መጠነኛ ቅኝት ስለ ኹለፋኡ ራሽዲን ዘመን (ክፍል 1)

0
7510

“ኹላፋኡ ራሽዲን” /የነቢዩን መሞት ተከትሎ ሙስሊሙን ህዝብ የመሩ ቅን መሪዎች/ የሚባለው ዘመን በሂጅራ አቆጣጠር ከ 11 ኛው አመት ጀምሮ እስከ 41 ኛው አመት ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያጠቃለል ሲሆን ይህም አምስቱ ኸሊፋዎች /ቅን መሪዎች/ ማለትም አቡበክር፣ ዑመር፣ ዑስማን፣ ዐሊ እና ሀሠን ህዝበ ሙስሊሙን ያስተዳደሩበት ዘመን ነው (የሁሉንም መልካም ሥራ አላህ ይውደድላቸው)።

የሚጀምረው ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሞት በኋላ በእግራቸው በተተኩት በአቡበክር አስ ስዲቅ በረቢዐል አወል 11ኛ አመት ላይ ሲሆን ያበቃውም የዐሊ ኢብኑ አቢጧሊብን ሞት ተከትሎ የዐሊ ልጅ ሀሠን ለሙዓዊያ በፈቃደኝነት ሥልጣን በለቀቁበት በረቢዐል አወል 41ኛ አመተ ሂጅራ ላይ ነበር። በዚህም ጊዜ በነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የህይወት ዘመን በዐረቢያ ደሴት ብቻ ተወስኖ የነበረው የሙስሊም መንግስት ግዛት እጅግ ሰፍቶ የዐረቢያን ደሴት ጨምሮ የሻምን ሀገር (የዛሬዎቹን ሶሪያን፣ ፍልስጤምን፣ ዮርዳኖስን) ዒራቅና ኢራንን፣ ግብፅን፣ ሞሮኮን፣ አፍጋኒስታንን፣ ከኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች ጀርባ ድረስ የዘለቀ ሲሆን ከፊል ህንድንም አካልሎ ነበር ።

ዘመኑ ከኢስላማዊ መንገድ አንፃር ያ ነቢዩ ሰላለለሁ ዐለይህ ወሠለም

عليكم بسنتي وسنة الخلفاء الراشدين المهديين من بعدي وعضوا عليها بالنواجذ

“አደራችሁን በሱናዬ /ፈለጌ/ እና ከኔ በኋላ በሚተኩ ተተኪ ቅን መሪዎች /ኹከፋኡ ራሽዲኖች/ ይሁንባችሁ። (ይህን መንገድ) በክራንቻችሁ ነክሣችሁ ያዙ” [1]

ያሉትን ነቢያዊ ዘመን ተከትሎ የመጣ በመሆኑ ለየት ያለና ምርጥ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

ለመንደርደሪያ ይህን ያህል ካልን ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ከዚያ ምርጥ ዘመን ልንቀስም የምንችለውን ትምህርት አጠር ባለ መልኩ ለመቃኘት አንሞክራለን። ከመጀመሪያው ኸሊፋ እንጀምር ፡-

አቡበክር (አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና)

ከርሣቸው ሞት በኋላ ሙስሊሞች ትልቅ ክፍተት የተፈጠረ መስሎ እንዳይሠማቸው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሙስሊሞችን ጉዳይ ይመሩና የኸሊፋነቱን /ተተኪነቱን/ ሸክም ለመቀበል ዘግጁ ይሆኑ ዘንድ አቡበክርን አለማምደዋል ።

የአላህ መልእክተኛ ሰለለሁ ዐለይህ ወሠለም አቡበክርን ለኸሊፋነት እጩ አድርገው ያቀረቡበት ምክኒያት ነበራቸው ። ለረጅም ዘመናት የርሣቸው ወዳጅ የነበሩ ከመሆናቸው ጋር ከሌሎች ሰሃቦች በተሻለ መልኩ ሀላፊነቱን መሸከም የሚችሉበትን ጠንካራ ጎኖቻቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ። እያንዳንዱን ትንሽ ትልቁን እንቅስቃሴውን ገምግመዋልና አቡበክር ትላልቅ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው እንዴት እንደሚፈቱ፤ ከባድ መሠናክሎችን በምን መልኩ እንደሚያልፉና የመንግስት ጉዳዮችን እንዴት በጥበብና በሥርኣቱ እንደሚያስኬዱ ያውቁ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በነዚያ ከነቢዩ ጋር ባሣለፏቸው ዘመናት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይ ወሠለም ከሌሎች አካላት ከጠላትም ይሁን ከወደዳጅ ጋር እንዴት እንደሚኗኗሩ አይተዋል ተምረዋል ልምድም ቀስመዋልና ነው።

ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በተለይ በታመሙበትና በህይወት በቆዩበት መጨረሻ አካባቢ የሠሩት ነገር አቡበክር ኢማም ሆኖ ሙስሊሞችን ሰላት ያሰግድ ዘንድ ሀላፊነት መስጠት ነበር። በዚህም በአንድ ወቅት “አቡበክርን እዘዙት ሰዎችን ሰላት ይምራ” በማለት አዘዋል [2]። አንድ ቀን አቡበክር በቀሩበት ቀን ግን ዑመር ረዲየሏሁ ዐንሁ ተነስቶ ሰላት ያሰግድ ጀመር ። ዑመር “አላሁ አክበር!” ብሎ ወደ ሰላት በገባ ጊዜ ነቢዩ ድምፁን ሰሙና “አቡበክር የለም እንዴ?” በማለት በመጠየቅ “ይህንን ድርጊት አላህና ሙስሊሞች አይፈቅዱትም፤ ይህንን ድርጊት አላህና ሙስሊሞች አይፈቅዱትም” በማለት የተናገሩበት ሁኔታ ነበር።

