መጠነኛ ቅኝት ስለ ኹለፋኡ ራሽዲን ዘመን (ክፍል 5)

0
2970

በባለፈው መጣጥፋችን በአስተዳደርና ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና  በኢስላማዊው መንግሰት ውስጥ ያስገቡትን አዳዲስ የአሠራር ለውጦች ተመልክተን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ የአላህ ፍቃዱ ከሆነ ይህንኑ ጉዳይ እናጠናቅቃለን፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በማስከተል

የሠሩት ሥራ በአስቸኳይ ጊዜዎች የሚተገበር አጠቃላይ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር አዋጅ ማውጣት ነበር፡፡ የፋርሱ ንጉስ የዝደጅርድ ተደጋጋሚ ሽንፈት ባጋጠመው ጊዜ እንደገና ለመጠናከር ከፋርስ/ኢራንና አካባቢው/ ያለውን ሀይል ሁሉ በማሰባሰብ ላይ መሆኑን ተደረሰበት፡፡ ዑመርም በተመሣሣይ መልኩ ምላሽ መስጠት ነበረባቸውና ወዲያውኑ በዐረቢያ ምድር ለሚገኙ ሀገረ ገዥዎችና የጎሳ አለቆች በሙሉ እንዲህ በማለት ፃፉ ‹መሣሪያ፣ ፈረስ፣ ቀስት፣ አሊያም ጥሩ መላና ሀሣብ ያለውን ሰው ሁሉ እጅግ አስቸኳይ በሆነ ሁኔታ ወደኔ ላኩ፡፡›

በአንድ የተወሰነ ሀገር ውስጥ አሣሣቢና አስቸኳይ ነገር ሲያጋጥም የሀገሪቱ አመራሮች ችግሩን ለመቅረፍ የመመካከርን ፋይዳ በመዘንጋት ለየት ያሉ የአስቸኳይ ጊዜ ህጎችንና የተለመዱ አሠራሮችን ሲከተሉ እናያለን፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ግን የጦርነት ጉዳዮች እጅግ ወሣኝ የሆኑ አቋሞች የሚያዙበት አሣሣቢና አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸውና ምክክር የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አካሄድ የተማሩትም ይህንኑ ነበር፡፡ ስለሆነም ሰዎች ሁሉ እንዲሰባሰቡላቸው በማሰብ ‹አሰላት ጃሚዓህ!› በማለት ተጣሩ፡፡ የዚህ አይነቱ ጥሪ አጣዳፊ የሆነ ነገር ሲያጋጥም የሚደረግ ነው፡፡ ሰዎች ሲሰበሰቡላቸውም እንዲህ አሏቸው ‹የተከበረውና የላቀው የሆነ ጌታ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በኢስላም ላይ ህዝቦቹን አሰባስቧል፡፡ በቀልቦች መካከልም መተሣሰርን ፈጥሯል፡፡ ወንድማማቾችም አድርጓቸዋል፡፡ ሙስሊሞች በመካከላቸው እንደ አንድ ሰውነት ናቸው፡፡ አንዱን ሰው ችግር ያገኘው እንደሆነ ሌላኛውም የችግሩን ህመም ይጋራዋል፡፡ እንዲሁ በሙስሊሞች መካከል መመካከር ግዴታ ነው፡፡ ከመካከላቸው የተሻሉ የሀሣብ ባለቤቶች ይኖራሉና፡፡ ሰዎች ጉዳያቸውን የያዘውን መንግስት ይከተላሉ፡፡ አመራሮችና ብልሃተኞች የተስማሙበትንና የተቀበሉትንም ነገር ይቀበላሉ፡፡ የመንግስት አመራሮችም የተሻሉ የሀሣብ ባለቤቶች የሆኑ ሰዎች ያቀረቡትን ምክር ይቀበላሉ፡፡ በጦርነት ስልትም ሆነ ባዩባቸው ብልጠት ከሌሎች ጎልተው የታዩትን ይከተላሉ፡፡ (3)

ዑመር ለምክክር ካቀረቧቸው አጀንዳዎች መካከል ‹ይህን ግዙፍ የሙስሊም ጦር እራሱ ይምራው ወይንስ ሌላ ሰው ይመድብበት?› የሚለው አንዱ ሲሆን የብዙሃኑም ሀሳብ ‹እሱ /ዑመር/ ራሱ ብልህ መሪ ይምረጥለት› የሚል ነበር፡፡ ይህንኑ ሀሣብ ከደገፉ ሰዎች መካከል ጦለሃ ኢብኑ ዐቢዱላህ እንዲህ ብሎ ነበር፡-

‹እናት አባቴ ፍዳ ይሁኑልህ፡፡ ሁሉን ነገር ለኔ ተውና ሥራህን ቀጥል፡፡ ሰራዊቱንም ላክ፡፡ ከዚህ በፊት በሰራዊትህ ላይ የአላህ ውሣኔ ላንተ ያጋደለ ሆኖ አይቻለሁ፤ ወደ ኋላ ላይም ይሀው ነው የሚሆነው፡፡ የሰራዊትህ መሸነፍ ያንተን መሸነፍ ያህል የሚጎዳ አይደለም፡፡ አንተ ምናልባት ወዲያውኑ ብትገደል አሊያም ብትሸነፍ ሙስሊሞች ‹አሏሁ አክበር› እንዳይሉ እና እስከመቼውም ‹ላኢላሀ ኢለላህ› በማለት እንዳይመሰክሩ እሠጋለሁ፡፡›

