አንድ ወላጅ ልጅ ሲወለድለት ምን ማድረግ ይኖርበታል?
ከአላህ (ሱ.ወ) የተሰጠን ምርጡ ሸሪዓችን ከመሰረታዊ ዕውቀት ከትንሽ እስከ ትልቅ ምንም ያስቀረብን ነገር የለም። ልጅን በተመለከተም አሳዳጊዎችና ወላጆች በእውቀት ላይ ተመስርተው እንዲንቀሳቀሱ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ በአስተዳደጉ ዙሪያ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ግልፅ የሆኑ መመሪያዎችና ህግጋቶችን አስቀምጧል። ከነኚህ መመሪያዎች እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት
1. የእንኳን ደስ ያለህ የደስታ መግለጫ መልእክቶች
የአንድ አማኝ ደስታ የሌላውም ደስታ ነውና ልጅ ያገኘን ወንድም ደስታ መጋራት እጅግ የተወደደ ነው። ደስታውንም በውስጥ አምቆ መያዝ ሣይሆን በርሱ ደስታ እንደተደሰቱ መግለፅ መልካም ነገር ነው። ይህም የደስታውን ባለቤት ይበልጥ ደስ ከማሰኘቱም በላይ ትስስርን ያጠብቃል፣ ወንድማማችነትን ያጠነክራል፣ ማህበራዊ ግንኙነትን ያጎለብታል፣ በሙስሊሞች መካከልም መዋደድና መፋቀርን ይጨምራል። አግኝቶት ደስታውን ለመግለፅ ከአቅሙ በላይ ቢሆንበት እንኳ በዱዓእ የወንድሙን ደስታ መጋራት ይኖርበታል። አላህ የተወለደውን ልጅ እንዲባርክለት ጥሩና የተባረከ ዝርያም እንዲያደርግለት።
ቁርዓናዊ መልእክቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ልጅ በሚወለድበት ጊዜ መደሰትና ማስደሰት እንደሚገባ ይጠቁማሉ። አላህ (ሱ.ወ) የነቢዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ታሪክ ሲነግረን እንዲህ ብሏል።
“መልክተኞቻችንም ኢብራሂምን በ(ልጅ) ብስራት በእርግጥ መጡት። ሰላም አሉት። ሰላም አላቸው። ጥቂትም ሳይቆይ ወዲያውኑየተጠበሰን የወይፈን ስጋ አመጣ።እጆቻቸውም ወደ እርሱ የማይደርሱ መኾነቸውን ባየ ጊዜ ሸሻቸው። ከነሱም ፍርሃት ተሰማው።“አትፍራ እኛ ወደ ሉጥ ሕዝቦች ተልከናልና” አሉት። ሚስቱም የቆመች ስትኾን (አትፍራ አሉት) ሳቀችም። በኢስሐቅም አበሰርናት።ከኢስሐቅም በኋላ (በልጁ) በያዕቁብ (አበሰርናት)።” (ሁድ 11፤ 69-71)
በነቢዩ ዘከሪያ ታሪክ ላይ ደግሞ
እርሱም በጸሎት ማድረሻው ክፍል ቆሞ ሲጸልይ መላእክት ጠራችው። «አላህ በየሕያ ከአላህ በኾነ ቃል የሚያረጋግጥ ጌታም ድንግልምከደጋጎቹ ነቢይም ሲኾን ያበስርሃል» በማለት (መላእክት ጠራችው)። (ኣሊዒምራን 3፤24)
በሌላ የቁርዓን አንቀፅ ደግሞ
«ዘከሪያ ሆይ! እኛ በወንድ ልጅ ስሙ የሕያ በኾነ ከዚህ በፊት ሞክሼን ባላደረግንለት እናበስርሃለን» (አለው)። (መርየም 19፤70)
በታሪክ መፅሃፎች ከተላለፉልን ዘገባዎች መካከል ደግሞ ይህን እንመልከት
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በተወለዱ ጊዜ የአጎታቸው የአቡ ለሀብ ባሪያ ሱወይቢያ ነበረች “ዛሬ ለሊቱን ለዐብደላህ ልጅ ተወለደለት።” በማለት የብስራቱን ዜና ያወጀችው። አቡ ለሀብም ይህን አስደሳች ዜና ከርሷ በሰማ ጊዜ በውልደቱ በመደሰት ሱወይቢያን ከባርነት ነፃ አድርጓታል። ምንም እንኳ አቡለሀብ ከሃዲ ሆኖ ቢሞትም አላህ (ሱ.ወ) ይህን ድርጊቱን ግን ቆጥሮለታል። አቡ ለሀብ ከሞተ በኋላ በአውራ ጣቱ ጎን ከምትገኝ ጎድጎድ ካለች ቦታ አላህ አጠጥቶታል።” ቡኻሪ ዘግበውታል።
