መጠነኛ ቅኝት ስለ ኹለፋኡ ራሽዲን ዘመን (ክፍል 4)

0
3613

የዑመር አልፋሩቅ ኸሊፋነት

አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በታመሙና አጀላቸውም እንደተቃረበ በተሠማቸው ጊዜ እርሣቸውን በሚተካ ሰው ዙሪያ ትላልቅ ሰሃቦቻቸውን አማከሩ፡፡ እንዲህም አሏቸው

“إني قد نزل بي ما ترون ، ولا أظنني إلا ميتا لما بي ، وقد أطلق الله أيمانكم من بيعتي، وحل عنكم عقدتي، ورد عليكم أمركم، فأمَروا عليكم من أحببتم، فإنكم إن أمرتم عليكم في حياة مني كان أجدر ألا تختلفوا بعدي

‹የምታዩት ነገር ላይ በኔ ደርሷል፡፡ እኔም ካገኘኝ ነገር የተነሣ ከሞት የምተርፍ መስሎ አይታየኝም፡፡ አላህ ለኔ የገባችሁትን የድጋፍ መሃላ አንስቶላችኋል፡፡

ለኔ የገባችሁትንም ቃልኪዳንም ፈትቶላችኋል፡፡ የናንተንም ጉዳይ ወደናንተው መልሶላችኋል፡፡ የወደደችሁትን ሰው በራሣችሁ ላይ አሚር/መሪ/ አድርጉ፡፡ እኔ በመካከላችሁ በህይወት እያለሁ አሚር የመረጣችሁ እንደሆነ ከኔ በኋላ የመለያያታችሁ ነገር አይታሰብም፡፡› (1)

በዚህ መልኩ ነበር ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ህልፈት በኋላ የመጀሪያው የሙስሊሞች ኸሊፋ የሆኑት አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ህዝቡን የሚመራ መሪ የመምረጥ መብት ያለው ህዝቡ ብቻ መሆኑን ያረጋገጡት፡፡ ያንን ዘመን ተከትሎ የመጣው የዓለም ማህበረሰብ ይህንኑ የቀደምት ሙስሊሙን መልካም አካሄድ ተከትሎ ቢሆን ኖሮ የፈረንሣይ አብዮት ተከስቶ ምዕራባውያን የዲሞክራሲንና የምርጫ ነፃነትን ከማስተዋወቃቸው በፊት በርካታ ዘመናትን በአምባገነንነት ሥርዓት ሥር ባላሣለፈ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን በሙስሊሙ ሀገራ አካባቢ ያለው የአስተዳደርና የመተካካት ሥርዓት ከኢስላማዊው አሠራር በእጅጉ የራቀ ነው፡፡  ሙስሊሞች አቡበክር አስስዲቅም ሆነ ከርሣቸው በፊትም ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም  ባሰመሩላቸው መንገድ ቢጓዙ ኖሮ ህዝበ ሙስሊሙ ኡማ ለበርካታ በደሎችና ችግሮች ባልተዳረገ ነበር፡፡

ወደ ታሪኩ እንመለስ .. ኸሊፋው አቡበክር የመረጧቸው ሰሃቦች ለተወሠነ ጊዜ ከተመካከሩ በኋላ ከመካከላቸው አንድ ሰው ይመርጡላቸው ዘንድ ተመልሰው መጡ፡፡ አቡበክርም ‹በምትመርጡት ሰው ላይ የተለያያችሁ መሠለኝ፡፡› አሏቸው፡፡ ‹አይ አይደለም፡፡› አሉት፡፡ ‹አደራችሁን በመስማማት ላይ የአላህ ቃልኪዳን ይኑራችሁ፡፡› አሏቸው፡፡ እነሱም ‹በጀ› አሉ፡፡ እሱም ‹ጥቂት ታገሱኝና ለአላህ፣ ለእምነቱና ለባሮቹ ጥቂት ላስብ፡፡› አሉ፡፡ (2)

አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ማንኛቸው ታላቁን ሀላፊነት ለመረከብ የተሻለ ብቃት እንዳለው ለመለየት ሙሉ ቀኑን በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች ማንነትና የሚበላለጡበትን ደረጃ ሲመረምሩ ዋሉ፡፡ ከዚያም ወደ ዑስማን ኢብኑ ዐፋን፣ ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ፣ ሰዒድ ኢብኑ ዘይድ፣ ኡሰይድ ኢብኑ አልኹደይር እና ወደ ሌሎች ሙሃጅሮችና አንሷሮች አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ላኩ፡፡ ሁሉንም እርሣቸው ወዳሉበት እንዲገቡ ካደረጉ በኋላ አንዳቸውም ያለእፍረትና ነገሮችን መሸፋፈን የየራሣቸውን ሀሣብ በግልፅ እንዲናገር አደረጉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም የጥቆማ እጆች ወደ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ነበር ያመለከቱት፡፡

ለዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ ‹ እስቲ ስለ ዑመር ንነገረኝ፡፡› አሉት፡፡ እሱም ‹የአላህ መልእክተኛ ኸሊፋ ሆይ! አንተ ካቀረብከው ሰዎች ሁሉ በላጩ እሱ ነው፡፡ ነገርግን ትንሽ ጠንከር ይላል፡፡› አለው፡፡ አቡበክርም ‹እኔን ለስላሣ ሆኜ ስለሚያየኝ ነው፡፡ ሁሉ ነገር ለሱ ቢሰጠው ግን ያለበትን በርካታ ነገሮች መተው ይችላል፡፡ የሙሀመድ አባት ሆይ! በርግጥ ፈትኜዋለሁ፡፡ በአንድ ሰው የተቆጣሁ እንደሆነ ድርጊቴን ሲወድ የተለሣለስኩ እንደሆነ ደግሞ ጠንከር ሲል አይቼዋለሁ፡፡› ካለው በኋላ ‹የሙሀመድ አባት ሆይ! እባክህን ይህን የነገርኩህን ነገር ለማንም እንዳትናገር› አሉት፡፡ ዐብዱረህማንም ‹ጥሩ› አለ፡፡

ቀጥሎም ዑስማን ኢብኑ ዐፋንን ጠሩትና ‹የዐብደላህ አባት ሆይ! እስቲ ስለ ዑመር ንገረኝ፡፡› አሉት፡፡ ዑስማንም ‹አንተ ስለሱ ጉዳይ ከኔ በላይ ታውቃለህ፡፡› አለው፡፡ አቡበክርም ‹የዐብደላህ አባት ሆይ! በርግጥ አውቃለሁ፡፡› አሉት፡፡ ዑስማንም ‹ጌታዬ ሆይ! እውስጡም እላዩን ከሚታየው የተሻለ እንደሆነና የሱ ዓይነት ሰውም በውስጣችን እንደሌለም አሣውቀኝ፡፡› አለ፡፡ አቡበክርም ‹የዐብደላህ አባት ሆይ! አላህ ይዘንልህ፡፡ እኔ የነገርኩህን ለማንም አትንገር፡፡› ዑስማንም ‹ጥሩ› አለ፡፡ (3)

