ጦልሐ ቢን ኡበይዱላህ – ህያው ሰማዕት

0
3793

ታሪኩ ባጭሩ

ጦልሐ፣ የኡበይዱላህ ልጅ፣ የኡስማን ልጅ፣ የአምር ልጅ፣ የከእብ ልጅ፣ የተሚም ልጅ፣ የሙራህ ልጅ፣ የከእብ ልጅ፡፡ ከአላህ መልእክተኛ ጋር ሙራህ ቢን ከእብ በተባለ አያታቸው ላይ፤ ከአቡበክር ጋር ደግሞ በከእብ ቢን ሰእድ ዘር ሀረግ ይገናኛሉ፡፡ የጦልሐ እናት ሰህባህ ቢንት ሐድረሚ ትባላለች፡፡

ኢብን ደሐክ እንደዘገቡት ጦልሐ ቢን ዑበይዲላህ እንዲህ ሲል አውግቷል፡-

የኡሁድ ዘመቻ እለት የአላህ መልእክተኛ “በጎው ጦልሐ”፣ በአሺረህ ዘመቻ ላይ ደግሞ፡- “ጦልሐቱል ፈያድ”፣ እንዲሁም በሁነይን ዘመቻ ጊዜ፡- “ጦልሐቱል ጀዋድ” በሚሉ ቅጽሎች ጠርተውታል፡፡ ጦልሐ በጣም ብልህ ነበሩ፡፡ ስለ አሰላለማቸው እንዲህ ሲሉ አውግተዋል፡-

ከበስራ ገበያ ተገኘሁ፡፡ አንድ መነኩሴ ከቤተ አምልኮው ውስጥ ሆኖ፡- ‹‹ከገበያተኞች መሐል ከሐረም (መካ) የመጣ ሰው ካለ ጠይቁ፡፡›› አለ፡፡ “እኔ የመጣሁት ከዚያ ነው” አልኩ፡፡ “አህመድ ተከሰተን?” አለ፡፡ “አህመድ ማን ነው?” ስል ጠየቅኩት፡፡ “ቢን አብደላህ፣ ቢን አብዱል ሙጦሊብ፣ ነብይ በሚሆን ጊዜ መጠሪያ ስሙ ይህ ሲሆን፣ የመጨረሻው ነብይ ነው፡፡ መነሻውም ሐረም መካ ነው፡፡ የተምር ዛፍና ጥቋቁር አለቶች ወዳሉባት ምድረ በዳ መሬትም ይሰደዳል፡፡ ፈጥነህ ተከተለው፡፡” አሉ፡፡ ንግግሩን ከልቦናዬ ውስጥ ገባ፡፡ ፈጥኘም ወደ መካ ተመለስኩ፡፡ አዲስ የተከሰተ ነገር እንዳለ ስጠይቅም፡- “ታማኙ ሙሐመድ ቢን አብደላህ ነብይ ነኝ እያለ ነው፡፡ አቡበክር ተከታዩ ሆኗል፡፡” አሉኝ፡፡ እንዲህ ስል ከራሴ ጋር አወጋሁ፡-

“በአላህ እምላለሁ፣ ሙሐመድና አቡበክር በመጥፎ ነገር ላይ አይሰማሙም፡፡ ሙሐመድ እድሜው አርባ ዓመት ደርሷል፡፡ ከዚህ ቀደም ውሸት ሰምተንበት አናውቅም’ በሰዎች ላይ ለመዋሸት ያልደፈረ በአላህ ላይ ለመዋሻት አይደፍርም፡፡”

ከዚያም ወደ አቡበክር ሄድኩ፡፡ “ይህን ሰው ተከተልከውን?” ስል ጠየቅኩት፡፡ “አዎ፣ አንተም ሂድና አግኘው፡፡ ተከተለውም፡፡ ወደ እውነት ነው የማጣራው፡፡” አለኝ፡፡ “ጦልሐ ለአቡበክር መነሱኬው የነገረውን አወጋቸው፡፡ ተያይዘው ወደ አላህ መልእክተኛ ሄዱ፡፡ እስልምናንም ተቀበሉ፡፡ በጉዞው ያጋጠመውንም ነገራቸው፡፡

