ሙስሊሞች ለግብርና ያበረከቱት አስተዋፅኦ

0
2334

መግቢያ

ታሪክ ብዙን ጊዜ የግብርና አብዮት የተካሄደው በቅርቡ ማለትም የሰው ልጅ አፈራርቆ መዝራትን፣ የተለያዩ ዘመናዊ የመስኖ አጠቃቀም ስልቶችንና የተሻሻሉ የእፅዋት ዝርያዎችን መጠቀም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ያትታል። ይህ አብዮትም በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የአውሮፓን ህዝብ ለመመገብ ያስቻለ እንደሆነና ከዚህም ሌላ በርካቶችን ከመሬቶቻቸው እንዲነሱ በማድረግ የእርሻ ምርትም ተትረፍርፎ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሣደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ይገልፃል። ኋላ ላይም ከ18ኛው እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ለተከሠተው የኢንዱስትሪው አብዮት ምክኒያት ሆኗል ይለናል።

በሙስሊሙ ዓለም የነበረው የግብርና ሁኔታ ተጠንቶ የግብርናው አብዮት በሙስሊሙ ዓለም ከምእተ አመታት በፊት አስቀድሞ የነበረ መሆኑ እስከተደረሰበት ጊዜ ድረስ ይህ አመለካከት ተቀባይነት አግኝቶ ቆይቷል። ያኔ በሙስሊሙ ዓለም ከግብርና አንፃር ከተከሰቱት ለውጦች መካከል ዛሬ ላለንበት ደረጃም ጭምር መሠረት የሆኑ ይገኙበታል።

ዋትሰን (Watson)፣ ግሊክ (Glick) እና ቦለንስ (Bolens)[1] የተባሉ ተመራማሪዎች በተለይ በጉዳዩ ዙሪያ ባደረጉት ጥናት በወቅቱ የሙስሊሞቹ አመርቂ ግኝቶችና የደረሱበት ደረጃ በገበሬዎቹ ዘንድ በመሬቶቻቸው ላይ ተተግብሮ፤ ምሁራኖቻቸው በጉዳዩ ዙሪያ በፃፏቸው ድርሰቶች ውስጥ አካተውት እንደነበረ አስረድተዋል። ከሁኔታው መገንዘብ የምንችለው በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሙስሊሙ የስኬት ታሪክ እንደተበረዘ ሁሉ በዚህ መስክም በተለይም ከአሥራዎቹ ምእተ አመታት በፊት የነበረው የሙስሊሞች ግኝት እንዲሁ ተቀምቶ ለሌላ አካል እንዲሆን የተደረገ መሆኑን ነው።

ቼርቦናሁ ሲናገር

“it is admitted with difficulty that a nation in majority of nomads could have had known any form of agricultural techniques other than sowing wheat and barley. The misconceptions come from the rarity of works on the subject. If we took the bother to open up and consult the old manuscripts, so many views will be changed, so many prejudices will be destroyed..”

“በርግጥም በአብዛኛው ዘላን ህዝብ በሚኖርበት (የሙስሊሙ) ምድር ላይ ያሉ ህዝቦች ስንዴና ገብስ ከማምረት ውጭ ስለተለያዩ የእርሻ ዘዴዎችና ስልቶች ጠንቅቀው ያውቃሉ ብሎ መቀበሉ የሚከብድ ይመስላል። የተሣሣተ ግንዛቤው የመነጨው በጉዳዩ ዙሪያ የተሠራው ሥራ አነስተኛ በመሆኑ ነው። ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን ጥንታዊ ፅሁፎችን ብንመለከት ግን ብዙ አመለካከቶች ይቀየራሉ። በርካታ መላምቶችም ይበላሻሉ።” ብሏል።[2]

የግብርና አብዮት

በ9ኛው መቶ ክ/ዘመን መባቻ አካባቢ ዘመናዊው የግብርናው ሥርዓት የሙስሊም ዓለም የኢኮኖሚው ህይወትና የታላላቅ ድርጅቶችም ሞተር ነበር። አርትዝ (Artz) እንዳብራራው በቅርብ ምስራቅ፣ በሰሜን አፍሪካና ስፔን የሚገኙ ትላልቅ ኢስላማዊ ከተሞች ሰፋፊ መስኖዎችን፣ በወቅቱ በዓለም ላይ ይገኛሉ የተባሉ የግብርና እውቀቶችንና እጅግ የተራቀቁ የግብርና ሥልቶችን ይጠቀሙ ነበር። ሙስሊሞች በጊዜው ድንቅ የተባሉ ፈረሦችንና በጎችን በማርባት የሚታወቁ ከመሆኑም በላይ ምርጥ የተባሉ የአትክልት ቦታዎችንና የፍራፍሬ ማሣዎችንም ያዘጋጁ ነበር። ከዚህም ሌላ መርዘኛ የሆኑ ነፍሣትን እንዴት መከላከል እንደሚችሉና ማዳበሪያን እንዴት እንደሚጠቀሙ እውቀት ነበራቸው። ተክሎችን በማዳቀልና ሌሎች አዳዲስ ዝርያዎችን በማግኘት በኩልም ከፍተኛ ክህሎት ነበራቸው።[3]

