5. ሕክምና
ሙስሊሙ በጤና ላይ ያለው ፍላጎት በቀጥታ ከኢስላም አስተምህሮ የመነጨና ከኢስላም ጋር ጥልቅ ትስስር ያለው ነው። በኢስላማዊ ስነ-ምግባር የሰው ልጅ አካል ባጠቃላይ ከአላህ የተሰጠ አደራ ነው። ይህ አደራ ሊጠፋ (ሕይወትን ማጥፋት) አልያም ሊጎዳ (በመጠጥ፣ በሃሺሽ) አይገባውም። በሽታን ቀድሞ የመከላከልና ከተከሰተም በኋላ የማከም ሂደቶች በኢስላም አስተምህሮት ውስጥ ተጠቃልለዋል።
በሕክምና ዘርፍ የሙስሊሙ አንዳንድ ቀደምት ሥራዎች የተጀመሩት ቀደም ብሎ በ8ኛው ክፍለ ዘመን ነበር። (እንደምሳሌ የኢብን አል-ሙቃፋእን ሥራዎች መጥቀስ ይቻላል።) ነገር ግን በዚህ ዘርፍ ትላልቅ ውጤቶች የተገኙት በ9ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን በዚያን ጊዜ ከነበሩት እንቁዎች መካከል ፉኹር አል-ዲን አልራዚ (ራዘስ) ይገኝበታል። ይህ ሰው በወቅቱ በባግዳድ የዶክተሮች የበላይ ኃላፊ የነበረና የመካከለኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ የህክምና ሰው ነበር። እሱ የጻፈው መጽሐፍ በአውሮፓ ውስጥ ለ600 ዓመታት በጣም ጠቃሚ የህክምና ማጣቀሻ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን ይህን መጽሐፍ ድራፐር “ግዙፍ የሕክምና አውደጥበብ (ኢንሳይክሎፒዲያ)” በማለት ገልፆታል። በፈንጣጣ እና በኩፍኝ ላይ የሠራቸው ሥራዎች ለበርካታ ዘመናት በተደጋጋሚ እየተተረጎሙ እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ጥቅም ላይ ውለዋል። ሳርቶን እንደገለፀው በማህጸንና ጽንስ ህክምና፣ እንዲሁም በአይን የቀዶ ጥገና ላይ የተደረጉ በርካታ አስተዋፅኦዎች በቀጥታ ከሱ የተወሰዱ ናቸው።
በ10ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው አሪብ ኢብን ሳዕድ በሕፃናት ሕክምና ላይ የጻፈ ሲሆን የሱም ሥራዎች ወደ ላቲንና ሂብሩ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በተመሳሳይ ዘመን ግብፅ ውስጥ የኖረው ማርዲኒ መድሃኒት በማዘጋጀት የተካነ ሰው ነበር። ይህ ሰው በ dispensatory[1] ላይ ጥንቅር የሠራ ሲሆን ይህም ጥንቅር በመካከለኛው አውሮፓ ውስጥ በጣም ታዋቂ ነበር። ለዘመናትም በዚሁ የትምህርት ዘርፍ ማጣቀሻ መጽሐፍ ተደርጎ ሲወሰድ ቆይቷል።
በ 11ኛው ዘመን የኖረው ኢብን ሲና (አቪሴና) ባለ አምስት ቅፅ መጽሐፍ የሆነውን “አልቃኑን ፊጢብ” (የህክምና መመሪያ) የጻፈ ሲሆን ይህም መጽሐፍ በንጽሕህና፣ physiology (የሰው አካል ጥናት)፣ pathology (ጥናተ-ደዌ)፣ therapeutics (በሽታን የሚያክም የህክምና ዘርፍ) እና “materia medica”[2] ዙርያ የሚያጠነጥኑ በርካታ ነጥቦችን የያዘ ነው። የኢብን ሲና ስራዎች በአውሮፓ ውስጥ ቢያንስ ለ600 አመታት የላቀ ስልጣን የነበራቸው ሲሆን በጣሊያንና በፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ለህክምና ትምህርት ማጣቀሻ መሰረት ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሥራዎቹ ወደ ላቲንና ሂብሩ በመተርጎምና በተደጋጋሚ በመታተም እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል።