ነውፈል ቢን ኹወይሊድ የአቡበክርንና የጦልሐን መስለም ሲሰማ ሁለቱንም ያዛቸው፡፡ በአንድ ገመድም ጠፈራቸው፡፡ የበኒ ተሚም ጎሳ አልታደጋቸውም፡፡ ነውፈል “የቁረይሽ አንበሳ” በሚል ቅጽል ነበር የሚታወቀው፡፡ ከዚህ ክስተት የተነሳ አቡበክር እና ጦልሐ “ተጣማሪዎች” ተብለው ተጠሩ፡፡ ጦልሐ በዚህ አኳኋን እስልምናን በመቀበል ቀዳሚ ሆነ፡፡ በእርግጥ የሰፊ ንግድና የብዙ ሐብት ባለቤት ነበር፡፡ ግና በበጎ ነገር ሌሎችን ቀደመ፡፡

የኡሁድ ንስር

በኡሁድ ዘመቻ ቁረይሾች በከፍተኛ ሁኔታ ተዘጋጅተው በነቢዩና (ሰዐወ) በተከታዮቻቸው ላይ ተመሙባቸው፡፡ በታላቁ የበድር ዘመቻ የደረሰባቸውን ብርቱ ሽንፈትና ውድመት ለመበቀል ቋምጠዋል፡፡ በዚህ ዘመቻ ድል ማግኘት እንዳለባቸውም ወስነዋል፡፡ ለዚህም ሲባል ከሙስሊሞች በተሰነዘረባቸው ብርቱ በትር ተስፋ ያልቆረጡ ጽኑና ጀግና ጦረኛቻቸውን አሰልፈው በሙስሊሞች ላይ ቁጣቸውን አዘነቡ፡፡ ይህም ሆኖ በመጀመሪያ ድል አልቀናቸውም፡፡ የሙስሊሞችን ጠንካራ ጥቃት መቋቃምም ሳይችሉ ቀርተው፣ በድንጋጤ ተውጠው ከጦርነቱ መስክ አፈገፈጉ፡፡ ሙስሊሞች በካህድያን ላይ የደረሰውን ውርደት እና ማፈግፈጋቸውን ሲመለከቱ ተቻኩለው መሣሪያ አስቀመጡ፡፡ ምክንያቱም የጦርነቱ ውሎ አድክሟቸው አካላቸው ዝሏል፡፡ ከጋራው ላይ ሆነው ጠላትን በቀስት እንዲከላከሉ የተመደቡ ቀስተኞችም ከምርኮው የድርሻቸውን ለማግኘት ስፍራቸውን ትተው ወረዱ፡፡

የጥንት ሰዎች እንደሚሉት “ጦርነት ማታለል” ነውና ቁረይሾች በድንገት ከበቧቸው፡፡ የጦርነቱን ልጓምም ተቆጣጠሩት፡፡ በዚህ የጦርነት ረመጥ ውስጥ ከሁለቱም ወገኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገደሉ፡፡ ሙስሊሞች በተፈጠረው ድንገተኛ ነገር እና በጠላት ፈጣን እና ጠንካራ ጥቃት ግራ ተጋቡ፡፡

በዚህ ፈታኝ ወቅት ጦልሐ የአላህን መልእክተኛ ተመለከተ፡፡ ነቢዩ በአደጋ ተከበዋል፡፡ ሰይፎች ወደርሳቸው ዞረዋል፡፡ የተራቡ ውሾች ሊበሏቸው አሰፍስፈዋል፡፡ በሁሉም አቅጣጫዎች የፈረሶች ድምጽ ያስገመግማል፡፡ ወንጀለኛ እጆች ሊያጠቋቸው ተዘርግተዋል፡፡ ግና አንድ ሐይል ይህን የጠላት ጦር ሰንጥቆ መጣ፡፡ ነብዩንም ከእኩያን ጥቃት ታደገ፡፡ ይህ ሐይል በአንድ ብርቱና ጀግና ሰው የተመሰለ ነው፡፡ ያ ሰው ጦልሐ ቢን ኡበይዲላህ ይባላል፡፡ በግራ እጁ የአላህን መልእክተኛ ያዘ፡፡ ወደ ደረቱም አስጠጋቸው፡፡ የሰይፉን እጀታ በቀኙ ይዞም ከወዲያ ወዲህ ያወናጭፈው ጀመር፡፡ እርሱ ሰይፉን ባንቀሳቀሰ ቁጥር አንገቶች ከአካላቸው እየተነጠሉ ልክ እንደ ዛፍ ቅጠል በዙሪያው ረገፉ፡፡

