፡ ወደ አላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሚንበር ላይ በመውጣትም ንግግር ለማድረግ ብለው አላህን አመሠገኑ፤ አወደሱትም፡፡ በነቢዩ ላይ ሰላትና ሰላም ካወረዱ በኋላም እንዲህም በማለት ተናገሩ ‹እናንተ በጊዜያዊ  በትንሽ ሀገር እና እድሜ ውስጥ ነው ያላችሁት፡፡ የምትችሉትን ያህል መልካም ነገር በመስራት የሞት ቀጠሮአችሁን ተሸቀዳደሙ፡፡ በነጋና በመሸ ቁጥር መሞቻችሁ እየቀረበ ነው፡፡ አዋጅ ስሙ! ይህች የቅርቢቱ ዓለም በማታለል የተከበበች ናት፡፡ የቅርቢቱ ዓለም አታታላችሁ፡፡ አታላዩም ከአላህ አያታላችሁ፡፡ (6)

ከንግግሩ በኋላ ህዝቡ እንዳለ ቃልኪዳን ሊሠጡት ወደ ዑስማን ጎረፈ፡፡ በዚህም አጠቃላይ እና የየብቻ የሆነ የቃልኪዳን ሥነሥርዓት ተገባላቸው፡፡፡

ከዚያም ወደየግዛቶች አስተዳዳሪዎች በመላክ እንዲህ አሏቸው፡፡ ‹አላህ መሪዎችን አገልጋዮች እንዲሆኑ አዟቸዋል፡፡ በዝባዥ እንዲሆኑ አልሾማቸውም፡፡ የዚህ ኡማህ ቀደምቶቹ (ሰሃቦች) አገልጋዮች ሆነው ነው የተፈጠሩት፡፡ ጨቋኝ ሆነው አልተፈጠሩም።  አሚሮቻችሁም ጨቋኞች እንጂ አገልጋዮች እንዳይሆኑ ያስፈራል፡፡ እንደዚያ ከሆኑ እፍረት፣ ታማኝነት እና አደራ ይጠፋል፡፡ ከታሪክ ሁሉ እጅግ ፍትሃዊው የሙስሊሞችን ጉዳይ በፅኑ መመልከታችሁ ነው፡፡ የነሱን ሀቅ ትሰጧችኋላችሁ ያለባቸውን ትቀበሏችኋለችሁ፡፡ የቃልኪዳን ስምምነት ካላችሁ ጋርም ኪዳናችሁን ትጠብቃላችሁ፡፡ የነሱን ሀቅ ትሰጧችኋላችሁ ያለባቸውን ትቀበሏችኋለችሁ፡፡ የቀረው ጠላታችሁ ሲሆን እሱንም በመልካም አያያዝ ያዙት፡፡(7)

ወደ ሰራዊቶች መሪዎችም እንዲህ በማለት ፃፉላቸው፡፡ ‹ እናንተ የሙስሊሞች ጠባቂዎችና ጋሻዎቻቸው ናችሁ፡፡ ዑመር ከኛ ሁሉ ድብቅ ያልሆነንና ሁላችንም የምናውቀውን ነገር አስቀምጦላችኋል፡፡ አንዳችሁም ተለወጣችሁ አሊያም ተቀየራችሁ የሚል ወሬ እንዳይደርሰኝ፡፡ አላህ ለናንተ የሰጠውን ይወስድባችሁና በናንተ ሌላውን ይተካል፡፡ ምን ልትሆኑ እንደምትችሉ አስቡ፡፡ እኔ አላህ ሀላፊነቱን በሠጠኝ ነገር ላይ ራሴን እገመግማለሁ ፤ግዴታዬንም እወጣለሁ፡፡› (8)