ግሊክ እንዳብራራው “የውሃ መስመሮችን ማስፋፋትንና የመስኖ ሥራን ማጠናከርን አቀናጅቶ የሚንቀሣቀሰው የሙስሊሙ የግብርና አብዮት አዳዲስ የእህል ዘሮችን ከማስተዋወቁም በላይ የተለያየ ዓይነት የተራቀቀ የእርሻ ሥርዓት ይፈጠር ዘንድም ምክኒያት ሆኗል። በዚህም ምክኒያት የተለያዩ የአፈር ዓይነቶችን ለተለያዩ የእህል ዘሮች በብቃት ለመጠቀም ተችሏል። ከሙስሊሙ የግብርና አብዮት በፊት በአመት አንድ ጊዜ አንድ ዓይነት የእህል ዘር ብቻ ይመረትባቸው የነበሩ መሬቶችም ከሦስት እና ከዚያም በላይ የእህል ዓይነት በማፈራረቅ ሊመረትባቸው ተችሏል። የግብርና ምርቶች ፍላጎት በጨመረባቸው የሰሜን አውሮፓ ከተሞችንም[4] በተለያዩ ዓይነት ቀድመው በማይታወቁ የግብርና ምርቶች ማዳረስ ችለው ነበር። ስኮት በተለይ በወቅቱ የነበረውን የስፔናውያን ሙስሊሞች የእርሻ ሥርዓት ሁኔታ ሲገልፅ:-

“the most complex, the most scientific, the most perfect, ever devised by the ingenuity of man..”

“እጅግ የተራቀቀ፣ እጅግ ሳይንሣዊ፣ እጅግ የተሟላና በሰው ልጅ የፈጠራ ታሪክ ውስጥም ያልታየ ነው።” ብሏል።[5]

ቦለንስ በበኩሉ በግብርናው በኩል ሙስሊሞች የደረሱበት ደረጃ የእርሻ ስልቶችን ከአካባቢው አስፈልጎት ጋር አጣጥሞ መሄድ በመቻሉና ከቅርብ ምስራቅ፣ ከመግሪብ እስከ ምዕራብ አንዱሊስያ ስፔን ድረስ አስደናቂ የሆነ ሣይንሣዊ የእውቀት አንድነትና ውህደት መፍጠር በመቻሉ መሆኑን ያስረዳል። በሰው ልጅ የስነምህዳር ጥበቃ ታሪክ ውስጥም ከፍተኛ ስኬት ታይቶበታል።[6] የተለያዩ ዓይነት ማዳበሪዎችም በተሻሻለ ሁኔታ ጥቅም የዋሉ ሲሆን የአፈር እርጥበትንም ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ ለመጠበቅ ተችሏል። የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልም ተከታታይ ሥራዎች ይሠሩ ነበር። ቦለንስ ጨምሮም ዘመኑን “ሥነ-ምህዳር /ኢኮሎጂ/ን በመቆጣጠሩ ረገድ ወርቃማ ነበር።” ብሎታል።[7]

እንደ ስኮት ገለፃ “የትኛውም ተፈጥሮአዊ መሠናክል የሙስሊሞችን ኢንዱስትሪና የግብርና ድርጅቶች ጥረት የመጋፈጥ አቅም አልነበረውም። በስፔን የተራራ ሰንሰለቶችን በመቦርቦር የውሃ መስመሮች ጥልቀት ወዳላቸው ሸለቆዎች እንዲወርዱ ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ ትእግስትን በሚጠይቅ አድካሚ ጉልበትም ወደ ላይ ወጥተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረግ ነበር።”[8]

ዋትሰን ሲያጠቃልል[9] የእርሻ መሬቶች ምርት ለመጨመራቸው ምክኒያት የነበረው የተሻለ የመሬት አጠቃቃም ዘዴን ተግባር ላይ በማዋል ድሮ የነበሩ የእህል ዘሮች በአዳዲስና ብዙ ምርት በሚሠጡ የተለያዩ የእህል ዘሮች በመተካታቸው ነው። ዘመናዊ የመስኖ አሠራር፣ አፈራርቆ መዝራት፣ አዳዲስ የእህል ዘሮችን መጠቀም፣ አዳዲስ መሬቶችን ማረስና የተለያየ ዓይነት የጉልበት ሥራ ዘዴዎችን መጠቀማቸው ለለውጡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ይህ ለውጥ ከግብርናው ላይ ሣይወሰን ለሌሎች ዘርፎችን መነቃቃትም ምክኒያት ሆኗል። ንግድ ተስፋፍቷል። የገንዘብ ኢኮኖሚ ጥቅም ላይ ውሏል። በሁሉም ዘርፎች ፋብሪካዎች ተገንብተዋል። የህዝብ ብዛት እየጨመረ ሲሄድም ከተሞች መስፋፋት ችለዋል።