ከዚህ በኋላም ቢሆን የሙስሊሞችን ጉዳይ እንዲፈፅሙ በነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የተወከሉ ሲሆን ሰዎች ነቢዩን በሚያጡበት ጊዜም ከርሣቸው ይጠይቁ የነበሩትን ነገሮች ከአቡበክር እንዲጠይቁ ወደሱ መርተዋል። በአንድ ወቅት አንዲት ሴት ለጉዳይ ወደነቢዩ በመጣች ጊዜ ተመልሣ እንድትመጣ ከነገሯት በኋላ “እርስዎን ካጣሁስ?” ብላ ስትጠይቃቸው (እርስዎ የሞቱ እንደሆነስ ለማለት በሚመስል መልኩ) “እኔን ካጣሽ ወደ አቡበክር ሂጂ” ብለዋት እንደነበርም ተዘግቧል [3]።

ከመሞታቸው ቀደም ብሎ ትንሽ ሻል ሲላቸው ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በሁለት ሰሃቦቻቸው መካከል ተደግፈው ወደ መስጊድ መጡ። አቡበክርም እርሣቸውን ለማስቀደም ብለው ወደኋላ እየተመለሱ መሆኑን ባዩ ጊዜ በቦታው እንዲረጋ በእጅ ምልክት ሰጡትና ከዚያም ከአጠገቡ በመቀመጥ በርሱ አሰጋጅነት የሰገዱበት ሁኔታም ነበር።

በሌላ በኩል የአቡበክርን ደረጃ የሚያመለክቱ ንግግሮችን ለሙስሊሞች ያሠሙ የነበረ ሲሆን በአንድ ወቅት

فإني لا أعلم امرأ أفضل يدا عندي في الصحبة من أبي بكر

“እኔ በወዳጅነት ደረጃ ከአቡበክር በላይ ውለታው የበዛብኝ ሰው የለም” ያሉ ሲሆን

لو كنت متخذاً من أمتي خليلاً لاتخذت أبا بكر خليلاً، ولكن أخي وصاحبي

“ከአላህ ውጭ ከህዝቦቼ መካከል ወዳጅ የሚይዝ ብሆን ኖሮ አቡበክርን በያዝኩ ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ወንድሜና ጓደኛዬ ነው …” ብለውም ተናግረዋል [4]።

በዚያው ሰሞን የመስጊዱን ንፅህና ለመጠበቅ ሲባል በሮቻቸው ወደ መስጊድ የሚያስገቡ ጎረቤቶች መግቢያቸውን እንዲዘጉ “እነኚህ በሮች ይየዘጉ የአቡበክር በር ሲቀር” በማለት ያዘዙ ሲሆን እርሣቸው ግን ሁሌም የአላህ መልእክተኛ ዘንድ የሙስሊሞችን ጉዳይ ይዘው ያለ ቀጠሮ ስለሚመላለሱ ስለሚወጡና ስለሚገቡ መግቢያና መውጫ በር መቀየሩ ይከብዳቸው ይሆናል በማለት እንደሆነ ተገምቷል ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም አንድም ቀን “አቡበክር ኸሊፋ ይሁን” በማለት በቀጥታ የተናገሩበት ሁኔታ አልታየም ነበር። ይህም ሙስሊሞች በጉዳዮቻቸው የሚቆምላቸውና የሚያስተዳድራቸው የፈለጉትን ሰው ይመርጡ ዘንድ መብታቸውንና ፍላጎታቸውን ላለመግፈፍ ይመስላል።

በመጨረሻም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሞቱ። ክስተቱም ሙስሊሞችን እጅግ ያስደነገጠ ከመሆኑ የተነሣ ብዙዎች ሁኔታውን መሸከም አልቻሉም ነበር። እራሱን የሣተና አእምሮው የተቃወሰ፤ ተቀምጦ መነሣት ያቃተው፤ ምላሱ ተሣስሮ መናገር ያቃተው፤ ሙሉ በሙሉ መሞታቸውን ክዶ የሚከራከርም የታየበት ክስተት ነበር። ለሰሃቦች የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ማጣት ቀላል ነገር አልነበረምና ነው ህመሙ እንዲህ የከበዳቸው። በዚህ ጊዜ ነበር አቡበክር እውነትም በሙስሊሞች ጉዳይ ለመቆም እጅግ ጠንካራው ሰው መሆናቸውን ያሣዩበት አጋጣሚ የታየው። መሞታቸውን በሰሙ ጊዜ ከመዲና ውጨ ከነበረው ቤታቸው እየተጣደፉ በመምጣት እራሣቸውን በተቆጣጠሩበት ሁኔታ ወደ አላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ቤት በመግባት ፊታቸውን በመግለጥ ሣሟቸውን “እንደው በእናት አባቴ ሞት! ኖረህም ሞተህም ምንኛ አማርክ! …” አሉ ።

