ሴት- እንደ እናት (ክፍል 3)

1
4427

የሰው ልጅ ከሴት ጋር በሚያደርገው ግንኙነት መጀመሪያ የሚያገኘው እናቱን ነው። ዘጠኝ ወራት በሆዷ ትሸከመዋለች። አምጣ ትወልደዋለች። አድካሚ በሆነ መልኩ አጥብታ ታሳድገዋለች።

ሴትን እንደ እናት ከፍተኛ ክብር በመስጠት ኢስላምን የሚወዳደር ሃይማኖትም፣ ሥርዓትም አስተሳሰብም የለም።

ኢስላም አላህን በብቸኝነት ከማምለክ ቀጥሎ ካስተላለፋቸው ኑዛዜዎች የመጀመሪያው የእናት እንክብካቤ ጉዳይ ነው። እናትን መንከባከብን የመልካም ሥነ-ምግባሮች መሠረት አድርጐታል። መብቷ ከአባትም መብት የበለጠ መሆኑን በአጽንኦት አስተምሯል።

ኢስላም የእናትነትን ስቃይና ክብደት፣ የውለታዋን ግዝፈት በተከታዮቹ ልቦና ውስጥ ለማስረጽ ደግሞ ደጋግሞ ያነሳዋል። የሚከተለውን የአላህ ቃል ለአብነት እናንሳ፡-

وَوَصَّيْنَا الْإِنسَانَ بِوَالِدَيْهِ حَمَلَتْهُ أُمُّهُ وَهْنًا عَلَىٰ وَهْنٍ وَفِصَالُهُ فِي عَامَيْنِ أَنِ اشْكُرْ لِي وَلِوَالِدَيْكَ إِلَيَّ الْمَصِيرُ

“ሰውንም በወላጆቹ (በጎ እንዲያደርግ) በጥብቅ አዘዝነው። እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው። ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው። ለእኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት (አዘዝነው)። መመለሻው ወደኔ ነው።” (ሉቅማን 31፤ 14)

وَوَصَّيْنَا الْإِنسَانَ بِوَالِدَيْهِ إِحْسَانًا حَمَلَتْهُ أُمُّهُ كُرْهًا وَوَضَعَتْهُ كُرْهًا وَحَمْلُهُ وَفِصَالُهُ ثَلَاثُونَ شَهْرًا

“ሰውንም በወላጆቹ በጎ መዋልን በጥብቅ አዘዝነው። እናቱ በችግር ላይ ኾና አረገዘችው። በችግርም ወለደችው። እርግዝናውና ከጡት መለያውም ሰላሳ ወር ነው።” (አል-አሕቃፍ 46፤ 15)

አንድ ሰው ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ቀረበና፡- “ ‘ይበልጥ በመልካም ልጐዳኘው የሚገባኝ ሰው ማን ነው?’ አላቸው። ‘እናትህ’ አሉት። ‘ከዚያስ?’ አላቸው። ‘እናትህ’ አሉት። ‘ከዚያስ?’ ‘እናትህ’ አሉት። ‘ከርሷ ቀጥሎስ?’ ‘አባትህ።’” ሲሉ መለሱለት። (ቡኻሪና ሙስሊም)

በዝ-ዛር እንዳስተላለፉት አንድ ሰው እናቱን በጀርባው ተሸክሞ ጦዋፍ ያደርጋል። ነቢዩን፡- “‘ውለታዋን (ሐቋን) መልሻለሁን?’ ሲል ጠየቃቸው። ‘አልመለስክም። ሙሉ ውለታዋን ይቅርና የአንድ ጊዜ ጭንቀቷን የሚመጥን ዋጋ እንኳ አልከፈልካትም’ አሉት።” (በዝ-ዛር)

