መጠነኛ ቅኝት ስለ ኹለፋኡ ራሽዲን ዘመን (ክፍል 3)

0
4917

በባለፈው መጣጥፋችን ሙስሊም ሙጃሂዶች/ታጋዮች/ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የሙርተዶችን/ ከእስልምና የወጡ ከሃዲያንን/ እንቅስቃሴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት እንደደመሰሱና በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉ፣ እንዲሁም ከዚያ በኋላም በኻሊድ ኢብኑል ወሊድ መሪነት በዚያው ዘመን ውስጥ የሂራን ግዛት እና ዒራቅን መክፈታቸውን አይተናል፡፡

ኻሊድ ኢብኑል ወሊድ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት ነበር በርካታ ሀገራትን የከፈተው፡፡

አንድን ሀገር ከመክፈቱ በፊትም የመጀመሪያ ሥራው ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መንገድ በመጥራት ሰዎች እስልምናን  እንዲወዱና እንዲቀበሉ ማድረግ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚሁ ጎን ለጎን አድብተው ለሚጠባበቁት ጠላቶቹ ሀይሉን ያሣይ የነበረ ሲሆን ለሌሎች ማስተማሪያ ይሆኑም ዘንድ ብርቱ አያያዝ ይይዛቸው ነበር፡፡ ኻሊድ በዋናነት ሀይሉንና ጥንካሬውን ያሣይ የነበረው ለሚወጉት ጠላቶቹ ሲሆን ሠላማዊ ለሆኑት የሀገሬው ሰዎች እና ገበሬዎች ግን እጅግ ለስላሣ ሰው ነበር፡፡

ሙስሊሞች ድል አድርገው በከፈቷቸው ሀገሮች ውስጥ የእስልምና ይቅርባይነትና አዛኝነት በስፋት ጎልቶ ታይቷል፡፡ እምነቱ ለሀገሬው ሰዎች እጅግ ብዙ መልካም ነገሮችን ይዞ ነበር የመጣው፤ በተለይም ለድሆች፡፡ የተቀፈደዱበትን የባርነት ሠንሠለት የፈታላቸው ሲሆን ለአሣዳሪዎቻቸው በነፃ ያለምንም ክፍያ ይሠሩበት ከነበረው መሬት ምርትም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ሠጥቶአቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከልጆቻቸው ውስጥ ተማርከው በሙስሊሞች እጅ የወደቁትን በአሣዳሪዎቻቸው አማካይነት ኢስላም ለነሱ የሚሆን ድርሻ መድቦላቸው ነበር፡፡ አሣዳሪዎቻቸውም አያያዛቸውን በማሣመር በጥሩ እንክብካቤ ስላሣደጓቸው ከመካከላቸው ኢብኑ ኢስሃቅ፣ አልዋቅዲ፣ ሀሠን አልበስሪን እና ኢብኑ ሲሪንን የመሣሠሉ ታላላቅ የሙስሊሙ ኡማው ዑለማዖች ሊወጡ ችለዋል፡፡ በዚህ መልኩ ዒራቅ ታላቁን የተውሂድ የኢስላም ባንዲራ ለማውለብለብ ቻለች፡፡

እስቲ ደግሞ ወደ ሻም/ ሦሪያና አካባቢው/ ሀገሮች የነበረውን ሁኔታ  እንቃኝ፡፡

አቡበክር አስስዲቅ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ፈለስጢንን ይከፍት ዘንድ ዐምር ኢብኑል ዓስን ወደዚያው ላኩ፡፡ አቡ ዑበይዳን ደግሞ የሦሪያዋ ሂምስን እንዲከፍት የላኩት ሲሆን አል ወሊድ ኢብኑ ዑቅባን ወደ ጆርዳን የዚድ ኢብኑ አቢ ሱፍያንን ደግሞ ወደ ደማስቆ ላኩት፡፡

ዐምር ኢብኑልዓስ በአቡበክር ትእዛዝ ወደ ፈለስጢን ከመላኩ በፊት ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በተሠጠው ሀላፊነት በኦማን ግዛት ላይ አስተዳዳሪ ሆኖ ይሠራ ነበር፡፡ ኋላ ላይ አቡበክር ሙርተዶችን ሊፋለሙ ባሰቡ ጊዜ ግን አስጠሩት፡፡ ዘመቻው ካለቀ በኋላ ወደ ኦማን እንዲመለስ ያዘዙት ቢሆንም እዚያ ከመድረሱ በፊት ግን እንዲህ የሚል ደብዳቤ ላኩለት፡፡

