ወደ አምላኩና የሱ ፍጥረት ወደሆኑትም ይበልጥ ይቃረብ ዘንድ አማኝ እውቀትን እንዲያካብት ቁርዓን በተደጋጋሚ ያነሣሣዋል። የተለያዩ የቁርዓን አንቀፆችም ይህንኑ ያዛሉ። ለምሣሌም ያህል
“እነዚያ የሚያውቁና እነዚያ የማያውቁ ይስተካከላሉን? የሚገነዘቡት ባለ አእምሮዎቹ ብቻ ናቸው።” (አዝ-ዙመር 39፤ 9)
“ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከእርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው። በዚህ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ተዓምራት አልለበት።” (አል-ጃሲያ 45፤ 13)
ላይ የተጠቀሱትን አንቀፆች መመልከት ይቻላል።
ቁርዓን አንዳንድ ወሣኝ የሆኑ ነገሮችን በድግግሞሽ የሚያወሣው አንባቢዎች ለዚያ ነገር ከፍተኛ የሆነ ትኩረት እንዲሠጡ ነው። በተከበረው ቁርዓን ውስጥ “አላህ” የሚለው ቃል 2800 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል። “ረብ” (ጌታ/ተንከባካቢ) የሚለው ደግሞ 950 ጊዜ የተጠቀሠ ሲሆን “ዒልም” (ዕውቀት) የሚለው ቃል ደግሞ በተከበረው ቁርዓን ውስጥ 750 ጊዜ ያህል በድግግሞሽ በመጠቀስ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሙስሊሞች ሁሉ የትም ይሁኑ የት በየትኛውም ሁኔታ ላይ ሆነው እውቀትን ይፈልጉ ዘንድ አዘዋል።
ከቁርዓን አንቀፆች አስተምህሮና ከነቢያዊ ሀዲሶች በመነሣትም ቀደምት ሙስሊም መሪዎች እያንዳንዱ ሙስሊም ታዳጊ ተጠቃሚ ይሆንበት ዘንድ ለትምህርትና ለተቋማቱ ከፍተኛ ትኩረትና እገዛ በመስጠት ተንቀሣቅሰዋል። በመሆኑም በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በአጠቃላይ ሁኔታ ለማለት በሚያስችል መልኩ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ በእጅጉ ተስፋፍቶ ነበር። ዊልድስ እንዲህ ይላል፡-
It was this great liberality which they displayed in educating their people in the schools which was one of the most potent factors in the brilliant and rapid growth of their civilisation. Education was so universally diffused that it was said to be difficult to find a Muslim who could not read or write.
“ይህ እነሱ ማህበረሰባቸውን በትምህርት ቤት ለማስተማር ያስቀመጡት ሰፊ አስተሣሰብ ነበር ምርጥ እና ፈጣን የሆነ ሥልጣኔያቸውን ለማስመዝገብ አቢይ ምክኒያት የሆነላቸው። በርግጥም በጊዜው ማንበብና መፃፍ የማይችል ሙስሊም ለማግኘት በሚቸግርበት መልኩ ትምህርት በከፍተኛ ሁኔታ ተሠራጭቶ ነበር።” (E.H. Wilds: The Foundation of modern Education, Rinehart & Co., 1959,p. 216)
ቀደምት ሙስሊም ሀገር በነበረችው ስፔን ሌላው ቀርቶ እጅግ ደሃ በሚባሉ ሰዎች መንደር ጨምሮ “የዕውቀት በረከት” ያልደረሰበት ሥፍራ አልነበረም። በኮርዶቫ ብቻ በአብዛኛው ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶችና ሌሎች ማህበረሰቦች የሚጠቀሙባቸው ከ800 በላይ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ነበሩ።[1] በታላቁ የኮርዶቫ ሙስሊም ዩኒቨርስቲም እስከ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በሚያደርስ ደረጃ አይሁዶችና ክርስቲያኖች ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር።[2] እነኚህ የመምህራንና የተማሪዎች ማፍሪያ የሆኑ ትላልቅ ተቋማት በሰፊው ህዝብ ዘንድ ታላቅ ከበሬታ ይሠጣቸው ነበር። ባለፀጋ በሆኑ የመሬት ባላባቶችና ነጋዴዎች የተደራጁ ቤተ-መፃህፍትም የሚያመለክቱት ይህንኑ ሲሆን ከ600 አመታት በኋላ በተከሠተው የጣሊያን አብዮት ላይ እንደተጠቀሠው እውቀት በርግጥም የተከበሩ ሰዎች ከፍተኛ መገለጫ መሆኑን ነው።[3] ፔደርሰን እንዲህ ይላል
In scarcely any other culture has the literary life played such a role as in Islam. Learning (ilm), by which is meant the whole world of the intellect, engaged the interest of Muslims more than anything. The life that evolved in the mosques spread outward to put its mark upon influential circles everywhere.
“እውቀትን ያማከለ ህይወት በእስልምና ውስጥ የነበረው ቦታና ሚና ከማንኛውም ማህበረሰብ አንፃር ሲታይ በጣም የላቀ ነበር። ሁሉንም የእውቀት መስክ ያጠቃልል የነበረው ትምህርት (ኢልም) ከማንኛውም ነገር በላይ የሙስሊሞችን ፍላጎት የማረከ ነበር .. መስጂድን መነሻ ያደረገው ህይወት ወደ ውጭ በመውጣትም በሁሉም ቦታዎች ላይ ዙሪያ መለስ በሆነ መልኩ የራሱን አሻራ ለማሣረፍ ችሏል።” (J.Pedersen: The Arabic Book, Tr. Geoffrey French, Princeton University Press; Princeton, New Jersey, 1984, P. 37.)
