ስለ ሲሳይ (ሪዝቅ) ስናነሳ አዕምሯችን ቶሎ ብሎ ወደ ገንዘብና ወደ ትላልቅ ህንፃዎች ጠልቆ ይገባል፡፡ ሌላው አዕምሮውም ከዚህ በላይ አልፎም ስለ ልጆች፣ ስለጤና፣ ስለ ደስታና ሚስት (ባል) ሊያስተነትን ይችላል፡፡ ምናልባት ሁሉም “ስልቻ የያዘውን…” የሚባለው አባባል ለምንለው ጉዳይ ጥሩ ምሳሌ ሳይሆን አይቀርም፡፡

የገንዘብ ጉዳይ አዕምሮውን ወጥሮ የያዘው ሰው፣ ዋናው ሲሳዩ ገንዘብ ማግኘት ይሆናል፡፡ ደስታ የሚያገኘው በልጆች ነው ብሎ ለሚያምን ሰው ደግሞ የሚፈልገውን በማግኘቱ አላህ እንዳከበረው አድርጎ ሊቆጥር ይችል ይሆናል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ አላህ ያማረ ሲሳይ የሰጠው ሰው፣ አላህ እውነተኛ ፀጋውን እላዩ ላይ እንዳፈሰሰበት አድርጎ ያስባል፡፡ በአባባልም “ምርጥ የሆነ ነገር ከተሰጠህ፣ አላህ አንተን መርጦሀል” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡

ሲሳይና አይነቶቹ

የሲሳይ ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ መልኮቹም እንዲሁ በአይናችን ከምናያቸው ነገሮች እንደ ገንዘብ፣ ልጅ፣ ሚስት፣ ህንፃ፣ ስልጣን፣ የትምህርት ደረጃ፣ ወዘተ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ከማይዳሰሱትና ከማይጨበጡት ደግሞ ዕውቀት፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ጤና ደግሞ ከሁሉም ወገን የሚመደብ ይሆናል፡፡

ኢማን ከሲሳዬች ዋንኛው ሲሳይ ነው፡፡ ደረጃውም ሰውዩው አላህ ጋር እንዳለው ግንኙነትና የአላህን ሲሳይ ለማግኘት እንዳለው ዝግጁነትም ይለያያል፡፡

ከሲሳይ መካከል ኢማንና የቂን (እርግጠኝት) ተጠቃሾችም ናቸው፡፡ በሐዲስ እንደተጠቀሰው ረሱል ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም

إن العبد ليحرم الرزق بالذنب يصيبه

“አንድ ሰው በሚሰራው ወንጀል ምክንያት ሲሳይ ሊከለከል ይችላል” ብለዋል፡፡

በሌላ ሐዲስም

إن للمعصية ظلمة في القلب وسوادا في الوجه وإن للحسنة ضياء في القلب وسعة في الصدر ونورا في الوجه

“ወንጀል ቀልብን ያጨልማል፤ ፊትን ያጠቁራል፡፡ በጎ ነገር ደግሞ ቀልብን ያበራል፤ ደረትን ያሰፋል፤ ፊትን ያፈካል”፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ኢማን ሲኖር ነው፡፡ ኢማን ከሲሳዬች ዋንኛው ሲሳይ ነው፡፡ ደረጃውም ሰውዩው አላህ ጋር እንዳለው ግንኙነትና የአላህን ሲሳይ ለማግኘት እንዳለው ዝግጁነትም ይለያያል፡፡ ይህን ጉዳይ ቀጣዩን የረሱል ሐዲስ የሚያመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ረሱል ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም

إن للقلوب إقبالا وإدبارا، فإن أقبلت فزيدوها وإن أدبرت فألزموها الفرائض

“ቀልብ ንቁና ፍዝ የምትሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ ንቁ በምትሆንበት ጊዜ መልካም ነገር እንድትሰራ አድርጓት፡፡ ፍዝ በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ ግዴታዎችን እንድትሰራ አድርጓት” ብለዋል፡፡

እንግዲህ ከሲሳይ ሁሉ ኢማን ዋንኛው ሲሳይ ከሆነ ቀልብ በኢማን ልታድግና ልትመነደግ ይገባታል፡፡ ይህች የአላህ ሰጦታ የሆነች ቀልብ አላህን ማሰቢያ ቦታ እንደሆነች ሁሉ ሰዎች ወንጀልንም ይፈጽሙባታል፡፡ አላህ ለሰዎች ሲሳይንና ቀልብን መስጠቱን ቁርኣን