ሱሀይሊ እንደዘገቡት ደግሞ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) አጎት ዐባስ (ረ.ዐ) እንዲህ አለ “አቡ ለሀብ በሞተ ከወር በኋላ በመጥፎ ሁኔታ ላይ ሆኖ በህልሜ አየሁት። እሱም “ከናንተ ከተለየሁ በኋላ እረፍት አላገኘሁም። ነገር ግን ሰኞ ቀን ብቻ ቅጣቱ ይቃለልኛል።” አለኝ ብለዋል። ሰኞ ቀን ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱበት ቀን ነው ። ቀኑ ሱወይቢያ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) መወለዳቸውን ለአቡ ለሀብ አብስራ እሱም እሷን ነፃ ያለበት ነው።
በልጅ መወለድ የእንኳን ደስ ያለህ የደስታ መግለጫ መልእክት ማስተላለፍን በተመለከተ ኢማም ኢብኑ አልቀይም አልጀውዚ ቱህፈት አልመውሊድ በሚባለው ኪታባቸው ውስጥ ከአቢበክር ኢብኑ አልሙንዚር እንደዘገቡት ሀሰን አልበስሪ እንዲህ በማለት ነገሩን ብለዋል። አንድ ሰው ሀሰን አልበስሪ ወዳሉበት መጣ። አጠገቡም ልጅ የተወለደለት ሰውዬ ነበር። ሰውዬውም “በፈረሰኛው እንኳን ደስ ያለህ!” አለው። ሀሰንም “ፈረሰኛ ይሁን አህያ ምኑን ታውቃለህ?” አሉት። ሰውዬውም “እንግዲያውስ ምንድነው የምንለው ታዲያ?” በማለት ጠየቀ። ሀሰን አልበስሪም እንዲህ በል አሉት…
“ቡሪከ ለካ ፊል መውሁብ ወሸከርተል ዋሂብ ወሩዚቅተ ቢረሁ ወበለጋ አሹደሁ”
“የተሰጠህን ይባርክልህ። የሰጠህንም አመስጋኝ ሁን። ለበጎ ተግባሩመሩም የምትታደል ያድርግህ፤ይድግ ይመንደግ።”
ይህ የደስታ መግለጫ መልእክት ለሁሉም አዲስ ለተወለደ ልጅ የሚደረግ ነው። ወንድ ይሁን ሴት ልዩነት መደረግ የለበትም። ሙስሊሞች ይህን ነቢያዊ ሱና መተግበር በእጅጉ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ላይ ነው ያለነው። እነኚህንና የመሣሰሉትን ሱናዊ ነገሮችን መላመዳቸው የርስ በርስ ግንኙነታቸውን ያጠነክረዋል፣ ቤቶቻቸውን በደስታ ይሞላዋል፣ ወደበለጠ መዋደድ መቀራረብና አንድነትም ያመጣቸዋል።
2. በተወለደው ልጅ ጆሮ ላይ አዛን እና ኢቃማ ማድረግ የሚወደድ ስለመሆኑ
በሸሪዓችን አዲስ ለተወለደ ልጅ መደረግ ከሚገባው ነገር መካከል በቀኝ ጆሮው አዛን እና በግራ ጆሮ ኢቃማ ማድረግ ነው። ይህም ልጅ እንደተወለደ ወዲያውኑ መደረግ ይኖርበታል። አቡ ዳውድ እና ቱርሙዚ አቢራፍዕን በመጥቀስ “ሁሴን የፋጢማ ልጅ በተወለደ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በሁሴን ጆሮ አዛን ማድረጋቸውን አይቻለሁ።” ማለቱን ዘግበዋል።
ኢማም በይሀቂ እና ሌሎችም ከሀሰን ኢብኑ ዐሊ ባስተላለፉት ዘገባ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል
“ልጅ ተወልዶለት በቀኝ ጆሮው አዛን በግራው ደግሞ ኢቃማ የተደረገ እንደሆነ ኡሙ_ሲብያን አትጎዳውም።”
