ልጅሽን ከቁርዓን ጋር ለማስተሣር የሚረዱ 25 ሀሣቦች

0
15202

የሀሣቡ ዋና ዓላማ

  1. ልጅን ቁርዓን እንዲወድ ማድረግ
  2. ልጅ የቁርዓን ሂፍዝ/በቃል ማጥናት/ እንዲቀልለትና እንዲገራለት ማድረግ
  3. ልጅ በቋንቋም ሆነ በቁርዓን እውቀት እንዲበለፅግ ማድረግ።

(ሀሳቦቹ ከ 5 እስከ 10 ደቂቃ ያህል ጊዜ ብቻ የሚፈልጉ ናቸው።)

ቁርዓን የአላህ (ሱ.ወ) ቃል ነው። ይህን የተከበረን ቃል ለልጅ ማስተማርና ማውረስ ታላቅ ሥራ ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “በላጫችሁ ቁርዓንን የተማረና ያስተማረ ነው።” ብለዋል።

ወላጆች በተለይም ከልጅ ጋር ጥብቅ ግንኘነት ያላት እናት ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ሀሣቦች ከልጅ ሁኔታና የግንዛቤ አቅም ጋር በሚጣጣም መልኩ በተደጋጋሚና ያለማቋረጥ እንድትሠራበት እንመክራለን።

1. ነፍሠጡር ሆነሽ ሣለ ቁርዓንን አዳምጭ

አንዲት እናት በእርግዝናዋ ወቅት የምትገኝበት መንፈሣዊም ሆነ ሥጋዊ ሁኔታ ከፅንሱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። በእርግዝናዋ ወቅት ቁርዓን በማድመጥ ላይ የምትዘወትር እናት መንፈሣዊም ሆነ ሥጋዊ እርካታ የምታገኝ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። እርካታው በሷ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ሆዷ ውስጥ ላለው ልጇም ይተርፋል። እናት የቁርዓንን ቋንቋ ዐረቢኛን ብታውቅም ባታውቅም ተፅእኖው ተመሣሣይ መሆኑ እጅግ የሚገርም የአላህ (ሱ.ወ) ተዓምር ነው። ይህም አላህ (ሱ.ወ) በቅዱስ ቁርዓኑ ውስጥ “አዋጅ አላህን በማውሳት ልቦች ሁሉ ይረካሉ።” ያለውን የሚያረጋግጥ ነው። ስለሆነም እናት ሆይ! ልጅሽ የቁርዓን ተፅእኖ እውስጡ ቀርቶ ያድግ ዘንድ በየቀኑ የተወሰኑ የቁርዓን አንቀፆችን ማንበብ ልማድሽ ይሁን።

2. በምታጠቢበት ወቅትም ቁርዓንን አዳምጭ

የሚጠባ ህፃን ዙሪያውን በሚያካብቡት ነገሮች ተፅእኖ ሥር የሚወድቅ ስለመሆኑ በሳይንስ ተረጋግጧል። በዚህ እድሜ የህፃኑ የመስሚያ ህዋሣት አገልግሎት ይጀምራሉ። የሰማውን ነገር ተቆጣጥሮና ተርጉሞ እንደ ትልቅ ሰው መመለስ አሊያም መተግበር ባይችልም እንኳ በውስጡ ያኖራቸዋል። ጡት ከጣለ በኋላና እድሜው እየጨመረ ሲሄድ ግን በውስጡ ያጠራቀማቸው ነገሮች ቀስ በቀስ ካሉበት ይወጣሉ። በቀን ውስጥ ለተወሠነ ጊዜ ለአምስት እና አሥር ደቂቃ ያህል ልጅን ቁርዓን ማሰማት (ለምሣሌ ፡ ጧት አምስት ማታ አምስት ደቂቃ) በውስጡ የሚያከማቸውን የቁርዓን ቃላትና ዐ.ነገር ያበዛለታል ማለት ነው። ኋላ ላይ አድጎ ቁርዓን መሀፈዝ/በቃሉ ማጥናት/ ቢፈልግ እርሾ ነበረውና ሂፍዙ ይገራለታል።

