አቡበክር ሲዲቅ (ረ.ዐ)

0
12260

ታሪካቸው ባጭሩ

የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኸሊፋ የሆኑት አቡበክር አስ-ሲዲቅ ዐብደላህ ቢን አቡ ቁሐፋህ ኡስማን ቢን ዓሚር አል-ቁረይሽይ አት-ተሚሚይ ሲሆን የዝሆኑ ክስተት እውን በሆነ በሁለት አመት ከስድሰት ወሩ ተወለዱ።

ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በነብይነት ከመላካቸው በፊት አቡበክር ባልንጀራቸው ነበሩ። ከነብይነት በኋላም ቀድመው ሰለሙ። በመካው የዳዕዋ ዘመን አብረዋቸው ሆኑ። ወደ መዲና ሲሰደዱ፣ በዋሻው ታሪክና ከዚያ በኋላ እስኪሞቱ ድረስ ከርሳቸው አልተለዩም።

በተቡክ ዘመቻ የሙሰሊሞችን አርማ ተሸካሚ ነበሩ። በዘጠነኛው ዓመተ ሂጅራ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በሕይወት እያሉ የሐጅ ሥርዓትን መርተዋል። ከርሳቸው ሞት በኋላም እርሳቸውን ተክተው የሙስሊሞች ኸሊፋ ሆነዋል። የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ምትክ (ኸሊፊቱ ረሱሊላህ) የሚል ማእረግም በሙስሊሞች አግኝተዋል።

ኢብን ኢስሐቅ “ሲረቱል ኩብራ” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንዳወሱት አቡበክር (ረ.ዐ) በወገኖቻቸው ዘንድ ተወዳጅ እና ተግባቢ ሰው ነበሩ። በቁረይሽ የዘር ሐረግና ታሪክ እውቀትም አቻ አይገኝላቸውም። ጸባየ መልካም ነጋዴ ነበሩ። ሰዎች የርሳቸውን እውቀት፣ ተሞክሮና መልካም ባህሪ በመሻት በጣም ይቀርቧቸው ነበር። ከርሳቸው ጋር መቀማመጥንም ይወዱ ነበር።

አቡበክር ይበልጥ የሚቀርቧቸውንና የሚያምኗቸውን ሰዎች ወደ እስልምና ጋበዙ። በርሳቸው እጅ፣ ዑስማን፣ ጦልሐ፣ ዙበይር፣ ሰዕድ እና ዐብዱረህማን ኢቢን አውፍ ሰለሙ።

የዕቁብ ኢቢን ሱፍያን በታሪክ ዘገባቸው እንዳወሱት፣ አቡበክር ሲሰልሙ አርባ ሺህ (የወርቅ ሳንቲሞች) ነበሯቸው። ወዲያውኑ በአላህ መንገድ መጸወቱት። ለአላህ ሲሉ ስቃይና መከራ ያስተናገዱ ሰባት ባሪያዎችን ገዝተው ነጻ ለቀቁ። እነርሱም ቢላል፣ ዓሚር ኢቢን ፋሀይራህ፣ ዚኒራህ፣ ነህዲያህንና ልጇን፣ የበኒ ሙእመል እንስት አልጋይና ኡምሙ ዓቢስ ናቸው።

ኡሳማ ኢቢን ዘይድ አባታቸውን ጠቅሰው እንዳስተላለፉት “አቡበክር እውቅ ነጋዴ ነበሩ። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በነብይነት ሲላኩ አቡበክር አርባ ሺህ የወርቅ ሳንቲሞች ነበሯቸው። ባሪያዎችን እየገዙ በመልቀቅና የተቸገሩ ሙስሊሞችን በመርዳት ሐብታቸውን ወጭ አደረጉ። ወደ መዲና ሲሰደዱ 5 ሺህ (የወርቅ ሳንቲሞች) ብቻ ቀራቸው። እርሱንም መዲና ውስጥ መጸወቱት።”

ቡኻሪ እንደዘገቡት ዐምር ኢቢን አል-ዓስ (ረ.ዐ) እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡-

“የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ከርስዎ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ሰው ማን ነው? በማለት ጠየቅኳቸው። ‘ዓኢሻ’ አሉኝ። ‘ከወንድስ?’ አልኳቸው። ‘አባቷ’ አሉኝ። ቀጥሎም ሌሎች ሰዎችን አወሱ።”

ዐብደላህ ኢቢን ጃእፈር (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፡- “ወዳጃችን አቡበክር፣ መልካም፣ እጅግ ሩህሩህና አዛኝ ኸሊፋችን ናቸው።”

ኢብራሂም አን-ነኸዒ እንዲህ ብለዋል፡- “አቡበክር በጣም አዛኝ ስለነበሩ ‘አውዋህ’ ተብለው ተጠሩ።”

በ 11ኛው ዓመተ ሂጅራ በወርሃ ጀማዱል ኡላ ሰኞ ቀን በ63 ዓመት እድሜያቸው ይህችን ዓለም በሞት ተሰናበቱ።

ባህሪያቸውና ስብእናቸው

በጃሂልያ ዘመን ከቁረይሾች መሐል በዘር ሐረግና በታሪክ እውቀት ወደር አይገኝላቸውም። ውጤታማ ነጋዴም ነበሩ። በመልካም ባህሪና በችሮታ ይታወቃሉ። ወገኖቻቸው ይወዷቸዋል። አስካሪ መጠጥ አይጠጡም፣ ጣኦት አያመልኩም። ስብእናቸውን የሚያጎድፍ አንዳች ድርጊት ሲፈጽሙ አልተስተዋሉም። ቆዳቸው ነጭና አካላቸው ሸንቃጣ፣ የፊታቸው ስጋ መጠነኛ ነበር። ዓይኖቻቸው ገባ፣ ግንባራቸው ወጣ ያሉ ነበሩ። ጸጉረ ብዙ፣ የተስተካከለ ቁመና ባለቤት ነበሩ።

ሰዎች በጃሂልያ ዘመን የአቡበክርን መልካም ስብእና እና ታማኝነት በማወቃቸው “አስ-ሲዲቅ” (እውነተኛው) በሚል ቅጽል ስም ጠሯቸው። በታማኝነታቸው ቁረይሾችን በመወከል ይፈጣጠሙ ነበር። ቁረይሾች እርሳቸው ያጸደቁትን ያጸድቃሉ። ሌላ ሰው ያጸደቀውን ግን ተቀብለው ለመተግበር ያንገራግራሉ።

ኢስላምን መቀበላቸው

ከነብይነት በፊት የመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረባ ነበሩ። አላህ ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) በመልእክተኝንት ሲያልቃቸው ወደ እስልምና መጀመሪያ የጋበዙት አቡበክርን ነበር። እርሳቸውም ሳያመነቱ እስልምናን ተቀበሉ። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን በማስመልከት ሲናገሩ፡-