አዛንም ሆነ ኢቃማ የማድረጉ ሚስጢር ኢማም ኢብኑ አልቀይም በኪታባቸው ውስጥ እንደጠቀሱት “የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ጆሮውን ማንኳኳት ያለበት የጌታን ታላቅነትና ክብሩን የሚያስተጋባ የሆነው ታላቁ ጥሪና የሰው ልጅ መጀመሪያ ወደ እስልምና ሲገባ የሚመሰክርበት ሸሃዳ/ላኢላሀ ኢለላህ ሙሀመድ ረሱሉላህ/ መሆን ስላለበት ነው። ክስተቱ የሰው ልጅ ከዚህች ምድር ሲለቅ የአላህን አንድነት ቃል እንዲል /ተልቂን/ እንደሚደረግ ሁሉ ወደዚህች ምድር ሲመጣም ይህን ቃል እንደማስባል ነው። አዲሱ ልጅ ምንም እንኳ ባይታወቀውም አዛኑ ቀልቡ ላይ ተፅእኖ ሊፈጥር ይችላል የሚል አንድምታም አለው።
ከዚህም በተጨማሪ ሌላም ጥቅም አለው። እሱም አዛን ሸይጣንን ማባረሪያ መሳሪያ በመሆኑ ነው። አዲሱን ልጅ በተንኮሉ ሊነካው እስኪወለድ ድረስ የሚጠባበቅ ሲሆን የአዛንን ቃላት ሲሰማ ግን ይዳከማል፣ ይበሣጫል፣ ከዚህም አልፎ አካባቢውን ጥሎ ይሸሻል።
ሌላም ትርጉም አለው፡- ይህም የተወለደውን ወደ አላህ፣ ወደ ሃይማኖቱ (እስልምና) እና አላህን ወደማምለክ የመጥራቱ ጉዳይ ከሸይጣን ጥሪ እንዲቀድም ታስቦ ነው። ሸይጣን ከመንገድ ሣያስወጣው በፊት አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅን የፈጠረበት መንገድም ይሀው ነውና።” ብለዋል። ኢብኑልቀይም ትንተናቸውን ሲቋጩ “በርግጥ ከዚህም ባለፈ ሌላ ጥበብና ሚስጢርም ሊኖረው ይችላል።” ብለዋል።
ይህ ኢብኑ አልቀይም የጠቀሱት አዛንን የማድረጉ ጥበብ እና ሚስጢር የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የሰው ልጅ ነፍስ ተዘርቶበት ወደዚህች ዓለም ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እምነቱና አመለካከቱ የተስተካከለ እንዲሆን ምን ያህል እንደሚጠበቡና የሸይጣንና የስሜት የበላይነትን ለማስወገድ የቱን ያህል እንደሚጨነቁ ማሣያ ነው።
3. ልጅን ተህኒክ ማድረግ
ልጅ እንደተወለደ ወዲያውኑ ተህኒክ ማድረግ ሌላው ነቢያዊ ሱና ነው። ተህኒክ ማለት ተምርን በማኘክ ጣት ላይ ድርጎ አዲስ በተወለደ ህፃን ልጅ አፍ ውስጥ በማስገባት በቀስታ ወደ ግራና ቀኝ ማዳረስ ነው። ተምር የማይገኝ ከሆነ በማንኛውም ጣፋጭ በተለወሰ ነገር ማድረግ ይቻላል።
የተህኒክ የአስፈላጊነት ሚስጢሩ ምናልባትም በተህኒክ ወቅት የልጅን ምላስን በማንቀሳቀስ የአፍ ጡንቻዎችን ለማጠንከር ሊሆን ይችላል። ይህም አዲሱ ህፃን በተፍታታ ምላሱ የእናቱን ጡት ለመያዝና ለመምጠጥ ያስችለዋል። ተህኒክ ማድረግ ያለበት ሰው በአላህ ፍራቻ የሚታወቅ ቢሆን ይመረጣል። ምክኒያቱም መጀመሪያ ወደዚህች ምድር የመጣን ሰው መልካምና በአላህ ፍራቻ የተሻለ ሰው ቢነካው የአዲሱ ልጅ መልካምነት እንዲበዛ ይከጀላልና ነው።
ለዚህ አቋም የፊቅህ ጠበብት እንደ ማስረጃ ከጠቀሷቸው ሀዲሶች፡-
ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡተ በአቢ ቡረዳህ ሀዲስ አቢ ሙሳ እንዲህ ይላል “ልጅ ተወለደልኝና ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ይዤው መጣሁ። እርሣቸውም “ኢብራሂም” በማለት ስም አወጡለት። በተምርም የአፉን ውስጥ ለወሱ። አላህ እንዲባርከውም ዱዓእ በማድረግ መልሰው ሰጡኝ።”
ከዚህ ቀደም ባየነው የኡሙ ሱለይም (ረ.ዐ) ሀዲስም ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከአቢ ጦለሃ የተወለደውን ልጅ ተህኒክ እንዳደረጉና ስሙንም ዐብደላህ እንዳሉት አይተናል።