ከዚያ ወጡና ዑመርን ሰዎች መሃል ሆኖ ሲጯጫህ አገኙት። እሱም ለአቡበክር እንዲህ አላቸው “አንዳንድ መናፍቃን የአላህ መልእተኛ ሰላለሁ ዐለይህ ወሠለም ሞተዋል” ይላሉ “የአላህ መልእክተኛ ግን አልሞቱም” አላቸው አቡበክርም “አንተ ሰው ተረጋጋ የአላህ መልእክተኛ ሰላሁ ዐለይህ ወሠለም በርግጥም ሞተዋል

إِنَّكَ مَيِّتٌ وَإِنَّهُم مَّيِّتُونَ – وَمَا جَعَلْنَا لِبَشَرٍ مِّن قَبْلِكَ الْخُلْدَ أَفَإِن مِّتَّ فَهُمُ الْخَالِدُونَ

“አንተም ሟች እነሱም ሟች ናቸው” [5] የሚለውንና “ካንተ በፊት ለማንኛውም ሰው ዘላለም መኖርን አላደረግንም ታዲያ አንተ ብትሞት እነሱ ዘውታሪዎች ናቸውን?” [6] የሚለውን የአላህን ቃል አልሠማሀም እንዴ! አሉት ።

ከዚያም ወደ ሚንበር ወጡና አላህን ካመሰገኑና ካወደሱ በኋለ

ألا من كان يعبد محمدا صلى الله عليه وسلم فإن محمدا قد مات، ومن كان يعبد الله فإن الله حي لا يموت

“ሙሀመድን የሚገዛ /የሚያመልክ/ ካለ ሙሀመድ በርግጥ ሞቷል አላህን የሚያመልክ ካለ ግን አላህ ህያው ነው አይሞትም።” በማለት አወጁ። አስከትለውም የአላህን ሱብሃነሁ ወተዓላ ቃል አነበቡ

وَمَا مُحَمَّدٌ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ أَفَإِن مَّاتَ أَوْ قُتِلَ انقَلَبْتُمْ عَلَىٰ أَعْقَابِكُمْ وَمَن يَنقَلِبْ عَلَىٰ عَقِبَيْهِ فَلَن يَضُرَّ اللَّهَ شَيْئًا وَسَيَجْزِي اللَّهُ الشَّاكِرِينَ

“ሙሀመድም ከርሱ በፊት መልእክተኞች በርግጥ ያለፉ የሆነ መልእክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም። ቢሞት ወይም ቢገደል ወደኋላችሁ ትገለበጣላችሁን? ወደ ኋላው የሚገለበጥም ሰው አላህን አንዳች ነገር አይጎዳም። አላህም አመስጋኞቹን በርግጥ ይመነዳል” [7]

በአካባቢው የነበሩ የመዲና ሰዎች ከአቡበክር የሰሙትን አዲስ የሆነባቸው በሚመስል መልኩ የአላህን ቃል ደጋግመው ማለት ጀመሩ። ድንጋጤውም እየቀለላቸው መጣ። ቀስ በቀስም ወደ ቀጥተኛው አመለካከት ተመለሱ። የነቢዩ መሞት እርግጥ መሆኑን ባወቁ ከነቢዩ ውጭ እንዴት ሕይወትን መኖር እንዳለባቸው፤ በመለየታቸው ላይ እንዴት መታገስ እንደሚችሉና ግላዊም ሆነ ማህበራዊ ኑሮአቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸው እራሣቸውን ማለማመድ ያዙ።

መጀመሪያ የታያቸው ነገር የአላህን መልእክተኛ ሰላላሁ ዐለይህ ወሠለም የሚተካና ከሣቸው በኋላ ሙስሊሙን የሚያነቃቃና በጉዳያቸው የሚቆም ሰው መምረጥ ነበር። ይህንንም ያደረጉበት ዋናው ምክኒያት ሰዕድ ኢብኑ ዘይድ እንዳለው አንድም ቀን ያለ ጀመዓ (አንድነት) እንዳይውሉ በመስጋት ነበር ። ሆኖም ግን ለአቡበክር የኸሊፋነቱን ጉዳይ በቀጥታ አልሠጡትም። ይህም ሊሆን የቻለው ነቢዩም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ይህንኑ ጉዳይ በግልፅ ያላስቀመጡ ከመሆኑም በላይ ከላይም እንደተጠቀሰው አንዳንድ ሙስሊሞች በተለይም የመዲና ሰዎች ነቢዩ በተደጋጋሚ የአቡበክርን ደረጃ ያነሱበት ሚስጢሩ ስላልገባቸው ነበር።

የአንሷር /የመዲና ሰዎች/ ሰዎች “ሰቂፈቱ በኒ ሣዒዳህ” በሚባለው ቦታቸው ተሰበሰቡ። ሰዕድ ኢብኑ ዑባዳን ኸሊፋ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይም ተመካከሩ። ይህን ለማድረግ የተነሣሱበት ምክኒያትም ሰዕድ እራሱ እንዳለው

لكم سابقة في الدين، وفضيلة في الإسلام ليست لأحد من العرب إن محمداً صلى الله عليه وسلم لبث في قومه بضع عشرة سنة، يدعوهم إلى عبادة الرحمن، وخلع الأنداد والأوثان، فما آمن به إلا القليل، ما كانوا يقدرون على منعه، ولا على إعزاز دينه، ولا على دفع ضيم، حتى إذا أراد بكم الفضيلة ساق إليكم الكرامة، ورزقكم الإيمان به وبرسوله، والمنع له ولأصحابه، والإعزاز له ولدينه، والجهاد لأعدائه، فكنتم أشد الناس على عدوه، حتى استقامت العرب لأمر الله …وتوفاه الله وهو عنكم راضٍ، وبكم قرير العين

