የልጆች አስተዳደግ በኢስላም (ክፍል-2)

0
4490

5. የእስልምናን ጥቅም ከልጅ ፍቅር ማስቀደም

ወላጅ ልጅን መውደዱና ለአብራኩ ክፋዩ እጅግ መሳሳሳቱ ተገቢ ቢሆንም ይህ ፍቅር ከልክ አልፎ እንዳይሄድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በእስልምና ከአላህ (ሱ.ወ) በላይ መወደድ የሚገባው ማንም ምንም የለም። ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) መውደድ ይከተላል። አንድ ሰው የአላህ ጉዳይና የልጁ ጉዳይ የተጋጩበት እንደሆነ ሁሌም የፈጣሪውን ጉዳይ ማስቀደም ይኖርበታል። የኢስላም ጥቅም ከሁሉም ጥቅም በላይ ነው። የአላህ ፍቅር ከየትኛውም ፍቅር ጋር ሊነፃፀር አይገባም።

ቀደምት ሰሃቦች (ረ.ዐ) በዚህ አቋማቸው ይታወቃሉ። በርካታ ቦታዎች ላይ ተፈትነውበታልም። ነገር ግን ፅኑ ኢማን ስለነበራቸው መሰናክሎችን በብቃት አልፈዋል። ከነሱ በኋላ የመጡ መልካም ሰዎችም ፈለጋቸውን ተከትለዋል። ትልቁ ዓላማቸው የነበረው ለኢስላም ፍፁም በሆነ መልኩ በመኖር የአላህን ውዴታ ማግኘት ነውና ይህንኑ ለመወጣት ጠንክረው ሰርተዋል። በአላህ (ሱ.ወ) መንገድ ላይ የትኛውንም መስዋእት ሁሌም ለመክፈል ዝግጁ ነበሩ።

ታላቁን ሶሃባ ዑባዳህ ኢብኑ ሷሚትን (ረ.ዐ) የግብፁ ንጉስ ሙቀውቂስ የሮማዊያን ከባድ ሀይል በመጥቀስ ሊያስፈራራው ሞከረ። በገንዘብና ውድ ነገሮችም ሊደልለው ፈለገ። ዑባዳህ ግን እንዲህ በማለት ነበር የጠንካራ ሙስሊምን አቋም የገለፀለት “አንተ ሰው! እራስህንም ሆነ ጓደኞችህን አታታልል… የሮሞችን ስብስብ አስመልክቶ ስለ ቁጥራቸው ስለ ብዛታቸው ለሰነዘርከው ማስፈራሪያ በርግጥ እኛ ከነሱ የምንልቅ አይደለንም። ነፍሴ በእጁ በሆነች ጌታ እምልሃለሁ። የምታስወሩት ነገር እውነት ቢሆን እንኳን ፈርተን ከአቋማችን የምንመለስ አይደለንም። እኛ ከናንተ ስንገጥም ከሁለት መልካሞች አንዱን አናጣም። ድል ካደረግናችሁ የዚህችን ዓለም ጥቅም (ምርኮ) እናገኛለን። ድል ካደረጋችሁን (ከተሰዋን) ደግሞ የአኺራን ስኬት እንጎናጸፋለን። ክቡር የሆነውና ልቅናው ከፍ ያለ ጌታ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል

فَلَمَّا فَصَلَ طَالُوتُ بِالْجُنُودِ قَالَ إِنَّ اللَّهَ مُبْتَلِيكُمْ بِنَهَرٍ فَمَنْ شَرِبَ مِنْهُ فَلَيْسَ مِنِّي وَمَنْ لَمْ يَطْعَمْهُ فَإِنَّهُ مِنِّي إِلَّا مَنِ اغْتَرَفَ غُرْفَةً بِيَدِهِ فَشَرِبُوا مِنْهُ إِلَّا قَلِيلًا مِنْهُمْ فَلَمَّا جَاوَزَهُ هُوَ وَالَّذِينَ آمَنُوا مَعَهُ قَالُوا لَا طَاقَةَ لَنَا الْيَوْمَ بِجَالُوتَ وَجُنُودِهِ قَالَ الَّذِينَ يَظُنُّونَ أَنَّهُمْ مُلَاقُو اللَّهِ كَمْ مِنْ فِئَةٍ قَلِيلَةٍ غَلَبَتْ فِئَةً كَثِيرَةً بِإِذْنِ اللَّهِ وَاللَّهُ مَعَ الصَّابِرِينَ