“የትኛውም ሰው ወደ እስልምና ስጋብዘው ይከብደዋል። ለመቀበልም ያመነታል። አቡበክር ሲቀር። እርሱ ግን ወዲያውኑ እንደጠራሁት ሳያመነታ ተቀበለኝ።” (ሲረት ኢቢን ሂሻም)

በተለያዩ የዳዕዋው እርከኖች ውስጥ ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሳይነጠሉ፣ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እያደረጉላቸው፣ ለአምላክና ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጥሩና አማኝ፣ ለሐይማኖታቸው ቀናኢ ሆነው ኖረዋል። በዚህ ሂደትም የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የስደት ጉዞ ተጋሪ፣ የዋሻ ውስጥ ባልደረባ እንዲሆኑ ያስቻሏቸውን በርካታ መከራዎች አስተናግደዋል። ገንዘባቸውን ሁሉ ለእስልምና ዳዕዋ ሳይሰስቱ ችረዋል። ከአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) “የአቡበክር ገንዘብ የጠቀመኝን ያህል በማንም ገንዘብ አልጠቀመኝም።” የሚል ምስክርነትአግኝተዋል። (አህመድ፣ አቡ ሐቲምና ኢቢን ማጃህ)

የዚህ ሁኔታ የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ደግፈው ለቀልባቸውም ይበልጥ ቅርብና ለኸሊፋነትም ይበልጥ ብቁ ሶሐባ ለመሆን ታደሉ። በዚህ ረገድ ታላቁ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ) የሰጡት ምስክርነት ከበቂ በላይ ነው። እንዲህ ብለዋል፡-

በባልደረባነትና በገንዘብ ከማንም በላይ የደገፈኝ አቡበክር ነው። ከአምላኬ ውጭ የመጨረሻውን ፍጹማዊ ፍቅር የምለግሰው ሰው ቢኖር ኖሮ ያ ሰው አቡበክር ይሆን ነበር። ቢሆንም የእስልምና ወንድማማችነት እና ፍቅር አስተሳስሮናል።” (ቡኻሪ፣ ሙስሊምና ቲርሚዚ ዘግበውታል)

ልቅናቸውን የሚገልጹ ምስክርነቶች

የአቡበክርን ልቅና ከሚያሳዩ ዘገባዎች መካከል አቡ ሰዒድ (ረ.ዐ) ያስተላለፉት ይገኝበታል። እንዲህ ብለዋል፡-

“ከእለታት አንድ ቀን የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‘አላህ አንድን ባሪያውን ከዚህች ዓለም ሕይወትና ከርሱ ዘንድ ካለው ጸጋ ሲያስመርጠው ከአላህ ዘንድ ያለውን መረጠ።’ በማለት ሲናገሩ አቡበክር አለቀሱ። ለቅሷቸው አስገረመን። ለካስ ምርጫ የተሰጣቸው መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ኖረዋል። አቡበክርም ከማንኛችንም ቀድመው ይህን ተረድተዋል:: መልእክተኛውም (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إنَّ من أمنِّ الناس علىَّ فى صحبته وماله أبا بكر ، ولو كنت متخذاً خليلاً غير ربى لاتخذت أبا بكر ولكن أخوة الإسلام ومودته ، لا يبقين فى المسجد باب إلا سُدَّ إلا باب أبى بكر

‘በባልደረባነትና በገንዘብ ከማንም በላይ የደገፈኝ አቡበክር ነው። ከአምላኬ ውጭ የመጨረሻውን ፍጹማዊ ፍቅር የምለግሰው ሰው ቢኖር ኖሮ ያ ሰው አቡበክር ይሆን ነበር። ቢሆንም የእስልምና ወንድማማችነት እና ፍቅር አስተሳስሮናል። የአቡበክር በር ሲቀር ሁሉም የመስጂዱ በሮች ይዘጋሉ’። (ቡኻሪ፣ ሙስሊምና ቲርሚዚ ዘግበውታል)

በሌላ ዘገባ እንደተወሳው እንዲህ ብለዋል፡-

“ከአምላኬ ውጭ ፍጹማዊ ፍቅር የምለግሰው ሰው ቢኖር ኖሮ ያ ሰው አቡበክር ይሆን ነበር። ይህም ሆኖ ወንድሜና ባልደረባዬ ነው። አላህ ባልደረባችሁን ፍጹማዊ ወዳጁ (ኸሊል) አድርጎታል።” (ቡኻሪ፣ ሙስሊምና ቲርሚዚ ዘግበውታል)

በአላህና በመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ማመን

አቡበክር የመጀመሪያው ሙስሊም እንዲሆኑና የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የሚናገሩትን ሁሉ ቅንጣት ሳይጠራጠሩና ሳያመነቱ እንዲቀበሉ የረዳቸው ይህ እምነታቸው ነው። በኢስራእ እና ሚዕራጅ ሐዲስ ውስጥ ያሳዩትን እጅግ አንጸባራቂ አቋም አስተውል። የአላህ መልእክተኛ ለባልደረቦቻቸውና ለቁረይሾች በዚያች ሌሊት ያጋጠማቸውን ክስተት ባጫወቷቸው ጊዜ እምነተ ደካሞች ከእስልምና እስከ መውጣት ደረሱ። ቁረይሾችም በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ተሳለቁ። አቡበክር ስለዚህ እንግዳ ክስተት የሚኖራቸውን አቋም ለማወቅም አቡ ጀህል ወደርሳቸው ሄደ። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተናገሩትንም አጫወታቸው። እርሳቸውም በፍጹም መተማመንና በእርጋታ፡- “በእርግጥ ይህን ተናግረዋልን?” በማለት ጠየቁ። አቡ ጀህልም “አዎ” ሲል መለሰ። እርሳቸውም፡- “ሙሐመድ ይህን ከተናገረ እውነቱን ነው” አሉ። አቡ ጀህልና አብረውት የነበሩት ባልደረቦቹም፡- “በአንድ ቀን ሌሊት ወደ በይተል መቅዲስ ሄጄ ሳይነጋ በፊት ተመለስኩ ማለቱን አምነህ ትቀበላለህን?” አሏቸው። አቡበክር የሚከተለውን አስገራሚ መልስ ሰጡ፡-

إني لأصدقه فيما هو أبعد من ذلك ،من خبر السماء يأتيه في غدوة أو روحة

“ከዚህ ይበልጥ እንግዳ የሆነ ነገር ተናግሮ አምኘዋለሁ። ጧት ማታ ከሰማይ መልእክት እንደሚወርድለት ነግሮኝ ተቀብየዋለሁ” አሉ። ወደ ነቢዩ (ሶ.ወ.ወ) በመሄድም የኢስራእን ታሪክ ሰሙ። “አንተ የአላህ መልክተኛ መሆንህን እምሰክራለሁ።” በማለትም የሰሙትን ሳያመነቱ መቀበላቸውን አረጋገጡ። (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

የመጨረሻውን የምጥቀት ጫፍ የደረሰ ኢማን፣ የዚህ እምነት ባለቤት የኢስላም ታላላቅ ሰዎች ፈርጥ ቢሆኑ ምኑ ያስገርማል!