أَهُمْ يَقْسِمُونَ رَحْمَتَ رَبِّكَ نَحْنُ قَسَمْنَا بَيْنَهُم مَّعِيشَتَهُمْ فِي الْحَيَاةِ الدُّنْيَا وَرَفَعْنَا بَعْضَهُمْ فَوْقَ بَعْضٍ دَرَجَاتٍ لِّيَتَّخِذَ بَعْضُهُم بَعْضًا سُخْرِيًّا وَرَحْمَتُ رَبِّكَ خَيْرٌ مِّمَّا يَجْمَعُونَ

“እነርሱ የጌታህን ችሮታ ያከፈፍላሉን? እኛ በቅርቢቱ ሕይወት ኑሯቸውን በመካከላቸው አከፋፍለናል፡፡ ከፊላቸውም ከፊሉን ሠራተኛ አድርጎ ይይዝ ዘንድ ከፊላቸውን ከከፊሉ በላይ በደረጃዎች (በሀብት) አበለጥን፡፡ የጌታህም ጸጋ (ገነት) ከሚሰበስቡት (ሃብት) በላጨ ናት፡፡” (አል-ዙኸሩፍ፣32) ይላል፡፡

የአንተ ቀልብ

ቀልብ የአላህ ስጦታ ነው ስንል ሁለት ነገሮችን ይይዛል፡፡ አንደኛው የአንተ ቀልብና የሌላው ቀልብ ነው፡፡ በአንተ ቀልብ እንጀምርና፣ ረሱል እንዲህ ብለዋል፡- “በአንተ በራስህ (ነፍስ) ጀምር ከዚም በምትቀርባቸው …” ብለዋል፡፡ ይህ ቀልብህ የአላህ ስጦታ ነው፡፡ ማነው የእዝነት ስሜት የርህራሄ ስሜት፣ እንዲኖርህ ያደረገው? ይህ አንቀፅ ሲቀራ

إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ الَّذِينَ إِذَا ذُكِرَ اللَّهُ وَجِلَتْ قُلُوبُهُمْ وَإِذَا تُلِيَتْ عَلَيْهِمْ آيَاتُهُ زَادَتْهُمْ إِيمَانًا وَعَلَىٰ رَبِّهِمْ يَتَوَكَّلُونَ

“ፍጹም ምእምናን እነዚያ አላህ በተወሳ ጊዜ ልቦቻቸው የሚፈሩት፣ በነሱም ላይ አንቀጾቻችን በተነበቡ ጊዜ እምነትን የሚጨምሩላቸው፣ በጌታቸውም ላይ ብቻ የሚመኩት ናቸው፡፡” (አል-አንፋል፣2)

ፍርሀትና የስጋት ስሜት እንዲኖርህ ያደረገውስ ማነው? የአላህን ዚክር እንድትዘክር ቀልብህን ማን አለሳለሰው?

ثُمَّ تَلِينُ جُلُودُهُمْ وَقُلُوبُهُمْ إِلَىٰ ذِكْرِ اللَّهِ ذَٰلِكَ هُدَى اللَّهِ يَهْدِي بِهِ مَن يَشَاءُ وَمَن يُضْلِلِ اللَّهُ فَمَا لَهُ مِنْ هَادٍ

“ከዚያም ቆዳዎቻቸውና ልቦቻቸው ወደ አላህ (ተስፋ) ማስታወስ ይለዝባሉ፡፡ ይህ የአላህ መምሪያ ነው፡፡ በእርሱ የሚሻውን ሰው ይመራበታል፡፡ አላህም የሚያጠመው ሰው ለእርሱ ምንም አቅኚ የለውም፡፡” (አል-ዙመር፣23)

ለበጎ ነገር እንዲነሳሳ ቀልብህን ማድረጉ የሱ ስጦታ አይደለምን? ቀልብህን ማስፈቱስ? ከመጥፎ ነገር መደንገጡስ? ቀልብህ ቁርአን ሲቀራ ከፍርሀቱ የተነሳ ዓይን እንዲያነባ ያደረገውስ ማነው? ይህን የምታደርግበት ስሜት የሰጠህ አላህ አይደለምን? ይህ ቀልብ ለደካማ ያዝናል፤ ለመስኪኖች ደግሞ ተገቢ ምላሽ ይሰጣል፤ ህፃናትን ይወዳል፤ የቲሞችን ይዳስሳል፤ ትንሽም ብትሆን ሶደቃ ይሰጣል፤ ሀዘን የገባውንና መጥፎ ቀናትን ካሳለፈው ሰው አፉ ላይ የሆነ ነገር ያስቀምጣል፡፡