‹በርግጥ የአላህ መልእክተኛህ በሾሙህ ሥራ ላይ እንድትመለስ አዝዤህ ነበር… እኔም የርሣቸውን ቃልኪዳን ለመጠበቅ ብዬ በቦታው ላይ መለስኩህ፡፡ አንተም በተደጋጋሚ እዚያው ላይ ቆይተሃል፡፡ የአብደላህ አባት ሆይ! አሁን ግን ለዛሬው ህይወትህም ሆነ ለመጨረሻው ዓለምህ በላጭ ይሆንልሃል ብዬ ባሰብኩት ነገር ላይ ሀላፊነት ልሰጥህ ወደድኩ፡፡ ሥራው ወዳንተም ተወዳጅ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡› ዐምርም እንዲህ በማለት መለሠላቸው ‹እኔ ከኢስላም ቀስቶች አንዱ ቀስት ነኝ፡፡ አንተ ደግሞ ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ቀጥሎ የቀስቱ ወርዋሪ ነህ፡፡ መልሦ ሰብሣቢውም አንተው ነህ፡፡ ለአላህ ፍራቻ ቅርብ፣ በላጭ እና ጠንካራ የትኛው እንደሆነ ለይና ወደ የትኛውም አቅጣጫ ወርውረኝ፡፡› (1)

አንድ ገዥ የሚያስተዳድራቸው ሰዎች የሚወረውራቸው ቀስቶቹ መሆኑን ካወቀ ቀስቶቹን እንደማያልቁበት በመተማመን ወደመረጠው አቅጣጫ በያንዳንዱ አምባገነን እና ከሃዲ ላይ መጠቀም እንዳለበት ነው፡፡ ዐምርም ለሀላፊያቸው ያለው ይህንኑ ነው፡፡ ‹እኔ አንድ ቀስት ነኝና ይበጃል ባልከው ቦታ ላይ ተጠቀምብኝ› ማለቱ ነበር፡፡

አቡበክር አስ ስዲቅ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በሦሪያ የሚገኘው የሙስሊም ሠራዊት ሀገራትን የመክፈት እንቅስቃሴው ከዒራቅ አንፃር ሲታይ ዘገምተኛ መሆኑን አስተዋሉ፡፡ በመሆኑም ኻሊድ ኢብኑ አልወሊድ ከጦሩ የተወሰነውን ከፍሎ ዒራቅ ውስጥ ሙሰና ኢብኑ አልሃሪሣ ዘንድ በመተው ወደ ሻም/ሦሪያ/ ሀገር በመሄድ እዚያ ያሉትን አመራሮች እንዲያግዝ አዘዙት፡፡ እንዲህ አሉት ‹የርሙክ የሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ እስክትደርስ ድረስ ተጓዝ፡፡ እዚያም ስትደርስ የተዘጋጁና ያዘጋጁ ሆነው ታገኛቸዋለህ፡፡›

ኻሊድም የኸሊፋውን ትእዛዝ በመቀበል ሙሠናን ዒራቅ ባለው ጦር ላይ አዛዥ በማድረግ የተወሠነ ጦር ይዞ ወዲያውኑ ወደ ሦሪያ ተንቀሣቀሠ፡፡ እግረ መንገዱንም መርጅ ረህጥን ከፈተ፡፡ ወደፊት በመገስገስም በበስራ ሸለቆ ዘንድ አረፈ፡፡ አቡ ዑበይዳን ከፊቱ በማስቀደም የበስራን ከተማ ያለ ጦርነት በስምምነት የከፈተ ሲሆን ይህም ከተከፈቱት የሻም ከተሞች ሁሉ በስራን የመጀመሪያው ያደርጋታል፡፡ ኻሊድ በበኩሉ የተድመርን ከተማ ከፈተ፡፡

ኻሊድ ከቀናት ጉዞ በኋላ የርሙክ ወንዝ ደረሠ፡፡ ሙስሊሞች እየጠበቁት ነበር፡፡ ከ240 ሺህ በላይ የሚሆን የሩሞች የጠላት ጦር ሙስሊሞችን ለመውጋት በከፍተኛ ሁኔታ ተዘጋጅቷል፡፡ ዝግጅታቸው የሚገርምና አስፈሪ ነበር፡፡ 80 ሺህ ያህሎቹ  ከጦርነቱ እንዳይሸሹ በሠንሠለት የታሠሩ ናቸው፡፡ አርባ ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በሠንሠለት ተያይዘው ለሞት የተዘጋጁ ሲሆኑ አርባ ሺህ ያህሎቹ ደግሞ በጥምጣም ታስረዋል፡፡ በጦሩ ውስጥ ሰማኒያ ሺህ  ፈረሠኞች እና ሰማኒያ ሺህ ያህል እግረኛ ተካተዋል፡፡

