ሴት- እንደ ሰብዓዊ ፍጡር (ክፍል 1)

0
3103

ኢስላም በመጣበት ዘመን ከፊል የሰው ልጆች የሴትን ልጅ ሰብዓዊ ፍጡርነት በእርግጠኝነት አይቀበሉም ነበር። ሌሎች ደግሞ ቢያንስ ይጠረጥሩታል። አንዳንዶቹ ሰብዓዊ ፍጡነርቷን ቢቀበሉም ወንዶችን ለማገልገል እንደተፈጠረች አድርገው ይቆጥሯታል።

ኢስላም ምስጋና ይግባውና ሴትን ከእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ነፃ አወጣ። ሰብዓዊ ፍጡርነቷን አፀና። ኃላፊነቷን የመሸከም፣ የተጠያቂነት እና በሥራዋም ጀንነትን የመጐናፀፍ ብቃት እንዳላት አረጋገጠ።

የተከበረች ሰብዓዊ ፍጡር እንደሆነች አወጀ። ልክ ከወንዱ ጋር እኩል የሰብዓዊ መብቶች ተጋሪ አደረጋት። ሁለቱም የአንድ ግንድ ቅርንጫፎች ናቸውና። ወንድማማቾች ናቸውና። የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች። የሐዋና የአደም ክፋዮች። በአፈጣጠር እኩል ናቸው። በኃላፊነትና ተጠያቂነት እኩል ናቸው። በምንዳና ፍጻሜም እኩል ናቸው። ቁርኣን ይህን በማስመልከት ሲናገር፡-

يَا أَيُّهَا النَّاسُ اتَّقُوا رَبَّكُمُ الَّذِي خَلَقَكُم مِّن نَّفْسٍ وَاحِدَةٍ وَخَلَقَ مِنْهَا زَوْجَهَا وَبَثَّ مِنْهُمَا رِجَالًا كَثِيرًا وَنِسَاءً وَاتَّقُوا اللَّهَ الَّذِي تَسَاءَلُونَ بِهِ وَالْأَرْحَامَ إِنَّ اللَّهَ كَانَ عَلَيْكُمْ رَقِيبًا 

“እናንተ ሰዎች ሆይ! ያን ከአንዲት ነፍስ የፈጠራችሁን፤ ከርሷም ተጣማሪዋን የፈጠረውንና ከነኝህ ከሁለቱ በርካታ ወንዶችንና ሴቶችን ያበዛውን ጌታችሁን ፍሩ። ያን በርሱ (የጋራ መብቶቻችሁን) የምትጠያየቁበትን አላህ ፍሩ፤ ዝምድናንም (ከመቁረጥ ተጠንቀቁ)። አላህ እናንተን ዘወትር ተጠባባቂ ነውና።” (አን-ኒሳእ 4፤ 1)

በመሆኑም የሰውን ልጆች ባጠቃላይ- ሴቶችንም ወንዶችንም- አምላካቸው የፈጠራቸው ከአንዲት ነፍስ ነው። ይህችም ነፍስ ምሉዕነትን ትጐናፀፍ ዘንድ ተጣማሪዋን አደረገላት። ይህንንም በሌላ አንቀጽ እንዲህ ገልጾታል፡-

هُوَ الَّذِي خَلَقَكُم مِّن نَّفْسٍ وَاحِدَةٍ وَجَعَلَ مِنْهَا زَوْجَهَا لِيَسْكُنَ إِلَيْهَا

“እርሱ ያ ከአንድ ነፍስ የፈጠራችሁ፤ ከርሷም ተጣማሪዋን -ይረካበት ዘንድ- የፈጠረ (አምላክ) ነው።” (አል-አዕራፍ 7፤ 189)

ከዚህች አንድ ቤተሰብ ውስጥ በርካታ ወንዶችንና ሴቶችን አስገኘ። ሁሉም የአንድ አምላክ ፍጡሮች ናቸው። የአንድ አባትና የአንዲት እናት ልጆች ናቸው። እናም በወንድማማችነት ተሳስረዋል። ይህም በመሆኑ አንቀጿ የሰው ልጆች አምላካቸውን እንዲፈሩ፤ የዝምድና ትስስራቸውንም እንዲጠብቁ አዘዘች፡-