በ 11ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የኖሩ ሙስሊም የህክምና ባለሞያዎች ብዙ ደም የመፍሰስ በሽታን (hemorrhage) ማዳን የቻሉ ሲሆን መተኮስንም (cauterization) ተጠቅመዋል።
በዚያን ጊዜ ከነበሩ ታዋቂ የቀዶጥገና ሃኪሞች መካከል በስፔን ኮርዶቫ ውስጥ ከ 11ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 12ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ የኖረው አቡል ቃሲም ይጠቀሳል። ሳርቶን ይህን ታላቅ የህክምና ሊቅ አስመልክቶ ሲናገር “እስከ የአውሮፓ ማንሰራራት (renaissance) ባለው ጊዜ ባለው የቀዶ ጥገና ህክምና እድገት ላይ በጣም ጥልቅ የሆነ አስተዋፅኦ አድርጓል” ብሏል። ጆን ድራፐርም “አቡል ቃሲም በቀዶ ጥገና የሰራቸው ስራዎች በአውሮፓ ውስጥ እስከ 1497 ድረስ ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበር” በማለትም ገልፆአል።
በኢብን ሩሽድ ፅሁፎች ውስጥ የአንጎል እና የዐይን ክፍሎችን፣ የዐይን ነርቮችን እና የቀዶጥገና እቃዎችን የሚመለከቱ ገለፃዎችን እናገኛለን። ከዚህም በላይ ከቀዶ ህክምናው በፊት ዳርኔል (darnel) ከሚባል ተክል የሚገኝ ጭማቂ በመጠቀም ማደንዘዣ ይሰጡ ነበር።
በሕክምናው ዘርፍ ሌሎች ተጨማሪ አስተዋፅኦዎኦችን ብንመለከት በብሮንኮቶሚ (bronchotomy)[3]፣ በወለምታ (dislocation) እና ስብራት (fracture) እና በቆዳ በሽታዎች ሕክምና (የኢብን ዙህር ወይም አቬንዘር ሥራዎች) በአእምሮ በሽታ ጥናት (psychopathology) በስነ-ልቦና ህክምና (psychological treatment) ያበረከቱትን መጥቀስ ይቻላል።
በተጨማሪም የደም ዝውውርን የሚመለከት ገለፃ በ 13ኛው ክፍለ ዘመን ኢብን አል-ነፊስ የሰጠ ሲሆን ይህም ዊሊያም ሀርቬይ ተመሳሳዩን ሥራ ለዓለም አበረከተ ተብሎ ከመሰበኩ 300 ዓመታት በፊት ነበር።
ተንቀሳቃሽና ቋሚ ሆስፒታሎችም ይታወቁ የነበረ ሲሆን ተንቀሳቃሽ ሆስፒታሎቹ በሰላማዊ ጊዜ በየገጠሩ በመጓዝ የህክምና እርዳታ ይሰጡ ነበር። በሰልጁክ ቱርኮች የአስተዳደር ዘመን እነዚህ ተንቀሳቃሽ ሆስፒታሎች ጭነታቸው እስከ 40 ግመሎች ደርሶ የነበረ ሲሆን ይህም ዶከተሮችን፣ መድሃኒቶችን፣ የህክምና መሳሪያዎችን ምግብንና አልባሳትን ጨምሮ የሚይዝ ነበር።
የመጀመሪያ እርዳታ ማእከላት በተለያዩ ቦታዎች ተቋቁመው የነበረ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ካይሮ ውስጥ በሚገኘው ኢብን ጡሉን መሰጅድ ውስጥ የሚገኘው ይጠቀሳል። በዚህ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ማእከል ሁልጊዜ ጁምዐ ህክምና ለመስጠትና መድሀኒቶችን ለማዘዝ አንድ ዶክተር ይመጣ የነበረ ሲሆን ከዚህ ማእከል የሚታዘዘውን መድሀኒት ታካሚው ከመስጅዱ ፋርማሲ እንዲወስድ ይደረግ ነበር።
የመጀመሪያው ቋሚ ሆስፒታል በባግዳድ በ8ኛው ክፍለ ዘመን አንደተቋቋመ ይገመታል። ይህም የሆነው በኸሊፋው አል-ዋሊድ ኢብን አብዱል መሊክ የአገዛዝ ዘመን ነበር።
