ሴት- እንደ እንስት (ክፍል 2)

0
3760

ኢስላም ለሴት ልጅ እንስታዊ ባሕሪ ከፍተኛ ክብር ሰጥቷል። የወንድ ማሟያ እንደሆነችም አስተምሯል። ወንዱም የርሷ ማሟያ ነው። አንዱ የሌላኛው ባላንጣ ወይም ተፎካካሪ አይደሉም። ሰብዕናው የተሟላ ይሆን ዘንድ አጋዥ የሚሆን እንጅ።  “ጣምራነት” የፍጡራን ባሕሪ እንዲሆን የአላህ ፈቃድ ሆኗል። በሰው፣ በእንስሳትና በዕፅዋት ዓለም ውስጥ እንስትና ተባዕት እናገኛለን።

በኤሌክትሪክ፣ በማግኔትና ሌሎችም የግዑዛን ዓለም ውስጥ ደግሞ “ፖዘቲቭ” እና “ኔጌቲቭ” ባሕሪያትን እናገኛለን። አቶም እንኳ “ኤሌክትሮን” እና “ፕሮቶን” የተባሉ የተለያዩ ቻርጅ ያላቸው ክፍሎች አሏት። ቀጣዩ የቁርኣን አንቀጽ ይህን እውነታ ያመላከተ ነው።

وَمِن كُلِّ شَيْءٍ خَلَقْنَا زَوْجَيْنِ لَعَلَّكُمْ تَذَكَّرُونَ

“(የአላህን ታላቅነት) ታስታውሱ ዘንድ ከሁሉም ነገር ጥንዶችን ፈጠርን።” (አዝ-ዛሪያት 51፤ 49)

ሴት እና ወንድ የሚነጣጠሉ አይደሉም። አንዱ ያለ ሌላው ሕልውና አይኖርም። አላህ የመጀመሪያውን ሰው- አደምን- ሲፈጥር መርኪያና መርጊያ ትሆነው ዘንድ ሐዋን ከርሱው ፈልቅቆ አወጣለት። ጀንነት ውስጥ እንኳ ብቻውን አልተወውም። ከዚያ በኋላ ለሁለቱ- በጋራ- ትእዛዝ አወረደ።

وَقُلْنَا يَا آدَمُ اسْكُنْ أَنتَ وَزَوْجُكَ الْجَنَّةَ وَكُلَا مِنْهَا رَغَدًا حَيْثُ شِئْتُمَا وَلَا تَقْرَبَا هَٰذِهِ الشَّجَرَةَ فَتَكُونَا مِنَ الظَّالِمِينَ

“አደም ሆይ! አንተ ከነሚስትህ በገነት ተቀመጥ፤ ከርሷም በፈለጋችሁት ስፍራ በሰፊው ተመገቡ፤ ግን ይህችን ዛፍ አትቅረቡ፤ ከበደለኞች ትኾናላችሁና- አልንም፡፡” (አል-በቀራህ 2፤ 35)

ሴት ልጅ በዚህ ዕይታ መሠረት ወንድ አይደለችም። የወንድ ማሟያ እንጅ። አንድ ነገር ለራሱ ማሟያ አይሆንም። ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

وَلَيْسَ الذَّكَرُ كَالْأُنثَىٰ

“ወንድም እንደ ሴት አይደለም።” (ኣሊ ዒምራን 3፤ 36)

ልክ “ኔጌቲቭ” እና “ፖዘቲቭ” የተለያዩ ባሕሪያት እንዳሏቸው ሁሉ።

ይህም ሆኖ ግን ሴት ልጅ የወንድ ባላንጣ ተደርጋ አልተፈጠረችም። ከርሱ፣ የርሱ፣ ለርሱ ናት።

بَعْضُكُم مِّن بَعْضٍ

“ከፊላችሁ የከፊሉ አካል ናችሁ።” (አን-ኒሳእ 4፤ 25)

