ኢስላም – የዓለማችን ታላቁ ሥልጣኔ

0
4665

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَكَذَٰلِكَ جَعَلْنَاكُمْ أُمَّةً وَسَطًا لِّتَكُونُوا شُهَدَاءَ عَلَى النَّاسِ وَيَكُونَ الرَّسُولُ عَلَيْكُمْ شَهِيدًا

“እንደዚሁም ( እንደመራናችሁ) በሰዎች ላይ መስካሪዎች ልትሆኑና መልእክተኛውም በናንተ ላይ መስካሪ ይሆን ዘንድ ሚዛናዊ ህዝቦች አደረግናችሁ።”(ቁርኣን 2፡143)

የኢስላማዊ ሥልጣኔ ዋና ዋና ባህሪያት

ኢስላም የዓለማችን ሃይማኖት እንዲሆንና አንዱን ጫፍ ከሌላኛው የዓለማችን ጫፍ የሚያገናኝ ታላቅ ሥልጣኔን ይፈጥር ዘንድ ነው ትልቁ ዓላማው። በመሆኑም ገና በመጀመሪያዎቹ የሙስሊም ከሊፋዎች (የነቢዩ ተተኪዎች) ዘመን መጀመሪያ ዐረቦች ቀጥሎም ፐርሺያዎች ኋላ ላይ ደግሞ ቱርኮች ድንቅ የሆነ ኢስላማዊ ሥልጣኔ ለማስቀመጥ ተንቀሣቅሰዋል። በ13ኛው ክፍለዘመን ደግሞ አፍሪካና ህንድ ትልቅ የኢስላማዊ ሥልጣኔ ማዕከል ለመሆን የበቁ ሲሆን ብዙም ሣይቆይ ደግሞ ኢስላማዊ መንግስታት በማሌዤያና ኢንዲኔዠያ አካባቢ ሊመሠረቱ ችለዋል። የቻይና ሙስሊሞችም እንዲሁ በመላዋ ቻይና ተበትነው የእስልምናን ስልጣኔ አስተዋውቀዋል።

ኢስላም የጎሣ መደቡ አሊያም ዘሩ ከየትኛውም ወገን ይሁን የሁሉም የዓለም ህዝቦች ሁሉ ሃይማኖት ነው። ለዚህም ነው ኢስላማዊ ሥልጣኔ ዘረኝነትን ወይንም የጎሣ ልዩነትን በሚፃረር መልኩ ፍጹም አንድነት ላይ መሠረቱን ያደረገው። እነኚህ ዋና ዋና የሚባሉ የዘርና የጎሣ መደቦች ከዐረብ፣ ከፐርሺያ (ኢራንና ከፊል ኢራቅ)፣ ከቱርክ፣ ከአፍሪካ፣ ከህንድ፣ ከቻይና እና ከማሌዠያ እንዲሁም ከሌሎች እስልምናን ከተቀበሉና ኢስላማዊ ሥልጣኔን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉ ትናንሽ የጎሣ ክፍሎች ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ኢስላም ከሌሎች ቀደምት ሥልጣኔዎች እውቀታቸውን፣ ሣይንሣቸውን፣ ትምህርታቸውን፣ ባህላቸውንና ሌሎች ጠቃሚ ነገሮችን ወደራሱ ዓለም አመለካከት ማስገባትን አይቃወምም። አመለካከቶቹ የኢስላምን መሠረታዊ ህግጋት እስካልተፃረሩ ድረስ። እያንዳንዱ ኢስላምን የተቀበለ ጎሣ ወይንም ብሄር ለዚያ ለሚገኝበት ኢስላማዊ ሥልጣኔ የራሱ አስተዋጽኦ አለው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢስላማዊ ወንድማማችነትና የእህትማማችነት ፅንሰ ሀሣብ በአንድ ጎሣ፣ ዘር፣ ቋንቋና አካባቢ ከመተሣሠር በባለፈ ትልቅ ትርጉም አለው። እነኚህ ሁሉ ነገሮች ዓለማቀፍ የሆነው የኢስላማዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት አካል ናቸውና።