ሁሉም ህዝባዊ ተቋማት፤ ከመስጂዶች እስከ መድረሣዎች፣ ሆስፒታሎችና የምርምር ቦታዎች ሁሉ የመማሪያ ማዕከላት ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ ሙስሊም ምሁራኖቹ ሰዎች እውቀት ፍለጋ ቤታቸው ድረስ መጥተው በሚሰበሰቡበት ወቅትም መልእክት ያስተላልፉላቸው ነበር። ከነኚህም መካከል አል-ጋዛሊ፣ አል-ፋራቢ እና ኢብኑ ሲና ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። አብዛኞቹ ሙስሊም ምሁራን በህዝብ ትምህርት ቤቶች ሲያስተምሩ ከቆዩና በግል ቤተ-መፃህፍቶቻቸውም በጥናት ከደከሙ በኋላም ቢሆን ማረፍ አይፈልጉም ነበር። ባይሆን መጋበዝ የሚገባቸውን ሰዎች በመጋበዝ ትምህርታቸውን በማስተማሩ ሂደት ይቀጥላሉ።[4]
ዛሬ ግን ይህ ሁሉንአቀፍ የሆነ አካሄድ፣ የእውቀት ጥማትና ጉጉት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ አይታይም። በርግጥም ከላይ ያወሣነው ጊዜ እስልምና እንደ ሃይማኖትም ሆነ እንደ ሥልጣኔ ጫፍ ላይ የደረሠበት የወርቃማው ዘመን ልዩ መለያ ነበር። በዚያን ዘመን የነበረው ለእውቀት የሚሠጠው ደረጃና ሚና ከትላልቅ ሥራዎች መካከል ይመደባል። የመድረሣዎች ሚናም ትልቅ ግምት የሚሠጠው ነው። በዚህ ጽሁፍ የትምህርት ተቋማት ዓላማ፣ እውቀትን እንዴት ማግኘትና ማስፋት እንደቻሉና ከሁሉም በላይ ደግሞ መስጂዶች የነበራቸውን ሚና እንመለከታለን።
በሙስሊሙ ዓለም እውቀትን በማስፋፋት ረገድ መስጂዶች ከፍተኛ የሆነ ድርሻ ነበራቸው። መስጂዶችና ትምህርት የነበራቸው ቁርኝትም በታሪክ ከዋናዎቹ መለያ ባህሪያቱ መካከል በመሆን ለዘመናት ኖሯል።[5] ትምህርት ቤቶችም ከመስጂዶች ተነጥለው የማይታዩ ቅርንጫፎች ነበሩ።[6] ከኢስላም መባቻ ጀምሮ መስጂዶች የሙስሊሙ ማህበረሰብ የፀሎት ማድረጊያ ሥፍራዎች፣ የእርቅ ቦታዎች፣ የሃይማኖት መመሪያ ማስተላለፊያ መድረኮች፣ ፖለቲካዊ ውይይት የሚደረግባቸው አዳራሾችና የትምህርት ማስፋፊያ ቦታዎች በአጠቃላይ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሁለገብ እንቅስቃሴ ማዕከላት ነበሩ። ኢስላም በአዲስ በደረሰበት ሥፍራ ሁሉ በቅድሚያ ይሠራ የነበረው መስጂድ ሲሆን በውስጡም መሠረታዊ የሆኑ ሃይማኖታዊና የእውቀት መመሪያዎች ይሠጣሉ። አንዴ ከተመሠረቱ በኋላ መስጂዶች እጅግ ወደተደራጀና በርካታና መቶና ሺህ ተማሪዎችን ባቀፈ መልኩ ትልቅ የትምህርት ማዕከል ወደመሆን ይሸጋገራሉ። በውስጣቸውም አስፈላጊና ወሣኝ የሆኑ ቤተመፃህፍን የያዙ ሆነው ይጠናከራሉ።[7]
ከመስጂድ ጋር ተያይዞ የተመሠረተው የመጀመሪያው ትምህርት ቤት እ.ኤ.አ. በ653 በመዲና ሲሆን በ900 አካባቢ እያንዳንዱ መስጂድ ለወንዶች እና ለሴቶች ማስተማሪያ የሚያገለግሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነበሯቸው።[8]
ህፃናት አብዛኛውን ጊዜ በአምስት አመት እድሜአቸው ትምህርት የሚጀምሩ ሲሆን መጀመሪያ አካባቢ ከሚሰጧቸው ትምህርቶችም መካከል መልካም የሆኑ ዘጠና ዘጠኙን የአላህን ሥሞች እና የተወሰኑ የቁርዓን ምእራፎችን እንዴት መፃፍ እንደሚችሉ ነበር።[9]ማንበብና መፃፍ በሚገባ ከቻሉ በኋላ ቁርዓንን በደንብ ማጥናት ይጀምራሉ። ቀጥሎም ሂሣብን ይማራሉ። በትምህርታቸው መቀጠል የሚፈልጉት ከፍ ያሉ ትምህርቶች ወደሚሠጡባቸው ትላልቅ መስጂዶች የሚሸጋገሩ ሲሆን እዚያም የዐረብኛ ስዋስዎ፣ ግጥም፣ ሎጂክ፣ አልጄብራ፣ ሥነህይወት፣ ታሪክ፣ ህግ እና የሃይማኖት ትምህርትንና የመሣሰሉትን ያጠናሉ።[10] ምንም እንኳ ከፍ ያሉ ትምህርቶች ይሠጡ የነበረው በመድረሣዎች፣ በምርምር ቦታዎች እና በምሁራን የግል መኖሪያ ቤቶች ቢሆንም በስፔን ግን አብዛኛው ትምህርት ይሠጥ የነበረው በመስጂዶች ነው። ይህም የተጀመረው ከ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኮርዶባ መስጂድ ነው።[11]