“እናንተ ወደ እምነት በመግባት ቀድማችኋል፤ በኢስላም ውስጥም የትኛውም የዐረብ ጎሣ ያልታደለውን ትልቅ ደረጃ አላችሁ። ምንም እንኳ ነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ህዝቦቻቸውን ወደ አላህ መንገድ እየጠሩ ጣኦታትንና ከአላህ ውጭ የሚገዙትን ነገር ሁሉ እንዲተው አሥራ ምናምን አመት በመካ የቆዩ ቢሆንም ያመነባቸው ጥቂት ሰው ብቻ ነበር። እነሱም ቢሆኑ ሊከላከሉላቸው አልቻሉም፤ ሃይማኖቱም እንዲጠናከር በቂ ድጋፍ ማድረግ አልተቻላቸውም፤ በመጨረሻም አላህ እድለኞች አደረጋችሁና ክብርን ወደናንተ አመጣ። በሱና በመልእክተኛው እንድታምኑ አደረጋችሁ። ከርሣቸውና ከሰሃቦቻቸውም ተከላካይ፤ ዲኑንም ጠባቂ፤ ጠላቶቹንም ተፋላሚ እንድትሆኑ አድርጎ መረጣችሁ። ዐረቦች በሙሉ ቀጥ ብለው ለአላህ ትእዛዝ አስኪያድሩ ድረስ በጠላቶቹ ላይ ጠንካሮች ነበራችሁ … እሣቸውም በናንተ ደስ ተሠኝተው ከናንተ እየወደዱ ሞቱ። [8] የሚለውን በመያዝ ነው።

ከመሃላቸው ኡሰይድ ኢብኑ ሁደይር የአንሷሮችን ሀሣብ ለመግለፅ ወደ አቡበክር ሲመጣ ከሙሃጅሮች ጋር የተሠበሠበ ሆኖ አገኙት። የአንሷሮችን ሁኔታ በነገራቸው ጊዜ አቡበክር አብራዋቸው የነበሩትን ሰዎች “በሉ ወደ ወንድሞቻችን ወደ አንሷሮች /የመዲና ሰዎች/ እንሂድ በዚህ ጉዳይ ላይ እነርሱም ሀቅ አላቸውና።” አላቸው [9]። ካሉበትም ሄደው አገኟቸው ። የወሠኑትንና የደረሱበትን ጉዳይ ባስረዱትና ሀሣባቸውንም ባየ ጊዜ

أنتم يا معشر الأنصار، من لا ينكر فضلهم في الدين، ولا سابقتهم في الإسلام، رضيكم الله أنصاراً لدينه ورسوله، وجعل إليكم هجرته … وإنكم لا تذكرون منكم فضلاً إلا وأنتم له أهل

“እናንተ የአንሷር ሰዎች ሆይ! በዲኑ ውስጥ የነበራችሁን አስተዋፅኦ ማንም መካድ አይችልም። በእስልምና ቀዳሚ መሆናችሁንም እንዲሁ። አላህ ሃይማኖቱንና መልእክተኛውን ትረዱ ዘንድ መርጧችኋል መልእክተኛውም ወደናንተም እንዲሰደዱ ፈቅዷል .. ፤ አንድ መልካም ነገር አይነሣም እናንተ ለዚያ ነገር ተገቢዎቹ ሰዎች የሆናችሁ ቢሆን እንጂ። በማለት ጥንካሬያቸውን አወሣላቸው [10]።

በመቀጠልም እነኚህ ነገሮች ብቻቸውን ኸሊፋነትን ለማግኘት /የነቢዩ ምትክ ለመሆን/ ዋስትና እንደማይሠጧቸው ነገራቸው። ዐረቦች በውስጣቸው ካለ የጎሠኝነት ችግር የተነሣ የነቢዩ ጎሣዎች ለሆኑት ለቁረይሾች ካልሆነ በቀር ለማንም ማደር እንደማይፈልጉም ጭምር አስረዳቸው። በውይይቱ መካከል ከአንሷር የሆነ አንድ ሰው “ከኛም አንድ አሚር ከናንተም አንድ አሚር ይመረጥ” በማለት ሀሣብ ሠጠ። ዑመር አንድ ህዝብ ለሆኑት ሙስሊሞች እንዴት ሁለት አሚር ሊሆን ይችላል በማለት ተቃወመ። የአላህ መልእክተኛ ከዚህ ዓይነቱ ድርጊት ከልክለዋል፤ “ወዮላችሁ በአንድ ዘመን ውስጥ ሁለት ነገሮች አይሰበሰቡም። ወላሂ ነቢያችን ከናንተ ከአንሷሮች ያልሆኑ ሆኖ ሣለ ሌሎች ዐረቦች መሪዎቻቸው ትሆኑ ዘንድ አይቀበሏችሁም። ነቢይነት ከነሱ ውስጥ የተመረጠን ሰው ግን ዐረቦች ለመታዘዝ ፈቃደኞች ናቸው።” [11] አላቸው ።

አቡበክር ንግግራቸው ደገሙ። የአንሷሮቹንም ደረጃ አወሱ። ስለ ኸሊፋነቱም ጉዳይ ለነሱ ያልታያቸውን ነገሯቸው

لقد علمتم أن رسول الله قال: لو سلك الناس وادياً وسلكت الأنصار وادياً سلكت وادي الأنصار، ولقد علمت يا سعد أن رسول الله قال وأنت قاعد: قريش ولاة هذا الأمر، فبر الناس تبع لبرهم، وفاجرهم تبع لفاجرهم، فقال سعد: صدقت، فنحن الوزراء وأنتم الأمراء، فقال أبو بكر: نعم… لا تفاتون بمشورة، ولا تقضي دونكم الأمور..