ከዚህ ውሳኔ በኋላ ዑመር እንዲህ አሉ ‹ እኔ የተሻሉ የሀሣብ ባለቤቶች (አማካሪዎች እና ጥልቅ ተንታኞች) ከሀሣቤ እንድመለስ እስካደረጉኝ ጊዜ ድረስ ከናንተ መካከል እንደ አንድ ሰው አድርጌ እራሴን እቆጥር ነበር፡፡›

በዚህ መልኩ ነበር ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እጅግ ወሣኝ በሆነው የሀገርና የመንግስት ጉዳይ ላይ ብዙ ካማከሩ በኋላ ከውሣኔ የደረሱት፡፡ ውሣኔያቸው ከአምባገነንነት የራቀ፣ የራስን ስሜት ብቻ ከመከተልም ፈፅሞ የፀዳ ነበር፡፡

ጦሩን በበላይነት ማን ይምራው የሚለው ሀሣብም መጨረሻ ላይ ጥቆማው ሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ ላይ ዐረፈ፡፡ ሀላፊነቱን አስረክበው ሲሸኙትም እንዲህ በማለት መከሩት ‹ ሰዕድ ሆይ! ሰዎች ‹የአላህ መልእክተኛ አጎት እና ወዳጅ ነው› የሚሉህ ነገር አደራህን እንዳያዘናጋህ፡፡ አላህ መጥፎን በመጥፎ አያብስም፣ ነገርግን መጥፎን በመልካም ነገር ያብሣል፡፡ በአላህ እና በሰው ልጅ መካከል ትስስር የሚኖረው እርሱን በመታዘዝ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሰው ልጅ ‹የተከበረ›ም ሆነ ‹ተራ› የሚባለው በአላህ ዘንድ እኩል ናቸው፡፡ አላህ ጌታቸው ሲሆን እነርሱ ደግሞ ባሮቹ ናቸው፡፡ በደህንነት ዋስትና ይበላለጣሉ፡፡ እርሱን እንደመታዘዝ ደረጃቸውም ከሱ ዘንድ ያለውን ችሮታ ይቋደሣሉ፡፡ ከተላኩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ እለተሞታቸው ድረስ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በኖሩበት ሁኔታ ላይ ፅና፡፡ ትክክለኛው መንገድ እሱ ነው፡፡ ይህ ላንተ የምሠጠው ምክሬ ነው፡፡ ይህን ትተህ ወደሌላ ነገር ብታዘነብል ሥራህ ይበላሻል፡፡ ከከሣሪዎችም ትሆናለህ፡፡› (4)

ከዚህም በተጨማሪ በጦርነት ጊዜ ሙስሊሞች ሊከተሉት የሚገባውን የጦርነት ሥርዓት አስታወሱት፡፡ ይህን የጦር ዲሲፕሊን የዛሬው ትውልድ ተከትሎት የሚሰራበት ቢሆን ኖሮ የሙስሊሙ ጦር ስብእና በጠላት ጭምር የሚመሠከርለት በሆነ ነበር፡፡ እንዲህ በማት ነበር ያዘዙት ‹ከናንተ መካከል አንዳችሁ ዐረብ ያልሆኑትን ሰዎች ስለ ሰላም በምልክት ወይንም በየትኛውም ቋንቋ አናግሮ ሰዎቹ ያልተረዷችሁ እንደሆነና እነርሱ ሰላም ፈላጊ ሆነው ካገኛችኋቸው የደህንነት መንገድ ክፈቱላቸው፡፡ አታላግጡባቸው አደራ፡፡ ቃልኪዳናችሁን ሙሉ፡፡ ቃልኪዳን አለመሙላት እዳ አለው፡፡ ክህደት መፈፀም ደግሞ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ በክህደት ምክኒያት መዳከም ያገኛችኋል፡፡ ጠላቶቻችሁ ደግሞ ያይላሉ፡፡ አደራችሁን ሙስሊሙን አትጉዱ፡፡ ለመዳከሙም ምክኒያት አትሁኑ፡፡ (5)

ሰዕድ እና የተቀሩት በአመራር ላይ ያሉ ሌሎች ሰሃቦች ምክሩን ተቀብለው በአግባቡ ተገበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ ሙስሊሞች ነሃውንድን በከፈቱበት ቀን ድንገት ከተማይቱን ከበው ነዋሪዎቿን አስደንግጠው አልገቡም፡፡ ነገርግን በሮቿ ሲከፈቱ፣ ቅፍለቶቿ ሲወጡና ገበያው ሞቅ ብሎ ነዋሪዎቿ ሲበተኑ ሙስሊሞቹ ‹ምን እንድናደርግ ትሻላችሁ?› ብለው ላኩባቸው፡፡ እነሱም ‹ስለ ሰላም ሀሣብ አቀረባችሁልን እኛም ተቀብለናል፡፡ እንዳትነኩንም ግብር ልንከፍላችሁ ተስማምተናል፡፡› አሉ፡፡ ሙስሊሞቹ ለዚህ የሰላም ሀሳብ ያበቃቸው ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው ግራ በመጋባት ‹ምን ያደረግነው ነገር አለ?› በማለት ጠየቁ፡፡ ሰዎቹም መልእክት ደርሷቸው እንደነበር በመግለፅና የስምምነት ሀሳባቸው እውነት መሆኑን ማሳወቅ ነበረባቸውና ‹እኛ አልዋሸንም፡፡› አሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ሙስሊሞች እርስ በርሣቸው ተጠያየቁ፡፡ በኋላ ሙከነፍ የሚባልና መሰረቱ ከዚች ከተማ የሆነ አንድ ባሪያ በሙስሊሞች ሥም የስምምነት ውል የፃፈላቸው መሆኑን ተረዱ፡፡ በዚህን ጊዜ ‹እርሱ እኮ ባሪያ ነው!› አሏቸው፡፡ እነሱም ‹ከናንተ ውስጥ ማን ባሪያ እንደሆነና እንዳልሆነ እኛ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ስለ ሠላም ሀሣብ አመጣችሁልን እኛም እንዳለ ተቀብለናል፡፡ እኛ ምንም የቀየርነው ነገር የለም፡፡ እናንተ ከፈለጋችሁ ቃላችሁን ማፍረስ ትችላላችሁ፡፡› አሏቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ሙስሊሞች እነሱን ከመንካት ታቀቡ፡፡ ስለ ጉዳዩም ለዑመር ፃፉላቸው፡፡ እሳቸውም እንዲህ በማለት መለሱላቸው ‹ አላህ ቃልኪዳን መሙላትን ከባድ አድርጎታል፡፡ ጥርጣሬ ላይም ሆናችሁ ጭምር ቃልኪዳናችሁን እስካልጠበቃችሁ ድረስ ቃልኪዳናችሁን ሞላችሁ አይባልም፡፡ ስለሆነም ያሉትን ተቀበሏቸው፡፡ ቃልኪዳኑንም ሙሉላቸው፡፡› በዚህ ሁኔታ መስሊሞች ያላሰቡትን የስምምነት ቃልኪዳን ተቀብለው ወደመጡበት ተመለሱ፡፡› (6)