በኢስላም የተፈጠረው ዓለማቀፋዊ ሥልጣኔ የሰው ልጆች በጎሣና በዘር ቢለያዩም የተለያዩ ጥበቦችንና እውቀቶችን አብረው እንዲሠሩና እንዲያመርቱ ያበረታታል። ምንም እንኳ ለሥልጣኔው መጎልበት ትልቁ ድርሻ የእስልምናና የሙስሊሞች ቢሆንም ሙስሊም ያልሆኑ ማህበረሰቦች በተለይም “የመጽሃፉ ባልተቤቶች (አይሁዶችና ክርስቲያኖች)” ፍሬው ለያንዳንዱ ሰው በደረሰው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ላይ የነቃ ተሣትፎ ነበራቸው። ዛሬ በአሜሪካ የሚታየው ሣይንሣዊ ድባብ ቀደም ባለው ጊዜ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ሣይንቲስት ወንድና ሴቶች አንድ ላይ በሚማሩበት ወቅት እያንዳንዳቸው ለእውቀት ማደግ ጉልህ ተሣትፎ ያደረጉበትን ጊዜ ያስታውሰናል።

የኢስላም ምንጭ የሆነው ዓላማቀፉ ሥልጣኔ ወደክልሉ የገቡትን ሰዎች አዕምሮ በማነቃቃትና ለምርምር በመጋበዝ ረገድም እጅግ የተሣካ ሥራ ሠርቷል ማለት ይቻላል። ይህም በመሆኑ በአንድ ወቅት ዘላን የነበሩ ዐረቦች የሳይንሱንና የእውቀቱን ዓለም እስከመምራት የደረሱበት ሁኔታ ነበር። ከእስልምና በፊት ትልቅ ሥልጣኔ የነበራቸው ፐርሺያኖች በእስልምና ዘመን በበለጠ መልኩ የሣይንስ እውቀትን ለዓለም አበርክተዋል። ስለ ቱርኮችም ሆነ ስለ ሌሎች እስልምናን የተቀበሉ ክፍሎች ይህንኑ ማለት ይቻላል። የእስልምና ሃይማኖት የተለያዩ ጎሣና መደብ የሆኑ የሰው ልጆች የተሣተፉበትን ዓለማቀፋዊውን ሥልጣኔ በመፍጠሩ ብቻ ሣይሆን እውቀትንና ባህላዊ ህይወትን ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ በማሣደጉ በኩልም ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ለ800 አመታት ያህል ዐረብኛ የአለማችን ዋና የትምህርትና የሳይንሣዊ ቋንቋ እውቀት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። የእስልምናን መሰበክ ተከትለው በመጡ የመጀመሪያዎቹ ክፍለ ዘመናት የሙስሊሙን ዓለም የተለያየ ክፍል ይገዙ ነበሩ ትናንሽ ስርወ መንግስታት ለኢስላማዊው ባህል አስተሣሰብ ማበብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው። በርግጥ ይህ ልምድና የዘመነ እንቅስቃሴ በያዝነው ክፍለዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሙስሊሞች እምነት መዳከምና በውጭ ተፅእኖ የተነሣ ተዳፍኖ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በሙስሊሙ ዓለም የተለያዩ አካባቢዎች እንደ አዲስ በማንሠራራቱ ሙስሊሞች የራሣቸው የሆነ የፖለቲካ ነጻነት እስከ መመለስ የበቁበት ሁኔታ ይታያል።

የእስልምና ታሪክ መጠነኛ ዳሠሣ

  • ኹለፋኡ ራሽዲን ( ከነቢዩ ሞት በኋላ የተተኩ ወደ ቀጥተኛው ጎዳና የሚመሩ ተተኪዎች )