وَاللَّهُ جَعَلَ لَكُم مِّنْ أَنفُسِكُمْ أَزْوَاجًا

“አላህ ከነፍሶቻችሁ የሆኑ መቀናጆዎችን አደረገላችሁ።” (አን-ነሕል ፤ 72)

የአላህ ፈቃድ ሆኖ ሴት ወንድን እንድትስብ፣ በርሱም እንድትሳብ ተደርጋ ተፈጠረች። ሕይወት ቀጣይነት ይኖራት ዘንድ አላህ በሁለቱም ፆታዎች ውስጥ እንዲሳሳቡና እንዲገናኙ የሚያደርግ ጠንካራ ስሜት አስቀምጧል። በመሆኑም ኢስላም ይህን ተፈጥሯዊ ሥርዓትና አወቃቀር የሚቃረንና የሚያናጋ ሥርዓት- ለምሳሌ ብህትውናን አጥብቆ ይቃወማል።

በሌላ በኩል ይህን የፆታዎች ወሲባዊ ኃይል፤ የቤተሰብ መሠረት ከሆነው ከጋብቻ ውጭ በሌላ መንገድ ማባከንን ከልክሏል። ለዚህም ሲባል እንደሌሎች መለኮታዊ ሃይማኖቶች ሁሉ ዝሙትን ከልክሏል። በግልጽም ይሁን በስውር የሚፈፀምን ብልግና አወገዘ። ሁለቱንም ፆታዎች ከወሲብ ፈተና ለመታደግ ሲልም ወደ ዝሙት የሚያደርስ መንገዶችን ሁሉ ዘጋ።

ኢስላም ለሴቷ ያለው ዕይታ ይህን ተፈጥሮዋንና ከወንድ ጋር ሊኖራት የሚገባውን ሚዛናዊ ግንኙነት መሠረት ያደረገ ነው። ሥርዓቱን ያነፀውና ሕግጋቱን የቀረፀው፤ ትምህርቶችን የሚሰጠው ይህን ዕይታ መነሻ በማድረግ ነው።

ኢስላም የሴቷን እንስታዊ ተፈጥሮ ይጠብቃል። ይንከባከባል። ከእንስታዊ ተፈጥሮዋ ለሚመነጩ ነገሮችም እውቅና ይሰጣል። ይህን ባሕሪዋን ሊያፍንና ሊጨፈልቅ አይሻም። እንዳይዳጥ ይከላከላል እንጂ። እንስትን ጠልፈው እና ነጥቀው፤ እንደ ሸንኮራ መጥጠው ከሚተፏት፤ ሥጋዋን በልተው አጥንቷን ከሚወረውሯት፤ የሰው ተኩላዎችና አዳኝ ውሻዎች ይጠብቋታል እንጅ።

ኢስላም በሴቷ እንስታዊ ባሕሪ ዙሪያ ያለውን አቋም በሚከተሉት ነጥቦች ማጠቃለል እንችላለን፡-

1. የእዝነት፣ የፍቅር፣ የልስልስነትና የውበት ስሜቶች ምንጭ ትሆን ዘንድ እንስታዊ ባሕሪዋን ይጠብቃል። ይንከባከባል። ለዚህም ነው ለወንዶች እርም የተደረጉ አንዳንድ ጌጣጌጦችን የፈቀደላት። እንስትነቷን ለመጠበቅና ለመንከባከብ። ለምሳሌ በወርቅ እንድታጌጥ፣ ንጹሕ ሐር እንድትለብስ ፈቅዶላታል። በሐዲስ የሚከተለው ተላልፏል።

إن هذين حرام على ذكور أمتى حِلٌ لإناثهم

“እነዚህ (ወርቅና ሐር) ከተከታዮቼ ለወንዶቹ ክልክሎች ሲሆኑ ለሴቶቹ ግን የተፈቀዱ ናቸው።” (ኢብን ማጃህ- ዐሊይን ዋቢ በማድረግ የዘገቡት ሲሆን፤ በሁሉም የመልዕክት ሰንሰለቶች ከሶሂህ ዘገባ ነው።)

