ሙስሊሞች ለዓለም ስልጣኔ ምን አበረከቱ? (ክፍል 6)

1
2773

6. ሙስሊሞች ካበረከቱት አስተዋጽኦዎች ንዑስ ምሳሌዎች

አሁን ደግሞ ሙስሊሞች በዋና ዋና የትምህርት ዘርፎች ካበረከቱት አስተዋጽኦዎች ንዑስ ምሳሌዎችን እንመለከታለን።

  1. አስትሮኖሚ (ሥነ-ጠፈር)

የጠፈር ጥናት የሙስሊሙን ትኩረት ከሳቡ ቀደምት የጥናትና የምርምር ዘርፎች አንዱ ነበር። ይህም ከ3ኛው ክፍለ-ዘመን በሂጅራ አቆጣጠር ቀደም ብሎ ነበር የሙስሊሞቹ የጥናት ዘርፍ የሆነው። ቀደምት ሙስሊሞች በዚህ የትምህርት ዘርፍ ከደረሱባቸው ግኝቶች መካከል “ሰንስ አፖጂን” (sun’s apogee)[1]ተንብየዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ በዐይን የሚታዩ ኮኮቦችን የያዘ ዝርዝር ካርታ በመስራት ለነዚህ ኮከቦች የአረብኛ ስም ሰጥተዋቸው ነበር። እንደዚሁም የፀሐይንና የጨረቃን አቆጣጠር በማስተካከል የዓመቱን ርዝመት የተወሰነ በማድረግ ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ቀደምት ሙስሊሞች የግድግዳ ሰዓት መቁጠሪያ ዘንግን (pendulum) ለሰዓት መቁጠሪያነት በመጠቀም የመጀመሪያዎቹ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የጠፈር የምርምር ጣቢያንም (observatory) ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሩት እነሱው ናቸው::

ኢብን የኑስ (1ኛው ክ/ዘ ሂጅራ) sundial (ሰንዲያል)[2] የተባለ መሳሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈበረከ። ይህንን መሳሪያ በተመለከተ ጆን ድራፐር ሲገልፅ በሰዓት አቆጣጠር ጥናት ዘርፍ (chronometry) ላይ ከተደረጉ ማሻሻያዎች ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ሲል ፅፏል።

ቀደምት ሙስሊሞች ነቁጠ-ፀሃይን (sun’s spot)፣ ግርዶሽንና (eclipse) እና የጅራታም ኮከቦችን (comets) ገፅታ ተንብየዋል። አቡልወፋእ የስነ-ጠፈር ዋና ክፍል የሆነውን “3rd lunar inequality”[3] ማግኘት የቻለ ሲሆን ይህ ግኝት ከ1000 ዓመታት በኋላ የዳኒሹ የጠፈር ጥናት ተመራማሪ ታይኮ ብራሆ እንዳገኘው ተደርጎ ይነገራል። በዚያን ጊዜ ከነበሩት ሙስሊም የጠፈር ጥናት ተመራማሪዎች መካከል፡-

  • በአንዳንድ የጠፈር ተመራማሪዎች ዘንድ የ10ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ የጠፈር ተመራማሪ ተደርጎ ይወሰዳል።አል-ባጣኒ (አልባቲጂኒስ)
  • አል-ባይሩኒ (10ኛውና 11ኛው ክፍለ ዘመን) – የባግዳድና የህንድ ትምህርት ቤቶች አገናኝ ድልድይ ተደርጎ ይወሰዳል።
  • ኡልግ ቤግ – በዚህ የትምህርት ዘርፍ ጠቅለል ያለ ጥናት ያደረገ ሲሆን ይህም ኬፕለር ተመሳሳይ ጥናት ከማድረጉ ከ1000 ዓመታት በፊት ነበር።

