የልጆች አስተዳደግ በኢስላም (ክፍል-1)

0
9613

የሰው ልጅ በዚህች የምድር በሚኖረው ጊዜያዊ ቆይታ ደስታን ሊጨምሩለት ከሚችሉ ነገሮች መካከል ልጅ ማግኘት አንዱ ነው። ለወላጅ ልጅ የሠጠ ጌታ ከወላጅ ጋር ለልጅ የሚያስፈልገውን ነገርም ፈጥሯል። ከየትኛውም የሰው ልጅ ግንኙነት በላይ የወላጅ ልጅ ትስስር ጥብቅ ይሆን ዘንድ አላህ (ሱ.ወ) የውዴታ፣ የርህራሄና የእዝነት ስሜቶችን በወላጆች ልብ ውስጥ አኑሯል። አንድ ወላጅ ልጅ ባገኘበት ቅፅበት ወደ ላይ ወደ አሣዳጊ ወላጆቹ መመልከት ትቶ ወደታች አዲስ ወደመጣው ፍጥረት በስስትና በእዝነት የሚመለከትበትን ሁኔታ ስናይ እውነትም ይህ ስሜት ተፈጥሮአዊ ድባብ የነገሠበት መሆኑን በትክክል እንረዳለን። ወላጆች እነኚህን መልካም ስሜቶች በውስጣቸው አምቀው እንድይዙ ሣይሆን ከልጆቻቸው አንፃር ተግባር ላይ ያውሉ ዘንድ ኢስላም አዟል። ቀጥሎ ስለነኚህ ስሜቶችና ከልጅ አስተዳደግ አኳያ መደረግ ስለሚገባቸው ቁምነገሮች በዝርዝር ለመዳሠስ እንሞክራለን።

1.     እናትና አባት ልጅን በመውደድ ስሜት ላይ ነው የተፈጠሩት

አላህ (ሱ.ወ) ልጅን የሙውደድና ለሱ የመራራት ስሜትን ወላጆች ልብ ውስጥ ባያኖር ኖሮ የወላጅና የልጅ ግንኙነት ትርጉም ባጣ፤ ‹የሰው ልጅ› የሚባለው ፍጡርም ምድር ላይ የመቆየቱ ነገር ባጠራጠረ ነበር። እናትና አባት ልጆቻቸውን ተንከባክቦ በማሳደግና እነሱን ትልቅ ደረጃ ላይ ለማድረስ እንዲለፉና እንዲደክሙ ትልቅ ስንቅ የሚሆናቸውም ይሄው ስሜት ነው። ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለፅ ቁርዓን የተጠቀመውን ድንቅ አገላለፅ እንመልከት።

الْمَالُ وَالْبَنُونَ زِينَةُ الْحَيَاةِ الدُّنْيَا

‹‹ገንዘብና ልጆች የቅርቢቱ ህይወት ጌጦች ናቸው።… ›› (አል-ከህፍ ቁ- 46)

ልጆች ትላልቅ ከሚባሉ የአላህ ፀጋዎች መካከል ናቸውና ልጅ የሰጠ ጌታ አላህ (ሱ.ወ) መመስገን ያለበት ስለመሆኑ ሌላ የቁርዓን አንቀፅ ይጠቁመናል።

وَأَمْدَدْنَاكُمْ بِأَمْوَالٍ وَبَنِينَ وَجَعَلْنَاكُمْ أَكْثَرَ نَفِيرًا

‹.. ገንዘቦችና ወንዶች ልጆችንም ጨመርንላችሁ። በወገንም የበዛችሁ አደረግናችሁ።› (አል-ኢስራእ ቁ- 6)

በሌላ የቁርዓን አንቀፅም አላህን ፈሪ በሆኑ መልካም ሰዎች ጎዳና ላይ የተጓዙ እንደሆነ ልጆች ምርጥ የዐይን ማረፊያዎቻችን እንደሆኑ ይነግረናል።