መስዋእትነት

አቡበክር ነፍሳቸዉንና ገንዘባቸውን ለእስልምና ዳዕዋ መሰዋታቸው የጽኑ እምነታቸው አይቀሬ ውጤት ነው። ኢማን ወደ ቀልብ ሲገባ ለመስዋእትነት ያነሳሳል። እንደ አቡበክር አይነት እጅግ ጽኑና ጥልቅ እምነት ከሆነስ?!

አቡበክር ራሳቸውን ለመስዋእትነት አቅርበው የአላህን መልእክተኛ የታደጉባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። አንድ ቀን ቁረይሾች ከካዕባ መስክ ላይ የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለማነቅ ሙከራ ሲያደርጉ አቡበክር ተከላከሉላቸው። በዚህ ጊዜ ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ትተው ከርሳቸው ላይ በመረባረባቸው ራሳቸውን ስተው እስኪወድቁ ድረስ ደበደቧቸው። አፍንጫቸውን ከዓይናቸው ወይም ከጉንጫቸው መለየት እስኪያዳግት ድረስ ክፉኛ ቆሰሉ። ሰዎች አንስተው ወደቤታቸው ወሰዷቸው። ራሳቸውን ሲያውቁ መጀመሪያ ያቀረቡት ጥያቄ፡- “የአላህ መልእክተኛ በምን ሁኔታ ውስጥ ናቸው?” የሚል ነበር። (ሲረቱ አን-ነበዊያህ ዘይኒ ደህላን፡፡)

ከመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ወደ መዲና በተሰደዱ ጊዜም ተመሳሳይ መስዋእትነት ከፍለዋል። ቁረይሾች አግኝተው ሊገድሏቸው ብርቱ ጥረት አድርገዋል። በዚህ ጊዜ የአቡበክር አቋም እጅግ አስገራሚ ነበር። ቁረይሾች ከዋሻው በር ላይ ቆመው በነበረ ጊዜ የተናገሩትን ድንቅ ቃል እንመልከት፡-

“የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አንደኛቸው ወደ እግሩ ስር ቢያይ ይመለከተናል።” መልእክተኛው ግን ባልደረባቸውን እንዴት እንደሚያጸኑ ያውቁ ነበር። እንዲህ አሉ፡- “አቡበክር ሆይ! አላህ አብሯቸው ባለ ሁለት ሰዎች ስጋት አይግባህ።”

አቡበክር ገንዘባቸውን ሁሉ ለእስልምና ዳዕዋ መስዋእት አደረጉ። ዓኢሻ እንዲህ ብለዋል፡-

“አቡበክር 40 ሺህ (የወርቅ ፍራንክ) ለዳዕዋ መጸወቱ። የአላህ መልእክተኛ ለአስቸጋሪው የተቡክ ዘመቻ ጦርነት ትጥቅና ስንቅ እንዲዘጋጅ ባልደረቦቻቸውን በጠየቁ ጊዜ ሶሐቦች ገንዘቦቻቸውን እየያዙ መጡ። ኡስማን ብዙ ገንዘብ አመጣ። ዑመር ግማሽ ሐብታቸውን መጸወቱ። አቡበክር ደግሞ ሙሉ ገንዘባቸውን ሰጡ። የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‘አቡበክር ሆይ! ለቤተሰቦችህ ምን አስቀረህ?’ ሲሏቸው። ‘አላህንና መልእክተኛውን’ ሲሉ መለሱ።” (ቲርሚዚ ዘግበውታል)

ብልህነትና ቆራጥነት

በጃሂልያ ዘመን ወገኖቻቸው ጣኦት ለማምለክ ሲጋፉ እርሳቸው አንድም ጊዜ እንኳ ለጣኦታት ለመስገድ ካለመፍቀዳቸው፣ ወገኖቻቸው በአስካሪ መጠጥ ሲነከሩ እርሳቸው ግን ኢምንት እንኳ ካለመጎንጨታቸው የበለጠ ብልህና አስተዋይ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነገር የለም። ጣኦት አምልኮ ቂልነት እና ጥመት፣ አስካሪ መጠጥ መጠጣትም ውድቀትና ውርደት መሆኑን በብሩህ አእምሯቸው ተረድተዋል።

ምን ያህል ጀግናና ቆራጥ እንደሆኑ ለማሳየት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በሞቱና ከፊል ዐረቦች በኢስላማዊው ስርዓት ላይ ባመጹ ጊዜ ያሳዩአቸው አስደናቂ የጀግንነት አቋሞች በቂ ናቸው።

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በሞቱ ጊዜ ሶሐቦች እጅግ ከማዘናቸው የተነሳ ከፊሎቹ አንደበታቸው ተሳሰረ። ሌሎችም ከተቀመጡበት መነሳት ተሳናቸው። ዑመርም (ረ.ዐ) “ነብዩ አልሞቱም። ይመለሳሉ።” እስከማለት ደረሱ። አቡበክር ግን ሌሎች ሰዎች እንደሚሞቱት መልእክተኛውም መሞታቸውን አወጁ። የዑመርን ንግግር ሐየሱ። ሶሐቦችን አረጋጉ። የሚከተለውን የአላህ ቃልም አስታወሱ፡-

وَمَا مُحَمَّدٌ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ

“ሙሐመድም ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡” (ኣሊ-ዒምራን 3፤144)

ሪዳህን ክስተትን የተቆጣጠሩበት ሁኔታም በወሳኝና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ የሚላበሱትን ፍጹም ጀግንነት ያሳያል። ያኔ አላህ የአቡበክርን ቀልብ በሐቅ ላይ ባያጸና እና የጽኑ ነብያትን ቆራጥነት ባያላብሳቸው ኖሮ ተከስቶ የነበረው ፈተና ገና ለጋ የነበረውን የእስልምና ሕንጻና መንግስቱን ባወደመው ነበር። ይህም ስለሆነ ነው አቡበክር ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በኋላ ሁለተኛው የእስልምና መንግስት መስራች ተብለው የሚወደሱት።

ትህትናና ቁጥብነት

እንደ አቡበክር ያለ ታላቅ ስብእና ስልጣን አያታልለውም። ከኢስላማዊው አደብና ስነምግባር አያወጣውም። እናም በኸሊፋነት ዘመናቸው ልክ እንደ ቀድሞው ለስላሳና አዛኝ፣ ለሕዝባቸው ጉዳይም ቀናኢ ሆነው ቀጠሉ። ተከታዩ ታሪክ አቡበክር በኸሊፋነት ዘመን የነበራቸውን ትህትና ለማሳየት ጥሩ ምስክር ነው፡-

