በክፍል አንዱ ቅኝታችን አንዳንድ ሙስሊሞች ኡሣማ ኢቡኑ ዘይድ ከእድሜው ገና ወጣት በመሆኑ ሙስሊሞች ከሚገኙበት ሁኔታና ከተልእኮው ከባድነት አንፃር ሩሞችን /ቢዛንታይኖችን/ የማንበርከኩ ሀላፊነት ሊከብደው ይችላል የሚል አቋም በመያዝ ወደ ኸሊፋው አቡበክር በዑመር በኩል ደብዳቤ ልከው እንደነበርና አቡበክርም አስተያየቱን እንዳልተቀበሉ ዑመርንም “የአላህ መልእክተኛ ለዚህ ሀላፊነት የመረጡትን ሰው እኔ እንዴት አወርዳለሁ” በማለት እንደተቆጡ አይተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሹራ /መመካከር/ ለሙስሊሞች እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነገር ግን የአላህንና የመልእክተኛውን ግልጽ ትእዛዛት በማስፈፀሙ በኩል ግን መደራደር፣ ከአቋም መለሣለስም ሆነ ሹራ እንደማያስፈልግ ተገንዝበናል። ሹራ ወደ ትክክለኛው ሀሣብና እይታ ለመድረስ የሚያስችል የምክክር ተግባር ነውና አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም። ሆኖም ግን እውቀቱ ሁሉን ነገር ካካበበው አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እና በወሕይ /መለኮታዊ ራእይ/ መልእክት እንጂ ከማይናገሩት ነቢይ የበለጠ ምልከታ ስለሌለ ሁሌም ለነርሱ ግልጽ ትእዛዛት ቅድሚያ መስጠት ይገባል።
ጀምረነው የነበረውን ሀዲስ እንጨርስ – ኡሣማ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ከመሞታቸው በፊት አዘጋጅተውት የነበረውን ጦር ይዞ በሻም/ሦሪያ/ በኩል አድርጎ ወደ ሩም/ ቢዛንታይን/ ወጣ። ከመነሣቱ በፊት አቡበክር ረዲየሏሁ ዐንሁ ኡሣማን ‹የአላህ ነቢይ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ያዘዙህን ሁሉ ፈፅም። ቀዷዓህ በሚባለው ሀገር ጀምር፤ ከዚያም ወደ ኣቢል አምራ። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ካዘዙህ ነገር ከአንዱም ችላ አትበል፤ እርሣቸው በህይወት በነበሩበተረ ዘመን ከመልካም ሥራ ወደ ኋላ ቀርቼ ነበረ ብለህ አትቻኮል። (1) በማለት መከሩት።
በተለምዶ አንድ አዲስ መሪ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በማህበረሰቡ ዘንድ ዝናውን ከፍ ለማድረግና የሱ አስተዋፅኦ ጎልቶ ይታይ ዘንድ ደፋ ቀና ማለቱና መጓጓቱ አይቀርም። አቡበክር (አስ ስዲቅ) ግን ከዚህ የተለየ ነገር ነበር ያደረጉት። ለኡሣማ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ያዘዙበትንና ከመሞታቸው በፊት ለጦሩ ያስቀመጡትን ንድፍ ተከትሎ እንዲሄድ ብቻ ነበር ሀላፊነት የሠጡት። የነቢዩን ትእዛዝ ለመሸራረፍ ምክኒያቶችን አልደረደሩም። ‹አሁን ሁኔታዎች ተቀይረዋል፤ ነገሮችም መልካቸውን ለውጠዋልና እንዲህ እንዲያ አድርግ› አላሉትም። ለኢስላም የሚሠሩ ሰዎች በነቢያዊው መንገድ መጓዝ የፈለጉ እንደሆነ ከዚህ የአቡበክር አስዲቅ አሠራር ትልቅ ትምህርት መውሰድ ይኖርባቸዋል።
አስ ስዲቅ ኡሣማን መክረው ከጨረሱ በኋላ ኡሣማ በፈረስ ላይ ሆኖ እርሣቸው በእግር እየተራመዱ አብረውት የጦሩ መነሻ ወደሆነው ካምፕ ድረስ ሊሸኙት መጡ። ኡሣማም በዚህን ጊዜ ሁኔታው ስለከበደው ‹አንቱ የአላህ መልእክተኛ ኸሊፋ /ምትክ/ ሆይ! ወይ ይሣፈራሉ ካልሆነ መውረዴ ነው።› አላቸው። እርሣቸውም ‹ወላሂ አትወርድም አልሣፈርምም። እስቲ ለአፍታም ቢሆን በአላህ መንገድ እግሬን አቧራ ይንካት። በአላህ መንገድ ለሚዘምት ሰው በያንዳንዱ እርምጃው ሰባት መቶ መልካም ነገር ይፃፍለታል፤ ሰባት መቶ ደረጃዎችን ከፍ እንዲል ይደረጋል፤ ሰባት መቶ ሀጢኣትም ይሠረዝለታል ።› አሉት።
ላንዳፍታ ይህን ክስተት በዐይነ ህሊናችን እናምጣው። አንድ ታላቅ መሪ ተዋጊዎቹ በፈረስ ላይ ሆነው እርሱ በእግር ሆኖ ፊትን በሚሸፍን አቧራ ተከቦ በጦሩ መሃል እየተንቀሣቀሠ ወደፊት በመጭው ዓለም ስለሚጠብቃቸው ምንዳ ሲዘረዝርላቸው የመዋጋት ወኔያቸው ምን ያህል ከፍ እንደሚል!። አቡበክር ኡሣማን ሸኝተው ለመመለስ ባሰቡ ጊዜ ለኡሣማ ‹በአንድ ነገር የምታዘኝ ከሆን ለመታዘዝ ዝግጁ ነኝ።› (3) አሉት። ኡሳማ ይህን ነገር ከአቡበክር ሲሰሙ በራስ የመተማመናቸው ላይ የበለጠ መተማመን ተሠማቸው። በኡሣማ የእድሜ ክልል ውስጥ ወጣቶች ይህንን በሠሙ ጊዜ የኡሣማን ትእዛዝ ለመፈፀም ለማንገራገርም ሆነ በሱ ላይ ከፍ ከፍ የማለት ስሜትን ጨርሰው ጣሉ ።
ዛሬ ሠልጣኞች በሚማሩባቸው ወታደራዊ ኮሌጆች አንድ የጦር መሪን በመታዘዝና መመሪያዎቹንና መንገዱን ከመከተል አንፃር ትልቅ መርህ አላቸው። ነገር ግን እነዚህ ጠቋሚ መመሪያዎች በሙሉ አቡበክር አስስዲቅ በአጭር ጊዜ ከሠጡት ሥልጠና በላይ የታለመለትን ግብ የሚያደርሱ አይደሉም።
