ሙስሊሞች ለዓለም ስልጣኔ ምን አበረከቱ? (ክፍል 1)

0
7633

መቅድም

በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝና ሩህሩህ በሆነው

ይህች የትርጉም ሥራ ለውጤት እንድትበቃ ፈቃዱ ለሆነው አምላካችን አላህ (ሡ.ወ.) ወደር የለሽ ምስጋና ይገባው። በርሱ ይሁንታ ቢሆን እንጂ ይህች ሥራችን ከግብ ባልደረሰች ነበር።

ይህችን መጽሐፍ ለመተርጎም ያነሳሳን ዋናው ምክንያት ለብዙ ሙስሊሞች ባይተዋር የሆነው የሙስሊሞች ታሪክ ነው።

ሙስሊሙ ኢስላምን በሙሉ ተግባር ላይ ባዋለበት በዚያ ወርቃማ ዘመን በሁሉም አቅጣጫ ፈርጥ የሆነበት ጊዜ ነበር። በዲኑ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ ትምህርት ከፍተኛ ደረጃ በመድረስ አሁን ዓለም ለደረሰበት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ነገር ግን ይህ ግዙፍ ታሪክ አሁን ባለንበት ዘመን ተደብቆ አብዛኛው የአለም ህዝብ ለዚህ ጉዳይ እንግዳ ሆኗል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ይበልጥ ባእድ ነው።

ይህን ሙስሊሞች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚመለከት ታሪክ ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ለማሳወቅ ይህች ሥራ አንድ ብላ መንገዱን ትጠርግ እንደሆን እንጂ ሁሉንም በዚህች አጭር ፅሁፍ ማካተት የማይታሰብ ነው።

በዚህች መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው “ባህርን በጭልፋ” እንዲሉ ሰፊ ከሆነው የሙስሊም ምሁራን ታሪክ እና አስተዋፅኦ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ቢሆንም ግን አንድ ብሎ በመጀመር መንገዱን ማሳየት እንደሚችል በዚህች መጽሐፍ መነሻነት ለማሳየት ሞክረናል።

ይህች ሥራችን ስህተት የሌለባትና ከእንከን የፀዳች ናት ብለን አናምንም፤ ምክንያቱም በአንድ በኩል የመጀመሪያ ሥራችን እንደመሆኗ አንዳንድ እንከኖች ሊኖሩባት ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰው እንደመሆናችን መጠን፣ ሰው በተፈጥሮው ተሳሳች ነውና፣ ግድፈት አያጣውም።

***ተርጓሚዎቹ***

1. መግቢያ

ታዋቂው የታሪክ ምሁር ሮብ ብሪፎልት (Rob Briffault) “The Making of Humanity” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ሲል ይገልጻል፡-

“ዘመናዊው የአውሮፓ ስልጣኔ አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰው በአረቦች ቢሆን እንጂ ሊታሰብ እንኳን የሚቻል አልነበረም… የእስልምና ባህል ተፅዕኖ ያላረፈበት አንድም የአውሮፓ እድገት የለም።… የሳይንስ በአውሮፓ የመከሰቱ ምክንያት- አዲስ የመንፈስ ጥንካሬ፣ የጥናትና ምርምር ዘዴ ቅየሳ፣ በተግባር የታገዘ ጥናት (experimentation)፣ በተግባር የመሞከር እና ሂሳብን አቆራኝተው በመጠቀማቸው ነው። ነገር ግን ይህ ዘመናዊ የጥናት ስልት በግሪኮች ዘንድ አይታወቅም ነበር። ያ መንፈስ እና ከላይ የጠቀስናቸው የዘመናዊ ሳይንስ መገለጫዎች ወደ አውሮፓው ዓለም የተዋወቁት እና የገቡት በአረቦች ነው። (ማለትም በሙስሊሞች)” Briffault, Rob, The Making of Humanity, quoted in K.A. Waheed, Islam and The Origins of Modern Science, Islamic Publication Ltd., Lahore, Pakistan, 1978, pp.25-26.