እንደዚሁም ይህን እንስታዊ ባሕሪ የሚያከስምን ነገር ሁሉ ኢስላም ይከለክላታል። ለምሳሌ በአለባበስ፣ በአረማመድ፣ በባሕሪና ሌሎችም ነገሮች ከወንድ ጋር መመሳሰልን ከልክሏታል። ሴት የወንድን፤ ወንድም የሴትን ልብስ እንዳይልብሱ ከልክሏል። በሐዲስ የሚከተለው ተነግሯል፡-

لعن الله الرجل يلبس لِبْسة المرأة، والمرأة تلبس لِبْسة الرجل

“የሴት ልብስ የሚለብሱ ወንዶችና የወንድ ልብስ የሚለብሱ ሴቶችን አላህ ረግሟቸዋል።” (አቡ ዳውድ፣ ነሳኢይ፣ አህመድ፣ ኢብን ሒባን እና ሐኪም ዘግበውታል)

“ከወንዶች በሚመሳሰሉ እንስቶችንና፤ ከሴቶች ጋር የሚመሳሰሉ ተባዕቶችንም ረግመዋል።” (ቡኻሪ፣ አቡ ዳውድ፣ ቲርሙዚና ኢብን ማጃህ)

በሐዲስ የሚከተለው ተነግሯል፡-

ثلاثة لايدخلون الجنَّة ولا ينظر الله إليهم يوم القيامة: العاق لوالديه، والمرأة المترجلة -المتشبهة بالرجال- والديُّوث

“ሦስት ሰዎች ጀነት አይገቡም። በዕለተ ቂያማ አላህ አያያቸውም። እነርሱም የወላጆችን መብት የጣሰ፣ ከወንድ ጋር የምትመሳሰል ሴትና ቅናት አልባ ወንድ ናቸው።” (አህመድ፣ ነሳኢና ሐኪም)

ቅናት አልባ ወንድ (ደዩስ) የተባለው ማንም ወንድ ከሚስቱ ጋር ሲቀራረብና ሲላፋ ደንታ የማይሰጠው ማለት ነው። በሌላ ሐዲስም እንዲህ ተብሏል፡-

لعن الله الرجُلة من النساء

“ወንዳወንድ ሴቶችን አላህ ረግሟቸዋል።” (አቡ ዳውድ)

2. ኢስላም የእንስቷን እንስታዊና ለስላሳ ባሕሪ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ከወንድ ከለላ ሥር በማድረግ ለቁሳዊ ፍላጐቶቿ ዋስትና ሰጥቷታል። ምንጊዜም በአባቷ፣ በባሏ፣ በልጇ ወይም በወንድሞቿ ጥበቃ ሥር ናት። ኢስላማዊው ሸሪዓ ባስቀመጠው አኳኋን ቁሳዊ ፍላጐቷን ማሟላት አለባቸው። ለእንጀራ ብላ ሕይወትን የመጋፈጥ፣ የመንገላታት፣ ከወንዶች ጋር ትከሻ ለትከሻ የመጋፋት ግዴታ የለባትም። የምዕራቡ ዓለም እንስቶች ግን ሕይወትን እንዲጋፈጡ ተገደዋል። ሴትን ልጅ አባት ወይም ልጅ፣ ወንድም ወይም አጐት አይደግፋትም። ራሷን ለመደገፍ መሥራት አለባት። ለመኖር የትኛውንም ዓይነት ሥራ ለመቀበል ትገደዳለች። በየትኛውም ደምወዝ።