ሁሉም አባላት በዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ኸሊፋነት መስማማታቸውን ባስተዋሉ ጊዜ አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ዑስማን ኢብኑ ዐፋንን በዑመር ኸሊፋነት ላይ የመስማማት ቃልኪዳናቸውን ይፅፍላቸው ዘንድ ለብቻው ጠሩት፡፡ ከዚያም እንዲህ በማለት ፃፍ አሉት ‹ቢስሚላህ ረህማኒ ረሂም.. ይህ አቡበክር ኢብኑ አቢ ቁሃፋ ለሙስሊሞች የገባው ቃልኪዳን ነው..› እንዳሉ አቡበክር እራሣቸውን ሣቱ፡፡ ዑስማን ግን የሀሣባቸውን ያወቁ ይመስል መፃፋቸውን ቀጠሉ ‹እኔ ዑመርን በናንተ ላይ ኸሊፋ እንዲሆን ሾሚያለሁ፡፡ ይህም የተሻለና መልካም ነገር ስለመረጥኩላችሁ ብቻ ነው፡፡› ወዲያው ግን አቡበክር እራሣቸውን ከሳቱበት ነቁና ‹የፃፍከውን አንብብልኝ፡፡› አሉት፡፡ ዑስማንም አነበበላቸው፡፡ አቡበክር የልባቸው የደረሠ በሚመሰል መልኩ ‹አሏሁ አክበር!› ካሉ በኋላ ‹በዚያው እራሴን በሣትኩበት ሁኔታ እንዳልሞት ፈርተህ ይህን ያደረግክ ይመስለኛል፡፡› አሉት፡፡ ዑስማንም ‹አዎን› አላቸው፡፡ አቡበክርም ‹ለእስልምና እና ለህዝቦቹ ላደረግከው ነገር አላህ በመልካም ይመንዳህ፡፡› አሉት፡፡ (4)

ከዚያም አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከባለቤታቸው አስማእ ቢንት ዑመይስ ቤት በኩል እሷ እየደገፈቻቸው እንዲህ እያሉ ወደተሰበሰበው ሰው ብቅ አሉ፡፡ ‹እኔ የምተካላችሁን/የምሾምላችሁን/ ሰው አትወዱምን? እኔ ወላሂ ለናንተ ጥሩውን ነገር ከመምረጥ አልቦዘንኩም፤ ዘመዴንም በናንተ ላይ አልሾምኩም፡፡ እኔ ዑመር ኢብኑ አልኻጧብን ተክቼላችኋለሁ፡፡ አዳምጡት ታዘዙትም፡፡› እነሱም ‹ሰምተናል ታዘናል፡፡› አሉ፡፡

የቃልኪዳን ፅሁፉን ካነበቡ በኋላ ጦልሃ ኢብኑ ኡበይዱሏህ ወደርሣቸው ገባ፡፡ የዑመር አያያዘ ብርቱነት አሁንም እንዳስፈራው ነው፡፡ ይህ ነገር ሙስሊሞችን እንዳይከብዳቸው የሠጋ ይመስላል፡፡ ‹በህዝቡ ላይ ዑመርን ኸሊፋ አደረግክ፡፡ አንተ ከርሱ ጋር እያለህ እንኳን በሰዎች ላይ ይደርስ የነበረውን ነገር የምታውቀው ነው፡፡ አንተ ካለፍክ በኋላ ለብቻ ሲያገኛቸው ደግሞ ሰዎችን ምን ሊያገኛቸው እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ አላህ ትተህ ስለመጣሀው ህዝብህ ቢጠይቅህ ምን ትመልሣለህ!፡፡› አለው፡፡ አቡበክርም ‹እስቲ አሣርፉኝ› ብለው ካረፉ በኋላ ‹በአላህ ታስፈራራኛለህን!? ጌታዬን ተገናኝቼ እሱም ከጠየቀኝ በህዝቦችህ ላይ ከህዝቦችህ ውስጥ የተሻለውን ሰው ተክቼያለሁ፡፡ እላለለሁ፡፡›› አሉት፡፡

በመካከላቸው የተደረገው ቃለ ምልልስ ሁለቱንም የሚያስመሰግን መሆን እንገነዘባለን፡፡ አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ሀቅን አውቀው በመያዛቸው ሊወደሱ ይገባል፡፡ ጦልሃም አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና ከራሱ ስሜት በመነሣት ሣይሆን የታየውን ክፍተትና የፈራውን ነገር በማንሣት ለኸሊፋው በማመላከቱ በጎ ነገር ሰርቷልና ሊመሰገን ይገባል፡፡ የጦልሃ ዓላማ ሆነ ብሎ ኸሊፋውን ለማሣሣት አልነበረም፡፡ ያለ አንዳች ማስመሰልና መለሣለስ መቃወም ያለበትን ነገር ተቃወመ። አንድን ነገር ለመቃወም ምርጡ አካሄድም ይሀው ነው፡፡ ሰዎች ርቀው እንዳይጠራጠሩና እንዳያስቡ ያደርጋልና፡፡

ጦልሃ አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና በዑመር የኸሊፋነት ዘመንም የሹራ/የምክር ቤት/ አባል ነበር፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከመሞታቸው በፊት ደግሞ ለኸሊፋነት ካጯቸው ስድሰት ሰዎች መካከልም አንደኛው ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያመለክተን ጦልሃ የዑመርን ኸሊፋነት የተቃወመው ለእስልምናና ሙስሊሙ ማህበረሰብ አብዝቶ ከማሰብ እንጂ በዑመር ላይ ክፉ አስቦ እንዳልሆነ ነው፡፡ ዑመርም ቢሆን ይህን የተረዱ ይመስላሉ፡፡ በመሆኑም ጦልሃ በተናገረው ላይ ቂም አልያዙበትም፡፡ ንግግሩም ሀቅን ከማየት አልጋረዳቸውም፡፡

ከጦልሃ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ አቡበክር ዑመርን ወደራሣቸው አቀረቡና ‹በአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰሃቦች ላይ ኸሊፋ አድርጌሃለሁ፡፡› አሉት፡፡ ከዚያም በአላህ ፍራቻ ላይ መከሩት፡፡ እንዲህም አሉት ‹ዑመር ሆይ! አላህ በቀን ውስጥ ሀቅ አለው በለሊት የማይቀበለው የሆነ፡፡ በለሊት ውስጥም ሀቅ አለው በቀን ሰዓት የማይቀበለው የሆነ፡፡ አላህ ግዴታውን ሣትወጣ  በፈቃደኝነት የምሰራውን ሥራ አይቀበልም፡፡ ዑመር ሆይ! የቂያማ ቀን ሚዛናቸው የከበደች ሰዎች ሚዛናቸው ከበድ ሊል የቻለው እውነትን በመከተላቸውና እውነትም በነሱ ላይ በመክበዱ እንደሆነ አታውቅምን!? ለነገ ብለው ያኖሩበት ሚዛን ከፍ/ከበድ/ ማለቱ ግድ ነው፡፡›

‹ዑመር ሆይ! የቂያማ ቀን ሚዛናቸው የቀለለችባቸው ሰው ሚዛናቸው ልትቀል የቻለችዉ ሀሠትን በመከተላቸውና ሀሠትም በነሱ ላይ በመቅለሏ መሆኑን አታውቅምን!? ለነገ ተብሎ ያላኖሩበት ሚዛን መቅለሉ ግድ ነው፡፡ ዑመር ሆይ! የረኻእ/ለዘብታ/ አንቀፆች ከሺዳ/ጥንካሬ አንቀፆች/፤ የጥንካሬ አንቀፆች ደግሞ ከለዘብታ አንቀፆች ጋር ጎን ለጎን መውረዳቸውን አታስተውልምን !? ይህም አንድ አማኝ አላህን በመከጀልና በፍራቻው መካከል አመዛዝኖ ይኖር ዘንድ ነው፡፡ ይህም የሌለውን ነገር በአላህ ላይ እንዳይመኝ አሊያም መፍራት የሌለበትን ነገር እንዳይፈራ ያደርገዋል፡፡›