የመስኖ ሥራ ከአንዱሊስያ ስፔን እስከ ሩቅ ምስራቅ፤ ከሱዳን እስከ አፍጋኒስታን የሁሉም ግብርና መሠረትና የህይወት ምንጭ ማዕከል ነበር። ሙስሊሞች ከቀደምቶቻቸው የወረሱት ጥንታዊው የመስኖ አሠራር ሥርዓት ተዳክሞ ተንኮታክቶ በነበረበት ሁኔታ ሲሆን እነሱ ከተረከቡት በኋላ ግን የጥገናና በአዲስ የመገንባት ስራዎች አከናውነዋል። በተጨማሪም ውሃውን ለመጥለፍ፣ ለማስተላለፍ፣ ለማጠራቀምና ውሃን ወደ ከፍታ ቦታ ለመውሰድ አዳዲስ ስልቶችንና መሳሪያዎችን ተጠቅመዋል። ቦለንስ የጠቀሰው የመግሪብ፣ የአንዱሊሲያ፣ የግብፅ፣ የዒራቅ፣ የፐርሺያም ይሁን የየመን ኪታብ አል-ፊላሃት (የእርሻ መፅሃፍ) በዋናናት የሚያተኩረው ለእርሻ ተግባር የሚያገለግሉ የተለያዩ መሳሪያዎችን በማስተዋወቅ እና በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ነው።[10]

የግብርና ማሽኖችና ግንባታዎች

በተለያየ ስልት የተጠለፈው ውሃ በቦይ/ቱቦ አማካይነት እንዲተላለፍ ይደረግና ከተጠራቀመ በኋላ ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም ለተለያዩ ሥራዎች ይውል ዘንድ ወደሚፈለግበት ቦታ ይወሰዳል። ይህም ተግባር የመስኖ ሥራን እጅግ ርካሽ ከማድረጉም በላይ ለመስኖ አዋጭ አይደሉም አለያም አይቻሉም ተብለው የተተው ቦታዎች ጭምር ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል። በመስኖ ከሚለሙ መሬቶች በአመት እስከ አራት ጊዜ ድረስ ምርት ማግኘት የተቻለ ሲሆን ይህም በተለይ ለሙስሊም ስፔን መበልፀግ ዋንኛ ምክኒያት ነበር[11]። ወንዞችን በመገደብ በሀይል የሚሰሩ ወፍጮዎችንና የመስኖ ሥራን ማስፋፋት ተችሏል። የኖሪያ (noria) መገኘት (ውሃ ለማውጣት የሚያገለግል መሣሪያ) በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የግብርናው ኢኮኖሚ ይበልጥ እንዲያንሠራራ ያደረገው አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም። ኖሪያ ለመገንባትም ሆነ ለመጠገን በአንፃራዊነት ብዙ ወጭ የማይጠይቅ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ በመስኖ ለመጠቀም ተችሏል።

አል-ሻቁንዲ (13ኛ ክፍለ ዘመን) እንደሚለው በኮርዶባ ጓዳቂልቪር ብቻ 5ሺህ ያህል ኖሪያዎች (መሳሪያ) ነበሩ።[12] የተወሰኑ ኖሪያዎች ከሙርሲያ ከተማ 6 ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው ላ ኖራ ዛሬም ድረስ አገልግሎት ላይ ናቸው። ምንም እንኳ ቀደምት የነበሩ መዘውሮች በንፁህ ብረት የተቀየሩ ቢሆንም የሙስሊሞቹ አሻራ ግን ዛሬም ድረስ አልተቀየረም። በአጠቃላይ ይህ ወደ ስፔን የዘለቀው ኢስላማዊ የመስኖ ሥራ ከተጨባጭ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ እንደነበር ለመገንዘብ ተችሏል።[13]