ኡሣማ ጦራቸውን ይዘው ከተንቀሣቀሱ በኋላ ስለ መርተዶች /ከእስልምና የወጡ ሰዎች/ የመጀመሪያ አስጠንቃቂ የሆነው ዑየይናህ ኢብኑ ሂስን ከአቅረዕ ኢብኑ ሃቢስ ጋር ሆኖ ወደ መዲና መጣ። ታላላቅ የዐረብ ሰዎችም አብረውት ነበሩ። ለአቡበክርም እንዲህም አለ ‹ትተን ከመጣነው አብዛኛው ሰው ከእስልምና ወጥቷል። ለአላህ መልእክተኛ ሲሠጡ የነበረውንም (ዘካ) የመስጠት ፍላጎት በውስጣቸው የለም። ለኛ የሆነ ነገር ካደረጋችሁልን የነሱን ነገር እኛ እንበቃላችኋለን›። (4)
ይህ እንግዲህ ‹የአላህን መልእክተኛ ትእዛዝ ከማስፈፀም አንፃር መሄዱ ግድ ነው።› ብለው በአቋማቸው ለፀኑበት የኡሣማ ጦር ከሄደ በኋላ አቡበክርን የገጠማቸው የመጀመሪያው ፈተና ነበር። ይህም በሣቸውና ሀሣባቸውን በሚቃወሙ (በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከመዲና ወጥተን መዋጋት የለብንም) በሚሉ ሰዎች መካከል ከፍተኛ የሆነ ክፍፍልንና ጭቅጭቅን ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ ነበር። የሀሣባቸው ተቃዋሚዎች ለአቡበክር እንዲህ እስከማለት የደረሱበት ሁኔታ ነበር። ‹አቅረዕ እና ዑየይናህን ደስ የሚሠኛቸውን ያህል አብላቸው። እነሱም የኡሣማ ጦር ከተላከበት ተመልሦ ተጨማሪ ጥንካሬ እስኪናገኝ ድረስ አነኚህን ሰዎች ለመከላከል ይጠቅሙናል። እኛ ዛሬ በብዙዎች ውስጥ የቀረን በቁጥር አናሦችቹ ነን።› (5)
በርግጥም ሁኔታው ሲታይ ለክፍፍል የሚያበቃ ነበር። ነገር ግን የተፈራው ነገር አልተከሠተም። ሌላው ቀርቶ አንድም የመከፋፈል ምልክት እንኳን አልታየም። ለምን ቢባል ሰሃቦቹ አቡበክር ሀሣባቸውን ባይቀበሉም እንኳ የአላህ መልእክተኛ መንገድ ተከታይ እንጂ የስሜታቸው ተከታይና በጭፍን ‹የኔ ሀሣብ ብቻ ..› የሚሉ ግብዝ እንዳልሆኑ ያውቃሉ። ይህ አንደኛው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዙሪያቸው የነበሩ ሰሃቦች ለእስልምና ጥቅም ሲሉ ከአመለካከታቸው ለመንሸራተት ፈቃደኛ የሆኑ ቅኖች ነበሩ። አቡበክርም ቢሆኑ የነቢዩን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መንገድ ለማስፈፀም የፀና አቋምና ሙሉ ጉጉት ያላቸው ሰው እንጂ አምባገነንና በግድም ህዝቡ ላይ የተጫኑ ጨቋኝ መሪ አይደሉም። ባይሆን ለስላሣ ይቅር ባይና ገራገር ሰው ነበሩ።
ወደሣቸው መጥተው ለነበሩ ሰሃቦች ‹ከዚህ ውጭ ምን ይታያችኋል? (ማለትም እነሱ ካቀረቡት ሀሣብ ውጭ) ያሉትንና እነሱም ‹ሌላ አይታየንም አሉ› ብለው የመለሱበትን ሁኔታ ስናይ ይህንኑ እንረዳለን። እርሣቸውም ‹ነቢያችሁ በአደራነት ካስተላላፉላችሁ ነገር ውስጥ በአንድ ጉዳይ ላይ እሣቸው ያልተናገሩት ካለ በቁርአንም ስለሁኔታው ያልተገለፀ እንደሆነ በዚያ ነገር ላይ ምክክር ማድረግ እንዳለብን ታውቃላችሁ። እኔም ከናንተ መካከል አንዱ ነኝ። እናንተ የምትጠቁሙኝንም ነገር እየተጠባበቅኩ ነው። እርግጠኛ ነኝ አላህ በጥመት ነገር ላይ አንድ አቋም አያስይዛችሁም። በትክክለኛው ነገር ላይ አንድ አይነት አቋም ይኖረናል ብዬ አስባለሁ። እኔም የደረስንበትን ውሣኔ ወደ ጠላቶቻችን አደርሣለሁ። ከነሱም የሻ ሰው ይመን የሻውም ይካድ። በኢስላም በላይ የምትመርጡት ሊኖር አይገባም። እሣቸው ጠላቶቻቸውን እንደታገሉ ሁሉ እኛም እንታገላቸዋለን ..። የዑየይናህ እና ሌሎችም ወዳናንተ መምጣት ደግሞ ይህ ጉዳይ ከሱ ድብቅ እንዳልሆነ ዑየይናህም አሣምሮ ያውቀዋል። ሀሣቡን ወደደው፤ ይዞትም ወደዚህ መጣ። (6) የሰይፍ መዓት ቢታያቸው ኖሮ የመጡበትን ጉዳይ ይዘው በተመለሱ አሊያም ደግሞ ሰይፍ እሣት ሆኖባቸው በጨረሣቸው። በከለከሉን ነገርና በተከተሉት ክህደት ምክኒያት ብቻ ነው የተጋደልናቸው። ሰሃቦችም ‹ያንተ ሀሣብ ከሁላችንም ይበልጣል የኛ ሀሣብ ያንተን ይከተላል። (የኛን ትተን ያንተን ተቀብለናል ።)› አሏቸው። (7)
እዚህ ላይ የአቡበክርን ሁኔታ እናስተውል። የኡሣማን ጦር በመላኩ ላይ የአላህ መልእክተኛ ትእዛዝ ነበረበትና ጉዳዩን ለድርድር አላቀረቡትም። ነገር ግን ሌላ ጉዳይ ሲሆን ለምክክር ዘግጁ እንደሆኑና ለነሱ የውሣኔ ሀሣብም እንደሚገዙ አስታወቁ። እራሣቸውንም እንደ አንድ ከነሱ የሆነ ሰውና ከስህተትም የጠሩ እንዳልሆኑ በማሳወቅ ሀሣባቸውንም እንዲመክሩበት እንዳቀረቡ አስታወቁ። በመጨረሻ ግን እነኚህ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ቀልባቸውን ለአላህ ያጠሩ እንደሆነ ፈፅሞ በጥመት ላይ አንድ አቋም እንደማይዙ አስገነዘቡ።