وَالَّذِينَ يَقُولُونَ رَبَّنَا هَبْ لَنَا مِنْ أَزْوَاجِنَا وَذُرِّيَّاتِنَا قُرَّةَ أَعْيُنٍ وَاجْعَلْنَا لِلْمُتَّقِينَ إِمَامًا

‹እነዚም ጌታችን ሆይ! ከሚስቶቻችን እና ከዘሮቻችን ለዐይኖች መርጊያን ለኛ ስጠን። አላህን ለሚፈሩትም መሪዎች አድርገን። የሚሉት ናቸው።› (አልፉርቃን ቁ- 74)

ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን እዝነት፣ ጥልቅና እውነተኛ ፍቅር የሚገልፁ በቁርዓን ውስጥ በርካታ አንቀፆች አሉ።ይህ በርግጥም አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅን የፈጠረበት ባህሪ ነውና ማንም ሊቀይረው አይችልም።

2.     ለልጆች አዛኝ መሆን የአላህ (ሱ.ወ) ስጦታነው።

እጅግ ምርጥ ከሆኑትና አላህ (ሱ.ወ) በወላጆች ቀልብ ውስጥ ካኖራቸው ስሜቶች መካከል ለልጆች ማዘንና መራራት አንዱ ነው። ይህ ባህሪ እጅግ የተከበረና በልጆች እድገት ላይም ትልቅ ተፅእኖ ያለው ሲሆን ለበለጠ ውጤትም ያግዛቸዋል።

ከእዝነት ባዶ የሆነ ቀልብ መለያ ባህሪው ጭካኔ፣ ድርቀት እና ክፋት ነው። ውጤቱም የከፋ ነው። ይህን ባህሪ በተላበሱ ወላጆች መካከል ያደጉ ልጆች ጥሩ ሥነ-ምግባር አይኖራቸውም፤ በጥመታቸውም ይታወቃሉ፤ ለማህበረሰቡም ሆነ ለሀገሪቱ ሸክም ከመሆን ባለፈ ጥቅም የላቸውም።

ምርጡ ሃይማኖት እስልምናችን የእዝነት ባህሪን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥቷል። አማኞችም ሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ይህን ባህሪ እንዲላበሱ አሣስቧል። አቡዳውድ ባስተላለፉት ዘገባ የአላህ መልእክተኛ ((ሰ.ዐ.ወ)) እንዲህ ብለዋል፡-

“ለታናሻችን የማያዝን የታላላቆቻችንን ሀቅ/መብት/ የማይገነዘብ ከኛ አይደለም።”

ኢማም ቡኻሪይ ደግሞ አቡ ሁረይራን (ረ.ዐ) በመጥቀስ ይህን ዘገባ አስተላልፈዋል

‹‹አንድ ሰው ልጅ ይዞ ወደ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣ። ሰውዬው ልጁን እቅፍ ያደርገዋል። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) (ይህን ባዩ ጊዜ) ‹ታዝንለታለህን?› አሉት ሰውዬውም ‹እንዴታ› አለ። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ‹አንተ ለሱ ከምታዝነው በላይ አላህ (ሱ.ወ) ላንተ ያዝናል። እርሱ የአዛኞች ሁሉ አዛኝ ነውና።› አሉት።››

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰሃቦቻቸው መካከል ለልጁ የማያዝን ሰው ካጋጠማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ያወግዙታል። ለቤቱ፣ ለቤተሰቡም ሆነ ለልጆቹ መልካምና በጎ ወደሆነ ነገርም ያመላክቱታል።

ኢማም ቡኻሪይ እናታችን ዓኢሻን (ረ.ዐ) በመጥቀስ እንደዘገቡት

‹አንድ የገጠር ሰው ወደ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣና ‹ልጆቻችሁን ትስማላችሁ እንዴ? እኛ እኮ አንስማቸውም።› አለ። የእዝነት ተምሣሌት የሆኑት ነቢያችንም (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉት ‹አላህ (ሱ.ወ) ከቀልብህ ውስጥ እዝነትን ያነሣ እንደሆነ እኔ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?!›

አሏሁ አክበር! በርግጥም ምንኛ ያማረ አባባል ነው!!

ከአቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) በተላለፈ በሌላ ዘገባ ደግሞ

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሀሠን ኢብኑ ዐሊይን (የልጃቸው ፋጢማ ልጅ) ሣሙ። አጠገባቸው አቅረዕ ኢብኑ ሃቢስ አትተሚሚ ተቀምጦ ነበር። አቅረዕ እንዲህ አላቸው ‹እኔ አስር ወንድ ልጆች አሉኝ። ሆኖም ግን አንዳቸውንም ስሜ አላውቅም።› የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) ወደሱ ተመለከቱና ‹የማያዝን አይታዘንለትም።› አሉ።

ሌላ እናክል.. ኢማም ቡኻሪይ አነስ ኢብኑ ማሊክን በመጥቀስ ይህን ጣፋጭ ዘገባ አስተላልፈውልና

‹እናታችን እመት ዓኢሻ (ረ.ዐ) ዘንድ አንዲት ሴት መጣች። ዓኢሻም ሦስት የተምር ፍሬዎችን ሠጠቻቸት። እናቲቱም ለያንዳንዱ ልጅ አንዳንድ ተምር ሠጠችና አንዱን ደግሞ ለራሷ አስቀረች። ህፃናቱ ሁለቱን ተምሮች ወዲያው በልተው በመጨረስ ወደእናታቸው መመልከት ያዙ። እናትም አስቀርታ የነበረውን ተምር በማውጣት ለሁለት በመክፈል ግማሽ ግማሽ ሠጠቻቸው። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በመጡ ጊዜ ዓኢሻ ያየችውን ሁሉ ነገረቻቸው። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ‹ይሄ ምኑ ያስገርማል? አላህ ለልጆቿ በማዛኗ እኮ እሱም አዘነላት!!› አሏት።

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለልጆች ያላቸው እዝነት ልዩ ነበር። በመንገድ ላይ ሲያገኟቸውም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ሲያዩዋቸው ሠላምታ ያቀርቡላቸዋል፤ ያጫውቷቸዋል፤ ይመክሯቸዋል፤ በቁምነገርም ያወሯቸዋል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በሞት አፋፍ ላይ ያለ ልጅ ያዩ እንደሆን ለልጆች ካላቸው እዝነትና ርህራሄ የተነሳ ዐይናቸው በእንባ ይርስ ነበር። ይህም ሁኔታቸው የእዝነትና ርህራሄን ክብደት ለህዝባቸው ከሚያስተምሩበት መንገድ አንዱ ነው።