ፎርብስ እንዳስቀመጠው ሙስሊሞች በተለይም በምእራብ ሜዴትራኒያን አካባቢ የመስኖ ሥራን በማሻሻሉና በማሳደጉ ረገድ ትልቅ ባለውለታዎች ናቸው። ሙስሊም ገበሬዎች በስፔንና ሲሲሊ አካባቢዎች መስኖን በማስፋፋት ብቻ አልተወሰኑም። ከዚያም አልፈው ከወንዝ ውሃን በመጥለፍ የተለያዩ ቦዮችን በመቅደድና በመገደብ ውሃን በተገቢው መልኩ እንዴት ወደ መሬታቸው ማድረስ እንደሚቻል እውቀት ነበራቸው።[14] ከዚህም ባለፈ የዝናብ ውሃን በኮረብታዎች አካባቢ በመገደብና በማቆር ወይንም ተራሮች ላይ የሚዘንበውን ውሃ በቀጥታ ወደ ቦዮችና ሸለቆዎች እንዲፈስ በማድረግ ያጠራቅሙ ነበር። የምድር ላይ ውሃን የሚያገኙት ከምንጮች፣ ከጅረቶችና እና ወንዞች ሲሆን ከከርሰ-ምድር ውስጥ ያለን ውሃ አዳዲስ ምንጮችን በመፍጠርና ጉድጓዶችን በመቆፈር ያወጡ ነበር።[15]

የውሃ አጠቃቀም

በእስልምና የውሃ ዋጋ እጅግ ውድ ነው። ከአጠቃቀሙ አንፃር ጥብቅ መመሪያ የተላለፈበት ሲሆን በእስልምና ውሃን በምንም መልኩ ማባከን የተከለከለ ነው። የውሃ ብክነት በኢኮኖሚም ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ሊያሣድር ይችላል። የውሃ ሀብትን በአግባቡና በተሟላ መልኩ ለመጠቀም በአልጄሪያ ሰሃራ የተለያዩ የውሃ አጠቃቀም ስልቶች ሥራ ላይ ውለው ነበር። የውሃ ብክነትን ለመከላከል ፎጋራስ የሚባል ስልት ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን ስልቱንም በመሬት ሥር የሚገኙ ተያያዥ የሆኑ የውሃ ቋቶችን በመጠቀም ውሃን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላኛው ቦታ ረጅም ርቀት ለመውሰድ ይጠቀሙበታል። የዚህ ዓይነቱ አሠራር ዛሬም ድረስ ጥቅም ላይ ያለ ሲሆን ውሃን ከመጠን በላይ መጠቀምንና ብክነትን ይቀንሣል። ዛሬም ድረስ በአልጄሪያ በበኒ ዐባስ ክልል ከኦራን በስተደቡብ በሚገኘው የሰሃራ በረሃ ክልል ውስጥ ገበሬዎች እያንዳንዱ የአካባቢው ሰው ውሃውን ለምን ያህል ጊዜ ሊጠቀምበት እንደሚችል የሚለካ ክሌፕሲድራ የሚባል መሣሪያ ይጠቀማሉ።[16] ክሊፕሴድራ የወቅቶችን መለያየት ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀንና በማታ አንድ ገበሬ ሊጠቀም የሚችለውን ውሃ በደቂቃ በመለካት አመቱን ሙሉ ምን ያህል ሊጠቀም እንደሚችል በትክክል ያስቀምጣል። በዚህም እያንዳንዱ ገበሬ ተራው መቼ እንደሆነ ይነገረውና የሚሠጠውን የውሃ ኮታ በተገቢው መልኩ ለእርሻው ለማድረስ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ይዘጋጃል። በስፔንም ተመሣሣይ የሆነ ጥብቅ የውሃ አጠቃቀም ሥርዓት ይሰራበት ነበር። ከአንድ ቦይ ወደ ሌላኛው ቦይ የሚፈሰው ውሃ ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያገለግል የሚደረግ ሲሆን ምን ያህል መሆን እንዳለበትም ተመጥኖ ነው የሚለቀቀው። የማከፋፈያ ጉድጓዶች የተለያዩ የአፈር ዓይነቶችን ለመያዝ የሚችሉ ሲሆን ከነኚህ መካከል ሁለት መቶ ሀያ አራቶቹ የራሣቸው የሆነ ሥም አላቸው።[17]

በውሃዎቹ ላይ የሚነሱ ውዝግቦችና ክርክሮች የሚፈቱት በራሣቸው በገበሬዎቹ በተመረጡ ዳኞች ነው። ይህ ችሎት “የውሃ ጉዳዮች ችሎት” የሚል ስያሜ የተሠጠው ሲሆን ዘወትር ሀሙስም ከዋናው መስጊድ ፊት ለፊት ከሚገኝ በር ይሰየማል። ከ10 ምእተ አመታት በኋላ ተመሣሣይ የሆነ ልዩ ፍርድ ቤት በቫሌንሽያ የተሠየመ ሲሆን መቀመጫውም ከካቴድራሉ መግቢያ ላይ ነበር።[18]