በተጨማሪም በኢስላማዊት ስፔን ከሚገኙ የጠፈር ጥናት ተመራማሪዎች መካከል የኢብን አል-ሩሽድ እና ኢብን ኸልዱን ስራዎች በ “inquisition”[4] ጊዜ እንዲወድሙ ተደርገዋል።[5]

2. ኬሚስትሪ

ከኮምጣጤ (vinegar) በስተቀር ሌላ ጠንካራ አሲድ በማይታወቅበት ዓለም የ8ኛው ክፍለ ዘመን ኬሚስት ጃቢር ናይትሪክ አሲድን በማግኘት ለዓለም አስተዋውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የማጣራት (distillation)፣ ከጠጣር ወደ ጋዝነት በሙቀት ኃይል የመቀየር (sublimation) የማጥለል (filtration)፣ የመርጋት ሂደት (coagulation)፣ እና ከፈሳሽ ወደ ጠጣርነት የመቀየር (crystallization)፣ ሂደቶች እንዴት እንደሚሰሩ ገልጿል።

በአውሮፓዊያን ዘንድ ራዘስ በመባል የሚታወቀው አቡበከር አል-ራዚ በ9ኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ታላቅ ኬሚስት ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰልፈሪክ አሲድን (sulfuric acid) ባህሪያት ያጠና እና ሰፊ ገለፃ የሰጠ ሰው ነበር። የሱን ሥራዎች በተመለከተ ጆን ድራፐር “እሱ ካለፈ ከዘመናት በኋላ ከመጡት ኬሚስቶች ላቮይዘርና ፕሪስትሊ ጋር ተወዳዳሪ ነበር” ሲል ገልጿል።

አቡሙሳ አል-ኩፊ በ8ኛው ክፍለዘመን የኖረ ኬሚስት ሲሆን ለኬሚስትሪ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። የሱም ሥራዎች ወደ ላቲንና ፈረንሳይኛ እየተተረጎሙ እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በጥቅም ላይ ሲውሉ እንደነበር ይነገራል።

በዚያን ጊዜ የነበሩ ሙስሊም ኬሚስቶች ያደሉ የነበሩት በተግባር (experiment) ላይ ነበር። ስለ ውሃ ማጣራት፣ ፕላስተር፣ ሽሮፕ (syrup)፣ ቅባት እና ስለ ብረት መሞቅ ቀደም ብለው ያውቁ ነበር።

ብዛት ያላቸው የእንግሊዘኛ የኬሚስትሪ ቃላት የመጡት ከአረበኛ ቃላት ተወስደው ሲሆን እንደምሳሌ አልኮሆል (alcohol)፣ ካምፎር (camphor)፣ ኤሌግዚር (elixir)፣ አልካሊ (alkali)፣ እና ሲረፕን (syrup) መጥቀስ ይቻላል።[6]

3. ሒሳብ

ምንም እንኳን የመቁጠሪያ ስርአት የመነጨው ከህንድ ቢሆንም ይህንን ስርዓትን ግን ለዓለም ያስተዋወቁት ሙስሊሞች ናቸው።

በ10ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ሙሐመድ ኢብን አህመድ የዜሮን ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጠረ። ይህም አስቸጋሪ የነበረውን የሮማን የቁጥር ስርአት የቀየረ ብቻ ሳይሆን በሒሳብ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ አዲስ አብዮትም ጭምር ነበር። ይህም እሳቤ ወደ አውሮፓ የገባው ከሶስት መቶ ዓመታት በኋላ ነበር።

አልጄብራ ወይም በምልክት ስሌት “አልጃብር” ከሚለው የዓረበኛ ቃል የመጣ ሲሆን ይህም በጥሬ ትርጉሙ የተሰባበሩ ክፍሎችን አንድ ማድረግ ማለት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ አልጎሪዝም የሚባለው የሒሳብ ክፍል ስያሜውን ያገኘው ከእውቁ ሙስሊም የሂሳብ ሊቅ ሙሐመድ ቢን ሙሳ አል-ኸዋሪዝም ስም ነው። ይህም የሂሳብ ሊቅ በ9ኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ሲሆን ጆርጅ ሳርቶን (An Introduction to the History of Science) በሚለው መጽሐፉ ውስጥ አል-ኸዋሪዝምን “አልጀብራ ወይም አናሊሲስ ከጂኦሜትሪ የተለየና እራሱን የቻለ የትምህርት ዘርፍ መሆኑን ካሳወቁት ውስጥ አንዱ ነው።” በማለት ገልፆታል።