“ታውቃላችሁ! የአላህ መልእክተኛ ‘ሰዎች በአንድ ሸለቆ ቢገቡና አንሷሮቹ በሌላ ሸለቆ ቢገቡ የአንሷሮች የገቡትን ሸለቆ እገባለሁ’ ማለታቸውን። አንተ ሰዕድ ሆይ! አንተ ተቀምጠህ ባለህበት የአላህ መልእክተኛ ‘ቁረይሾች የዚህ ጉዳይ ተረካቢዎች እነርሱ ናቸው’ ማለታቸውን ታውቃለህ። መልካሞችን መልካሞች ይከተሏቸዋል፤ ክፉዎችንም የሚከተሉ ክፉዎች ናቸው።’ ሰዕድ ‘እውነት ተናገርክ፤ እኛ ሚኒስቴሮች እናንተ ደግሞ መሪዎች ናችሁ’ አለው። አቡበክር በጀ .. አለ ። ቀጥሎም እናንተን ምክክር ላይ የምናስቀራችሁ አይደለንም፤ ነገሮችም ያለናንተ መገኘት አይወሰኑም። አለው ። [12]

አቡ ዑበይዳም እንዲህ በማለት አከሉ “እናንተ አንሷሮች ሆይ! መጀመሪያ ነቢዩን የረዳችሁ እናንተ ናችሁ። መጀመሪያ ያጠፋና ያበላሸ ልትሆኑ ግን አይገባም።” በሺር ኢብኑ ሰዕድ አቡ ኑዕማን ኢብኑ በሺርም ተነሣና እንዲህ አለ “እናንተ የአንሷር ሰዎች ሆይ! ወላሂ ምንም እንኳ ሙሽሪኮችን /አጋሪዎችን/ በመዋጋት እኛ ብልጫውን ቢኖረንም፤ ወደ ሃይማኖቱ ለመግባትም ቅድሚያውን ብንወስድም በዚህ ጉዳይ የፈለግነው ግን የአላህን ውዴታ፣ መልእክተኛውን መታዘዝና ራሣችንንም መጥቀም አስበን እንጂ ሌላ አይደለም። ይህን እንደ ምክኒያት በማቅረብም በሰዎች ላይ ድንበር ማለፍ የለብንም። የዱኒያንም ጥቅም መፈለግ አይኖርብንም። ሙሀመድ ከቁረይሽ ናቸው። ህዝቦቹም ይህ ጉዳይ የሚገባቸውም እነርሱ ናቸው። ወላሂ በዚህ ጉዳይ ላይ ከነርሱ ጋር መጨቃጨቅ እንደሌለብን አምናለሁ። አላህን ፍሩ። ሀሣባቸውን አትቃወሙ፤ አትጨቃጨቋቸውም።” [13]

ከዚያ በኋላ ተፅእኖ ባሣደረው የዑመር ንግግር ነበር ሁሉም ለአቡበክር ኸሊፋነት ቃልኪዳን ለመስጠት ፈቃደኝነታቸውን የገለፁት “በአላህ ይዤችኋለሁ ሰዎችን እንዲያሰግዱ አዘው አልነበረምን?” ሰዎችም “አዎን ወላሂ” አሉ ። “ታዲያ ማናችሁ ናችሁ እርሱን /አቡበክርን/ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ካስቀመጧቸው ቦታ ሊያነሣቸው የሚችል?። እርግጠኛ ነኝ ሁላችንም ይህን አንወድም፤ አላህ ይቅር ይበለን።” አለ። አቡበክር ሊከተል የሚችለው ነገር ከበዳቸውና “አንተ ዑመር ሆይ! ከኔ በላይ ለቦታው ጠንካራውና ተገቢው ሰው አንተ ነህ።” አሉት። ዑመርም እንዲህ በማለት መለሱለት “ያንተ አንዱ ጥንካሬ የኔንም ይጨምራል።” [14]

ይህ ሁሉ የተከሠተው ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በሞቱበት እለት ነበር። በተከታዩ ቀን አቡበክር ከተቀሩትና በቦታው ካልነበሩ ሰዎች በይዓ /ቃልኪዳን/ ለመውሰድ ተቀመጡ። የዐረብ ልኡካንም እስልምናቸውን የቀየሩት ሲቀሩ ተሰባስበው ቃል ኪዳን ለመስጠት መጡ። ስለሁኔታው ሰዒድ ኢብኑ ዘይድ “የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሞቱ እለት በቦታው ነበርክ ወይ?” ተብሎ ተጠየቀ። እሱም “አዎን” አለ። “አቡበክር መቼ ነው ቃልኪዳን የተገባላቸው?” ተባሉ። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በሞቱበት ቀን ነው። “በእለቱ የቀረ ሰው ነበረ ወይ?” ተባለ። “አይ ማንም አልቀረም ሙርተድ /ከነቢዩ ሞት በኋላ ከእስልምናው የወጣ/   ወይንም ሙርተድ ለመሆን የተቃረበ ሲቀር” በማለት መለሠ። [15]