وَاتَّقُوا اللَّهَ الَّذِي تَسَاءَلُونَ بِهِ وَالْأَرْحَامَ

“ያን በርሱ (የጋራ መብቶቻችሁን) የምትጠያየቁበትን አላህ ፍሩ፤ ዝምድናንም (ከመቁረጥ ተጠንቀቁ)።” (አን-ኒሳእ 4፤ 1)

በሌሎች አናቅጽ መልዕክት መሠረት ወንድ የሴት ወንድም ነው። ሴትም የወንድ እህት ናት። የአላህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ይህን አስመልክተው ሲናገሩ፡-

إنما النساء شقائق الرجال

“ሴቶች የወንዶች እህቶች ናቸው።” (አህመድ፣ አቡዳዉሩ፣ ቲርሚዚና ዳረሚይ ዓኢሻን ዋቢ በማግረግ ዘግበውታል።)

በመለኮታዊ ትእዛዙ፣ በአምልኮዎችና በሃይማኖታዊ አጀንዳዎች ሴት ልጅ ከወንድ እኩል መሆኗን ቁርኣን ሲያስተምር፡-

إِنَّ الْمُسْلِمِينَ وَالْمُسْلِمَاتِ وَالْمُؤْمِنِينَ وَالْمُؤْمِنَاتِ وَالْقَانِتِينَ وَالْقَانِتَاتِ وَالصَّادِقِينَ وَالصَّادِقَاتِ وَالصَّابِرِينَ وَالصَّابِرَاتِ وَالْخَاشِعِينَ وَالْخَاشِعَاتِ وَالْمُتَصَدِّقِينَ وَالْمُتَصَدِّقَاتِ وَالصَّائِمِينَ وَالصَّائِمَاتِ وَالْحَافِظِينَ فُرُوجَهُمْ وَالْحَافِظَاتِ وَالذَّاكِرِينَ اللَّهَ كَثِيرًا وَالذَّاكِرَاتِ أَعَدَّ اللَّهُ لَهُم مَّغْفِرَةً وَأَجْرًا عَظِيمًا

ሙስሊም ወንዶችና ሙስሊም ሴቶች፣ አማኝ ወንዶችና አማኝ ሴቶች፣ ታዛዥ ወንዶችና ታዛዥ ሴቶች፣ እውነተኛ ወንዶችና እውነተኛ ሴቶች፣ ታጋሽ ወንዶችና ታጋሽ ሴቶች፣ አላህን ፈሪ ወንዶችና አላህን ፈሪ ሴቶች፣ መጽዋች ወንዶችና መጽዋች ሴቶች፣ ጿሚ ወንዶችና ጿሚ ሴቶች፣ ብልቶቻቸውን (ከዝሙት) ጠባቂ ወንዶችና ሴቶች፣ አላህን በብዛት የሚያወሱ ወንዶችና ሴቶች አላህ ምሕረትንና ታላቅ ምንዳን አዘጋጅቶላቸዋል።” (አል-አሕዛብ 33፤ 35)

በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ቁርኣን ሁለቱንም ጾታዎች እኩል ያደርጋል።

وَالْمُؤْمِنُونَ وَالْمُؤْمِنَاتُ بَعْضُهُمْ أَوْلِيَاءُ بَعْضٍ يَأْمُرُونَ بِالْمَعْرُوفِ وَيَنْهَوْنَ عَنِ الْمُنكَرِ وَيُقِيمُونَ الصَّلَاةَ وَيُؤْتُونَ الزَّكَاةَ وَيُطِيعُونَ اللَّهَ وَرَسُولَهُ أُولَٰئِكَ سَيَرْحَمُهُمُ اللَّهُ إِنَّ اللَّهَ عَزِيزٌ حَكِيمٌ