በግብር ሰብሣቢነት ሥራ ላይ ወደተሰማሩትም ሰዎች እንዲህ በማለት ፃፉላቸው ‹አላህ ፍጡራንን የፈጠረው በሀቅ ነው፤ እሱም ሀቅን እንጂ አይቀበልም፡፡ እውነትን ተቀበሉ፤ በሱም ሀቅን ስጡ፡፡ አደራ በቃልኪዳናችሁ ፅኑ፡፡ መጀመሪያ ከሚያፈርሷትም አትሁኑ፡፡ ከኋላችሁ የሚመጡት ቢያጠፋ ጥፋታቸውን ትጋራላችሁ፡፡ ቃላችሁን ጠብቁ አደራ አደራ፡፡ የቲምን /ወላጅ አጥ የሆኑትን/ አትበድሉ፡፡ የቃልኪዳን ስምምነት የተገባለትንም አትበድሉ፡፡ አላህ እነሱን የበደሉትን መክሰሱ አይቀርም፡፡› (9)

ለሌሎች የመንግስት ሠራተኞች ደግሞ አጠቃላይ የሆነ መልእክት አስተላለፉ ‹እናንተ አሁን የደረሣችሁበት ደረጃ ልትደርሱ የቻላችሁት የአላህን ዲን በመያዝና በመከተል ነው፡፡ ይህች ዓለም ከዋናው ጉዳያችሁ አታዘናጋችሁ፡፡ ….› (10)

ዑስማን ክፍያ ላይም መቶ መቶ ጭማሪ አደረጉ፡፡ የደሞዝ ክፍያን ለመጨመር የመጀመሪያው ኸሊፋ እርሣቸው ናቸው፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በረመዷን ውስጥ ምርኮ ገንዘብ የሚገባቸው ለሆኑ ለያንዳንዱ ሰው በየቀኑ አንድ አንድ ድርሃም ይሠጡ ነበር፡፡ ለነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ባለቤቶች ደግሞ ሁለት ሁለት ድርሃም መድበው ነበር፡፡ ‹በድርሃሙ ምትኩ ምግብ ብትሠጣቸውና አንድ ላይ ብትሰበስባቸውስ› ተባሉ፡፡ እርሣቸውም ‹ሰዎች በቤታቸው ነው የሚጠግቡት፡፡› በማለት ዑስማንም ዑመር የሰሩበትን አሠራር ቀጠሉበት፡፡ በረመዷን ደግሞ በመስጊድ ውስጥ ዒባዳ እያደረገ ለሚያድር፣ ለመንገደኛ ሰው እንዲሁም በረመዷን ውስጥ በሰዎች ለሚረዱ ወገኖች ቀለብ አደረጉ፡፡ (11)

ዑስማንም አቡበክር የጀመሩትንና ዑመርም የገፉበትን ሀገራትን የመክፈቱን ሥራ ቀጠሉበት፡፡ አልወሊድ ብኑ ዑቅባ አዘርቢጃን እና አርሚኒያን መልሦ ይከፍት ዘንድ ላኩት፡፡ ዐብዱላህ ኢብኑ ሰዕድ ኢብኑ አቢ ሰርህን ደግሞ አፍሪካን እንዲከፍት ላኩት፡፡ ሙዓዊያ በበኩሉ ደግሞ በሜዲትራኒያን አካባቢ የሚገኙ ደሴቶችን ይከፍት ዘንድ እንዲፈቅዱለት ኸሊፋውን ጠየቀ፡፡ ኸሊፋውም አንድንም ሰራዊት በግድ እንዳያስወጣ በማሣሰብ ፈቀዱለት፡፡ ሙዓዊያ የባህር ላይ ጉዞውን በመጀመር በ28 አ.ሂ የቆጵሮስን ደሴት ከፈተ፡፡ ከነዋሪዎቿም ብዙ ሰው ማርከው ነበር፡፡  አቡደርዳእ ይህንን ባየ ጊዜ አለቀሠ፡፡ ‹አላህ ኢስላምንና ተከታዮቹን ከፍ ባረገበትና ክህደትንና ተከታዮቹን ባዋረደበት በዚህ ታለቅ ቀን ታለቅሣለህ እንዴ ምነው!› አሉት፡፡ እሱም ‹ ሰዎች አላህን ምንኛ ተዳፋሪዎች ናቸው! ትእዛዙን ጣሱ፡፡ ለሰዎች ትላልቅና ጠንካራ መስለው የሚታዩና ሥልጣን በእጃቸው ያለ ሁሉ ዛሬ እንደምናየው ሆነዋል፡፡ ….›(12) ሙዓዊያ ቀጥሎም  ወደ ቁስጠንጢኒያ (ኮንስታንቲኒፖል) ዘመተ፡፡