አቡበክር አስ ስዲቅ ከዚህ ውሣኔ በኋላ ብዙም ሣይቆዩ በመዲና ላይ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል አንድ በአንድ ስልት ቀየሱ። በመግቢያ በሮቿ ላይ ጠባቂዎችን አስቀመጡ። ዐሊ፣ ዙበይር፣ ጦልሃ እና ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ ለዚህ ጉዳይ ተመደቡ። መንገዱንም በንቃት እንዲጠብቁም ታዘዙ። በተጨማሪም በመዲና ውስጥም አጠቃላይ የሆነ አዋጅ በማወጅ ሁሉም ሰው ወደ መስጊድ እንዲመጣ አደረጉ። እንዲህም አሏቸው ‹ምድር በከሃዲን ተሞልታለች። የነሱ ልኡካን (የነ ዑየይናህ) በቁጥር አናሣ መሆናችሁን ተመልክቷል። በምሽት ይሁን በቀን መቼ እንደሚያጠቋችሁ አታውቁም ። ከበታቾቻችሁ ያሉት በቅርብ ርቀት ላይ ናቸው። ሰዎች የነሱን ሀሣብ እንድንቀበልና ስምምነትም እንድምናደርግ ተስፋ አድርገው ነበር። እኛ ግን አንቀበልም ብለናል። ስምምነታቸውንም አፍርሠናል። ተዘጋጁ ሌሎችንም አዘጋጁ።› (8)
ሙስሊሞች የኡሣማ ጦር እስኪመለስ ድረስ በከፍተኛ የተጠንቀቅ ሁኔታ ላይ ቆዩ። የኡሣማ ጦር በሄደበት ጉዳይ አትርፎና በምርኮ ተንበሽብሾ ከስልሣ ቀናት በኋላ ተመለሠ። በመመለሱም በመዲና ሙስሊሞች ዘንድ እርጋታ ሠፈነ። አቡበክር የቱን ያል መስዋእት ቢያስከፍለንም የኡሣማን ጦር በመላክ የአላህን መልእክተኛ ትዛዝ መፈፀም አለብን በማለት ላይ መፅናታቸው ትክክል እንደነበሩ በርካቶች ተረዱ። የኡሣማ ጦር መላክ በርግጥም ትልቅ ውጤት አምጥቷል። በሩሞች፣ በሌሎች ዐረቦችና በሙሽሪኮችም ልቦና ውስጥ ፍራቻ እንዲነግስ ምክኒያት ሆኗል። ሩሞች ‹ሙስሊሞች ጥንካሬያቸውን ባይተማመኑ ኖሮ ነቢያቸውን ካጡ በኋላ በዚያ አስቸጋሪ የወገንተኝነት ስሜት ላይ ሆነው አገራችን ድረስ መጥተው ባልተዋጉን ነበር።› የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። የዐረብ ሙሽሪኮች (አጋሪዎች) እና ሙርተዶች (ከእስልምና እምነት የወጡት) የሩም ጦር ከፍተኛ ጥንካሬን በሰው ሀይልም የገዘፈ ሆኖ ሣለ የኡሣማ ጦር በነሱ ላይ ድል ማግኘቱን ሲሠሙ በእጅጉ ደነገጡ።
ኡሣማ እንደተመለሠ አቡበክር ከጊዜው ጋር መሽቀዳደም ያዙ። ወዲያው ኡሣማን መዲና ላይ ሀላፊ በማድረግ ለሱም ለጦሩም ‹እረፍት ውሰዱ፤ ጀርባችሁን አሣርፉ› አሏቸውና መዲናን ሲጠብቁ ከከረሙ ሰዎች ጋር በመሆን ዚልቂሷ በሚባል ቦታ ላይ መርተዶችን (ከእስልምና የወጡትን) ሰዎች ለማጥቃት ወጡ። ከርሣቸው ጋር የነበሩ ሰሃቦች ለአቡበክር ‹በአላህ ይሁንብህ እራስህን ለአደጋ እንዳታጋልጥ አንተ የሙስሊሞች ኸሊፋ ሆይ! አንተ የተጎዳህ እንደሆነ ሰዎች ቅንጅት አይኖራቸውም። ያንተ ቦታ በጠላት ላይ እጅግ ከባድ ነው (ጠላት ይፈልግሃል)። አንድ ሰው አድርግ (ባንተ ፈንታ የጦሩ መሪ የሚሆን)። እሱም የተጎዳ እንደሆነ ሌላ ሰው ትተካለህ።› አሉት ። እሱም ‹ወላሂ አላደርገውም ከናንተ ጋር እሄዳለሁ› አላቸው ። (9)
ዚልቂሷ ላይ ከበርካታ ሙርተዶች ጋር ተገናኙ። አላህም የጠላቶቻቸውን ጥንካሬ ሰበረ፤ ለሙስሊሞቹም ድልን ሠጠ። ከድሉም በኋላ ወደ መዲና ተመለሱ። የኡሣማ ጦር በቂ እረፍት አድርጎ ነበር። መዲና እንደደረሱ በመዲና ዙሪያ የሚኖሩትን የገጠር ሰዎች ሰበሰቡ። ሁሉንም አደራጁና በአስራ አንድ ክፍለጦር ሥር አሥራ አንድ ብርጌድ አቋቋሙ። እያንዳንዱንም የጦር መሪ ባልተለመደ ሁኔታና እንግዳ በሆነ አካሄድ በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት ይከፍት ዘንድ ወደ ዐረብ ግዛት ዳርቻዎች ላኩ።
ከእስልምና ወደወጡት የዐረብ ጎሣዎችም አንድ ደብዳቤ ላኩ። ደብዳቤው ሰዎቹ ጥመትንና ሞኝነትን ትተው ቀጥተኛ ወደሆነው ወደ ጌታቸው መንገድ እንዲመለሱ የሚያወሣ ነበር። ለሁሉም የጦር አዛዦች ይህንኑ መልእክት በሚያልፉበት አካባቢ ሁሉ እንዲያነቡ በአደራ ጭምር አሣሠቡ። ወደ አላህ መንገድ ሣይጠሩ ማንንም እንዳይጋደሉ አዘዟቸው። ጥሪውን የተቀበለ፣ ያመነና ከመጥፎ ድርጊቱም የተመለሠ እንደሆነ ተቀባይነት እንዲያኝና ትብብርም እንዲደረግለት አዘዙ። ያልተቀበለ እንደሆነ ደግሞ ይጋደሉታል። ሥልጣን ላይ በወጡ አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የዐረብ ግዛት ሁሉ ለአቡበክር አገዛዝ እጅ ሠጡ። ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መንገድም ተመለሱ። በዚህ ሁኔታ በሙርተዶች ላይ በማያዳግም መልኩ እርምጃ ተወሠደ ። የነሱም ነገር ፍፃሜ አገኘ።
አቡበክር ላስመዘገቡት ለዚህ ወሣኝና ፈጣን የሆነ ድል ተጠቃሽ ምክኒያቶች አሉ
- የሣቸው ጥንካሬና ከነሱ ጋር ላለመለሣለስ ያሣዩት ቁርጠኝነት
- የአቡበክርን ሀሣብ ከተቀበሉ በኋላ ሙስሊሞች ከሃዲያንን ከመጋፈጥ አንፃር ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውና አንድ መሆናቸው ሌላኛው ሲሆን የአመለካከት አቅጣጫቸው ተለያይቶና ሀሣባቸውም ተበታትኖ በሙስሊሞችም መካከል እነሱን መተው አለብን የሚል ውሳኔ ቢተላለፍ ኖሮ በቀላሉ ወደ ጀመዓው ውስጥ በመግባት ተንኮላቸውን ባሠራጩ ነበር።