ኢማም ቡኻሪይ እና ሙስሊም (ረ.ዐ) ኡሣማ ኢብኑ ዘይድን በመጥቀስ የሚከተለውን ዘግበዋል

“በአንድ ወቅት አንዲት የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሴት ልጅ ‹ልጄ ሞት አፋፍ ላይ ነውና ይምጡልን።› በማለት ወደርሣቸው ላከች። እርሣቸውም ‹የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሠላምታ ያቀርቡልሻል የወሰደውም ሆነ የሰጠው አላህ ነው። ሁሉም ነገር በርሱ ዘንድ የተወሠነለት ጊዜ አለው። ትታገስ ምንዳዋንም በአላህ ዘንድ ትተሣሰብ።› ይሉሻል በሏት።› በማለት ላኩባት። እሷም ‹በአላህ ይሁንብዎ የግድ መምጣት አለብዎት።› በማለት በድጋሜ ላከችባቸው። ነቢዩም  (ሰ.ዐ.ወ) ከሰዕድ ኢብኑ ዑባዳህ፣ ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል፣ ኡበይ ኢብኑ ከዕብ፣ ዘይድ ኢብኑ ሳቢት እና የተወሰኑ ሰዎች ጋር በመሆን ወደ ቤቷ ሄዱ። ልጁም ለነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)ተሠጠ። ግቢ ነፍስ ውጭ ነፍስ ላይ ባለበት ሁኔታ ላይ ነበር። ወደ ደረታቸው አስጠጉት። ወዲያውኑ ከዓይኖቻቸው እንባ ፈሠሠ። ሰዕድም ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ይህ ምንድነው?› አላቸው። እርሣቸውም  (ሰ.ዐ.ወ) ‹ይህ አላህ (ሱ.ወ) በባሮቹ ልብ ውስጥ ያስቀመጣት እዝነት ናት።› አሉ። በሌላ ዘገባ ደግሞ ‹ ይህ አላህ  (ሱ.ወ) ከባሮቹ በሻው ውስጥ የሚያኖራት እዝነቱ ናት። አዛኞችን አላህ ያዝንላቸዋል።› ብለዋል።”

እዝነት በእናትና አባት ቀልብ ውስጥ ቦታ የያዘች እንደሆነ ወላጆች ለልጆቻቸው ማድረግ የሚገባቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። የሚጠበቅባቸውንም ሁሉ ይፈፅማሉ። አላህ ግዴታ ያደረገባቸውን የልጅ እንክብካቤ ለመወጣት ዝግጁ ሆኑ ማለት ነው።

3.     ሴት ልጅን መጥላት አስቀያሚ የሆነ የጃሂሊያ /መሃይማን/ ባህሪ ነው

ኢስላም ጥሪ ከሚያደርገው አጠቃላይ የእኩልነት መርህ እንዲሁም ሁለንተናዊ ከሆነው ፍትሀዊነቱ አንፃር እዝነት በማሳየትም ሆነ በመራራት ደረጃ ሴትን ከወንድ የለየበት ሁኔታ አናገኝም። በዚህ ረገድ ቁልፉ መርህ የአላህ (ሱ.ወ) ቃል ነው።

اعْدِلُوا هُوَ أَقْرَبُ لِلتَّقْوَىٰ
 

‹‹አስተካክሉ (ፍትሀዊ ሁኑ) ። እርሱ ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው።› (አል-ማኢዳህ ቁ-8)

ከኑዕማን ኢብኑ በሺር በተላለፈው ዘገባ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)

‹‹በልጆቻችሁ መካከል ፍትሀዊ ሁኑ›፣ በልጆቻችሁ መካከል ፍትሀዊ ሁኑ፣ በልጆቻችሁ መካከል ፍትሀዊ ሁኑ›› ብለዋል።

ከቁርዓናዊም ሆነ ነቢያዊ መመሪያዎች መረዳት የምንችለው ወላጆች ልጆቻቸውን ሲወዱም ሆነ ሲያቀርቧቸው፤ ሥራ ሲሰጧቸውም ሆነ ሲያዟቸው፤ ልብስ ሲገዙላቸውም ሆነ ስጦታ ሲሠጧቸው ያለ ልዩነት በእኩል ዐይን ማየት ያለባቸው መሆኑን ነው። ይህም በልጆች አስተዳደግ ላይ መሠረታዊው ነገር ነው።

ከዚህ ወጣ ባለ ሁኔታ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ወንዱን ከፍ ሴቷን ዝቅ አድርጎ የማየት አመለካከት ካለ ይህ ነገር የተገኘው አለያም የተወረሰው ከእስልምና አስተምርሆት ሣይሆን ከቀደምት የማሃይማን ልማዶች፣ ባህሎችና ድርጊቶች መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። አላህ (ሱ.ወ) ቅድመ ኢስላም ስለነበረው የተዛባ ስርዐት እንዲህ በማለት ገልፆታል፡-