በዑስማን የኸሊፋነት ዘመን የመጨረሻው የፋርስ ንጉስ የዝደጅርድ ተገደለ፡፡ የዝደጅርድ በስደት ከሀገር ወጥቶ እያለ ነበር የተገደለው፡፡ በሱ መገደልም የክህደት፣ የግፍ፣ የበደልና ጨለማ ሥርዓት ተገፈፈ፡፡ ከመሞቱ በፊት ሙስሊሞችን ሽሽት ከአንደኛው ከተማ ወደ ሌላኛው ከተማ በድብቅ ሲዘዋወር ኖሯል፡፡ የቱርክንና የቻይና ነገስታት እርዳታ ቢጠይቅም ሊተባበበሩት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ወደ ሞሮ በመሄድም የገንዘብ እርዳታ ጠይቆ ስለከለከሉት እዚያም ለመጋደል ወስኖ የተወሰኑ ሰዎችን ገድሎ ቀስቱን፣ ሰይፉንና ዘውዱን ብቻ ይዞ በእግር ሸሸ፡፡ በጉዞውም ላይ በወንዝ ዳርቻ የሠፈረ አንድ ቀራጭ ዘንድ መጣ፡፡ የዝደጅርድ ተዘናግቶ ባለበት ሁኔታም ቀራጩ ሰውዬ ገደለውና የያዘውን እቃ ወስዶበት በድኑንም ወደ ወንዙ ወረወረ፡፡ (13)

የዝደጅርድ ከተገደለ በኋላ ሙስሊሞች አብርሽሀርን፣ ጡስን፣ ቢዮርድን፣ ነሣን፣ ሰረክስን፣ ሞሮንና ሌሎች በፋርስ አገዛዝ ሥር የነበሩ ከተሞችን ከፈቱ፡፡

አል አህነፍ ኢብኑ ቀይስ ሞሮ ሩዝን ያለጦርነት በሠላም ከፈተ፡፡ መሪዎቿ ለነበሩትም እንዲህ በማለት ፃፈ ‹ቢስሚላህ ረህማኒረሂም የሠራዊት መሪ ከሆነው ሰኽር ኢብኑ ቀይስ ለሞሮ ሩዝ መሪ ባዛን እና ከርሱ ጋር ላበሩት ወገኖች በሙሉ፡፡ ሰላም ትክክለኛውን መንገድ በተከተለው፣ ባመነውና አላህን በፈራው ላይ ሁሉ ይሁን፡፡ የወንድምህ ልጅ ማሂክ ወደኔ መጥቶ ባደረገው ጥረት ዙሪያ ሀሣብ ሰጥቶሃል፡፡ ያንተም ሀሣብ ወደኔ የደረሠ ሲሆን እኔም ከኔ ጋር ላሉት ሙስሊሞች አቅርቤ ተወያይተናል፡፡ ባንተ ጉዳይ እኔም ሆንኩ እነሱ አንድ ነን፡፡ ያልከውን ተቀብለናል፡፡ ከገቢህ፣ ከገበሬዎችህና መሬትህ ስልሣ ሺህ ድርሃም ከኔ በኋላ ለሚተካው የሙስሊሞች መሪ እንድትሠጥ ተስማምቻለሁ፡፡ ይህም ግፈኛው አያትህ ኪስራ ቆርሦ ያስቀረውን መሬት አያካትትም።  መሬት ለአላህ ናት፡፡ ከባሮቹም የሻውን ያወርሣል፡፡ ሙስሊሞች የፈለጉ እንደሆነ ሙስሊሞችን ልትረዳና ካንተ ጋር ካሉት ጋር ሆነህ ጠላቶቻቸውን ልትዋጋ ይገባል፡፡ በዚህ ከተባበርክ ካንተ መንገድ የሆኑ ሰዎች አንተን ሊወጉ ከተነሱብህ ሙስሊሞች ያግዙሃል፡፡ ከኔ ዘንድም መጠጊያ ይኖርሃል፡፡ ይህ ከኔ በኋላም ቢሆን ተፅፎ የሚቀመጥ ነው፡፡ አንተም ሆንክ ቤተዘመድህ የሆኑ የቅርብ ሰዎች ግብር መክፈል አይጠበቅባቸውም፡፡ አንተ ከሠለምክ እና መልእክተኛውን የተከተልክ እንደሆነ ከክፍያ፣ ከማረፊያም ሆነ ከሲሣይ ለሙስሊሞች የሚሠጣቸው ሁሉ ይሠጥሃል፡፡ አንተም ወንድማቸው ነህ፡፡ በዚህም የኔ፣ የአባቴ፣ የሙስሊሞችና የአባቶቻቸው ሁሉ ቃልኪዳን አለልህ፡፡› አሉት፡፡(14)