“የወንድና የሴት አማኞች ከፊሉ የከፊሉ ረዳት ናቸው። በመልካም ያዛሉ። ከክፉ ይከለክላሉ። ሶላትንም ደንቡን አሟልተው ይሰግዳሉ። ዘካንም ይሰጣሉ። አላህንና መልዕክተኛውንም ይታዘዛሉ። ለእነርሱ አላህ ያዝንላቸዋል። አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና።” (አት-ተውባህ 9፤ 71)

በአደም ታሪክ ውስጥ መለኮታዊ ትእዛዝ የተላለፈላቸው ለርሱም ለባለቤቱም ነው፡-

وَقُلْنَا يَا آدَمُ اسْكُنْ أَنتَ وَزَوْجُكَ الْجَنَّةَ وَكُلَا مِنْهَا رَغَدًا حَيْثُ شِئْتُمَا وَلَا تَقْرَبَا هَٰذِهِ الشَّجَرَةَ فَتَكُونَا مِنَ الظَّالِمِينَ

“አደም ሆይ! አንተ ከነሚስትህ ገነት ውስጥ ተቀመጥ። ከርሷም (ከመልካም ፍሬዎቿም) በፈለጋችሁበት ሥፍራና ጊዜ ያሻችሁትን ተመገቡ። ይህችን ዛፍ ግን አትቅረቡ፤ ከበዳዮች ትሆናላችሁና።” (አል-በቀራህ 2፤ 35)

ይሁንና በዚህ ታሪክ ውስጥ- በቁርኣን ትረካ መሠረት- ኃጢአት የማሠራቱን “ተግባር” የፈፀመው ሰይጣን እንጅ ሐዋእ አይደለችም።

فَأَزَلَّهُمَا الشَّيْطَانُ عَنْهَا فَأَخْرَجَهُمَا مِمَّا كَانَا فِيهِ

“ሰይጣንም ከርሷ (ከገነት) አስወገዳቸው። ከነበሩበት (በውስጧም ከነበረው የገነት ድሎትም) አወጣቸው።” (አል-በቀራህ 2፤ 36)

ሐዋእ ፍሬዋን ብቻዋን አልበላችም። ጀማሪም አልነበረችም። ስህተቱ የሁለቱም ነበር። ፀፀቱና ንስሐቸውም እንዲሁ የሁለቱም ነበር።

قَالَا رَبَّنَا ظَلَمْنَا أَنفُسَنَا وَإِن لَّمْ تَغْفِرْ لَنَا وَتَرْحَمْنَا لَنَكُونَنَّ مِنَ الْخَاسِرِينَ

“ታችን ሆይ! ራሳችንን በድለናል። ካልማርከንና ካላዘንክልን ከከሣሪዎች እንሆናለን በማለት (ጌታቸውን) ተማፀኑ።” (አል-አዕራፍ 7፤ 23)

እንዲያውም በአንዳንድ የቁርኣን አንቀጾች ኃጢአቱ በዋነኛነት የአደም መሆኑ ተገልጿል፡-

وَلَقَدْ عَهِدْنَا إِلَىٰ آدَمَ مِن قَبْلُ فَنَسِيَ وَلَمْ نَجِدْ لَهُ عَزْمًا

“ከዚህ ቀደም ከአደም ቃልኪዳን ይዘናል። ግና ረሳው። ቁርጠኝነትንም አላገኘንበትም።” (ጧሃ 20፤ 115)

فَوَسْوَسَ إِلَيْهِ الشَّيْطَانُ قَالَ يَا آدَمُ هَلْ أَدُلُّكَ عَلَىٰ شَجَرَةِ الْخُلْدِ وَمُلْكٍ لَّا يَبْلَىٰ

“ግና ሰይጣን ጐተጐተው። አደም ሆይ! ዝንተዓለም መኖርና የማይወገድ ሥልጣን ማግኘት የምታስችልህን ዛፍ ላመላክትህን? አለው።”(ጧሃ 20፤ 120)