وَإِذَا بُشِّرَ أَحَدُهُمْ بِالْأُنْثَىٰ ظَلَّ وَجْهُهُ مُسْوَدًّا وَهُوَ كَظِيمٌۗيَتَوَارَىٰ مِنَ الْقَوْمِ مِنْ سُوءِ مَا بُشِّرَ بِهِ ۚأَيُمْسِكُهُ عَلَىٰ هُونٍ أَمْ يَدُسُّهُ فِي التُّرَابِ ۗ أَلَا سَاءَ مَا يَحْكُمُونَ

‹‹አንዳቸውም በሴት ልጅ በተበሰረ ጊዜ እርሱ የተቆጨ ኾኖ ፊቱ ጠቁሮ ይውላል። በእርሱ ከተበሰረበት ነገር መጥፎነት በውርደት ላይ ኾኖ ይያዘውን? ወይስ በዐፈር ውስጥ ይደብቀውን? (በማለት እያምታታ) ከሰዎች ይደበቃል። ንቁ! የሚፈርዱት (ፍርድ) ምንኛ ከፋ! ››(አን-ነህል ቁ-58- 59)

ልጅን ወንድም ይሁን ሴት ማበላለጥ የደካማ ኢማን ውጤት ነው። ምክኒያቱም እነሱም ሆኑ ማንም ሊቀይረው የማይችለውን የአላህን (ሱ.ወ) ችሮታ በደስታ ባለመቀበላቸው ነው። አላህ (ሱ.ወ) ሁሉም ነገር በእጁ ነው። ክፍፍሉም ፍትሃዊ ነው። የሰው ልጅ አላህ (ሱ.ወ) የወደደለትን ሊወድ ይገባዋል።

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

لِلَّهِ مُلْكُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۚ يَخْلُقُ مَا يَشَاءُ ۚ يَهَبُ لِمَنْ يَشَاءُ إِنَاثًا وَيَهَبُ لِمَنْ يَشَاءُ الذُّكُورَ﴿٤٦﴾أَوْ يُزَوِّجُهُمْ ذُكْرَانًا وَإِنَاثًا ۖ وَيَجْعَلُ مَنْ يَشَاءُ عَقِيمًا ۚ إِنَّهُ عَلِيمٌ قَدِيرٌ

‹የሰማያትና ምድር ንግስና የአላህ ነው። የሻውን ይፈጥራል። ለሚሻው ሴቶች ልጆችን ይሠጣል። ለሚሻውም ወንዶች ልጆችን ይሠጣል። ወይንም ወንዶችና ሴቶች አድርጎ ያጠናዳቸዋል። የሻውንም መካን ያደርጋል። እሱ አዋቂ ቻይ ነውና።.› (አሽ-ሹራ 49-50)

ታላቁ የኢስላም መልእክተኛ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን በአንዳንድ ደካማ ነፍሶች ውስጥ የተተከለውን የጃሂሊያ (ኋላቀር አመለካከቶችን) አስተሣሰብ ከሥር መሠረቱ መንግለው ለመጣል ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጡ። ወላጆችም ሆኑ ሌሎች አሣዳጊዎች የአላህን ጀነት ያገኙ ዘንድ ሴቶችን በአግባቡ እንዲንከባከቡ፣ በልዩ ትኩረትም እንዲጎደኟቸው፣ የሚያስፈልጋቸውን በአግባቡ አሟልተው እንዲያሳድጉ አዘዋል።

ኢማም ሙስሊም አነስ ኢብኑ ማሊክን (ረ.ዐ) በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)

“ሁለት ሴት ልጆችን ለአቅመ ሄዋን እስኪደርሱ ድረስ የተንከባከበ ሰው በእለተ ቂያማ (ትንሳኤ) እኔና እሱ በዚህ መልኩ የተጠጋጋን ሆነን እንመጣለን። (ጣቶቻቸውን በማጠጋጋት)” ብለዋል።