የነቢዩን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሞት ተከትሎ የነቢዩ የቅርብ ወዳጅና ከአዋቂ ወንዶች ኢስላምን ለመቀበል የመጀመሪያው የነበሩት አቡበክር ረዲየሏሁ ዐንሁ ከሊፋ ( የሣቸው ተተኪ ) ሆኑ። እርሣቸውም ለሁለት አመታት ካስተዳደሩ በኋላ ዑመር ረዲየሏሁ ዐንሁ በእግራቸው ተተኩ። ዑመርም ለ10 አመታት ያህል ህዝበ ሙስሊሙን ያስተዳደሩ ሲሆን በርሣቸው ዘመን እስልምና የፐርሺያን ( የዛሬዋን ኢራንና ከፊል ዒራቅን እስከ ፓኪስታን ) ግዛት አልፎ ሶሪያና ግብፅን አጠቃሎ ከምስራቅ እስከ ምእራብ የዓለም ዳርቻዎች ሊስፋፋ ችሏል። ኢየሩሣሌም የደረሰውን የሙስሊሙን ጦር በእግር የመሩትና የክርስቲያኖች ቦታዎችና ይዞታዎች ለጥቃት እንዳይጋለጡ ያዘዙትም እርሣቸው ነበሩ። የመጀመሪያውን የህዝብ ግምጃ ቤት ለሙስሊሙ ዓለም ያስተዋወቁ ሲሆን ዘመናዊውን የፋይናንስ ሥርኣት አስተዳደር ዘርግተዋል። ከዚህም ባለፈ ለኢስላማዊው መንግስት ግብአት ሆነው ለሚያገለግሉ በርካታ ወሣኝ ነገሮች መሠረት ጥለዋል።

በዑመር የተተኩት ዑስማን ረዲየሏሁ ዐንሁ ነበሩ። እርሣቸውም ለ12 አመታት ያህል ህዝበ ሙስሊሙን ያስተዳደሩ ሲሆን በርሣቸውም ዘመን ኢስላም መስፋፋቱን አላቆመም ነበር። ዑስማን የቅዱስ ቁርኣንን ዋና ቅጂ ወደ አራቱም የዓለም ማእዘናት በመላክም ይታወቀሉ። እርሣቸውን የተኩት አራተኛው ኸሊፋ ዓሊ ረዲየሏሁ ዐንሁ ነበሩ። ዓሊ ኢብኑ አቢጧሊብ ልብ በሚነኩ ምክሮቻቸውና መልእክቶቻቸው እንዲሁም በጀግንነታቸው ዛሬም ድረስ ይታወቃሉ። በርሣቸውም ሞት በሙስሊሙ ልብ ውስጥ ትልቅ ክብርና ቦታ የነበረው የኩለፋኡ ራሽዲን ዘመን ሊያበቃ ችሏል።

  • ኸሊፋዎች    

በ661 የተመሠረተው የኦማያድ /ኡመያውያን/ ሥርወ መንግሥት የአንድ ምእተ አመት ያህል እድሜ ነበረው። በዚህን ጊዜ ዳማስቆ ከምእራብ ቻይና እስከ ደቡባዊ ፈረንሣይ ድረስ ተንሠራፍቶ ለነበረው የሙስሊሙ ዓለም ግዛቶች ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች። በዚህ ዘመን የሙስሊሞች ግዛት ከሰሜን አፍሪካ እስከ ስፔን ድረስ የዘለቀ ሲሆን በምእራብ በኩል እስከ ፈረንሣይ በመካከለኛው ኢስያ ደግሞ እስከ ሲንድና በምሥራቅ እስከ ትራኖክሲያና ሊስፋፋ ከመቻሉም በላይ መሠረታዊ የሆኑ ማህበራዊና ህጋዊ አገልግሎት የሚሠጡ ድርጅቶችም ሊመሠረቱ ችለዋል።

የኡመያውያኑን ዘመን መውደቅ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው የአባሲድ (አባሳውያን) ሥርወ መንግስት ዋና መቀመጫውን ወደ ባግዳድ ያዛወረ ሲሆን ባግዳድም በዘመኑ ወደር የማይገኝላት የትምህርትና የባህል ማእከል እንዲሁም ለሰፊው ሙስሊሙ ዓለም የአስተዳደርና የፖለቲካ ልብ ሆና አገልግላለች።

አባሳውያን ለ500 አመታት ያህል ያስተዳደሩ ሲሆን ኋላ ላይ ቀስ በቀስ ሀይላቸው ተዳክሞ በቅጡ የታጠቀ ወታደራዊ ሀይል ባላቸው የተለያዩ ሱልጣኖችና ልኡላውያን ላይ ሥልጣን ያላቸው በመምሰል ለምልክት ብቻ የቀሩ መሪዎች እስከመሆን ደርሰው ነበር። በመጨረሻም የአባሲድ ሥርወ መንግስት ሁላጉ የሚባል የሞንጎላውያን መሪ በ1258 ባግዳድን ሲይዝ ከናካቴው ሊወድቅ ችሏል። በወቅቱ ሞንጎሎቹ ትልቁን ቤተመፃህፍት ጨምሮ ከተማዋን በከፍተኛ ሁኔታ አውድመው ነበር።