- የሙርተዶች መሪዎች ሁኔታ ጥሩ አልነበረም። በተለይ ነቢይ ነን ብለው የተነሱት ውሸታቸው፣ አምባገነንታቸውና መጥፎ ድርጊታቸው ሁሉ ጎልቶ ወጥቷል። ይህም ከመሆኑ ጋር አንዳቸውም የነቢዩ ሙሀመድን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መልእክተኛነት አላስተባበሉም፤ ባይሆን እኛም እንደሣቸው የአላህ መልእክተኞች ነን አሉ እንጂ።
- የዚህ አይነቶቹ ሰዎች ዋና ግባቸው ዓለማዊ ጥቅም ብቻ ነበር። ከሃይማኖቱም የወጡት አንድም የዘካን ገንዘብ በመፈለግ አሊያም የመስጠት ግዴታቸውን ላለመወጣት ነበር። እነ ዑየይናህ ኢብኑ ሂስንና ማሊክ ኢብኑ ኑወይራህን ጨምሮ አብዛኞቹም በነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘመን ዘካን በመሰብሰብ ላይ ይሠሩ የነበሩ መሆናቸው ደግሞ ይህንኑ ጥርጣሬ ያጎላዋል።
የሙርተዶች ፈተና በኢስላም ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ። ሰዎችም ከጥርጣሬና ውዠንብር ንፁህ ሆነው ወደ አላህ ተመለሱ። የአላህ ነቢይ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በመካከላቸው በነበሩ ጊዜ ከቁጥራቸው ማነስ ጋር ይደርስላቸው የነበረው የአላህ እርዳታ በሣቸው መንገድ ላይ ፀንተው እስከተጓዙ ድረስ እንደማይለያቸውም አወቁ። ከዚያ በኋላ ሙስሊሞች ከእስልምና የወጡትን ሁሉ እንዴት ሊጋፈጡ እንደሚችሉ ግልፅ ሆነላቸው። የሙስሊሙ ጦር ኋላ ላይ ሌሎችንም ሀገራት ለመክፈት ያስቻለውን አስደናቂ የሆነ የጦር ልምድና ታክቲክም ከዚህ ጦርነት አግኘቷል።
በየማማ ጦርነት ወቅት በርካታ ቁርአንን የሀፈዙ ሰሃቦች መገደላቸው በተለያየ ቁራጭ ነገሮች ላይ ተፅፈውና ተበታትነዉ የሚገኙትን ቁርኣን አንቀፆች በመሰብሰብና በአንድ መፅሃፍ በመጠረዙ ረገድ የንቃት ደወል ሆናቸው። ከዚህም ሌላ የቁርኣን ሃፊዞች በቃላቸው ካጠኑት በኋላ ቁርኣኑ ሊረሣቸው ይችላልና ይህ ነገር አሣሣቢ ሆነ። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ አቡበክር ዘይድ ኢብኑ ሣቢትን አዘዙ።
ከሙርተዶች ዘመቻ ፍፃሜ በኋላ ሙስሊም ታጋዮች በምድሪቱ ምሥራቅና ምእራብ አቅጣጫዎች ተበተኑ — እስልምናን ለማስፋፋት። አሥራ አንዱ ክፍለጦሮች በየግንባሩ በተመሣሣይ ጊዜና በተለያዩ ቦታዎች ለመዋጋት ከፊሎቹ ወደ ዒራቅ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ሦሪያ አቅጣጫ ተበተኑ። አቡበክር ከላይ እንደተገለፀው ጊዜን ይሽቀዳደሙ ነበር። በመሆኑም ከጦርነቱ በኋላ የሙስሊሙ ጦር ለትንሽ ጊዜ እንኳን እንዲያርፍ አልፈቀዱለትም ነበር።
ማንኛውም ዙሪያውን በጠላት የተከበበ መንግስት ሀይልና ጥንካሬን የሚያስገኝለትን ነገር ሁሉ መያዝ ዘወትርም በሙሉ ንቃትና ዝግጅት ላይ መኖር ይኖርበታል። በያዘው እምነት ትክክለኛነት መዘናጋት የለበትም። ይህም በምድር ላይ በእድሜ ለመቆየት ያስችለዋል። በመሠረቱ የሰው ልጅም በታሪኩ ውስጥ እውነትን ሲያከብር የታየው እውነት ጥንካሬዋ ግልፅ የወጣ እንደሆነ ብቻ ነው።
አቡበክር ይህን ጦር ከመላካቸው በፊት በሰዎች መሃል ሆነው ንግግር አደረጉ ። እንዲህ በማለት ‹ለሁሉም ነገር መዳረሻ አለው። ከዚያ መዳረሻ የደረሠ ሰውም አለማውን አሣካ። ለአላህ ብሎ የሚሠራ አላህ ከመጥፎ ነገር ሁሉ ይጠብቀዋል። በጥንካሬና በመካከለኛነት አደራ ይሁንባችሁ። መካከለኛነት እጅግ የተሻለና ካሰቡበትም የሚያደርስ አካሄድ ነው። ኢማን የሌለው ሰው ሃይማኖት የለውም። ሥራ የሌለውም ምንዳ አያገኝም። ካለ ኒያ ደግሞ ሥራ የለም። አንድ ሙስሊም በአላህ መንገድ በመታገሉ አላህ ያዘጋጀለት ምንዳ እንዳለ በመፅሃፉ ውስጥ አለ። እሷም አላህ ያመላከታት ንግድ ናት። በዚያችም ከውርደት ይጠበቃል፤ በዚህ ዓለምም ሆነ በመጭው ዓለም ክብርን ያገኛል።› (10)
እነኚህንና መሠል መልካም አስተምህሮዎችን የኢስላም ጠላቶች ከታሪካችን ለማጥፋት ብዙ ሠርተዋል። እነሱ በፈጠሩት ተፅእኖም የተነሣ ስለነኚህ ነገሮች ማስታወሱም ማውራቱ ክልክል ሆኗል። ስለዚህ ነገር የሚያነሣ ሰውም በሌሎች ሰዎችም ሆነ በራሣቸው በሙስሊሞች መካከል እንደሌለና የተለየ ሀሣብ ባለቤትም እንደሆነ ተደርጎ ተቆጥሯል።
አቡበክር አገራትን የመክፈት ዘመቻቸውን በዒራቅ በኩል ጀመሩ። ወደሷም ኻሊድ ኢብኑልወሊድንና ዒያድ ኢብኑ ገነምን ላኩ። ኻሊድ በደቡብ በኩል ዒያድ ደግሞ በሰሜን አቅጣጫ በኩል እንዲገቡና ከዚያም መሃል አገር የምትገኘውን ሂራ ለመያዝ እንዲሽቀዳደሙና ወደ ሂራ ቀድሞ የደረሠ የሌላኛው መሪ /አዛዠ/ እንዲሆን ነገሯቸው። አክለውም ‹ሂራ ላይ የተገናኛችሁ እንደሆነ የፋርስን ጦር ፈታችሁ፤ ከኋላችሁ ለሚመጡ ሙስሊሞችም ከለላ ሆናችሁ ማለት ነው። በመሆኑም አንዳችሁ ከሙስሊሞችም ሆነ ከሌላኛችሁ ይከላከል፤ ሌላኛችሁ ደግሞ የአላህን ጠላቶችና ጠላቶቻችሁን የሆኑትን የፋርስ ሰዎች ግዛቶችን ያጥቃና ይያዝ። ጠንክራችሁ ተዋጓቸው። በአላህ ታገዙ እሱንም ፍሩ። መጭውን ዓለም ከቅርቢቱ ዓለም ምረጡ ሁለቱንም ዓለም ታተርፋላችሁ። ይህችን ዓለም አታስበልጡ ሁለቱንም ዓለም ታጣላችሁ። አላህ ከከለከላችሁ ወንጀል ተከልከሉ። ወደ አላህ ለመመለስም ፍጠኑ። አደራችሁን ተውባን /ንስሃን/ በማዘግየት በሀጢኣት ላይ አትዘውትሩ።› አሏቸው።