ኢማም አህመድ ከዑቅባ ኢብኑ ዓሚር አልጁሀኒይ እንደዘገቡት ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው ብሏል

“አንድ ሰው ሦስት ሴት ልጆች ኖረውት በነሱ ላይ በመታገስ ከሀብቱም ወጭ በማድረግ ያጠጣቸውና ያለበሣቸው እንደሆነ የትንሣኤ ቀን ከእሣት ግርዶ ይሆኑለታል።”

አል-ሁመይዲ አቢ-ሰኢድን በመጥቀስ ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳስተላለፈው

‹ሦስት ሴት ልጆች አሊያም እህቶች አሊያም ሁለት ሴት ልጆች አሊያም እህቶች ኖረውት እነሱን በአግባቡ የተንከባከበና የታገሠ በነሱም ጉዳይ አላህን የፈራ ጀነት ገባ።›

ከነኚህ ሀዲሦች የምንወስደው ትምህርት ሴት ልጅን ማሣደግ ትልቅ ደረጃ ያለው መሆኑን ነው። በወንዶች ልጆችና በነርሱ መካከል አድልዎ ሣያደርጉ ለነርሱ ጊዜ ሰጥቶ እምነትን አስተምሮ በመልካም ሥነምግባር ላይ ማሣደግ የጀነትን ፀጋና የአላህን ውዴታ ወደማግኘት ያደርሣል።

4.     በልጅ ሞት ላይ መታገስ ያለው ደረጃ

አንድ ሙስሊም በኢማኑ ትልቅ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ በአላህ ላይ የመተማመን ስሜቱ ከፍ ሲል፣ በአላህ (ሱ.ው) ፍርዶችና ውሣኔዎችም በትክክል ሲያምን፣ አሣማሚ ክስተቶችና ሁኔታዎች ሁሉ ለሱ ምንም ማለት አይደሉም። መከራዎችና ችግሮችን ከምንም አይቆጥራቸውም። የሚያስፈራም ሆነ የሚያስደነግጠው ነገር አይኖርም። ነፍሱ ሁልጊዜም የተረጋጋች ናት። በመከራ ላይ ብርቱ ፅናት አላት።

ከዚሁ መነሻነት ነው እንግዲህ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ልጅ የሞተበት ሰው መርዶ ቢነገረው እንዲታገስ እስትርጃዕ እንዲያረግ (ኢና ሊላህ ወኢና ኢለይህ ራጅዑን/ እኛም ለአላህ ነን ወደ አላህም ተመላሾች ነን) እንዲል ያዘዙት። ይህንንም ያደረገ እንደሆነ የመካሱ ነገር እርግጥ ነው። በጀነት ውስጥ በይተልሀምድ /የምስጋና ቤት/ የሚባል ተዘጋጅቶለታል።

ቱርሙዚ እና ኢብኑ ሂባን አቢ ሙሳ አል-አሽዐሪን በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል

“የአንድ የአላህ ባሪያ ልጅ ሲሞትበት ክቡር የሆነውና ልቅናው ከፍ ያለ ጌታ- አላህ (ሱ.ወ) ለመላእክቱ ‹ የባሪያዬን ልጅ ነፍስ ወሠዳችሁን?› ይላቸዋል። እነርሱም ‹አዎን› ይላሉ። ‹የልቡን ፍሬ/የአብራኩን ክፍይ/ ወሠዳችሁበት?› ይላቸዋል። እነርሱም ‹አዎን› ይላሉ። ‹ ታዲያ ባሪያዬስ ምን አለ?› በማለት ይጠይቃቸዋል። እነርሱም አመሠገነህ ኢስቲርጃዕ አደረገ /ኢና ሊላህ ወኢና ኢለይህ ራጅዑን/ አለ።› ይሉታል ። አላህም ‹በሉ በጀነት ውስጥ ለባሪያዬ ቤት ሥሩለት። ስሙንም በይተልሀምድ /የምስጋና ቤት/ በሉት።› ይላቸዋል።