‹ዑመር ሆይ! የእሣት ሰዎች በመጥፎ ሥራዎቻቸው የተወሱ መሆኑን አታይምን! አንተም እነሱን ያወሣህ እንደሆነ ‹እኔ ከነሱ እንዳልሆን እከጅላለሁ› ትላለህ፡፡ የጀነት ሰዎች ደግሞ በመልካም ሥራዎቻቸው ነው የተወሱት፡፡ ምክኒያቱም ጥሩ ሥራቸው ከመጥፎው በልጦ አመዝኗልና፡፡ እነሱንም ያወሣህ እንደሆነ ‹ከነሱ ሥራ አንፃር እኔ ምን ሥራ አለኝ!!› ትላለህ፡፡ ይህን የኔን ምክር የተቀበልክ እንደሆነ እሩቅ ከሆነው ነገር ሁሉ ከሞት በላይ ወዳንተ ተወዳጅ የለም፡፡ አንተም ከሱ የምትቀር አይደለህም፡፡› አሉት። (5)

እንዲህ እንዲህ እያለ አላህ በፈቀደው መልኩ ሁሉም ነገር  ወደፊት ይጓዛል፡፡ አንድም ገዥ የለም የትኛውን ያህል እድሜው ቢረዝም ስዲቁ አቡበክር ባለፉበት መንገድ ላይ ያለፈ ቢሆን እንጂ፡፡ ማንኛውም ፍጥረት አንድ ቀን ይህችን ዓለም በመሰናበት አኺራን ለመቀበል ዝግጁ ይሆናል፡፡ ያኔ የሰው ልጅ ምርመራው ለወደፊት ህይወቱ ባስቀደመው ነገር ላይ ነው፡፡ ታዲያ ለምንድነው እያንዳንዱ ገዥ/ መሪ/ ከአቡበክር ስዲቅ ሁኔታ ትምህርት የማይወስደው!? አላህ ፊት ተጠያቂ እንዳይሆን፣ ከሱ በኋላ የሚመጡትም ሆነ የሚመራቸው ህዝቦች እንዲደሰቱበት ከሱ በኋላ ለሚመጡትም በተመሣሣይ መልኩ አደራ የማይለው!?

አቡበክር ይህን አደራ እንዳደረሱ ህይወታቸው አለፈች፡፡ ጊዜውም በ13ኛው አመተ ሂጅራ ለጁማደል አኺር ወር ስምንት እና ሰባት ቀን ሲቀረው ነበር፡፡ የኸሊፋነት ዘመናቸውም ሁለት አመት ከሦስት ወር እና ከአሥር ቀን የቆየ ሲሆን እድሜያቸውም 63 አመት ነበር፡፡

የመጀመሪያው የሙስሊሞች ኸሊፋ አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በሞቱበት እለት ሰዎች ወደ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና መጡና ቃልኪዳናቸውን ሰጡ፡፡ ሂደቱም እስከ ሦስት ቀን ድረስ የዘለቀ ነበር፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ወደ ሚንበር ወጡና እንዲህ አሉ ‹የዐረቦች ምሣሌ መሪውን እንደሚከተል ግመል አፍንጫ ነው፡፡ መሪው ወዴት እንደሚመራው ይመልከት፡፡ እኔማ.. ወላሂ በጌታዬ ይሁንብኝ በመንገድ ላይ ቀጥ አድርጌ እመራችኋለሁ፡፡› አሉ፡፡ (6) ዑመር በመልካም ነገር ላይ እስካገኛችሁኝ ድረስ ተከተሉኝ የሚሉ ይመስላሉ፡፡

በቀጣዩ ቀን ፈጅር/ንጋት/ ላይ የዒራቅ ሀገራትን የመክፈቱ ሥራ ይጠናቀቅ ዘንድ አቡበክር ከመሞታቸው በፊት አዘውበት ስለነበር ይሀው ትእዛዝ በፍጥነት እንዲፈፀም ሰዎች ከሙሰና ኢብኑ አልሃሪሣ ጋር በመሆን ወደ ዒራቅ ለመውጣት ፈለጉ፡፡ በወቅቱ አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹እኔ ዛሬውኑ ልሞት እችላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ የሞትኩ እንደሆነ ከሙሰና ጋር ቶሎ ትሄዱ ዘንድ አታቆዩኝ፡፡ የደረሳባችሁ ችግርም ከሃይማኖት ጉዳያችሁና ከጌታችሁ ትእዛዝ አያዘናጋችሁ፡፡ በርግጥ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሲሞቱ አይቻቸዋለሁ፡፡ እኔም ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ የሰው ልጅ በርሣቸው ሞት እንደተጎዳ በማንም አልተጎዳም፡፡› (7)

የያኔውን የሙስሊሞች ሁኔታ ከዛሬው ጋር ስናነፃፅር ሌላው ቀርቶ የሀዘን ሥርዓቱ እንኳን እጅግ የተራራቀ መልክ ይዞ እናገኛለን፡፡ ታላቁ ነቢይም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሆነ አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ሲሞቱ ሰሃቦች እንዴት ለቀብር ሥርዓቱ እንደተቻኮሉና ወደ ቀጣዩ ሥራ ለመግባት እንዴት እንደተጣደፉ አይተናል፡፡ ዛሬ ዛሬ ሙስሊም ንጉሣውያንና ገዥዎች ሲያልፉ ባለሥልጣናት በርካታ የሀዘን ቀናትን በማወጅና ለቀብር ሥርዓቱም ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ የሀገር ሀብት ሲያባክኑ ይታያሉ፡፡ ለከፍተኛ ልማት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ቀናትና ጊዜያትም ሲባክኑ ይስተዋላሉ፡፡ እነሱ ግን ለማንም የሰው ልጅ ለማይቀረው ዓለም ለተሸጋገረው መሪያቸውና ለሀገራቸው ጥሩ ነገር የሠሩ እየመሠላቸው ነው ይህን የሚያደርጉት፡፡ ትክክለኛ የሀገርና የህዝብን አደራን መወጣትን ግን ከአቡበክር እና ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ሥነምግባር መማር እንችላለን፡፡ እነሱ ስለህዝባቸውና ስለዲናቸው እንጂ ስለራሣቸው ፈፅሞ አልተጨነቁም፡፡ ዲናቸውንና ማህበረሰባቸውን ለማገልገልም አንዳችም አልተሣነፉም፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደ አቡበክር ሁሉ ኸሊፋ ከመሆናቸው በፊት በንግድ ሥራ ይተዳደሩ ነበር። ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ቢሆን ለተወሠነ ጊዜ ሰርተዋል፡፡ በቃዲሲያ እና በደማሰቆ ሙስሊሞች ድል ካደረጉ በኋላ ግን እንዲህ በማለት ያሉበትን ሁኔታ አስረዱ ‹እንደምታውቁት እኔ ነጋዴ የነበርኩ ስሆን በንግድ ሥራዬም ቤተሰቤን አስተዳድር ነበር። ዛሬ ግን በጉዳያችሁ ተጠምጄ ጊዜ አጥቻለሁ፡፡ ይህ የህዝብ ገንዘብ ለኔ ሀላል ይሆናልን?› በማለት ጠየቀ፡፡ ሰዎችም በአንድ ደምፅ የተስማሙ መሆኑን ገለፁለት፡፡ ዐሊይ ኢብኑ አቢጧሊብ ግን በመካከላቸው ሆኖ ዝምታን መርጧል፡፡ ይህን ያስተዋሉት ዑመርም ‹ዐሊይ ሆይ! ምን ትላለህ?› አሉት፡፡ እሱም ‹አንተንና ቤተሰቦችህን የሚበቃ ያህል መልካም በሆነ መልኩ ውሰድ ከዚህ ውጭ ገንዘብ የለህምና፡፡› አለ፡፡ ሰዎችም ‹የአቢ ጧሊብ ልጅ ያለው ነገር ትክክል ነው፡፡› አሉ፡፡

