4. ይህች ዓለም- የጌታን ፀጋ ተቋዳሽ
የተፈጥሮ ሃብትና ኸሊፋነት
የሰው ልጅ በምድር ላይ የአላህ ኸሊፋ[1] እንዲሆን መፈጠሩ በዓለም ላይ የተበረከቱለትን ሃብቶች እንደመሳሪያ በመጠቀም ይህን የኸሊፋነት ኃላፊነት እንዲወጣ ነው። ቁርኣንም ይህንኑ በሚከተለው መልኩ ግልፅ አድርጎታል።
“በሰማያትም በምድርም ያሉ (ነገሮችን) ሁሉ ገራላችሁ። (ይህ ሁሉ) ከርሱ (የሆነ ችሮታ ነው)። በዚህ ውስጥ ለሚያስተነትኑ ሰዎች ተአምራት አሉ።” (አል-ጃሢያህ 45፤ 13)
ሁሉም በምድር ላይ ያሉትን ነገሮች የሰው ልጅ እንዲጠቀምባቸው (እንዳያበላሻቸው) ተደርገዋል። ከዚህ በዘለለ መልኩ ከምድር ውጪ ያለን ዓለም ለማወቅና ለመመራመር መጣር እና መትጋት አይቻልም ማለት የአላህን ትእዛዝ መጣስ ይሆናል። በአምላክ የተሰጡትን ሃብቶች በተለያዩ የኢኮኖሚ ጥቅሞች እንድናውላቸውና ገደባቸውንም እንድናወቅ መሠረትም ይሆናል።
ኸሊፋነት (ምትክ መሆን)
የሰው ልጅ በምድር ላይ የአላህ ኸሊፋ በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚያከናውነው ወይም የምታከናውነው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የግድ በዚህ የኸሊፋነት መስፈርት የተመዘነ መሆን ይገባዋል። ተውሂድ የአላህን ብቸኛ የበላይንት፣ የዓለማት ትክክለኛ ባለቤት እሱ መሆኑንና የእሱን ንብረቶችን እንዴት መጠቀም እንዳለብን፤ የመወሰን ባለሙሉ መብት እነደሆነ ያረጋግጣል። ስለዚህም ነው ንብረት በኢስላም ውስጥ የሚለካው በኸሊፋነት መስፈርት የሆነው።
በቁርኣን ውስጥ የንብረት ባህሪይ በተለያዩ ተዛምዶ ባላቸው አጠቃላይ ደረጃዎች ይለያያል። በአንደኛ ደረጃ ሁሉም ንብረቶች የአላህ ብቻ ናቸው።
ይህም አገላለፅ የአላህን አጠቃላይ ባለቤትነት ያሳያል። በሌላ ደረጃ ደግሞ ንብረት በተናጠልም ሆነ በህብረት የሰዎች ሃብት ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ በሁሉም የሰው ልጆች መካከል ንብረት ለመያዝ የሚደረግ ፍላጎት አብሮ የተወለደ ባህሪ መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ የሚሆነው ባለቤትነቱ ፍጹማዊ ሆኖ ሳይሆን ይልቁንም አላህ የሰጠን የኸሊፋነት ሃላፊነት ከማረጋገጥ አኳያ ነው። ስለዚህም የነዚህን የባለመብትነት አጠቃቀም የሚፈቀደው የተቀመጠውን የኸሊፋነት መሰፈርት ሲከተል ነው። ይህ ደግሞ በቁርኣን ውስጥ በግልፅ ተቀምጧል። ለዚህም እንደ ምሳሌ የገንዘብና የንብረት አንቀሳቃሾችን አቅም ለሌላቸው ስጡ ብሎ ማዘዙ።
“እነዚያ ለጋብቻ አቅም የሌላቸው አላህ በችሮታው ብቁ እስኪያደርጋቸው ድረስ (ከዝሙት) ይጠበቁ። ከስሮቻችሁ ካሉት ባሮች ውስጥ እነዚያን (ገንዘብ ሰጥተው ራሳቸውን ነጻ ለማድረግ ውል) መጻጻፍ የሚሹትን – ከነርሱ ላይ መልካም ነገርን ካያችሁ – ተጻጻፏቸው። አላህ ከሰጣችሁ ገንዘብም ስጧቸው። ሴቶች ባሮቻችሁም (ከዝሙት) መጠበቅ እየፈለጉ – እናንተ የዚህችን ዓለም ጥቅም በመሻት ዝሙት እነዲፈፅሙ አታስገድዷቸው። ያስገደዳቸው ሰው (ሃጢእቱን ተሸካሚ እርሱ ነው)። (እርሱ ግን) ተገደው (ለሚፈጽሙት ተጠያቂዎች አይደሉም)። ከተገደዱ በኋላ አላህ (ለነርሱ) መሓሪ – አዛኝ ነውና።” (አን-ኑር 24፤33)
“በአላህና በመልክተኛው እመኑ። (አላህ) በእርሱ ላይ ባለአደራ ያደረጋችሁን ገንዘብም (በርሱ መንገድ) ለግሱ። ከመካከላችሁ ለነዚያ ላመኑትና (ገንዘባቸውን በአላህ መንገድ) ለለገሱት ታላቅ ምንዳ ተዘጋችቷል።” (አል-ሐዲድ 57፤7)
የኸሊፋነት (የምትክነት) መስፈርቶች
- ንብረት የምንከፋፈልበትን መንገድ ህጋዊና አግባብ ያለው ማድረግ። ማለትም ከሌብነት የጸዳ፣ ማስገደድ ያልታከለበት፣ በእስልምና ሃይማኖት መሠረት ከተከለከሉ ህገ-ወጥ ስምምነቶች የጸዳ እንዲሁም ከማጭበርበር የራቀ መሆን ይገባዋል።