በተለምዶ ‹ህዝቦች በነገስታቶቻቸው ሃይማኖት ላይ ይኖራሉ፡፡› ይባላል፡፡ ሰዕድ የፋርስ ዋና ከተማን አል መዳኢንን በድል ገቡ፡፡ ውድ ማዕድናትን በሚሰበሰብበት ወቅት አንድ ወታደር እርሱ ዘንድ የነበረውን ለሰብሣቢው ሠጠ፡፡ ሰዎችም ‹ይህን የሚስተካከል አሊያም ከዚህ ተቀራራቢ የሆነ ፈፅሞ አይተን አናውቅም፡፡ ከላዩ ላይ አጉድለሃልን?› አሉት፡፡ ሰውዬውም ‹ወላሂ አላህን ፈርቼ ባልሆን ኖሮ ይዤ ባልመጣሁ ነበር፡፡› አላቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ሰውዬው ጥሩ ሰው እንደሆነ ገመቱ፡፡ ‹ማነህ?› በማለትም ስለማንነቱ ጠየቁት፡፡ ‹ወላሂ እንድታወድሱኝ ብዬ አልነግራችሁም፡፡ ለሌሎችም ብሆን ከፍ ከፍ እንዲያረጉኝ ብዬ ስለማንነቴ አልናገርም፡፡ ነገርግን አላህን አመሰግናለሁ፡፡ ምንዳዬንም ከሱ ብቻ እፈልጋለሁ፡፡› አለ፡፡ (7)

ዓላማቸውን የዚህች ዓለም ጥቅም አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አንዲትን ከተማ ድል አድርገው የተቆጣጠሩ እንደሆነ ቤተመንግስቱንና ውስጡ ያለውን ሀብት ንብረት ለመቀራመት ይሽቀዳደማሉ፡፡ ሰዕድ ኢብኑ አቢወቃስና ሰሃቦቹ ግዙፍ፣ በቅንጦት እና በከበሩ ማዕድናት የተሞሉትን የፋርስ ከተሞች ሲከፍቱ ግን ለዚህ ዓይነቱ ጉጉት ቦታ አልነበራቸውም፡፡ የዝደጅርድ እና ጀሌዎቹ ጥለውት የሸሹትን ቤተመንግስት ወደ መስጅድ በመቀየር በውስጡ ሚንበር አኖሩ፡፡ መስጊዱንም ለስግደትና ለሙስሊሞች ጉዳይ መሰባሰቢያ ቦታ አድርገው ይጠቀሙበትም ነበር፡፡ (8)

ከድሉ በኋላ ሰዕድ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሠጣቸውን ድል ለማብሠር ወደ ዑመር ፃፈ፡፡ የሀገሪቱንም ሆነ የነዋሪዎችን ሁኔታ ገለፁለት፡፡ ዑመርም መልዕክቱን ካነበቡ በኋላ ‹የተዋጉህ አሊያም ሸሽተው ወደ ጠላት ወገን በመሄዳቸው አሣደህ የያዝካቸው ሲቀሩ ገበሬዎችን በሙሉ ባሉበት እንዲረጉ አድርጋቸው፡፡ ከነሱ በፊት ለነበሩት ገበሬዎች ስታደርግ የነበረውን ነገር ሁሉ አድርግላቸው፡፡› በማለት መለሱለት፡፡ (9)

ከብዙ ታሪኮች እንደሰማነውና እንዳየነውም ብዙን ጊዜ ጦርነት ሲቀሰቀስ የውጤት ወላፈኑ ያለ አንዳች አዘኔታና ርህራሄ ትንሽ ትልቅ፣ ደሃ ሀብታም ሣይል ሀገሩን ሁሉ ያዳርሣል፡፡ በሙስሊሞች ሥርዓት ግን ከጦርነት በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ዝቅተኛ የሚባሉ የማህበረሰብ ክፍሎችና ገበሬዎች አይነኩም፡፡ ምክኒያቱም ጦርነትን ሁሌም ቢሆን የሚያቀጣጥሏት የሥልጣን፣ የጥቅም ባለቤቶችና ሀብታሞች ናቸው፡፡ በመሆኑም ከድል በኋላ በብዝበዛና በችግር ሥር ማቅቀው ህይወትን ያሣለፉ ድሆች የቅድሚያ ትኩረት ያገኛሉ፡፡ ይህንንም ከዑመር ደብዳቤ መልእክት መረዳት እንችላለን፡፡