وَعَصَىٰ آدَمُ رَبَّهُ فَغَوَىٰ

“አደም (በዚህ አኳኋን) የጌታውን ትእዛዝ ጣሰ። ስህተት ላይ ወደቀም።” (ጧሃ 20፤ 121)

ንስሐውም እንዲሁ የርሱ ብቻ እንደሆነ ተደርጐ ቀርቧል፡-

ثُمَّ اجْتَبَاهُ رَبُّهُ فَتَابَ عَلَيْهِ وَهَدَىٰ

“ከዚያም ጌታው መረጠው። ንስሐውንም ተቀበለው። መቀናትንም ለገሰው።” (ጧሃ 20፤ 122)

ከነዚህ አናቅጽ የምንረዳው የኃጢአቱ አነሳሽ እርሱ እንደነበር እና ሐዋእ ተከታይ ብቻ እንደነበረች ነው።

ምንም ይሁን ምን የሐዋእ ኃጢአት በርሷ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንጅ ወደ እንስት ልጆቿ የሚተላለፍ አይደለም። የአንዷን ነፍስ ኃአጢት ሌላዋ አትሸከምምና።

تِلْكَ أُمَّةٌ قَدْ خَلَتْ لَهَا مَا كَسَبَتْ وَلَكُم مَّا كَسَبْتُمْ وَلَا تُسْأَلُونَ عَمَّا كَانُوا يَعْمَلُونَ

“ይህች ያለፈች ሕዝብ ናት። ለርሷም የሥራዋ አላት። ለናንተም የሥራችሁ አላችሁ። እነርሱ ይሠሩት በነበረው እናንተ አትጠየቁም።”(አል-በቀራህ 2፤ 134)

ሁለቱም ፆታዎች በምንዳና ጀነትን በመጐናፀፍ እኩል መሆናቸውን ቁርኣን ሲያብራራ፡-

فَاسْتَجَابَ لَهُمْ رَبُّهُمْ أَنِّي لَا أُضِيعُ عَمَلَ عَامِلٍ مِّنكُم مِّن ذَكَرٍ أَوْ أُنثَىٰ بَعْضُكُم مِّن بَعْضٍ

“ጌታቸውም ልመናቸውን ተቀበለ። እኔ ከናንተ ውስጥ ሴትም ሆነ ወንድ የማንኛችሁንም (መልካም) ሥራ ከንቱ አላደርግም። ከፊላችሁ የከፊሉ አካል ነው (አለ)።” (ኣሊ ዒምራን 3፤ 195)

መልካም ሥራ እንደማይጠፋ በግልፅ አስቀምጧል። የወንድም የሴትም መልካም ሥራ። ሁለቱም ፆታዎች አንድ ናቸው። ከአንድ ዓይነት አፈር ከተመሳሳይ ቁስ ተፈጠሩ። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

مَنْ عَمِلَ صَالِحًا مِّن ذَكَرٍ أَوْ أُنثَىٰ وَهُوَ مُؤْمِنٌ فَلَنُحْيِيَنَّهُ حَيَاةً طَيِّبَةً وَلَنَجْزِيَنَّهُمْ أَجْرَهُم بِأَحْسَنِ مَا كَانُوا يَعْمَلُونَ

“ከሴትም ይሁን ከወንድ አማኝ ሆነው መልካም የሠሩትን ጥሩ ሕይወትን እናኖራቸዋለን። ምንዳቸውንም ከሠሯቸው መልካም ሥራዎች ይበልጥ መልካም በሆነው (መኖሪያ) እንመነዳቸዋለን።” (አን-ነሕል 16፤ 97)

وَمَن يَعْمَلْ مِنَ الصَّالِحَاتِ مِن ذَكَرٍ أَوْ أُنثَىٰ وَهُوَ مُؤْمِنٌ فَأُولَٰئِكَ يَدْخُلُونَ الْجَنَّةَ وَلَا يُظْلَمُونَ نَقِيرًا

“ከሴትም ከወንድም አማኝ ሆነው መልካም ሥራዎችን የሚሠሩ በእርግጥም ገነትን ይገባሉ። ቅንጣት ያህልም በደል አይደርስባቸውም።”(አን-ኒሳእ 4፤ 124)