አባሣውያን ባግዳድን ያስተዳድሩ በነበረበት ዘመን በርካታ ጠንካራ ሥርወ መንግስታትንም የመሠረቱበት ሁኔታ ነበር። ከነዚህም ወስጥ ፋጢማውያን፣ አዩባውያን፣ እና መምሉኮች የሚባሉት በግብጽ በሶሪያና በፍልስጤም ከፍተኛ ሀይል ነበራቸው። የሙስሊሙንና የምእራቡን ዓለም ግንኙነት አስመልክቶ በዚሁ ዘመን ትልቅ ክስተት የነበረው በጳጳሱ የታወጀውና በበርካታ የአውሮፓ ነገስታት ድጋፍ ያገኘው ተከታታይ የመስቀል ጦርነት ነበር። ምንም እንኳ ምክኒያቱ ፖለቲካዊ ቢመስልም ያነጣጠረው ግን ቅዱሣን መሬቶችን በተለይ ኢየሩሣሌምን (ቁድስን) መልሶ በክርስቲያኖች እጅ ለማስገባት ነበር። በዚህም ክርሲቲያኖቹ አውሮፓውያን በመጀመሪያ አካባቢ የተወሰነ ድል ያገኙ ሲሆን የሶሪያንና የፍልስጤም ከፊል ግዛቶችን ለመቆጣጠር ችለው ነበር። በመጨረሻ ግን በታዋቂው ጀግና ሰላሃዲን አልአዩቢ በሚመራው ጦር በ1187 መስቀል ጦረኞቹን በማሸነፉ ኢየሩሣሌም እንደገና በሙስሊሞች እጅ ልትገባ ችላለች።

ከዐረብኛ የተወሠዱ አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቃላት

እንግሊዝኛ    

ዐረብኛ

አድሚራል (ADMIRAL)

አሚረል- ረህል

አዶቤ (ADOBE)

አልቱብ

አልኬሚ (ALCHEMY)

አልኪሚያ

አልኮቭ (ALCOVE)

አልቁባ

አለምቢክ (ALEMBIC)

አለንቢቅ

አልጀብራ (ALGEBRA)

አል ጃቢር

አምበር (AMBER)

አምበር

አሙሌት (AMULET)

ሃማኢል

አንቲሞኒ (ANTIMONY)

ኢትሚድ

አረቲቾክ (ARTICHOKE)

አልከርሹፍ

አትላስ (ATLAS)

አትላስ

አዚሙት (AZIMUTH)

አል ሱት

ባናና( BANANA)

ባናና

ባሮቅ (BAROQUE)

ቡርቃ

ኬብል (CABLE)

ሀብል

ካሜል (CAMEL)

ጀመል

ቼክሜት (CHECKMATE)

ሻህማት

ኮፊ (COFFEE)

ገህዋ

ኮተን (COTTON)

ኩትን

ጊራፌ (GIRAFFE)

ዘራፋ

ጃስሚን (JASMINE)

ያስሚን

ሌመን (LEMON)

ሌሙን

ሉት (LUTE)

አል ኡድ

መጋዚን (MAGAZINE)

መካዚን

ማስክ (MASK)

ማሰካራ

ሞንሱን (MONSOON)

መዋሲም

ሙስክ (MUSK)

ሙስክ

ናዲር (NADIR)

ናዚር

ኦሬንጅ (ORANGE)

ናራንጅ

ራይስ (RICE)

ሩዝ

ሳፋሪ (SAFARI)

ሳፋራ

ሳፈሮን (SAFFRON)

ዘዕፋራን

ሳንዳልውድ (SANDALWOOD)

ሰንደል

ሶፋ (SOFA)

ሱፋ

ሹገር (SUGAR)

ሱከር

ሺረፕ (SYRUP)

ሸራብ/ ሹርባ

ታምቡር (TAMBOUR)

ታቡራክ

ተራውባዱር (TROUBADOUR)

ተራብ

ዜሮ (ZERO)

