ስራ የተባለ ሁሉ በኒይያህ ነው (አንደኛ ሐዲስ- ከአርበዒን አን-ነወዊያ)

0
5256

عن أَمِيرِ المُؤمِنِينَ أَبي حَفْصٍ عُمَرَ بنِ الخطَّابِ رَضِيَ اللهُ عَنْهُ قَالَ : سَمِعْتُ رَسُولَ اللهِ صلى الله عليه وسلم يَقُولُ: ” إِنَّما الأَعْمَالُ بالنِّيَّاتِ وإنَّما لكُلِّ امْرِىءٍ ما نَوَى، فَمَنْ كانَتْ هِجْرَتُهُ إلى اللهِ ورَسُولِهِ فَهِجْرَتُهُ إلى اللهِ ورَسُولِهِ، ومَنْ كانَتْ هِجْرَتُهُ لِدُنْيا يُصِيبُها أو امْرأةٍ يَنْكِحُها فَهِجْرَتُهُ إلى ما هَاجَرَ إليه”. (رواه البخاري ومسلم)

“ስራ የተባለ ሁሉ በኒይያህ ነው። እያንዳንዱ ሰው የኒይያውን ያገኛል። ስደቱ ወደ አላህ እና ወደ መልእክተኛው የሆነ ስደቱ ወደ አላህና መልእክተኛው ነው። ሊያገኛት ወዳለማት ዱንያ ወይም ሊያገባት ወደ ፈለጋት እንስት የተሰደደ ስደቱ ወደተሰደደበት ነገር ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)።


የሐዲሱ ክብደትና ጠቀሜታ

ሐዲሱ እጅግ ከፍተኛ ክብደት ከሚሰጣቸው ሐዲሶች መካከል አንዱ ነው። የእስልምና ሐይማኖት መሰረት ነው። አብዛኛው የእስልምና አሕካሞች (ሕግጋት) የሚሽከረከሩት በዚህ ሐዱስ ዙሪያ ነው። ኢማም አቡ ዳውድና ሻፊዒ፡- “ስራ የተባለ ሁሉ በኒይያህ ነው፣ ከሚለው ሐዲስ ውስጥ የእውቀት ሲሶው ይካተታል።” ብለዋል። ምክንያቱም ሰውየው በጎ ስራ የሚሰራው በቀልቡ፣ በአካሉና በምላሱ ሲሆን፣ የቀልብ ስራ (ኒያ) የሦስቱ አንድ ክፋይ ስለሆነ ነው።

አጠቃላይ መልእክት

ይህ ሐዲስ ለስራ መስተካከል ኒይያህን መመዘኛ አድርጎ ያቀርባል። ኒይያህ ከተስተካከለ ስራም ይስተካከላል። ኒይያህ ከተበላሸ ስራም ይበላሻል። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- “ስራ የተባለ ሁሉ” ማለታቸው፡- “ስራ የሚስተካከለው ወይም ተቀባይነት የሚያገኘው” ማለታቸው ሊሆን ይችላል። ኢማም አቡ ሐኒፋ ሐዲሱን የተረዱት በዚህ መልክቱ ነው። ከስራዎች መካከል ነጃሳን ማስለቀቅ፣ የተቀማን ገንዘብ መመለስ፣ ስጦታን ማድረስና መሰል ተግባራት ለትክክለኛነታቸው የኒያ መስፈርት አያስፈልጋቸውም። ግና ምንዳ ያስገኙ ዘንድ ወደ አላህ በመቃረብ ኒይያህ መከናወን ይኖርባቸዋል። ልክ እንደዚሁ አንድ ሰው ከአላህ ምንዳን በመከጀል እንስሳውን ቢመግብ ምንዳ ያገኛል። ግና ኒይያህው ንብረቱን መንከባከብ ከሆነ ምንዳ አይኖረውም። ከዚህ ምድብ ውስጥ የሙጃሂድ ፈረስ የተለየ ብይን ይሰጠዋል። ለጅሃድ ተግባር ከመደባት እርሱ እንድትጠጣ ሳይፈልግ ብትጠጣ እንኳ ምንዳ ያገኛል። በሶሒህ አል-ቡኻሪ ውስጥ ይህ ተጠቅሷል:: ለሚስት የሚደረግ እንክብካቤም እንደዚሁ ነው። እንደዚሁ ሌላ ነገር ከነያ ግን አያገኝም።፡

ኒይያህ የተደነገገው የልምድ (ዓዳ) ክንውኖችን ከዒባዳ ለመለየት ነው። ወይም ደግሞ የዒባዳዎችን የተለያዩ ደረጃዎች ለመለየት ነው።

  • በመጀመሪያው ምሳሌ፡- ከመስጊድ ውስጥ መቀመጥን ይመስል ነው። እረፍት በመፈለግ መስጊድ ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል። በዚህ ጊዜ ነገሩ ዒባዳ አይደለም። ኢዕቲካፍ ከነያ ደግሞ ዒባዳ ይሆንለታል። ይህን ልዩነት የፈጠረው ኒይያህ ነው። መታጠብም እንደዚሁ ነው። ለንጽህና ብሎ ካከናወነው ዒባዳ አይሆንም። በአንጻሩ አምልኮ ከነያበት ዒባዳ ይሆንለታል። እዚህም ላይ ልዩነቱን ያመጣው ኒይያው ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሶ.ዐ.ወ)፣ ለይዩልኝ፣ ለዘር ክብር እና ለጀግንነት ስለሚጋደሉ ሰዎች፡- “በአላህ መንገድ የተፋለመው የትኛው ነው?” ተብለው ተጠይቀው “የአላህ ቃል የበላይ ትሆን ዘንድ የተገጋደለው፣ በአላህ መንገድ የተፋለመው እርሱ ብቻ ነው።” በማለት መመለሳቸው ይህንኑ ይጠቁማል። (ቡኻሪና ሙስሊም)
  • የሁለተኛው ምሳሌ፡- የዒባዳን የተለያዩ ደረጃዎች ለመለየት የኒይያን ጠቀሜታ የሚያሳይ ሲሆን፣ አንድ ሰው የዙህርን ሶላት አስቦ ወይም ሱንና ለመስገድ አስቦ 4 ረከዐዎችን ሊሰግድ ይችላል። ልዩነቱን የፈጠረው ኒያ ብቻ ነው።