በዚህ ሁኔታ ነበር የመጀመሪያው የሙስሊሞች መሪ የኸሊፋነት ቃልኪዳን የተፈፀመላቸው። ሁኔታው የሙስሊሞች መሪ መሆን ያለበት በላጭ ብልህና በመምራት ላይም ብቃት ያለው ሰው መሆን እንዳለበትና መራጮችም የጉዳዩ ባለቤቶች መሆን እንዳለባቸውና የትኛውንም ሥልጣን ቢኖረው ማንም ሊመርጥላቸውና ግፊት ሊያደርግባቸው እንደማይገባ ለሰዎች ሁሉ ግልፅ የሆነበት ነው። እዚህ ላይ የምንገነዘበው ነገር እስልምና ታዋቂና ትላልቅ ሰዎች ለህዝቡ ይበጃል ያሉትን አስተዳዳሪያቸውን እንዲመርጡ የሚጋብዝ መሆኑንና ኋላ ላይ የተቀረው ህዝብ ቃል ኪዳን የሚፈፅምበት ሁኔታ ያለ መሆኑን ነው። ይህም በአቡበክር ሹመት ወቅት ታይቷል። አስተዳዳሪው ምክትሉን በመምረጥ ወሣኝ ለሆኑ ሰዎች ጉዳዩን እንዲስማሙበት በማቅረብ የሚያስወስንበት ሁኔታ እንዳለም በዑመር ወቅት የታየው አመራረጥ አመላካች ነው። የተለያዩ ሰዎችን እጩ አድርጎ በማቅረብ ከነሱ ውስጥ አንዱን መምረጥ የሚቻል መሆኑንም በዑስማን ጊዜ የሆነው ያሣየናል።

አቡበክር አስ ስዲቅ ረዲየሏሁ ዐንሁ ንግግር ለማድረግ ተነሱ። በመንግስታቸው ውስጥ ሊከተሉ ያሰቡትን መሠረታዊ ነጥቦች አነሱ

أما بعد، أيها الناس! فإني قد وُليت عليكم، ولست بخيركم، فإن أحسنت فأعينوني، وإن أسأت فقوموني، الصدق أمانة، والكذب خيانة، والضعيف فيكم قوي عندي حتى أريح عليه حقه إن شاء الله والقوي فيكم ضعيف عندي، حتى آخذ الحق منه إن شاء الله لا يدع قوم الجهاد في سبيل الله إلا ضربهم الله بالذل، ولا تشيع الفاحشة في قوم قط إلا عمهم الله بالبلاء، أطيعوني ما أطعت الله ورسوله، فإذا عصيت الله ورسوله فلا طاعة لي عليكم

“ሰዎች ሆይ! አኔ በናንተ ላይ ብሾምም በላጫችሁ ሆኜ ግን አይደለም። ጥሩ የሠራሁ እንደሆነ አግዙኝ። ያጠፋሁ እንደሆነ ደግሞ አርሙኝ። እውነት አደራ ናት። ውሸት ግን ክህደት ናት። በአላህ ፈቃድ ሀቁን እስካስመልስለት ድረስ ደካማ የተባለው ሰው በናንተ ውስጥ ጠንካራ ነው። ጠንካራችሁ ደግሞ ደካማ ነው፤ የወሠደው የሌሎችን ሀቅ ካለ በአላህ እገዛ እስክቀበለው ድረስ። ሰዎች በአላህ መንገድ መታገልን አይተውም አላህ ውርደትን ያከናነባቸው ቢሆን እንጂ። ዝሙት በህዝቦች ውስጥ አይስፋፋም አላህ በመከራ የለቀቀባቸው ቢሆን እንጂ። (ህዝቦቼ ሆይ!) አላህንና መልእክተኛውን እስከታዘዝኩ ድረስ ታዘዙኝ። አላህንና መልአክተኛውን ያልታዘዝኩ እንደሆነ ደግሞ አትታዘዙኝ። [16]

አቡበክር የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት እስልምናቸውን የቀየሩትን ሰዎች ለመዋጋት መዘጋጀት ነበር። በወቅቱ ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሞት በኋላ በከተማ አካበቢ የሚገኙ ሰዎች በእምነታቸው የፀኑ ሲሆን በሰፊው የዐረቢያ የገጠር ክፍል የሚገኙ የተወሰኑት ደግሞ የነቢዩን ሞት እንደሰሙ ከሃይማኖታቸው ተመለሱ። ከዚህም አልፈው የአላህ መልእክተኛ ያስቀመጧቸውን ገዠዎቻቸውንም አንታዘዝም አሉ። የአካባቢውን አብዛኛውን ነዋሪ ለመሰብሰብ ያስችለናል በሚል እሣቤም ከመካከላቸውም ነቢይ ነኝ ብሎ የተነሣ ነበር። ይህ በርግጥም ለሙስሊሞች ትልቅ የፈተና ወቅት ነበር።

አብዛኞቹ ከእስልምና የወጡ ሰዎች ከሰለሙ ጥቂት እድሜ ብቻ የነበራቸው ሲሆን የእምነቱ ምንነት ወደ ውስጣቸው አልገባም ነበር። በተሣሣተ ግንዛቤም እስልምናን እና የአላህን መልእክተኛ በማያያዝ በርሣቸው ሞት ሁሉ ነገር የሚያበቃ መስሏቸው የተመለሱ አሉ። በመፍራት አሊያም ከአላህ መልእክተኛ ስጦታ እናገኛለን በማለት የሰለሙ መሪዎቻቸውን በመከተል ብቻ የሠለሙ ስለ እምነቱ ምንም የማያውቁም ነበሩ። የነቢዩን ሞት ተከትሎ መሪዎቻቸው ከእስልምና ተመልሰው ነቢይ ነን ብለው በተነሱ ጊዜ እነሱም አብረዋቸው ከእስልምና ወጡ ።

