5. ለጥናትና ምርምር የሚገፋፉ ቁርኣናዊ አንቀፆች
ከዚህ በመቀጠል ከቁርኣን ውስጥ በግልፅ የሰው ልጅን የሕይወት ደረጃ የሚያሳድግና ወደ ተሻለ ጎዳና የሚያመሩ ጥናትና ምርምር እንዲደረግ የሚያነሳሱ አንቀፆች ተጠቅሰዋል። ጥቂት ምሳሌዎችን ለአብነት ያህል እንመለከታለን።
“በምድር ላይ ጎረቤታሞች የሆኑ (ግና እየቅል የሆነ ባህሪ ያላቸው) ቁርጥራጭ መሬቶች አሉ። ከወይን የሆኑ የአትክልት ስፍራዎችም-አዝርዕቶችም- መንታዎች የሆኑም መንታዎች ያልሆኑም የዘንባባ ተክሎችም አሉ። (ሁሉም) አንድ ዓይነት ውሃ እንዲጠጡ ይደረጋል። ግና የከፊሎችን ጣእም ከከፊሎቹ (የተለየ እና) የተሻለ እናደርጋለን። እነኝህ አስተዋፅኦዎች (ድንቅ) ተአምራት ናቸው።” (አል-ረዕድ 13፤4)
“አላህ ከሰማይ ውሃ እንዳወረደና ምድር ውስጥ ምንጮች አድርጎ እንዴት እንዳስገባው አላየህምን? ከዚያም በርሱ የተለያዩ ቀለሞች ያላቸውን አዝርዕት ያበቅላል። ከዚያም ይደርቃሉ። የገረጡ ሆነውም ታያቸዋለህ። ከዚያም እንዲደርቁና እንዲሰባበሩ ያደርጋቸዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ለአዕምሮ ባለቤቶች (እጅግ ጠቃሚ) መልዕክት ተካቷል።” (አል-ዙመር 39፤21)
“አላህ ባህሩን መርከቦች ይጓዙበት- ከችሮታውም ትከጅሉ- ታመሰግኑትም ዘንድ- በትእዛዙ የገራላችሁ (አምላክ) ነው።” (አል-ጃሢያህ 45፤12
“ያ ባህርን ከርሱ ለጋ ስጋ ትመገቡ- የምተለብሷቸውን ጌጦች ታወጡ ዘንድ የገራላችሁ (አምላክ) ነው። መርከቡንም (ባህሩን) እየገመሰ በውስጡ (ሲንሳፈፍ) ታያለህ። ከችሮታው ትፈልጉና ታመሰግኑትም ዘንድ (ይህን ሁሉ ፀጋ ለገሳችሁ)።” (አል-ነሕል 16፤ 14)
“እንስሳትንም ፈጠራቸው እናንተም ከነርሱ ሙቀትን ታገኛላቸሁ- ሌሎች ጥቅሞችንም እንዲሁ። ከነርሱም ትመገባላችሁ። ከነርሱም ለናንተ (ማታ) ወደ ማረፊያቸው በምት መልሷቸው፣ (ጧትም) በምታሰማሯቸውም ወቅት፣ ውበት አለላችሁ። ጓዞቻችሁንም – ነፍሶቻችሁ ተቸግረው (በከፍተኛ ድካምና ልፋት) እንጂ ወደማትደርሱባቸው ሃገሮች ይሸከማሉ። ጌታችሁ በእርግጥም ርሁርህ፣ እጅግ አዛኝ ነው።ፈረሶችንም፣ በቅሎዎችንም፣ አህዮችንም ትጋልቧቸውና ጌጥም ይሆናችሁ ዘንድ (ፈጠረላችሁ)። የማታውቋቸውንም (እጅግ አስደናቂ) ነገሮች (ወደፊት) ይፈጥራል።” (አል-ነሕል 16፤5-8)
ጥቅላዊ በሆኑ ሀረጎች ውስጥ ደግሞ ቁርኣኑ በምድርና በሰማያት ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ የሰው ልጆች ይጠቀሙበት ዘንድ መፈጠራቸውን ያመላክታል።
“ምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ሁሉ የፈጠረላችሁ እርሱ ነው። ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ። ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው። እርሱ ሁሉንም ነገር አዋቂ ነው።” (አል-በቀራ 2፤29)