የሙስሊሞች ቁጥር መጀመሪያ ላይ 27 ሺህ ያህል የነበረ ሲሆን ኻሊድ ዘጠኝ ሺህ ወታደር ይዞ  ከተቀላቀላቸው በኋላ ቁጥራቸው ወደ ሠላሣ ስድስት ሺህ ከፍ ሊል ችሏል፡፡

ኻሊድ ጦሩን ይዞ ወደ ዋናው ሙስሊም ጦር ከመቀላቀሉ በፊት የሙስሊም አመራሮች እያንዳንዳቸው አቡበክር አስስዲቅ ባስቀመጡላቸው አቅጣጫ ብቻ ነበር የሚዋጉት፡፡ ሩሞች አንድ ላይ ተሠባስበው ለወሣኙ ፍልሚያ ሲቀርቡ ግን ሙስሊሞቹም በአንድ ላይ በመሠባሰብ ሠልፍ ያዙ፡፡ ይህንንም ያደረጉት በመካከላቸው አንዳች የሥራ ድርሻ ክፍፍል ስምምነት ሣያደርጉ ነበር፡፡ ኻሊድም እንዲህ አላቸው ‹ዛሬ ቀኑ የአላህ ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ውስጥ አንድም ሰው ሊኩራራም ሆነ ድንበር ሊያልፍ አይገባውም፡፡ ትግላችሁን ጥርት ባለ መልኩ አድርጉ፡፡ በሥራችሁም የአላህን ፊት ብቻ ፈልጉ፡፡ የዛሬው ቀን ከኋላው ያለው ለሱ ነው፡፡ በተደራጀና በተጠናከረ ሁኔታ ላይ ያሉትን ሰዎች በመከፋፈልና በመበታተን አትዋጉት፡፡ ይህ አይበቃምም አያስፈልግምም። ከናንተ ኋላ ያለው (ኸሊፋው) ያላችሁበትን ሁኔታ ቢያውቅ አሠላለፋችሁን ይቀይር ነበር፡፡ ባትታዘዙበትም ትክክል ነው ብላችሁ የገመታችሁትን ነገር ሥሩ፡፡›

ኻሊድ ይህን ያሉት አቡብክር ከምንም በላይ የሚያስጨንቃቸው የብዙሃኑ ጥቅም ስለሆነ አሁን ሙስሊሞች ያሉበትን ሁኔታ በቅርበት ቢያውቁ ኖሮ አሠላለፋቸውን ቀድሞ ከነበረበት መልኩ ሊቀይሩ እንደሚችሉ እርግጠኛ በመሆን ነበር፡፡ አመራሮችም ቢሆኑ የደመነፍስ ጉዞ እንዲጓዙ አይፈቅዱላቸውም፡፡

ከዚያም ኻሊድ በዚህ ቁጥሩ እጅግ ግዙፍ በሆነው የጠላት ጦር ላይ እንዴት ድል መቀዳጀት እንደሚቻል እጅግ ጥሩ ነው ያለውን ስልት አቀረቡ፡፡ እንዲህ አላቸው ‹ተሰብሰቡና እንደ አንድ ወታደር ሁኑ፡፡ ወደናንተ የሚወረወረውን የከሀዲያን ማዕበል በሙስሊሙ ማዕበል መልሱ፡፡ አላህ ይረዳችኋል፡፡ አላህ የሚረዱትን ይረዳል፡፡ የካዱትን ያዋርዳል፡፡ በቁጥር በማነሣችሁ አይደለም የምትሸነፉት፡፡ በርካታ አሥር ሺዎችም ሆኑ ከዚያ በላይ ያሉት የሚሸነፉት በሚሠሩት ወንጀል ምክኒያት ነው፡፡ ስለሆነም ከወንጀል ተጠንቀቁ፡፡ በየርሙክ ጎን ለጎን ሆናችሁ በጥንካሬ ተሰብሰቡ፡፡ እያንዳንዳችሁ ጓደኛችሁን አጥብቃችሁ ያዙ፡፡› (2)