አልኺላል ደግሞ ሙሀመድ ኢብኑ ዐሊ የአህመድ ኢብኑ ሀንበል ሚስት እንዲህ ስትል ሰምቻታለሁ ብሏል። “ምጥ በያዘኝ ጊዜ አሣዳሪዬ/ባሌ ተኝቶ ነበር። እኔም “ጌታዬ ሆይ! እየሞትኩ ነው።” አልኩት። እሱም “አላህ ይፈርጅሽ።” አለኝ። እሱ እንዲህ እንዳለ ወዲያውኑ ሰዒድን ተገላገልኩ። ከመካ ያመጣነው ተምር ቤት ውስጥ ነበረና ያንን ተምር አምጡ ካለ በኋላ ለዐሊ እናት ይህን ተምር አኝኪና አፉ ውስጥ አላውሺ።” አላት። እሷም እንደተባለቸው አደረገች።
4.አዲስ የተወለደን ህፃን ፀጉር መላጨት የተወደደ ስለመሆኑ
በሰባተኛው ቀን አዲስ የተወለደን ልጅ ፀጉር መላጨትና መዝኖ በሚዛኑ ልክ ብርን ለድሆችና ለችግረኞች በምፅዋት መስጠት የተወደደ ነው። የዚህ ድርጊት ዓላማና ሚስጢሩ
- አንደኛ- የህፃን ልጅ ፀጉርን መላጨት ጥንካሬን ይጨምርለታል። የራስ ቅሉንም ክፍት ያደርግለታል። እንዲሁም የእይታን፣ የማሽተትና የመስማት ጥንካሬን ይጨምርለታል።(ኢብኑልቀይም ተህፋ ላይ ጠቅሰዎታል)
- ሁለተኛ- ፀጉሩን መዝኖ የኪሎውን ዋጋ ያህል ለድሆች መመፅወት ማህበራዊ ጥቅም አለው። በዚህም ድርጊት ድህነትን በመጠኑም ቢሆን መቀነስ ይቻላል። በማህበረሰቡ ውስጥም መተዛዘንና መተጋገዝን ያሣያል። ኢማም ማሊክ አልሙወጠዕ በተባለ ኪታባቸው ውስጥ ጀዕፈር ኢብኑ ሙሀመድ ከአባቱ ያወራውን እንዳወሱት ፋጢማ ረዲየሏሁ ዐንሃ የልጆቿን የሀሰን፣ የሁሴን፣ የዘይነብና የኡሙኩልሱምን ፀጉር ላጭታ በመመዘን በዚያው መጠን ብር መፅውታለች።” ብለዋል።
ኢብኑ ኢስሃቅ ከሙሀመድ ኢብኑ ዐሊ ኢብኑ አልሁሴን እንደዘገቡት ደግሞ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አንዲት ፍየል ለዐቂቃ አረዱና “ፋጢማ ሆይ! ፀጉሩን ላጭው። በሚዛኑ ልክም ብር ምፅዋት አድርጊ። ፋጢማም የተላጨውን ፀጉሩን መዘነች። ሚዛኑም የድርሃምና የግማሽ ያህል ድርሃም ዋጋ ነበረው።”
ከአነስ ኢብኑ ማሊክ በተላለፈልን ዘገባ ደግሞ ሀሰንና ሁሴን በተወለዱ በሰባተኛው ቀናቸው ፀጉር እንዲላጭ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)በማዘዝ በሚዛኑ ልክ እንደመፀወቱ ተነግሯል።
በዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባን ነጥብ አለ፡- ይሀውም የተወለደው ህፃን ልጅ ፀጉር ሙሉ በሙሉ ነው መላጨት ያለበት መሆኑ ነው። ምክኒያቱም ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ፀጉር ግማሽ ተላጭቶ ግማሽ ማስቀረትን ከልክለዋልና። ከመሃል በማስቀረት ዳር ዳሩን መላጭት፤ እዚህም እዚያም በመላጨት የተወሰነውን ማስቀረት፤ አሊያም መሃሉን በመላጨት ዳር ዳሩን ማስቀረት ወይም ደግሞ ከፊት በመላጨት የኋላውን በማስቀረት የሚደረጉ አለጫጨቶች ሁሉ ኢማም ኢብኑ አልቀይም እንዳሉት የተከለከሉ ናቸው። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሌላው ቀርቶ በፀጉር አቆራረጥ ጭምር ፍትህንና እኩልነትን እንድናሰፍን ነው የመከሩን። ይህም ሙሉ በሙሉ መላጨት አሊያም ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ማመሣሰል ነው። በሸሪዓችን ግማሽ ፀሃይ ግማሽ ጥላ ላይ መቀመጥ የተከለከለ ነው። በአንድ አግር ጫማ መሄድም የተከለከለ ነው። ነቢያዊ ምልከታዎች በርግጥም አስገራሚዎች ናቸው። ሱብሃነላህ!!