የዘር ሥርጭት

ዋትሰን የእስልምናን የግብርና አብዮት ሲያብራራ “ይህ ሁሉ ለውጥ የታየው ከሦስት እና አራት ምእት አመት በላይ ተዋህዶ በቆየውና አዳዲስ ሁኔታዎችንም ለመቀበል ዝግጁ በሆነ ሰፊ ክልል ውስጥ ነው። ስለሆነም ቀደምት የነበሩትንም ሆነ አዳዲስ ልምዶችን ለማስተላለፍና ለማሠራጨት ሁኔታዎች የተመቻቹ ነበሩም። የሰዎች አመለካከት፣ ማህበራዊ መዋቅሮች፣ መሠረተ ልማቶች፣ ተቋማት፣ የሣይንስ እድገትና የኢኮኖሚ ሁኔታና ሌሎችም ተደማምረው አብዬቱ እንዲስፋፋ አስተዋፅኦ ነበራቸው። ግብርናው ብቻ ሣይሆን ሌሎች የኢኮኖሚም ሆነ ከኢኮኖሚው ክፍል ውጭ ያሉ የህይወት ዘርፎችም በከፍተኛ ሁኔታ ይህን ጉዳይ ለማስረፅና ለማስተላለፍ ተፅእኖ አሣድረው ነበር።

ፎርብስ እንዳብራራው ሙስሊሞች እያደጉ ሲሄዱ በምሥራቁ አካባቢ ቀደምት ስልቶችንና ማሽኖችን እንዲሁም በተለመደው የእርሻ ዘዴ ሊበቅሉ የማይችሉ አንዳንድ የእህል ዘሮችንም ጭምር አስተዋውቀዋል።

ሮማውያን ሩዝ ከሌላ ሀገር የሚያስገቡ የነበረ ሲሆን በሰፊው መሬታቸው ላይ አብቅለው አያውቁም ነበር። ሙስሊሞች ግን በሲሲሊና በስፔን በመስኖ በሚጠቀሟቸው መሬቶች ላይ ማብቀል የጀመሩ ሲሆን ከዚያም በመነሣት የሩዝ ምርት ወደ ፒዛን ገላጣ ሥፍራዎች በ1468 እና ወደ ሎምባርዲ 1475 ሊስፋፋ ችሏል።[19]

ዊከንስ እንደሚለው ሙስሊም ስፔኖች በበኩላቸው የፍራፍሬ አበቃቀል ሂደትን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት የግብርና ዘዴና አዳዲስ ተክሎችን፣ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች በማስተላለፋቸው ከፍተኛ የባለውለታነት እውቅና ተሠጥቷቸዋል።[20] ከአዳዲሦቹ የእህል ዘሮች መካከል ሸንኮራ አገዳ፣ ሩዝ፣ ትርንጎ፣ አፕሪኮት፣ ጥጥ፣ አርቲሆክ፣ አውበርጂን፣ ሳፍሮን እና ሌሎችም ከዚህ ቀደም ይታወቁ የነበሩና እንዲሻሻሉ የተደረጉ ይገኙበታል።[21]

ሙስሊሞች ከዚህም በተጨማሪ ለሀገራቱ ሩዝን፣ ብርቱካንን፣ ሸንኮራ አገዳና ጥጥን ያስተዋወቁ ሲሆን የከፊል ሞቃታማ አካባቢ ምርቶችን ማለትም ሙዝና የሸንኮራ አገዳ በሀገሪቱ የባህር ዳርቻዎች አካባቢ ተክለዋል። አብዛኞቹም ኋላ ላይ በአሜሪካ ወደሚገኙ የስፔን የቅኝ ግዛት አካባቢዎች ተወስደዋል።

የሙስሊሙ ባለውለታነት ከዚህም ያለፈ ነበር። በአዳዲስ ምርቶች ተፅእኖ የተነሳ የሀር አንዱስትሪ ዳብሯል። የቃጫ ተክል ተመርቶ ላይነን ወደ ውጭ ለመላክ በቅቷል። በደረቅ መሬቶች አካባቢ በሰፊው የሚበቅለውን ስፓርቶ ሳርንም በመሰብሰብ ወደ ተለያዩ ቁሣቁሦች ለመለወጥ ተችሏል።[22]

በሲሲሊ ያኔ በሙስሊም ማህበረሰቦች የተዋወቁት የእህል ዘሮችና የእርሻ ስልቶች ዛሬም ድረስ የኢኮኖሚው መሠረቶች ናቸው።[23]የእህል ዘሮቹን በማስተዋወቁ ረገድ የአንዳንድ ግለሰቦች ሚና ቀላል አልነበረም። አብዱልረህማን 1ኛ የተምር ዛፍን ጨምሮ በርካታ የእህል ዘሮችን ከሶሪያ ምድር ውጭ በማስተዋወቁ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው።[24] የተለያዩ ዓይነት የሩማን ፍሬዎች ሊተዋወቁ የቻሉት በወቅቱ የኮርዶቫ ገዥ በነበረው ሙዓዊያ ቢን ሳሊህ ሲሆን ሳፈር የሚባል አንድ የጆርዳን ወታደር ደግሞ በለስን ቆርጦ በመውሰድና በማላጋ በሚገኘው ማሣው ላይ በመትከል ለአካባቢው አስተዋውቋል። ይህ ዝርያ ሳፈሪ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከዚያ በመነሣትም በዓለም ዙሪያ በሰፊው ተሠራጭቷል። የሸንኮራ አገዳን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያስተዋወቁት ሙስሊሞች ሲሆኑ የምስራቅ አፍሪካን ደሴት ዛንዚባርን ጥራት ላለው የስኳር ምርት እውቅና ያበቋትም እነርሱ ናቸው።[25]