ሰዎች ለውጊያ መስመር ሠርተው እንደቆሙ አንድ ሰው መጣና ለኻሊድ ‹ሩሞች ምንኛ በዙ ሙስሊሞችስ ምንኛ አነሱ!› አለው። ኻሊድም ‹ሩሞች ምንኛ አነሱ ሙስሊሞች ምንኛ በዙ! የሠራዊት ብዛት የሚለካው በድል ነው፡፡ ማነስም በሽንፈት ነው እንጂ በቁጥር ብዛት አይደለም …› በማለት መለሰለት፡፡

ምንም እንኳ ኻሊድ በብዙ እጥፍ ከሚበልጠው 240 ሺህ ጦር ጋር ፊት ለፊት ቢፋጠጥም በዓለማዊው የውትድርና ት/ቤት ሣይሆን በነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የውትድርና ማዕከል ነውና ያደገው ምንም ባይመስለው የሚገርም አይሆንም፡፡ ድል ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መሆኑን ያልተረዱ ሰዎች አላህንና የሱን መሻት ከሚፈሩት በላይ ጠላቶቻቸውን ፈርተው ይንቀጠቀጣሉ፡፡

ይህ ‹የበላይነቱ ለኛ ነው› የሚለው ስሜት የጦሩ መሪ የኻሊድ ብቻ አልነበረም፡፡ በመሠረቱ የሙስሊሞች አስተሣሰብ በአንድ ሰው መኖር አሊያም መሞት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ መሪ ቢሞትም ቢኖርም የሙስሊሙ ዓላማ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ በመሆኑም ለውጊያ ዝግጁ የሆኑ 36ሺህ ሙስሊሞች በዚህ ግዙፍ ሠራዊት ላይ ድል እንደሚቀዳጁ እርግጠኞች ነበሩ፡፡ በወቅቱ ዒክሪማ ኢብኑ አቢ ጀህል በፍልሚያው ሜዳ ላይ ሆኖ እንዲህ ብሎ ነበር ‹የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በሁሉም የውጊያ ሜዳዎች ላይ ተፋልሜያለሁ፡፡ ዛሬ ግን ከናንተ እሸሻለሁ፡፡› ካለ በኋላ ለመሞት ከሱ ጋር ማን ቃልኪዳን ሊጋባ እንደሚችል ተጣራ፡፡ አልሃሪስ ኢብኑ ሂሻምንና ዲራር ኢብኑ አልአዝወርን ጨምሮ አራት መቶ የሚሆኑ ሙስሊሞችና ፈረሠኞች ቃልኪዳን ተጋቡ፡፡

ከዚህ ትልቅ ጦርነት ጀርባ ታላቁ ኸሊፋ አቡበክር አስስዲቅ ነበሩ፡፡ ከጀርባቸው በመሆንም በጦርነቱ ላይ ያነሣሷቸው፣ ያበረታቷቸውና ያሞጋግሷቸው ነበር፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በየጊዜው እያንዳንዱን ሰው በጥልቀት ይገመግሙ ነበር፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የሙስሊሞች ሠራዊት ከወንጀል ሁሉ ንፁህ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ኻሊድ ኢብኑ አልወሊድ በራሱ ሀሣብ ተነሣስቶ የሙስሊሙን ጦር ትቶ በድብቅ ሀጅ አድርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ ምንም እንኳ ኻሊድ በድል ጎዳና ላይ የነበረ ቢሆንም ከኸሊፋው አቡበክር ወቀሣ አላመለጠም፡፡ እንዲህ ብለውት ነበር፡፡ ‹የዚህ ዓይነቱን ድርጊት ዳግም እንዳትፈፅም፡፡ አላህ ቢሰብርህ የሰዎች ስብስብ ሊጠግንህ አይችልም፡፡ የአላህ እገዛ ካለም ማንም ሊያሸንፍህ አይችልም፡፡ የሱለይማን አባት ሆይ! ውስጥህን በማሣመሩና ወደፊት በመራመዱ ላይ በርታ፡፡ ሙላ አላህ ይሞላልሃል፡፡ በራስ መደነቅ ውስጥህ አይግባ ትከስራለህ፡፡ ለአላህ ተገቢ የሆነውንም ምስጋና ለራስህ አታድርግ አደራ፡፡ እሱ የምንዳ ባለቤት ነውና፡፡› (3)

