ታሪካዊ መገለጫዎች
በመጀመሪያ ገፆች እንደተመለከትነው ቁርዐንና የነብዩ አስተምህሮ (ሀዲስ) የምርምር፣ የፈጠራና የለውጥ ጎዳናን በአዲስ እንዲመነጭ ማድረጋቸው ግልፅ ነው። በዚህ ክፍል ደግሞ ይህ “አዲስ መንፈስ’’ (“new sprit’’) እርሱን በታሪክ እንዴት ማስፈር እንደቻለ ለማሳየት ተሞክሯል። የመጀመሪያው ክፍል ኢስላማዊ ስልጣኔ እና በአውሮፓ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በስፋት ሲዳስስ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ለሳይንስና ስልጣኔ ከተበረከቱት ውስጥ የተወሰኑ ምሳሌዎችን ይጠቅሳል።
የስልጣኔ ዕድገት መፈንጠቅ የጀመረው በ 7ኛው ምዕተ ዓመት መዳረሻ ወይንም የ 8ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነው። ይህ ደግሞ በኡመይድ (Umayyad) የስልጣን ዘመን ማለት ነው። ነገር ግን ወርቃማው ዘመን የተከሰተው በኢስላማዊዋ ስፔን (755-1492) በአባሲድ የአስተዳደር ዘመን ነበር። በትንሹ ለአምስት ክፍለ ዘመናት ኢስላማዊ ስልጣኔ በአለም ላይ ስመጥር ነበር። ይህ ማለት ደግሞ የአውሮፓ ስልጣኔ ስመጥር ሆኖ ከቆየበት ጊዜ የበለጠ መሆኑን ያሳያል።
መስጊዶች ሲገነቡ ትምህርት ቤቶችን እና ቤተ-መጽሐፍትንም አብሮ ያካትት ነበር። ለትምህርት ተቋማት ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ለተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል መስጠት የተለመዱ ተግባሮች ነበሩ። እነዚህ ነፃ የትምህርት እድሎች እና የተለያዩ ምርምሮች ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣቸው እና የሚበረታቱ ሲሆን የማንኛውንም ሀይማኖት ተከታይ በነፃነት ያሳተፉም ነበሩ። ለዚህም እነደምሳሌ- በኸሊፋ እልማሙን (Calipha Al-Ma’moon) ድጋፍ ስር በ9ኛው ምዕተ ዓመት የነበረው ‘’ሃውስ ኦፍ ዊዝደም’’ (“house of wisdom’’) ተጠቃሽ ነው። ይህም ትልቅ የትምህርት ማዕከል፣ ቤተ-መጽሐፍት እንዲሁም የትርጉም ማዕከል ሆኖ አገልግሏል።
ከምዕራቡ የሙስሊም ዓለም ውስጥ ዋነኛ የምርምር ማዕከል የነበረው ቶሌዶ (ስፔን) ሲሆን በዚህም ማዕከል የሙስሊሙ ሥራዎች የነበሩት ከአረብኛ ወደ ላቲን ተተርጉመዋል። በተለይም በአስትሮኖሚ (Astronomy)፣ ሂሳብ፣ በህክምና፣ በኬሚስትሪ፣ በዕፅዋት ጥናት (Botany) እና በፍልስፍና (philosophy) የጥናት መስኮች ከፍተኛ የትርጉም ስራዎች ተሰርተዋል። ፖፕ ሲልቬስተር (Pope Sylvester) በቶሌዶ ውስጥ አስትሮኖሚን፣ ሂሳብን፣ ኬሚስትሪን እንዲሁም ሌሎች የትምህርት ዘርፎችን ከሙስሊም ሳይንቲስቶች እነደቀሰሙ ይነገራል።[1]
“ጨለማው ዘመን” – ስያሜ
እነዚህ አስደናቂ ስልጣኔዎች እደሚያረጋግጡት በተለምዶ “የጨለማው ዘመን’’ ተብሎ የሚጠራው “የአውሮፓ ጨለማ ዘመን’’ ተብሎ ሊስተካከል ይገባዋል። ቢያንስ እንኳን ኢስላማዊ ስልጣኔ ከፈነጠቀበት አንስቶ ያለውን ጊዜ በዚህ መልኩ መሰየም ይኖርበታል።
ጆን ድራፐር (John Draper) በአውሮፓ ውስጥ ሳይንስ ምን ያህል ቦታ እንደተነፈገው እንዲሁም አካላዊ እና ተፈጥሮአዊ ክስተቶችን ከእምነት ጋር እንዴት እንደሚያገናኙት ሲያብራራ “አንድ ሰው በከፍተኛ ትኩሳት ህመም ሲሰቃይ ታዕምራዊ ፈውስን በመፈለግ ወደ አቅራቢያው ወደ ሚገኝ ቅዱስ ስፍራ እንዲሄድ ይገደዳል።”[2] ከዚህ በተቃራኒ ሙስሊም ሳይንቲስቶች እና ዶክተሮች በሽታዎችን ለማከምና ለመፈወስ ሲመራመሩ በስራ ተጠምደዋል። ታዲያ ይህ ሚዛን ላይ ያልወጣ ስያሜ- “ጨለማው ዘመን’’- የአውሮፓን ታሪክ ልክ የዓለም ታሪክ ብቻ አድርጎ በማሰብ መሆን አለበት። አልያም የታሪክ ክህደት ይሆናል።
ተሃድሶና አዲስ ግኝት
ሌላው የተሳሳተ ግንዛቤ ደግሞ ሙስሊም ምሁራን የግሪክ ዓይነተኛ ተሞክሮዎች ላይ ብቻ ተሃድሶ አድርገዋል የሚል ነው። እነሱ ባይኖሩ የሙስሊሙ ሥራ የውሃ ሽታ ሆኖ በቀረ ነበር ይላሉ። ይህ ደግሞ ሙስሊሞችን ከተሃድሶ በተጨማሪ ያበረከቱትን የራሳቸውን የፈጠራና አዲስ ግኝት ይቀብራል። እንደ ዌልስ (H.G. Wells) ገለፃ ግሪካውያን የሰው ልጅን ታሪክ አያውቁም። ዕውቀታቸውም “ጥልቀት በሌለው ግምት የተንተራሰ” ሲሆን በተግባራዊ ሙከራ የታገዘ ምርምር ምንም አልነበራቸውም ማለት ይቻላል።