የእናትን መብት ማክበር ማለት ከርሷ ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር፣ እርሷን ማክበር፣ ለርሷ መተናነስ፣ ከወንጀል ውጭ ባሉ ነገሮች እርሷን መታዘዝ፣ ምንጊዜም እርሷን ለማስደሰት መጣር፣ በሁሉም ጉዳዮች ፈቃዷን መጠየቅ ይገኙበታል። ለጂሃድ እንኳ -የሁሉንም ዜጐች ተሳትፎ የማይጠይቅ ከሆነ- የርሷ ይሁንታ ያስፈልጋል። እርሷን መንከባከብ የጂሃድ አካል ነውና።

አንድ ሰው ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ቀረበና፡- “ ‘የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! መዝመት እሻለሁ። ላማክርዎት ነው የመጣሁት’ አላቸው። ‘እናት አለህን?’ አሉት። ‘አዎ’ አለ። ‘እንግዲያውስ እርሷኑ ተንከባከብ። ጀነት ከርሷ እግር ሥር ነው’ አሉት።” (ነሳኢይ፣ ኢብን ማጃህና ሐኪም)

አንዳንድ ሕጐችና ልምዶች በእናት በኩል ላሉ ዘመዶች ዝቅተኛ ግምት ነበራቸው። ኢስላም ይህን አስተሳሰብ በመቀየር በእናት በኩል ስላሉ አክስቶችና አጐቶች እንክብካቤ ማስተማር ጀመረ።

አንድ ሰው ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ቀረበና፡- “ ‘ኃጢአት ፈጽሜያለሁ። ንስሐዬ ተቀባይነት ይኖረው ይሆን?’ አለ። ‘እናት አለህን?’ አሉት። ‘የለኝም’ አለ። ‘የእናትህ እህት አለችህን?’ አሉት። ‘አዎ’ አለ። ‘እንግዲያውስ (ንስሐህ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ) እርሷን ተንካበከብ’ አሉት።” (ቲርሚ፣ ኢብን ሒባን እና ሐኪም)

ኢስላም በዚህ ረገድ ከሰጣቸው ትምህርቶች በጣም የሚገርመው እናት አጋሪ (ሙሽሪክ) እንኳ ብትሆን መንከባከብ ግድ መሆኑን ማስተማሩ ነው።

አስማእ ቢንት አቡበክር በአንድ ወቅት ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) አጋሪ እናቷን ስለመንከባከብ ጠየቀቻቸው። ከርሷ ዘንድ በእንግድነት መጥታ ነበር።

نعم، صِلى أمك

“አዎ፤ እናትሽን ተንከባከቢያት” አሏት። (ቡኻሪና ሙስሊም)

ኢስላም ለእናት ስሜት እጅግ መጨነቁን ከሚያሳዩ ነገሮች አንዱ፡- ባልና ሚስት በፍች ከተለያዩ ልጅን የማሳደግን መብት ከአባት ይልቅ ለእናት መስጠቱ ነው።

ዐብደላህ ቢን ዑመር ቢን አል-ዓስ እንዳስተላለፉት አንዲት ሴት ነቢዩን፡- “ ‘የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይህ ልጄ ሆዴ መጠለያው፣ ጡቶቼ ምግቦቹ፣ ጭኖቼ ማሪፊዎቹ ናቸው። አባቱ ፈታኝ። እናም ሊነጥቀኝ አሰበ’ አለች። ነቢዩም፡- ‘ሌላ ባል እስካላገባሽ ድረስ ልጁን የማሳደግ መብት ያንች ነው’ አሏት።” (አህመድ)

ኢማም አል-ኸጧቢ “መዓሊም ሱነን” በተባለ መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

“ይህ ሐዲስ የእናትን ክብር የበለጠ ያገዝፋል። በወላጅነት አባትን ትጋራለች። በተገለፁት ባሕሪያትና ሚናዎች ደግሞ እርሷ ከአባት ትለያለች። ልጅን መንከባከብና የማሳደግ ትርጉም ይሄው ነው። አባት የተዘረዘሩትን ተግባራት አይፈጽምም። በመሆኑም በልጆች ጉዳይ ውዝግብ ሲፈጠር ልጁ ለርሷ ተገቢ ይሆናል።”