“ጤና ባለቤቱ ያላወቃት ጭንቅላቱ (ራሱ) ላይ ያለች ዘውድ ነች” ከተባለው፣ እኛ ደግሞ “የአላህ ፀጋ የሆነው ሲሳይ፣ በባለቤቱ እጅ ነው ያለው” እንላለን፡፡ ይህን የሚያውቀው ያጣው ሰው ነው፡፡ የቀልብን ደረጃ ፀጋ የሚያውቀው፤ የቀልብን ፀጋ የተነጠቀ ሰው ነው፡፡ ለእዚህም ቁርአን ማስረጃ ይሆነናል፡-

أَفَلَا يَتَدَبَّرُونَ الْقُرْآنَ أَمْ عَلَىٰ قُلُوبٍ أَقْفَالُهَا

“ቁርኣንንም አያስተነትኑምን? በእውነቱ በልቦቻቸው ላይ ቁልፎቿ አልሉባትን?” (ሙሐመድ፣24)

ቁርአን በዚህ አንቀፅ፣ ቀልብ የማስተንተን ፀጋ ስትነጠቅ፣ ዝግ ትሆንና የአላህን ሲሳይ መቀበል ይሳናታል፡፡ በሐዲሶችም እንደተወሳው ረሱል ሐሰንና ሑሴን ሲስሙ የተመለከተው ሰው፣ ለረሱል ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “እኔ አስር ልጆች ሲኖሩኝ አንዱንም ስሜው አላውቅም” አላቸው፡፡ ረሱልም እንዲህ ብለው መለሱለት “ምናልባት አላህ እቀልብህ የእዝነትን ስሜት አውጥቶብህ ይሆናል፡፡ የማያዝን ሰው አይታዘንለትም” አሉት፡፡

ቀልብ የማሰብና የማስተንተን ሲሳይን ሲነፈግ፣ በጎ ነገርን ይቀማል፤ የቅን ጎዳናውም ይዘጋበታል፡፡ በዚህም የአላህን ጥሪ ለመቀበል ፈቃደኛ አይሆንም፡፡

ከአላህ ሲሳይ የተነፈገ ቀልብ የአላህን ቱሩፋት የሚያጣ ይሆናል፡፡ ቁርአን፣ ቀልብ ከተሰጡ በኋላ ቀልብ መስራት የሚገባውን ስራ እንዳይሰራ የተነፈጉም እንዳሉ ይናገራል፡፡ ይህም የአላህን ፀጋ እንዳያውቅ መነፈጉ ነው

لَهُمْ قُلُوبٌ لَّا يَفْقَهُونَ بِهَا

“በእውነቱ በልቦቻቸው ላይ ቁልፎቿ አልሉባትን?” (አል-አዕራፍ፣7)፡፡

እነዚህ ሰዎች የቀለብን ተገቢ ስራ ያጡ፤ የመገንዘብ፣ የመረዳትና የማስተዋልንም ስጦታ የተነፈጉ ናቸው፡፡ የዚህ ቀልብ ሲሳዩን መነፈጉ ቀልብ ጥሩውን እንዳይመለከት የተጋረደበት መሆኑ፣ የኢማን መዓዛ የማሽተት ዕድል ማጣቱ፣ የእርግጠኛነትና (የቂን) ጣዕም መቀማቱ ነው፡፡ ይህ የሚሆንው አንድ ሰው መንፈሱን ለማርካት ጥረት ከማድረጉ ይልቅ፣ አካላዊ እርካታን ለማግኘት መጣሩ ነው፡፡ በተጨማሪም የሲሳይ ምንጭ ከሆነው አላህ ጋር ግንኙነቱ የተቋረጠ ነው

أَفَرَأَيْتَ مَنِ اتَّخَذَ إِلَٰهَهُ هَوَاهُ وَأَضَلَّهُ اللَّهُ عَلَىٰ عِلْمٍ وَخَتَمَ عَلَىٰ سَمْعِهِ وَقَلْبِهِ وَجَعَلَ عَلَىٰ بَصَرِهِ غِشَاوَةً فَمَن يَهْدِيهِ مِن بَعْدِ اللَّهِ أَفَلَا تَذَكَّرُونَ