ከጥቂትም ጭፍራ በአላህ ፈቃድ ብዙን ጭፍራ ያሸነፈች ብዙ ናት፡፡ አላህም ከታጋሾች ጋር ነው፡፡(በቀራህ 2፤249) አለው።

ዑባዳህ ንግግሩን በመቀጠል

“ከኛ መካከል ዘወትር ጠዋት ማታ አላህ ሸሃዳን/ በመንገዱ መስዋእት መሆንን/ እንዲሰጠውና ወደ ሀገሩ፣ ቤተሰቡና ልጁ እንዳይመልሰው የማይለምን ማንም የለም። ከኋላችን ትተን የመጣነው ቤተሰብም ሆነ ልጅ ሁሉ ጭንቀታችን አይደለም። ሁላችንም ቤተሰባችንን ተሰናብተንና ለአላህ ትተን ነው የመጣነው። ሀሣባችን ሁሉ በአላህ መንገድ ላይ መታገልና የሱን ቃል ከፍ ማድረግ ነው‘በኑሮው በኩል ችግርና የተጣበበ ሁኔታ ላይ ናችሁ።’ ላልከኝ ደግሞ እኛ ሰፋ ባለ ድሎት ውስጥ መሆናችንን ልነግርህ እፈልጋለሁ። የዚህች ዓለም ጥቅም ሁሉ ለኛ ቢደረግ ከዚህ አሁን ካለንበት በላይ ከዚህች ዓለም የምንፈልገው ምንም የለምበማለት አስረግጦ ነገረው።

ይህ የዑባዳ ኢብኑ ሷሚት አቋም የሁሉም የቀደምት መልካም የዲን አያቶቻችን አቋም ነው። ይህ ሁሉ ቁርጠኝነትና ፍፁም በሆነ መልኩ ለአላህ (ሱ.ወ) የመኖር ፅናት ሊገኝ የቻለው የያኔዎቹ ሰዎች የአላህን (ሱ.ወ) ቃል ለመተግበር ካላቸው ውስጣዊ ስሜትና ጉጉት የተነሣ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

قُلْ إِنْ كَانَ آبَاؤُكُمْ وَأَبْنَاؤُكُمْ وَإِخْوَانُكُمْ وَأَزْوَاجُكُمْ وَعَشِيرَتُكُمْ وَأَمْوَالٌ اقْتَرَفْتُمُوهَا وَتِجَارَةٌ تَخْشَوْنَ كَسَادَهَا وَمَسَاكِنُ تَرْضَوْنَهَا أَحَبَّ إِلَيْكُمْ مِنَ اللَّهِ وَرَسُولِهِ وَجِهَادٍ فِي سَبِيلِهِ فَتَرَبَّصُوا حَتَّى يَأْتِيَ اللَّهُ بِأَمْرِهِ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ

አባቶቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁም፣ ሚስቶቻችሁም፣ ዘመዶቻችሁም፣ የሰበሰባችኋቸው ሀብቶችም፣ መክሰሩዋንየምትፈሩዋት ንግድም፣ የምትወዷቸው መኖሪያዎችም እናንተ ዘንድ ከአላህና ከመልክተኛው በርሱ መንገድም ከመታገል ይበልጥየተወደዱ እንደኾኑ አላህ ትእዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ተጠባበቁ» በላቸው አላህም አመጸኞች ሕዝቦችን አይመራም(ተውባህ9፤24)