ኢብን ዐባስ እንዳስተላለፉት ዑመር ኢብነል ኸጧብ አንሷር ባለቤታቸውን ፈቱ። ዓሲም የተባለ ልጅ እናት ነበረች። መሕሰር የተባለ የገበያ ቦታ ላይ ልጃቸውን ተሸክማ አዩዋት። ተቆጡና ወደርሷ ሄዱ። ሊነጥቋትም አንገራገሩ። ታገሏት። ልጁ አያያዛቸውን አይቶ አለቀሰ። “ልጁን ካንች ይልቅ የማሳደግ መብቱ የኔ ነው” አሏት። ከአቡበክር ዘንድ ተካሰሱ። አቡበክር ለርሷ ፈረዱላት። “የርሷ ትንፋሽ፣ እቅፏና ጐኗ ለልጁ ከአንተ የተሻለ ነው። አድጐ የራሱን ምርጫ እስኪወስን ከርሷ ጋር መኖር አለበት” አሉ።

በልጅ እንክብካቤና አስተዳደግ ከአባት እናት ትሻላለች። እርሷ ትመረጣለች።

ኢስላም ይህን ሁሉ መብት ያጐናፀፋት እናት ግዴታዎችም አሉባት። ይህም ግዴታ ልጆቿን በመልካም ሥነ ምግባር አንጻ ማሳደግ ነው። አላህን እንዲያመልኩ ማላመድ፤ የሐቅ አጥር እንዲሆኑ ማበረታታት አለባት። የእናትነት አንጀት ይዟት ከጂሃድ ማዳከምና ማሳነፍም የለባትም። ሐቅን መርዳት ከእናትነት ስሜት የበለጠ ዋጋ ሊሰጠው ይገባልና። ኸንሳእ የተባለች እናት በቃዲሲያህ ጦርነት ወቅት አራቱንም ልጆቿን ወደ ጂሃድ ስትልክና ስታበረታታ፣ በፅናት እንዲታገሉ ስትመክር ታሪክ አስነብቦናል። ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ሁሉም መገደላቸው ተነገራት። አልጮኸችም። ራሷን ስታ አልወደቀችም። ሐዘኗን በፀጋ ተቀብላ እንዲህ አለች እንጅ፡-

“ልጆቼ በርሱ መንግድ ሲታገሉ እንዲሞቱ በማድረግ ክብር ላጐናፀፈኝ አላህ ምስጋና ይድረሰው።”

ዝንተዓለም የሚዘከሩ እናቶች

ከቁርኣን ትምህርቶች መካከል ለአማኞች የመልካም እናት ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ እንስቶችን ቁርኣን አስተዋውቋል። በእምነት ታሪክ ውስጥ የጐላ ሚና እንዳላቸው ለመጠቆም።

የሙሳን እናት እንውሰድ። አላህ ልጇን በውሃ ላይ እንድትጥል ያስተላለፈላትን ኑዛዜ በፀጋ ተቀበለች። በቃልኪዳኑ በመተማመንም የአብራኳን ክፋይ በውሃ ውስጥ ጨመረች። አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَأَوْحَيْنَا إِلَىٰ أُمِّ مُوسَىٰ أَنْ أَرْضِعِيهِ فَإِذَا خِفْتِ عَلَيْهِ فَأَلْقِيهِ فِي الْيَمِّ وَلَا تَخَافِي وَلَا تَحْزَنِي إِنَّا رَادُّوهُ إِلَيْكِ وَجَاعِلُوهُ مِنَ الْمُرْسَلِينَ