“ዝንባሌውን አምላኩ አድርጎ የያዘውን፣ አላህም ከዕውቀት ጋር ያጠመመውን፣ በጆሮውና በልቡ ላይም ያተመበትን፣ በዓይኑም ላይ ሺፋን ያደረገበትን ሰው አየህን! ታዲያ ከአላህ በኋላ የሚያቀናው ማነው? አትገሠጹምን?” (አል-ጃሲያ፣23)፡፡

ቀልብ የማሰብና የማስተንተን ሲሳይን ሲነፈግ፣ በጎ ነገርን ይቀማል፤ የቅን ጎዳናውም ይዘጋበታል፡፡ በዚህም የአላህን ጥሪ ለመቀበል ፈቃደኛ አይሆንም፡፡ በሰውዩው ና በአላህ መካከል ግርዶሽ ይኖራል

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اسْتَجِيبُوا لِلَّهِ وَلِلرَّسُولِ إِذَا دَعَاكُمْ لِمَا يُحْيِيكُمْ وَاعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ يَحُولُ بَيْنَ الْمَرْءِ وَقَلْبِهِ وَأَنَّهُ إِلَيْهِ تُحْشَرُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! (መልክተኛው) ሕያው ወደሚያደርጋችሁ እምነት በጠራችሁ ጊዜ ለአላህና ለመልክተኛው ታዘዙ፡፡ አላህም በሰውየውና በልቡ መካከል የሚጋርድ መኾኑን ወደርሱም የምትሰበሰቡ መኾናችሁን እወቁ፡፡” (አል-አንፋል፣24)

በዚህ ጊዜ ቀልብ ይደርቃል፤ የድንጋይነት ባህሪይ ይይዛል

ثُمَّ قَسَتْ قُلُوبُكُم مِّن بَعْدِ ذَٰلِكَ فَهِيَ كَالْحِجَارَةِ أَوْ أَشَدُّ قَسْوَةً

“ከዚያም ከዚህ በኋላ ልቦቻችሁ ደረቁ፤ እርሷም እንደ ድንጋዮች ወይም በድርቅና ይበልጥ የበረታች ናት፡፡ ከድንጋዮችም ከርሱ ጂረቶች የሚፈሱለት አልለ፡፡ ከነርሱም በእርግጥ የሚሰነጠቅና ከርሱ ውሃ (ምንጭ) የሚወጣው አልለ፡፡ ከነርሱም አላህን ከመፍራት የተነሳ ወደ ታች የሚወርድ አልለ፡፡ አላህም ከምትሠሩት ነገር ዘንጊ አይደለም” (አል- በቀራ፣74)፡፡

የቀልብ መተሳሰር

ብዙዎቹ ለአላህ ብሎ መውደድን ችላ ይላሉ፡፡ አላህ ላቅ ባለ ደረጃ ቀልብን በጥሩ ስሜት ያቀራረበና ያስተሳሰረ ነው፡፡ አላህ ቀልብን ከሌላው ጋርም የሚያላምድ ነው

وَأَلَّفَ بَيْنَ قُلُوبِهِمْ لَوْ أَنفَقْتَ مَا فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا مَّا أَلَّفْتَ بَيْنَ قُلُوبِهِمْ وَلَٰكِنَّ اللَّهَ أَلَّفَ بَيْنَهُمْ إِنَّهُ عَزِيزٌ حَكِيمٌ

“በልቦቻቸውም መካከል ያስማማ ነው፡፡ በምድር ያለውን ሁሉ (ሀብት) በለገስክ ኖሮ በልቦቻቸው መካከል ባላስማማህ ነበር፡፡ ግን አላህ በመካከላቸው አስማማ፡፡ እርሱ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡” (አል-አንፋል፣63)፡፡

ሌላው ቀልብ ደግሞ የሰዎችን ቀልብ ለመማረክ ለሚጥሩ ዳዒዎች ትኩረት ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ቀልብ የአላህ ሲሳይ ነው እንላለን፡፡ ይህ ማለት አንተ ወደ አላህ መንገድ ጥሪ ለሚያደርጉ ሰዎች ምላሽ ትሰጣለህ ማለት ነው፡፡ ሌላው ቀልብ ግን ማዳመጫው ስለተዘጋ ነገሮች ይዘጋጉበታል፡፡ ስለሆነም ወደ አላህ መንገድ ጥሪ ለሚያደርጉ ሰዎች ምላሽ ለመስጠት ይሳነዋል፡፡

አላህ የሰው ልጅ ቀልብን ለመማረክና ሪዝቅ ያገኝ ዘንድ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት ይናገራል