አንድ ሰው በዙሪያቸው አደጋ የተባለ ሁሉ ያካበባቸውን ዐረቦችን ፤ ከተለያዩ ሀገራት ተጠራርተው በፍልስጤም ምድር ላይ የተሠባሰቡትን አደገኛ አይሁዶችን፤ ጦሯን አደራጅታ የሙስሊም አገራትን ሁሉ ተራ በተራ የምትወረውን አሜሪካን፤ በሺኣ አስተሣሰብ ተጠምቃ ዐረቦችንና የምታስፈራራውን ኢራንን ሁኔታ በማየት ይገረም ይሆናል። ነገር ግን ከዚህ በላይ የሚያስገርመው በአሁኑ ጊዜ የአረብ ሀገራት መሪዎች ዜጎቻቸውን ከቀን ወደ ቀን ከሃይማኖታቸው ለማራቅ የሚያደርጉትን ተጋድሎ ማየቱ ነው። እንዲያውም አንድ የሙስሊም ሀገር መሪ በአንድ ወቅት በግልፅ እንዲህ ያለበት ሁኔታ አለ ‹ሀገራችን ከሃይማኖት ነፃ ወደሆነ የአስተዳደር ጎዳና እያመራች ነው፤ የሰዓት ቆጣሪውን ወደ ኋላ መመለሱ አይቻልም።› ብሏል። እነኚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ኢማን በነሱም ሆነ በህዝቦቻቸው ላይ ለዘላለም ነግሦ የሚኖር የደህንነት መንገድ መሆኑን አለማወቃቸው ጎድቷቸዋል። አቡበክር ህዝቦቻቸው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በገቡበት ወቅት በኢማን ምሽግ ውስጥ እንዲገቡ እንዲህ በምን ብለው እንደመከሯቸው ከላይ ባሣለፍነው አንቀፅ አይተናል።
ኻሊድ ኢብኑ አልወሊድ አቡበክር ባስቀመጡት ንድፍ በመጓዝ አብላህን ከፈተ። ቀጥሎም ሚሣንንና በዙሪያዋ ያሉ መንደሮችን ያዘ። ከዚያም ወደ መሃል ዒራቅ በመዝለቅ የከስከርንና የዘንዱርድን መሬቶች ተቆጣጠረ። ከዚህም በተጨማሪ አሊስን፣ የመሊክን ወንዝ፣ የሂራን ምድር፣ አንባርን እና ዐይን ተምርን ጭምር በቁጥጥሩ ሥር አስገባ። በዚህ ሁኔታ አብዛኛው የኢራቅ ምድር በተወሰኑ ወራት ውስጥ ብቻ በሙስሊሞች እጅ ገቡ። አቡበክር የነዚህ ሁሉ ድሎች ዜና ወደሱ በመጣ ጊዜ በዙሪያቸው ለተሰበሰቡ ሰዎች እንዲህ አሉ ‹እናንተ ቁረይሾች ሆይ ! አንበሣችሁ ከአንበሣ ጋር ተጋጠመና ድል ነሣ። ሴቶች የኻሊድ ዓይነት ጀግና መውለድ ምነዋ አቃታቸው!› አለ። (12) ባይሆን በዐረቦች ውስጥ የኻሊድ ዓይነቶች ሞልተዋል። ጦሩን የሚያደራጅለት አቡበክርስ ከሱ ይተናነስ ይሆን!።
በዒራቅ ምድር ኻሊድ ካደረጋቸው ዘመቻዎችና ካገኛቸው ድሎች እነኚህን ሁኔታዎች እናስተውላለን
- ፍጥነቱ የሚገርም ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሂራን ምድርና አብዛኛውን የዒራቅ መሬት ተቆጣጥሯል።
- በባህሪው ኻሊድ ለጠላት የማሠቢያ ጊዜ አይሠጥም። ባይሆን የጦር አዛዦቹ ሥራቸውን ወደ ኢስላም ጥሪ በማድረግ እንዲጀምሩ ያዛቸው ነበር። ጥሪውን ከተቀበሉ ተቀበሉ ካልሆነ ግን ለተወሠነ ቀን ጊዜ ይሠጣቸዋል። እንዲህም ይላቸው ነበር ለጠላቶቻችሁ ስለናንተ እንዲያውቁ እድል አትስጧቸው። አዘናግተው ያጠቋችኋልና። ሙስሊሞችንም ጠላቶቻቸውን ከመዋጋት አትከልክሏቸው። ምክኒያቱም እነሱን መከልከል በጠላቶቻቸው እንዲጠቁ እድል መስጠት ነውና። ሌላው ደግሞ ከሃይማኖትና ከሀገር ክብር አንፃር የሙስሊም ልቦች ያላቸውን ቅናትና ተቆርቋሪነት ከቀልባቸው ውስጥ ሊያጠፋ ይችላል። ይህም ተስፋ ወደ መቁረጥና ሀይላቸውንም ባልሆነ ቦታ ላይ እንዲያውሉ ሊያደርጋቸው ይችላል።
- ሥራውን ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መንገድ በመጥራት ይጀምራል። በተግባርም የሰዎችን ልብ ለመሣብ በመሞከሩ ላይ ያተኩራል። ይህንንም የሚያደርገው እንዲህ በማለት የመከሩትን የአቡበከር አስ ስዲቅን ፈለግ ለመከተል ነው የፋርስ ህዝቦችንና በነሱ አገዛዝ ሥር ያሉትን ሰዎች ልብ ማርኩ።
- በተመሣሣይ ሁኔታም ኻሊድ ለባላጋራው ሀይሉንን ጥንካሬውን ያሣይ ነበር። ኻሊድ ከጦርነቱ በፊት ለፋርስ ነገስታት እንዲህ በማለት ፅፈውላቸው ነበር ሰላም ቀናውን መንገድ በተከተሉት ላይ ሁሉ ይሁን። ቀጥሎም ምስጋና ለናንተ ማጎብደድን ላስቀረ፣ ንግስናችሁን ላፈራረሠ፣ ሴራችሁንም ላዳከመ አላህ ይሁን። ሰላታችንን የሠገደ፤ ቂብላችንን የተቀጣጨ፤ ያረድነውን የበላያ ነው በኛ ዘንድ ሙስሊም። እሱም ከኛ መብት ያለው እኛም ከሱ ያለን። ይህ መልእክቴ የደረሣችሁ እንደሆነ ወደኔ ዋስትና የሚሆናችሁን ላኩ፤ ከኔም ከለላ አግኙ። ካልሆነ ግን ነፍሴ ነእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ፤ እናንተ ህይወትን እንደምትወዱ ሁሉ ሞትን የሚወዱ ሰዎችን እልክባችኋለሁ።
ሀይልን ማሣየት በትንሽ ኪሣራ ድልን ለማግኘት በላጩ መንገድ ነው። ይህም በጠላት ልብ ውስጥ ፍራቻን ይዘራል። ለመዘጋጀትም ጊዜ ያሣጣቸዋል። ተስፋም ያስቆርጣቸዋል።