አቡበክር ለአዛውንትና ረዳት አልባ እንስቶች ዘወትር ጠዋት ፍየል ያልቡ ነበር። ኸሊፋ በሆኑ ጊዜ አንዲት የመንደራቸው እንስት፡- “ከእንግዲህ አቡበክር ፍየሎቻችንን አያልብልንም” አለች። አቡበክር ይህን ማለቷን ሲሰሙ፡- “በአላህ እምላለሁ፣ እንደወትሮው ሁሉ ማለቤን እቀጥላለሁ። የኖርኩበትን መልካም ባህሪ አላህ እንደማይቀይርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ።” አሉ።

የዓለማችን ታላላቆች ለክብራቸው እንዲያጎበድዱ የሚያደርግ አንጸባራቂ አቋም ነው።፡ ከስጋዊ ስሜቶችና ዝንባሌዎች በላይ በመምጠቅ የኡምማውን መብትና አስፈልጎት የማስታወስ፣ ክብሩንና ገንዘቡን የሚጠብቅለት ታላቅነት ነው።

የአቡበክር ዙህድ

የአቡበክርን ዙህድ (ለዓለማዊ ጸጋና ድሎት አለመጓጓት) ከሚያሳዩ ክስተቶች መሐል ኢማም አህመድ፣ አኢሻን ጠቅሰው የዘገቡት ታሪክ ይገኝበታል። እንዲህ ብላለች፡-

“አቡበክር ሲሞቱ አንዲት ዲናር ወይም ዲርሃም አልተውም። ከመሞታቸው በፊት ገንዘባቸውን በሙሉ ወደ በይተል ማል (የሙስሊሞች የገንዘብ ግምጃ ቤት) አስገብተውት ኖሯል።”

ዑርወት እንዳስተላለፉት አቡበክር ኸሊፋ በተደረጉ ጊዜ ያላቸውን እያንዳንዷን ዲርሃምና ዲናራቸውን ወደ ሙስሊሞች በይተል ማል አስገቡ። “በዚህ ገንዘብ እነግድ ነበር። አሁን ግን ኸሊፋቸው ሲያደርጉኝ መነገድ አልቻልኩም።” አሉም።

አጧእ ቢን ሳኢብን በመጥቀስ ቢን ሰእድ እንደዘገቡት አቡበክር ኸሊፋ በተደረጉ ማግስት ጠዋቱኑ በርካታ ኩታ በትከሻቸው ተሸክመው ሲሄዱ ዑመር ተመለከቷቸው። “የት እየሄድክ ነው?” ሲሉም ጠየቋቸው። “ወደ ገበያ” በማለት መለሱ። “የሙስሊሞች ሐላፊ ተደርገህ እያለ ኃላፊነትህን ትተህ ገበያ ውስጥ ምን ትሰራለህ?” ሲሉም ጠየቋቸው። “ቤተሰቦቼን ምን ላበላ ነው?” አሉ አቡበክር። “አቡ ዑደይዳህ ቀለብ ይወስንልሃል” አሏቸው። ተያይዘው ወደ አቡ ዑበይዳህ ዘንድ ሄዱ። እርሳቸውም፡- “አንድ ሙሃጅር የሚበቃውን ቀለብ፣ ሳይበዛም ሳያንስም፣ እቆርጥልሃለሁ። ለክረምትና ለበጋ የሚሆን ልብስም እገዛልሃለሁ። እርሱ ሲነትብ ትመልሰውና በልዋጩ ሌላ ትወስዳለህ” አሉ። በየቀኑ ግማሽ ፍየል ወሰኑላቸው። ገላቸውን የሚሸፍኑበት እራፊ ጨርቅም ሰጧቸው!

በበጎ ነገሮች ሁሉ ቀዳሚ

አቡ ሁረይራ እንዳስትላለፉት ነቢዩ (ሶ.ዐ.ወ)፡- “ከናንተ ውስጥ ጾም ይዞ ያነጋ ማን ነው? በማለት ጠየቁ። አቡበክርም፡- ‘እኔ’ አሉ። ከናንተ ውስጥ ጀናዛን የሸኘ ማን ነው? ሲሉም ጠየቁ። አቡበክርም፡- ‘እኔ’ አሉ። ዛሬ ምስኪንን ያበላ ማን ነው? አሉም። አቡበክርም፡- ‘እኔ’ አሉ። በሽተኛ የጠየቀስ ማን ነው? ሲሉ፣ አቡበክር ‘እኔ’ አሉ። የአላህ መልእክተኛም፡- እነዚህ በጎ ድርጊቶች በአንድ ሰው ላይ አይሰባሰቡም፣ ያ ሰው ጀነት የገባ ቢሆን እንጅ አሉ።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

“ጅብሪል መጣና እጄን ይዞ ተከታዮቼ የሚገቡበትን የጀነት በር አሳየኝ። አሉ። አቡበክርም፡- ‘ከርስዎ ጋር ሆኜ ባየው እወድ ነበር’ አሏቸው። ነቢዩም፡- አቡበክር ሆይ! ከኡመቴ (ሕዝቦቼ) ውስጥ መጀመሪያ ጀነት የምትገባው አንተ ነህ አሏቸው።” (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)

የአላህ ፍራቻ እና ጥንቃቄ

አቡበክር አንድ ባሪያ ነበራቸው። ዘወትር ጠዋት እየወጣ ስራ በመስራት ገንዘብ ያገኛል። አንድ ቀን ምግብ ይዞ መጣ። አቡበክርም አንድ ጉራሽ ተመገቡለት። ባሪያውም በመሐይምነት ዘመን ለፈጸመው የጥንቆላ ተግባር ከተሰጠው ክፍያ ያገኘው ምግብ እንደሆነ ነገራቸው። አቡበክርም፡- “ልታጠፋኝ ተቃርበህ ነበር።” አሉና ጣታቸውን ወደ ጉሮሯቸው በመላክ እንዲያስመልሳቸው ሞከሩ። አልወጣ ብሎ አስቸገራቸው። “በውሃ እንጅ አይወጣም” ሲሏቸው በሳህን ውሃ እንዲቀርብላቸው አደረጉና እርሱን እየጠጡ የበሉትን ሁሉ አስመለሱ። “አላህ ይዘንልዎት። ለአንዲት ጉርሻ ይህን ያህል ራስዎን ያንገላታሉን?” ተባሉ። “ነፍሴ ከአካሌ ካልተነጠለች ይህች ጉርሻ የማትወጣ ቢሆንም እንኳ ነፍሴን ከማውጣት ወደኋላ አልልም። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‘በሐራም ምግብ የበቀለ ስጋ እሳት ለርሱ ይበልጥ የተገባ፣ ነው’ ሲሉ በመስማቴ በዚህ ጉርሻ አማካይነት ከአካሌ አንዳች ነገር እንዳይበቅል ስለፈራሁ ነው” አሉ። (በይሐቂ እንደዘገቡት አል ሒልያህ 2/31)