የሴትን ልጅ የገንዘብ መብቶች በተመለከተ ኢስላም የበርካታ ዐረብና ዐረብ ያልሆኑ ሕዝቦች ሴትን ልጅ ከባለሃብትነትና ከውርስ የመከልከል፣ ወይም በሃብታቸው ያሻቸውን እንዳያደርጉ የማፈን፣ ወይም ሃብታቸውን በባሎቻቸው የመነጠቅ ልምድ ተቃረነ። ሃብት የመያዝ፣ ሃብታቸውን በሕጋዊ መንገድ ለሚፈልጉት ነገር የማዋል መብትን አፀደቀላቸው። ኑዛዜን እና ውርስን ደነገገላቸው። የመሸጥና የመግዛት፣ የማከራየት፣ የመስጠት እና የማዋስ፣ ወቅፍና ምፅዋት የመለገስ እና ሌሎችም ውሎች የመፈፀም መብትን አጐናፀፋቸው።

ለገንዘባቸውና ለጥቅማቸው በሕጋዊ መንገድ የመከራከር መብትም ከዚሁ ይመነጫል። ሴት ልጅ እንደ ወንድ ሁሉ ዕውቀት የመፈለግ መብት አላት። ከመብትም አልፎ ግዴታ ተደርጐባታል። ሐዲስ የሚከተለው ተላልፏል።

طلب العلم فريضة على كل مسلم

“ዕውቀት መፈለግ በሁሉም ሙስሊሞች ላይ ግዴታ ነው።”

በሁሉም ላይ። ፆታ አልተለየም። ይህ በዑለሞች አጠቃላይ ስምምነት የፀደቀ ነው። ሴት ልጅ ወደ መስጊድ ሄዳ የጀመዓ ሶላት መስገድም መብትም አላት። እንደ ወንዱ ሁሉ እርሷም የግዴታ ዒባዳዎችን የመፈፀም ግዴታ አለባት። ሶላት፣ ዘካ፣ ሐጅ፣ ፆም እና ሌሎችም የኢስላም መሠረታዊ ተግባራት የማከናወን ግዴታ አለባት። እንደ ወንዱ ሁሉ ምንዳ ታገኝባቸዋለች። ልክ እንደ ወንዱ ማኅበራዊ ኃላፊነትም አለባት።

وَالْمُؤْمِنُونَ وَالْمُؤْمِنَاتُ بَعْضُهُمْ أَوْلِيَاءُ بَعْضٍ يَأْمُرُونَ بِالْمَعْرُوفِ وَيَنْهَوْنَ عَنِ الْمُنكَرِ

“የወንድና የሴት አማኞች ከፊሉ የከፊሉ ረዳት ናቸው። በመልካም ያዛሉ። ከክፉ ይከለክላሉ።” (አት-ተውባህ 9፤ 71)

ጥበቃና ከለላ ለጠየቃት የመስጠት መብትም አላት። ከለላዋም ይከበርላታል። የአቡ ጧሊብ ልጅ ኡም ሃኒእ መካ በድል በተከፈተችበት ዕለት ከአጋሪዎች ለአንዱ ከለላ ሰጥታለች። በእርግጥ ወንድሟ ሊገድለው ፈለገ። ለነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰሰችው። “የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኔ ጥበቃና ከለላ የሰጠሁትን ሰው የእናቴ ልጅ ሊገድለው ያንገራግራል” አለቻቸው። የአላህ መልዕክተኛም፡- “አንች ከለላ የሆንሽለትን ከለላ ሰጥተነዋል” አሏት። (ቡኻሪና ሙስሊም)

_________

ይህ ፅሁፍ የተወሰደው ከዶ/ር ዩሱፍ አል-ቀረዳዊ በፅሐፍ “መካነቱል መርኣ ፊልኢስላም” ትርጉም በሀሰን ታጁ፣ ነጃሺ አሳታሚ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here