ሌላም ጥበብ አለው፡- ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) አማኙ ሙስሊም በማህበረሰቡ ውስጥ በተከበረና ሥርዓት ባለው ሁኔታ እንዲታይ ስለሚፈለጉም ጭምር ነው። ከፊሉን ፀጉር ተላጭቶ ከፊሉን ማስቀረት ግርማ ሞገስንና ውበትን የሚያደበዝዝ ከመሆኑም በላይ አንድ ሙስሊም ከነኚህ ወጣ ካሉ ባህሪያትና መስመር ከለቀቁ ግለሰቦች፣ እምነቶችና አመለካከቶች መገለጫ ከሆኑ ድርጊቶች እራሱን ማራቅ ስለሚኖርበት ነው።
ሆኖም ግን ዛሬ አብዛኞቹ ለዚህም ሆነ ለሌላው ኢስላማዊ እሴት ብዙም ሲጨነቁ አይስተዋልም። ከሸሪዓዊ ምልከታዎችም የሚያውቁት ጥቂቱን ምናልባትም ግዴታዎችን ብቻ ነው። ዲናዊ አስተምህሮ የእለት ተዕለት መኖሪያችንና መመሪያችን ነውና እያንዳንዷን ነገር ማወቅ፤ ያልገባን ከሆነም እንደሆነም መጠየቅ ይኖርብናል። አላውቅም ማለት ከተጠያቂነት አያድንም። በዲን ጉዳይ ችላ ማለት፤ ስለ ልጅ ኢስላማዊ አይታ ምን እንደሆነ አለማሰብና አለመጨነቅ ለዲኑ አለመጨነቅ ነውና ነገ በዐለማት ጌታ አላህ (ሱ.ወ) ፊት ያስጠይቃል።
በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት ህግጋት ምንም እንኳ የሚወደዱ ነቢያዊ ሱናዎች (ግዴታ ያልሆኑ) ቢሆኑም በነሱ መሥራት፣ በልጆቻችንና በቤተሰባቻችን በዘመዶቻቸን ላይ መተግበር ፈፅሞ ቸል ልንለው የማይገባ ድርጊት ነው። የሚወደዱ አሊያም ሱናዊ የሆኑ ነገሮችን ችላ ማለት ለግዴታውም አለመጨነቅን ያስከትላል። ይህም አካሄድ ቀስ በቀስ ወደ ግልጽ ጥመት እንዳያስገባ ይፈራል። የአላህን ህግጋት ማክበር ውዴታውን ያስገኛልና ወላጆች ይህን ጉዳይ በእጅጉ ሊያስቡበት ይገባል።
5.ለልጅ ሥም ማውጣት
ልጅ ሲወለድ እናት አባት ልጁ የሚጠራበት በማህበሰረሰቡም ዘንድ የሚታወቅበት ሥም የማውጣቱ ነገር የተለመደ ነው። ኢስላም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቷል። አጽንኦትም ችሮታል። ሙስሊሙ ማህበረሰቡ ስለሁኔታው ያውቅ ዘንድም በዚህ ዙሪያ ህግጋትና መመሪያዎችን አስተላልፏል። ጥቂቶቹን እንመልከት
5.1. ልጅ ሥም የሚወጣለት መቼ ነው?
ዋንኞቹ የሀዲስ ዘጋቢዎች ከሰሙራህ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል
“እያንዳንዱ ልጅ በዐቂቃው የታሰረ ነው። በሰባተኛው ቀኑ ትታረዳለች። ሥምም ይወጣለታል። ፀጉሩም ይላጫል።” ከሀዲሱ የምንረዳው ሥም መውጣት ያለበት በሰባተኛው ቀን መሆኑን ነው።
በተወለደበት ቀን ሥም መውጣት እንዳለበት የሚያመለክቱ ሶሂህ የሆኑ ሀዲሦችም አሉ። ከነኚህም መካከል ቡኻሪ እና ሙስሊም ከሰህል ብኑ አስ ሣዒዲ የዘገቡት ይጠቀሳል።
አልሙንዚር ኢብኑ ኡሰይድ በተወለደ ጊዜ ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ይዘውት መጡ። አቡ ኡሰይድ በተቀመጠበት ሁኔታ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኡሰይድን ጭናቸው ላይ አስቀመጡት። ነቢዩ ከፊት ለፊታቸው ያለ የሆነ ነገር ትኩረታቸውን ወሰደና ኡስይድ ልጁን እንዲቀበላቸው አደረጉ። ኋላም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “ህፃኑ የታለ?” አሉ። “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! መልሰነዋል።” አለ አቡ ኡሰይድ። “ስሙን ማን አላችሁት?” “እገሌ ይባላል።” አላቸው። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) “አልሙንዚር በሉት።” አሉ።
ኢማም ሙስሊም ከሱለይማን ኢብኑ አልሙጊራህ እሱ ደግሞ ከሣቢት በዘገበውና ከአነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) በተላለፈው ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ
“ዛሬ ሌሊቱን ልጅ ተወለደልኝ። በአባቴ ሥም በኢብራሂም ሰየምኩት።”