የአምላካቸውን ከለላነት መምረጣቸው

ቡኻሪ እንደዘገቡት ዓኢሻ (ረ.ዐ) የሚከተለውን ተናግረዋል፡-

“ወላጆቼ ሙስሊም ሆነው እንጅ አላውቃቸውም። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጠዋትና ማታ ከኛ ዘንድ የሚመጡ ሆነው እንጅ አንድም ቀን አላለፈም።”

ሙስሊሞች መካ ውስጥ እንግልት ሲበዛባቸው አቡበክር ወደ ሐበሻ ለመሰደድ መካን ጥለው ወጡ። “በርከል ገማድ” ከተባለ ቦታ ሲደርሱ ኢብን ዱግነህ አገኛቸው። የጎሣ አለቃ ነው። “የት እየሄድክ ነው?” ሲልም ጠየቃቸው። “ወገኖቼ ከሀገር አስወጡኝ፤ ሀገር ላገር እየተዘዋወርኩ አምላኬን ማምለክ እፈልጋለሁ” ሲሉ መለሱ። ኢብን ዱግነህም፡- “አቡበክር ሆይ! አንተን የመሰለ ሰው ሀገር ጥሎ አይወጣም። እንዲወጣም አይደረግም። አንተ ችግረኛን የምትረዳ፣ ዝምድናን የምትቀጥል፣ ችግርን የምትጋራ፣ እንግዳ የምታስተናግድ፣ ከባለመብት ጎን የምትቆም ሰው ነህ። ስለዚህ እኔ ከለላ እሆንሃለሁ። ተመለስና እዚያው ሀገርህ ውስጥ ጌታህን አምልክ” አላቸው። ወደ መካ ተመለሱ። ኢቢን ዱግነህም አብሯቸው ሄደ። ማታ ላይ የቁረይሽ ባላባቶችን በየቤታቸው እየዞረ፡- “አቡበክር ከሀገር የሚወጣ ወይም እንዲወጣ የሚደረግ ሰው አይደለም። ችግረኛን የሚታደግን፣ ዝምድናን የሚቀጥልን፣ ችግርን የሚጋራን፣ እንግዳ የሚንከባከብንና ከተበዳይ ጎን የሚቆምን ሰው ከሀገር ታስወጣላችሁን?” ሲል ወቀሳቸው። ቁረይሾች ለአቡበክር ከለላ መሆኑን ተቀበሉ። ግና እንዲህ ሲሉ አስጠነቀቁት፡-

“ለአቡበክር አምላክን ቤቱ ውስጥ ብቻ እንዲያመልክና እንዲሰግድ ንገረው። በቤቱ ውስጥ ያሻውን ነገር ያንብብ። እኛን እያወከን ግን፣ እነዚህን ነገሮች በይፋ ከፈጸመ ሴቶቻችንና ልጆቻችን እንዳይፈተኑ እንሰጋለን።” ኢብን ዱግነህ ለአቡበክር ይህንኑ ነገራቸው።

አቡበክር ጌታቸውን በቤታቸው ውስጥ ማምለካቸውን ቀጠሉ። ሶላት በይፋ አይሰግዱም፤ ቁርአንም ከቤታቸው ውጭ አይቀሩም። በኋላ ግን ከካዕባ ግቢ ውስጥ የመስገድ ሐሳብ መጣላቸው። ይህንኑ አደረጉ። ከርሱ ውስጥም መስገድና ቁርአን መቅራት ጀመሩ። የጣኦታውያን እንስቶችና ሕጻናትም በአግራሞት ይመለከቷቸው ጀመር። አቡበክር አልቃሽ ሰው ነበሩ። ቁርአን ሲቀሩ በለቅሶ ይንፈቀፈቃሉ። ይህ ድርጊታቸው የቁረይሽ ባላባቶችን አስደነገጠ። ለኢቢን ዱግነህም እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ፡-

“አቡበክር አምላኩን ከቤቱ ውጭ ላያመልክ ቃል አስገብተን ከለላ ትሆን ዘንድ ፈቅደን ነበር። እርሱ ግን ቃሉን ጥሶ በካዕባ ግቢ ውስጥ መስገድ እና መቅራት ጀምሯል። ሴቶቻችንና ልጆቻችን እንዲፈተኑ ስለማንሻ ከልክለው። ቤቱ ውስጥ ብቻ ማምለክ ከፈለገ ይችላል። አምልኮውን ይፋ ማድረግ የሚፈልግ ከሆነ ግን ከለላነትህን መልስለት፤ የሰጠንህን ቃል ማፍረስ አንሻም። በይፋ እንዲያመልክም አንፈቅድለትም።”

ዓኢሻ እንዳስተላለፉት ኢቢን ዱግነህ ወደ አቡበክር ዘንድ መጣና፡- “እኔና አንተ የተጋባነውን ቃል ታውቃለህ። ስለዚህም በቃልህ መሠረት ቤትህ ውስጥ ብቻ አምልክ፤ ካልሆነ ከለላነቴን መልስልኝ። ከለላዬ እንዲጣስና ዐረቦችም ይህን ጉድ እንዲሰሙ አልሻም” አለ። አቡበክርም፡- “ከለላነትህን መልሸልሃለሁ። ከእንግዲህ የአላህን ከለላነት ብቻ እሻለሁ።” አሉ።

ከአቡበክር ሌላ ይህን የጀግንነት አድራጎት ማን ሊፈጽም ይችላል። በዚህ ድንቅ አቋም ሊዋብ የሚችለው የአቡበክር ስብእና ብቻ ነው። በአላህ ላይ የነበራቸው እምነት ይህን ያህል ጽኑና ጠንካራ ነበር። የክህደት ሐይሎች ዙሪያውን ከበው ሊያጠፏቸው ባሰፈሰፉበት ወቅት አላህ ከየትኛውም ፍጡር የላቀ፣ ከለላው የሚከጀል፣ ተስፋ የሚጣልበት ብቸኛ ሐይል መሆኑን፣ አላህ የረዳውን የሚያሸንፈው እንደሌለ በጥልቅ ተረዱ።

በኸሊፋነት ዘመን

አቡበክር ኸሊፋ የሆኑት ሙስሊሞች በነብያቸው (ሰ.ዐ.ወ) ሞት ምክንያት ግራ በተጋቡበት አስፈሪ ወቅት ነው። በወቅቱ ከፊል ዐረቦች ከኢስላም አፈንግጠዋል። ሌሎች ከመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) በኋላ ለማንም ላለማደር ወስነዋል። ሮሞች ሂጃዝን ለመውረር በዝግጅት ላይ ናቸው። የሮሞችን ጥቃት ለመመለስ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ያዘጋጁት የኡሳማ ኢቢን ዘይድ (ረ.ዐ) ጦር ጉዞውን ለመቀጠል ከመዲና አፋፍ ላይ ሆኖ ትእዛዝ ይጠባበቃል። በዚህ ሁሉ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ኸሊፋ የተደረጉት አቡበክር ሐላፊነታቸውን በሚገባ ተወጡ።