ትምህርት ይሠጥ የነበረው ክብ ክብ ሆነው በመስጂድ ውስጥ በሚደረግ የአቀማመጥ ሥርዓት “ሀለቃት አል-ዒልም” ወይም ባጭሩ “ሀለቃ” በሚባለው ነው። “ሀለቃ” ማለት ክብ ሠርተው ተሰባስበው የተቀመጡ ሰዎች አሊያም በአስተማሪያቸው ዙሪያ ክብ ሠርተው ከአስተማሪያቸው ትምህርት የሚወስዱ ተማሪዎች ማለት ነው።[12] ምሁራን የሆኑ ጎብኚ እንግዶች ክብራቸውን በሚገልፅ መልኩ ከዋናው አስተማሪ ጎን እንዲቀመጡ ይደረጋሉ። በበርካታ ሀለቃዎች ላይ አብዛኛውን ጊዜ ጎብኚዎቹ ምሁራን ትምህርት የሚሠጡበት የተያዘላቸው የተወሠነ ክፍለጊዜ ይኖራል።[13] ሀለቃውን የሚመሩት አስተማሪዎች ሲሆኑ ተማሪዎች ደግሞ አስተማሪዎቻቸውን በጥያቄ እንዲጋፈጡና እንዲያርሙ ይደረጋሉ። በዚህም ይበረታታሉ አንዳንዴም ሞቅ ያሉ ክርክሮች ይካሄዳሉ።[14] በያንዳንዱ የእውቀት መስክ ላይ የተደረጉ ውዝግቦችና አለመስማማቶች ዘወትር ጁሙዓ በመስጂዱ ዙሪያ ክብ ተሠርተው በሚደረጉ ስብስቦች ውይይት ይደረግባቸዋል።[15] ምንም አይነት ግደባም አልነበረም።[16]
በአንድ ወቅት የህግ ባለሙያ የሆነው አልባህሉሊ (በ930 የሞተ) በዒራቅ ውስጥ ከምትገኝ አንዲት ከተማ በመነሣት ከወንድሙ ጋር በመሆን እነኚህኑ ክብ የዕውቀት ማዕዶች ለማየት ወደ ባግዳድ ሄዶ ነበር። ሁለቱ ሰዎችም በመስጂዱ ውስጥ በየማዕዘናቱ በተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች የበለጸጉ አሊሞችን ለመመልከት ችለዋል።[17] ኢብኑ በጡጣ በኦማያድ መስጂድ ውስጥ በአንድ ሀለቃ ላይ ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ማየቱን ዘግቦ ነበር።[18] በካይሮ የሚገኘው የዓምር ኢብኑ አል-ዓስ መስጂድ በአንድ ጊዜ ከአርባ በላይ ሀለቃዎችን ያስተናግዳል።[19] በዋናውና ትልቁ የካይሮ መስጂድ ውስጥ ደግሞ መቶ ሀያ ሀለቃዎች ነበሩ።
ተጓዥ እና አሣሽ የሆነው አልሙቀደሲ እንደዘገበው በአንድ ወቅት በመግሪብና መኢሻአ ሰላቶች መካከል በዓምር ኢብኑ አል-ዓስ መስጂድ ውስጥ እርሱ እና ጓደኞቹ ተቀምጠው በማውጋት ላይ ሳሉ “ወደ ትምህርት ክፍለጊዜዉ ፊታችሁን መልሱ!” የሚል ከፍ ያለ ድምፅ ሰሙ። ኋላ ላይ ነበር አልሙቀዲሲ በሁለት ሀለቃዎች መካከል ተቀምጦ ያለ ስለመሆኑ የተገነዘበው። መስጂዱ የህግ፣ የቁርዓን፣ የሥነፅሁፍ፣ የፍልስፍና እና የሥነምግባር ትምህርቶችን በሚከታተሉ ተማሪዎች ተጨናንቆ ነበር።[20]
በአብዛኞቹ ትላልቅ መስጂዶች የማስተማር ሥርዓትና ጥናት የሚካሄደው የተሟላ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ሲሆን የመስጂድ ትምህርት ቤቱም ከትምህርት ተቋም አሊያም ኋላ ላይ ከመጣው ዩኒቨርስቲ ጋር የሚቀራረብ ነው። በዚህ መልኩ ነበር ወሣኝ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ማዕከላት እውን ሊሆኑ የቻሉት። እነኚህ ተቋማትም እውቅናቸው እየገነነ ሲሄድ በርካታ ተማሪዎችንና ምርጥና ትላልቅ ሥም ያላቸውን ምሁራንን ለመሣብ ችለዋል።
በዒራቅ ባስራ አል-ኸሊል ኢብኑ አህመድ በመስጂድ ውስጥ የፍልስፍና አስተማሪ ሲሆን ከተማሪዎቹም መካከል ኋላ ላይ ከምንጊዜውም የዐረቡ ዓለም የቋንቋ ስዋስዎ አዋቂዎች መካከል ቁንጮ የሆነው ሲባዋይህ ይገኝበታል። በጥንቷ ሙስሊም ስፔን በዋናነትም በግሪናዳ፣ በሲቪያ እና በኮርዶቫ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች መነሻቸው መስጅዶች ነበሩ። እነኚህ ዩኒቨርስቲዎችም በዓለም ላይ ከፍተኛ ክብር የሚሠጣቸው ናቸው። ከተመራቂዎቻቸው መካከልም ታዋቂዎቹ ኢብኑ ሩሽድ (አቬሮሽ)፣ ኢብኑ ሣይህ እና ኢብኑ ባጃ ይገኙበታል። በዘጠነኛው መቶ ክፍለዘመን በኮርዶቫ ዩኒቨርስቲ በቲዎሎጂ ዲፓርመንት ብቻ አራት ሺህ ተማሪዎች ይማሩ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ በወቅቱ በዩኒቨርስቲው ውስጥ አሥራ አንድ ሺህ ያህል ተማሪዎች ነበሩ።