ወደ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንመለስና የዘመናችን ታላቅ የዳእዋ ሰው የኢማም ሀሰን አልበናን አቋም ደግሞ እንመልከት። ኢማሙ በዒድ ቀናት እየዞሩ በከተማው ዳርቻና በየጎዳናው የሚገኙትን የሙስሊም ወጣቶችን ሁኔታ መቃኘት ልምዳቸው አድርገው ነበር። በአንድ ወቅት ለዚሁ ጉዳይ ፕሮግራም በያዙበት ቀን ልጃቸው ሰይፈልኢስላም በጠና ታመመ። በዚህን ጊዜ ሚስታቸው እንዲህ አለቻቸው “በዛሬው የዒድ ቀን ከኛ ጋር ዋልና ባንተ እንፅናና። ከታመመው ልጅህም ጎን ሁን።” ኢማሙም የመንገደኛ ቦርሣቸውን በእጃቸው እንደያዙ “አላህ በፀጋው ልጄን ካዳነልኝ ለሱ ምስጋናና ውዳሴ ይገባው። ይሞታል ብሎ ውሣኔውን ካስተላለፈ ግን አያቱ የመቃብርን መንገድ እጅግ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡” በማለት የሚከተለውን የቁርዓን አንቀፅ እያነበበላት ወጣ።

قُلْ إِنْ كَانَ آبَاؤُكُمْ وَأَبْنَاؤُكُمْ وَإِخْوَانُكُمْ وَأَزْوَاجُكُمْ وَعَشِيرَتُكُمْ وَأَمْوَالٌ اقْتَرَفْتُمُوهَا وَتِجَارَةٌ تَخْشَوْنَ كَسَادَهَا وَمَسَاكِنُ تَرْضَوْنَهَا أَحَبَّ إِلَيْكُمْ مِنَ اللَّهِ وَرَسُولِهِ وَجِهَادٍ فِي سَبِيلِهِ فَتَرَبَّصُوا حَتَّى يَأْتِيَ اللَّهُ بِأَمْرِهِ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ

አባቶቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁም፣ ሚስቶቻችሁም፣ (ተውባህ 9፤24)

በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለዲን ቅድሚያ መስጠት ማለት እንዲህ ነው!። ይህ አቋም የአላህን ውዴታ ከማንኛውም ውዴታ ቃሉንም ከየትኛውም ቃል የማስበለጥ ውጤት ነው። በተለይ ወደ አላህ (ሱ.ወ) መንገድ የሚጣሩ ይህን ዓይነቱን ባህሪ መጎናፀፍ ይኖርባቸዋል።

ሙስሊም ወላጆች ከመቼውም ጊዜ በላይ እስልምናን መውደድ ይኖርብናል፡፡ በአላህ መንገድ መታገልና ወደ መንገዱ መጥራትም በቀልባችንና ሰውነታችን ላይ ሊነግስ ይገባል። ይህ ሲሆን ነው እስልምና የምንመኘው ደረጃ ሊደርስ የሚችለው። የነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ህዝቦችም ክብርን የሚያገኙት።

ኢማናቸው እንዲሟላላቸውና ቀልባቸውን ሰርስሮ ገብቶ ጥፍጥናውን ለማጣጣም ለሚከጅሉ ሰዎች የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ምን እንዳሉ እንመልከት።

ቡኻሪ ከአነስ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

“ሦስት ነገሮች ያሉት ሰው የኢማንን ጥፍጥና አገኘ። አላህ (ሱ.ወ) እና መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ከሌሎች ነገሮች በበለጠ ወደሱ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ፣ አንድን ሰው ለአላህ ብቻ ብሎ እንጂ ለሌላ ላይወድ፣ አንድ ሰው ወደ እሣት መወርወርን እንደሚጠላው ሁሉ ወደ ክህደት መመለስን አብዝቶ ሲጠላ።”

የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከራስ ነፍስ፣ ከልጅ፣ ከወላጅም ሆነ ከማንኛውም ዱኒያዊ ጥቅም በላይ አስበልጦ መውደድን በተመለከተ ደግሞ ቡኻሪይ እንደዘገቡት ኡመር ኢብኑ አልኻጧብ (ረ.ዐ) ለአላህ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ)

“የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ከነፍሴ በስተቀር ከሁሉም በላይ አንቱ ከኔ ዘንድ ተወዳጅ ነዎት።” አላቸው።  ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) “አንዳችሁምአላመናችሁም ከነፍሱ በላይ ወደርሱ ዘንድ ተወዳጅ እስካልሆንኩ ድረስ።” አሉ። ዑመርም (ረ.ዐ) “ባንቱ ላይ መፅሀፍን ባወረደው ጌታእምላለሁ ከነፍሴም በላይ እወድዎታለሁ።” አላቸው። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) “አሁን ትክክል ነህ ዑመር ሆይ! (አሁን እምነትህ ሞላ)።”አሉት።

እኛ ሙስሊሞች በዚህች ምድር ላይ ከዲኑ ስሜት በላይ የትኛውም ስሜት ሊበልጥብን አይገባም። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)

“አንዳችሁም አላመናችሁም። ስሜታችሁ እኔ ይዠ የመጣሁትን ነገር ፍፁም በሆነ መልኩ እስካልተከተለ ድረስ።” ማለታቸው ተዘግቧል።

ቡኻሪና ሙስሊም ባስተላለፉት ሌላ ዘገባ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል

“ከሀብቱ፣ ከልጁ፣ ከገንዘቡና ከሰዎች ሁሉ በላይ እኔ በርሱ ዘንድ ተወዳጅ ካልሆንኩ በቀር አንዳችሁም አታምኑም።”

6. ለመልካም አስተዳደግ ሲባል ልጅን መቅጣት

ልጅ ትንሽ ሆኖ በእናት አባቱ ቤት ውስጥ እስካለ ድረስ ተከታታይ ትምህርትና የበለጠ እንክብካቤ ያስፈልገዋልና ወላጆች እሱን ሊያስተካክል የሚችሉትንና ያዋጣል የሚሉትን ነገሮች ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህም ልጅ በተሟላ የእስልምና እሴትና ባማረ የማህበራዊ ሥርዓት ግንኙነት ላይ ያድግ ዘንድ ያግዘዋል።

እስልምና ልጅን በመልካም ሁኔታ ለማሣደግ የራሱ የሆነ መንገድ አለው። ወላጆች ልጃቸውን ከማኩረፍና ከማግለል ይልቅ ምክርና ልስላሴ የሚያዋጣ መሆኑን ካወቁ ይህንኑ ማድረግ ይኖርባቸዋል። መቆጣትና ማኩረፍ ይበልጥ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙ ደግሞ ወደ መምታቱ ከመፍጠን መቆጠብ ይኖርባቸዋል። በሁሉም አማራጮች ልጅን ማስተካከሉ የከበደ እንደሆነ ደግሞ ጉዳትን በማያስከትል መልኩ ቀለል ያለ ምት በመምታት ልጅን መቅጣትም ችግር የለውም። ባህሪውን ገርቶ ስርዐት ሊያስይዘው ይችላልና።

ውድ ወላጆች! ኢስላማዊ የልጆች እነፃን አስመልክቶ መልካም ምሳሌ ይሆናችሁ ዘንድ የሚከተሉትን የነቢዩና የሰሀቦችን ድርጊት በአንክሮ ተመልከቱት።

ልጅን በእዝነት፣ በተለሳለሰ ሁኔታ ማስተማርና መምከርን በተመለከተ ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ዐምር ኢብኑ አቢ ሰለማ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ “ልጅ ሆኜ በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ቤት ውስጥ በማድግበት ወቅት ምግብ ለመብላት ስንቀርብ እጄ በትሪው ላይ ወዲህና ወዲያ ትዞር ነበር። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉኝ

“አንተ ልጅ ሆይ! የአላህን ስም አውሳ (ቢስሚላህ በል)። በቀኝ እጅህ ብላ። በሚቀርብህ በኩልም ብላ።”