የፋርስ መሪዎች የኻሊድን ደብዳቤ ባነበቡ ጊዜ ይህ ንግግር ከነዚያ ሁሌም ለፋርሦች ተገዠ ከሆኑ ዐረቦች ስለመውጣቱ ማመን አቅቷቸው በጣም ተገረሙ። ከሂራ መከፈት በኋላ አቡበክር ደግመው ፃፉላቸው። ግልባጩንም ለተለያዩ መሪዎቻቸውና ንጉሦቻቸው ላኩ። ሌላው ኮፒ ደግሞ በብዙሃኑ ህዝብ ላይ እንዲነበብ አስደረጉ። በደብዳቤው ውስጥም እንዲህ የሚል መልእክት ተካቶ ነበር ‹በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩህሩህና አዛኝ በሆነው። ከኻሊድ ኢብኑልወሊድ ወደ ፋርስ ንጉሥ .. ምስጋና የናንተን አደረጃጀት ላፈራረሠ፣ ሴራችሁን ላዳከመና አንድነታችሁንም ለበተነ ጌታ ይሁን። እሱ ይህን ባያደርግባችሁ ኖሮ ነገሮች ለናንተ በከፋ ነበር። ወደኛ እንድትጠቃለሉ እናንተንም ሆነ መሬታችሁንም እንጋብዛለን። ካልሆነ ከናንተ ወደልሆነ አካል እናስረክባችኋለን። ሣትወዱ በግድ ይህ ነገር ይፈፀማል። በነዚያ እናንተ ህይወትን እንደምትወዱ ሞትን የሚወዱ በሆኑ ሰዎች አማካይነት።›
በፋርሦች ሥም በነሱ ተወክለው ሂራን ያስተዳድሩ ወደነበሩ የዐረብ ገዠዎችም እንዲህ በማለት ፃፉላቸው ‹ወደ አላህ እና ወደ እስልምና እጠራችኋለሁ። ጥሪዬን ከተቀበላችሁ እናንተ ከሙስሊሞቹ ናችሁ። ለነሱ (ለሙስሊሞች) ያላቸው ለናንተም አላችሁ በነሱ ላይ ያለ በናንተም ላይ አለ። አይሆንም ካላችሁ የግብር ግዴታ አለባችሁ። ግብር በመክፈል የማትስማሙ ከሆነ እናንተ ህይወትን ከምትወዱት በላይ ሞትን የሚወዱ የሆኑ ሰዎችን ይዤላችሁ መጥቻለሁ። በኛና በናንተ መካከል አላህ እስኪፈርድ ድረስም እንዋጋችኋለን።› ይህ መልእክት የተላከው ከፉርሦች ከተሸነፉና አካባቢውንም ከለቀቁ በኋላ ነበር። ቀቢሣ ኢብኑ ኢያስ የተባለ የነሱ የሆነ አንድ ሰው ‹ከኛ የምትፈልገው ምንድነው? በሃይማኖታችን ፀንተን መኖር እንፈልጋለን። ግብርህን እንከፍላለን።› በማለት በዘጠና ሺህ ድርሃም ግብር ተስማማ።
ሌላው ደግሞ ኻሊድ አደገኛ የሚባሉትን ሰዎች አሣድዶ በመያዝ ሌሎች ትምህርት እንዲወስዱበት ያደርግ ነበር። በአሊስ መከፈት ጊዜ ከሰልፉ ፊት ለፊት በመቆም ወደ ፋርሦች ያደሉትን የዐረብ መሪዎችን በመጥራት ‹የታላ አብጀር? የታለ ዐብዱል አስወድ? የታለ ማሊክ ኢብኑ ቀይስ?› በማለት ጠየቀ። ሆኖም ግን ከማሊክ በስተቀር አንድም ሰው የሚወጣ ጠፋ። በዚህን ጊዜ ኻሊድ የሚጋፈጠው ሆኖ ወጣለትና ‹አንተ የመጥፎ ልጅ! ያውም በሰው ውስጥ ግምት የሌለህ ሰው ስትሆን ደፍረህ ወደኔ እንድትወጣ ያደረገህ ምንድነው?› አለው። ከዚያም በሀይለኛ ምት መትቶ ጣለው። የተቀሩትም በፍራቻ ተርበተበቱ።
ኻሊድ ከጦረኞች ጠላቶቹ ጋር ባህሪው እንዲህ ጠንከር ያለ ቢሆንም ከተራው ሰላማዊ ህዝብ አንፃር ግን እጅግ ለስላሣ ሰው ነበር። ይህም ላይገርም ይችላል። ምክኒያቱም የተነሣለት ዓላማ እነኚህን ህዝቦች ከአምባገነኖች መዳፍ እጅ ፈልቅቆ ነፃ ማውጣት ነውና። አቡበክር በወቅቱ ኻሊድ ወደ ዘመቻ ከመንቀሣቀሱ በፈት እንዲህ በማለት መክረውት ነበር ‹አርሦ አደሮችን አታፈናቅል፤ የከለላ ዋስትናም ስጣቸው› ለነኚህ ማህበረሰቦች ያደረገው ጥሩ አያያዝ ኋላ ላይ ፈጥነው ወደ እስልምና እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
ኻሊድ በድርጊቶቹ የእስልምናን ገርነትና ፍትሃዊነት አሣይቷል። ሀገራት ከተከፈቱ በኋላ ይደረጉ የነበሩ ውሎችና ስምምነቶች ይህንኑ ያመለክታሉ። ከነኚህም ውስጥ ኻሊድ ለባትቂያ፣ ለባሮስማና ለአሊስ ህዝቦች የፃፉት ይጠቀሣል። በመልእክቱም ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበታል ‹በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩህሩህና አዛኝ በሆነው። ከኻሊድ ኢብኑ አልወሊድ ለኢብኑ ሰሉባ አስ ሰዋዲ የተሠጠ ውል (ከሱ ጋር ስምምነቱን የፈፀመ ሰው ነበር)። አድራሻው በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ ሲሆን የግብር መክፈል ግዴታህን ስለተወጣህ ደምህም ሆነ ደህንነትህ በኛ መሃል የተጠበቀ ነው። ከራስህ፣ ከአጠቃላይ ገቢህ፣ ከግዛትህና ከመንደርህ ሰዎች (ከያትቂያና ባሮስማ) አንድ ሺህ ድርሃም ከፍለህ ተቀባይነት አግኝቷል። በዙሪያዬ የሚገኙ ሙስሊሞችም ይህንኑ ወደው ተቀብለዋል። ስለዚህ አንተ አላህ በሠጠህ ደህንነት ውስጥ ነህ። አንተ በአላህ ፣ በነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲሁም በሙስሊሞች ከለላ ውስጥ ነህ የሚነካህ የለም።(18)