የዚያ ዘመን ቅሪት የሆኑ በርካታ የሙስሊም የትምህርት ማዕከላት ዛሬም ድረስ አሉ። እነኚህ ማእከላት ዛሬ በዓለም ላይ ረጅሙን እድሜ እንዳስቆጠሩ ዩኒቨርስቲዎች ነው የሚታዩት። ከነኚህም መካከል በቱኒዚያ የሚገኙት አል-ቀይረዋን እና አዝ-ዘይቱና ዩኒቨርስቲዎች የሚጠቀሱ ሲሆን በግብፅ ደግሞ የአል-አዝሃር በሞሮኮ ፌዝ የሚገኘው አል-ቀረዊዪን ይገኙበታል።
በዘጠነኛው መቶ ክፍለዘመን የተመሠረተው አል-ቀረዊዪን ዩኒቨርስቲ በድንቅ ዑለማኦቹ /የሃይማኖት ሊቃውንቶቹ/ ይታወቃል። እዚያ ትምህርታቸውን ካጠኑትና ከተማሩት ምርጥ ምሁራን መካከል ኢብን ኸልዱን፣ ኢብን አል-ኸቲብ፣ ኢብን አል-ቢትሩጂ፣ ኢብን ሀራዚም፣ ኢብን መይሙን እና ኢብን ዋዛን የሚገኙበት ሲሆን ምናልባትም በ1003 የሞተውና የዐረቢኛ ቁጥሮችን ለአውሮፓውያን ያስተዋወቀው ኋላ ላይም ሲልቬስተር 2ኛ ጳጳስ ለመሆን የበቃው ጌርበርት ኦፍ ኦሪላክ /Gerbert of Aurillac/ ይጠቀሣል። አል-ቀረዊዪን ከመላዋ የሰሜን አፍሪካ፣ ከስፔን እና ከሰሃራ አካባቢ በርካታ ተማሪዎችን ለመሣብ ችሎ ነበር። ተማሪዎቹም ከሞሮኮ የንጉሣውያን ቤተሰብ እና በፌዝ ከሌሎች ነዋሪዎች እስፖንሰርሺፕ ያገኙ ነበር።
ዛሬም ድረስ እጅግ ገናና የሆነው የአል-አዝሃር ኢስላማዊ ዩኒቨርስቲ ምሁራን መካከል ደግሞ ለረጅም አመታት እዚያ የኖረው ኢብኑል-ሀይሰም፣ በ12ኛው መቶ ክፍለዘመን ህክምናን ሲያሰተምር የነበረው አል-ባግዳዲ እና በ14ኛው መቶ ክፍለዘመን መጨረሻ አካባቢ ላይ ከአል ቀረዊዪን መጥቶ እዚያ ያስተማረው ኢብኑ ኸልዱን ይገኙበታል።
ግብፅ በ1881 በእንግሊዝ ስትወረር በአል-አዝሃር ዩኒቨርስቲ ብቻ 7600 ተማሪዎች እና 230 ፕሮፌሠሮች ነበሩ። በእስልምና መባቻ አካባቢ በመስጂዶች ውስጥ አንድ አሊያም ሁለት ኢስላማዊ ሣይንሦች ብቻ ነበሩ የሚሠጡት። ነገርግን ከ9ኛው መቶ ክፍለዘመን አጋማሽ ጀምሮ ወደ ህጋዊ ትምህርቶች መግባቱ እየተጠናከረ ሲመጣ[21] ሣይንሣዊ ትምህርቶችም በሰፊው መሠጠት ተጀመሩ። ከነኚህም መካከል በአል-አዝሀር ዩኒቨርስቲ የሚሠጡት የአስትሮኖሚ፣ የኢንጂነሪንግ እና ህክምና ትምህርቶች ይጠቀሣሉ።[22] እነኚህ ትምህርቶች ኋላ ላይ በግብፅ ኢብኑ ቱሉን መስጂድም ይሠጡ ነበር።[23]
በዒራቅ ደግሞ ፋርማኮሎጂ /የመድሃኒት ትምህርት ጥናት/፣ ኢንጂነሪንግ፣ አስትሮኖሚ /የሥነከዋክብት ጥናት/ እና ሌሎች ትምህርቶች በባግዳድ በሚገኙ መስጂዶች ይሠጡ ነበር። ተማሪዎችም ከሦሪያ፣ ከፋርስ እና ከህንድ እነኚህን ሣይንሦች ለመማር ይመጡ ነበር።[24]
በአል-ቀረዊዪን መስጂድ ደግሞ በሰዋስዎ ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች ሥነቋንቋ፣ ሎጂክ፣ ሂሣብ፣ እና አስትሮኖሚ እንዲሁም የታሪክ፣ የመልክዓ ምድር ጥናት፣ እና ኬሚስትሪ ትምህርቶች ይሠጡ ነበር።[25]
በቱኒዚያ ቀይረዋን እና ዘይቱና መስጂዶች ደግሞ የሰዋሰው፣ የሂሣብ፣ የሥነከዋክብት ጥናት እና የህክምና ትምህርቶች ከቁርዓን እና የሸሪዓ ህግጋቶች ጋር ጎን ለጎን ይሠጡ ነበር።[26] በቀይረዋን ዚያድ በህክምና ዙሪያ የተለያዩ ክፍሎችን ይሠጥ ነበር። ኢብኑ ኸልፉን፣ ኢስሃቅ ኢብኑ ዒምራን እና ኢስሃቅ ኢብኑ ሱለይማን ሥራቸው በኮንስታንቲን ተተርጉሞላቸው በ11ኛው መቶ ክፍለዘመን ላይ በላቲን-አውሮፓ የመጀመሪያው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመሆን በበቃው በሣሌርኖ ደቡብ ኢጣሊያ ይሰጥ ነበር።[27]