የዑመር ደብዳቤ ከያዛቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል በዒራቅ ስላረፉት የበኒ ተግለብ ነሣራዎች/ ክርስቲያኖች/ የኑሮ ሁኔታ በመጠየቅ ስለነሱ በመልካም ነገር አደራ ካለ በኋላ ከነርሱ ውስጥ የሠለመ ሰው ሙስሊሞች የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅም ሁሉ እንደሚያገኝ፤ ከሙስሊሞች የሚጠበቅ ማንኛውም ግዴታ እንደሚጠበቅበትና አሻፈረኝ የሚል ካለም ግብር መክፈል እንደሚኖርበት የሚገልፅ መልእክት ይገኝበታል፡፡

ዒራቅን የመክፈቱ ዘመቻ ተጠናቆ የሙስሊም ወታደሮች በሀገሪቱ ከረጉ በኋላ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ሰሃቦች ከአየሩ ጋር መላመድ ባለመቻላቸው ምክኒያት ሰውነታቸው እየተዳከመ መሆኑን አወቁ፡፡ በመሆኑም ለጤናቸው ተስመሚ የሆነ ቦታ ይፈልግላቸው ዘንድ ሰው ላኩ፡፡ ወደ ሰዕድም አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ በማለት ላኩ ‹ ዐረቦች የሚመቻቸው ግመሎችና ፍየሎች የሚገኙበትና ተክል የሚበቅልበት አካባቢ ነው፡፡ ስለሆነም በደቡብ ባህር አቅጣጫ በኩል ሜዳ ፈልግና ለሙስሊሞች መስፈሪያ እንዲሆን አድርግ፡፡› ፍለጋውም ተጀመረ፡፡ በመጨረሻም በደቡብ ዒራቅ ግዛት የተሻለ ነው ባሉት ቦታዎች ላይ የኩፋንና የበስራን ከተሞች ቆረቆሩ፡፡

በነኚህ ሁለት ከተሞች መጀመሪያ ወታደሮችን በማስፈር ድንኳን ጥለው እንዲኖሩ ተደረገ፡፡ ቀጥሎም ቤተሰቦቻቸው ወደ ከተሞቹ እንዲመጡ ሆነ፡፡ መሰረት ያለው ቤት ለመሥራትም አስፈቀዱ፡፡ ዑመር ግን ‹ለሚገጥማችሁ ጦርነት ቀልጠፍ የሚያረጓችሁ እና አመቺ የሚሆኑት ጎጆዎች/ወታደራዊ ድንኳኖች/ ናቸው፡፡ እኔ ሀሣባችሁን መቃወም ፈልጌ አይደለም፡፡› አላቸው፡፡ ሆኖም ግን ከትንሽ ጊዜ ቆይታ በኋላ ላይ በበስራና በኩፋ ከተሞች የእሣት ቃጠሎ ተከሠተ፡፡ በቃጠሎው እጅጉን የተጎዳችው ኩፋ ነበረች፡፡ ለቃጠሎው መክፋት የቤቶቹ አሠራር ቀላል መሆን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ሰዕድ ሙስሊም ሰፋሪዎች ቤቶቹን ጠንከር ባለ ሁኔታ ይገነቡ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው የተወሰኑ ሰዎችን ወደ ዑመር ላከ፡፡ ስለ ቃጠሎውም ሁኔታ አስረዱት፡፡ ዑመርም ‹እንግዲያውስ ጥሩ፡፡› ካሉ በኋላ ‹ነገር ግን አንዳችሁ ከሦስት ቤት በላይ አይስራ፡፡ በቤት ግንባታዎችም ላይ አትፎካከሩ፡፡ በሱናው/የነቢዩ መንገድ/ ላይ ፅኑ፣ መንግስታችሁ ይፀናል፡፡› በማለት አሣሰቧቸው፡፡ ሰዎቹም ይህን ሀሣብ ይዘው ወደ ኩፋ ተመለሱ፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በተመሣሣይ መልኩ ወደ ዐተባህ እና የበስራ ሰዎችም ፃፉ፡፡ (10)

ከተሞቹን የማስፋፋቱ ሥራ ቀጠለ፡፡ ዋና ዋና መንገዶች ስፋታቸው አርባ ክንድ ያህል እንዲሆኑ በአስፈላጊነታቸው ከነሱ ቀጥለው የሚገኙት ሠላሣ፤ ቀጥለው ያሉት ሀያ፤ በጣም አነስ ያሉት ደግሞ ሰባት ክንድ ያህል ስፋት እንዲኖራቸውና ከዚህ በታችም እንዳይኖርና በሁለት መንገዶች መካከል መለያ ስላሣ ክንድ ያህል እንዲያደርጉ አዘዙ፡፡

በዚህ በተደራጀና ሥርዓት ባለው ሁኔታ ላይ ሌሎች ኢስላማዊ ከተሞችም መልክ መልካቸውን እንዲይዙ ተደረገ፡፡ በመሆኑም በመንገዶችም ላይ የመጨናነቅና የመጋፋት ችግር ሊቀረፍ ቻለ፡፡ ንፁህ አየር በመንሸራሸሩ ምክኒያትም ከመጨናነቅ መንስኤ የሚመጡ በሽታዎች ተወገዱ፡፡