በዑስማን ዘመን ሀገራትን የመክፈቱ ሥራ በምስራቅ አቅጣጫ እስከ ታልቃን፣ ፋርያ፣ ጆዝጃን፣ ተኻርስታን እና በለኽ ድረስ የዘለቀ ሲሆን በምዕራቡ በኩል ደግሞ በሱ ዘመን በመጨረሻ የተከፈተችው ከተማ ዐሙሪያ ነበረች፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ሙስሊሞች መናፍቃን በመሪያቸው አይሁዳዊው ኢብኑ ሰበእ አማካይነት በቀሰቀሱት ፊትና/ውዥንብር/ ተጠመዱ፡፡ ይህ ፈተናም ተስፋፍቶ በመጨረሻም በ35ኛው አመተ ሂጅራ በዚልሂጃ 18ኛው ቀን ኸሊፋው ዑስማን ሊገደሉ ችለዋል፡፡

ሙስሊሞች በዑስማን ዘመን ባገኟቸው ሰፋፊ ድሎች የተነሣ  በርካታ መልካም ነገሮችን አግኝተዋል፡፡ ሀብት ከየአቅጣጫው ጎረፈላቸው፡፡ ለዚሁ ተብሎ ትላልቅ መጋዘኖችም ተሰሩ፡፡ ዑስማን ለአንድ ሰው መቶ ሺህ በድረህ ያዙ የነበረ ሲሆን እያንዳንዱ በድረህም አራት ሺህ ወቄት ይይዝ ነበር፡፡ ሰዎች በሱ ዘመን የኖሩትን ዓይነት የተድላ ኑሮ ኖረው አያውቁም ነበር፡፡

የዑስማን የኸሊፋነት ዘመን አሥራ አንድ አመት ከአሥራ አንድ ወርና የተወሰኑ ቀናትን ይጨምር ነበር፡፡ ዕድሜያቸውም ሰማኒያ አልፎ ነበር፡፡ ዕድሜ ካለን በሌላ ከፍል እንገናኛለን ኢንሻ አላህ፡፡

የፅሁፉ ምንጮች

[1].   ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 580

[2].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 581

[3].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 582

[4].  ታሪኽ አል መዲና ቅ. 3 ገፅ 928

[5].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 583

[6]. አል ሙንተዘም ቅ. 2 ገፅ 52

[7].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 580 ጀምሮ

[8].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 591

[9]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 581

[10].ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 591

[11]. አል ኢክቲፋእ ቢማ ተደመነሁ ሚን መጋዚ ረሱሊላህ ወሰላሰቱል ኹለፋእ ቅ. 4 ገፅ 371

[12].ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 602

[13].አል ኢክቲፋእ ቢማ ተደመነሁ ሚን መጋዚ ረሱሊላህ ወሰላሰቱል ኹለፋእ ቅ. 4 ገፅ 376

[14].አል ኢክቲፋእ ቢማ ተደመነሁ ሚን መጋዚ ረሱሊላህ ወሰላሰቱል ኹለፋእ ቅ. 4 ገፅ 383

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here