ሕያው ሰማዕት

አቡበክር የጦልሐን የኡሁድ ውሎ በሚያምር ቋንቋ ገልጸውታል፡፡ ልጃቸው አኢሻ ባስተላለፉት ዘገባ እንዲህ ብለዋል፡-

አቡበክር የኡሁድን ዘመቻ ሲያወሱ እንዲህ ይሉ ነበር፡-

“ቀኑ የጦልሐ ቀን ነበር፡፡ ከነቢዩ ዘንድ ቀድሜ ደረስኩ፡፡ ለኔና ለአቡኡበይዳህ ወንድማችሁን እርዱት” አሉን፡፡ ጦልሐን ማለታቸው ነበር፡፡ ከሰባ ቦታዎች ላይ በጦር፣ በቀስትና በሰይፍ ተወግቶ፣ ጣቶቹም ተቆርጠው አገኘነው፡፡ እገዛም አደረግንለት፡፡”

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከዚያ ቀን በኋላ ስለ ጦልሐ ሲናገሩ፡- “ሞቶ በምድር ላይ የሚራመድ ሰው ማየት የፈለገ ጦልሐ ቢን ኡበይዱላህን ይመልከት።”  ይሉ ነበር፡፡ አላህ ጦልሐንና መሰሎቹን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡-

مِّنَ الْمُؤْمِنِينَ رِجَالٌ صَدَقُوا مَا عَاهَدُوا اللَّهَ عَلَيْهِ ۖ فَمِنْهُم مَّن قَضَىٰ نَحْبَهُ وَمِنْهُم مَّن يَنتَظِرُ ۖ وَمَا بَدَّلُوا تَبْدِيلًا

“ከአማኞቹ በእርሱ ላይ ለአላህ ቃል ኪዳን የገቡበትን በእውነት የፈጸሙ ወንዶች አልሉ፡፡ ከነርሱም ስለቱን የፈጸመ (ለሃይማኖቱ የተገደለ) አልለ፤ ከነርሱም ገና የሚጠባበቅ አልለ፡፡ (የገቡበትን ቃል) መለወጥንም አልለወጡም።” (አል አህዛብ: 23)

የጦልሐ አስተዋጽኦ ቁሳዊ ብቻ አልነበረም፡፡ አላህ የሰጠውን ገንዘብ ለዳእዋው በገፍ እንደቸረው ሁሉ ነፍሱንም ችሯል፡፡ በውጊያው መስክ ከፊት በመሰለፍ የአላህን መልእክተኛና ሐይማኖቱን ከጥቃት ታድጓል፡፡

ነፍሱን የሚቸር በእውነቱ

ሰዎች ሁሉ ሲሰስቱ

የነፍስ የሕይወት ሰጦታ

አቻ የለሽ ችሮታ

ጦልሐ የምርጥ ስብእና ባለቤት ነው፡፡ እርሱ አብዱረህማን ቢን አውፍና ኡስማን ቢን አፋን በዘመነ መሐይምነት ባለጸጋዎች ነበሩ፡፡ አንዳች ማሕበራዊ ቦታ ያለው ሰው በተለምዶ ሐብቱንና ክብሩን ከአደጋ ላይ በማጥል ጉዳይ ውስጥ ላለመሳተፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ስብእናዎች ግን ለዱንያ ሳይጓጉ እስልምናን ተቀበሉ፡፡ የዚህች ዓለም ብልጭልጭ አላታለላቸውም፡፡ ለመጭው ዓለም ስኬት ተጠቀሙበት፡፡ ለእስልምና ዳእዋ መሳካት ሐብታቸውን ያለ መሰሰት መጸወቱ፡፡ ይህ ከመሆኑ አኳያ አላህ በመጭው ዓለም ጸጋውን ያለ ገደብ ቢሰጣቸው የሚገርም አይደለም፡፡

በመጭው ዓለም ጀነት እንደሚገቡ የተሰጣቸው ምስክርነት ብቻ ለውለታቸው በቂ ምላሽ ነው፡፡

የጦልሐ ቸርነት

የጦልሐ ቸርነት እስከ ጥግ የደረሰ ነበር፡፡ ይህን ባህሪውን ከባለቤቱ ከሱዓዳ ቢንት ዓውፍ በላይ የሚነግረን የለም፡፡ እንዲህ ስትል አውግታለች፡-

አንድ ቀን ከጦልሐ ዘንድ ስገባ በሐሳብ ተውጦ አገኘሁትና፡- “ምን አገኘህ?” ስል ጠየቅኩት፡፡ “ገንዘቤ በጣም በዝቶ አሳሰበኝ፡፡” አለኝ፡፡ “ይህን ያህል የሚያስጨንቅህ ከሆነ ለሰዎች አካፍለው” አልኩት፡፡ ተነሳና ሰዎችን ጠራ፡፡ አንዲት ዲርሃም (ቤሳቤስቲን) ሳያስቀርም ሁሉንም አደላቸው፡፡