በኩፋ የተገነባው የመጀመሪያው ነገር መስጅድ ነበር፡፡ አንድ ጠንከር ያለ ቀስት ወርዋሪ ሰው መስጊዱ ሊሰራ ከታሰበበት ቦታ መሃል ላይ ቆመና በቀኙ በኩል ቀስቱን ወረወረ፡፡ አንዱ ቡድን ቀስቱ ካረፈበት ከመጀመሪያው ቦታ ግንባታውን እንዲጀምር ታዘዘ፡፡ እንዲሁ ከፊት ለፊቱም ከኋላውም በኩል ወረወረ፡፡ ሌላኛው ቡድን በዚያ በኩል ግንባታ እንዲጀምር ታዘዘ፡፡ በአራቱም አቅጣጫዎች በኩል ሰፊ ቦዶ ቦታዎች ተትተው መስጅዱ መሃል ላይ እንዲያርፍ ተደረገ፡፡ ግቢው እንዲህ እንዲሠፋ የተደረገው ሰዎች በሚሰበሰቡበት ጊዜ እንዳይጠባቸው ተብሎ ነው፡፡ ከመካው መስጅደል ሀራም በስተቀር ሌሎች በጊዜው የነበሩ መስጅዶች በሙሉ በዚሁ መልኩ ነበር የተገነቡት፡፡ ካላቸው ከፍተኛ ክብር የተነሣ መስጅደል ሀራምን እንደማንኛውም መስጅድ አይመለከቱም ነበርና ነው፡፡

ወደ መስጅዱ አንድም ተንኮል ያሠበ ሰውም ሆነ አስቸጋሪ ነገር እንዳይገባ ለመከላከል በመስጅዱ ዙሪያ ቦይ ተቆፈረ፡፡ ለሰዕድ ደግሞ ጫፉ ላይ ቤት ሰሩለት፡፡ በመስጊዱና በቤቱ መካከል ያለው ርቀት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ነበር፡፡ የሙስሊሙ ንብረቶችም እዚያ እንዲቀመጡ ተደረጉ፡፡ በመስጅዱ ዙሪያ ባዶ ቦታዎች ላይ ገበያዎች ተመሠረቱ፡፡ ገበያው ወደተለያየ አቅጣጫ ለሚበተኑ መንገዶችም መነሻ ሆነ፡፡ በዚህ በመልኩ ከተማዋ በመስጅዱ ዙሪያ ክብ በሆነ መልኩ ተመሠረተች፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከዚህ ቀደም የማይታወቅ በዓይነቱ ለየት ያለ የአሠራር ሂደት አስተዋወቁ፡፡ አሠራሩ ሀላፊነት ላይ ያለ ሰው ከሥራው ዝንፍ ሣይል እንዲሠራ የሚያደርግ ነበር፡፡ ለሀገረ ገዥነት አሊያም አስተዳደር ጉዳይ አሚር አስቀመጡ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይሀው ሰው በመስጅድ የሙስሊሞች ኢማም እንዲሆን ሀላፊነት ተሰጠው፡፡ ተጠሪነቱ ለአሚሩ ያልሆነ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ በሙስሊሙ ግምጃ ቤት ላይ ሀላፊ አደረጉ፡፡ ይህ ሰው ተጠሪነቱ ለከተማው ከንቲባ ነው። በሰዎች መካከል የሚነሱ ውዝግቦችን ይፈቱ ዘንድም ቃዲዎችን መደቡ፡፡

ዑመር ዘወትር ወደ ገዥዎቻቸው እንዲህ በማለት ይፅፍ ነበር፡፡ ‹እኔ በሙሀመድ ህዝቦች በፀጉሮቻቸው አሊያም በሰውነቶቻቸው ላይ አይደለም የሾምኳችሁ፡፡ እኔ የሾምኳች ሰላትን እንድታቆሙላቸው፣ በመካከላቸው በፍትህ እንድትፈርዱና ፍትህን እንድታሰፍኑ ነው፡፡ እኔ እያንዳንዷን ነገሮቻቸውን እንድትቆጣጠሩና አምባገነን እንድትሆኑባቸው አላዘዝኳችሁም፡፡ ዐረቦችን ለማዋረድ ብላችሁ አትግረፏቸው፡፡ እሣት ላይ የመጣድ ያህልም አትፈታናኗቸው፤ የመከልከል ያህልም አትዘንጓቸው፡፡ ለቁርዓን ነፃ ጊዜ አድርጉለት…እኔ አብሬያችሁ ነኝ፡፡›

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና አንድ ሰራተኛ በሀላፊው ላይ አቤቱታ ያቀረበ እንደሆን ባለጉዳዩና ሀላፊው ባለበት በማገናኘት ጉዳዩን ያጣሩ፤ የሚያስቀጣ ሆኖ ከተገኘም ለአቤቱታ ሀላፊውን ይቀጡ ነበር፡፡

በአንድ ወቅት አቢ ሙሣ አንድ ከዐነዛ ጎሣ የሆነና ደባህ ኢብኑ መህሲን የተባለ ሰው ጋር ያጋጠማቸውን ታሪክ የያዘ ደብዳቤ ዘርዘር አድርገው ለዑመር ፃፉላቸው፡፡ ደብዳቤው፣ ልዑኩ እና የድሉ ብስራት ለዑመር በደረሠው ጊዜ የዐነዛው ሰውዬም መጣና ‹አሰላሙ ዐለይኩም› አለው፡፡ ዑመርም ‹አንተ ማነህ?› አሉት፡፡ ሰውዬውም ነገረው:: ዑመርም ‹እንኳን ደህና መጣህ ላንተ አቀባበል አያስፈልግም፡፡› አሉት፡፡ ሰውዬውም ‹አቀባበል የአላህ ነው ያንተ አያሣስበኝም፡፡ ቤተሰብ ደግሞ የለኝም አለው፡፡ (11)