አፈንጋጮችን (አል-ሙርተዲን) አደብ (ሥርዓት) ለማስያዝ ቆራጥ ውሳኔ ወሰኑ። ሌሎች ሶሐቦች የጦርነቱን ሐሳብ ባይደግፉም እርሳቸው ግን በዚሁ ሐሳባቸው ጸኑ። በኋላ ላይ ግን ሶሐቦች የርሳቸውን ሐሳብ ደገፉ። በአላህ በረከትም እስልምናን በዐረቢያ ውስጥ እንደ አዲስ ለማጽናት ተመሙ። አላህ የለገሳቸው ድል ታላቅ ነበር። የአመጽ እንቅስቃሴውን በእንጭጩ ቀጩት። የኡሳማንም ጦር የአላህ መልእክተኛ ወዳሰማሩት ግንባር አዘመቱ። ይህ ጦር እስልምናን ለማስፋፋትና ሕዝቦችን ነጻ ለማውጣት የተገኙ ድሎች ሁሉ መነሻ ሆነ። የአስተዳደር ፖሊሲያቸው ኸሊፋ በተደረጉ ጊዜ ያሰሙት ተከታዩ ታሪካዊ ንግግር ነበር፡-

إنى قد وليت عليكم ولست بخيركم ، فإن أحسنت فأعينوني ، وإن أسأت فقوموني ، الصدق أمانة والكذب خيانة ، والضعيف فيكم قوى عندى حتى آخذ له الحق ، والقوى فيكم ضعيف عندى حتى آخذ الحق منه ، لا يدع قوماً الجهاد فى سبيل الله إلا ضربهم الله عز وجل بالذل ، ولا تشيع الفاحشة فى قوم قط إلا عمهم الله بالبلاء ، أطيعوني ما أطعت الله ورسوله ، فإذا عصيت الله ورسوله فلا طاعة لى عليكم

“እኔ በናንተ ላይ ተሹሚያለሁ። ይህ ማለት ግን ከናንተ ብልጫ አለኝ ማለት አይደለም፤ በጎ ከሰራሁ አግዙኝ። ክፉ ከሰራሁ አስተካክሉኝ። እውነት መናገር አደራን መጠበቅ ሲሆን፣ መዋሸት ደግሞ ክህደት ነው። ከናንተ መካከል ደካማው መብቱን እስካሟላለት ድረስ ከኔ ዘንድ ጠንካራ ነው። ከናንተ ዘንድ ጠንካራው ግዴታውን እንዲወጣ እስካደርገው ድረስ ከኔ ዘንድ ደካማ ነው። ሰዎች በአላህ መንገድ መፋለምን ሲተው አላህ ውርደትን ያከናንባቸዋል። በአንድ ሕዝብ ውስጥ ዝሙት ከተስፋፋ አላህ ሁሉንም በቅጣቱ ያጠቃልላቸዋል። አላህንና መልእክተኛውን እስከታዘዝኩ ድረስ ታዘዙኝ። የአላህን እና የመልእክተኛውን ፈቃድ ስጥስ ግን ልትታዘዙኝ አይገባም።”

አቡበክር የአስተዋይ ልቦና፣ የሩቅ አሳቢ አእምሮ ባለቤት ነበሩ። በዘመናቸው ያሉ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ከማየት፣ በጥልቀት ከማስተዋል የመነጨ ንግግራቸው የልብ ብርታትን፣ ፍጹም መተማመንና ጽኑነትን የተላበሰ ነው።

የኸሊፋነት ዘመናቸው ጥቂት ቢሆኑም እጅግ አስደናቂና ታላላቅ በሆኑ ስኬቶች የተሞሉ ናቸው። የአቡበክር ብልህነት በበርካታ አጋጣሚዎች ተስተውሏል። በተለይም እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች። ታላቅ ሰው ታላላቅ አቋሞችን ያስመዘግባል።

ቁርኣንን የመሰብሰብ ድንቅ ተግባር

በየማማህ ጦርነት ወቅት በርካታ የቁርአን አዋቂዎች የመገደላቸውን ዜና አቡበክር በሰሙ ጊዜ ዑመር አብረዋቸው ነበሩ። በዚህ ጦርነት በርካታ የቁርአን አዋቂዎች ተገድለዋል። “በሌሎች ጦርነቶችም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሮ አዋቂዎቻችን እንዳያልቁ እሰጋለሁ። ስለዚህም በነቢዩ ዘመን የተጻፉ የቁርኣን ጽሑፎች እንዲሰበሰቡ ብታደርግ መልካም ይመስለኛል” አሉ።

አቡበክርም፡- “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ያላደረጉትን ነገር እንዴት እኔ አደርገዋለሁ?” ሲሉ ጠየቁ። ዑመርም፡- “በአላህ እምላለሁ! ይህን ብታደርግ መልካም ነው” አሉ። ዑመር አቡበክርን ደጋግመው ጎተጎቱ። በመጨረሻም አቡበክር በሐሳቡ ተስማሙ። ዘይድ እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡- አቡበክር እንዲህ አሉኝ፡-

“አንተ አስተዋይ ወጣት ነህ። በመጥፎ ነገር አንጠረጥርህም። ለአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ቁርኣን ሲወርድላቸው እየተከታተልክ ትጽፍ ነበር። ስለዚህም የተጻፉ የቁርኣን መልእክቶችን በአንድ አሰባስብ” አሉኝ። በአላህ እምላለሁ! ይህን ሐላፊነት ከሚያሸክሙኝ ተራራ እንድገፋ ቢያዙኝ እመርጥ ነበር። “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ያላደረጉትን እንዴት እናንተ ታደርጋላችሁ?” አልኳቸው። አቡበክርም “በአላህ እምላለሁ! በጎ ነገር ይመስለኛል” አሉኝ። ደጋግመውም ጎተጎቱኝ። በመጨረሻ በሐሳባቸው ተስማማሁ። በተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ ተጽፎ የነበረውን ቁርአን ከያለበት ተከታትዬ ሰበሰብኩት። የአት-ተውባህን የመጨረሻ አናቅጽም ከኹዘይማህ ቢን ሳቢት ዘንድ አገኘሁት።

لَقَدْ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مِّنْ أَنفُسِكُمْ عَزِيزٌ عَلَيْهِ مَا عَنِتُّمْ حَرِيصٌ عَلَيْكُم بِالْمُؤْمِنِينَ رَءُوفٌ رَّحِيمٌ فَإِن تَوَلَّوْا فَقُلْ حَسْبِيَ اللَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ عَلَيْهِ تَوَكَّلْتُ وَهُوَ رَبُّ الْعَرْشِ الْعَظِيمِ