ከሁለቱ ሀዲሦች የምንረዳው ጉዳዩ አማራጮች እንዳሉት ነው። ልጅ በተወለደበት ቀን ሥም ማውጣትም ሆነ እስከ ሦስት ቀን አሊያም እስከ ዐቂቃው ቀን ማለትም ሰባተኛው ቀን ድረስ ማቆየት የሚቻል መሆኑን ነው።
5.2.ከሥም የሚወደድ እና የሚጠላ
ሥም የሰው ልጅ ወደዚህች ምድር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የአንድ ሰው መታወቂያ ሆኖ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይዘልቃል። ምድርን በሞት ከተሰናበተ በኋላም ቢሆን ሥሙ በመልካም ይሁን በመጥፎ ይጠራል። በመሆኑም ወላጅ ለልጁ ጥሩና ውብ የሆነ ሥም በማውጣቱ ረገድ በእጅጉ ሊያስብበት ይገባል። ነቢያችንም (ሰ.ዐ.ወ) በዚሁ ጉዳይ መክረዋል
አቡ ዳውድ ከአቢደርዳዕ (ረ.ዐ) እንዳስተላፉት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል
“እናንተ በትንሣኤ እለት በሥሞቻችሁና በአባቶቻሁ ሥም ነው የምትጠሩት። ስለዚህ ሥማችሁን አሣምሩ/ ቆንጆ ይሁን።”
ኢማም ሙስሊም ከዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ
“አላህ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሥሞች ዐብደላህ እና ዐብዱረህማን ናቸው።”
- ወላጆች ለልጆቻቸው አስቀያሚ የሆነ፤ መጥፎ ትርጉም ያዘለ፤ ሲጠሩበት የሚያሣፍራቸው፤ እንዲሁም ለሰዎች ተረባና መቀለጃ የሚዳርጋቸው ሥም ማውጣት የለባቸውም። ቱርሙዚ ከእናታችን ዓኢሻ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) መጥፎ ስሞችን ይቀይሩ ነበር።
- ቱርሙዚ እና ኢብኑ ማጀህ ከዐብደላህ ኢብኑ ዑመር እንዳስተላለፉት “ዑመር (ረ.ዐ) ዓሲያ (አመፀኛ/ እምቢተኛ) በመባል የምትጠራ ልጅ ነበረችው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጀሚላ (ቆንጂት) ብለው ሌላ ሰም አውጡላት።
- አቡዳውድ እንዳሉት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አልዓሲ፣ ዐዚዝ፣ ዑትላህ፣ ሸይጧን፣ አልሀከም፣ ጉራብ፣ ሀባብ የሚሉ ስሞችን የቀየሩ ሲሆን ሀርብ (ጦርነት) የሚባለውን ሲልም (ሰላም) አልሙድጠጅዕ (የተኛ) የሚባለውን (የተነሣ) በሚለው ቀይረውታል።
- ከዚህም ሌላ ወላጅ መጥፎ ገድ ያለባቸውን ሥሞች ከማውጣት ሊጠነቀቅ ይገባል። ቡኻሪ ከሰዒድ ኢብኑ አልሙሰየብ እሱም አባቱን ጠቅሶ እንዳስተላለፈው
“ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣሁና “ሥምህ ማነው?” አሉኝ። እኔም “ሁዝን/ሀዘን/ጭካኔ› አልኳቸው። እርሳቸውም “አንተ ሰህል /ገር ነህ” አሉኝ። እኔም “አባቴ ካወጣልኝ ሥም ውጭ መጠራት አልፈልግም።” አለ ኢብኑ ሙሰይብ ሲናገር “ከዚያን በኋላም ሀዘን ተለይቶት አያውቅም።”
- አማም ማሊክ ከየህያ ኢብኑ ሰዒድ እንደዘገቡት ደግሞ ዑመር ኢብኑ አልኸጧብ (ረ.ዐ) ለአንድ ሰው ‹ስምህ ማነው?› አሉት። ሰውየውም ‹ጀምረህ (ፍም)” አላቸው። “የማን ልጅ ነህ?” “የሺሃብ (ነበልባል)” አላቸው። “ከየት ነህ?” “ከሀረቃህ (አቃጣይቱ)” አላቸው። “የት ነው የምትኖረው” አሉት። “በሀረት አን ናር (በሞቀችው እሣት ውስጥ)” አላቸው። “ከየትኛው?” አሉት። “ከለዟ” አላቸው። ዑመር (ረ.ዐ) ለሰውየው እንዲህ አሉት “ቶሎ ወደ ቤተሰቦችህ ተመለስ በርግጥ ጠፍተዋል ተቃጥለዋል።” ሰውየው ሲመለስ ሁኔታው ዑመር እንዳሉት ሆኖ ነበረ ያገኘው።
- እንዲሁም ለአላህ (ሱ.ወ) ብቻ ባህሪና መጠሪያው የሆኑ ሥሞችን ማውጣት አይፈቀድም። በመሆኑም አሀድ /አንዱ፣ ሰመድ /መጠጊያ፣ ኻሊቅ/ ፈጣሪ፣ ረዛቅ/ ለጋሽ እና የመሳሰሉ ሥሞችን መራቅ ያስፈልጋል።