“በሰማያትም በምድርም ያሉ (ነገሮችን) ሁሉ ገራላችሁ። (ይህ ሁሉ) ከርሱ (የሆነ ችሮታ ነው)። በዚህ ውስጥ ለሚያስተነትኑ ሰዎች-ተአምራት አሉ።” (አል-ጃሢያህ 45፤13)
ቁርኣናዊ አስተምህሮዎቹ በቁሳዊ ሃብት ላይ ብቻ የተገደቡ አይደሉም። አንቀፆቹን በሚገባ ማጥናትና መመራመርን ተፈጥሮአዊ ህጎችን እንድናውቅና እንድናጠና ጎዳናውን ያመላክቱናል። ለምሳሌ የቀንና የሌሊት መፈራረቅ፣ ዝናብን መተንበይና ስነ-ፈለካዊ ክስተቶች (astronomical phenomena) እንድናስተውልና እንድናስተነትን ይጋብዛሉ።
“አላህ ሌትንና ቀንንም ያፈራርቃል። በዚህ ውስጥ ለአስተውሎት ባለቤቶች ትምህርትና ተግሳፅ አለ።” (አን-ኑር 24፤44)
“የሰማያትና የምድር መፈጠር፣ የቀንና የሌሊት መፈራረቅ ለአስተዋዮች ታላላቅ ተአምራት ናቸው። እነርሱ አላህን ቁመውም ተቀምጠውም፣ በጎኖቻቸው ተጋድመውም የሚያወሱት፣ የሰማያትን (ድንቅ) አፈጣጠር የሚያስተነትኑት፣ ‘ጌታችን ሆይ! ይህን (ድንቅ ዓለም) እንዲሁ (ያለ ዓላማ) አልፈጠርከውም፣ ክብር ላንተ ይሁን። ከእሳት ቅጣት ጠብቀን።’ (የሚሉት ናቸው)።” (አሊ-ዒምራን 3፤190-191)
“አላህ ዳመናን እነደሚነዳ፣ ከዚያም እርስ በእርስ እነደሚያገናኘው፣ ከዚያም የተነባበረ እነደሚያደርገው አላየህንምን? ዝናብም በውስጡ (እየተጨመቀ) ሲወጣ ታያለህ። ከሰማይ ውስጥ ካሉ (የደመና) ቁልልሎች በረዶን ያወርዳል። በርሱም የሚሻውን (ክፍል) ይመታል። ከሚሻውም (አካባቢ) ያስወግደዋል። የብልጭታውም ብርሃን ዓይኖችን ሊያጠፋ ይቃረባል።” (አን-ኑር 24፤43)
“ሌሊቱም ለነርሱ (ሌላ) ምልክት ነው። ቀኑን ከርሱ እንገፍፋለን። ወዲያም እነርሱ በጨለማ ይወጣሉ። ፀሃይም ወደ መርጊያዋ በፍጥነት ትጓዛለች። ይህ-አሸናፊና ዐዋቂ የሆነው አምላክ ውሳኔ ነው። ጨረቃንም እንደ አሮጌ የዘንባባ ቀንዘል እስክትሆን ድረስ የምትጓዝበትን ማረፊያዋን ወሰንላት። ፀሐይ ጨረቃን እንድታገኝ፣ ሌሊቱም ቀኑን እንዲቀድም አልተፈቀደላቸውም። ሁሉም (በየራሳቸው) ምህዋር (በአላህ የተሰመረላቸውን የጉዞ መስመር ተከትለው) ይዋኛሉ።” (ያሲን 36፤37-40)
የመማር ሚና
ከላይ የተጠቀሱት ቁርኣናዊ ምክሮች ለትምህርት ጥሩ አመለካከት እንዲኖረን እንዲሁም ዕውቀትን መፈለግ ግዴታ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ ደግሞ በቁርኣን ውስጥ እንደ መሠረት ሆኗል። ለነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መጀመሪያ የወረደላቸው የቁርዐን ቃል ‘ኢቅራዕ’ ሲሆን ትርጉሙም አንብብ ማለት ነው።
“አንብብ፣ በዚያ (ሁሉንም ነገር) በፈጠረው ጌታህ ስም።” (አል-አለቅ 96፤1)
ቅዱስ ቁርኣንም ደግሞ እነዛ እምነትን ከእውቀት ጋር ያጣመሩትን ያልቃቸዋል።