“ከጎሳችሁ የሆነ ችግራችሁ በእርሱ ላይ ጽኑ የሆነ፣ በእናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን (ላይ) ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ ቢያፈገፍጉም አላህ በቂዬ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ በእርሱ ላይ ተጠጋሁ እርሱም የታላቁ ዐርሽ ጌታ ነው በላቸው፡፡” (አል-ተውባህ 9፤ 128-129) (ሐዲስ ሐሰኑን ሶሂህ)

ዘመን ተሻጋሪ መልእክቶቻቸው

أيها الناس: إن كثر أعداؤكم،وقل عددكم، ركب الشيطان منكم هذا المركب؟ والله ليظهرن هذا الدين على الأديان كلها، ولو كره المشركون، قوله الحق، ووعده الصدق  بَلْ نَقْذِفُ بِالْحَقِّ عَلَى الْبَاطِلِ فَيَدْمَغُهُ فَإِذَا هُوَ زَاهِقٌ وَلَكُمُ الْوَيْلُ مِمَّا تَصِفُونَ ٢١:١٨

“ሰዎች ሆይ! በአላህ እምላለሁ! ጠላቶቻችሁ ቢበዙ፣ ወዳጆቻችሁ ቢያንሱና ሰይጣን በሙሉ ኃይሉ ቢዘምትባችሁም እንኳ አላህ ይህን ሐይማኖት የሐይማኖቶች ሁሉ የበላይ ያደርገዋል። ጣኦታውያን ይህን ቢጠሉም። ንግግሩ እውነት፣ ቃል ኪዳኑም የማይታበል ነው።”

“በእርግጥ እውነትን በውሸት ላይ እንጥላለን፡፡ አንጎሉን ያፈርሰዋልም፡፡ ወዲያውም እርሱ ጠፊ ነው፡፡ ለእናንተም ከዚያ (ሚስትና ልጅ አለው በማለት) ከምትመጥኑት ነገር ብርቱ ቅጣት አላችሁ፤ (ወዮላችሁ)፡፡” (አል-አንቢያእ 21፤ 18)

أيها الناس: إني أوصيكم بتقوى الله العظيم في كل أمر، وعلى كل حال، ولزوم الحق فيما أحببتم وكرهتم؛ فإنه ليس فيما دون الصدق من الحديث خير، من يكذب يفجر، ومن يفجر يهلك، وإياكم والفخر، وما فخر من خلق من التراب وإلى التراب يعود؟!

“ሰዎች ሆይ! የተላቀውን አላህን በሁሉም ጉዳዮችና ሁኔታዎች እንድትፈሩት፣ በምትወዱትም በምትጠሉትም ሁኔታ ሐቅን አጥብቃችሁ እንድትይዙ እመክራችኋለሁ። ከእውነት የበለጠ በጎ ወሬ የለም። የዋሸ ወነጀለ። የወነጀለ ጠፋ። ኩራትን አደራ ተጠንቀቁ። ከአፈር ተፈጠሮ ወደ አፈር የሚመለስ ሊኮራ አይገባውም።”

أإلا إن لكل أمر جوامع، فمن بلغها فهي حسبه، ومن عمل لله كفاه الله. عليكم بالجد والقصد، فإن القصد أبلغ. إلا أنه لا دين لأحد لا إيمان له، ولا أجر لمن لا حسبة له، ولا عمل لمن لا نية له، ألا وإن في كتاب الله من الثواب عل الجهاد في سبيل الله لما ينبغي للمسلم أن يحب أن يخص به. هي التجارة التي دل الله عليها، ونجى بها من الخزي ، وألحق بها الكرامة في الدنيا والآخرة

“አዋጅ! እያንዳንዱ ጉዳይ መቋጠሪያ ውል አለው። እርሱን ያገኘ በቂው ነው። ለአላህ የሰራ አላህ ይበቃዋል። ብርቱና ቆጣቢዎች ሁኑ። ቁጠባ እጅግ ጠቃሚ ባህሪ ነው። እነሆ፣ ራሱን የማይቆጣጠር ሰው ዲንም ኢማንም የለውም።፡ ኒይያ የሌለው ስራ የለውም። አዋጅ! በአላህ መጽሐፍ ውስጥ የጅሃድን ምንዳ የሚከር መልእክት አለ። ሙስሊም በዚህ እድል ብቸኛ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል። ጅሃድ አላህ ያመላከተው ንግድ ነው። በርሱ አማካይነት ሰዎችን ከኪሣራ ይታደጋል። በዚህችም በመጭውም ዓለም ክብር ያጎናጽፋቸዋል።”

የኸሊፋው ኹጥባ

“አላህን እንድትፈሩ፣ ተገቢውን ውዳሴ እንድታደርሱለት፣ ፍርሃትን ከጉጉት እድታጣምሩ፣ አጥብቃችሁና አዘውትራችሁ እንድትለምኑት እመክራችኋለሁ። አላህ ዘከሪያንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲህ ሲል አወድሷል፡-

إِنَّهُمْ كَانُوا يُسَارِعُونَ فِي الْخَيْرَاتِ وَيَدْعُونَنَا رَغَبًا وَرَهَبًا وَكَانُوا لَنَا خَاشِعِينَ

“እነርሱ በበጎ ሥራዎች የሚቻኮሉ ከጃዮችና ፈሪዎች ኾነው የሚለምኑንም ነበሩ፡፡ ለእኛ ተዋራጆችም ነበሩ፡፡” (አል-አንቢያእ 21፤ 90)

የአላህ ባሮች ሆይ! አላህ ነፍሳችሁን መዋሱን እወቁ። ከናንተ ቃል ኪዳን ተቀብሏል። ጠፊና ጥቂት የሆነውን ዘልዓለማዊና ብዙ በሆነው ገዝቷችኋል። እነሆ፣ የአላህ መጽሐፍ ማስደመሙ አያልቅም። ብርሃኑም አይከስምም። ስለዚህም መልእክቱን አምናችሁ ተቀበሉ። በምክሩም ተጠቀሙ። ለጽልመታማው ቀን ብርሃን አድርጉት። አላህ የፈጠራችሁ ለአምልኮ ነው። ስራችሁን ይመዘግቡ ዘንድም የተላቁ የመላእከት ጸሐፊዎችን በናንተ ላይ ወክሏል።፡ የምትሰሩትን ሁሉ ያውቃሉ። የአላህ ባሮች ሆይ! ለናንተ የተሰወረው የምትሞቱበት ቅጽበት ካጠገባችሁ ሆኖ ታነጋላችሁ፣ ታመሻላችሁ። ለአላህ በሆነ ስራ ላይ ሆናችሁ ሞት እንዲወስዳችሁ ማድረግ የምትችሉ ከሆነ ይህንኑ አድርጉ። በአላህ እገዛ ብቻ እንጅ ይህን ማድረግ አትችሉም። እድሚያችሁ አልቆ ወደ ክፉ ስራችሁ ከመመለሳችሁ በፊት በበጎ ስራ ተሽቀዳደሙ። ከሰዎች መሐል ራሳቸውን ረስተው እድሜያቸውን ለሌላ የሰጡ ይገኛሉ። እንደነርሱ እንዳትሆኑ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ እባካችሁን ፍጠኑ፣ በጣም ፍጠኑ። ከኋላችሁ ፈጣን አባራሪ (ሞት) እያሳደዳችሁ ነው። ቅጣቱም ፈጣን ነው።” (አልሁልየህ 1/35)