- አንድ ሰው በንብረቱ ሲጠቀም የሌሎችን ተመሳሳይ የሆኑ መብቶችን መጣስ የለበትም። ለምሳሌ ሰዎች በሚኖሩበት አከባቢ ፋብሪካ ማቋቋም፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ለሌሎች እንዳይደርሱ ማድረግ (ለምሳሌ በባህር ዳርቻዎች ወይም በውሃ መተላለፊያዎችን ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ችግር በሚፈጥር መልኩ መጠቀም)። ይህ ሲባል ንብረት በሚይዝበት ጊዜ የሕዝብን ፍላጎት ከግምት ያስገባ መሆን ይኖርበታል። የህዝብ አውራ ጎዳናዎች ወይም ሌላ የሕዝብ መሠረታዊ የልማት ግንባታዎችን በቦታው ላይ መገንባት ካለበት ቅድሚያ ለባለቤቱ ካሳ ተከፍሎ ቦታው ለህዝብ ጥቅም መዋል ይኖርበታል።
- ባለቤቱ ንብረቱን ለመቆጣጠር በአእምሮ የበሰለ እንዲሁም የመምራት ክህሎቱ ሊኖረው ይገባል። ወይም ደግሞ ተቀጣሪ የሱን ቦታ ወክሎ ሊያገለግል ይችላል። ለምሳሌ ቀለል ባሉ ጉዳዮች መወሰን እንዲችል።
- ፍጹማዊ ባለቤት በሆነው በአምላካችን አላህ እንደተወሰነው በንብረት ላይ ግድ የተደረገውን መጠን ማውጣት፤ መክፈል ይኖርበታል። ‘ዘካት’[2]-ታክስ ወይም ዐስራት አይደለም። ከሁለቱም በበለጠ ሁኔታ የሚያስመሰግን የአምልኮ ተግባር እና ተውሂድ ከንብረት ጋር ያለውን ግንኙነት በተግባር የሚያሳይ ነው። ይህ የተደረገው ሀብትን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማከፋፈል እና በህብረተሰብ ውስጥ የንብረት ነፃነት፣ መተሳሰብና መተባበርን እንዲሰፍን ለማስቻል ነው።
ከተደነገገው አነስተኛ ዘካት በተጨማሪም በአጠቃላይ ሁኔታ ምፅዋት ማብዛት በእጅጉ የሚበረታታ ነው። ምፅዋት ሌሎችም እንዲሰጡ ለማበረታታት ሲባል ያለኩራት በግልፅ በአደባባይ ሊሰጥ ይችላል። ሆኖም ሌላ ሰው ሳይመለከተው በድብቅ መስጠት የተወደደ ነው። ለዚህም ቅዱስ ቁርኣን
“ምጽዋታችሁን በግልጽ ብትሰጡ መልካም ነው። በድብቅ ለድሆች ብታደርሱት ደግሞ ለናንተ የተሻለ ይሆናል። (አላህ በመልካም ስራዎቻችሁ) ሃጢአታችሁን ያብስላችኋል። አላህ የምትሰሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው።” (አል-በቀራ 2፤271)
ነብዩ ሙሐመድም (ሰ.ዐ.ወ) ይህን የለጋስነት ተግባር ከታላላቅ ጀብዶች ውስጥ አስቀምጠውታል፤
“ቀኝ እጁ ስትመጸውት ግራ እጁ ምን እንደፈጸመ የማታውቅ’”
ልክ ኩራትና መመፃደቅን ማስወገድ የአላህ ውዴታና የበጎነት ማሳያ እንደሆነው ሁሉ ነብያቶች ለተከታዮቻቸው ያስተማሩት በጎ ተግባር ነው።
“በአንድ ሰው ንብረት ውስጥ ከዘካ በተጨማሪም የሚደረጉ ምፅዋቶች አሉ።” ነብዩ ሙሀመድ እንዳስተማሩት።
ሥራ አምልኮ ነው
ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሁሉም ተግባራት እምቅ ኃይል ያላቸው እንቅስቃሴዎች ስለሆኑ ሥራ በሕይወት የመቆያ መንገድ ብቻ ሳይሆን ሽልማት የሚያሰጥ የአምልኮ ተግባር ጭምር ነው። ይህ ሃሳብ ምርታማነትን ለማነቃቃት በጊዜ ገደብ፣ በሚጠበቀውና በዋናነት ደግሞ በውጤታማ ሥራ ለመመስገን ወሳኝ ነው። እነዚህ ከየትኛውም ውስን ሃሳብና ግለሰብ የራቁ ናቸው። ይህ ደግሞ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሰጡት መመሪያ እንዲህ ተብሎ ይብራራል። “አንድ ሰው ችግኝ እየተከለ የትንሳኤ ቀን ቢታወጅ መጀመሪያ የያዘውን ሥራ ይጨርስ”።
አንድ ሰው እንዲህ ሊል ይችላል “ችግኝ ተካዩ ወዲያውኑ ሊጠቅመው የማይችል መሆኑን እያወቀ የመትከል ቁም ነገሩ ምንድን ነው? የትንሳኤ ቀን ደርሷል። ለምንስ የተክሉ ፍሬ በጭራሽ ሊበስል እንደማይችል እያወቀ ይተክላል?”