3. ቁርዓንን እሱ ፊት አንብቢ

አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጆችን በትክክለኛ የተውሂድና የበጎ ሥራ አመለካከት ላይ ነው የፈጠረው። ክርስቲያን አሊያም አይሁድ በማድረግ ከቀናው መንገድ የሚያስወጡት ወላጆቹ ናቸው። ቁርዓን ማንበብን ጨምሮ አንዲት እናት ልጇ ፊት አንድ በጎ ነገር የፈፀመች እንደሆነ ልጅ ወደዚያ ነገር መሣቡ አይቀሬ ነው። ልጅሽ ፊት ሆነሽ ቁርዓንን በምታነቢበት ወቅት ልጅ እንዳንች መሆን ምኞት ውስጡ ይሠረፃል። አብራችሁ ስታነቡ ደግሞ ቁርዓንን ይበልጥ እንዲወድ ያደርገዋል። ልጅ ፊት ቁርዓንን ማንበብ “ተማር፤ አንብብ” ብሎ ከማዘዝ በበለጠ የተሻለ ውጤት አለው። ይበልጥ የሚመረጠው ደግሞ አባትና እናት በየቀኑ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሰብሰብ ብለው ከልጆቻቸው ጋር ቁርዓንን ማንበቡ ነው።

4. ቁርዓንን በስጦታ መልክ ስጭው

ይህም ልጅ የራሱ የሆነ ቁርዓን እንዳለው እንዲሠማው ያደርጋል። በዚህም ውስጡ ደስ ይሠኛል። ተደጋጋሚ አንስቶ ከፍቶ ለማየትም ቅርብ ይሆንለታል። ከዚህም ባለፈ ከቁርዓን ጋር ልዩ ግንኙነት እንዲኖረውና በየጊዜውም ሣይሠለች እንዲያነብ ምከሪው።

5. ቁርዓን የጨረሠበትን ቀን አክብሪለት

ቁርዓን መማር የእውቀቶች ሁሉ የበላይ የስኬቶችም ሁሉ ቁንጮ ነው። ቁርዓን በጁዞች (እርከኖች) የተከፋፈለ እንደመሆኑ ልጅሽ ከቁርዓን የተወሰነውን ጁዝ ያከተመ እንደሆነ ደስታሽን ለመግለፅና ለስኬቱም እውቅና ለመስጠት እኩዮቹ የሆኑ ጓደኞቹን በማጋበዝ መጠነኛ ዝግጅት አድርጊለት። በዝግጅቱም ላይ አነስተኛ ስጦታ ስጪው። ይህን ማድረጉ ልጅ የተቀረውን የቁርዓን ክፍል ቶሎ ለመጨረስ እንዲጓጋ ሞራል ይሆንለታል።

6. የቁርዓን ታሪኮችን ተርኪለት

ልጆች በከፍተኛ ሁኔታ ትረካን ይወዳሉ። በመሆኑም ከልጅሽ የግንዛቤ ደረጃ ጋር ሊሄድ በሚችል መልኩ ቃላቶችን ጭምር በመምረጥ በቁርዓን ውስጥ የሚገኙ ታሪኮችን ንገሪው። ትረካሽን ደግሞ ባለማስፋትና ባለማናዛዛት በቁርዓን ውስጥ በተቀመጠው መልኩ ብቻ አድርጊ። መቋጫሽም ከቁርዓን አንቀፅ በመጥቀስ ይሁን።

7. በትናንሽ የቁርዓን ምእራፎች ዙሪያ ውድድር አዘጋጂለት

ይህም ውድድር በርሱና በወንድሞቹና እህቶቹ አሊያም ከራሱ ጋር ሊሆን ይችላል። ከዕድሜው ጋር የሚመጣጠን ጥያቄና መልስ በማዘጋጀት ስለ ቁርዓን ያለው እውቀትና ግንዛቤ እንዲሠፋ አድርጊ።