በቀደመው ዘመን ሙስሊሞችን ይመራ የነበረው መንግስት አካሄድ ይህን ይመስል ነበር፡፡ ሰዎች ተሰብስበው የኸሊፋው ደሞዝ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ወሰኑ፡፡ ውሣኔውም ተቃውሞ አላጋጠመውም ነበር፡፡ ሙስሊሞች ድል በድል ሆነው በርካታ ሀገራትን ከፍተው ገቢያቸው በጨመረ ጊዜ ምክር ቤቱ ለዑመር ክፍያውን መጨመር ፈለገ፡፡ ዑመርም እንዲህ በማለት ሀሣቡን ተቃወሙ ‹የኔና የሁለቱ ጓደኞቼ (የአላህ መልእክተኛና አቡበክር) ጉዳይ ወደ መንገድ እንደገቡ ሦስት ጓደኛሞች ነው፡፡ የመጀመሪያው አለፈ፤ ጥሩ ሰንቅ ይዞ ነበርና ካሰበውም ደረሠ፡፡ ሁለተኛውም ወደ መንገዱ ገባ፤ የመጀመሪያውን መንገድ ተከተለና እሱ ካለበትም ደረሠ፡፡ ከዚያም ሦስተኛው ተከተለው፤ እሱም የነሱን መንገድ ፀንቶ የያዘ እንደሆነና እነሱን ይዘው የነበረውን ስንቅ ወዶ ከያዘ ከነሱ ጋር ሊሆን ይችላል፡፡ ከነሱ ውጭ መንገድ የተከተለ እንደሆነ ደግሞ ሊያገኛቸው አይችልም፡፡› (8)

ዛሬ በተለይ በሙስሊም ሀገራት አካባቢ የምናየው አሠራር ግን አንድ ንጉስ አሊያም መሪ ሥራውን ለማስፈፀም የተመደበለትን ክፍያ በግልፅ የሚያሣይ አይደለም፡፡

አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና አንድን ጉዳይ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ባለሙያና አዋቂ ለሆነው ሰው ይሠጡ እንደነበረው ሁሉ ዑመርም ይህንኑ በማድረግ የቀደማቸውን ኸሊፋ መንገድ ይከተሉ ነበር፡፡ ሰዎች ከሙሰና ኢብኑል ሀሪሳ ጋር በመሆን ወደ ዒራቅ ለመውጣት በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡ ለመውጣት ግን ብዙዎች ዘገዩ፡፡ አቡ ዑበይዳና ኢብኑ መስዑድ ግን ፈጥነው ወጡ፡፡ ዑመርም አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና የጦሩን አመራር ለሱ ሠጡት፡፡ ይህን አስመልክቶ ከሙሃጅሮች እና ከአንሷር ቀደምት የሆነውን ሰው  አሚር ማድረግ ሲገባቸው ለምን እንዳላደረጉ ተጠየቁ፡፡ ዑመርም ‹ወላሂ አላደርገውም፡፡ አላህ እናንተን ከፍ ሊያደርግ የቻለው ወደ ጠላት በመቅደማችሁና ፈጥናችሁ በመውጣታችሁ ነው፡፡ የፈራችሁና ከጠላትም መገናኘት የጠላችሁ እንደሆነ ከናንተ ይልቅ ወደ ጠላት ቀድሞ የወጣው ለመሪነት የሚገባው እሱ ነው፡፡ … ወላሂ ቀድሞ የወጣውን ሰው እንጂ በነሱ ላይ አልሾምም፡፡› በማለት አስረግጠው ነገሯቸው፡፡

በዚህ መልኩ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ብቃትን መስፈርት ባደረገ መልኩ በተገቢው ቦታ ላይ ተገቢውን ባለሙያ በማስቀመጥ አሠራሩንም ለሌሎች መንገድ አደረጉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ አካሄድ በወቅቱ የነበሩት ሙስሊሞች በከፍተኛ ፍጥነት እንዲስፋፉና ጠላቶቻቸውን ድል እንዲነሱ በላቀ ደረጃ አግዟቸዋል፡፡

አቡ ዑበይዳ አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና ጦሩን ይዞ ከመንቀሣቀሱ በፊትም ዑመር እንዲህ በማለት ምክር ሰጡት ‹አንተ የምትሄደው ተንኮልና ሴራ፤ ክህደትና አምባገነንነት ወደሞላበት ምድር ነው፡፡ እድሜያቸውን በሙሉ በጥፋት ላይ በኖሩና ባስተማሩ፤ ስለመልካም ነገር የማያውቁና ግድም የሌላቸው ሰዎች ዘንድ ነው የምትሄደው፡፡ በመሆኑም ምን ማድረግ እንዳለብህ ካሁኑ በደንብ አስብበት፡፡ ምላስህን ጠብቅ፣ ሚስጢርህን አታውጣ፡፡ የሚስጢር ባለቤት ሚስጢሩን እስከጠበቀ ድረስ ጥብቅ ነው፡፡ በሚጠላው ወገን በኩል አደጋ አያጋጥመውም፡፡ ሚስጢሩን ያዝረከረከ እንደሆን ግን ውጤቱን በእጁ ማግኘቱ ይቀርም፡፡› (9)

ይህ ሁሉ የሚያሣየን ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ስለ ጠላቶቻቸው ሁኔታ በሚገባና ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውን ነው፡፡ ምናልባት በዚህ ጉዳይ ላይ ሙሉ መረጃም ኖሯቸው ሊሆን ይችላል፡፡

የዒራቅን ጉዳይ በጨረሱ ጊዜም በሻም ምድር ላይ ለሚገኘው ሠራዊት መሪ ይሆን ዘንድ አቡ ዑበይዳን በኻሊድ ምትክ ሾሙ፡፡ ይህን ያደረጉት የሙስሊም ጦር ከኻሊድ ባየው አመራርና ድል ድራጊነት የተነሣ ሁሌም መዋጋት የሚፈልገው በኻሊድ ጥላ ሥር ብቻ ሆኖ መሆኑን ስለተረዱ ነው፡፡ ተጠራጣሪዎች በበኩላቸው ዑመር ኻሊድን በማንሣታቸው በዑመር ላይ ብዙ መጥፎ ጥርጣሬዎችን አስነሱ፤ አስወሩም፡፡ ዑመር ግን ኻሊድን ያነሱት ለብዙሃኑ ጥቅም አስበው እንጂ ከሱ አንዳች ነገር ሰምተው እንዳልሆነ ይህን ያደረጉት ሰዎች ኻሊድን ከመጠን በላይ ስላጋነኑትና ስላተለቁት ድል ከአላህ ብቻ እንደሆነ ለማሣወቅ ብቻ መሆኑን ለማስረዳት ሞከሩ፡፡ (10)

ዑመር በስሜት የማይነዱ ሰው ናቸው፡፡ ሰዎችንም የሚሾሙት በርሣቸው ዘንድ ባላቸው ቅርበትና ርቀት ሣይሆን በብቃታቸው ነው፡፡ በራሣቸው ስሜት ምክኒያት አንድም መሪ ከቦታው አላስነሱም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ለአላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እራሣቸውን አሳልፈው  የሠጡ ናቸው፡፡