ይህንን እጅግ ደረቅ የሆነውን የሰውዬውን መልስ የሠማ ሰው የዑመርን ትእግስት ማድነቁ አይቀርም፡፡ የዚህ ዓይነቶቹን የሙስሊም መሪዎች ታሪኮች ቀደም መሪዎቻችን ምን ያህል አስተዋይና በሳል እንደሆኑ ያመላክቱናል፡፡ የዛሬዎቹ አብዛኞቹ የሙስሊም ሀገራት መሪዎች ኢስላማዊውን ታሪክ በተለይም የዘመነ ኸሊፋውን ከጥናት ተቋማት፣ ከትምህርት ቤትና ከዩኒቨርስቲዎች  ወዲያ ገፍተውና አርቀው መልካም ሥነምግባርም ሆነ ለጥሩ አስተዳደግ እዚህ ግባ የማይባሉ የሌሎች ግለሰቦች ታሪኮችን የማሣደዳቸው ነገር እጅጉን ያሣዝናል፡፡

ይህ ሰው ሦስት ቀን ሙሉ ዑመር ዘንድ ሲመላለስ ቆየ፡፡ ሲጠይቁት ይህንኑ ቃል እንጂ አያሠማውቸም፡፡ በዚህ መልኩ እንጂ አይመልስላቸውም ነበር፡፡ በአራተኛው ቀን ዑመር ሰውየው ወዳለበት ገቡና ‹ከአሚርህ ምን ያስቆጣህ ነገር አለ?›› አለው፡፡ እሱም እንዲህ በማለት ከሠሠ ‹ስልሣ ምርጥ ምርጥ አገልጋዮችን ለራሱ አደረገ፡፡ ዐቂላ የምትባል አገልጋይ ባሪያ ያለችው ሲሆን ክብር ያላቸው ወታደሮች ከሷ ዘንድ ጧት ማታ እየገቡ ከአገልግሏ ይበላሉ፡፡ ከኛ መካከል አንድም ሰው ይህ እድል የለውም፡፡ ሁለት ፈረሦችና ሁለት ቀለበቶች አለው፡፡

ዑመር ሰውየው ያለውን ሁሉ በመፃፍ ለአቢ ሙሣ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከላኩ በኋላ እንዲመጣም አስጠሩት፡፡ አቢ ሙሣም በደረሠ ጊዜም ለተወሰኑ ቀናት አላናገሩትም ነበር፡፡ በመጨረሻም ሁለቱ ሰዎች ተጠሩና እንዲቀርቡ ተደረገ፡፡ ደብዳቤውንም ሰጡትና የፃፍኩትን አንብብ አለው፡፡ እንዲህ በማለት አነበበ ‹ስልሣ አገልጋዮችን ለራሱ ወሠደ፡፡› አቢ ሙሣም እንዲህ አለ ‹ስለነሱ ተጠቆምኩኝ፡፡ እዳ ነበረባቸው እዳቸውን ከፍዬ ነፃ በማውጣት ለሙስሊሞች ከፋፈልኩኝ፡፡› ድባህም እንዲህ አለ ‹ወላሂ አልዋሸም እኔም አልዋሸሁም፡፡ ‹ሁለት ፈረሦች አሉት› አለ፡፡ አቢ ሙሣም ‹አንዱ ለቤተሰቤ ሲሆን ለነሱ ቀለብ አቀርብበታለሁ አንዱ ደግሞ በሙስሊሞች እጅ ነው ያለው ሲሣያቸውን ይፈልጉበታል፡፡› አለ፡፡ ዲባህም ‹እሱ ዋሽቷል እኔ ግን አልዋሸሁም፡፡› አለ፡፡ ስለ ዐቂላ ሲያነሣ ደግሞ አቢ ሙሣ ዝም አለ፡፡ በዚህ ዙሪያ ምንም ምክኒያትም ባለማቅረቡም ድባህ ያመነለት መሠለው፡፡ ቀጥሎም ‹ዚያድ የሰዎችን ጉዳይ ያውቃል፡፡ ይህ ግን አያውቅም፡፡ ብልህና አስተዋይ ሆኖ ስላገኘሁት ሥራዬን ለሱ ሰጠሁት፡፡› አለ፡፡ (12)

ዑመር አቢ ሙሣን እንዲመለስ አዘዘው፡፡ ‹በተመለስክም ጊዜ ዚያድን እና ዐቂልን ላክ፡፡› አለው፡፡ አቢ ሙሣም ሁለቱን ሰዎች ላከ፡፡ ቀድማ የደረሠችው ዐቂላ ነበረች፡፡ ዚያድ መጣና በሩ ላይ ቆመ፡፡ ዑመር ሲወጡ ዚያድ ነጭ ኩታ ነገር ለብሦ በር ላይ ቆሞ አገኙት፡፡ ‹ይህ ልብስ ምንድነው?› አሉት፡፡ ዚያድም ነገራቸው፡፡ ‹ዋጋው ስንት ነው?›› በማለት ጠየቁት፡፡ ሲነግራቸው ዋጋው በጣም ቀላል ነበር፡፡ ስንት ነው የሚከፈልህ አሉት፡፡ ‹ሁለት ሺህ› አላቸው፡፡ ‹መጀመሪያ በተከፈለህ ምን ሠራህበት?› አሉት፡፡ ‹እናቴን ከባርነት ነፃ አወጣሁበት፡፡ በሁለተኛው ክፍያ ደግሞ አንድ አብሮ አደጌን ነፃ አወጣሁበት፡፡› ‹አላህ ገጥሞሃል፡፡› አሉት፡፡ ስለ ግዴታዎች፣ የነቢዩ ሱናዎች እና ስለ ቁርዓን ሲጠይቁት ከመለሰው መልስ ጥሩ የሃይማኖት ሊቅ መሆኑ ተረዱ፡፡ እንዲመለስ አደረጉ፡፡ የበስራንም አስተዳዳሪዎች የሱን ሀሣብ እንዲቀበሉ አሳሳቧቸው፡፡ (13) ዐቂላን ግን እዚያው አስቀሯት አልመለሷትም፡፡