አቡበክር የጦርቱን ውጤት በመጠበቅ ላይ ሣሉ በሽታ ጣላቸውና ከ15 ቀናት ህመም በኋላ ህይወታቸው አለፈ፡፡ ህመሙ እጅግ ጠንቶባቸው በነበረበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳን ስለ ኢስላም እና ሙስሊሞች ሁኔታ ከመጨነቅ አልቦዘኑም ነበር፡፡ ከመሞታቸው በፊት  ዑመር ኢብኑ አልኻጧብን አስጠርተው ሲመጣ እንዲህ አሉት፡፡ ‹ዑመር ሆይ! የምልህን ስማ፡፡ ከዚያም ያልኩህን ተግብር፡፡ እኔ ዛሬውኑ እሞት ይሆናል ብዬ እከጅላለሁ፡፡ (ቀኑ ሰኞ ነበር)፡፡ የሞትኩ እንደሆነ ከሙሰና ጦር ጋር ቶሎ ትሄዱ ዘንድ አታቆዩኝ፡፡ የደረሳባችሁ ችግርም ከሃይማኖት ጉዳያችሁና ከጌታችሁ ትእዛዝ አያዘናጋችሁ፡፡ በርግጥ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሲሞቱ አይቻቸዋለሁ፡፡ እኔም ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር፡፡ የሰው ልጅ በርሣቸው ሞት እንደተጎዳ በማንም አልተጎዳም፡፡ ወላሂ ከአላህ እና ከመልእክተኛ ውጭ ብሆን ኖሮ በተዋረድን እና በተቀጣን እንዲሁም መዲናም በእሣት በተቀጣጠለች ነበር፡፡ …› (4)

አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በኸሊፋነት ዘመናቸው መጀመሪያ መዲና ሆነው ከሁለት እጅግ ጠንካራና አደገኛ ሀይሎች ያደረጉት ይህ ጦርነት ለስድስት ወር ያህል የዘለቀ ነበር፡፡ ወቅቱንም በመንግስት ሥራዎችና ከራሣቸው የንግድ ሥራ ጋር አሣልፈውታል፡፡ ኋላ ላይ ግን የሙስሊሙ ጉዳይ ሰፊ ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን በመገንዘብ ‹ወላሂ ንግድ እና የሰዎች ጉዳይ አብረው የሚሄዱ አይደሉም፡፡ ጉዳዮቻቸው ጊዜ ሰጥቶ ማየትን ይፈልጋሉ፡፡ ለቤተሰቦቼም ቢሆን የሚያብቃቃቸው ነገር የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡› በማለት መተዳደሪያቸው የነበረውን ንግድ በመተዋቸው ከሙስሊሞች ገንዘብ ለራሣቸውና ቤተሰቦቻቸው በቀን በቀን የሚበቃቸው ያህል ተመደበላቸው፡፡ በየጊዜው ሀጅ እና ዑምራም ያደርጉ ነበር፡፡

በሙስሊሙ ግምጃ ቤት ላይ ሀላፊ የሆኑት በየአመቱ ስድስት ሺህ ድርሃም እንዲመደብላቸው አደረጉ፡፡ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስም በዚሁ ደሞዝ ኖሩ፡፡ ሞት አፋፍ ላይ በደረሱ ጊዜም እንዲህ አሉ ‹ ከሙስሊሞች ገንዘብ እኛ ዘንድ ያለውን መልሱላቸው። እኔ ከዚህ ገንዘብ አንዳችም መንካት አልፈልግም፡፡ ከዚህ ቀደም የወሰድኩትን ገንዘብ በዚህ በዚህ ሥራ ላይ አውዬዋለሁ፡፡› በዚህ መልኩ አቡበክር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በሙስሊሞች ጉዳይ ላይ ያሣለፉትን ጊዜ ሁሉ ያለ አንዳች ክፍያ ምንዳውን ከአላህ ዘንድ በመተሣሰብ ብቻ አደረጉት፡፡ አላህ ይውደድላቸው፡፡

ታሪኩ ይቀጥላል፡፡ አላህ ካለ በክፍል አራት እንመለሣለን፡፡

የታሪኩ ምንጮች

[1].   ታሪኽ አጥ ጦበሪይ  ቅ.2 ገጽ 587

[2].   ታሪኽ አጥ ጦበሪይ  ቅ.2 ገጽ 594

[3].   ታሪኽ አጥ ጦበሪይ  ቅ.2 ገጽ 602

[4].   ታሪኽ አጥ ጦበሪይ  ቅ.2 ገጽ 607

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here