ወዳጆቼ ጀነት በቀላሉ የማትገኝ ውድ ነገር ናት። ሆኖም ግን የልጅ ፍቅር ከባድ ነውና ልጅ ሞቶበት የታገሠና አላህን ያመሠገነ ሰው አላህ ምንዳውን ሊያበዘለት በጀነት ቃል ገብቶለታል። ይህም ልጅም ሆነ ገንዘብ በማይፈይድበት የቀውጢ ቀን ትልቅ ፋይዳን የሚያስገኝ የትእግስት ውጤት ነው።

ከፍሬዎቹ…የጀነት መዳረሻና የእሳት መጋረጃ ነው..

ቡኻሪ እና ሙስሊም አቢ ሰዒድ አልኹድሪን በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ

“አንዲት ሴት ሦስት ወንዶች ልጆች አይሞቱባትም ልጆቿ ከእሣት ግርዶ ቢሆኗት እንጂ።› አንዲት ሴት ‹ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ሁለትስ? › በማለት ጠየቀቻቸው። እርሣቸውም ‹ ሁለትም› በማለት መለሱላት።”

ኢማም አህመድ እና ኢብኑ ሂባን ጃቢርን በመጥቀስ እንዳስተላለፉት ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው አሉ

“ሦስት ወንድ ልጆች ሞተውበት ምንዳውን በአላህ (ሱ.ወ) ዘንድ የተሣሰበ ሰው ጀነት ገባ።› ‹ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ሁለትስ?› አልናቸው። እርሣቸውም ‹ ሁለትም› አሉን። አንዱ ዘጋቢ ለጃቢር (ረ.ዐ) ‹አንድስ?› ብትሏቸው ‹አንድም› የሚሉ ይመስለኛል።› አለው። ጃቢርም ‹አዎን እኔም እንደዚያ ይመስለኛል።” አለው።

ሌላው የትእግስት ትሩፋት ደግሞ ገና በልጆነቱ የሚሞት ህፃን የትንሣኤ ቀን ለእናት አባቱ አማላጅ መሆኑ ነው። ጦበራኒ ጥሩ ደረጃ ባለው የሀዲስ ዘገባ እንዳስተላለፉት ሀቢባ ዓዒሻ (ረ.ዐ) ዘንድ ሳለች ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) መጡና ወደ ውስጥ ገቡ። እንዲህም አሉ

“ሁለት ሙስሊሞች ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሦስት ልጆች አይሞቱባቸውም። የትንሣኤ ቀን በጀነት በር ላይ ተቁሞ ልጆቹ ‹ጀነት ግቡ› የተባሉ ቢሆን እንጂ። እነርሱም ‹እናት አባቶቻችን እስካልገቡ ድረስ እኛም አንገባም።› ይላሉ። ከዚያም ‹እናንተም ወላጆቻችሁም ጀነት ግቡ።› ይባላሉ።”

ኢማም ሙስሊም አቢ-ሀሳንን በመጥቀስ እንደዘገቡት እንዲህ ብለዋል ‹ሁለት ልጆቼ ሞቱብኝና ለአቢ ሁረይራ (ረ.ዐ) ‹ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ሙታኖቻችን ነፍሣችንን ደስ የሚያሠኝ ሀዲስ አሰማን እስቲ።› አልኩት። እርሱም ‹አዎን ትናንሽ ልጆቻቸው አይለዩቸውም። አንደኛ ከአባቱ አሊያም ከወላጆቹ ጎን ይሆናል። የልብሣቸውን ጫፍ በመያዝም (እኔ አሁን ልብስህን እንደያዝኩት) እሱን ጀነት እስኪያስገባ ድረስ አይለየውም።›