ሲፍር

ዚረኮን (ZIRCON)

አዝረቅ

  • ሰሜን አፍሪካና ስፔን

አባሲዶች ደማስቆን ሲይዙ ከኦማያድ ሥርወ መንግስት የሆነ አንድ ልዑል ተለዋጭ የኦማያድ አገዛዝ ለመመስረት ብሎ ረጅም ጉዞ በማድረግ ከደማስቆ ወደ ስፔን ሸሽቶ ነበር። ይህም ክስተት በስፔን ወርቃማው የኢስላም ዘመን እንዲጀመር ምክኒያት ሆነ። ኮርዶቫ በዋና ከተማነት የተመረጠች ስትሆን ኋላ ላይም በህዝብ ብዛት ብቻ ሣይሆን የባህልና የዘመናዊ ትምህርት ማእከል በመሆንም ጭምር የአውሮፓ ትልቋ ከተማ እስከመሆን ደርሣ ነበር። ኡመያውያን ስፔንን ለሁለት ምእተ አመታት ያህል ያስተዳደሩ ሲሆን በመጨረሻም ተዳክመው በአካባቢ ገዠዎች ሊተኩ ችለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜን አፍሪካ በርካታ አካባቢያዊ ሥርወ መንግስታት አንድ ላይ በመጣመር ሁለት ጠንካራ የበርበር መንግስታትን በመመሥረት አብዛኛውን የሰሜን አፍሪካ እንዲሁም በ12ኛውና በ13ኛው ክፍለዘመን ስፔንን ጨምሮ ለማዋሀድ በቅተዋል። ከነሱ በኋላም ይሀው አካባቢ እንደገና ለምሣሌ አሁንም ድረስ ሞሮኮን በሚገዛው ሸሪፊድስ እና በመሣሠሉት ትናንሽ ስርወ መንግስታት ሊመራ ችሏል። በስፔን ግን የሙስሊሙ ሀይል የበላይነት እየተዳከመ ሄዶ በመጨረሻም በ1492 በግራናዳ የተሸነፈበት ሁኔታ ነበር። በዚህም ሙስሊሞች ለ800 አመታት ያህል ስፔንን ያስተዳደሩበት ሁኔታ ፍፃሜ አግኝቷል።

  • የእስልምና ታሪክ ከሞንጎሎች ወረራ በኋላ

ሞንጎላውያን ክፉኛ በመመታታቸው ከሙስሊሙ ዓለም ምስራቅ መሬቶች በመባረር ከሲናእ በረሃ ወደ ህንድ ለአንድ መቶ አመታት ያህል ተገፍተው ቆይተው ነበር። ነገር ግን ኋላ ላይ እስልምናን በመቀበል ‹ኤልካኒድስ› በሚባል መጠሪያ ሊታወቁ ችለዋል። ቀጥሎም በቲሙሮች የተተኩ ሲሆን የልጅ ልጆቻቸውም ሰመርቀንድን ዋና ከተማቸው በማድረግ ከ1369-1500 ገዝተዋል። የቲሞሮች ድንገት መነሣት የኦቶማን አገዛዝን መደራጀትና መስፋፋት ያዘገየ ቢሆንም ኋላ ላይ ግን ኦቶማኖች በሙስሊሙ ዓለም ትልቁ የሀይል ባለቤት ሆነዋል።

ቱርኮች ከምንም በመነሣት አጠቃላይ አናቶሊያንና የተወሰነውን የአውሮፓ ክፍል የተቆጣጠሩበት ሁኔታ አስገራሚ ክስተት ነበር። በ1453 በሚገጥመው ጦርነት ሁሌም አሸናፊ የሆነው ሜህሜት ኮንስታንኖፕልን በመውረር ለቢዛንታይኖች አገዛዝ ፍፃሜ አስገኝቷል። በዚሁ ጊዜ ኦቶማኖች ብዙውን የምሥራቅ አውሮፓ ክፍልና አጠቃላይ ሊባል በሚችል መልኩ የዐረቡን ዓለም ወረው የያዙ ሲሆን በምእራብ በኩል ሞሮኮና ሞሪታኒያ ብቻ ሲቀራቸው በዐረቡ ባህረ ሰላጤ ደግሞ የመንና ሀድረሙት ብቻ ነበር በቁጥጥራቸው ሥር ያልዋለው። በአስደናቂ መሪያቸው በሱሌይማን አማካይነት የሀይል ቁንጮ ላይም በመድረስ ጦራቸው ሀንጋሪና ኦስትሪያ ድረስ ዘለቀበት ሁኔታ ነበር።