የእርሻ አሠራር ማንዋሎች

የሙስሊሞች የእርሻ አሠራር ዘዴ መድበሎች (manuals) በጊዜው ከነበረው ሁሉ የላቁ ነበር።[26] ከአፈሩ ባህሪና ዓይነት በመነሣት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንዲሁም የአፈርን ለምነት ለመጠበቅ ተግባር ላይ የዋሉት ዘዴዎች ከአፈሩ ሁኔታና አስፈላጊነት በመነሳት በዝርዝር የቀረቡ ነበሩ። አፈርንም ሆነ ውሃ እንደየጥራት ደረጃቸው ከፋፍለው ነበር። የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም አፈርን እንዴት ማበልፀግ እንደሚቻል ተብራርቷል። የአስተራረስ ስልቶች፣ የመኮትኮትና በጥልቀት የመቆፈር አስፈላጊነትም እንዲሁ ተገልጧል።

ኢብኑ ባሣል በድርሰቱ አፈርን በአሥር ቦታዎች ከፋፍሎ ያስቀመጠ ሲሆን እያንዳንዱም ከተስማሚ አየርና ወቅት አንፃር መድቦ ነበር። ኢብኑ ባሳል እዳሪ መሬቶች ከጥር እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ ውስጥ አራቴ መታረስ አለባቸው የሚል አቋም ነበረው። እስከ ዐስር ጊዜ ድረስ ማረስንም ይጠቁም ነበር።[27]

በአልጄሪያ እና በስፔን ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው የኢብኑ አል-ዐዋም ድርሰት 18ኛው እና በ19ኛ መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ላይ ወደ ስፓኒሽ እና ፈረንሣይኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ሊታተም ችሏል።

ይህ ኪታብ አል-ፍላሃት (የእርሻ መፅሃፍ) 34 ምዕራፎች የነበሩት ሲሆን በእርሻና እንሣሳት እርባታ ዙሪያ ያጠነጥናል። በውስጡም 585 ዕፅዋቶች የተካተቱ ሲሆን ከ50 በላይ የሚሆኑ ፍራፍሬዎችንም በመጥቀስ እንዴት እንደሚመረቱ ያብራራል። ከዚህም በተጨማሪ ስለ ተክሎች አደቃቀል፣ ስለ አፈር ባህሪ፣ ስለ ማዳበሪያ እንዲሁም ስለ ተክሎች በሽታዎችና መድሃኒቶችም ተካተውበታል።

ኢብኑ አል-ዐዋም ስለ አትክልት ቦታዎች፣ ስለ መስኖ፣ ስለ ተክሎች ማዳቀል፣ ስለ እንሰሳት እርባታ እና ንብ ማነብም በጥናቱ ውስጥ አካቷል።

የአል ኢሽቢሊ ኪታብ አል-ፍላሃ (የእርሻ መፅሃፍ) ደግሞ በዚሁ ዙሪያ ያጠነጠነ ሲሆን ለገበሬዎችም ስለያንዳንዱ ሁኔታ በትኩረት ያስረዳል። በውስጡም ስለ ወይራ ዛፍ አመራረትና አሰባሰብ፣ ስለ በሽታዎች ህክምና፣ ስለ ድቀላ፣ ስለ ወይራ ፍሬ ባህሪና ከሱም ዘይት እንዴት እንደሚወጣና አጠቃላይ ሁኔታዎቹ ተካተውበታል።[28]

በ961ዱ የኮርዶባ ካሌንደር /የጊዜ አቆጣጠር/ ውስጥ ግዙፍና ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች የተካተቱ ሲሆን ትክክለኛነቱም እጅግ አስገራሚ የሚባል ነው። በያንዳንዱ አመት ውስጥ የሚገኝ ወር የራሱ የሆነ ሥራና የጊዜ ሠሌዳ አለው። ለምሳሌ መጋቢት በለስ የሚዳቀልበትና ጥራጥሬዎችም መብቀል የሚጀምሩበት ወር ነው። ከዚህም በተጨማሪ የሸንኮራ አገዳ የሚተከልበትና የፅጌረዳ አበቦችና ሊላክስ አበባ የሚፈነዳበት ወር ነው። ኩውልስ የሚባል የወፍ ዘርም በዚሁ ወር ውስጥ ይታያል። የሀር ትል ይፈለፈላል….ሌላም ሌላም። ከዚህም ሌላ ለአብዛኞቹ ወፎች የመራቢያ ጊዜ ነው።[29]