መስጂዶች ከትምህርት ማዕከልነታቸው በተጨማሪ ቀስ በቀስ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ያዙ። የዚህን የቅየሣ አብዮት ሲያብራራ አል-መቅዲሲ እንዲህ ብሏል- በ10ኛው መቶ ክፍለዘመን አዲስ የኮሌጅ ዓይነት ማስፋፋት ተጀመረ። ይሀውም መስጂዱ-ኻን (ከከተማ ውጭ የሚመጡ ተማሪዎች የሚኖሩበት- አዳሪ ት/ቤቶች) እንዲኖረው ለማድረግ የታሠበ ነበር። ኮሌጆችን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሣደግና ለማሻሻል በዚያ ዘመን የግንባር ቀደምነቱን ሚና የተጫወተው በቡዪድስ አገዛዝ ሥር በርካታ ግዛቶች አስተዳዳሪ የነበረው በድር ኢብኑ ሀሰናዊህ (1014/1015 የሞተው) ነበር። ይህ ሰው በ30 አመታት የአገዛዝ ዘመኑ ከ3ሺህ በላይ የመስጂድ ውስጥ አዳሪ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች ግንባታዎችንም እንደገነባ ይነገራል።[28] የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የተገነቡበት ምክኒያት ነበር። የህግ ተማሪዎች የመጀመሪያ ድግሪ ትምህርታቸውን በአማካይ ከአራት አመት እና ከዚያም በላይ ለሚሆን ረጅም ጊዜ መከታተል ይኖርባቸዋል። ከምረቃ በኋላም ቢሆን በትምህርቱ ዓለም ልዩ ብቃት እንዲያገኙ እስከ ሀያ አመት ጊዜ ድረስ ሊቆዩ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። በአንዳንድ ልዩ ምክኒያቶች ካልሆነ በስተቀር መስጂዱ እራሱ ለማረፊያነት አያገለግልም። በመሆኑም ማረፊያ ቤቶቹ ለመምህራን እና ለተማሪዎች በቅርብ የሚገኙ ቦታዎች ሆኑ።
ከፍ ባለ ደረጃ የሚታዩት መድረሣዎች መቅዲሲ እንዳተተው የሙስሊም ኮሌጆቹ የመጨረሻ የእድገት ደረጃዎች ናቸው። በመስጂድ ውስጥ የሚሠጠውንም ሆነ በኻን የሚሠጠውን አገልግሎት አጠቃለው ይይዛሉ። ይህ ልምድ በነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘመን ይደረግ የነበረውን አሠራር የተከተለ ይመስላል። በወቅቱ መስጂዶች ለማስተማሪያ አገልግሎት ከመዋላቸው በተጨማሪ ከሩቅ ለሚመጡና መጠጊያ ላጡ ድሆች ተማሪዎች ማረፊያነትም ያገለግሉ ነበር።[29]
ለተማሪዎች የሚደረገው እገዛ ከፍተኛ ነበር። በቀረዊዪን ለምሣሌ ተማሪዎች ከክፍያ ነፃ የሆነ አገልግሎት ብቻ ሣይሆን በየጊዜውም የድጎማ ክፍያ ገንዘብ ይሠጣቸዋል። ዶግስ እንዲህ ይላል- ተማሪዎች የሚኖሩት የአራት ማእዘን ቅርፅ ባለው መኖሪያ ውስጥ ሲሆን ህንፃውም በመጠን የተለያዩና ከ60-150 ተማሪዎችን መያዝ የሚችሉ ሁለት እና ሦስት ፎቆች ነበሩት። ሁሉም መጠነኛ የሆነ የምግብ እና የመጠለያ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው።[30]
በአል-አዝሃር ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ቁጥር ሁልጊዜም ከፍተኛ ነው። አል-መቅሪዚ እንዳተተው ከመላዋ ግብፅ ከሚመጡ ተማሪዎች ውጭ 750 ያህል የውጭ ተማሪዎች ከሞሮኮና የፋርስ ምድር እሩቅ አካባቢዎች መጥተው በአንድ ጊዜ በመስጂዱ ውስጥ ይኖሩ ነበር።[31] በካይሮ ውስጥ መጠጊያ የሌላቸው ተማሪዎች ለነርሱ በተዘጋጀ የመኖሪያ ቦታ ላይ ይመደባሉ። የተመደቡበት ክፍልም ለነሱ ከክፍያ ነፃ በሆነ መልኩ ዳቦ የሚሠጣቸው ሲሆን ይህንንም ከቤተሰባቸው ከሚላክላቸው ስንቅ ጋር ይመገቡታል። የተሻለ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ተማሪዎች ከመስጂዱ አቅራቢያ ከሚገኘው ማረፊያ መኖር ይችላሉ። እያንዳንዱ ክፍል የራሱ የሆነ ቤተመፃህፍት፣ ማዕድ ቤት፣ መታጠቢያ ክፍል እና የቤት እቃ ማስቀመጫ የተወሰነ ቦታ ነበረው።[32]