ዑርወት ኢብኑ ዙበይር አባቱን ጠቅሦ እንደተናገረው የአላህ መልእክተኛ ሰለለሁ ዐለይህ ወሠለም ሲሞቱ ዐረቦች በሙሉም በከፊልም ከእስልምና ወጡ። ሙሰይለማና ጠሊሃን የመሣሠሉት ደግሞ ነቢይ ነን ብለው በመነሣታቸው ነገሮች ተመሠቃቀሉ። በጠሊሃ ዙሪያ አብዛኛው የጤይእና የአሰድ ጎሣዎች ተሰበሰቡ። ገጥፋኖች ከአሽጀዕና ከአፍናኦች የተወሰኑት ሲቀሩ ሁሉም ከእስልምና በመውጣት በርሱ ለመመራት ቃል ኪዳን ገቡለት። ሀዋዚኖች የወጡም ሰው የቀሩም ነበሩ። በሰቂፍና ዙሪያዋ ካሉት ጎሣዎች በስተቀርም አብዛኞቹ ዘካን ከለከሉ … ከበኒ ሱለይምም ተወሰኑት ከእስልምና ወጡ እንዲሁ በየቦታው ይሀው ሁኔታ ተከሠተ። [17]

በመዲና የሚገኙ የሰሃቦች በዚህ አሣሣቢ ለውጥ ዙሪያ አቋማቸው የተለያየ ነበር። አብዛኛው ሰው ሀይል በመጠቀም ነገሩን ለመለወጥ ቢሞከር የሁኔታውን መጨረሻ ፈሩ። በመሆኑም ጦርነት ባይከፈት ይሻላል የሚለውን አቋም ያዙ። ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ተስፋ ቆረጡ። “ሞት እስኪመጣብን ድረስ አርፈን አምላካችንን መገዛት አለብን” አሉ። አቡበክር ግን በጉዳዩ ላይ ከቁርጥ ውሣኔ ደረሱ። ከእስልምና የወጣውን እያንዳንዱን ሰው ለመጋፈጥ ..

والله لأقاتلن من فرق بين الصلاة والزكاة، فإن الزكاة حق المال، والله لو منعوني عناقا كانوا يؤدونها إلى رسول الله صلى الله عليه وسلم لقاتلتهم على منعها

“ወላሂ ሰላትና ዘካን ለይቶ የሚያይን ሰው እዋጋዋለሁ። ዘካ የንብረት ሀቅ ናትና ማንም መከልከል አይችልም። ወላሂ ለአላህ መልእክተኛ ይሰጡ የነበሩትን ገመድ እንኳ ቢከለክሉኝ የከለከለኝን ሰው እዋጋዋለሁ። አሉ ። [18]

እውነተኛው ኸሊፋ በዚህ አቋማቸው በሌላ ሰው ያልታየ ጀግንነታቸውን አፀኑ። የቂን /በአላህ ላይ እርግጠኝነት/ ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ። ይህንንም በሂጅራ /ወደ መዲና ስደት/ ወቅት፣ በበድር ዘመቻና በአህዛብ ጊዜ በነቢዩ ሰለለሁ ዐለይህ ወሠለም አይተዋል። ያኔ ሁሉም ቁሣዊ ነገሮች እስልምና ያበቃለት መሆኑን ያመለክቱ ነበር። የአላህ ነቢይ ግን በዚያች ቀውጢ ሰዓት ሙስሊሞች ለሽንፈት ምክኒያት ሊሆኑ የሚችሉትን እስካስወገዱ ድረስ አላህ ድሉን እንደሚሠጣቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበሩ።

ኢብኑ መስዑድ እንዲህ ይላል “ከነቢዩ ሞት በኋላ አላህ ግዴታ ያደረገብንን ነገር በመተዋችን ምናልባትም አላህ እኛን የሚያጠፋበትን አቋም ይዘን ነበር፤ አላህ አቡበክርን ሰበብ ባያደርግልን ኖሮ እኛ ላለመጋደል ተስማምተን ነበር .. እኛው ብቻ ሞት እስኪመጣብን ድረስ አላሀን ለመገዛት። አቡበክር ግን እነኚህን ሰዎች ለመዋጋ ቆረጡ …”

አቡበክር ሙርተዶችንና /ከእስልምና የወጡትን/ እና ነቢይ ነን ያሉትን ለመዋጋት ቆርጠው መነሣታቸውን ባዩ ጊዜ በዙሪያቸው የነበሩ ሰሃቦች “ያኔ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ከመሞታቸው በፊት ለዘመቻ አዘውት የነበረው የኡሣማ ኢብኑ ዘይድ ጦር ለርስዎ እገዛ እንዲያደርግና መዲናን ለመጠበቅ እዚሁ እንዲቀር” በማለት ሀሣብ አቀረቡ። ይህንንም ያሉት የኡሣማ ጦር የሙስሊም ጦር በመሆኑና ያመፁት በዙሪያ ያሉ ዐረቦች በመሆናቸው ታማኝ እንደሆነ ስላመኑበት ነው። ኡሳማም በዚህ ጉዳይ ላይ አቡበክርን ለማሣመን ብዙ ጣረ “ከኔ ጋር ትላልቅና የሚባሉ ሰዎች አሉ፤ በአላህ መልእክተኛ ኸሊፋ፣ በአላህ መልእክተኛና በሙስሊሞች ክብር ላይ ሙሽሪኮች ሊያጠቋቸው ይችላሉና ማንንም አላምንምና (እዚሁ ቀርተን መዲናን ብንጠብቅ)” አላቸው። [19]