- አቡ ዳውድ እንደዘገቡት ሃኒዕ ከጎሣዎቹ ሰዎች ጋር በመሆን ወደ መዲና በመጣ ጊዜ አቢ አልሀከም (የፍርዱ አባት) በማለት ይጠሩት ነበር። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጠሩትና “ፈራጅ አላህ ነው ፍርድም ወደርሱ ነው። ለምንድነው አባልሀከም ተብለህ የተጠራሀው?” አሉት። እሱም “ህዝቦቼ በሆነ ነገር ላይ የተወዛገቡ እንደሆነ ወደኔ ይመጡና በመካከላቸው እፈርዳለሁ። ሁለቱም ወገኖች ፍርዱን ወደው ይቀበላሉ። ለዚህ ነው› አላቸው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “ይህ ምንኛ መልካም ነው። ልጆች አሉህ ?ማን ማን ይባላሉ?” አሉት። ሹረይህ፣ ሙስሊም፣ ዐብደላህ የሚባሉ ናቸው።” አላቸው። ‹ትልቅየው ማነው?” አሉት። “ሹረይህ” አላቸው። “እንግዲያውስ አንተ አቡ ሹረይህ /የሹረይህ አባት ነህ/።” አሉት።
- ኢማም ሙስሊም ከአቢ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ
“በትንሣኤ ቀን አላህ (ሱ.ወ) እጅግ የሚቆጣበትና ሲበዛ መጥፎው “መሊከል አምላክ” ንጉሰ ነገስት ብሎ እራሱን በሰየመው ነው። ንጉስ ከአላህ ውጭ የሌለ ሲሆን።”
- እንዲሁ በጣም ፍፁም በሆነ መልኩ ስኬትን የሚያጎሉና የሚያደላድሉ ኋላ ላይ ሣይሆኑ ሲቀሩ ቁጭት ሊያመጡ የሚችሉ ሥሞችን አለማውጣት የተሻለ ነው። ለምሳሌ …አፍለህ( ስኬታመው)፣ ናፍዕ (ጠቃሚ)፣ ረባህ (አትራፊ)፣. የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። ሙስሊም አቡዳውድ እና ቱርሙዚ ከሰሙራህ ኢብኑ ጁንዱብ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ
“አላህ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ቃላት አራት ናቸው- ሱብሃነላህ፣ አልሀምዱሊላህ፣ ላ ኢላሀ ኢለላህ እና አላሁ አክበር። ልጅህን የሣር ብለህ አትሰይመው። ረባህም አትበለው፤ ነጂህም እንዲሁ፤ አፍለህ ብለህም ሥም አታውጣለት።”
- ሌላው ደግሞ ከአላህ ውጭ የሚመለኩ የሆኑ ሥሞችን ከማውጣት መጠንቀቅ ተገቢ ነው ። ለምሣሌ ዐብዱልዑዛ (የዑዛ ባሪያ)፣ ዐብዱልከዕባ (የከዕባ ባሪያ)፣ ዐብዱ ነቢ(የነቢዩ ባሪያ) እና የመሣሰሉትን ያጠቃልላል። እነኚህ ሁሉ የተከለከሉ ናቸው።
- በመጨረሻም ከሌሎች እምነቶችና ባህሎች የሚያመሣስሉ የሆኑ ትርጉም አልባና ወፈፌ ስሞችንም መራቅ የተሻለ ነው። ምክኒያቱም እስልምና የራሱ የሆኑ ውብ እና ምርጥ ሥሞች አሉት። ሙስሊሙ ማህበረሰብም እነኚህን ሥሞቹን ማሳደግና በሰፊው ማስተዋወቅ ይኖርበታል። በዓለም ላይ የሚበዛው ሥም ሙሀመድ ነው ሲባል ይህ ለእስልምናችን ትልቅ ክብር ነው።
- ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) የነቢያት ሥሞችን እንዲሁም ዐብደላህ (የአላህ ባሪያ) እና ዐብደረህማንን (የረህማን ባሪያ) የመሣሰሉ ሥሞችን ለልጆቻችን እንድናወጣ ነው የመከሩት። አቡዳውድ እና ነሣኢ ከአቢ ወህብ አልጀሸሚ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)
“በነቢያት ሥም ተጠሩ። አላህ ዘንድ ተወዳጆቹ ሥሞች ዐብደላህ እና ዐብዱረህማን ናቸው። እውነተኞቹ ሃሪስ እና ሀማም ሲሆኑ እጅግ መጥፎዎቹ ደግሞ ሀርብ እና ሙራህ ናቸው።” ብለዋል።
5.3. ልጅን “የእገሌ አባት” ብሎ መጥራት ሱና ነው
ከልጆች ተርቢያ(እነፃ) ኢስላም ካስቀመጣቸው መንገዶች በልጅ ተክኒያ መደረግ /የእገሌ አባት ተብሎ መጠራት/ ይጠቀሳል። ይህም በርከት ያሉ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን እንደሚከተለው ለማየት ተሞክሯል።
- በልጅ ውስጥ የመከበር ስሜትን ይፈጥራል። የትላልቆችን የክብር ደረጃ በማግኘት ስሜቱ ከፍ ይላል።
- የማህበራዊነትን ባህሪ ያዳብራል። ይህም የትላልቆቹን ደረጃና በሌሎች አክብሮት የማግኛ እድሜ እንደደረሰ ስለሚሰማው ነው።
- ገና በልጅነቱ ከትላልቆችም ሆነ ከታናናሾቹ ጋር የአቀራረብ እና የንግግር ሥርዓትን እንዲለማመድ ይረዳዋል።
ለዚህም ይመስላል ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ልጆችን ልጅ ሣይኖራቸው “የእገሌ አባት” በማለት የሚጠሩት። ይህም ድርጊታቸው ወላጆች የርሣቸውን መንገድ እንዲከተሉ ለማመላከት፣ ትምህርት ለመስጠትና ልጆቻቸውንም በዚህ መልኩ ይጠሩ ዘንድ ለማስተማር ይመስላል።
አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላል። “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰዎች ሁሉ የምርጥ ሥነምግባር ባለቤት ናቸው። አቡ ዑመይር የሚባል ወንድም ነበረኝ። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) “የዑመይር አባት ሆይ! ኑገይር (መጫወቻ አሻንጉሊቱ) ምን ሆነ?” ይሉት ነበር።”
- የነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ባለቤት እናታችን ዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ ልጅ አልነበራትም። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ግን “ኡሙ ዐብደላህ/የዐብደላህ እናት/. በመባል እንድትጠራ ፈቅደውላታል። ዐብደላህ የዙበይር ልጅ ሲሆን እህቷ አስማእ ቢንት አቢ በክር አስ ስዲቅ (ረ.ዐ) ደግሞ እናቱ ናት።
- አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) ልጅ ሳይወለድለት በፊት አቢ ሃምዛ /የሃምዛ አባት/ በመባል ይጠራ ነበር።
- ታላቁ የሀዲስ ዘጋቢ አቡሁረይራም ምንም ልጅ ሣይኖራቸው በዚሁ ሥም ይጠሩ ነበር።
- ከነኚህ ሁሉ የምንረዳው አንድ ሰው ልጅ ባይኖረው እንኳን የእገሌ አባት/እናት ተብሎ ቢጠራ ችግር የሌለው መሆኑን ነው።
- የነቢዩ የልብ ወዳጅ የሆኑት አቡበክር (ረ.ዐ) በክር የሚባል ልጅ ባይኖራቸውም በዚሁ ሥም ይታወቁ ነበር።
- ዑመር ኢብኑ አልኸጧብ (ረ.ዐ) ደግሞ ሀፍስ የሚባል ልጅ ሣይኖራቸው ‹አቡ ሀፍስ/የሀፍስ አባት/ ይባሉ ነበር።
- አቡዘርም እንዲሁ ናቸው። ዘር የሚባል ልጅ ሣይኖራቸው አቡ ዘር /የዘር አባት/ በሚለው መጢሪያቸው ይታወቁ ነበር።
- ጀግናው ኻሊድ ኢብኑ አልወሊድ አቢ ሱለይማን በመባል የሚታወቁ ሲሆን ሱለይማን የሚባል ልጅ አልነበራቸውም። በዚህ ዙሪያ በርካታ ምሣሌዎችን ማንሣት ይቻላል።
ባጠቃላይ ትላልቆችን “የእገሌ አባት” ብለን እንደምንጠራው ሁሉ ልጅን የእገሌ አባት ብሎ መጥራት ተወዳጅ ነገር ነው። ይህን ለማድረግ ልጅ ሊኖረው አለያም በልጁ ስም መሆኑ የግድ አይደለም።
ከልጆች የስም አወጣጥ ጋር ተያይዞ የሚከተሉትን ተጨማሪ ነጥቦችን ማየት ይቻላል።
1. አባትና እናት በልጅ ሥያሜ ላይ የተወዛገቡ እንደሆነ ሥም መስጠቱ የአባት መብት ነው የሚሆነው። ከላይ ያየናቸው ሀዲሦችም ይህንኑ ያመለክታሉ። በቅዱስ ቁርዓንም አላህ (ሱ.ወ) ልጅ መጠራት ያለበት በአባት መሆኑን አላህ (ሱ.ወ) ገልፆልናል….
ادْعُوهُمْ لِآبَائِهِمْ هُوَ أَقْسَطُ عِنْدَ اللَّهِ ۚ فَإِنْ لَمْ تَعْلَمُوا آبَاءَهُمْ فَإِخْوَانُكُمْ فِي الدِّينِ وَمَوَالِيكُمْ ۚ وَلَيْسَ عَلَيْكُمْ جُنَاحٌ فِيمَا أَخْطَأْتُمْ بِهِ وَلَكِنْ مَا تَعَمَّدَتْ قُلُوبُكُمْ ۚ وَكَانَ اللَّهُ غَفُورًا رَحِيمًا
(አል አህዛብ 33፤5)
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለደላቸውን ልጅ “በአባቴ ሥም ኢብራሂም ብዬ ሥም አወጣሁለት” ማለታቸው ይታወሣል።
2. ወላጆች የልጁን ሥነ-ልቦና ሊጎዳ የሚችል ስም ከማውጣት በሸሪአው ተከልክለዋል። ለምሣሌ ባሪቾ፣ አጭሬ፣ ሸፋፌ እና በመሳሰሉት …
5.4. ልጅን አቢ ልቃሲም ብሎ መጥራት
አቢል ቃሲም የታላቁ ነቢያች (ሰ.ዐ.ወ) መጠሪያ ነው። ዑለማኦች በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሥም ማለትም ሙሀመድ ብሎ መጠራት ክልክል አለመሆኑን ተስማምተውበታል። የነቢያትን ሥም ለልጆቻችን እንድናወጣ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እራሣቸው አመላክተዋልና። ነገር ግን በመጠሪያ ሥማቸው አቢልቃሲም በሚለው መጠራትን በተመለከተ ዑለማኦች የተለያያ አቋም ይዘዋል።