ወደ ዳማስቆ ባደረገው ጉዞ ተጓዡ ኢብኑ ጁበይር በኦማያውያን መስጂድ ውስጥ ለውጭ ተማሪዎችና ጎብኚዎች የሚያገለግል በቁጥር ከፍተኛ የሆነና የተሟላ ቁሣቁስ ማየቱን ዘግቧል። ይህም ሁኔታ “በምዕራቡ ዓለም የሚገኝ ማንኛውም ስኬትን የሚፈልግ ሰው እዚህ ይምጣና ይማር። ምክኒያቱም እዚህ ከፍተኛ የሆነ እገዛ አለ። ዋናው ነገር ተማሪዎች ከምግብና መጠለያ ሀሣብ እፎይ ማለታቸው ሲሆን በርግጥም ይህ ትልቅ እገዛ ነው።” እንዲል አስችሎታል።[33]
መስጂዶችን የትምህርት ማዕከላት በማድረጉ በኩል መሪዎች ከፍተኛ የሆነ ሚና ተጫውተዋል። በቀረዊዪን መስጅድ ሦስት የተለያዩ ቤተመፃህፍቶች ነበሩ። ከሦስቱ እጅግ የላቀ ክብር የሚሠጠው በሜሪኒድ ሱልጣን አልሙተወኪል ኢብን አናን የተመሠረተው ኢብን ኢናን ቤተመፃህፍት ነበር።[34] እጅግ አንባቢ እና መፅሃፍ ሰብሣቢ የነበረው ሱልጣን በሃይማኖት፣ በሣይንስ፣ በጥበብ፣ በቋንቋና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ በርካታ መፃኅፍትን በአዲሱ ቤተመፃህፍቱ ውስጥ ከማጠራቀሙም በላይ ሥራውንም በበላይነት የሚቆጣጠር የቤተ-መፃህፍት ባለሙያ ቀጥሯል።[35]
በቱኒዚያ ስፔኖች ከ1534-1574 ባለው ጊዜ ዋና ከተማዋን ቱኒስን ውስጥ በተቆጣጠሩበት ወቅት መስጂዶቿንና ቤተመፃህፍቶቿን አውድመዋል። በርካታ ውድ መፃህፍትንና እና ረቂቅ የሥነፅሁፍ ሥራዎችንም አስወግደዋል።[36]
የኦቶማን ሱልጣን ስፔናውያኑን ድል አድርጎ ባባረረበት ወቅት የዘይቱናን መስጂድ በማደስና በማስፋፋት ቤተመፃህፍቱንና መድረሣውን በመጠገን ዳግም ከፍተኛ የሆነ የእስልምና ሥልጣኔ ማዕከል እንዲሆን አድርጎታል።[37]
በካይሮ በ1365 የመምሉክ አልጋ ወራሽ የነበረው የል-ባገሀ አል-ዑመሪ በኢብን ቱሉን መስጂድ ውስጥ ለሚገኝ ለያንዳንዱ ተማሪ አርባ ድርሃም እና በየወሩ አንድ ኢርደብ ስንዴ እንዲሠጠው አዞ ነበር።[38] መምሉኮች ከዚህም በተጨማሪ ደሞዝና የተለያዩ ድጎማዎችን ለበርካታ አስተማሪዎችና ተማሪዎች ይሠጡ ነበር።[39] ይህም አሠራር በሌላው የካይሮ ክፍል የሚገኘውን የኢብን ቱሉንን መስጂድ ባደሠው በሱልጣን ሁሣም አድ-ዲን ላጂን ከፍተኛ የሆነ እውቅና የተሠጠው ሲሆን እሱም ለፕሮፌሰሮች ደሞዝና ለተማሪዎች ደግሞ ድጎማ ይሠጥ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የራሱን የግል ሀኪም ሸረፍ አድ-ዲን ሙሀመድ ኢብን አል-ሀዋፍርንም በህክምና ዙሪያ እዚያ ትምህርት እንዲሠጥ ጠይቆታል።[40]
ቀጥሎ ያለው አጭር ታሪክ በትምህርትና ባጠቃላይ ህይወት በዚያ ወርቃማ የኢስላም ዘመን ነበረውን ምስል ይሠጠናል።[41] ኢብን ቱሉን ግብፅን ይገዛ በነበረበት ዘመን የተወሰኑ ተማሪዎች በየቀኑ የአንድን ፕሮፌሰር ትምህርት የተወሠነ ክፍል የግድ መጨረስ ነበረባቸው። ነገርግን ትምህርቱ ከማለቁ በፊት ገንዘባቸውን ጨረሱ። ምግብ ለመግዛት ሲሉ ሁሉንም ነገር መሸጥ ነበረባቸው። ከሦስት ቀናት ርሃብ በኋላ እርዳታ ፍለጋ ለመለመን አሰቡ። ነገርግን ከነርሱ ውስጥ የዚህ ዓይነቱን ክብር የሚነካ ነገር መዳፈር የሚፈልግ ማንም አልነበረም። በመሆኑም ብዙ ጣሩ። ከመካከላቸው አንደኛው ወደሚኖሩበት መስጂድ ጥግ በማምራት ካለበት ጭንቅ ያወጣው ዘንድ አላህን ለመነ። ወዲያውኑ ከኢብን ቱሉን ዘንድ አንድ መልእክተኛ ገንዘብ ይዞ መጣ። ኢብን ቱሉን ይህን ያደረገው በህልሙ እነኚህን ተማሪዎች እንዲረዳ ማስጠንቀቂያ ስለደረሰው ነበር። ኢብን ቱሉን በዚህም ሣይወሰን በሚቀጥለው ቀን እርሱ እራሱ በአካል እንደሚጎበኛቸውም ጭምር መልእክት ላከላቸው። በዚህን ጊዜ ተማሪዎች የወሰኑት ውሳኔ የሚገርም ነበር። በአንዳንዶች ዘንድ እንደ ትልቅ እድልና ሽልማት ከሚታየው ከዚህ ክብር ለመሸሽ ሲሉ ተማሪዎቹ የዚያኑ ምሽት ካይሮን ለቀው ጠፉ። ኢብን ቱሉንም ያንን እነሱ የነበሩበትን ክፍል በመግዛት በውስጡም መስጂድ በመስራት ለተማሪዎችና እንግዶች መኖሪያ እንዲሆን አደረገ።