ዋይትሄድ (A.N. Whitehead) የዌልስን ሃሳብ በመጋራት “ግሪኮች ሙሉ በሙሉ በንድፈ ሃሳብ የተሞሉ ናቸው። ሳይንስ ለነሱ መወያየትና ሃሳብ ማመንጨት ነው። ስለዚህም የግሪክ እና የሮማን አስተዋፅኦ በተግባራዊ ሙከራ (experimentation) የተመሰረተ አልነበረም። ይህ ደግሞ የኢስላማዊ ስልጣኔ መለዮ ሲሆን ለዘመናዊ ሳይንስም መሰረታዊ መስፈርት ሆኗል። ስለዚህም የአውሮፓ ዳግም ማንሰራራት ከግሪክ እና ከሮማን ካካበቱት ቅርስ አዲስ ነገር ላይ ተመስርተው የፈጠሩት አዲስ ተሃድሶ ነው የሚባለው ግምትም የተሳሳተ ነው። የሮማን ኢምፓየር ከተንኮታኮተበት ጊዜ አንስቶ የጥንት ቅርሶችን ተሃድሶ ከፈጠረው የአውሮፓ ማንሰራራት መካከል ለብዙ ምዕተ ዓመታት ያልታወቀ ‘ክፍተት’ አለ ለማለት ተፈልጎ ይመስላል። ይህ በተጨማሪም ተሸሽጎ የማይቀረውን እውነታ-ዳግም ማንሰራራቱ የተመሰረተው ከዚያ በኋላ በተቆረቆረውና በአበበው ኢስላማዊ ስልጣኔ መሆኑን በግልፅ ይክዳል። ለብዙ ምዕተ-ዓመታት የቁርኣን (አረብኛ) ቋንቋ ለሳይንሳዊ ጥናቶች እና ምርምሮች ልክ እንደ ዛሬው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ዓለም አቀፋዊ አንቀሳቃሽ ሆኖ አገልግሏል።
በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በሒሳብ፣ በአስትሮኖሚ ወይንም በህክምና ሳይንስ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ፍላጎት ያደረባቸው አውሮፓውያን ወደ ሙስሊሙ ዩኒቨርስቲዎች ይጎርፉ ነበር፤ በተለይም ወደ ሙስሊማዊቷ ሰፔን። “የሙስሊሙን ሳይንስ” ለማስተዋወቅ የሞከሩ አውሮፓውያን ‘መሐመዳውያን’ ተብለው ተንገላተዋል፤ ታስረዋል። ለምሳሌ ሮጀር ቤከን በዚሁ ጉዳይ ተከሶ ለዐስራ አራት ዓመት ወህኒ ቤት ወርዷል።
የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ ሳርቶን (Gorge Sarton) ታዋቂ በሆነበት ሥራው “An Introduction to the History of Science’’ በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እንደጠቀሰው- የሙስሊሞች ሳይንስ ከ 14ኛው ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ወደ አውሮፓ ገብቷል። 14ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ዳግም ማንሰራራት የጀመረችበት እንዲሁም ከሙስሊሞች የቀሰሙትንና ያካበቱትን ተግባራዊ አቅጣጫ በመጠቀማቸው በአውሮፓ የዩኒቨርስቲዎች መቆርቆር ሊፋጠን ችሏል።[3]
አብዛኛውን ጊዜ የሙስሊሞች ግኝት በአውሮፓውያን ልክ እንደራሳቸው የፈጠራ ሥራ ወይንም ደግሞ በግኝት ላይ እራሳቸውን ተሳታፊ እንደነበሩ በማድረግም ተርጉመዋል። ለምሳሌ- ኬፕለር (Kepler) በከባቢ አየር ላይ ያደረገውን ጥናት (atmospheric refraction) ሃሳቡን የወሰደው ከኢብኑ አል-ሀይተም ነው። አይሳክ ኒውተን (Isaac Newton) የመሬት ስበትን (gravity) ሃሳብ የወሰደው ከዛፍ ላይ ከሚወድቅ ፍራፍሬ ሳይሆን ከሙሐመድ ቢን-ሙሳ ቀደምት ሥራዎቹ ነው። ሙሐመድ ቢን ሙሳ በህዋ አካላት መካከል የሚኖረውን የመሳሳብ ኃይል (attraction between heavenly bodies) ስለ መኖሩም ተናግሯል።[4]
በኢስላማዊ አስተምህሮዎች ተነሳስተው ለሰው ልጅ የእውቀት ደረጃ ልቅና እንዲሁም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ የተወሰኑ ምሳሌዎችን መጥቀስ ጠቃሚ ይሆናል።
[1] Bammate, Haider, Muslim Contribution to Civilization, Islamic Center, Geneva, Swizerland, 1962, p. 17 and Draper, History of the Intellectual Development of Europe, op. Cit, Vol II, p. 49
[2] Draper, John, History of The Intellectual Development of Europe, Revised Edition, Harper and Brothers, N.Y., 1876, vol. I, pp. 386-387.