“ወደ ሙሳም እናት ‘አጥቢው፣ በርሱም ላይ በፈራሽ ጊዜ በባሕሩ ውስጥ ጣይው አትፈሪም፣ አትዘኝም፣ እኛ ወዳንቺ መላሾቹና ከመልክተኞቹም አድራጊዎቹ ነንና’ ማለትን አመለከትን።” (አል-ቀሶስ 28፤ 7)

የመርየም እናትም ተጠቃሽ ናት። ከማኅፀኗ ውስጥ ያለችውን ፅንስ ለአላህ አገልጋይነት ተሳለች። አላህም ስለቷን እንዲቀበላት እንዲህ ስትል ተማናፀነች፡-

إِذْ قَالَتِ امْرَأَتُ عِمْرَانَ رَبِّ إِنِّي نَذَرْتُ لَكَ مَا فِي بَطْنِي مُحَرَّرًا فَتَقَبَّلْ مِنِّي إِنَّكَ أَنتَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ

“የዒምራን ባለቤት (ሐና) ‘ጌታዬ ሆይ! እኔ በሆዴ ውስጥ ያለውን (ፅንስ ከሥራ) ነጻ የተደረገ ሲኾን ለአንተ ተሳልኩ። ከእኔም ተቀበል አንተ ሰሚው ዐዋቂው ነህና’ ባለች ጊዜ (አስታውስ)።” (ኣሊ ዒምራን 3፤ 35)

ልጇ ከጠበቀችው ውጭ ሴት ሆና ብታገኛትም ስለቷን ከመሙላት ወደኋላ አላለችም። ልጇን ከክፉ ነገር ሁሉ እንዲጠብቅላትም ተማፀነች፡-

فَلَمَّا وَضَعَتْهَا قَالَتْ رَبِّ إِنِّي وَضَعْتُهَا أُنثَىٰ وَاللَّهُ أَعْلَمُ بِمَا وَضَعَتْ وَلَيْسَ الذَّكَرُ كَالْأُنثَىٰ وَإِنِّي سَمَّيْتُهَا مَرْيَمَ وَإِنِّي أُعِيذُهَا بِكَ وَذُرِّيَّتَهَا مِنَ الشَّيْطَانِ الرَّجِيمِ

“በወለደቻትም ጊዜ፡- ‘ጌታዬ ሆይ! እኔ ሴት ኾና ወለድኋት።’ አላህም የወለደችውን ዐዋቂ ነው። ‘ወንድም እንደ ሴት አይደለም። እኔም መርየም ብዬ ስም አወጣሁላት። እኔም እስዋንም ዝርያዋንም ከተረገመው ሰይጣን በአንተ እጠብቃቸዋለሁ’ አለች።” (ኣሊ ዒምራን 3፤ 36)

የዒሳ እናት መርየምም የመልካም እናቶች ተምሳሌት ናት። አላህ በንጽሕናና እርሱን በመፍራት፣ ቃሉን በማመን ረገድ የእንስቶች ፈርጥ እና ተምሳሌት አድርጓታል።

وَمَرْيَمَ ابْنَتَ عِمْرَانَ الَّتِي أَحْصَنَتْ فَرْجَهَا فَنَفَخْنَا فِيهِ مِن رُّوحِنَا وَصَدَّقَتْ بِكَلِمَاتِ رَبِّهَا وَكُتُبِهِ وَكَانَتْ مِنَ الْقَانِتِينَ

“የዒምራንን ልጅ መርየምንም ያችን ብልቷን የጠበቀችውን (ምሳሌ አደረገ)። በእርሱም ውስጥ ከመንፈሳችን ነፍፋን። በጌታዋ ቃላትና በመጻሕፍቱም አረጋገጠች። ከታዛዦቹም ነበረች።” (አት-ተሕሪም 66፤ 12)

____________

ይህ ፅሁፍ የተወሰደው ከዶ/ር ዩሱፍ አል-ቀረዳዊ መፅሐፍ “መካነቱል መርኣ ፊልኢስላም” ትርጉም በሀሰን ታጁ፣ ነጃሺ አሳታሚ።

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here