እንደሌሎችም ብዙ ጸሐፍት ሁሉ ብሪፎልት ሙስሊሞች ለዓለም ስልጣኔ ያበረከቱትን እጅግ በርካታ አስተዋፅኦዎች እንዲሁም ለአወሮፓ ዳግም ማንሰራራት ላይ ያሳደሩት ተፅዕኖ በሚገባ ተረድቶታል። ብሪፎልት ከሌሎች ጸሐፍት በተለየ መልኩ ይህ ታላቅ አስተዋፅኦ በ “አዲስ መንፈስ” (new sprit) የተነሳሳና የተመራ ነው ብሎ ያምናል። ነገር ግን ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እምብዛም አስተዋፅኦ አድርገው በማያውቁት አረቦች በ 17ኛው ክፍለ ዘመን በቅጽበት ለተሰፋፋው ለዚህ “አዲስ መንፈስ” መገኛ እና ምንጭ በቂ የሆነ ስፍራ አልተሰጠውም። በተጨማሪም ያቺ አሸዋማዋ እና ደረቃማዋ የአረቢያ ምድር ለእውቀት መቅሰሚያ እና ለምርምር ማዕከል ሆናም አታውቅም።

ከእዚያ ከነበሩበት ጨለማ ተላቀው ለእድገት እና መሻሻል ቀዳሚ ያደረጋቸው እንዲሁም በተለያዩ ዘርፈ ብዙ የጥናት መስኮች እንደነቢያት ማስተማር ቻሉ። ታዲያ ይህን አስገራሚ ለውጥ ምን ሊገልጸው ይችላል? በ17ኛው ክፍለ ዘመን ይህን ቅፅበታዊ ለውጥ ሊያንቀሳቅሰው የሚችል ነገር ምን ተከሰተ?

የእስልምና ሃይማኖትና የሃይማኖቱ መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብ የሆነው ‘ተውሂድ’ መመንጨቱ ያመጣው ለውጥ ነው ከሚለው ውጪ ሌላ ተቀባይነት ያለው መረጃና ገለጻ ሊኖር አይችልም። የተውሂድ መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብ ሁሉም ፀጋ ከፈጣሪ መሆኑን ይገልጻል። በሚቀጥለው ክፍል ፈጣሪ የሁሉም ጸጋዎች ምንጭ መሆኑን እንመለከታለን።

2. አምላክ – የሁልም ጸጋዎች ምንጭ

እኛ ሰዎች ወደዚህኛው ዓለም ለመምጣት ምንም የከፈልነው ነገር ሰይኖር ተወለድን፤ ከዚያም ምንም ጥሪት ያስቀረነው ሳይኖር ምድራዊውን ሕይወት እንለቃለን። ከተወለድን አንስቶ በአካል እስክንሞት ድረስ በጌታችን ጸጋ ላይ ፍጹም ጥገኛ ነን። አላህ በስነ-ፍጥረት ውሰጥ ያለውን በሙሉ ብቸኛ ፈጣሪ፣ ተንከባካቢ እና በህይወት የሚያቆይ ነው። ስለዚህም ኢስላም ስለ አምላክ ያለው አስተምህሮ ምን ይመስላል ከሚለው ገለፃ መጀመር ጠቃሚ ይሆናል። ይህ አስተምህሮ ተውሂድ በሚለው ቁልፍ ቃል ሊጠቃለል ይችላል። ተውሂድ የኢስላም የመሠረት ድንጋይ፣ ለህይወት መመሪያና ደንቦች መፍለቂያ ምንጭ እንዲሁም ለመዋቅሩ እና ለአደረጃጀቱ መተዳደሪያ ሕግ ሆኖ ያገለግላል።

የተውሂድ ትርጉም

ተውሂድ ቃሉ አረብኛ ሲሆን ብዙውን ጊዜ “ሞኖቲዝም’” (Monotheism) በሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ይተረጎማል። በጥቅሉ በአንድ አምላክ ብቻ ማመን የሚል ትርጉም ሲኖረው ይህም ከአንድ በላይ አምላክ (Dualism, polytheism) እንዲሁም ጭራሹንም አምላክ የለም (Atheism) የሚሉትን ሃይማኖቶች በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ ነው። በተጨማሪም በአንድ አምላክ ማመን የሚለው ትርጓሜ የተውሂድን ቃል ሙሉ በሙሉ አይተካም። ተውሂድ ጥሬ ትርጉሙ አንድ እና አንድ (oneness)፣ አምሳል የሌለው (uniqueness) እና አላህ ከማንኛውም የሱ ፍጥረት ጋር የማይነጻጸር የሚሉ ናቸው። የእስልምና ሃይማኖት ልሂቃን ቁርዓንን መሠረት በማድረግ ለ “ተውሂድ” ሶስት መሠረታዊ ነጥቦች ያስቀምጣሉ።