የአል-ኸዋሪዝም ሥራ ተሟልቶ የተጠናቀቀው በ10ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በአቡልወፋእ ሲሆን ይህም የሒሳብ ሊቅ በ “quadratic equation” ላይ ሰርቷል።

በሒሳብ ዘርፍ በሙስሊሞች የተሠሩት ሥራዎች ወደ ላቲን ተተርጉመው ለምእራቡ ዓለም የቀረቡት በቸስተሩ ሮበርት፣ በባዙ አዴላርድ፣ እና በሴቪሉ ጆን ሥራዎች ነው።

ከነዚህም በተጨማሪ የኢውክሊድን እውቅ ሥራዎች ሙስሊም ምሁራን ባይጠብቁት ኖሮ ከምድረ-ገፅ በጠፉ ነበር። በሌላ በኩል አል-ቱሲ (13ኛው ክፍለ ዘመን) በ “non-Euclidean geometry” እድገት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ሙስሊም ምሁራን ትኩረታቸውን በተግባራዊ ጥናት ላይ ከማድረጋቸውም ጋር ትሪጎኖሜትሪን ከግሪኮች በኋላ አሁን ባለው ቅርፅ በማሳደግ ቀዳሚዎች ነበሩ። ለአስትሮኖሚ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ “sine”ን እና “cosine”ን በመጠቀም ሙስሊሙን የቀደመ አልነበረም። በ“spherical trigonometry”ም ላይ እንደዚሁ የፃፉ ሲሆን በ“tangent trigonometry” ላይ የሠሯቸው ሥራዎች ደግሞ በአውሮፓዊያን ዘንድ እውቅናን ማግኘት የጀመረው ከአምስት ክፍለ ዘመናት በኋላ ነበር። ይህንንም በተመለከተ ጆርጅ ሳርቶን እንዲህ ሲል ፅፏል። “በ 13ኛው ክፍለ ዘመን በትሪጎኖሜትሪ ላይ የታየው እድገት ሙሉ በሙሉ በሙስሊሞች ጥረት ነበር።”[7]

4. ፊዚክስ

ታዋቂውን ሙስሊም የፊዚክስ ምሁር አል-ሀሰን ኢብን አል-ሀይሰምን (አልሃዘን) (11ኛው ክፍለ ዘመን) በተመለከተ ሳርቶን እንዲህ ሲል ፅፏል። “ታላቁ ሙስሊም የፊዚክስ ምሁርና ከሁሉም ጊዜ ታላላቅ የኦፕቲክስ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር።”

የኢብን አል-ሃይሰም “አልመናዚር” የሚለው መፅሃፉ በምእራቡ ዓለም ሳይንስ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳደር የቻለና በተግባራዊ የሳይንስ እድገት ላይ ለውጥ ያመጣ ነበር።

በርግጥም በመነፅር ሥራ (optics) ዙሪያ የሠራቸው ሥራዎች በዚሁ ዘርፍ ቀዳሚ የነበሩና ተመሳሳይ ሥራ ከሠሩት ከባኮንና ኬፕለር እጅግ ቀድሞ የተሠሩ ነበሩ። ኢብን አል-ሃይሰም የሰራቸው ሥራዎች ለማይክሮስኮፕ፣ ለቴሌስኮፕ እና ለካሜራ መፈብረክ ባለውለተኞች ናቸው።