8. የሚታዩ ተፈጥሮአዊ ነገሮችን ከቁርዓን አንቀፆች ጋር በማስተሣሰር አስታውሽው

ለምሣሌ፡- ሰማይ፣ መሬት፣ ፀሃይ፣ ጨረቃ፣ ባህር፣ ውሃ፣ ቀን፣ ለሊትንና የመሳሰሉትን በማንሣት ስለነኚህ ነገሮች በቁርዓን ውስጥ ምን እንደተባለ በትረካ መልክ ንገሪው። ይህም ልጅሽ በቁርዓን እንዲመሠጥ ያደርገዋል።

9. ከቁርዓን ውስጥ አንዳንድ ቃላቶችን በመምዘዝ በየትኛው የቁርዓን ምእራፍ ውስጥ እንደሚገኝ ጠይቂው

ልጅሽ የደረሰበትን እውቀትና ግንዛቤ በማመዛዘን አንዳንድ ቁርዓን ውስጥ የተጠቀሱ ቃላቶችም ሆኑ አንቀፆች በየትኛው ምእራፍ ውስጥ እንደሚገኙ ጠይቂው። ይህም ልጅ ከቁርዓን ይበልጥ እንዲተሣሰርና ከጥናቱ እንዳይርቅ ያግዘዋል።

10. በሄደበት ቦታ ሁሉ ቁርዓንን የማይለየው ጓደኛው አድርጊለት

ለምሳሌ ከቤት ሲወጣ አንድ የቁርዓን ጁዝ ወይንም ምዕራፍ በቦርሣው ውስጥ አድርጊለት። ይህም ፍራቻም ሆነ አለመረጋጋት ባጋጠመው ጊዜ ቁርዓን ከርሱ ጋር እስካለ ድረስ ደህንነትና እርጋታ እንዲሠማው ያደርገዋል።

11. በቁርዓን እና እውቀቱ ዙሪያ ከሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ጋር አስተሣስሪው

በዓለማችን ላይ የቁርዓንን አስተምህሮ የሚያሠራጩ በርካታ የቴሌቭዥን እና የሬዲዮ ጣቢያዎች አሉ። ልጅሽ እነኚህን ጣቢያዎች እንዲከታተል አድርጊው። በቁርዓን ዙሪያ የተሠሩ ማራኪ ካሴቶችንና ሲዲዎችንም አቅርቢለት። ይህም ከእኩዮቹም ሆነ ከሌሎች ትላልቅ ታዋቂ ቃሪኦች ጋር እንዲተዋወቅና እንደነርሱ ጥሩ አቀራርና ድምፅ እንዲኖረው ይበልጥ ያነሣሣዋል።

12. አጋዥ ነገሮችን ግዥለት

ቁርዓንን በተዋበና ቀለል ባለ መልኩ እንዲማር የሚረዱ፣ ለሂፍዝ እገዛ የሚያደርጉለት፣ እራሱን ቀርፆ መልሦ የሚያዳምጥበትንና ሌሎች የተለያዩ ሶፍትዌሮችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በየጊዜው በመከታተል ግዥለት። ይህም ልጅሽ ለቁርዓን ይበልጥ እንዲማረክ ያደርገዋል።

13. በውድድሮች ላይ እንዲሣተፍ አበረታችው

ልጆች መፎካከር ይወዳሉ። የዚህን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ አጋጣሚውን በመጠቀም ልጅሽ ቁርዓንን ለማወቅና ለመሀፈዝ ይበልጥ እንዲነሳ ገፋፊው። በውድድሮች አጋጣሚ ያየሻቸውን ልጆች እንደምሣሌ በማንሣት “የእገሌ ልጅ..” እያልሽ እልህ ውስጥ እንዲገባና በላጭ ሆኖ እንዲገኝ አድርጊው። ሽልማቶችና ስጦታዎች ልጅ በርትቶ ቁርዓን እንዲያጠና ያነሣሱታል። ልጅሽ መጀመሪያ አካባቢ ሽልማትን ዓላማው አድርጎ ቢነሣም እንኳ ኋላ ላይ ከጣእሙ የተነሣ በቁርዓን ተፅእኖ ሥር መውደቁ አይቀርም። ሽልማቶቹ ቁርዓን ተከታትሎ እንዲይዝና እንዳያቋርጥ ምክኒያት ይሆኑታል። ተወዳዳሪዎች እንዳሉት ካወቀ ደግሞ ስንፍናና ድብርት በተጫነው ጊዜ የማንቂያ ደወል ይሆኑለታል።