ወደ ሂራ ሰዎችም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፈ ‹ይህ ኻሊድ ኢብኑ ልወሊድ ለዐዲያ እና ለዐምር የዐዲ እና የዐምር ኢብኑ ዐብዱልመሲህ ልጆች ለሆኑት እንዲሁም ለኢያስ ኢብኑ ቀቢሣ፣ ለሂራ ኢብኑ አካል ጋር ዑመር ያደረገው ስምምነት ነው። እነሱ በሂራ ህዝቦች ውስጥ የተመረጡ ሰዎች ናቸው። ውክልናቸውንም የሂራ ሰዎች ወደው ከኛ ጋር ሰምምነት እንዲፈፅሙ አድርገዋል። በመሆኑም በመቶ ዘጠና ሺህ ድርሀም ስምምነት አድርገናል። ይህም በየአመቱ የሚከፈል ግብር ሲሆን ምንም ሀብት የሌለው ድሃና ለመክፈል በማያስችል አስገዳጅ ነገር የደረሠበት ሲቀር መነኩሴዎቻቸውንና ቄሦቻቸውንም ይጨምራል። መክፈል ያልቻሉት መክፈል እስኪችሉ ድረስ ምን የለባቸውም። በተግባርም ይሁን በቃል ይህን ውል ያፈረሱ እንደሆነ ምንም ከለላና ዋስትና የላቸውም።(19)
ኻሊድ ለከፈሉት ግብር ማካካሻ የሚሆን መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ሊያሟላላቸው ቃል ገባ። መሠረተ ልማቶችን መዘርጋት፣ ትላልቅ ግድቦችን መሥራት፣ የውሃ ጉድጓድ መቆፈር፣ መንገድ ማስተካከል፣ የመስኖ ቦዮችን መዘርጋት፣ የህክምና ተቋማትን ማቋቋም፣ ሽንት ቤቶችን ለመሥራትና ከዚህም በተጨማሪ በእድሜ ለገፉ ሰዎቻቸው ወርሃዊ የሆነ ክፍያ ሊፈፅምላቸው ቃል ገባ። በሌላ ፅሁፍ ውስጥ ደግም ‹መሥራት ለማይችል በእድሜ ለገፋ ሁሉ፣ እንዲሁም ችግር አግኝቶት ለደሀየ ሀብታምና የሀገሬው ሰዎች የሚረዱት ከሆነ ሰው ላይ ግብር ተነስቶለታል። ከሙስሊሞች የንብረት ክፍልም ለሱና ለቤተሰቦቹ የሚሆን ድጎማ ይሠጠዋል።› (20) የሚል አለ።
ይህም ፍትሃዊ ስምምነት ከክርስቲያን የዐረብ መሪዎች የሆነውን ዐምር ኢብኑ ዐብዱልመሲህ የሚባለውን ሰው እንዲህ እስከማለት አድርሦት ነበር ‹ወላሂ እናተ ዐረቦች ሆይ! የመቶ አመታት እድሜ ቢኖራችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ ታገኛላችሁ።› ካለ በኋላ ወደ ሂራ ሰዎችም በመዞር ‹ እንደ ዛሬ ግልፅ የሆነ ነገር አይቼ አላውቅም› አላቸው
የሂራ መሪዎች በርካታ ስጦታዎችን በመሰብሰብ ለኻሊድን ለወደሮቹ አመጡ። ኻሊድም ወዲያውኑ ወደ አቡበክር ላካቸው። አቡበክርም ወደ ኻሊድም እንዲህ በማለት ፃፈ ‹ሥጦታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ግብር ቀንስላቸው።› ይህ ሁሉ የሚያሣየን የሰው ልጆች ከሙስሊም ታጋዮች ሊማሯቸው የሚገባቸውን ቅንነነትና ንፅህና ነው።
ኻሊድ ግብራቸውን የከፈሉ ሰዎች ነፃ መሆናቸውን በሚያረጋግጠው ደብዳቤው ውስጥ እንዲህ በማለት ይፅፍ ነበር ‹ በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩህሩህና አዛኝ በሆነው። ከአስተዳዳሪው ኻሊድ ጋር በተስማማው መሠረት ይህን ያህል የግብር ክፍያ የነበረበት ይህ ሰው አሁን ከክፍያው ነፃ ነው። ኻሊድ የተስማማበትን ተቀብያለሁ። በመሆኑም በሁኔታችሁ እስከፀናችሁ ከመተናኮልም አስከተቆጠባችሁ ድረስ ኻሊድን ሆነ ሙስሊሞች የኻሊድን ስምምነት በሚያፈርስ ላይ አንድ ናቸው። ደህንነታችሁም ሆነ የተጠበቀ ነው። ስምምነታችሁ ስምምነት ነው። እኛን ለናንተ የገባንለችሁን ቃል እንሞላለን።› (23)
በሌላ በኩል ኻሊድ እሱን የሚዋጉትን ጠላቶቹን ድል ከነሣቸው በኋላ ያለ አንዳች ማስገደድ ወደ እስልምና ይጋብዛቸው ነበር። በሂራ ምድር ከሌሎች በተለየ መልኩ በያንዳንዱ ቤተመንግስት በመግባት ‹ምን ሆናችሁ! ምን ነካችሁ!። ወዮላችሁ ዐረቦች ናችሁ? ዐረቦች ከሆናችሁ ከዐረቦች መልካም ነገር እንጂ መጠበቅ የለባችሁም። ወይንስ ዐጀም/ዐረብ ያልሆናችሁ/ ናችሁ። ከሆናችሁ ደግሞ ከፍትህና ሚዛናዊነት ሌላ ከኛ ምን ትጠብቃችሁ?። ከመካከላቸው አንዱ ‹ባይሆን እኛ ከዐረቦች ነን። ሌሎች ደግሞ የዐረብ ዝርያ ያለብን አለን።› አለው። እሱም ‹እንዳላችሁት ብትሆኑማ ኖሮ ለምን ትጋፈጡናለችሁ ለምንስ ያመጣንላችሁን ነገር ትጠላላችሁ?።› አላቸው።
እነኚህ ሰዎች ‹ግብር መክፈል ይሻለናል› በማለት ወደ እስልምና ሣይገቡ በቆዩ ጊዜ ‹ወዮላችሁ! ምንኛ የተረገማችሁ ናችሁ! ኩፍር /በአላህ መካድ/ እኮ ወሠን የሌለው ጥመት ነው። ‹እጅግ ሞኞች› የሚባሉ ዐረቦችም ኩፍርን /ክህደትን/ የመረጡት ናቸው።› አላቸው። ከዚያም ከሁለት የመንገድ መሪዎች ጋር ተገናኙ ። አንደኛው ዐረብ ነበር። እሱ የተጓዘበትን መንገድ በመተው ዐረብ ያልሆነው ሰውዬ የመራቸውን መረጡ። ይህም ተቃውሞአቸውን ለማሣየት ይመስላል።
በእንቢተኝነታቸው ሲፀኑ ግን አላህ ሂዳያ/መስተካከልን/ እስኪሠጣቸው ድረስ በዚያው ሁኔታ ላይ ተውዋቸው። ሰዎችን እስልምና እንዲቀበሉ ማስገደድ የእስልምና አስተምህሮ አይደለምና። ማንኛውም የሙስሊሞችን ታሪክ ያነበበና ሚዘናዊ አመለካከት ያለው ሰው ሁሉ ይህንኑ ይመሠክራል። ቶማስ አርኖልድ እንዲህ ይላል ‹ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች እስልምናን እንዲቀበሉ ሲገደዱም ሆነ የክርስትናን ሃይማኖት ለመጨቆን የተደረገ የተደራጀ ዘመቻም ሆነ ሃይማኖቱን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት የተደረገ ሙከራ አልሠማንም።› (24)