በአንድ ወቅት ከእስልምና በፊት ወንድማቸውን የገደለ አንድ ሰው ወደርሣቸው መጣ፡፡ እርሣቸውም ‹ዘይድን ስለገደልክ ፈፅሞ አልወድህም፡፡› ይሉታል፡፡ ሰውዬውም በተራ የገጠር ሰው ደረቅ አነጋገር ‹እኔን መጥላትህ መብቴን ከመስጠት ይከለክለሃልን?› አላቸው፡፡ ዑመርም ወዲውኑ ‹የለም/አይከለክልም› አሉት፡፡ ባላገሩ ሰውዬም ‹ሰዎች ለፍቅር የሚያለቅሱት ለምን ይሆን!› በማለት በመገረም መልክ እስከመጠየቅ ደርሷል፡፡ ሰውዬው ‹ዑመር ሆይ! ብወድህም ባልወድህም ከኔ የሚቀነስ አሊያም ለኔ የሚጨመርልኝ ነገር ስለሌለ ግድ የለኝም፡፡› የሚል ይመስላል፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና አቡ ዑበይዳ ኢብኑ አልጀራህን ከመሠናበታቸው በፊትም እንዲህ ብለውታል ‹ቀሪ በሆነውና ከሱ ውጭ ያለ ሁሉ ጠፊ በሆነውና ያ ከጥመት ወደ ቀጥተኛ ጎዳና ከጨለማዎችም ወደ ብርሃን ለመራን አላህ ፍራቻ እመክራሃለሁ፡፡ በኻሊድ ኢብኑ አልወሊድ ጦር ላይ አዛዥ እንድትሆን ሹሜሃለሁ፡፡ ካንተ የሚጠበቀውን ተገቢ አመራር ስጣቸው፡፡ ለምርኮ ቋምጠህ ሙስሊሞችን ለጥፋት አትዳርግ፡፡ ለነሱ ሣታዘጋጅላቸው በፊትም ከአንድ ቦታ አታሣርፋቸው፡፡ እንዴት ከዚያ መድረስ እንደምትችልም እወቅ፡፡ ከብዙ ሰዎች ጋር ካልሆነ በቀር አንዲትን ጭፍራ አትላክ፡፡ አደራህን ሙስሊሞችን ወደ ጥፋት አትላክ፡፡ አላህ እኔን ባንተ ፈትኗል አንተንም በኔ ፈትኗል፡፡ ከዚህች ዓለም ጥቅም ዐይንህን ጨፍን፡፡ ፊትህንም ከሷ አዙር፡፡ አደራህን ካንተ በፊት የነበሩትን እንዳጠፋች ሁሉ አንተንም እንዳታጠፋህ፡፡ በርግጥም መውደቂያቸውን አይቻለሁ፡፡› (11)

በዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና የኸሊፋነት ዘመን በርካታ የሻም /ሰሜን ዐረቢያ/ አካባቢ አገሮች ተከፍተዋል፡፡ ሁሉም ግዛቶች የተከፈቱት በአቡ ዑበይዳና ከሱ ጋር በነበሩ የጦር መሪዎች አማካይነት ነው፡፡ የተከፈቱ ሀገሮች ህዝቦችም በሙስሊሞቹ አመራር ሥር ለመኖር ቃልኪዳን ገቡላቸው፡፡ ኻሊድ ለዒራቅ ሰዎች የሠጠውን ዓይነት የደህንነት ዋስትናም ሠጧቸው፡፡ ለዚህም ምሣሌ መሠረት ሹረህቢል ኢብኑ ሀሠና ለጦበሪያ ሰዎች ያቀረበው ቅድመ ሁኔታን ማንሣት ይቻላል፡፡ ሹረህቢል የሀገሬው ነዋሪ ህዝቦች እሱን ትተው ከጠላት ወገን ጋር እስካልወገኑ ድረስ ለነፍሦቻቸው፣ ለንብረቶቻቸው፣ ለልጆቻቸው፣ ለፀሎት ቤታዎቻቸውም ሆነ ለቤቶቻቸው ሁሉ ሙሉ የደህንነት ዋስትና ሠጣቸው፡፡ ለሙስሊሞች መስጅድ የሚሆን ቦታም መረጠ፡፡

አቡ ዑበይዳ አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና ለዘመቻ ወደ ሂምስ በማምራት ላይ እያለ የበዕለበካ ሰዎች ወደሱ በመውጣት የሰላም ስምምነት በመካከላቸው ይኖር ዘንድ ተደራደሩ፡፡ እሱም በሰላም እስከኖሩ ድረስ ነፍሦቻቸው፣ ሀብት ንብራቶቻቸውና የፀሎት ቤታዎቻቸው ደህንነት የተጠበቀ መሆኑን በመግለፅ እንዲህ በማለት ፃፉላቸው፡፡ ‹ቢስሚላህ ረህማኒ ረሂም፡፡ ይህ የደህንነት ዋስትና ፅሁፍ ለእገሌ የእገሌ ልጅና በበዕለበካ ለሚገኙ የሮማውያን፣ ፋርሣውያንና  ዐረቦች የተሠጠ ሲሆን በከተማ ውስጥ ከከተማ ውጭም ሆነ ሌሎች ርቀው የሚገኙ ሀብት ንብረቶቻቸው፣ የፀሎት ቦታዎቻቸው፣ ቤቶቻቸው፣ ወፍጮዎችቻውና ነፍሦቻቸውም ጭምር የደህንነት ዋስትና ተሠጥቷቸዋል፡፡ ሮማውያን በመካከላቸውና በአሥራ አምስት ማይል ርቀት መካከል የሚገኘውን አካባቢ መጠበቅ የሚኖርባቸው ሲሆን የዓሚራን መንደር መግባት የለባቸውም፡፡ የረቢዕ እና የጁማዳ አልኡላ ወር የተጠናቀቀ እንደሆን ወደፈለጉበት መሄድ ይችላሉ፡፡ ከነሱ ውስጥ የሠለመ ለኛ ያለን ነገርም ሆነ በኛ ላይ ያለ (ከኛ የሚጠበቀው ግዴታ) ሁሉ አለበት፡፡ ነጋዴዎቻቸው ከኛ ጋር ስምምነት ወዳላቸው ማንኛውም አገር መሄድ የሚችሉ ሲሆን ነዋሪ የሆነ ማንኛውም የነሱ ሰው ግብር የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ አላህ ሆይ! ምስክር ሁን፡፡ ከምስክርነትም አላህ በቃ፡፡› (12)

ስምምነቶቹ በከፊል ይህን የሚመስሉ የነበረ ሲሆን በውስጣቸውም ለማንኛውም የሰው ልጅ ሁሉ ሙሉ መብቱንና ነፃነቱን የሚያጎናፅፉ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክኒያት ሌሎች ያልተከፈቱ የሻም ሀገሮች ድል አድራጊውን የሙስሊሙን ጦር በመደገፍ ከሮማውያን የቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ የሂምስ ሰዎች ደግሞ የሂረቅልን መሽሽ ባወቁ ጊዜ ሙስሊሞችን ለመቀበል በነቂስ ወጡ፡፡ ምግብና ስንቅም ይዘው ተቀበሏቸው፡፡ ከነሱ ጋርም ጥሩ ግንኙነትን ፈለጉ፡፡ ሙስሊሞቹም ለነፍሦቻቸው፣ ለከተማቸው ህንፃዎች፣ ለቤተ ክርስቲያኖቻቸውና ወፍጮዎቻቸው ሁሉ ዋስትና ሰጧቸው፡፡ የላዚቂያ ሰዎች ጥለው የሸሹትን አራት የዩሀንስ ቤተክርስቲያናትን ግን መስጊድ ለማድረግ ከሌሎች ለዩ፡፡ ነገርግን የሸሹት ሰዎች የሙስሊሞችን ይቅር ባይነት በተረዱ ጊዜ ወደ መሬቶቻቸው ለመመለስ የደህንነት ዋስትና እንዲሠጣቸው ጠየቁ፡፡ ሙስሊሞቹም ተቀበሏቸው፡፡ ቤተክርስቲያኖቻቸውንም ተውላቸው፡፡