14. ቁርዓን በሚቀራበት ወቅት ድምፁን ቅረጭው

ልጅ ትንሽ ነገር ያስደስተዋል። የራሱን ድምፅ መልሦ በሚሰማበት ወቅትም ልዩ ስሜት ይሠማዋል። ቀረፃውን መልሦ ሲያዳምጥ በድምፁም ሆነ በአቀራሩ ላይ ያስተዋለውን ችግር ለማሻሻልና ነጥሮ ለመውጣት ይነሣሣል።

15. በትምህርት ቤትም ሆነ በሌላ ቦታ በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ እንዲሣተፍ ገፋፊው

ልጅሽ በትምህርት ቤት ደረጃ በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ መሣተፉ ኋላ ላይ ለሚያጋጥመው ውድድር መለማመጃና መተዋወቂያ ይሆንለታል። ከአቻ ተማሪዎችና ከአስተማሪዎቹ አድናቆት የተቸረው እንደሆነ ደግሞ ለበለጠ ሥራ የሞራል ስንቅ ይሆነዋል። በልጅ ላይ በተለይ የተለየ ተሠጥኦ የታየ እንደሆነ ይህን ችሎታውን ለአደባባይ ለማብቃት ወላጅና አስተማሪዎች አብረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

16. የቁርዓን ታሪኮችን እንዲነግርሽ ጋብዥው

ብዙዎቻችን ልጆቻችንን ወደ ቁርዓን ቤት ከመላክ ውጭ ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉና በትምህርታቸውም የት እንደደረሱ አንከታተልም። ልጅ የተማረውን የሰማውንና ያየውን ነገር ለወላጆች ማካፈል ደስታ ይሠጠዋል። ታዲያ እኛም ልጃችን ሲያናግረንና ከኛ የሆነ ነገር ሲፈልግ ልናዳምጠው ይገባል። ከቁርኣንም የሆነ ታሪክ አንስቶ ሊነግረን ሲሞክር በቁምነገር ልናዳምጠውና በታሪኩ ላይ ግድፈቶች አሊያም አግባብ በሆነ መልኩ መረዳቱን ካየን ልናስተካክልለት ይገባል። ልጃችን ሁሌም እንዲሰማን ብቻ ሳይሆን እንዲያወራልንም መገፋፋት ይኖርብናል።

17. ኢማም ሆኖ እንዲያሰግድ አበረታችው

እናት ይህንኑ እቤቷ ውስጥ የሠፈር ልጆችን ሰብስቦ እንዲያሰግድና በሌላም በተለያየ መልኩ እንዲለማመድ ልታደርገው ትችላለች። ይህም ልጅ ገና ትንሽ ሆኖ እንደ ትልቅ እንዲያሰብና ትልቅ ዓላማ እንዲኖረው ያግዘዋል።

18. ቤት ውስጥ በሚደረግ የቁርዓን ስብሰብ ላይ እንዲካፈል አድርጊው

ቤተሰብ በሙሉ ቁርዓን ለመቅራት በሚሰባሰብበት ወቅት ልጅ በቦታው ላይ ቢገኝ የቁርዓን ተፅእኖና ጣእሙን በተለያየ መልኩ እንዲረዳ ያስችለዋል። ቤተሰብ ለዚህ ጉዳይ መሰባሰቡ ለቁርዓን ያላቸውን ልዩ ቦታና ክብር ያሳያል። ስለሆነም ቤተሰቦች በቀን ለአምስት ደቂቃም ቢሆን ማድረግ ይኖርባቸዋል።