ኻሊድ ጦርነቶችና ተከታታይ የሆኑ ድሎችም እጅግ የበዙበት ከመሆኑ ጋር አንድ ሀገር በከፈተ ቁጥር ነቢያዊውን አካሄድ የዘነጋበት ሁኔታ አልነበረም። ሂራን በከፈተ ጊዜ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መካን በከፈቱ ጊዜ ያደረጉትን ፈለግ በመከተል ስምንት ረከዓ የድል ሰላት ሰግዶ ነበር።
በአጠቃላይ እነዚያ ድሎች ለሀገሬው ነዋሪዎች መልካም ነገር ያመጡ ነበሩ። በተለይ ለድሆቹ። በነሱ ላይ ተተብትቦ የኖረው የጭቆና ሰንሰለት ተነስቶላቸዋል። በፊት ያለ አንዳች ክፍያ በገዛ መሬታቸው ለአለቆቻቸውና ለገዠዎቻቸው ሲሠሩ የነበረ ሲሆን ኋላ ላይ እሷ ከምታበቅለዉ መልካም ነገር ሁሉ ተጠቃሚዎች ለመሆን ችለዋል። ያኔ ከተከሠቱ አስገራሚ ነገሮች መካከል ለፋርስ ንጉሦች ብቻ የሚዘራ በዓይነቱ ለየት ያለ የተምር ዘር ነበር ። ሙስሊሞች አካባቢውን ሲቆጣጠሩ ግን ከዚህ ተምር እንደልባቸው ማግኘትና መብላት የቻሉ ሲሆን ለዒራቅ ገበሬዎችም ይህንነኑ የደከሙበትን ነገር ግን ለመብላት ያልታደሉትን ተምር ያከፋፍሉ ነበር። ወደ ዑመርም እንዲህ በማለት ፃፉ ‹የኪሥራ ሰዎች እንዳንበላው በከፍተኛ ሁኔታ ሲጠብቁት የነበረውን ተምር አላህ አብልቶናል። እኛም አላህ የዋለብንን ፀጋና ችሮታ ታዩ ዘንድ ወደድን።› (25)
በልጅነታቸው በባርነት ቀንበር ሥር የወደቁ የነሱ ልጆች እንኳ ኢስላም በእኩልነት የማደግና ሀብት የማፍራት መብት ሠጣቸው። በመሆኑም በጥሩ ሁኔታ ተኮትኩተው አደጉ። ከነዚያ ሰዎችና ከልጅ ልጆቻቸውም እንደ ኢብኑ ኢስሃቅ፣ አልዋቂዲ፣ ሀሠን አልበስሪ እና ኢብኑ ሲሪን የመሣሠሉ ታላላቅ የሙስሊሙ ዓለም ዑለማኦች ሊወጡ ችለዋል።
ከጌታቸው መንገድ በራቁ ሰዎች ላይ የአላህ ውሣኔ እንደሚተላለፈው ሁሉ ፋርሦች ዘመን በራቀ ቁጥር በጥመት ጎዳና ውስጥ ገቡ። ምግብ ለመብላት ፊት ለፊታቸው አስቀምጠው ሣለ መሞትና ከምድር ላይ መጥፋት የነሱ እጣ ፈንታ የሆነበት ጊዜ ነበር። በአሊስም የሆነው ይህንኑ ያስታውሰናል። ፋርሦች የምግብ ማእዳቸውን ዘርግተው፣ ተጠራርተውና በምግቡም ዙሪያ ተሠባስበውም ባለበት ሁኔታ ከመመገባቸው በፊት ጦርነት ተነሣ። ሽንፈትንም ተከናነቡ። ምግቡም የተራቡ ሙስሊሞች ምርኮ ሆነ። በምሽቱ ሰዓትም ለእራት ተሠባሠቡበት። (26)
የፅሁፉ ምንጮች
[1]. ሙኽተሰር ታሪኽ ዲመሽቅ ቅ. 1 ገፅ 53
[2]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 246
[3]. አል ሙኽተሰር ፊ አኽባሪል በሸር ሊ አቡል ፊዳእ ቅ. 1 ገፅ 107
[4]. አል ኢክቲፋእ ቢማ ተደመነት ሚን መጋዚ ረሱሊላህ ወሰላሰቱል ኹለፋእ ሊ አቢ ረቢዕ ሱለይማን ኢብን ሙሳ አል ከለዒ ቅ. 3 ገፅ 9
[5]. አል ኢክቲፋእ ቢማ ተደመነት ሚን መጋዚ ረሱሊላህ ወሰላሰቱል ኹለፋእ ሊ አቢ ረቢዕ ሱለይማን ኢብን ሙሳ አል ከለዒ ቅ. 3 ገፅ 9
[6]. አል ኢክቲፋእ ቢማ ተደመነት ሚን መጋዚ ረሱሊላህ ወሰላሰቱል ኹለፋእ ሊ አቢ ረቢዕ ሱለይማን ኢብን ሙሳ አል ከለዒ ቅ. 3 ገፅ 9
[7]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 477
[8]. ታሪኽ ዲመሽቅ ቅ. 25 ገፅ 162
[9]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 588
[10]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 544 ጀምሮ
[11]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 563
[12]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 564
[13]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 551
[14]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 553
[15]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 572
[16]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 552
[17]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 551
[18]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 567
[19]. ኪታብ አል ኸራጅ፡ አቡ ዩሱፍ ገፅ 306
[20]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 567
[21]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 566
[22]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 572
[23]. አድ ዳዕዋ ኢለል ኢስላም ሊ ቶማስ አርኖልድ ገፅ 99
[24]. ታሪኽ አጥ ጠበሪ ቅ. 2 ገፅ 636
[25]. አል ሙንተዘም ቅ. 1 ገፅ 449