በዚያን ጊዜ የነበሩት ሆስፒታሎች ሁለት ክንፎች ሲኖራቸው ለወንድና ለሴት ተብለው ለሁለት የተከፈሉ ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ክፍል የራሱ ኃላፊ ነበረው። እንዲሁም በየክፍሉ አንድ የበላይ ዶክተር ሲኖረው ረዳት አካላትም (እንደ ነርሶች፣ ፅዳት ሠራተኞች እና ምግብ አብሳዮች) ነበሩት። የህክምና ባለሞያዎቹ በሽተኞቻቸውን ከጐበኙ በኋላ ከተማሪዎቻቸው ጋር ስለ ህክምናው ሂደት ለመወያየት በሰፊ የመማሪያ አደራሽ ውስጥ ይሰባሰባሉ። ለበሽተኞች የሚቀርበው ምግብ የተሸፈነ ሲሆን በተጨማሪም አንዳንድ ሆስፒታሎች የራሳቸው የአትክልት ቦታ ነበራቸው። ይህም ለሆስፒታሎቹ አገልግሎት የሚውሉ ፍራፍሬዎችና አትክልቶችን ለማብቀል እንዲጠቅም ታስቦ የተደረገ ነው።
በየሆስፒታሎቹ የጥበበኛ ሰው አጅ ያረፈባቸው ሥራዎችና የተሰናዱ የቤት እቃዎችን ማስተዋል የተለመደ ነበር። በተጨማሪም ለበሽተኞች መዝናኛ የተዘጋጀላቸው ሲሆን ይህም ታሪኮችንና ቀልዶችን በመንገር በሸተኞችን የሚያዝናኑበት ነበር። አንድ ጊዜ በትሪፖሊ (ሶሪያ) ልዩ የአደራ ማእከል (trust) ተቋቁሞ ነበር። ይህም ሁለት ሰዎችን በመቅጠር እነዚህ ሰዎች በበሽተኛው አካባቢ በመዟዟር በሽተኛው እንዲስማማው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ስለ በሽተኛው ጤና መመለስ ይነጋገራሉ። “የሚያንፀባርቀው ዐይኑን አየኸው!”፤ “የፊቱን ቅላት አየኸው!”፤ “በጤናው ላይ ያለውን ለውጥ አየኸው!” ይባባላሉ። ይህም ስነ- ልቦና በአንድ ሰው ህክምና ላይ ያለውን ተፅእኖ ያውቁ እንደነበር ያሳያል።
እነዚህ የሚያመላክቱት የህክምና አገልግሎት፣ ተኝተው የሚታከሙትን ጨምሮ ነፃ የነበረ መሆኑንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሁሉም ሰው የተመቻቸ ሲሆን ይህም እንግዶች፣ መንገደኞች እና ጎብኚዎችንም ይጨምራል።
አንድ በሽተኛ ሆስፒታል ለህክምና ሲገባ ምርመራ ይደረግለታል። ተኝቶ መታከም ካላስፈለገው በሽተኛው መድሃኒት ተሰጥቶት ወደ ቤት እንዲሄድ ይደረጋል። ከታመነበት ደግሞ በሽተኛው ተመዝግቦ ሻወር እንዲወሰድ ከተደረገ በኋላ ሙሉ ልብስ ይሰጠው ነበር። በሽተኛው በጤናው ላይ መሻሻል ሲያሳይ ወደ ማገገሚያ አዳራሽ ይዛወራል። በጤናው ላይ መሻሻል ማሳየቱ የሚለካው አንድ ዶሮና አንድ ዳቦ በልቶ መጨረስ ሲችል ነበር። ከሆስፒታሉ በሚወጡበት ጊዜ ችግረኛ ሰዎች ልብስ ይሰጣቸዋል። እንደ አስፈላጊነቱ ደግሞ ሥራቸውን እስኪጀምሩ ድረስ የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ተሰጥቷቸው ከሆስፒታሉ እንዲወጡ ይደረግ ነበር። በቤታቸው ሆነው መታከም ለሚፈልጉ ደግሞ ከመፍቀድም አልፎ ቤታቸው ድረስ መድሀኒት ይላክላቸው ነበር። በቤቱ የሚታከመው ሰው ችግረኛ ከሆነ ምግብም ጭምር ነበር የሚላክለት። በ12ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ አንድ ሆስፒታልን አስመልክቶ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው “የተሠሩት አንዳንድ ቅድመ-ሁኔታዎችን እንዲያሟሉ ታስቦ ነው። ከንጽህና አንፃር በአሁኑ ዘመን ካሉት ተቋማት እጅግ ባላጮች ናቸው። በቁጥር በርካታ ሲሆኑ አየርና ውሃ በውስጣቸው እንደልብ ይዘዋወራል።”[4]
6. ጂኦግራፊ
ልክ እንደ አስትሮኖሚ ሁሉ ጂኦግራፊ ከሙስሊሙ የጸሎት ተግባር (እንደ ሶላትና ሐጅ) ጋር የተያያዘ ነው። በተጨማሪም የእስልምናን መልዕክት ለዓለም ለማድረስ ሙስሊሙ ካለበት ኃላፊነት ጋር የተያያዘ ነው። ይህም በአለም ላይ መዞሩን የግድ አድርጎታል።