የቀደምት የሙስሊሙ ዓለም የትምህርት ሥርዓት በአውሮፓውያን ቀጥሎም በመላው ዓለም ላይ በብዙ መልኩ ተፅእኖ አሣድሯል። ለምሣሌ አለማቀፋዊነቱ፣ የትምህርት አሠጣጥ ዘዴውና ዲፕሎማ አሠጣጡ። ጆርጅስ መቅዲሲ በየዩኒቨርስቲዎች የሚደረጉ ክንውኖችን ማለትም የዶክትሬት መመረቂያ ፅሁፎችንና ዲፌንሶችን፣ በአቻ ምሁራኖች በላቁ ሣይንሣዊ ሥራዎች ላይ የሚደረጉ የርስ በርስ ግምገማዎችን (peer review)፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለፕሮፌሰሮችና ለተማሪዎች የአካዳሚክ ነፃነት ፅንሠ ሀሣቦችንና የመሣሰሉትን በመጥቀስ ይህንን ተፅእኖ ለማሣየት ሞክሯል። ከላይ የተጠቀሱትንና የመሣሰሉትን ሁሉ አውሮፓውያኑ ከሙስሊሙ ዓለም በመቅዳት በሚገባ ተጠቅመውባቸዋል።
በዚያ ከሙስሊሙ ውጭ ባለው አለም ሣይንሣዊ አለመቻቻሎች በነገሱበትና ነፃ የሆኑ ምሁራዊ አስተሣሠቦች በእሣት ጭምር በሚያስቀጡበት ዘመን በመስጂድ ውስጥ የሚደረጉ ግልፅና ነፃ ውይይቶች በሌላው አለም ላይ ተፅኖአቸው የዋዛ አልነበረም። የአካዳሚክ ተፅእኖው በሙስሊም ምሁራን በተፃፉ በርካታ መፅሃፎችም በኩል ነበር። መፃህፍቶቹ በ12ኛውና በ13ኛው መቶ ክፍለዘመን መካከል በተመሠረቱትና በአውሮፓ የመጀመሪያዎቹ ዩኒቨርስቲዎች በነበሩት በሞንቴፒላር፣ ቦሎኛ ፓሪስ፣ ኦክስፎርድና በመሣሰሉት ዋንኛ ማስተማሪያዎች ነበሩ። ሙስሊሞች አውሮፓ ትምህርት ላይ ተፅእኖ ያሳደሩባቸውን ሌሎች መንገዶች ለመዘርዘርም ሆነ ለመናገር ጊዜም ሆነ ወረቀት አይበቃንም። በዚህ ዙሪያ በመቅዲሲ እና በሪቤራ የተሠሩ ምርጥ ሥራዎችን ማየት ይቻላል።[42]
በመጨረሻም- አንዳንዶች የሙስሊሞች ሥልጣኔ የመንኮታከት ምንጩ እስልምና ነው ለማለት ሲሞክሩና ሲወቅሱ እናያለን። ሆኖም ግን ለሙስሊሞች ሥልጣኔ መውደቅ ትልቁን ድርሻ ያበረከተው በዚያን ዘመን የማስተማሪያ ማዕከላት የነበሩት ተቋማት እንደ ኮርዶቫ፣ ባግዳድ እና ሲቪያ በአውሮፓውያን እና ሞንጎሎች እጅ መወረራቸውን መውደማቸው መሆኑን መዘንጋት የለብንም። እስልምና ከመባቻው ጀምሮ ከምርምርና እውቀት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞና ተቆራኝቶ ነው የመጣው። የቁርዓን አንቀፆችም ሆኑ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) መልዕክቶች ሰዎች እንዲማሩና እውቀትን ፍለጋ እንዲንቀሣቀሱ የሚያነሣሱ ናቸው። መስጅዶች ትልቅ የእስልምና ምልክት ሲሆኑ በሙስሊሙ ዓለም ዋንኞቹ የዕውቀት ምንጮችም እነርሱ ናቸው። በአብዛኛው ሙስሊም ሀገራት “ጀመዓ” የሚለው ቃል በመስጅድም ሆነ በመድረሳ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ ያጠቃልላል። በዐረቢኛ “ጃሚዓ” (ዩኒቨርስቲ) የሚለው ቃል የተወሰደው “ጃሚዕ” (መስጂድ) ከሚለው ቃል ነው። በየትኛውም ቋንቋ አሊያም ባህል የዚህ ዓይነት መወራረስ ልናገኝ አንችልም። የእስልምናን እና የእውቀትን ቁርኝት ለማሣየት ደግሞ ከዚህ የበለጠ ማሣያ ማምጣት ይከብዳል።
[1] S.P.Scott: History of the Moorish Empire in Europe, J.B. Lippincott Company, Philadelphia and London, 1904 Vol iii, at pp 467-8.
[3] F.B. Artz: The mind, The Mind of the Middle Ages; Third edition revised; The University of Chicago Press, 1980, p.151.
[4] M. Nakosteen: History of Islamic origins of Western Education, 800-1350; University of Colorado Press, Boulder, Colorado, 1964, P.48.