هُوَ الَّذِي جَعَلَ لَكُمُ الْأَرْضَ ذَلُولًا فَامْشُوا فِي مَنَاكِبِهَا وَكُلُوا مِن رِّزْقِهِ وَإِلَيْهِ النُّشُورُ

እርሱ ያ ምድርን ለእናንተ የተገራች ያደረገላችሁ ነው፡፡ በጋራዎችዋና በመንገዶችዋም ኺዱ፡፡፡ ከሲሳዩም ብሉ፡፡ (ኋላ) መመለሻውም ወደእርሱ ብቻ ነው፡፡(አል-ሙልክ፣15)፡፡

ከምንም በላይ ቀልብን ለመማረክ የሚደረገው ጥረት ከሁሉ በላጭ ነው፡፡

ረሱል ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አላህ ሰፊ የሆነ የቀልብ ሲሳይ የሰጣቸው፣ አላህ ስለወደዳቸው ነው፡፡ በሰዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደር እንዲችሉም እገዛ አድርጎላቸዋል፡፡ ጠንካራ፣ ሰፊ የሆነ ትዕግስትና እዝነትን ስለተላበሱ ጭምርም ነው፡፡ ከራሳቸው በበለጠ የባልደረቦቻቸውን ሁኔታ በቅጡ ጠባቂና ጉዳያቸውንም በቅርቡ ተመልካች ናቸው

وَاعْلَمُوا أَنَّ فِيكُمْ رَسُولَ اللَّهِ لَوْ يُطِيعُكُمْ فِي كَثِيرٍ مِّنَ الْأَمْرِ لَعَنِتُّمْ وَلَٰكِنَّ اللَّهَ حَبَّبَ إِلَيْكُمُ الْإِيمَانَ وَزَيَّنَهُ فِي قُلُوبِكُمْ وَكَرَّهَ إِلَيْكُمُ الْكُفْرَ وَالْفُسُوقَ وَالْعِصْيَانَ أُولَٰئِكَ هُمُ الرَّاشِدُونَ

“በውስጣችሁም የአላህ መልክተኛ መኖሩን ዕወቁ፡፡ ከነገሩ በብዙው ቢከተላችሁ ኖሮ በእርግጥ በተቸገራችሁ ነበር፡፡ ግን አላህ አምነትን ወደናንተ አስወደደ፡፡ በልቦቻችሁም ውሰጥ አጌጠው፡፡ ክህደትንና አመጽንም እንቢተኛነትንም ወደናንተ የተጠላ አደረገ። እነዚያ (እምነትን የወደዱና ክሕደተን የጠሉ) እነርሱ ቅኖቹ ናቸው፡” (አል-ሑጁራት፣7)፡፡

የቀልብ ጉዳይ በደንብ የተመለከተው ሰው፣ ቀልብ ከአላህ ጋር ያለውን ግንኙነት ባጠናከረና በሱ ትዕዛዝ ቀጥ ባለ ቁጥር፣ የአላህ ሲሳይ ይጨምርለታል፡፡ ለዱንያም ያለው ጭንቀት ዝቅተኛ (ዱንያን ማሳነስ) እና ኢማኑም ይጨምርለታል፡፡ ከሌላ የሚፈልገው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም አላህ ከሱ ጋር ነውና፡፡ ኢብኑ ዐጧአላህ አል-እስክንድሪይ እንዲህ ብለዋል፡-

إلهي! ماذا وجد من فقدك، أم ماذا فقد من وجدك. عميت عين لا تراك عليها رقيبا، وخسرت صفقة عبدٍ لم يجعل له من حبك نصيبا

“ጌታዬ! አንተን ያጣህ ምን አገኘ! አንተን ያገኘህስ ምን አጣ?! ተጠባባቂ አይን እንኳ የማታይህን ሌላው ዐይን አያይህም፡፡ የአንተን ውዴታ የተነፈገው ሰውም ከሰረ፡፡

ደረቅ ቀልብ የሚያመነጨው ነገር የለውም፡፡ መልካም ቀልብ እሳት አይገባም፡፡ ከቀልብ የወጣ ቀልብ ይዳረሳል፡፡ ከምላስ የወጣ ከጆሮ አያልፍል፡፡ እንግዲህ የቀልብ መንገድ ይህ ከሆነ የኛና የሌላው የቀልብ ሪዝቅ ይጨምር ዘንድ በዚህ መንገድ እንትጋ! ከፈለጉት ጉዳይ አድራሹ አላህ ነው፡፡

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here