የአሜሪካ መገኘት ሙስሊሞች ለጂኦግራፊ ባደረጉት አስተዋፅኦ የተደገፈ እንደሆነ ይታመናል።
ኢ-ሬናን “አቬሮስና አቬሮሲዝም” በሚለው መፅሐፋቸው ውስጥ ኮሎምቦስ በኦክቶበር 1498 የፃፈውን ደብዳቤ ጠቅሰዋል። በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ኮሎምቦስ አዲስ ዓለም አለ የሚል ሃሳብ እንዲይዝ የረዳው በ 12ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው የኢብን ሩሽድ (አቬንቱዝ) ሥራ እንደሆነ መስክሯል።[5]
ቁርአን ላይ በቀረቡት አገላለፆች በመመሰጥ ሙስሊም የጂኦግራፊ ባለሞያዎች መሬት ክብ መሆኗን ቀድመው ያውቁ ነበር።[6] ይህንንም በማስመልከት ሳርቶን ሲያስቀምጥ “ሁሉም የአረብ የጂኦግራፊ ባለሞያዎች መሬት ክብ መሆኗን ያምኑ ነበር ብሎ መናገር አስፈላጊ አይደለም::”[7]
አውሮፖዎች መሬት ጠፍጣፋ ናት ብለው በፀኑበት ወቅት ሙስሊሞች ሉልን (globe) ጂኦግራፊን ለማጥናት ይጠቀሙበት ነበር::[8]
የ12ኛው ክፍለ ዘመን ሙስሊም የጂኦግራፊ ባለሞያ የሆነው አል-አድሪሲ እንዲህ ሲል ፅፏል። “መሬት እንደ ሉል ክብ ስትሆን የውሀ አካላት ከመሬት ጋር የተጣበቁት በተፈጥሮአዊ ሚዛን (equilibrium) ሲሆን ይህም ምንም አይነት መለያየትን አያሳይም።”[9]
ከ አል-ኢድሪሲ በፊትም በ9ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ከሊፋው አልማእሙን የመሬትን ዙሪያ 2400 ማይል እንደሆነ ገምቷል። ይህም በዘመናዊ መልኩ ከተገኘው የመሬት ዙሪያ ጋር እጅግ በጣም የተቀራረበ ነው።[10] ከዚህም በተጨማሪ የአለምን ካርታ በትልቁ እንዲሳል ያዘዘውም አልማእሙን ነበር።
በ9ኛው ክፍለ ዘመን የተፃፈው “አል መማሊክ ወልመሳሊክ” (መንገድና ግዛት /Provinces/) የሚለው መፅሀፍ በታሪካዊ የምድር አቀማመጥ /historical topography/ ጥሩ ምንጭ ነበር። ይህም መጽሐፍ በ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ወደ ፈረንሳይኛ ተተርጐሟል። ተመሳሳይ ጥቅም የነበረው የአልያኩቢ “ኪታብ አልቢልዳን” ስለ መልከአምድራዊ አቀማመጥ ሙሉ ገለፃ አለው።
በ10ኛው ክፍለ ዘመንም በርካታ ሙስሊም የጂኦግራፊ ባለሞያዎች /geographers/ ፈልቀዋል። ከነዚህም መካከል አልመስኡዲ ተጠቃሽ ሲሆን የሱ ሥራዎች በጂኦግራፊያዊ ቅደም ተከተል የተቀናጀ ኢንሳይክሎፒዲያ (አውደ ጥበብ) በሚል ቢገለፅ ማጋነን አይሆንም። በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ምንም ዓይነት የጂኦግራፊ ሥራ አልተሠራም። ሳርቶን የአልያቁቱን “ሙእጃሙል ቢልዳን”ን ሲገልፅ “በፊደል ተራ ቅደም ተከተል የተቀመጠ ስለ ጂኦግራፊያዊ እውነታዎች የሚገልፅ ጥልቅ ስብስብ”[11] ብሎታል ።
በሌላም በኩል ሂሳባዊ ጂኦግራፊ /Mathematical geography/ ሳይቀር የተዳሰሰ ሲሆን ይህም በ 13ኛው ክፍለ ዘመን በአቡልሀሰን አልመራቂሺ ሥራዎች ውስጥ ነበር። እነዚህ ስራዎች ከሌሎች መረጃዎች በተጨማሪ የ 130 ቦታዎችን coordinates ይዘዋል። ሳርቶን ስለ አልመርቀሺ ሲናገር “ማንም የመካከለኛው ክፍለዘመን ፀሀፊ ሳይንሳዊ መንገዶችንና መሳሪያዎች በመግለፅ ላይ እንደሱ ልፋት አላደረገም”።[12]