በእይታ ምንጭ ላይ የነበረውን የግሪኮችን የተሳሳተ አመለካከት ( ይህም እይታ የሚመነጨው ከዐይናችን የሚወጣው ጨረር እቃው ላይ ሲያርፍ ነው የሚል ነበር) በማስተካከል እይታው የሚመነጨው እቃው ላይ ያረፈው ጨረር በመንፀባረቅ ዐይን ውስጥ ሲገባ እንደሆነ ገልጿል። ጆን ድራፐር ኢብን አል-ሃይሰም በ11ኛው ክፍለዘመን የፃፈውን መጽሐፍ በተመለከተ መገረሙን ሲገልፅ፡-

“Retina (ረቲና) የእይታ ማእከል እንደሆነ ማወቅ ችለናል። ብርሃን ረቲና ላይ በሚያርፍበት ጊዜ የሚኖረው ቅርፅ በኦፕቲክ ነርቭ በኩል ወደ አንጎል ይሄዳል።”

የኢብን አል ሃይሰም ሥራዎች በአውሮፓ ውስጥ ለብዙ ምእተ-አመታት የጥናትና ምርምር ዋነኛ ምንጭ ነበሩ።

በዚህ የትምህርት ዘርፍ ሙስሊሞች ያበረከቱት ሌላኛው አስተዋፅኦ የኮምፓስ መገኘት ነው። ምንም እንኳን ግሪኮች ስለማግኔት ባህሪያት ቀድመው ያውቁ የነበረ ቢሆንም፣ ቻይናዎች ስለማግኔት አቅጣጫ ጠቋሚነት ባህሪ ማወቅ የቻሉ ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ እነዚህን እውቀቶች ተግባር ላይ በማዋል ኮምፓስን ሀገርን ለማሰስ የተጠቀሙበት ሙስሊሞች ናቸው።

በዚህ የትምህርት ዘርፍ ሙሊሞች ያበረከቱት ተጨማሪ አስተዋፅኦዎችን ብንመለከት፡-

በሃይድሮ ስታቲክስ ጥናት (ቀደም ብሎ በ9ኛው ክፍለ ዘመን) እና በ “water wheel” (ወተር ዊል)[8] ጠቀሜታ ላይም ማሻሻያ በማድረግም ይታወቃሉ። ዓብዱራህማን አልኹሰይኒ የፃፉት “ሚዛኑልሂክማን” የሚለው መፅጽሐፍ በሳርቶን እይታ እንዲህ ተገልጿል። “በመካከለኛው ክፍለዘመን ከተገኙ ዋና ዋና የተፈጥሮ ድርሰቶች (physical treatises) መካከል አንዱ ነው። ይህም በውስጡ የፈሳሽና የጠጣር አካላትን ውስን የመሬት ስበት (specific gravity) የያዘ ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ ተፈጥሮአዊ እውነታዎችንና መላምቶችን ይዟል።”[9][1] በጨረቃ ላይ የሚገኝ ነጥብ ሲሆን ይህም ጨረቃ ከምድር የምትርቅበት ትልቁ ርቀት ነው

[2] በፀሃይ ሃይል የሚሰራ ሰዓት ነው

[3] የጨረቃን ከፍተኛ ላቲቲውዶች ቅርፅ አልባነት

[4] እስከ 19ኛው ክፍለዘመን ድረስ የቆየ ሲሆን የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ እና ሌሎች ሃይማኖቶችን በተለይም እስልምናን እንደስህተት በመቁጠር እርምጃ የወሰዱበት ጊዜ ነው።

[5] Draper John “History of the intellectual development of Europe” op.cit vol2 p49

[6] Draper op.cit p.26-27

[7] Sarton op. cit. vol2 p.12 and John Draper “history of the conflict between religion and science

[8] በውሃ ሀይል የሚሽከረከር ጎማ ሲሆን ማሽኖችን ለማንቀሳቀስ ይጠቅማል።

[9] Sarton op. cit. vol1 p.26

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here