ጃቢር ቢን አብደላህ የጦልሐን ቸርነት ሲያወሳ እንዲህ ይላል፡-

“ንዘብ ሳይለምኑት በመስጠት እንደ ጦልሐ ቸር አላየሁም፡፡ ለቤተሰቦቹና ለዘመዳቹ በጣም ደግ ነበር፡፡ ብዙ ቢሆኑም ሁሉንም ይቀልባቸዋል፡፡ ይህን በተመለከተ ከበኒ ተሚም ጎሳ ውስጥ የማይረዳው አንድም ግለሰብ እንደሌለ ተነግሮለታል፡፡ እያንዳንዱን አባወራ ከነቤተሰቡ ይደጉመዋል፡፡ ያላገቡትን ያጋባል፡፡ ድሆችን ያገለግላል፡፡ የባለ እዳዎችን እዳ ይከፍላል፡፡”

አንድ ሰው ከጦልሐ ቢን ዑበይዲላህ ዘንድ መጣና ገንዘብ ይደጉመው ዘንድ ጠየቀው፡፡ የዝምድና ትስስር እንዳላቸውም አጫወተው፡፡ “ይህ ከአሁን ቀደም አንድም ሰው ያልነገረኝ የዝምድና መስመር ነው፡፡ ዑስማን ቢን አፋን 3 ሺህ (ዲርሃም) ሊገዛኝ የጠየቀኝ መሬት አለ፡፡ ከፈለግክ ውሰደውና ተጠቀምበት፡፡ ከፈለግኩም ለዑስማን በ3 ሺህ ዲርሃም ልሽጠውና ገንዘቡን ልስጥህ፡፡” አለ፡፡ ሰውየውም “ገንዘቡን ብትሰጠኝ ይሻለኛል” አለ፡፡ ገንዘቡን ሰጠው፡፡

ሕልፈተ ሕይወት

ጦልሐና ዙበይር ከዓሊ ጋር ተወዛገቡ፡፡ ውዝግባቸውም ወደ አሳዛኝ እርምጃ ተሸጋገረ፡፡ ዓሊ ለሰላም ጉጉ በመሆናቸው እንዳች ነገር ለሁለቱም አስታወሷቸው፡፡ እነርሱም ሳይከራከሩ ተቀበሏቸው፡፡ ጦልሐ በዓሊ ንግግር ልቡ ተነካ፡፡ ዓሊ እንዲህ ነበር ያሉት፡-

“የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ማለታቸውን አልሰማህምን? አላህ ሆይ፣ ዓሊን የተወዳጀን ተወዳጀው፡፡ እርሱን ጠላት ያደረገን ጠላት አድርገው፡፡”

ከኔ ጋር ቃል ኪዳን (በይዓ) የፈጸምከው ቀድመህ ነበር፡፡ ግና ቃል ኪዳንህን አፈረስክ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

إِنَّ الَّذِينَ يُبَايِعُونَكَ إِنَّمَا يُبَايِعُونَ اللَّهَ يَدُ اللَّهِ فَوْقَ أَيْدِيهِمْ ۚ فَمَن نَّكَثَ فَإِنَّمَا يَنكُثُ عَلَىٰ نَفْسِهِ ۖ وَمَنْ أَوْفَىٰ بِمَا عَاهَدَ عَلَيْهُ اللَّهَ فَسَيُؤْتِيهِ أَجْرًا عَظِيمًا

“እነዚያ ቃል ኪዳን የሚጋቡህ ቃል ኪዳን የሚጋቡት አላህን ብቻ ነው፡፡ የአላህ እጅ (ኀይሉ) ከእጆቻቸው በላይ ነው፡፡ ያፈረሰም ሰው የሚያፈርሰው በነፍሱ ላይ ብቻ ነው፡፡ በእርሱ ላይ አላህን ቃል ኪዳን የተጋባበትን የሞላም ሰው ታላቅ ምንዳን በእርግጥ ይሰጠዋል፡፡” (አልፈትህ: 10)

ጦልሐ ይህን የአሊ ቃል ሲሰማ “አላህን ምህረት እለምናለሁ” አለና ተመለሰ፡፡ መርዋን ቢን ሐከም አየው፡፡ በቀስት አስወነጭፎም ገደለው፡፡

አኢሻ እንዲህ ብለዋል፡-

ከቤት ውስጥ ነበርኩ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ከሳሎን ተቀምጠዋል፡፡ ጦልሐ ቢን ኡበይዲላህ መጣ፡፡ በኔና በነርሱ መካከል ግርዶ አለ፡፡ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ አሉ፡- “ሞቶ በምድር ላይ የሚራመድ ሰው ማየት የፈለገ ጦልሐን ይመልከት፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here