አቡበክር ግን የሁሉንም ሀሣብ አልተቀበሉም። በእይታቸው አምባገነን ለመሆን ፈልገው ሣይሆን የኡሳማ ጦር እንዲዘጋጅ አዘው የነበሩት ነቢዩ ነበሩና ይህ ጦር ሥራውን ነቢዩን ባለመታዘዝ መጀመር የለበትምና መሄድ አለበት ከሚል የተነሣ ነው። “ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታዬ እምላለሁ። አውሬዎች ቢቀራመቱኝ እንኳ የኡሣማን ጦር ከመላክ ወደኋላ አልልም። የአላህ መልእክተኛ አዘውበታልና በመንደሩ ብቻዬን የምቀር ቢሆን እንኳ እልከዋለሁ” [20] በማለት አስረግጠው ተናገሩ። አቡበክር ከዚህም በተጨማሪ በሀገሪቱ ሰላምን ማምጣት የሚቻለው በሩሞች ላይ መንገድ በመዝጋትና እነሱንም እንዳይዘምቱባቸው በማጨናነቅ ነው የሚል እሣቤም ነበራቸው።

ኡሣማ እድሜው ገና በመሆኑ “ይህን ታላቅ ተልእኮ ያሣካ ይሆን!” በሚለው ላይ ጥርጣሬ የነበራቸው ሰዎች ቁጥርም ቀላል አልነበረም። በመሆኑም ይህን የተጠራጠሩ ሰዎች በዑመር በኩል አድርገው ለአቡበክር ደብዳቤ ላኩ። ዑመርም ለአቡበክር እንዲህ አሉ “የአንሷር ሰዎች ይህን ጉዳይ እንዳደርስህ ልከውኛል። ከኡሳማ በእድሜ ከፍ ያለውን ሰው መሪ ታደርግላቸው ዘንድ የጠይቃሉ።” አላቸው። አቡበክር ከተቀመጡበት ብድግ ብለው የዑመርን ፂም በመያዝ “እናትህ ትጣህና አንተ የኸጧብ ልጅ ሆይ! የአላህ መልእክተኛ ለቦታው ሾመውት እኔ እንዳወርደው ታስባለህን!” [21] አሉት።

ከሰሃቦችና ከአቡበክር ገጠመኞች የምንወስደው ትምህርት ሹራን /መመካከርን/ ሙስሊሞች ልምዳቸው ሊያደርጉትና ሊዘወትሩበትም የሚገባ መሆኑን ነው። ሆኖም ግን አንድ ነገር የአላህን ትእዛዝ የመፈፀምና ያለመፈፀም ጉዳይ ሆኖ ሲገኝ ግን በትእዛዙ መመራት ለሹራ የሚቀርብ መሆን የለበትም። የሹራ ዋና ጥቅሙ እጅግ ወደተሻለውና ትክክለኛ ወደሆነው ሀሣብ ለመድረስ የሚደረግ ጥረት ነውና። በመሆኑም የሁሉ እውቀት ባለቤት ከሆነው ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እና በራእይ ከሚመጣላቸው መልእክት እንጂ ከስሜታቸው ከማይናገሩት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በላይ የሆነ ትክክለኛ ሀሣብ ይኖራል ተብሎ አይታሠብም።

. . . ይቀጥላል

የፅሁፉ ምንጮች

[1].       አቡዳውድ፣ ቱርሙዚ እና ኢብኑ ሂባን ዘግበውታል

[2].      ኢብኑ ሂባን

[3].      ቡኻሪይ

[4].      ቡኻሪይ

[5].      ሱረቱ ዙመር:- 30

[6].     ሱረቱ አል አንቢያእ:- 34

[7].      ሱረቱ ኣሊ ዒምራን:- 144

[8].      አልካሚል ፊ ታሪክ ቅ.1 ገጽ 359

[9].     ሙዕጀም አልከቢር ሊጠበራኒ ቅ.6 ገጽ 162

[10].    አልካሚል ፊ ታሪክ ቅ.1 ገጽ 359

[11].     ታሪክ አር ሩሱል ወልሙሉክ ቅ.2 ገጽ 125

[12].    ታሪክ አር ሩሱል ወልሙሉክ ቅ.2 ገጽ 117

[13].    አልካሚል ፊ ታሪክ ቅ.1 ገጽ 360

[14].    ታሪክ አር ሩሱል ወልሙሉክ ቅ.2 ገጽ 117

[15].    ታሪክ አር ሩሱል ወልሙሉክ ቅ.2 ገጽ 119

[16].    ጃሚዕ አል አሃዲስ ቅ.25 ገጽ 212

[17].    ታሪክ አጥ ጦበሪይ ቅ.2 ገጽ 254

[18].    ቡኻሪይ

[19].    አልካሚል ፊ ታሪክ ቅ.1 ገጽ 362

[20].   አልሙንተዘም ሊብን አልጀውዚ ቅ.1 ገጽ 437

[21].    ታሪክ አጥ ጦበሪይ ቅ.2 ገጽ 246

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here