ችግኙን ይትከል የተባለበት የራሱ የሆኑ ምክንያቶች አሉት። ይህ ረዘም ላለ ጊዜ የመሥራት አስተሳሰብን ለማስረፅ እና ምናልባትም መጪውን ትውልድ በማሰብና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከፈጣሪ ሽልማትን በመከጀል ነው።
ይህ ነብዩ ካስተማሩት ጋር ደግሞ አንድ ዓይነት መንፈስ አለው።
“አንድ ሰው ችግኝ ከተከለ ከሱ ደግሞ የሰው ልጅ፣ እንስሳ ወይም ወፍ ከተመገበ እሱ/እሷ ከፍሬው ተጠቃሚ ከሆኑት ሁሉ ምንዳ ያገኛል/ታገኛለች” (ሙስሊም)።
በተመሳሳይ መልኩ ወደ ፈጣሪ ለማቃረብ አንድ ሰው ለስነ-ምህዳር (ecology) ያለው አመለካከት በጊዜ ያልተገደብ አርቆ አሳቢነትና ትልቅ አላማ ያነገበ ሊሆን ይገባዋል። ይህ ደግሞ ለመጪው ትውልድ ፍላጎት መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ለእዚህም እነደምሳሌ ተጠቃሽ የሚሆነው ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ውዱእ ሲያደርግ ውሃ ያባክን የነበረን ሰሃባ ባዩ ጊዜ ስህተት መሆኑን በምልክት ሲያሳውቁት
“ውሃን በመጠቀም ማባከን አለ’’ ብሎ ጠየቃቸቀው። ነብዩም “አዎን በወራጅ ውሃ እንኳን ውዱዕ ብታደርግ”’ በማለት መለሱለት። (አህመድና ኢብኑ ማጃህ)
ኢስላም አንድ ሰው አላህ ፊት ከመቅረቡ በፊት ያለበትን ኃላፊነት ያስተምራል። እንዲሁም በትንሰኤ ቀን እና ከዚያ በኋላ ዘላለማዊ ህይወት እንዳለ እንዲያምኑ ይህም ደግሞ በምድር ላይ ሳለን በሰራነው ስራ ይወሰናል።
ተውሂድ በሌላ በኩል ደግሞ በፈጣሪ መገለጫዎች ፍፁምነት ማመን ማለት ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ፍፁማዊ ዕውቀት አንዱ ነው። በልብ የሚታሰብ ሚሰጥር እንኳን ቢሆን ከፈጣሪ ዕውቀት ሊሰወር እንደማይችል መገንዘብ ተገቢ ነው። የእንደዚህ አይነቱ እምነት ውጤት ደግሞ ከሀጢያትና ከመጥፎ ድርጊቶች ለመራቅ እራስን ማነፅና ሁሉን ነገር ፈር ማስያዝ ሲሆን እንዲህ አይነቱ ተግባር ደግሞ በአላህ ዘንድ ተወዳጅ ያደርገዋል። ይህ በወጉ ከተተገበረ አንዱ በአላህ ዘንድ ያለውን የኃላፊነት ስሜት ያጠራለታል። “ማጭበርበር በምትችለው አቅም አጭበርብር እስካልተያዝክ ድረስ’’ የሚባል ነገር በኢስላም እንደማይሰራ፤ ወይንም ደግሞ ከአላህ ምንም አይነት ነገር ሊደበቅ እንደማይችል እንዲሁም እያንዳንዱ በሚፈጽመው ድርጊት ተጠያቂ መሆኑ ያስተምራል። ያም ደግሞ የአላህን ፍራቻ (ተቅዋን) ያዳብራል።