3. ኢስላም ባሕሪዋንና ዓይናፋርነቷን ይንከባከባል። ስሟንና ክብሯን ይጠብቃል። ጥብቅነቷን ከመጥፎ ነገር ይከላከላል። ከእኩይ ምላሶች ይታደጋታል። ለዚህም ሲባል ተከታዮቹን ግዴታዎች ጥሏል፡-

i. ዓይኗን እንድትቆጣጠር፤ ቁጥብና ጥብቅ እንድትሆን፡-

وَقُل لِّلْمُؤْمِنَاتِ يَغْضُضْنَ مِنْ أَبْصَارِهِنَّ وَيَحْفَظْنَ فُرُوجَهُنَّ

“ለምእምናትም ንገራቸው፡- ዓይኖቻቸውን ይከልክሉ፡፡ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ፡፡” (አን-ኑር 24፤ 31)

ii. በአለባበሷ አካሏን እና ጌጦቿን እንድትሸፍን አዟታል፡-

وَلَا يُبْدِينَ زِينَتَهُنَّ إِلَّا مَا ظَهَرَ مِنْهَا وَلْيَضْرِبْنَ بِخُمُرِهِنَّ عَلَىٰ جُيُوبِهِنَّ

“ጌጦቻቸውንም ግልጽ ከሆነው በቀር አይግለጡ። ጉፍታዎቻቸውንም ከአንገቶቻቸው ላይ ያጣፉ።” (አን-ኑር 24፤ 31)

“ግልጽ ከሆነው በቀር” የሚለውን አንቀጽ ኩል፣ ፊትና መዳፍ ተብሎ ተተርጉሟል። ከፊል የፊቅህ ጠበብት ሁለት እግሮችንም ጨምረዋል።

iii. እንደ ፀጉር፣ አንገት፣ ክንዶችና ባቶች ያሉ የውስጥ ጌጦቿን እንደ ባዕድ መሸፈን አስቸጋሪ ከሚሆንባት ከባሏና ከቅርብ ዘመዶቿ (ሙሕሪም) ውጭ ለማንም እንዳታሳይ አቅቧታል፡-

وَلَا يُبْدِينَ زِينَتَهُنَّ إِلَّا لِبُعُولَتِهِنَّ أَوْ آبَائِهِنَّ أَوْ آبَاءِ بُعُولَتِهِنَّ أَوْ أَبْنَائِهِنَّ أَوْ أَبْنَاءِ بُعُولَتِهِنَّ أَوْ إِخْوَانِهِنَّ أَوْ بَنِي إِخْوَانِهِنَّ أَوْ بَنِي أَخَوَاتِهِنَّ أَوْ نِسَائِهِنَّ أَوْ مَا مَلَكَتْ أَيْمَانُهُنَّ أَوِ التَّابِعِينَ غَيْرِ أُولِي الْإِرْبَةِ مِنَ الرِّجَالِ أَوِ الطِّفْلِ الَّذِينَ لَمْ يَظْهَرُوا عَلَىٰ عَوْرَاتِ النِّسَاءِ

“(የውስጥ) ጌጦቻቸውንም፤ ለባሎቻቸው ወይም ለአባቶቻቸው ወይም ለባሎቻቸው አባቶች ወይም ለወንዶች ልጆቻቸው ወይም ለባሎቻቸው ልጆች ወይም ለወንድሞቻቸው ወይም ለወንድሞቻቸው ልጆች ወይም ለእህቶቻቸው ልጆች ወይም ከነርሱ ለሆኑ ሴቶች (ጓደኞቻቸውና አገልጋዮቻቸው) ወይም በሥሮቻቸው ላሉ (ባሮች) ወይም ለሴት ግድ ለሌላቸው (ወሲባዊ ስሜት ለሌላቸው) ወንዶች ወይም የሴትን ሐፍረት ገላ ለማያውቁ ሕጻናት ካልሆነ በቀር አይግለጡ።” (አን-ኑር 24፤ 31)

iv. በአነጋገሯና በአረማመዷ ቁጥብ እንድትሆን አስተምሯታል፡-

وَلَا يَضْرِبْنَ بِأَرْجُلِهِنَّ لِيُعْلَمَ مَا يُخْفِينَ مِن زِينَتِهِنَّ

“ከጌጦቻቸው የሸፈኑት ይታወቅ ዘንድም በእግሮቻቸው (መሬቱን) አይምቱ።” (አን-ኑር 24፤ 31)