“አላህ ከመካከላችሁ እነዚያን ያመኑትንና እነዚያን ዕውቀት የተሰጣቸውን በደረጃ ከፍ ያደርጋል። አላህ የምትሰሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው።” (አል-ሙጃደላህ 58፤11)
እውቀትን የተቸሩ ከሌሎች የተለዩና የተመረጡ ያደርጋቸዋል።
“እነዚያ የሚያውቁትና እነዚያ የ ማያውቁት እኩል ናቸውን?” በላቸው። (አዝ-ዙመር 39፤9)
ዕውቀት በራሱ ለእምነት አስጊም ከቅድስናና ከአላህ ፍራቻ ጋርም አብሮ የማይሄድ አይደለም። በእርግጥም ያልተዛባ እና ትክክለኛ ዕውቀት ወደ ቅድስና ይመራል።
“አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት አዋቂዎቹ ብቻ ናቸው።” (ፋጢር 35፤28)
በጥቅሉ ቁርኣን እውነትን ለመፈለግ ምክንያታዊ አለመሆንን እንደ ሀጢያት ይቆጥረዋል። በተለይም እነዛ በዕውቀት ላይ ያልተመረኮዙትን እና በጭፍንነት ከቅድመ አባቶቻቸው የወረሱትን ብቻ የሚያንፀባርቁትን ቁርኣን ያስጠነቅቃል ይገስፃልም።
“ከአላህ ዘንድ ከነፍሳት ሁሉ መጥፎዎቹ እነዚያ (እውነትን) መረዳት ያልቻሉት ደንቆሮዎችና ዲዳዎች ናቸው።” (አል-አንፋል 8፤22)
“የማይገነዘቡባቸው ልቦች፤ የማያዩባቸው ዓይኖች፤ የማይሰሙባቸው ጆሮዎች ያሏቸውን በርካታ ሰዎችና አጋንንት ለገሃነም ፈጠርን። እነርሱ ልባቸው እንደእንስሳ፤ ከዚያም የባሱ ናቸው። እነርሱ በ እርግጥም (ማስጠንቀቂያውን) የዘነጉ ናቸው።” (አል-አዕራፍ 7፤179)
ለትምህርት ሊኖረን የሚገባ አመለካከት በብዙ የነብዩ ንግግሮች ላይ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
“ዕውቀትን መፈለግ በእያንዳንዱ ሙሰሊም ላይ ግዴታ ነው’’
“ዕውቀትን ለመፈለግ ብሎ ጉዞ የጀመረ አላህ ለእሱ/እሷ ወደ ጀነት የሚወስደውን መንገድ ያገራለታል/ያገራላታል’’
“ዕውቀት ያለው አማኝ ዕውቀት ከሌለው ጋር ያለው ብልጫ ልክ ጨረቃ በሌሎች ኮከቦች ላይ እንዳላት የበላይነት ነው’’
“የዕውቀት ባልተቤቶች የነብያቶች ወራሾች ናቸው።’’
በተግባር የተደገፈ
በቁርኣን ውስጥ ለትምህርት ከሚገፋፉ አንቀፆች ውስጥ አንዱ ክፍል በተግባር የተደገፈ (experimental) ዘዴን እንድንከተል መንገዱን ያመላክታል። የተወሰኑ ምሳሌዎችን ብቻ መመልከት ይህን በግልጽ ሊያብራራልን ይችላል። አላህ በቁርኣን ውስጥ ስለ ንቦች ሲገልፅ፤
“ ‘ከዚያም ከፍሬዎች ሁሉ ብይ፡፡ የጌታሽንም መንገዶች (ላንቺ) የተገሩ ሲኾኑ ግቢ፡፡’ ከሆዶችዋ መልኮቹ የተለያዩ መጠጥ ይወጣል፡፡ በእርሱ ውስጥ ለሰዎች መድኃኒት አለበት፡፡ በዚህ ውስጥ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች በእርግጥ ተዓምር አልለበት፡፡” (አል-ነሕል 16፤ 69)