በጎ ነገር አላህን በመታዘዝ ብቻ

“አላህ በጎ ነገርን እንዲሁ እንዲሰጥ፣ ከክፉም እንዲሁ እንዲከላከል የሚያስገድደው የዝምድና ትስስር ስለሌለው ይህ እድል የሚገኘው እርሱን በመገዛት እና ትእዛዙን በመፈጸም ብቻ ነው። ከበስተኋላው ጀሃነምን የሚያስከትል መልካም ነገር መልካም አይደለም። ጀነትን የሚያስከትል መጥፎ ነገርም መጥፎ አይደለም።” (አልሁልየህ 1/36)

ለምትካቸው ያስተላለፉት ኑዛዜ

አቡበክር ከሞት አፋፍ ላይ በሆኑ ጊዜ ዑመርን ጠሩና እንዲህ ሲሉ መከሯቸው፡-

“ዑመር ሆይ! አላህን ፍራ። አላህ በቀን ካልሆነ በሌሊት የማይቀበለው ስራ አለው። ፈርድን እስክትወጣ ድረስ ሱናን አይቀበልም። በእለተ ቂያማ ሚዛናቸው የሚከብድላቸው ሰዎች ይህን እድል ያገኙት በዚህች ዓለም ሐቅን በመከተላቸው ነው። ሐቅ የስራ ሚዛናቸውን አከበደው። ነገ ሐቅ የሚቀመጥበት ሚዛን ሊከብድ ተገባው። በእለተ ቂያማ ሚዛናቸው የሚቀልባቸው ሰዎች ይህ የሆነባቸው በዚህች ዓለም ሐሰትን በመከተላቸው ነው። ሐሰት ስራቸውን አቀለለው። ነገ ሐሰት የሚቀመጥበት ሚዛን ሊቀል ተገባው። አላህ የጀነት ሰዎችን ሲያወሳ ከስራዎቻቸው መካከል ይበልጥ መልካሙን አወሳ። ግድፈቶቻቸውንም አለፈ። እነርሱን ሳስታውስ፡- ‘ከነርሱ ሳልሆን እንዳልቀር’ የሚል ስጋት ያድርብኛል። የእሳት ሰዎችን ሲያወሳም ከስራዎቻቸው መሐል ይበልጥ ክፉውን አብሮ አወሳ። ጥሩውን ስራቸውን መለሰባቸው። እነዚህንም ሳሰታውስ፡- ‘ከነርሱ እንደማልሆን ተስፋ አደርጋለሁ’ እላለሁ። በፍርሃትና በተስፋ መሐል መሆን ተገቢ ነው፤ በአላህ ላይ መመጻደቅም ከእዝነቱ ተስፋ መቁረጥም ተገቢ አይደለም። ይህን ምክሬን ከሰራህበት ወዳንተ መምጣቱ አይቀሬ ከሆነው ሞት ይበልጥ ተወዳጅ ሩቅ እንግዳ አይኑርህ። ካልሰራህበት ደግሞ ከሞት ይበልጥ የምትጠላው ሩቅ እንግዳ አይኑርህ።” (አልሁልየህ 1/36)

በጸጋ መሸንገል

የአማኞች እናት ዓኢሻ (ረ.ዐ) አዲስ ልብስ ለበሰች። ወደርሱ እያየችም ተኩራራች። አቡበክርም፡- “ምን እያየሽ ነው? አላህ ወዳንቺ እያየ አይደለም” አሏት። “ለምን?” አለቻቸው። “አንድ ሰው በዓለማዊ ጌጥ ምክንያት ኩራት ወደቀልቡ ከገባ ያን ጌጥ እስኪተወው ድረስ አላህ ይጠላዋል።” ዓኢሻ ልብሷን ወዲያውኑ አወለቀች። መጸወተችውም። አቡበክርም፡- “ምን አልባት ይህ ድርጊትሽ ወንጀልሽን ያብስልሽ ይሆናል” አሉ። (አልሁልየህ 1/37)

የአላህን ጸጋ በመግለጽና በርሱ በመኮፈስ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ተገቢ ነው። የአላህን ጸጋ መግለጽ በቁርአንና በሐዲስ እንደተነገረው ለርሱ ችሮታ እውቅና መስጠትና ማጽደቅ ሲሆን፣ መኮፈስ ደግሞ ሐቅን ወደ መተው፣ ጸጋን ወደ መካድና በሰዎች ላይ ወደ መኩራት የሚያደርስ ድርጊት ነው።

አቡበክር ሲሞቱ ሐብት ንብረት አልተውም። ለሐላፊነታቸው ከሚሰጣቸው ጥቂት ገንዘብ በላይም ከሙስሊሞች ንብረት አልወሰዱም። የሚገርመው ባለቤታቸው ጣፋጭ ነገር መግዛት ፈልጋ ገንዘብ አጣች። “ከቀለባችን እየቀናነስኩና እየቆጠብኩ አጠራቅሜ ልግዛ” በማለት ወሰነች። ከቀለባቸው ቆጥባም ጣፋጭ የሚያስገዛትን ገንዘብ አጠራቀመች። አቡበክር ይህን ድርጊቷን ሲሰሙ፡- “ከሙሰሊሞች በይተል ማል ከሚያስፈልገን በላይ እየወሰድን ነበር ማለት ነው።” አሉና ባለቤታቸው ቆጥባ ታስቀምጠው የነበረውን ያህል ገንዘብ ከደሞዛቸው ቀነሱ።

አቡበክር በአስራ አራተኛው አመተ ሂጅራ በወርሃ ጀማዱል አኺር 11ኛ ቀን ሰኞ ቀን ይህችን ዓለም በሞት ተሰናበቱ። አላህ ይዘንላቸው። ከርሳቸውና ከልጆቻቸው፣ እንዲሁም የሰው ልጆች ፈርጥ ከሆኑት ከነቢዩ ሙሐመድ፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከባልደረቦቻቸው ጋር በዘልዓለማዊው ሐገር ውስጥ ያገናኘን።

*****

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here