ቡኻሪና ሙስሊም ከሰህል ኢብኑ ሰዕድ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት ደግሞ ለአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የሚጠጣ ነገር መጣና ከላዩ ላይ ጠጡ። በቀኛቸው በኩል አንድ ልጅ ነበር። በግራቸው ደግሞ ትላልቅ ሰዎች ነበሩ። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለልጁ

ለነሱ(ለትላልቆቹ) እንድሰጣቸው ትፈቅድልኛለህን?” አሉት። አለሳልሰው እያግባቡት ነበር። ልጁም ለነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) “ወላሂ አይሆንም። ካንቱ በሚደርሰኝ ድርሻዬ ማንንም አላስቀድምም።” ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) በእጁ ላይ አስቀመጡለት። ይህ ልጅ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ እንደሆነ ይነገራል።

ልጅን ሲያጠፋ ማኩረፍን /አለማናገርን/ በተመለከተ ደግሞ ቡኻሪ እና ሙስሊም ከአቢ ሰዒድ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከኸዝፍ /በጣት ጠጠርን ከማስፈንጠር/ ከለከሉ። እንዲህም አሉ

“ኸዝፍ ታዳኝን አይገድልም ጠላትን አይሰብርም። ነገርግን ዐይንን ያጠፋል። ጥርስን ይሰብራል።”

በተያያዘ ዘገባ “ለኢብኑ ሙገፈል ዘመድ የሆነ ልጅ በጣቱ ጠጠር አስፈነጠረ። ልጁ ትንሽ ነበር። አቢ ሰዒድም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከማስፈንጠር ከልክለዋል፡፡ “እሱ ለአደን አይጠቅምም…” ብለዋል፡፡ በማለት ከለከለው። ልጁ ግን ተመለሰበት። “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ማስፈንጠርን ከልክለዋል እያልኩህ መልሰህ ታስፈነጥራለህን? ሁለተኛ አላናግርህም፡፡” አለው፡፡

ልጅን ለማስተካከል መምታት የሚቻል ስለመሆኑ ደግሞ ይህን ዘገባ እንመልከት፡፡ አቡ ዳውድ እና ሃኪም ከዐምር ኢብኑ ሹዐይብ ከአባቱ እንዲሁም ከአያቱ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ

“ልጆቻችሁን ሰባት አመት ሲሞላቸው በሰላት እዘዟቸው፡፡ አሥር አመት ሲሞላቸው (አልሰግድም ብለው ካስቸገሩ) ምቷቸው፡፡ በመኝታም ለያዩዋቸው(ለየብቻ ይተኙ )፡፡”

ይህ ሥርዓት የማስያዝ ሁኔታ የታዘዘው ልጅ ገና በልጅነት ዕድሜ ላይ ሣለ ነው፡፡ ወደ ወጣትነት ዕድሜ ከገባና ትልቅ ሰው ወደመሆኑ የተጠጋ እንደሆነ ግን አካሄዱ ከዚህ ይለያል፡፡ ልጅ በምክር የማይመለስ ከሆነና በጥመቱም የገፋ እንደሆነ ከድርጊቱ እስኪመለስ ወላጅ እስከመጨረሻው ሊያኮርፈው ይገባል፡፡ የሚከተሉትን ሀዲሦች እንመልከት

ጦበራኒ ከኢብኑ አባስ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ

“አስተማማኙ የመተሳሰሪያ ገመድ ኢማን (እምንት)ነው፡- ለአላህ ብሎ መወዳጀት፣ ለአላህ ብሎ ጠላትነትን ማወጅ፣ ለአላህ ብሎ መውደድና ለአላህ ብሎ መጥላት ነው፡፡”