  1. በአንድ እና በእውነተኛው አምላክ አላህ የዚህ ስነ-ፍጥረት ብቸኛው ፈጣሪ፣ ተንከባካቢ እና አስተናባሪ መሆኑን ማመን
  2. አላህ በብቸኝነት ተነጥሎ ሊመለክ የሚገባው እንዲሁም የስልጣን ተጋሪ የሌለው መሆኑን ማመን
  3. በአላህ አንድነት እና በባህሪያቱ እንዲሁም እነዚህ ባህሪያቱ የሱ ፍጹማዊነት መገለጫዎች መሆናችውን ማመን

አንድምታው

ይህ ጥቅላዊ የአላህ አንድነት ትርጓሜ ሌሎች የአንድነት ዓይነቶች እንዳሉ ያመላክታል።

  1. ለሰው ልጆች በተለያየ መልኩ የተገለጹ መለኮታዊ አስተምህሮቶች መሠረታዊ አንድነት፡- ቁርኣን በተከታዮቹ ላይ በሁሉም ነብያትና መልእክተኞች እንዲያምኑ፣ ሁሉንም እንደ አንድ ወንድማማቾች እንዲወዳቸው፤ እንዲያከብራቸው፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውሰጥ በሙሉ ያላቸውን የአስተምህሮ ሰንሰለት፤ ሰንሰለቱም በመጨረሻው ነብይ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መቋጫውን እንዳገኘ፤ መልዕክተኛውም መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ቁርኣን እንደገለጸው የመጨረሻው የመደምደሚያው ነብይ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን መልዕክተኛነታቸውና ተልዕኮአቸው መላውን ዓለም ያካለለ፤ እንዲሁም ከሳቸው በፊት የነበሩትን በማጠቃለልና በመቋጨት ብቸኛው መልክተኛ እንደሆኑ እንዲያምኑ ግዴታ ይደርጋል። (እንደ ምሳሌ ቁርኣን  21:107, 9:34, 48:28, 61:9, 34:28. ይመልከቱ)
  2. የሰው ልጅ የዘር አንድነት፡- የሰው ልጅ መጀመሪያ በአላህ ተፈጥሮ ከዚያም አንድ ዓይነት ከሆኑ ወላጆች መምጣት። ይህም የሰው ልጅ ልክ እንደአንድ ትልቅ ቤተሰብ በልዩነት ውስጥ አንድነትን የሚያንፀባርቅ መሆኑን ያሳያል። ከዚህ የምንረዳው አንድ ሰው ለሌሎች ያለው አመለካከት ሙስሊም ላልሆኑትም ጭምር በዚህ መልኩ ሊቀርጸው ይገባል።
  3. ሁሉም በአላህ ፈቃድ ስለመጡ፡- በምድር ላይ ያሉ የሰው ፍጥረት ክንውኖች አንድነት። ስለዚህም ሕይወትን ሃይማኖትና ዓለማዊ (religious and secular) ወይም መንፈሳዊና የዚህ ዓለም (spiritual and mundane) ብሎ ለመከፋፈል መሞከር ከተውሂድ ጋር መጣረስ ይሆናል።
  4. በአሁኗ ሕይወትና ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት መካከል ያለው አንድነት፡- ሁለቱም በአንድ መለኮታዊ ስልጣን ይፈጸማሉ። ስለዚህም በተናጥልም ሆነ በኅብረት የሚፈጸሙ ውሳኔዎች በጊዜ ቀመር የተመሩ ናቸው። ያ ማለት በአንድ ሰው የሕይወት ዘመን፣በአንድ ወይም በብዙ ትውልድ ወይም በሁሉም ትውልዶች የሕይወት ዘመን የተገደበ አይደለም። ማንኛውም የምንፈፅመው ተግባር በዚህችኛዋ ምድራዊ ህይወት እንዲሁም በመጪው ዓለም የራሱ የሆነ ውጤት ያስከትላል።

ይህ ፅሁፍ የተወሰደው ከዶ/ር ጀማል በደዊ  መፅሐፍ “muslim cotributions to world civilizations” ትርጉም በአወሊያ 98 ጀማዐህ ፣ ነጃሺ አሳታሚ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here