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)፡- “ስደቱ ወደ አላህና ወደ መልእክተኛው የሆነ” ማለታቸው ኒይያና ዓላማውን ለመግለጽ ሲሆን፡- “ወደ አላህና ወደ መልእክተኛው ይሆናል” ማለት በሸሪዓው ብይን ይህው ዓላማው ተቀባይነት ያገኛል ማለት ነው።

“ሊያገኛት ወዳለማት ዱንያ ወይም ሊያገባት ወደፈለጋት እንስት የተሰደደ ስደቱ ወደ ተሰደደበት ነገር ነው።” ይህን አባባል የተናገሩበትን መነሻ በተመለከተ አንድ ታሪክ ተላልፏል። ይኸውም የስደትን ምንዳ አስቦ ሳይሆን ኡምሙ አል-ቀይስ የተባለች እንስት ለማግባት በመፈለግ ከመካ ወደ መዲና ተሰደደ። በዚህ የተነሳ “የኡምሙ ቀይስ ስደተኛ” ተባለ። (ጦበራኒ ዘግበውታል)

ጋብቻ ሸሪዓው ጽድቅ ከቸራቸው ነገሮች መካከል አንዱ ሆኖ እያለ እንዴት ከዱንያዊ (ዓለማዊ) ዓላማ ሊካተት ቻለ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። መልሱም ሰውየው የስደቱ ዓላማ እንስት ማግባት መሆኑን በግልጽ አሳውቆ አልተሰደደም። የስደቱን እውነተኛ ዓላማ በመደበቅ ለአላህና ለመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ሲል የተሰደደ በማስመሰሉ ለዚህ ስመሳይነቱ ነቀፌታ የተገባው ሆኗል።

“ስደቱ ወደተሰደደበት ነገር ነው።” ለምሳሌ በሐጅ ጊዜ ንግድንና ሐጅን ነይቶ ከቤቱ የወጣ ምንዳ አያገኝም ማለት ነው። ግና ይህ የሚሆነው የመጀመሪያ መነሻው፣ ወደ ሐጅ የቀሰቀሰው ዓይነተኛ ዓላማ ንግድ ከሆነ ነው። ዋነኛ ፍላጎቱና ኒይያው ሐጅ ሆኖ እግረ መንገዱን ንግድ ቢያስብ ግን ምንዳ አይቀርበትም። ባይሆን ለሐጅ ብቻ አስቦ ቢሆን ኖሮ ከሚያገኘው ምንዳ ይጎድልበታል። ሁለቱንም በጣምራ አስቦ ከተጓዘ ደግሞ ምንዳ የማግኘት እድል ይኖረዋል። ምክንያቱም ስደቱ ለዱንያ ብቻ አይደለምና ምንዳ ሊያገኝም ይችላል። ምክንያቱም የአኼራን ስራ ከዱንያ ስራ ጋር ቀላቅሏልና። ሐዲሱ ብይኑን ያስተላለፈው ኒያን እና ዓላማን መሰረት አድርጎ በመሆኑ ሁለቱንም በጣምራ የኒይያ ዱንያን ብቻ ነይቷል ሊባል አይችልም። ልዑል የሆነው አላህ ይበልጥ አዋቂ ነው።

ከሐዲሱ የምንማራቸው ቁም ነገሮች

  • በጎ ስራ ለመስራት አስቦ በሽታ፣ ሞት እና መሰል አስገዳጅ ሁኔታዎች ያሰበውን ከመፈጸም ቢያሰናክሉት በኒይያው ብቻ ምንዳ ያገኛል።
  • ተግባር ያለ ኒይያ ፋይዳ የለውም። ኒይያ ግን ያለ ተግባር ምንዳ የሚያስገኝበት ሁኔታ አለ። ኒይያ ለስራ ያለው ፋይዳ ነፍስ ለአካል ያላትን ፋይዳ ያህል ነው። አካል ያለ ነፍስ ሕልውና አይኖረውም። ነፍስ ደግሞ ያለ አካል በዚህ ዓለም መገለጽ አትችልም።
  • ሐዲሱ በበጎ ስራዎቻችንና በዒባዳዎቻችን በመጭው ዓለም ምንዳ፣ በዚህች ዓለም ደግሞ ስኬት እናገኝ ዘንድ “ኢኽላስ” (ቅንነት) እንዲኖረን ያስተምረናል።
  • ጠቃሚና በጎ የሆነ ስራ ሁሉ በኒይያ፣ በኢኽላስና የአላህን ውዴታ በመሻት ሲፈጸም ዒባዳ ይሆናል።
  • ኒያና ኢኽላስ ይኖርህ ዘንድ ሁሌም ጉጉና ትጉ ሁን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here