ዑመር የዚህን በአደባባይ የተደረገውን ምርመራ ውጤት በህዝብ መሃል ይፋ አደረጉ፡፡ ዱኒያዊ ጥቅምን ስላስመለጠውና ስለሱም እውነት ተናግሮ ስላስዋሸው የሱ እውነት ውሸቱን ስላበላሸበት ዲባህ በአቢ ሙሣ እጅግ በመናደድ ወዲያውኑ ተለየው፡፡ ‹አደራችሁን ውሸትን ተጠንቀቁ፡፡ እሱ ወደ እሣት ይመራልና፡፡› (14)

እምነት በሙስሊሞች ውስጥ እጅግ ሰርፆ በነበረበት ሁኔታ ዑመር እንዲህ ጠንከር ያለ ግምገማ ማድረጋቸው እያንዳንዱ ሀላፊ በሚያስተዳደድረው ህዝብ ላይ እምብዛም ሀይል እንደሌለው ሆኖ እንዲታየው አድርጎታል፡፡

በአንድ ወቅት ሙስሊሞች ከከፈቷቸው ሀገሮች መካከል ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ለአባ ዑበይዳ ኢብኑ መስዑድ ሰቀፊ ‹ይህ ላንተና ካንተ ጋር ላሉ ሰዎች ክብራችንን የገለፅንበት ነው› በማለት የፋርስ ሀገር ውድ የሆነ ምግብ የያዘ እቃ ላኩለት፡፡ እሱም ‹ወታደሩንም በዚሁ መልኩ ነው ክብር የሠጣችሁትና ያስተናገዳችሁት?›› በማለት ጠየቃቸው፡፡ እነሱም ‹ይህን ለማድረግ አቅማችን አልፈቀደልንም፡፡› አሉት፡፡ አባ ዑበይድም ‹እንግዲያውስ ለወታደሮቻችን የማይበቃ ከሆነ እኛም አያስፈልገንም፡፡› በማለት መለሠላቸው፡፡

አባ ዑበይድ ከባሮስማ ግዛት መካከል የሆነችውን አንዲት መንደር በድል ሲገቡ ተመሣሣይ ክስተት ያጋጠመው ሲሆን ነዋሪዎቿ ምግብ ሰርተው ሲያመጡ ‹እኔ ይሄን ነገር ከሙስሊም ጓደኞቼ ውጭ የምበላ አይደለሁም፡፡› አላቸው፡፡ እነሱም ‹እባክህን ብላ፡፡ ለያንዳንዱ ባልደረባህ የዚህ ዓይነት አሊያም ከዚህ የሚበልጥ የሆነ ምግብ ቤቱ ድረስ እናደርስለታለን፡፡› ሲሉትና በላ፡፡ ሲመለሱ ምግብ ደርሷቸው እንደሆነ ባልደረቦቹን ጠየቃቸው፡፡ እነሱም ጥሩ ምግብ እንደመጣላቸው ነገሩት፡፡ (16)

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በወታደሩና በአለቃው አሊያም በመሪው መካከል ያደረጉት እኩልነት እዚህ ላይ ብቻ ያበቃ አልነበረም፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ከሙስሊሞች ወገን የሆነ ሰው አቢ ዑበይድን ለመውጋት ጦር አሰባስቦ የነበረን መጦር ኢብኑ ፍዷ (ጃባን) የሚባልን ሰው ማረከ፡፡ ሲማርከው አላወቀውም ነበር፡፡ ሰውዬው ትልቅ ሰው ሆኖ አርጅቶም ስለነበር አዘነለት፡፡ ጃባን ግን ይበልጥ ሊያታልለው በማሰብ ‹እናንተ ዐረቦች ሆይ! ቃላችሁን የምትሞሉ ታማኞች ናችሁ፡፡ ሥራ የሚያቀልሉህ ሁለት ቆንጆ ባሪያዎች ልስጥህና በሠላም ልትለቀኝ ትችላለህን?›› በማለት ሰውየውን ጠየቀው፡፡ ሰውየውም አልገባውም ነበርና ይበልጥ አዝኖለት ‹እሺ› አለው፡፡ ጃባንም ‹ እንግዲያውስ ንጉሣችሁ ዘንድ አስገባኝና እርሱ ባለበት ይሁን፡፡› አለው፡፡ አባ ዑበይድ ዘንድ ሲገቡ በዙሪያው የነበሩት ሰዎች አወቁት፡፡ ይህ እኮ ‹ ጃባን › የሚባለው ንጉስ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ጦር ያሠለፈብን እሱ ነው፡፡› አሉ፡፡ አቡ ዑበይድም ‹ የረቢዓ ሰዎች ሆይ! ምን የማደርግ ይመስላችኋል ! ጓደኛችሁ የደህንነት ዋስትና ሠጥቶት እኔ እገድለዋለሁን?› ከዚህ ዓይነቱ ድርጊት በአላህ እጠበቃለሁ፡፡› በማለት አሰናበቱት፡፡ (17)