19. በመስጅድ ውስጥ በሚደረጉ ቁርዓን ሀለቃዎች ላይ እንዲገኝ አድርጊው

ልጅሽ በቂርዓት ሀለቃዎች /ስብስቦች/ ላይ መገኘቱ የበለጠ ልምድ እንዲያገኝና ስህተቱንም እንዲያርም መንገድ ይከፍትለታል። ለውድድርም ያነሣሣዋል።

20. ስለ ቁርዓን ጥያቄዎችን ጠይቂው

ከእድሜውና ግንዛቤው ጋር ሊሄዱ የሚችሉትን ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን በማዘጋጀት ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲያዳበር እርጂው።

21. የቁርዓን ቃላት ትርጉም የያዘ መዝገበ ቃላት አዘጋጂለት

22.  ቀለል ያሉ የቁርዓን ትርጉሞችን አመቻቺለት

ልጅ እንደ እድሜው ሁሉ በእውቀትም ከትንሽ ወደ ትልቅ ደረጃ ነው ማደግ ያለበት። ስለሆነም የቁርዓንን ትርጉም እድሜውን በሚመጥን መልኩ እንዲረዳ ትናንሽ ሱራዎች ላይ የተሠሩና ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጁ የቁርዓን ትርጉሞችንና ትንታኔዎችን አቅርቢለት። ይህ አካሄድ ልጅ የቁርዓንን ትርጉምና የዑለማኦችን አባባል ሣይረዳ በቀጥታ ወደ ቁርዓን ትርጉም መግባትን እንዳይዳፈር ያደርገዋል።

23.   ከእውቀት ባለቤቶችና ዓሊሞች ጋር አገናኚው

ልጅ ውሎውን ከዑለማኦችና ምሁራኖች ጋር ያደረገ እንደሆነ ፍራቻና እፍረት ይወገድለታል። በራስ የመተማመን ስሜቱም ይጨምራል። ጥያቄዎችንም በነፃነት መጠየቅ ይለማመዳል። በዚህም ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል። ዓለማችን በዚህ መንገድ በርካታ ትላልቅ ዓሊሞችን አፍርታለች።

24. ትምህርቱን ከቁርዓን ጋር ማገናኘት

እናትም ሆነች የልጅ አስተማሪ ልጅ ከትምህርት ቤት ውሎው ያገኛቸውን እውቀቶች በማንሣት ከቁርዓን ጋር በማያያዝ ልጅ በቁርዓን ተዓምራዊነት እንዲደመም ማድረግ ይኖርባቸዋል።

25.   እለታዊ ክስተቶችን ከቁርዓን መልእክቶች ጋር ማገናኘት

ለምሣሌ ልጅሽ አንድ ነገር ያባከነ አንደሆን ቁርዓን በብክነት ዙሪያ ምን እንደሚል ሌላም ከቁርዓን አስተምህሮ ጋር የሚጋጭ ነገር የፈፀመ እንደሆነም ቁርዓን በዚያ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚናገርና የክልከላውም ምክኒያት ምን እንደሆነ በማብራሪያ ጭምር አስረጅው። ይህም ልጅ ቁርዓንን ከማንበብ አልፎ አስተምህሮቱንም ገና በልጅነቱ በእለት ተእለት ኑሮው ላይ እንዲተገብር ያግዘዋል።

ከነኚህ ሀሳቦች እንዴት መጠቀም እንችላለን

  1. ሁሉንም ሀሣቦች በአንድ ገፅ ወረቀት ላይ አስፍሪ
  2. እንደ ቀላልነታቸው ደረጃ በመመደብ ወደ ትግበራው ግቢ።
  3. በሦስት ሀሣቦች ላይ ዘውትሪ። በነኚያ ሀሣቦችም ልጅሽን ምሪ። ጥቅሙ ይዳረስ ዘንድ ደግሞ ሀሳቡን ለሌሎችም አስተላልፊ።
  4. ልጅሽ ባደገ ቁጥር እንደ እድሜው እርከን ከአንዱ ሀሣብ ወደ ሌላኛው ተሸጋገሪ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here