ከ17ኛው ክፍለዘመን ቀጥሎ ባሉት አመታት የምእራብ አውሮፓውያንን ሀይል ማንሠራራትና የራሺያን መጠናከር ተከትሎ የኦቶማኖች ሀይል እየተዳከመ መጣ። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት በምእራባውያን ሀገራት እስከተሸነፉበት ጊዜ ድረስም ቱርኮች የዓለማችን ተጠቃሽ ሀይል ሆነው ቆይተዋል። ነገር ግን በ1924 ከማል በቱርክ አታቱርክ ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት ለ6 ክፍለዘመናት የቆየው የኦቶማን አገዛዝ ተወገደ። ኦቶማኖች በምእራብ ግንባር በኩል ባለው ግዛታቸው ተጠምደው ሣለም በምስራቅ በኩል ፐርሺያ ውስጥ ሣፋቪድስ የሚባል አዲስ ሥርወ መንግስት በ1502 ወደ ሥልጣን መጣ። ሣፋቪዶች የራሣቸው የሆነ ጠንካራ ግዛት የመሠረቱ ሲሆን ለሁለት ምእተ አመታት ያህል በነበራቸው እድሜም በዋናነት የበርካታ ጥበቦች መፍለቂያ ሆነው ነበር። በሰማያዊ ጡብ መስጊዶቿና በማራኪ ቤቶቿ የምትታወቀው ዋና ከተማቸው እስፈሃንም እጅግ ቆንጆ ከሚባሉ ከተሞች ለመሆን ችላለች። በ1736 አፍጋኖች ባደረሱት ወረራ የሣፋዚዶች አገዛዝ ፍፃሜ ያገኘ ሲሆን አፍጋኒስታንም በመጨረሻ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሙሉ ነፃነቷን ልታገኝ ችላለች። በሌላ በኩል ፐርሺያ ደግሞ የመጨረሻው የምሥራቃውያን ወራሪ ናድር ሻህ መልሦ እስኪያዋህዳት ድረስ አለመረጋጋት ውስጥ የገባችበት ነበር። ናድር ከፐርሺያም አልፎ ህንድንም እስከ መውረር ደርሦ ነበር። ቢሆንም ግን እዚያ የተመሠረተው አገዛዙ አጭር እድሜ ነበረው። ኋላም የዛንድ ሥርወ መንግስት ሥልጣን ላይ የወጣ ቢሆንም ወዲያውኑ መቀመጫቸውን ቴህራን ባደረጉት ቀጃርስ በ1779 ሊወገድ ችሏል። እነሱም እስከ 1921 የገዙ ሲሆን በመጨረሻም በፓልቪሦች ተተክተዋል።

ስለ ህንድ ስናነሣ እስልምና ወደ ምስራቃዊ ኢንዱስ ወንዝ መሬቶች የደረሰው ሰላማዊ በሆነ መልኩ ነበር። ቀስ በቀስም ሙስሊሞች በ13ኛው ክፍለዘመን መባቻ ጀምሮ የፖለቲካ የበላይነት እያገኙ መጡ። ነገር ግን እስልምናና ኢስላማዊ ባህሎች በእጅጉ እየተስፋፉ በነበረበት በዚህ ዘመን አብዛኛው የህንድ ክፍል በ1526 ከቲሙሪድ ልዑሎች መካከል አንዱ በሆነው በባቡር በመወረሯ ምክኒያት መስፋፋቱ ሊገታ ችሏል። ባቡር ጠንካራ የሞጉል ግዛትን የመሠረተ ሲሆን ከግዛቲቱም አክባር፣ ጀሀንጊር እና ሻህ ጀሃን የሚባሉ ታዋቂ መሪዎች ሊፈልቁ ችለዋል። ይሀው አገዛዝ በህንድ የብሪታኒያን ሀይል ተቋቁሞ ቆይቶ በመጨረሻም በ1857 ሊወገድ ችሏል። እሩቅ ምሥራቅ በማላይ ዓለም (ማሌዠያና ኢንዶኔዠያ አካባቢ) እስልምና ከ12ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሰሜን ሱማትራ የተስፋፋ ሲሆን ሙስሊም ግዛቶችም በጃቫ ፣ በሱማትራና በዋናው የማሌዠያ ክፍል ሊመሠረቱ ችለዋል። ምንም እንኳ ሰፊው የማላይ አካባቢ በቅኝ አገዛዝ ሥር የወደቀ ቢሆንም እስልምና ግን መስፋፋቱን ቀጥሎ በዚያ አካባቢ የዛሬዎቹን ኢንዶኔዠያን፣ ማሌዠያን፣ ደቡብ ፊሊፒንስን፣ ደቡብ ታይላንድን ለመሸፈን በቅቷል። ይሀው ሰላማዊ የሆነ መስፋፋቱ ዛሬም ድረስ ወደ ሩቅ ምስራቅ ደሴቶች እየተለጠጠ ነው።