ሙስሊሞች ሂረቅል ሂምስን ለማስመለስ ጦር እያደራጀ መሆኑን በሰሙ ጊዜ ከሂምስ ሰዎች ተቀብለው የነበረውን የግብር ክፍያ በመመለስ ‹እናንተ በዚህ ሁኔታ ላይ እያላችሁ እያየን እናንተን ከመርዳትና ለመከላከል መዘነጋታችን ትክክል አልነበረም፡፡› አሏቸው፡፡ የሂምስ ሰዎችም ‹የናንተ አስተዳዳሪነትና ፍትሃዊነት ከነበርንበት የግፍ እና የጭቆና ዘመን የተሻለልን ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ የሂረቅልን ጦር ከናንተ ሰዎች ጋር በመሆን ሂምስ እንዳይደርስ እንከላከላለን፤ አይሁዶችንም ከኛ ጋር እንዲሆኑ እናነሣሣለን፡፡ በተውራት ይሁንብን አንድም የሂረቅል ገዥ የሂምስ ከተማ አይገባም እስክናሸንፈው ድረስ የተከላከልን ቢሆን እንጂ፡፡› በማለት  የከተማዋን በሮች ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ጥበቃቸውን አጠናከሩ፡፡ በሌሎችም ከአይሁዶችና ክርስቲያኖች ጋር ስምምነት በተደረሰባቸው ከተሞች ሁሉ ተመሣሣይ ሁኔታ ተደረገ፡፡› (13)

በተለይም የአዲራ ሰዎች ለሙስሊሙ ጦር መንገድ ሁሉ አልጋ ባልጋ እንዲሆን ይተባበሩ ነበር፡፡ ኻሊድ ኢብኑ አልወሊድ በአንዲት መንደር በኩል ሲያልፉ በሰላም የተቀበሉት ሲሆን ይህም ስምምነታቸው አንድ እጅግ ጠንካራ የሆነ ምሽግ ይከፍት ዘንድ አግዞታል፡፡ እሱም ለሰሩት መልካም ነገር ውለታቸውን መልሶላቸዋል፡፡ ግብር እንዲቀነስላቸውም ደብዳቤ ፅፏል፡፡

ሙስሊሞች ከሀገሬው ህዝብ ጋር የፈፀሙት ይህ ስምምነት በምርኮ ሥር ወድቆ በነበረ አንድ ምርኮኛ አማካይነት ለሂረቅል ደረሰው፡፡ ‹እስቲ ስለነዚያ ሰዎች ሁኔታ ንገረኝ?› አለው ሂረቅል፡፡ ሰውዬውም ‹እንደምታያቸው አድርጌ ልንገርህ! ሰዎቹ ቀን ቀን ድንቅ ፈረሠኞች ለሊት ደግሞ በፀሎት አዳሪዎች ናቸው፡፡ በራሣቸው ገንዘብ እንጂ ዘርፈው የሚበሉ አይደሉም፡፡ ወደ ሀገራትም ሲገቡ በሠላም እንጂ አይገቡም፡፡ የተዋጓቸው ሰዎች ወደነርሱ እስካልመጡ ድረስ አይነኳቸውም፡፡› አለው፡፡ ሂረቅልም ‹ያልከው እውነት ከሆነ በሁለት እግሮቼ ሥር ያለውን ሁሉ (ግዛቴን) ይወርሣሉ፡፡› አለው፡፡ (14)

የቁድስ መከፈት ከኸሊፋው ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ቦታው ላይ መገኘት ጋር የተገጣጠመ ነበር፡፡ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ያኔ የሙስሊሞችን ጦር ሁኔታ ለመጎብኘት ወደ ሻም ሀገር መጥተው ነበር፡፡ ከደማስቆ ምድር ከመጡ በኋላም የመዲናይቱ ቁድስን ቁልፍ ለመረከብ ወደዚያው አመሩ፡፡ በመንገድ ላይ ከክርስቲያን ወገን የሆኑና የቆዳ በሽታ ያገኛቸው ሰዎችን አግኝተው የነበረ ሲሆን ለነኚህ ሰዎችም ከሰደቃ ገንዘብ እንዲሠጣቸውና ለኑሮአቸው የሚያስፈልጋቸው የሆነ ቀለብ እንዲታደላቸው ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡ (15)

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በሚያልፉባቸው የሻም ከተሞች ሁሉ አቀባበል ይደረግላቸው ነበር፡፡ ሙቅሊሦች (የሀገር መሪዎች ሲመጡ አቀባበሉን ለማድመቅ ሰይፍ እና ዘንባባ ይዘው የሚጫወቱና የሚያዝናኑ ሰዎች) ለአቀባበሉ ይወጡ የነበረ ሲሆን ዑመር እነኚህን ሰዎች ‹ከልክሏቸው› አሉ፡፡ አቡ ዑበይዳ ‹ ይህ እኮ የዐጅም አመት ነው (አሊያም በተመሣሣይ ቃል ተናገረ፡፡) አንተ የከለከልካቸው እንደሆነ ውስጣቸው አንተ የነሱን ቃልኪዳን ያፈረስክ እንደሆነ ይሠማቸዋል፡፡› በማለት ሁኔታውን ለኸሊፋው አስረዳው፡፡ ዑመርም ‹ እንግዲያውስ ተውዋቸው፡፡ የዑመር ሰዎች አቡ ዑበይዳን ለመታዘዝ ዝግጁ ናቸው፡፡› አሉ፡፡ (16)