የሥነ ምህዳር መራቆት

ቦለንስ እንደምትለው ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለተፈጥሮ ካለው ጥልቅ ፍቅርና ሕይወትን ቀለል አድርጎ ለመኖር ካለው ፍላጎት በመነሣት፡- ፅንሠ ሀሣብን ብቻ ሣይሆን ከበርካታ ስልጣኔዎች የተገኘውን እውቀት መሠረት ባደረገ መልኩ በተሣካ ሁኔታ የአማካይ ኢኮኖሚ እድገት መሠረት የሆነውን የሥነ-ምህዳር ሚዛን (ecological balance) ለመጠበቅ ችሏል።[30]

በማከልም የቅኝ አገዛዝ (colonialism) ሥርዓቱ የቅኝ ገዢዎቹን ትርፍ ለመጨመር ሲባል ልማዳዊውን የእርሻ አሠራር በተከታታይና በእጅጉ እንዲጎዳ ዐቢይ ምክኒያት እንደነበር አብራርታለች።[31] እንደ ሌሎች ኢስላማዊ የስልጣኔ ዘርፎች መውደም ሁሉ የእርሻው እንቅስቃሴ መዳከም የጀመረው ከበኑ ሂላል እስከ ኖማንስ እና የምዕራቧ ስፔን ድረስ የዘለቀውን የመስቀል ተዋጊዎችንና ሞንጎሎችን ወረራ ተከትሎ ነው። በዚህ ወረራ ሰፋፊ ትላልቅ መስኖ ፕሮጀክቶች ፈራርሰዋል። ለዋና ዋና የእህል ዘሮች መጥፋትም ምክኒያት ሲሆን የንግድ መስመሮችም ተቋርጠዋል። በርካታ ገበሬዎችም ለስደት ተዳርገዋል።[32]

ሙስሊም ገበሬዎች በአዲሶቹ የስፔንና ሲሲሊ ክርስቲያን ገዝዎቻቸው ከፍተኛ ግብር ተጥሎባቸው በገዛ ሀገራቸው የተገለሉ ሲሆን የግብርና አሠራራቸውም ከነርሱ ጋር ተንኮታኩቷል።[33] ኋላ ላይ የመጡት ቅኝ ገዝዎቹ ፈረንሣዮች ደግሞ የተቀረውን ጨርሰውታል።

ፈረንሣዮች በ1830 በቅኝ ግዛትነት የተቆጣጠሯት አልጄሪያ በአረንጓዴነቷ ከሌሎች አካባቢዎች እጅግ የተሻለች ነበረች። ህዝቦቿም በየአካባቢቸው በሰላምና በፍቅር ይኖሩ ነበር። ነገር ግን ፈረንሳዮች የአልጄሪያውያንን የመቋቋም አቅም ለመስበር ባደረጉት አስከፊ ጦርነት በከተሞች አካባቢ ይገኙ የነበሩ በርካታ ለም የሆኑ መሬቶችን፣ የእርሻ ማሳዎችን፣ ዛፎችንና የፍራፍሬ ማሳዎችን አወድመዋል። ቀጥሎም የደን እንጨቶችን ለመጠቀም ሲባል የሀገሪቱን ደኖች በዘግናኝ ሁኔታ ጨፍጭፈዋል። ለም የሆኑ መሬቶችንም ከሙስሊሞች እጅ በመቀማት ወደ ደረቃማ መሬቶች ገፍተዋቸዋል። በደን ተሸፍነው የነበሩ መሬቶችንም ሙሉ በሙሉ አራቁተዋል።

ከ1952-1962 በተደረገው የነፃነት ጦርነት ፈረንሣውያኑ ጥቅጥቅ ባሉ ደናማ መሬቶች ላይ እሳት በመለኮስ የተራቆተ መሬትና ጥላቻን በማውረስ ከአካባቢው የለቀቁ ሲሆን ይህ የአልጄሪያ አካባቢ አገግሞ ዛሬም ድረስ ቀድሞ ወደነበረበት አረንጓዴነት መመለስ አልቻለም።[34][1]-A.M Watson: Agricultural Innovation in the Early Islamic World, Cambridge University Press, 1983.

-A.M Watson: ‘The Arab agricultural revolution and its diffusion,’ in The Journal of Economic History 34፣ (1974).

-T.Glick: Islamic and Christian Spain in the early Middle Ages, Princeton University Press, New Jerzey, 1979.

-T.Glick: Irrigation and hydraulic technology: Medieval Spain and its legacy, Varorium, Aldershot, 1996.

-L.Bolens: Les methodes culturales au moyen age d’apres les traites d’agronomie andalous: traditions et techniques. Geneva, 1974.