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ለሁሉም ሰዎች ያሣዩት የነበረው እዝነት ከዚህ ሁሉ ይልቃል፡፡ ደህንነታቸው ይጠበቅ ዘንድ ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው፡፡ አቡ ዑበይዳ አስ ሰቀፊ ጂስር በተባለው ቦታ ላይ በወረርሽኝ በሽታ ተለክፈው ታመሙ፡፡ በሽታውን ፈርተው ከሸሹት ሰዎች መካከል የተወሰኑት ወደ መዲና መግባት እንዳፈሩ ዑመሩ ወሬ ደረሣቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ዑመር ‹አላህ ሆይ! እኔ እያንዳንዱን ሙስሊም ይቅር ብዬዋለሁ፡፡ እኔ ከጠላት ጋር ተገናኝቶ አንዳች ድንጋጤ ካገኘው ሙስሊም ወገን ነኝ፡፡ እኔ ወገኑ ነኝ፡፡ አላህ ለአባ ዑበይዳ ይዘንለት፡፡ ወደኔ ተጠግቶ በሆን ኖሮ መጠጊያው በሆንኩት ነበር፡፡› አሉ፡፡(18)

ዑመር በቃዲሲያ ጦርነት ወቅት በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ወደ በረሃው ይወጡና እስከ እኩለ ቀን ድረስ እዚያው በመቆየት ስለ ሠራዊቱ በመልካም ዜና የሚያበስራቸውን ሰው ይጠባበቁ ነበር፡፡ ካጡም ወደቤታቸው ይመለሣሉ፡፡ አንድ ቀን አንድ ብስራት ነጋሪ አጋጠማቸው፡፡ ሰውዬው አላወቃቸውም ነበር፡፡ ከየት እንደመጣ ጠየቁትና ‹አንተ የአላህ ባሪያ ሆይ! እስቲ አውራኝ፡፡› አሉት፡፡ ሰውዬውም ‹አላህ ጠላትን አዋርዷል፡፡› በማለት ተናግሮ ዞር ሣይል በግመሉ ላይ ሆኖ በፍጥነት ወደፊት ገሠገሠ፡፡ ዑመርም ፈጠን እያሉ እየተከተሉ ያናግሩታል፡፡ በዚሁ ሁኔታ መዲና ደረሱ፡፡ ሰውየው ሰዎች ለዑመር ‹የምእመናን መሪ ሆይ! አሠላሙ ዐለይኩም፡፡› ሲሉ ሰማ፡፡  በዚህን ጊዜ በሠራው ነገር አፈረ፡፡ ‹ምናለ የምእመናን መሪ እንደሆኑ ነግረውኝ በሆን ኖሮ አላህ ይዘንልዎ! አንተ የምእመናን መሪ ነዎትን!› አላቸው፡፡ ዑመርም ‹አይዞህ ግዴለም ተረጋጋ፡፡› አሉት፡፡ (19)

በሦሪያና አካባቢው የዐምዋስ ወረርሽኝ በተከሠተ ጊዜ አቡ ዑበይዳን ይህ በሽታ እንዳያገኛቸው ዑመር ተጨነቁ፡፡ እንዲህ በማለትም ፃፉለት ‹ሰላም ባንተ ላይ ይሁን፡፡ በግልፅ የማዋይህ ጉዳይ ነበረኝ፡፡ ይህ ደብዳቤ እንደደረሠህ ወዲያውኑ በአስቸኳይ እንድትመጣ፡፡› አሉት፡፡ አባ ዑበይዳህ ግን ዑመር እሱን ከወረርሽኙ ለማዳን የተጠቀሙት መላ እንደሆነ ገባው፡፡ በመሆኑም እንዲህ አለ ‹አላህ ለምእመናን መሪ ይዘንለት፡፡› ‹የምእመናን መሪ ሆይ! እኔ ጉዳይህን አውቄያለሁ፡፡ እኔ በሙስሊም ወታደሮች መካከል ነው ያለሁት፡፡ እነሱን ትቼ መሄድ አልፈልግም፡፡ አላህ በኔና በነሱ መካከል ቀዷና ቀደሩን እስኪወስን ድረስ ከነርሱ መለየት አልፈልግም፡፡ የምእመናን መሪ ሆይ! ባለመምጣቴ ይቅር በሉኝ፡፡ ከሰራዊቴ ጋር ይተውኝም፡፡› ዑመር ደብዳቤውን ባነበቡ ጊዜ አለቀሱ፡፡ ሰዎችም ‹አቡ ዑበይዳ ሞተ እንዴ!› በማለት ጠየቁት፡፡ ዑመርም ‹ አይ ያው እንደሆነ ነው..› አሏቸወ፡፡

ከዚያም መልሰው ፃፉለት ‹ ሰላም ባንተ ላይ ይሁን፡፡ በርግጥ ሰዎችን ረባዳ ቦታ ላይ ነው ያሰፈርከው፡፡ በመሆኑም ከፍ ወዳለ ቦታ ውሰዳቸው፡፡› ደብዳቤው በደረሰው ጊዜ አባ ዑበይዳ አቢ ሙሣን አስጠሩትና ‹አባ ሙሳ ሆይ! የምእመናን መሪ ደብዳቤ የያዘውን መልእክት አይተሃል፡፡ በል ውጣና ለሰዎች ማረፊያ ቀይርላቸው፡፡ እኔም እከተልሃለሁ፡፡› አሉት፡፡(20)

የፅሁፉ ምንጮች

[1].   ፉቱህ አል ቡልዳን ሊልቡልዳን ገፅ 78

[2].  ታሪኽ አልረስል ወልሙሉክ ቅ. 2 ገፅ 248

[3].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 660

[4].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 4

[5].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 12

[6]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 505

[7].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 128

[8].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 130

[9]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 471

[10].አል ካሚል ፊታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 437

[11]. አል ካሚል ፊታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 468

[12].ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 556

[13].ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 557

[14].አል ካሚል ፊታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 468

[15].ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 637

[16]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 637

[17].ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 635

[18].ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 642

[19]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 84

[20]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 488 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here