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እዚሁ እንዳሉ ቀድሞ የገሣን ንጉስ የነበረ ጀብለህ ኢብኑ አልብሀም የሚባል ሰው አንድ ተራ ከሆነ ሰው ጋር ተሰዳድቦ ዐይኑን በጥፊ ይመታዋል፡፡ ሰውዬው ሁኔታውን ለኸሊፋው ዑመር አቤት አለ፡፡ ዑመርም አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና የሰውዬውን አቤቱታ በማዳመጥ በተመሣሣይ መልኩ ሰውዬው ንጉሱን እንዲመታ ይፈርዳሉ፡፡ ንጉሱም ‹የሱና የኔ ዐይን አንድ ነው እንዴ!› በማለት ለማፌዝ ሞከረ፡፡ በማህበረሰባቸው መካከል ፍትህን ለማስፈን የወጡት ታላቁ ዑመር ግን አንደኛው ሰው ንጉስ ሁለተኛው ተራ ሰው ቢሆኑም እንኳ ጉዳዩን ከማስፈፀም ወደኋላ አላሉም፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ቁድስን ለቀው ከመመለሳቸው በፊትም ለነዋሪዎቿ እንዲህ የሚል ፅሁፍ ትተው ነበር ‹ቢስሚላህ ረህማኒ ረሂም፡፡ ይህ የአላህ ባሪያና የምዕመናን መሪ የሆነው ዑመር ለኢልያእ ሰዎች የሠጠው የደህንነት ዋስትና ነው፡፡ ለነፍሦቻቸው፣ ለሀብት ንብረቶቻቸው፣ ለቤተክርስቲያኖቻቸው፣ ለመስቀሎቻቸው፣ ለታመመውም ሆነ በጤና ላለው እንዲሁም በየትኛውም የአመላከት መንገድ ላይ ላለ ሁሉ የሠጠው ነው፡፡ ቤተክርስቲያኖችቻቸው በሀይል ላይያዙ፣ ላይፈርሱ፣ ክብራቸው ለይደፈር፣ መስቀሎቻቸውም ላይነኩ፣ ከሀብት ንብረቶቻቸውም አንዳች ነገር ላይነካ፣ በሃይማኖታቸው መገደድ እንደሌለባቸው፣ ከነርሱ አንድም ሰው ጉዳት እንዳይደርስበትና በኢልያእም ከነሱ ጋር አንድም አይሁድ እንዳይኖር የተሠጠ ዋስትና ነው፡፡  የሌሎች ከተሞች ሰዎች ግብር እንደሚከፍሉት ሁሉ የኢልያእ ሰዎችም መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሮማውያን ወታደሮችና በስርቆት የተሠማሩ ሰዎች ከከተማዋ እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ በሰላም የወጣ ሰውም ደህንነቱ የተጠበቀበት ቦታ እስኪደርስ ድረስ እሱም ሆነ ንብረቱ እንደማይነኩ ዋስትና አለው፡፡ ከነሱ ጋር በሠላም የኖረም ደህንነቱ ይጠበቅለታል፡፡ በሱ ላይም በኢልያእ ሰዎች ላይ የተጣለው ግብር ይጣልበታል፡፡ ከኢልያእ ሰዎች እራሱንና ንብረቱን ይዞ ከሮማውያን ሰዎች ጋር መሄድ የፈለገ ሰው መሄድ እንደሚችልና መስቀሉንም ሆነ የፈለገውን ነገር መሸጥ መለወጥ እንደሚችል ይዞም ቢሄድ ሙሉ የደህንነት ዋስትና እንዳለው ነው፡፡ ከነሱ ውስጥም ኢልያእ መቀመጥ የፈለገ መቀመጥ እንደሚችልና የኢልያእ ሰዎች የሚከፍሉት ግብር እንደሚጠበቅበት ነው፡፡ የፈለገ ሰው ከሮማውያኑ ጋር መሄድ፣ የፈለገ ደግሞ ወደ ቤተሰቡ መመለስ ይችላል፡፡ ምርት እስካልተሰበሰበ ድረስ ከነሱ ምንም እንዲከፍሉ አይጠበቅም፡፡ ግብር የከፈሉ እንደሆነ ደግሞ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የተካተተው የአላህ፣  የሙስሊም መሪዎችና የአማኞች ጥበቃ እንዳለው ነው፡፡ › ይላል፡፡ (17)

ቤይተል መቅዲስንና የተቀሩትን የፈለስጢን ምድር አካባቢዎች የመክፈቱ ዘመቻ ካበቃ በኋላ ዐምር ኢብኑል ዓስ ግብፅን ለመክፈት ይፈቅዱለት ዘንድ ኸሊፋውን ጠየቀ፡፡ ዑመርም ፈቀዱለት፡፡ ዐምርም ወደዚው አመራ፡፡ ሙስሊሞች በአንድ ጎራ ሆነው ከሮማውያንና ከነሱ መኖር ተጠቃሚ ከሆኑ ጥቂት ግብፃውያን ጋር ከተደረጉ የተወሰኑ ጦርነቶች በኋላ ግብፅን ከሮማውያኑ አገዛዝ ሙሉ ለሙሉ ነፃ የማውጣቱ ሥራ ተጠናቀቀ፡፡

ዐምርም ለአጭር ጊዜ ጉብኝት ወደ አሌክሣንደሪያ ሄደ፡፡ የአሌክሣንደሪያው መሪም እንዲህ በማለት ለዐምር ፃፈለት፡፡ ‹እናንተ ዐረቦች ሆይ! እኔ ግብር ስከፍል የነበረው ከናንተ ይልቅ እጅግ እጠላው ለነበረው የሮማውያንና ፋርሣውያን አገዛዝ ነው፡፡ አሁን ግብር እንድከፍል የፈለግክ እንደሆነ የወሰድከውን ምርኮ ሁሉ ልትመልስልኝ ይገባል፡፡› ዓምርም እንዲህ በማለት መለሠለት ‹እኔ ከሱ ሣልማከር በራሴ ነገሮችን ማስኬድ የማልችል አሚር/መሪ/ አለኝ፡፡ አንተ ባቀረብከው ሀሳብ ላይ ለሱ ደብዳቤ እስክጽፍ ጠብቀኝ፡፡ እስከዚያው ፍላጎትህ ከሆነ እኔ አልነካህም አንተም እንዳትነካኝ፡፡ እሱም ጉዳዩን የተቀበለ እንደሆነ እኔም እቀበልሃለሁ። ከዚህ ውጭ የሚያዘኝ እንደሆነም ትእዛዙን እፈፅማለሁ፡፡›አለው፡፡ ሰውዬውም ‹ጥሩ› በማለት ሀሳቡን ተቀበለ፡፡

ከዚያም ዓምር ኢብኑል ዓስ ይህንኑ ጉዳይ የሚገልፅ ደብዳቤ ለኸሊፋ ዑመር ኢብኑ አልኸጧብ ፃፈ፡፡ ዑመርም ለዐምር እንዲህ በማለት መለሱለት

‹የአሌክሣንደሪያው መሪ ያቀረበውን ሀሣብ የሚገልፀው ደብዳቤህ ደርሦኛል፡፡ ነፍሴን በያዘው ጌታ ይሁንብኝ ለኛና ከኛ በኋላ ለሚመጡ ሙስሊሞች ሁሉ የሚከፈል ግብር አሁኑኑ ተከፋፍሎ ከሚያልቀው ምርኮ ይበልጥ ለኛ የተሻለ ነው፡፡ ለአሌክሣንደሪያው ሰውዬህ ግብር እንዲከፍልህ ሀሳቡን ተቀበል፡፡ በእጆችህ ያሉትን ምርኮኞች ደግሞ ከእስልምና እና ከቀደምት ሃይማኖታቸው መካከል አማርጣቸው፡፡ እስልምናን የመረጠ ከሙስሊሞች ነው፡፡ ለሙስሊሞች ያለ ነገር ለነሱ አለ፡፡ በሙስሊሞችም ላይ የተደነገገ ነገር በነሱም ላይ አለ፡፡ የወገኖቹን እምነት የመረጠ ደግሞ በእምነቱ ተከታዮች ላይ የሚጣለው የግብር ክፍያ ይጣልበታል፡፡ ከነሱ ምርኮ መካከል ወደ ዐረብ ሀገር ሄዶ መካ፣ መዲና አሊያም የመን የደረሠን ሰው እኛ መመለስ አይጠበቅብንም፡፡ በማንችለው ጉዳይ ላይ ልንደራደረው አንችልምና፡፡›