-L. Bolens, Agronomes Andalous du Moyen Age, Geneva/Paris, 1981.

-L.Bolens: L’Eau et l’Irrigation d’apres les traites d’agronomie Andalus au Moyen Age (XI-XIIem siecles), Options Mediterraneenes, 16 (Dec, 1972).

[2] A. Cherbonneau: Kitab al-Filaha of Abu Khayr al-Ichbili, in Bulletin d.Etudes Arabes, pp 130-44; at p. 130.

[3] Frederick. B.Artz: The Mind of the Middle Ages; Third edition revised; The University of Chicago Press, 1980, p, 150.

[4] 4 T.Glick: islamic, op cit, p. 78.

[5] S.P. Scott: History of the Moorish Empire in Europe. 3 Vols, J.B. Lippincott Company, London, 1904; p. 598.

[6] L.Bolens: ‘Agriculture. in Encyclopedia of the history of Science, technology, and Medicine in Non Western Cultures, Editor: Helaine Selin; Kluwer Academic Publishers. Dordrecht /Boston/ London, 1997. pp 20-2, at p. 20.

[7] T. Glick: Islamic, op cit, p. 75.

[8] S.P. Scott: History, op cit, p.604.

[9] A.Watson: Agricultural innovation, op cit, pp 2-3.

[10] L. Bolens, Irrigation, op cit, p. 451.

[11] D.R. Hill: Islamic science and Engineering, Edimburgh University Press, 1993; p. 161.

[12] Al-Saqundi, Elogio del Islam espanol, p. 105; in T.Glick: Islamic, op cit, p.75.

[13] E. Levi Provencal: Histoire de l.Espagne Musulmane; 3 vols; Maisonneuve, Paris, 1953; vol iii, p. 279.

[14] R.J. Forbes: Studies in Ancient technology; vol II, second revised edition, Leiden, E.J Brill, 1965, p. 49.

[15] A.M. Watson: Agricultural innovation, op cit p. 107.

[16] L. Goonalons: La Clepsydre de Beni Abbes, in Bulletin d.Etudes Arabes, vol 3, 1943, pp 35-7:

[17] S.P. Scott: History, pp 602-3.

[18] Ibid, pp 602-3.

[19] R.J. Forbes: Studies, op cit, p. 49.

[20] G.M. Wickens: What the West borrowed from the Middle east, in Introduction to Islamic Civilisation, edited by R.M. Savory, Cambridge University Press, Cambridge, 1976, pp 120-5; at p. 125.

[21] M. Watt: The Influence of Islam on Medieval Europe, Edimburgh University Press, 1972; pp 22-23.

[22] W.Montgomery Watt: The influence, op cit, pp 22-3.

[23] Francesco Gabrieli: .Islam in the Mediterranean World., in The Legacy of Islam, edited by J.Schacht with C.E. Bosworth, 2nd edition. Oxford Clarendon Press, 1974. pp 63-104, at p. 75.

[24] T.Glick: Islamic, op cit, p. 76.

[25] A. Pacey: Technology in World Civilization, a thousand year history, The MIT Press, Cambridge, Massachusetts, 1990, p. 15.

[26] በተለይ፡-

-Ibn Al-Awwam: Le Livre de l’Agriculture d’In al-Awwam, tr. from Arabic by J.J. Clement-Mullet, Vol. I,

Paris 1864.

-Ibn Bassal: Libro de agricultura, Jose M.Millas Vallicrosa and Mohammed Azinan eds, Tetuan: instituto

Muley al-hasan, 1953.

[27] Millas Vallicrosa, ‘Sobre la obra de agricultura de Ibn Bassal,’ in Nuevos estudios sobre historia de la ciencia espanola (Barcelona: Consejo Superior de Investigaciones Cientificas, 1960), pp 139-40.

[28] In A Charbonneau: Kitab al-Filaha of Al-Ichbili, in Bulletin d.Etudes Arabes, vol 6 (1946); pp 130-144.

[29] E.L. Provencal: History, op cit, pp. 289-90.

[30] L.Bolens: Agriculture, in Encyclopaedia, op cit, p. 22.

[31] Ibid.

[32] የዋትሶንን የመጨረሻውን ምእራፍ ይመልከቱ: ‘Agriculture in retreat,’. in A. Watson: Agricultural.. Op cit.

[33] Charles H. Lea: A History of the Inquisition in Spain, in four volumes, The MacMillan Company, New York, 1907, volume three, pp 317-410.

[34] በይበልጥ እነዚህን ይመልከቱ፡-

-Charles.R. Ageron: Histoire de l.Algerie contemporaine, 3 vols, Presses Universitaires de France, 1979.

-Charles.A. Julien: Histoire de l.Algerie Contemporaine, Presses Universitaires de France, 1964.

-Henry Aleg et all: La Guerre d.Algerie, Temps Actuels, Paris, 1981.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here