ኢማም ቡኻሪ (ረ.ዐ) በኪታባቸው “እንቢ ያለን ሰው ማኩረፍ ይበቃል› በሚለው ምዕራፍ ሥር ከዕብ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለተቡክ ዘመቻ ሲሄዱ በቀረ ጊዜ ከዕብ “ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሙስሊሞች እኛን እንዳያናግሩ ለሃምሣ ቀናት ከልክለው ነበር፡፡” ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡ በወቅቱ እነ ከዕብ ሰፊዋ መሬት እስክትጠባቸውና ነፍሣቸውም እስክትጨነቅ ድረስ የሚያናግራቸው፣ ሰላም የሚላቸው ሆነ የሚቀማመጣቸው አንድም ሰው አላገኙም ነበር፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ተውባቸው ተቀባይነት ማግኘቱን በቁርዓኑ ውስጥ እስካወረደበት ጊዜ ድረስ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተወሰኑ ሚስቶቻቸውን ለመቆጣት እና ሥርዓት ለማስያዝ አኩርፈዋቸው እንደነበርም ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢማም ሱዩጢ እንደዘገቡት ደግሞ ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር እስከሞቱበት እለት ድረስ ልጃቸውን አኩርፈው ነበር፡፡ ይህም የሆነው አንድ ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የነገሩትን ሀዲስ ልጃቸው ተግባር ላይ ባለማዋሉ ነበር፡፡

ይህ በኢስላምና በኢማን ላይ በሆነበት ሁኔታ ጥፋቶችን ሲያጠፋ ነው፡፡ ሆኖም ጥፋቱ ብሶ ወደ ክህደት የገባ እንደሆነ ደግሞ ከርሱ ጋር ግንኙነት አይታሰብም፡፡ ተበሩእ (ከሱ ራስን ማጥራት) ኢማኑ የሚያዘው ትንሹ ነገር ነው፡፡

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑትን ሕዝቦች አላህንና መልክተኛውን የሚከራከሩትን ሰዎች፤ አባቶቻቸው፣ ወይም ልጆቻቸው፣ወይም ወንድሞቻቸው፣ ወይም ዘመዶቻቸው ቢኾኑም እንኳ የሚወዳጁ ኾነው አታገኛቸውም፡፡ እነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ እምነትንጽፏል፡፡ ከእርሱም በኾነ መንፈስ ደግፏቸዋል፡፡ ከሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑያገባቸዋል፡፡ አላህ ከእነርሱ ወዷል፡፡ ከእርሱም ወደዋል፡፡ እነዚያ የአላህ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ንቁ! የአላህ ሕዝቦቸ እነርሱ ምኞታቸውንየሚያገኙ ናቸው፡፡ (ሙጃደላህ 5822)

በሌላ የቁርዓን ሱራ ደግሞ

ኑሕም ጌታውን ጠራ፡፡ አለምጌታዬ ሆይ! ልጄ ከቤተሰቤ ነው፡፡ ኪዳንህም እውነት ነው፡፡ አንተም ከፈራጆች ሁሉ ይበልጥ ዐዋቂነህ፡፡” (አላህም) “ኑሕ ሆይ! እርሱ ከቤተሰብህ አይደለም፤ እርሱ መልካም ያልሆነ ሥራ ነው፤ በርሱ ዕውቀት የሌለህንም ነገርአትጠይቀኝ፤ እኔ ከሚሳሳቱት ሰዎች እንዳትሆን እገስጽሀለሁ» አለ፡፡ (ሁድ 11 45-46)

በሌላ የቁርዓን አንቀፅ ደግሞ

ኢብራሂምንም ጌታው በቃላት (በሕግጋት) በፈተነውና በፈጸማቸው ጊዜ (አስታውስ)እኔ ለሰዎች መሪ አድራጊህ ነኝ» አለው፡፡ከዘሮቼም (አድርግ)” አለ፡፡ ቃል ኪዳኔ በዳዮቹን አያገኝም አለው፡፡ (በቀራ 2124)

ከነኚህ ሁሉ የቁርዓን አንቀፆች የምንረዳው ነገር ልጅ ያጠፋ እንደሆነ ለማስተካከል ማኩረፍ፣ መዝጋትም ሆነ ማግለል የሚቻል መሆኑን ነው፡፡ በእስልምና መተሣሰር በደም፣ በቋንቋ፣ በጥቅም፣ በኢኮኖሚም ሆነ በሌላ ነገር ከመተሣሰር የበለጠ ነውና፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here