ዐምር ወደ አሌክሣንደሪው ሰውዬ የምእመናን መሪ ያሉትን ነገር በማሳወቅ ላኩለት፡፡ ሰውዬውም ‹ተስማምቻለሁ፡፡› አለ፡፡

ይህ በርግጥም ሙስሊሞች በሚከፍቷቸው ሀገራት ላይ የሚጣሉ የግብር ክፍያዎች ለምን እንደሆኑ ጥሩ ማሣያ ነው፡፡ በቀደምትም ሆነ በዛሬው ማህበረሰብ ውስጥ የግብር ክፍያ ያለ ነው፡፡ ማህበረሰቡም ቢሆን ጥቅሙ ለራሱ ነውና መቃወም አይችልም፡፡ በጊዜው አንድ ሀገር ከመከፈቱ በፊት እንኳን በነበሩት መንግስታት አማካይነት ግብር ይሰበሰብ ነበር፡፡ ኢስላም ሲመጣ ግን ይህንን አሠራር በአዲስ መልክ አደራጅቶ መራው፡፡ የክፍያ ዓይነቱ እየበዛ ሲሄድም መክፈል በሚችሉ ሀብታሞች ላይ ብቻ የተደነገገ ሆነ፡፡ ክፍያው ድሆችን፣ ልዩ እገዛ የሚፈልጉ የማህበረሰቡ ክፍሎችን፣ የሃይማኖት ሰዎችን፣ በዘመቻ ላይ የተሠማሩና ለመንግስት የሚያገለግሉ እንዲሁም መንገድ የሚመሩ ሰዎችን ነፃ ያደረገ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሴቶች፣ ህፃናት፣ በሽተኞችና ለአምልኮ የተገለሉ ሰዎችም ነፃ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ይህን አሠራር ግን ከኢስላም በስተቀር አንድም ሥርት የማይቀበለው ሲሆን በህገ መንግስቱም ውስጥ እያንዳንዱ ሰው በሚችለው መጠን መክፈል እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ዛሬ ዛሬ በሙስሊሙ ዓለም ላይ የነገሱት መሪዎች ከክርስቲያኖች ጋር ለመቀራረብ ሲባል የግብር ክፍያውን አንስተናል ይላሉ፡፡ ይህ ግን ቃል ማንሣት ብቻ ነው፡፡ ምክኒያቱም ዛሬ ህዝቦች ሁሉ ሙስሊሞቹም ሆኑ ያልሆኑት ግብርን በእጥፍ ድርብ እየከፈሉ ነውና፡፡ ይህም የአንድን ሰው አጠቃላይ ገቢ የሚገዛ የሚሸጠውን ሁሉ ባጠቃለለ መልኩ ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገራት በመሪው መንግስት በነፃ ሊቀርቡ ይገባቸው የነበሩ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የስልክና ሌሎችም አገልግሎቶች ሌላው ቀርቶ አንድ ዘካ የሚገባው ድሃን ጨምሮ አጠቃላይ ነዋሪው የሚከፍል ሲሆን ይህም ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የእጥፍ ድርብ ወጭዎች ባለእዳ አድርጎታል፡፡

ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በ15ኛው አ.ሂ. ከሻም ሀገር ሲመለሱ ለሙስሊሞች መተዳደሪያ የሚሆን ደሞዝ ደነገጉ፡፡ የሰዎች ሁሉ ስምና የሥራ ክፍፍላቸውን፣ ዕድሜያቸውንና አድራሻቸውን የያዘ ሰነድም እንዲዘጋጁ አደረጉ፡፡

ዐሊይ ብኑ አቢ ጧሊብ እና ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ ‹በራስህ ጀምር (የሀገሪቱ መሪ ነህና ማለታቸው ነው፡፡) እሱም ‹አይሆንም ባይሆን በአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም አጎት ከዚያም ወደርሣቸው ቀረብ በሚሉት ነው የምጀምረው፡፡› አላቸው፡፡ (18)

የዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ስጦታ ህጻናት ልጆችንም ጭምር ያካተተ ነበር፡፡ ለያንዳንዱ ልጅ አሊያም ህፃን መቶ ድርሃም መድበውለታል፡፡ ከዚያም ስልሣ ድሆችን ሰበሰቡና ምግብ አበሏቸው፡፡ የበሉትን ምግብ ሲያሰሉ ከሁለት ስልቻ የወጣ መሆኑን ተገነዘቡ፡፡ በመሆኑም ለያንዳንዱ ሰውና ለቤተሰቡ በየወሩ ሁለት ስልቻ እንዲመደብ አደረጉ፡፡ ዑመር ከመሞታቸው በፊት እንዲህ ብለው ነበር ‹ስጦታውን አራት አራት ሺህ ለማድረግ ፈልጌ ነበር፡፡ አንድ ሺህ አንድ ሰው ለቤተሰቡ ያደርጋል፡፡ አንዱን ሺህ ደግሞ ለራሱ ይሰንቅበታል፡፡ አንዱን ሺህ ደግሞ ለዘመቻ ሲወጣ የሚዘጋጅበት ሲሆን የተቀረው አንድ ሺህ ደግሞ የሚመፀውተው ነው፡፡› አሉ፡፡ ነገርግን ይህ ያሰቡት ነገር ሣይመቻችላቸው ህይወታቸው አለፈች፡፡

የተገኘውንም ነገር በመጀመሪያ ለሙጃሂዶችና ለምርኮኞቻቸው የሚሠጡ ሲሆን ቀጥሎም ሌሎችን በሚያጠቃልል መልኩ አዳርሰዋል፡፡ አንድ ቀን በጉዞ ላይ ሣሉ በአንድ በር ላይ አንድ አዛውንት ‹በእድሜ የገፋሁ ሽማግሌ ነኝ ዐይን ያጣሁ፡፡› በማለት ሲለምን ሰሙት፡፡ እርሣቸውም ‹ከየትኛው የመፅሃፉ ሰዎች ነህ?› በማለት ጠየቁት፡፡ ሽማግሌውም ‹አይሁድ ነኝ፡፡› አላቸው ‹ምንድነው ለልመና የዳረገህ?› አሉት፡፡ ‹ግብር፣ ችግር እና እድሜ ናቸው፡፡› አላቸው፡፡ ዑመርም የሰውዬውን እጅ በመያዝ ወደቤት ወስደው የሆነ ነገር ከሰጡት በኋላ ወደ የሙስሊሞች ንብረት ክፍል ጠባቂ በመላክ ‹ይህን ሰው ተመልከት እስቲ ወላሂ ከሱ አንፃር ትክክል አልሠራንም፡፡ እስኪያረጅ በልተነው አሁን በጃጀ ጊዜ እንተወዋለን፡፡  ሠደቃ የሚገባው ለድሆች እና ለድሃ ድሃ/ሚስኪኖች/ ነው። ድሆች ሲባል ደግሞ ሙስሊሞች ሲሆኑ ይህ ደግሞ ከመፅሃፉ ሰዎች መካከል የሆነ የድሃ ድሃ ነው፡፡ ግብሩን ሁሉ አውርዱለት፡፡› አሉ፡፡

የፅሁፉ ምንጮች

[1].   ታሪኽ አል መዲና ቅ.2 ገፅ 665 ፣ ዐስር አል ኸሊፈተ ራሺዳ ሊ ዶ/ር አክረም ዲያእ አልዑመሪ ገፅ 55

[2].  አል ከማል ፊታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 397

[3].  አል ከማል ፊታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 397

[4].  አል ከማል ፊታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 398

[5].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 355

[6]. አል ከማል ፊታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 394

[7].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 112

[8].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 639

[9].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 98

[10].  አል ከማል ፊታሪኽ ቅ. 1 ገፅ 398

[11].  ፉቱህ አል ቡልዳን ገፅ 162

[12].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 445

[13].  ፉቱህ አል ቡልዳን ገፅ 153

[14].  አል አምዋል ሊልቃሲም ቢን ሰላም ቅ. 1 ገፅ 405

[15].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 105

[16].  ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 3 ገፅ 109

[17]. ፉቱህ አል ቡልዳን ገፅ 124

[18]. አል ሙንተዘም ቅ. 1 ገፅ 486

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here