ከህመም ማገገምን ከንብ ጋር ተያይዞ መቅረቡ ለህክምና ጥበብ ማር ከበሽታ የመፈወስ አቅም እንዳለው እና እንድንመራመር መንገዱን ክፍት መሆኑን የሚጋብዝ ነው። በተመሳሳይ መልኩ የብረቶችን ባህሪ (properties of metals) እንድናጠና ትኩረት እንድንሰጠው ይገፋፋል።
“ብረትንም አወረድን፤ ከውስጡ ብርቱ ኃይል አለበት። ለሰው ልጆችም በርካታ ጥቅሞቸን (ይሰጣል)።” (አል-ሐዲድ፤ 25)
የጽንስ ዕድገትን በግልጽና በሚደንቅ መልኩ ቁርኣን እንዲህ ይገልጸዋል።
“የሰውን ልጅ ከነጠረ ጭቃ በእርግጥ ፈጠርነው። ክዚያም የፍትወት ጠብታ( አድርገን) ምቹ ከሆነ ማረፊያ ውስጥ አስቀመጥነው። ክዚያም የፍትወት ጠብታውን የረጋ ደም፤ የረጋውን ደም የተላመጠ (የሚመስል) ቁራጭ ስጋ፤ ቁራጩን ስጋም አጥንት አድርገን ፈጠርነው።አጥንቱንም ስጋ አለበስነው። ከዚያም (ነፍስ ዘርተን) ሌላ ፍጡር አደረግነው። አቻ የለሽ ፈጣሪ የሆነው አላህ ተባረከ።” (አል-ሙእሚኑን 23፤12-14)
ከላይ ከቁርኣን ውስጥ የተወሰዱ አንቀፆች በተግባር የተደገፈ አካሄድ እንድንከተል እንዲሁም የይሆናልን አካሄድ – በዕውቀት ላይ በተመሰረተ እውነታ እንድንተካው የመሰረት ድንጋዩን ያኖራል። እነዚህ ደግሞ ለሳይንሳዊ ዕድገት አሳማኝ እና ወሳኝ የሆኑ መስፈርቶች ናቸው። ይህ ጥሪ ደግሞ በፍልስፍና የተሞሉ ግምቶች እንዲሁም ምናባዊ አስተሳሰቦችን ያወግዛል።
ለዚህም ቁርኣን
“ለነርሱ በዚህ ምንም ዕውቀት የላቸውም። የሚከተሉት ጥርጣሬን ብቻ ነው። ጥርጣሬ ሐቅን ፈፅሞ አይወክልም።” (አን-ነጅም 53፤ 28)
አሁን አንድ ታሪካዊ ስህተት እንዳለ እንረዳለን፤ ያም ‘የሳይንስ አባት’ እየተባለ የሚጠራው ሮጀር ቤከን – ስያሜው ለሱ እንደማይገባው ወይም ይህን ማዕረግ ለሱ መሰጠት የተሳሳተ እውነታ መሆኑን ወይም የታሪክ ንፍቅና መሆኑን እንረዳለን። ምክንያቱም ሮጀር ቤከን የተወለደው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1214 ሲሆን ይህ ማለት ደግሞ ቁርኣን በግልፅ ለዚህ ሳይንሳዊ ክህሎት ጥሪ ካደረገ ከስድስት ክፍለ ዘመናት በኋላ ነው። ታዲያ እንዴት ሆኖ ሮጀር ቤከን የሳይንስ አባት ሆነ? እንደ ሮብ ብሪፎልት ገለፃ ሮጀር ቤከን የሙስሊሞችን ሳይንስ እንዲያስተምር ወደ አውሮፓ የተላከ መልዕክተኛ።[1] እንደ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (Encyclopedia Britannica) ደግሞ
‘’ሮጀር ቤከን የአረቢያን ትምህርት በሚገባ እንደተማረ እንዲሁም ብዙዎቹ የሱ ፍልስፍናዎች ከዚሁ ከትምህርቱ የመነጩ መሆናቸው ጥርጥር የለውም’’[2]
እስካሁን የተመለከትናቸው–ሙስሊሞች ለዓለም ስልጣኔ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ላይ የሚያጠነጥኑ እውነታዎች ላይ ብቻ ነው። በቀጣዩ ገጾች ደግሞ እነዚህ እውነታዎች በታሪክ እራሳቸውን መግለፅ መቻላቸውን እንመለከታለን።