እስቲ የሰሃቦች ሴቶችን ጀግንነትና ጥንካሬ ከሚያሣዩ ሀዲሦች ደግሞ አስደማሚ የሆነውን ይህን ላካፍላችሁ። ታሪኩ የኡሙ ሱለይም ነው።

ከአነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው አቢ ጦለሃ (ረ.ዐ) የታመመ ልጅ ነበረው። ልጁ በዚሁ ሁኔታ ላይ ሳለ አቢ ጦለሃ መንገድ ወጣ። ሣይመለስም ልጁ ሞተ። አቡ ጦለሃ ከጉዞው ሲመለስ ለሚስቱ ‹ልጄ እንዴት ነው?› አላት። ኡሙ ሱለይምም ‹በፊት ከነበረው በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ነው ያለው።› አለችው። እራት አቀረበችለትና በላ። ከዚያም ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ ተዋበችና ተዘገጃጀችለት። አብረውም ተኙ። እራቱን በልቶ መጥገቡንና ከሷም ተገናኝቶ መርካቱን ባየች ጊዜ እንዲህ በማለት ጠየቀችው ‹ የጦለሃ አባት ሆይ! የሆኑ ሰዎች ለሆኑ ሰዎች የሆነ ዕቃ ቢያውሱና ያንን ዕቃ መልሰው ቢወስዱ ተዋሾቹ መከልከል ይችላሉን?› አለችው። እሱም ‹አይ አይችሉም።› አላት። እሷም እንግዲያውስ የልጅህን ምንዳ በአላህ ዘንድ ተሣሰብ።› አለችው። በዚህን ጊዜ አቡ ጦላሃ እጅግ ተቆጣ ‹ካንች ጋር እስክጨማለቅ ድረስ ጠብቀሽ ነው አሁን የልጄን ሞት የምትነግሪኝ?› አላት። አቡ ጦለሃ እየገሰገሰ ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ በመሄድ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው። የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) ኡሙ ሱለይም ያደረገችው ነገር መልካም መሆኑን አረጋገጡ። ከዚያም

“የትናንቱን ለሊት አላህ ይባርክላችሁ።›አሉት። በሌላ ዘገባ ደግሞ ‹ አላህ ሆይ! በለሊቱ ባርክላቸው።› ብለው ዱዓእ አደረጉላቸው።

‹ጌታዬ ሆይ! ለሊቱን ባርክላቸው!› ያሉት ነቢይ ዱዓኣቸው ፍሬ አፈራ። ኡሙ ሱለይም ወንድ ልጅ ወለደች። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ለልጁ ዐብዱላህ በማለት ሥም አወጡለት። አንድ ከአንሷር/መዲና የሆነ ሰው እንዲህ ይላል።“ዐብደላህ ዘጠኝ ልጆች ተወልደውለት አየሁ። ሁሉም ቁርዓን ሀፍዘዋል።” አጃዒብ ነው ወላሂ!! በርግጥ የትእግስት ውጤት ምንኛ ያማረ ነው!! አላህን የወደደውን ነገር ወዶ መቀበልስ ምንኛ ፍሬያማ ነው!

ኢማን በአንድ ሰው ልብ ውስጥ የሠረፀ እንደሆነ በርግጥም ድንቅ ነገር ይሠራል። ደካማው ብርቱ ይሆናል። ፈሪው ወደ ጀግና ይለወጣል። ንፉግ የነበረው ወደ ለጋስነት ይሸጋገራል። በትንሽ ትልቁ ሙሲባ ይደናገጥ የነበረውም ታጋሽ እና ቻይ ይሆናል።

ታዲያ ምን እንበል.. ወላጆች ከልጆቻቸው አንፃርም ሆነ ከሌላ በኩል የሚያጋጥማቸውን የዚህችን ዓለም ፈተና ለመቋቋም ብቃቱ ይኖራቸው ዘንድ ከምንም በላይ ኢማን አያስፈልጋቸውምን??… እባካችሁ ለኢማን እንሥራ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here