አፍሪካን በተመለከተ እስልምና ወደ ምሥራቅ አፍሪካ በመጀመሪያዎቹ የኢስላም መባቻ አካባቢ የገባ ሲሆን በዳርቻዎች አካባቢ ተወስኖ ቆይቶ ሱዳንና ሶማሊያ ብቻ ቀስ በቀስ ዐረብም ሙስሊምም ሊሆኑ ችለዋል። እስልምና ወደ ምእራብ አፍሪካ ሊደርስ የቻለው ደግሞ በግመሎቻቸው ቅፍለቶች ወደ ደቡብ የሰሃራ በረሃ ይጓዙ በነበሩ የሰሜን አፍሪካ ነጋዴዎች ነው። በ14ኛው ክፍለ ዘመን በምእራብ አፍሪካ ማሊ እና ቲምቡክቱ አካባቢ ሙሰሊም ሱልጣኔቶች የነበሩ ሲሆን ሀረር ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ የኢስላማዊ ትምህርት ማዕከል ነበረች። ቀስ በቀስ እስልምና ወደ መሃል አህጉሩና ወደ ደቡብም ሊስፋፋ ችሏል። ይህ አካባቢ የአውሮፓን የሀይል የበላይነት በከፍተኛ ሁኔታ የተቋቋሙ የሚገርሙ ከፍተኛ አድናቆት የተቸራቸው ዝነኛ ሰዎችን ያፈራ ነበር። አፍሪካን ሙስሊም የማድረጉ ሂደት በቅኝ አገዛዙም ዘመን ያልተቋረጠ ሲሆን አሁንም ድረስ ቀጥሎ አብዛኞች ከሰሃራ በታች የሚገኙ አፍሪካውያን ረጅሙ የኢስላም ታሪክ በአንድ ወቅት በተወሰነ አካበቢ ጥሎት ያለፈውን ልማድ የሚከተሉ ሆነው እናገኛለን።

  • በኢስላም ታሪክ አበይት ቀናት ( ሁሉም አቆጣጠር በጎርጎርሣውያን ነው)

570

የነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልደት

609

የመጀመሪያው የቁርኣን አንቀፅ በነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የወረደበት

622

የነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስደት ከመካ ወደ መዲና /ሂጅራ/። በሙስሊሞች የዘመን አቆጣጠር የመጀመሪያው ቀን

632

የነቢዩ ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይሀ ወሠለም ሞት

632-661

የኩላፋኡ ራሽዲን ዘመን

661-750

የኦማያድ ሥርወ መንግስት

750-1258

የአባሲድ ሥርወ መንግስት

756-1031

ኡመያውያን ስፔንን የገዙበት ዘመን

909 -1171

ፋጢሚዮች

137-1300

ሴልጁቆች

1187

ሰላሃዲን ኢየሩሣሌምን የከፈተበት

1252-1517

የመምሉኮች አገዛዝ

1258

ሞንጎሎች ባግዳድን የወረሩበት

1299-1924

የኦቶማን አገዛዝ

1369-1500

ቲሙሪዶች

1453

የኮንስታንቲኖፕል መከፈት

1492

የግራናዳ መውደቅ

1502-1736

ሣፋቪዶች አገዛዝ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here