فَلَا تَخْضَعْنَ بِالْقَوْلِ فَيَطْمَعَ الَّذِي فِي قَلْبِهِ مَرَضٌ وَقُلْنَ قَوْلًا مَّعْرُوفًا

“ስትናገሩ (የድምጻችሁን ቅላጼ) አታለስልሱ፤ በልቡ ውስጥ በሽታ ያለበት (እናንተን ለፀያፍ ነገር) እንዳይመኝ። ግና መልካም ንግግርን ብቻ ተናገሩ።” (አል-አሕዛብ 33፤ 32)

መናገር አልተከለከለችም- ድምጿ “ዐውራህ” አይደለም። ልዝብና መልካም ቃል እንድትናገር ብቻ ነው የታዘዘችው።

v. የወንድን ስሜት ከሚስቡ ድርጊቶች መቆጠብ ይጠበቅባታል። ከዘመነ-ጃሂሊያ እርቃንነት መራቅ አለባት። መራቆት የሙስሊም ሴት ባሕሪ አይደለም። በሐዲስ የሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን፡-

أيُما امرأة استعطرت ثم خرجت من بيتها ليشم الناس ريحها فهى زانية

“አንዲት ሴት ሽቶ ተቀብታ መልካም ሽታዋን ሰዎች ያሸቱላት ዘንድ በማሰብ ከቤቷ ከወጣች ዝሙት ፈጽማለች።” (አቡ ዳውድ፣ ቲርሙዚና ነሳኢ)

ከእንዲህ ዓይነቱ ባሕሪ መቆጠብ ይኖርባታል።

vi. ራሷንም ሆነ ወንዱን ከወንጀል፤ ክብሯንም ከሐሰት ምላሶች ለመጠበቅ ሲባል ከባሏ ወይም ከቅርብ ዘመዷ ጋር ካልሆነ የትኛውም ወንድ ጋር መገለል ተከልክላለች።

لا يَخْلُوَنّ رجلٌ بامرأةٍ، ولاتسافرنَّ امرأة، إلاومعها محرم

“አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ተከልሎ አይኑር። አንዲት ሴትም ያለ ሙሕሪም ጉዞ አትውጣ።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

vii. ከባዕድ ወንዶች ጋር መቀላቀል የለባትም። የግድ እና አስፈላጊ ካልሆነ በቀር። ለምሳሌ ለሶላት፣ ለትምህርትና በመልካም ጉዳዮች ለመተባበር መጠኑም አስፈላጊውን ያህል ብቻ መሆን አለበት። በዚህ ረገድ የተሰጠው ፈቃድ ሴት ልጅ ከወንድ ጋር የሚኖራት ግንኙነት የሸሪዓውን ወሰኖችና ገደቦች ጠብቃ ሕብረተሰቧን እንድታገለግል ዕድል ይሰጣታል።

ኢስላም ከላይ በሰፈሩት ድንጋጌዎች በአንደኛ ደረጃ ሴትን ልጅ ከነጣቂ ተኩላዎች ይጠብቃል። በሁለተኛ ደረጃ ከጥመትና መንገድ ከመሳት ይታደጋታል። እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ ክብሯን ከእኩይ ምላሶች ትችት ይከለክልላታል። በአንድ በኩል ይህን ሁሉ እያደረገ በሌላ በኩል ሥነ-ልቦናዋን ከውስጥ ሐሳቦችና ጭንቀቶች፤ ከቀልብ መበታተንና ከውጥረት ያድናታል። እነኝህ ድንጋጌዎች ወንድን ከወሲብ ፈተናዎች፤ ቤተሰብን ከመበታተን አደጋ፤ ኅብረተሰብን ለዝቅጠት እና ውድቀት ከሚያበቋት ሰበቦች ይጠብቃሉ።

ይህ ፅሁፍ የተወሰደው ከዶ/ር ዩሱፍ አል-ቀረዳዊ መፅሐፍ “መካነቱል መርኣ ፊልኢስላም” ትርጉም በሀሰን ታጁ፣ ነጃሺ አሳታሚ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here