[7] J. Waardenburg: Some institutional aspects of Muslim higher learning, NVMEN, 12, pp.96-138; At p. 98.
[15] George Makdisi: The Rise of Humanism in Classical Islam and the Christian West; Edinburgh University Press, 1990, pp. 210-1.
[18] Ibn Battutah in K.A. Totah: The Contribution of the Arabs to Education; Bureau of Publications, New York: Columbia University, 1926, p 45.
[19] 24Al-Maqrizi, Ahmad Ibn Ali. Al-Mawaiz wa Alitibar fi dhikr Al-Khitat wa-Al-athar. Edited by Ahmed Ali Al-Mulaiji. 3 Vols. Beirut: Dar al Urfan. 1959, Vol 3, p 203.
[20] A. s. Tritton: Materials on Muslim education in the Middle Ages, p. 100, Luzac and Company, London.
[21] George Makdisi: Islamic Schools, Dictionary of the Middle Ages, Vol 11; Charles Scribners and Sons, 1988; p.65.
[22] M. Alwaye: ‘Al-Azhar…in thousand years.’ Majallatu’l Azhar: (Al-Azhar Magazine, English Section 48, July 1976: 1-6 in M. Sibai, Mosque Libraries.)
[23] Pedersen, Johannes. ‘Some aspects of the history of the madrassa’ Islamic Culture 3 (October 1929) pp 525-37, p. 527.
[25] R. Le Tourneau: Fes in the age of the Merinids, trsl from French by B.A. Clement, University of Oklahoma Press, 1961, p. 122.
[26] H. Djait et al: Histoire de la Tunisie (le Moyen Age); Societe Tunisienne de Difusion, Tunis; p. 378.
[27] Al-Bakri, Massalik, 24; Ibn Abi Usaybi’a, Uyun al-anba, ed. and tr A. Nourredine and H. Jahier, Algiers 1958, 2.9, in Encyclopedia of Islam, Vol IV, pp 29-30.
[34] M. Sibai: Mosque Libraries, an historical study; Mansell Publishing Ltd; London and New York; 1987; p 55.
[35] Levi Provencal, Evariste, Comp. Nukhab Tarikhiya Jamia li Akhbar al-Maghrib al-Aqsa, Paris: La Rose, 1948: pp 67-68.
[36] Mary J. Deeb: Al-Zaytuna; in The Oxford Encyclopaedia of the Modern Islamic World; edt: J.L. Esposito; Oxford University Press; 1995; Vol 4; p. 374.
[38] Al-Maqrizi, Ahmad Ibn Ali. Al-mawaiz wa Alitibar fi dhikr al-Khitat wa-Alathar. Edited by Ahmed Ali al-Mulaiji. 3 Vols. Beirut: Dar al-Urfan. 1959. Vol 3, pp: 222-3.
Comment:ደስ ይላል